Sunday, July 12, 2015

ኦባማ ምን አጠፋ? ሀማ ቱማ


ቦ ጊዜ ለኩሉ እንደሚባለው ሁሉ ለሁሉም ሁለት ፊት ገጽታ አለ ሊባል ይቻላል። ወያኔ በአራቱም አቅጣጫ ቢታይ አስቀያሚ መሆኑ አይቀሬ ቢሆንም የክልል አንድ ልጆች ቆንጆ ነው ማለታቸው መጠበቅ ያለበት ነው። የአድዋ ልጆች የዓይን ችግር አለባቸው ለማለት ሳይሆን በጥቅም ታውረዋል ለማለት ነው። ሰይጣኑ መለስ ሲሞት ጮቤ የረገጠው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊው ሲሆን ዕንባ ያነባው ደግሞ ወያኔና ሆዳሙ ብቻ ነው። ጅላ ጅሎችም--ሁሉም ሀገር ዘለዓለማዊ ሞኞችን ይይዛል። ሁለት ገጽታ ለሁሉም።
ይህ መንደርደሪያ የመጣው ወደ ኦባማና ኢትዮጵያን ለመጎብኘት መነሳቱን በተመለከተ የተነሳውን ውዝግብና ተቃውሞ የሰይጣን ጠበቃ ሆኜ ለመከራከር በመፈለጌ ነው። የዛሬ ስንት ዓመት ባራክ ኦባማ አሜሪካዊ ሳይሆን ኬንያዊ፤ አፍሪካዊ፤ ጥቁርም የመሰላቸው ጥቂቶች አልነበሩም። ግለሰቡ አሜሪካዊና ለሀገሩ ጥቅም ብቻ የሚቆም መሆኑንም በተመለከተ ብዥታ ሰፍኖ ነበር ማለት ይቻላል። ሀገራቸውን የረሱ እንበልና ስንት ኢትዮጵያውያን የነበሩ ሁሉ ለኦባማ ገንዘብ ሰበሰቡ፤ ሲመረጥም ፈነደቁ፤ አንዳንዶቹማ ኦባማ ስለዴሞክራሲ የለፈፈውን አምነው፤ ፖለቲከኛ መሆኑን ረስተው፤ ለአሜሪካ ጥቅም የቆመ መሆኑ ዘንግተው ወያኔ አለቀላት ሲሉም ተደምጠዋል። ማለቅ የጀመረው የራሳቸው የተሳሳተ ድምዳሜ ሆኖ ሳለ። የአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር ተጻሮና ተፋጦ ከቆየ ዘመን ያለፈ ቢሆንም ታሪክን ማወቅና መረዳት ያቃታቸው ክፍሎች ይህን ሀገር የኢትዮጵያ ወዳጅ አድርገው ለመፈረጅ ሁሌም ደፋ ቀና ሲሉ ማየት ምጸታችን ከሆነም እንዲሁ ዘመን አልፏል። ኦባማ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሳይሆን ባለው ሀላፊነት የአሜሪካ ቡችላና መጋዣ ለሆነ ወያኔ ጥብቅና የሚቆም መሆኑን መገመት ባላዳገተ ነበር። ለወያኔ ስልጣን መያዝና ለተከተለው የኤርትራ መገንጠል ዋናው ደጀን/ረዳት አሜሪካ ካልነበረ ማን ሌላ ሊወቀስ ነው! አሜሪካንን በሚገባው ቋንቋ ማነጋጋር ሲገባ (ይህን ትምህርት ደግሞ ሞቃዲሾም ቤይሩትም ብሎ መማር ይቻል ነበር) አትርሱን፤ እዘኑልን፤ ፕሊስ ፕሊስ ማለቱና መለመኑ ስለበዛ መናቅ መከተሉ የሚጠበቅ ነበር:: አሜሪካም ወያኔን ስትደግፍ ህዝብን ግን ንቃለች፤ አሁንም የተለወጠ የለም። ኦባማ ደግሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እንደመሆኑ የአሜሪካን ጥቅም ማስቀደሙ የሚጠብቅ ነውና 90 ሚሊዮን ድሀ ደንታ ሊኖረው አይችልም። የለውምም።
ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት መሄዱ ለምን ብዙዎችን እንዳስቆጣ በበኩሌ ግራ አጋብቶኛል። ተቃውማችሁ አትሰለፉ ለማለት ሳይሆን እንዲያው ለነገሩ እንዲሉ ምን አለበት ለማለት ነው። አንድ
2
ባሕታዊ “ምን አለበት?” ሲባል “በእበትማ ትል አለበት” ሲሉ አስታውሳለሁ፣ ግን በዚህ ጽሁፍ ልረሳው ወስኛለሁ። ኦባማ ኢትዮጵያ ቢሄድ ምን አጠፋ ለማለት የተነሳሁት ክሱ አባት ልጁን፤ የውሾ ባለቤት ቡችላውን አይይ አይጠይቅ ዓይነት ስለመሰለኝ ነው። የኦባማና አሜሪካ ወዳጅ ወያኔ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም። ለአሜሪካ የቆመ ወያኔ እንጂ የሀሬን ሉአላዊነት ላስጠብቅ ባዩ ሕዝብ አይደለም። ለአሜሪካ ጦር ሰፈር የሰጠው (በጋሞ ጎፋ ወዘተ ) ወያኔ እንጂ ህዝብ አይደለም። ወያኔ በስልጣን መቀጠሉን አሜሪካ ትፈልገዋለች። ለዚህም ነው ኦባማ ህግን ጥሶ ለአራተኛ ጊዜ ሊመረጥ የሚንገዳገደውን የጅቡቲውን ኦማር ገሌ የምትደግፈው፡፡ ለዚህም ነው ትዕዛዟን ተቀብሎ ወደ ሶማሊያ ጦር የላከው የቡሩንዲውን ጨቋኝና በሕዝብ የተጠላ መሪ መሪ ወዳጅ የምትለው። አንዳንድ ዜጎች አሜሪካ በኢራንና አፍጋኒስታን ለዴሞክራሲና ለሕዝቦች ጥቅም ስትል ውጊያ የገባች ይመስላቸዋል። ጋዳፊ የተገደለው ለሊቢያ ህብ ደግ ታስቦም የሚምስላቸው የዋሆች አሁንም አሉ። መደናገራቸውን ግን በኦባማ ላይ ማሳበብ አይችሉም። ፖለቲከኛ ወንዝ በሌለበት ድልድይ ሊሰራና ድልድይ በማያስፈልግበት ወንዝ ሊያስገባ ቃል ሊገባ መነሳቱ መጠበቅ ያለበት ሆኖ ሳለ በግልቡና በሌጣው ወይም እንደወረደ የሚለፈፈውን የሚያምኑ (ብጿአን ማለቱ ይከብዳል) ሞልተዋል። ኦባማ በሙስና ያልተጨማለቁ መሪዎችን እንፈልጋለን ሲል ከልቡ ይመስላቸዋል። ዴሞክራሲን ካላከበራችሁ አንረዳችሁም ሲልም አምነውት እስየው ጉድ ፈላ ይላሉ። አረቦች ካለም ፋዲ--የማይረባ ንግግር--የሚሉት መሆኑን አይገነዘቡም። አሜሪካም ሆነ ምዕራቡ በዝባዥ ዓለም ሀገር ወዳድ መሪን አይፈልጉም:: ሉአላዊነትን ሲያስከብር ዝርፊያችውን ያስቆማቸዋልና። የሕዝብ መንግስትንም ይጠላሉ በዚሁ የተነሳ። ንክሩማህ፤ ሉሙምባ፤ ሞሳዴግህ ከኢራን፤ ሳንካራ ፤ መንግስቱና ገርማሜ ንዋይ፤ ዳጃዝማች ታከለ ወልድ ሀዋርያት፤ ኢሕአፓ ወዘተ ተፈላጊ ያልሆኑት፤ የተጠቁት፤የተገለበጡትና አሁንም የሚጠቁት በዚሁ የተነሳ ነው።
ይህን በግንዛቤ ከያዝንና ስለ አሜሪካና ኦባማ የተዛባ ግምትን ካስወገድን እንዳውም ኦባማ እስካሁን እንዴት ወያኔን ከወረረው መዲና ድረስ ሄዶ እንዳላመሰገነውና እንዳላሞገሰው አነጋጋሪ ይሆናል። ወያኔ ለጌታው በፍጹም ታማነትና ተገዥነት ያደረ ውሾ ሆኖ እንጂ ቅሬታውን እስካሁን ባሰማ ነበርም ማለት ይቻላል። ማንም በስልጣን ያለ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ወያኔን የጎበኘው ባይሆንም ኦባማ በብዙ መስክ የመጀመሪያው መሆንን ይመርጣልና ብቅ ማለቱ ወያኔን የሚያስፎክር ባይሆንም ማስደሰቱ አያስገርምም። ኦባማ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያ ግማሽ ጥቁር (ግማሽ ነጭነቱም ሳይረሳ) ፕሬዚዳንት መሆኑ በታሪክ ያለው የሆነ እንዴ አንደምታ እንዳለ ሆኖ (የአሜሪካውን ለሚያውቁት ስንተው) ለአፍሪቃ ግን ቡሽ ሶስተኛው እንጂ የተለየ ፍጡር አልሆነም፡፡ ባይብስ እንዳውም የሚሉ ብዙ ናቸው! የኦባማ የአፍሪቃ ወዳጆች አምባገነኖች ናቸው። የፈረደበትን ሙጋቤንና የጎረቤቱን አል በሺር ዓይናችሁን ላፈር ሲል የአዲስ አበባዎቹን፤ የካምፓላን፤ የጅቡቲን፤ የቻድና ኤክዋቶሪያል ጊኒና ሌሎችንም አምባገነኖች ግን ወዳጅ ብሎ
3
አቅፏል፤ አሞግሷል፤ ደግፏል። ወደ ዋሺንግተን ድረስ ጋብዞም አጆሃ፤ ካሪ ኦን ሲላቸው ቆይቷል። እኛ እንደ ህዝብ ማየት ያቃተንን የወያኔና የአረመኔውን መለስ ዴሞክራሲያዊነት አይቶ ተገለጸልኝ ተዓምር ሲልም ተደምጧል። አዲስ አበባ ሲሄድ የሚለው የተለይ ነገር አይኖርም። ኤኮኖሚው ማደጉን፤ የድህነት ብዛቱ መቀነሱን፤ ወያኔ የአሜሪካ ወዳጅ መሆኑን፤ ወዘተ ልብ ወለዶች አንስቶ ይሞጋገሳል። ዋሾነት የወያኔ የብቻ ንብረት አይደለምና የአሜሪካ ባልስልጣኖች ከወያኔ ባልተናነሰ ስለ ወያኔ ሲዋሹ ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል። የማይነሱ ነገሮችም ምስጢር አይደሉም።
ወያኔ ከ፵/40 ሺ ያላነሰ የፖለቲካ እስረኞⶭ ማገቱና በስየል መጥበሱ አይነሳም። ወያኔ ዓይን አውጣ የመርጫ ማጭበርበርን አካሂዶ መቶ በመቶ ምርጫ አሸነፍኩ ማለቱ በዝምታ ይታለፋል። ሚሊዮኖች በረሃብ መጠቃታቸው፤ መቶ ሺዎች መጠለያ ማጣታቸው፤ ወያኔ በሙስና መጨማለቁ፤ የሀገሪቷ ለም መሬት ለባዕዳን ተሸጦ ብዙ መቶ ሺዎች መፈናቀላቸው፤ ተቃዋሚዎች መታገታቸውና መገደላቸው፤ የጋዜጠኞች ሰቆቃ ወዘተ የሚነሱ ጉዳዮች አይደሉም። የአሜሪካ ባለስልጣኖች ከአምባገነኖች ጋር መተቃቀፋቸውን ለመደበቅ ወይም ውግዘትን ለማለዘብ በይፋ ሳይሆን በር ዘግተን ሁሉም ችግር እናነሳለን የሚሉት የሞኝ የተበላ፤ ማንም የማይቀበለው አሳዛኝ ማደናገሪያ ብጤ አላቸው። በኦባማ ጉብኝት ጊዜ ይህ መባሉ መጠበቅ ያለበት ነው። ኦባማ እስቲ ቃሊትንና ሊሎችን እስር በኢቶች ልጎብኝ እንዲል ባይጠበቅም ጉዞው ለሙገሳ እንጂ ለወቀሳ አለመሆኑን የሚስት ሊኖር አይችልም፤ ሊኖርም አይገባም። መለስ ሞተ ብለው ያላቀሱ ደግሞ በየመንገዱ ተኮልኩለው ኦባማዬ ብለው ቢጮሁ የሚያስገርም ሊሆን አይገባም። ከዚህ ባሻገር ኦባማ ከወያኔ በቀጥታ ሊቀስማቸው የሚችላቸው ትምህርቶች አሉ። ይሉኝታንና ማፈርን መቼና እንዴት እንደገደሉት ማወቅ መፈለጉ አይቀርም። የውሸት ችሎታቸውንም ከቅርብ ሆኖ ቢረዳ የሚጠላም አይሆንም። ድርቅናቸውን ወይም እስራኤሎች ቹትዝፓህ የሚሉትን እንዴት እንደተራቀቁበት ሊያስረዱትም ይችላሉ። ምርጫ ሰርቀው ዴሞክራሲያው ምርጫ ተካሄደ፤ ተቃዋሚ ገድለው ከጥይት ፊት ድርቅ ብሎ ቆሞ ራሱን ገደለ፤ የሶማሊያን ድንበር ተሻገርን እንጂ ወረራ አላካሄድንም፤ ወዘተ ብለው በድፍረት ለዓለም የሚለፍፉትን በተመለከተ ድፍረታቸውን ቢጋራም ደስታውን የሚችለው አይሆንም። ኦባማ ስልጣን ከያዘ ወዲህ መገርጣቱና መጎሳቀሉ ሲታይ የአዲስ አበባዎቹና የአፍሪካ አምባገነኖች ግን ለምንና እንዴት እንደሚወፍሩ እንደሚደልቡ መወያየት ማወቅም ይፈልጋል ተብሏል። ኦባማ ኦባማ ነውና ለዚህ ሁሉ ለወያኔ የማጭበርበር ዘመቻ ተጠያቂ እኔና አሜሪካንም ነን ሊል መቸም የሚጠበቅ አይሆንም። ማን ኦሳማ ቢን ላደንንና አክራሪ ሰው አራጆችን ረዳ! ማን ሳውዲና ሌሎችንም አቅፎ ደግፎ ባጀ! ምላሽ የሚጠበቅ አይሆንም።
4
ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ መጓዙ ስለ ዴሞክራሲ የሚለፍፈውና ከአምባገነኖች ጋር አንተቃቀፍም የሚለውን ሁሉ ከንቱነት የሚያጋልጥ በመሆኑ ቢቻልማ ኖሮ ወጪውን በኢትዮጵያ ላይ ብለን በጋበዝነው ነበር። “አሜሪካ እናቴ/ኦባማ አባቴ/ እኔ ምን ሊገደኝ ቢቆረስ መሬቴ/ ቢደፈርም መብቴ/ቢዋረድ ታሪኬ” ለሚሉት ሁሉ ምናልባትም የንቁ ደወል ይሆንላቸው ይሆናል። ተስፋ አይከለከልም አይደል! ወያኔ በኦባማ መጎብኘቱ የሚያስደስተው የቆሸሸና የከረፋ ስሙንና መልኩን ስለሚያድስለት ብቻ ሳይሆን ምናልባትም የኦባማን ትልቂቷን ልጅ የኬንያ ሀብታም በላምና በሬ ገዝሚ ሳይወስዳት የገዢዎቹ ልጆች ሊያጯት ይችሉ እንደሆነም ለማየት ነው የሚልም ጥርጣሬ አለ። ለዚህም ነው ኦባማ ቤተሰቡን ይዞ መሄድ ያለበት። ሂላሪ ክሊንተን ከተጠላው ሰምብል እስር ቤት አጠገብ ከነሴት ልጇ ከኢሳያስና የያኔ ሚስቱ ጋር ደርብ ብላ እንደጨፈረችው ሁሉ የኦባማ ሚስትም ከአዜብ ወይም ከሌሎቹ የወያኔ ሚስቶች ጋር አስረሽ ምቺው ብላ እንደ ባሏ በኢትዮጵያ ቁስል ላይ ጨው ስትነስነስ ማየትም እንችል ይሆናል። ይህን ከማየት እምቢ የሚል ይኖራል ብሎ መገመት ሊከብድ ይችላል። አሚሪካ ለስንቱ ቪዛ እየሰጠች ኢትዮጵያ እንዴትስ ኦባማን ባለህበት ቆይ፤ አትምጣብን ልትለው ትችላለች የሚሉም አሉ። ጨዋ ሕዝብ አይደለንም እንዴ! የስልጡንና ተንበርክኮ ትግል አማኝ መሆናችን ቀረ! አሜሪካንን ተቃውመን ስንሰለፍ እንኳን ባንዲራቸውን ልናቃጥል ሳይሆን በክብር እያውለበለብን መሆኑን ማንስ ዘንግቶ ነው ጠበቅ ያለ ተቃዋሞ የሚታሰበው ማለትም የግድ ሊሆን ይችላል።
ሉዓላዊነታችንን ለባዕዳን ካስረከብን ውሎ አድሯልና ኦባማ ኑ ዋሺንግተን ስገዱን ትቶ ወደ ኬንያና ኢትዮጵያ ብቅ ለማለት መወሰኑ ነገሮች ሁሌም ሁለት ገጽታ አላቸው ብለው ዶክተሮቻችን እንደሚገስጹን ጠቀሜታም ሊኖረው ይችላል። ውርደትን ክብር ማለት የወያኔ ብቻ ጉድ አይደለምና እንኳን ደህና መጣህ ብለው እንደ ጆሴፍ ቲቶ ቢቀበሉት መገረም የለብንም። አትሂድ የሚሉትም ይበሉት--ለታሪክ ተቃውሞን ለማስመዝገብ። በበኩሌ ግን ኦባማ በግላጭ ያውም አዲስ አበባ ድረስ ሄዶ ወያኔን ማቀፉ የተበላሸና ሕዝብና ሀገርን የሚጎዳውን የአሜሪካ ፖሊሲ፤ አቅዋምና ፖለቲካ ያጋልጣልና አደራህን ብቻህንም ቢሆን መጓዙን እንዳትተው ብዬ ባያዳምጥም እነሆ መክሪያለሁ።

No comments:

Post a Comment