Wednesday, July 15, 2015

ከዝንጀሮ ቆንጆ ቢመረጥ፥ወያኔ አስቀያሚ ነውከዝንጀሮ ቆንጆ ቢመረጥ፥ወያኔ አስቀያሚ ነው
ቢንያም ግዛው

                     
ሽቅብ ቁልቁል፣ተራራ እና ሸለቆ፣ሽርክት እና ለስላሳ ከፍ ማለት እና የማዘቅዝቅ፣ በሆነው ረዥም የአመታት ጉዞ በሀዘን ግዜ፣ በደስታ ግዜ፣በመዝራት እና በማጨድ ወቅት፣ እንዲሁም በድህነት ወይም በሀብት ዘመን ፣ ኑሮ የሌሊት ሲሆን የመከራ አሊያም የቀን ሲሆን የድሎት … በሁሉም አይነት አቅጣጫ የህይወት ዘመናቸው ሲያልፍ ሀገሬ ኑሪ! የሚለውን ቃል በልባቸው ላይ አትመው እትብታቸው ላረፈበት ምድር ቃል ኪዳናቸውን የጠበቁ ነበሩ። ከሀገራቸው ሰሜን እስከ ደቡብ ድንበሯን ለማስጠበቅ በእኩልነት ለሁሉም ዙሪያ ሲታገሉ፤ ሁሉንም በር ላለማስደፈር ማለዳ በምስራቅ ወጥተው ብርሀናቸውን ለምድሪቱ የፈነጠቁ።

           ለነገው ብርሀን ተሳምሊት በመሆን ማምሻውን በምዕራብ የዳመኑ የጨለሙ። ለምድራቸው፤ ከምድራቸው፤ በምድራቸው ሆነው በአድሎና በጎሰኝነት ሳንካ ሳያይሸበቡ ለሁሉም የኢትዮጵያ ክልል ዘብ የቆሙ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች። ለሚተካቸው ትውልድ ደማቸውን በማፍሰስ በሉዐላዊነት አንድነቷን የጠበቀች ሀገር ያለ ባዕዳን ቅይጥ ባህልና ቋንቋ ሳትበረዝ ከአካልዋም ሳይቆረስ በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱትን የውስጥ እና የውጭ አንጃዎችን የመከቱ። በመስዋዕትነታቸው ህይወትን በሞት የዘሩ። የብዙ ቋንቋ፣ባህል፣ብሔር፣እና ሀይማኖት ምድር ብትሆንም ሁሉም እንዲቻቻሉ በማስተማር እና በመዘከር አንድ ክብርት ሀገር ገንብተው ያስተላለፏት የእኩልነት ቤት ኢትዮጵያ፤ዘመናትን ተሻግራ ከኖረች ወዲያ ዛሬ ላይ ባለቤት የሌላት ሆና ወይባለች። ያ ውበት እና ለዛዋ ተሟጦ ዜጋዋ የሚኖርባት ሳይሆን የሚማረርባት እና ተስፋ የማያይባት ምድር ሆና የአንድ ትውልድ እድሜን ያህል ማስቆጠርዋ አሁን ላይ በየስፍራው የተበተኑ አዛውንት ዜጎችዋ ምስክር ናቸው።

           ጥቂት በጥቂት ሰላሟ እየተናጋ ፈፅሞ ልትጥራ ባልቻለችበት መልኩ በአዳፋ ስርዓት ውስጥ እያለፈች ለዛሬ ገፅታዋ ስትበቃ፤ለደህንነቷም ሆነ ለመሰበሯ ምክንያት በሚሆኑ ልዩ ልዩ መሪዎች ስር አልፋ ነው። አንዳንዶቹም ኢትዮጵያዊነቷ በክብር እንዲኖር ስለ ደም ግባቷ ዘብ የቆሙ ሌሎችም ደግሞ አኩሪ ታሪኳን በመበረዝ ለውጭ ባዕዳን ተልዕኮ ስኬት የተቀጠሩ ሀገርን ከተቻለ በጅምላ ካልሆነም በችርቻሮ እየቆነጠሩ እና እየሰፈሩ የሚቸበችቡ በበግ ለምድ ሽፋን የሚኖሩ ተኩላዎች፤አሁን ላለችበት መልከ ጥፉ ገፅታ ዳርገዋታል። አንበሳ ሲያረጅ የዝንብ መጫወቻ ይሆናል የሚለው አባባል እዚህ ጋር አይሰራም፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አያረጅም አያፈጅም። ዝንቦች መጫወቻ ቢያደርጓትም አንበሳነቷን አስረው ነው።ስለዚህ አሁን ላለንበት የቅሚያና የዝርፊያ እንዲሁም የቅኝ ግዢ ዘመን፤ እንዲህ ቢባል ይሻላል፤ በቆሸሸ ስርዓት የተከማቹት ዝንቦች አንበሳውን አስረው ኢትዮጵያን ተጫወቱበት!

          እርግጥ ነው፤ኢትዮጵያ የምትሮጥበት እግሯ በየዘመናቱ አራት ኪሎ ቤተመንግስትን የሚቀራመቱት ገዢዎቿ ተብትበውት በቀስታ መሔድ ከጀመረች ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል። አፄው የራሳቸውን የማሰር አስተዋፆ አበርክተው በየካቲቱ የህዝብ ትግል ድል ዙፋናቸው ሲገረሰስ የትግሉን ውጤት በማምታታት ደርግ ተብዬው በወታደራዊ ትጥቅ ሰፍሮባት፤ ጎንበስ፣ጠብ፣እርግፍ እያለ ጫማ በመሳም የተሽቆጠቆጠውን ህዝብ ተረክቦ የተጫነበትን ቀንበር ከጫንቃው ላይ ሳይሰብርለት፣እስሩን ሳይፈታለት ለተጨማሪ 17 ዓመታት የባሰ ሀገሪቷ የታሰረችበትን ገመድ ውትብትብ በማድረግ እና ኢላማውን በመሳት ጥይቱን ሁሉ አባክኖ ሀራሬ ሲከትም፤ጓዶች እያል ሲጠራቸው የነበሩትም ሁሉ ባገኙት ቀዳዳ አንዳንዶቹ ቢሾልኩም የሚበዙቱ ለእስር እና ለጎዳና ልመና ተጋልጠው የሚታዩ ነበሩ።በቅጡ እና በእውቀት ያለመታገል ውጤት ነውና እንዲህ መሆኑ ያልተጠበቀ አልነበረም። ህዝብ ባልተሳተፈበት አገዛዝ ሁልግዜም ሽንፈት ከፊት ለፍት እንደሚጋረጥ ይህንን አበክረው የሚያውቁ ሀገር ከመሰባበሯ በፊት መፍትሔው በጋራ እና በእኩልነት መታገል ብቻ እንደሆነ  ከአጥር ውጪ እንዲሰደዱ የተገደዱ እና በህብዕ ራሳቸውን ሰውረው በውስጥም የሚታገሉ ሀገር ወዳድ ምሁራን ደርግ ሊወድቅ አንድ ዓመት ሲቀረው የመከሩት እና የሚናገሩት ብዙ ትንቢታዊ ልሳን ነበረ። ይህንንም ለማስታወስ ከዴሞክራሲያ ቅፅ 16 ቁጥር 3 እትም ላይ በሐምሌ1982 ዓ.ም ከተፃፈው ላይ ትንሽ ቀንጭቦ መተረኩ በሩቅ ዘመን ኢትዮጵያ ምን ሊገጥማት እንደሚችል አስቀድመው ያዩ ታጋዮች እንዳሉም ለማውሳት ይጠቅማል። ያለውን ስርዓት ገምግመው ኢትዮጵያን ወደ ገደል እንደሚገፈትራት ሲናገሩ
          
             …“ኢትዮጵያ ወደ ጦርነት እንጂ ወደ ሰላም፣ወደ እድገት፣ሊመሯት ባህሪያቸው የማይፈቅድላቸው፣ለምበተን እንጂ ለማሰባሰብ ብቃቱንም ሆነ ተሰጥዖውን ባልታደሉ፤የህዝብን እምነት ባላተረፉ መሪዎች እየተመራች ከገደል አፋፍ መድረሷን ራሳቸው ወደዚሁ መርተው ያደረሷት መሪ ተብዬዎች አፋቸውን ሞልተው ይህንኑ መርዶ የምስራች ይመስል ደጋግመው እያወሩት ነው።ወደ ወደገደሉ አንድያዋን ይገፈትሯት እንደሁ ነው እንጂ ያድኗታል ተብሎ አያታሰብም።ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ፣ዲሞክራሲያውያን ሀይላት ላይ፣ሀገር ወዳዶች ላይ ከመርግ የከበደ ሀላፊነት አሸክሟቸዋል።ይህን ሀገርን ከመፈራረስ የማዳን የመጨረሻ እና ከፍተኛ የሆነው ታሪካዊና ቅዱስ ሀላፊነት ነው። ከዚህም አኳያ ነው መፍትሄው በጥንቃቄ መፈለግ ያለበት።
           ፋሺስታውያኑ (ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር) ብለው ሁሉን ነገር በጦርነት አወደሙ፤ሀገሪቱን ለፃዕረ ሞት ዳረጉ።እኛ ደግሞ ሁሉም ነገር ለፍቅር፣ ለዕርቅ፣ለስምረት፣ለህዝባችንና ለሀገር አንድነት፣ለዴሞክራሲ፣ለሰላም ክተት ብለን በአንድ ለመካተት ድምፃችንን እስከ ዓርያም አዝልቀን ማወጅ ይኖርብናል። ስለፍቅር በስመ አብ ይቅር የሚባለው በእንደዚህ ኣይነቱ ጊዜ ነው።ስለ ፍቅር፣ ስለ ህዝቦች አንድነት፣የፖለቲካ ልዩነትን፣የርዕዮት አለመጣጣምን፣በዚህም በዚያም ምክንያት የተፈጠረ ቂምና ቅራኔን በዴሞክራሲ ጥላ ስር ተሰብስበን አገር የምትድንበትን የጋራ መፍትሔ ለማፍለቅ፣ትንሽ ትልቅ በሚል ሳንናናቅ፣እኩልነትን አክብረን፣ብስለትን በሚያንፀባርቅ ወግ ባለው መንገድ መራመድ የነገሩ ክብደት ግድ የሚለው አካሔድ ነው።”
                   
        በማለት የኢሕአፓ ልሳን ከ25 አመት በፊት በሰፊው ተርኮልን ነበር። የተፈራው ድቅድቅ ጨለማ እና ድጡ አልቀረም። ደርጉም ኢትዮጵያን ሰብሮ ለሰባሪ ሰጣት፣ ስድቦ ለሰዳቢ አስተላለፋት። መቼም ከዝንጀሮ ቆንጆ መምረጡ ግራ ቢያጋባም የአሁኑ ይባስ እንዲሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ድካም የወለደው አረመኔው ጉልቤ የፈራ የተሽቆጠቆጠ ትውልድ ላይ ደረሰና፤ደርግ . . .   ወደፊት ሂድ! አሳርፍ! ሰላምታ ስጥ! እያለ ኢትዮጵያዊውን ከፊት እርሱ ከኋላ ቆሞ ለጥይት ወላፈን አስማግዶት ሲያበቃ የተጀገነበትን ሀገር፣ባዕዳን የማረኩትን እና በሀገራቸው ወስድው ያሰሩትን ኢትዮጵያዊ ካሰሩብት ከጣልያን ድረስ እየፈቱ እንደገና ወደ ምድራቸው እንዲመልሱ ያስደረጉ ቁርጠኛ የኢትዩጵያ ልጆች የኖሩበትን ሀገር ወታደር ነኝ ባዩ ደርግ ከእርሱ ለባሰ አረመኔ ቡድን አስረከባት። ባለቤት የሌለው ቤት!!!

        የዘንድሮው ጉልቤ 24አመት ኢትዮጵያን በመግዛት ሲያስቆጥር ብቻውን አይደለም፤በስውር ነጂዎቹ ሁሉ ያብሩታል። ብቻውን መብላት ቢያቅተው ጎረቤት አፈራበት። ማዕዱን ሊካፈሉ ብዙዎች ተጠራርተው ኢትዮጵያን ዘነጠሏት።ጋጥዋት። ድሮም የታሰረ አንበሳ ዝንቦች ቢጫወቱበት ምን ሊደንቅ። ዳሩ የሚደንቀው ወያኔ ዝንብ ሆኖ ሳለ ንብ ነኝ ማለቱ ነው። ዝንቦች የተቀመመውን ሽቶ ያገሙታል ተብሏል። እውነተኛ የጥበብ ቃል ነው። የኢትዮጵያ ጠረን እስኪቀየር እስኪገለማ ድረስ የወያኔ ርብርብ ስኬትን አግኝቷል። ያ የአንድነት ወዟ፣ሉአላዊነቷ፣ከብዙ አፍሪቃውያን ይልቅ ስልጣኔን መቀበሏ እና አስቀድማ መንቃትዋ፣ድንበሯን መጠበቋ እና የህዝቧ ሰላም እና መረጋጋት በውስጡ የያዘው ጥዑም መአዛ እና ልሳላሴዋ ይህ ሁሉ ብዙ ሀገሮችን ያወደው ጠረኗ አሁን ላይ በተቀራመታት አምባገነን መንግስት ተበረዘ፣ረከሰ፣ገለማ፣ ሸተተ።

        የኢትዮጵያ አበባ ረግፎ ሳለ ወያኔ ንብ ነኝ እያለ በየ 5ዓመታቱ ብቅ ብሎ ጆሮ ግንዳችንን በሀሰት ሲያግለው፤ንብ በባህሪዋ አባባ መቅሰሟን ማስተዋል እንዳቃተው ያሳያል። ተኩላ የበግ ለምድ እንደለበሰ ዝንቧም የንብ ኩታ ደርባ መሆን አለበት። የሀገሪቷ አባባ ከረገፈ ሰነባብቷል፤የኢትዮጵያ አበባ ህብረቀላማዊ ብሔሯ እና ዘርፈ ብዙው ቋንቋዋ ነው ሲጀምር። ሲቀጥልም ከዚህ ጋር አብሮ ሊነሳ የሚችለው ሀቅ አንድነቷ ነው። ብዙ ቅርፅ እና መልክ ባለቤት የሆነች አንዲት ሀገር!!! ይህ ነው አበባዋ። ዜጎችዋ በሰሜን ያለውን በር ላለማስደፈር ከደቡብ ተነስተው ሲዋደቁላት፤ሰሜን የከተመው ለደቡብ ዳር ድንበር ደሙን ሲያፈስ። የምስራቅ ጀግኖችዋ ብርሀናቸውን ተግ አድርገው ወደ ምዕራብ ገስግሰው በዚያው የዳመኑ፤ለመጪው ብርሀን ስፍራ ለቀው በምዕራቡ የከሰሙ። ለሌላ አዲስ የብርሀን ትውልድ ዋጋቸውን ተምነው በክብር የጨለሙ። በመጨለማቸው አዲስ ንጋትን በምድሪቱ ላይ ፍንትው አድርገው ማድመቅ መሆኑን ተረድተው አደራ! አደራ! አደራ ምድሬን እያሉ በቁልምጫ ቃል ኢትዮጵያን የተሰናበቱቱ፤ እነዚህና መሰል ታሪኳ ነው አባባዋ። በአሁን ዘመን በወያኔ የረገፈው።

         ውሸት ጠርቄው ወያኔ፤ ጭንብሉን ቀድዶ ዝምብ ነኝ! ቢል በሁለት መንገድ ያዋጣወል።
1ኛ) አንበሳውን አስሮ መጫወቱ።
2ኛ) በየጥጋጥጉ ያለው የሙስና ክርፋት፣በጎሳ በብሔር በዘር መገነጣጠሉ፣መሬትን ለባዕዳን በመሸጥ                         
    እድፈት ተነክሮ ይህ የቆሻሻ ስርዓቱ ክምር ዝንብ በመፍጠር፤ባልፀዳው ፍትህ አልባ አስተዳደሩ
    ዙርያ የተቀፈቀፉት እንቁላሎች ተፈልፍለው በተቆራረሰችው ምስኪን ሀገር ሰማይ ላይ ሊበሩ       
    ማሰፍሰፋችውን በማጤን፤ዝንብ መሆኑን አምኖ ቢናዘዝ ይመከራል። 
   
        ብዙ ጋዜጠኞችና ጦማሪያ ያለአግባብ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው ያለፍርድ የሚማቅቁባት፤ ከስም በቀር ምንም የሌላት ባዶ ሀገር ኢትዮጵያ ያለ እኩልነት፣ያለሰላም፣ያለነፃነት ያለ አንድነት፣ ቅርፅ አልባ ሆና በቅኝ አገዛዝ ስር ወድቃለች። በእርግጥ የማይገረሰስ መንግስት የለም።ያ ከመሆኑ በፊት ግን ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ ሁሉ ስለ ማታለሉ ይቅርታ መጠየቁ ከወዲሁ አዋጪ ብልሀት እንደሆነ ሊያስብ ግድ ነው።ያኘከውን ሳይውጥ የውርደቱን ካባ ሊከናነበው በልኩ እየተሰፋለት መሆኑን ሊረዳ ይገባዋል።
 
         አፋኙ የወያኔ ቡድን አንቀፅ 39 ብሎ በሽነቀረውም ተውሳክ ሀገሪቷ ስትናጥ እና በየስፍራው ተበታትኖ የሚገኝውን ኢትዩጵያዊ እርስ በርሱ ሲያነታርከው ሲያባላው ምን ያህል ለጥፋት እንደቆመ አስረጅ ያደርገዋል። ለምሳሌ ግሪኮች የጀርመን ቋንቋ እና ባህል ሳይውቁ ምድሪቷ እንኳን ደህና መጣችሁ ብላ ስታስተናግዳቸው፤በምልክት ተግባብተው በነፃነት ወጥተው ሲገቡ ሌሎቹንም አጠቃሎ አብዛኞች አውሮጳውያን መገበያያ ገንዛባቸውን አንድ በማድረግ በጉልህ የተገለጠ አንድነታቸውን አሳይተዋል። የኛው ሀገር ዲግሪ ሸማች መሪዎቻችን ግን በደነቀሩት የመከፋፈል ነቀርሳ፤በብዙ አይነት ጎዳና መገነጣጠል ሰደደ እሳት ሆኗል። ሩቅ ሳንሔድ ከመሀል አዲስ አበባ እስከ ሰንዳፋ 40ኪሎ ሜትር ገደማ እና በተመሳሳይ ርቀት ወደ ሆለታ ገነት ቢጓዙ በአንድ ቋንቋ ተረድቶ አልያም በምልክት ተግባብቶ ወይም በአስተርጓሚ ሀሳብን መቀያየር አብሮ መኖር አብሮ መስራት አብሮ መምከር የማይታሰብ ነው። የጉራጌው ተወላጅ ኦሮሚያ ክልል ገብቶ ቢኖር፣ቢማር፣ቢሰራ የኢትዮጵያ አፈር ላይ ቆሞ ሙሉ ነፃነት ካልተሰማው እና ባይተዋር ሆኖ ሂድ ወደመጣህበት ተብሎ ከተባረረ፤የሰሜኑ ደስታ የደቡቡ ካልሆነ፣ የምዕራቡ ስኬት የመሀል ሀገር እና የምስራቁ ስኬት ካልሆነ፤ እንዲሁ ኢትዮጵያዊነት እርስ በእርስ መናጨት እና መበላላት ሆኖ ሲታይ ትልቅ ኪሳራ እና ድህነት ከዚህ በላይ የለም። እርስ በእርሷ የምትለያይ መንግስት አትፀናም። ማነፃፀሩ ሽሙጥ እንዳያስነሳ እንጂ፤ የምዕራብ እና ምስራቅ ከተሞች ከካሊፎርንያ እስከ ማዶ ቨርጂኒያ የተንጣለለው 3591 ኪሎሜትር በ 5ሰአት የአየር በረራ ቢገባደድ ሌላ ሀገር ሳይሆን ያው አሜሪካ ነው። አንድ ቋንቋ፤ግን ብዙ ልዩ ልዩ ህዝብ!አንድ አገዛዝ “እኩል የመኖር መብት!”  

         ዘመን እያደገ በስልጣኔ በተለወጠበት በዚህ ወቅት የኛዎቹ የአንቀፅ 39ሰለባዎች የሆኑት ተላላ ዜጋዎቻችን መገንጠልን እንደስልጣኔ መርጠው ለመቆራረስ መጋደላቸው የእድገት ጉዞ ሳይሆን የድቀት ጉዞ ቢባል ስህተት አይደለም። ይህም ሂደት ሀገሪቱን ባለ ብዙ ባንዲራ ባለቤት አድርጓት አማራው በነፃነት ትግራይ ሔዶ እንዳይሰራ፣ጋምቤላው ከኦሮሚያው ዘንድ ምንም ወዳጅነት እንዳይኖረው ሀረሪው ትግራይ እንዳይከትም፤ባይተዋርነትና እርስ በእርስ የማቃቃሩ አስከፊነት በየክልሉ ተንሰራፍቷል። በተጨማሪም በብዙ የእምነት ቤቶች መሀከል ከዚህ በፊት ተሰምቶ እና ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ አንድ አምላክ እናመልካለን በሚሉት ዘንድ ሁሉ የኤርትራውያን የእምነት ቤት፣የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የእምነት ቤት፣የኢትዮጵያውያን የእምነት ቤት በማለት ምንም እንኳን አማርኛ ጠንቅቀው የሚናገሩ ቢሆኑም አንድ ላይ ለመሆን ትልቅ ገደል መፈጠሩ እና እርስ በእርስ ያለው አንድነት የማጣት እና መገነጣጠል የ1983  ወረርሽኝ መሆኑን ማንም አይስተውም።

          የኢትዮጵያ እስከዛሬ በሁሉም ስፍራ በብሔራዊ ቋንቋዋ ስትናገር ብትቆይም በአሁኑ ወቅት ከትናንሽ የመንደር ቢሮ እና እስከትልቁ የሀገሪቷን ጠቅላላ ጉዳይ ከሚመሩ ቢሮዎች ውስጥ እና ከኢትዮጵያም ውጪ በሚገኙ የወያኔ ኤምባሲዎች ጭምር የመግባቢያ ቋንቋው ከመይ ከመይ! ፅቡቅ? ብቻ መሆኑ ምን ያህል የኢትዮጵያ ደብዛ እንደጠፋ ያሳያል።በተለይም ብዙ ብሔሮች ለሚወልዷቸው ህፃናት አማርኛ የሚባለውን ቋንቋ እና ፊደላቱን ደብቀዋቸው፤ከጥቂት አመታት በኋላ ፈፅሞ በፊደልም በንግግርም ወደማንስማማበት አስከፊ የመገነጣጠል ኩይሳ ላይ ተቆልለን መገኝታችን የተረጋገጠ ነው። የወያኔ የክፋት ተልዕኮ ማሳኪያ የሆነ ትውልድ መታየቱ በእጅጉ አሳዛኝ እና አሳፋሪ ነው። ይህም የአረመኔው መሪ መሰሪነት ነው። ህዝብ ሲለያይ እና ሲከፋፈል በእርግጥም ወያኔ ሀገሪቷን የመስበር ጅማሮውን ወደ ዳር ለማድረስ በእጅጉ ይቀለዋል። ወያኔ ከወዲሁ በተቀናጀ ህዝባዊ አመፅ ከኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ ከነ ጋሻ ጃድሬዎቹ ካልተነቀለ 80 ትንንሽ ሀገራት ወደ አለማችን ብቅ ማለታቸው እና ከነበሩት ሀገራት መሀል ደግሞ ኢትዮጵያ ተረት ሆና እንደምትቀር እና እንደምትጠፋ ከወዲሁ ማሰብ ያስፈልጋል። ነገር ግን ይህ ትልቅ ውርደት ሳይንሰራፋ በፊት የምድሪቷን ጠላት እና ገንጣይ፣ አሽባሪ ቡድን በሁሉ አቅጣጫ መፋለም፤ ወጋችን፣ ባህላችን፣ኑሮአችን ሊሆን ይገባል።

       ወያኔ አስቀድሞ ገና በጠዋቱ ኤርትራን ከባህር በር ጋር ሲያሸበልል፤ በማስከትልም ሁሉም ነገር ትግራይን ለማልማት!!! በሚለው መፈክሩ የልማት ትልሙ ሁሉ ሰሜኑ ላይ አተኩሮ የትውልድ ቦታውን ለማሳደግ ከጎረቤት ከተሞቹ መሬትን እየተቀራመተ የትግራይን የቆዳ ስፋት በመለጠጥ፤የሀገሪቱን ደህንነት ማስጠበቂያ ክፍሎችን እና ታላላቅ ተቋሞች ዋና ቢሮአቸው መቀሌ ከተማ እንዲሆን አብዛኞቹን አዘዋውሮታል። ቀሪዎቹንም ማዛወሩ አይቀርም። የህዝብን ንብረት ለአንድ ብሔር ብቻ መበልፀጊያ ማዋል ስርቆት እና ስርዓተ ቢስነት ነው።የፋሺሽት ጣልያን ማህተም። ከዚህ ሁሉ ዝርፊያ በኋላ የመጨረሻ መደምደሚው፤ደህና ሁኑ! ደህና ሁኑ ጅሎች! የዛሬ ተላሎች የነገ ለማኞች! ደህና ሁኑ ደህና ሁኑ! ብሎ በኢትዮጵያውያን ላይ በማፌዝ የቋመጠለት የደደቢት አጀንዳው፤ትግራይን መገንጠሉን ተግባራዊ ያደርጋል። ሁሉንም እርስ በእርሱ አናቁሮታልና የፈለገውን ቢዘጋ ቢከፍት ከልካይ የለውም። የአንቀፅ 39 ዋና ተፈላጊነቱም ኢላማውን መታ ማለት ነው። ሲቀጥልም ከኤርትራ ጋር ያለውን የናፍቆት ፍቅር አሀዱ ብሎ በኢትዮጵያውያን ብርና ወርቅ የመጅምርታውን መለኪያ ያጋጫሉ።ቺርስ!!! ወያኔ አነጣጥሮ አልሞ የተኮሰው ለዚሁ ነው ትግራይን ከኢትዮጵያ ነፃ ለማውጣት። ነገር ግን የኢትዮጵያ ቁርጠኛ ልጆች ባሉበት ምድር ላይ መበታተኑ መለያየቱ መገነጣጠሉ ግቡን አይመታም። አዋጪ ሆኖ ሀገርን የማያለማ እና ለህዝብ እድገት ደንቃራ መሆኑ በተጨባጭ ታምኖበታል። ስለሆነም በሚገነፍል ቆራጥ የህዝብ እምቢተኛነት ይህ ውጥን እንደ ከንቱ እና እብቅ መሆኑ አይቀሬ ነው። ይልቁንም ለወያኔ የተሻለ የሚሆነው ስለፈፀመው ትልቅ በደል እንዲሁም ለአንዲት ኢትዮጵያ መታገል በሚል ጭንብሉ ሀገርን በመዝረፍ ገንጥሎ በማስገንጠል ስለፈፀመው ትልቅ ወንጀል እና ሀጥያት የኢትጵያን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ አሊያም በፍርድ ወንበር ፊት ቆሞ ቅጣትን ለማጣጣም መዘጋጀት ብቻ ነው። ከዝንጀሮ ቆንጆ የቱ ነው ተብሎ መረጣ ውስጥ ቢገባ በርግጥ ወያኔ ከሁሉም አስቀያሚ ነው። በግፍ የተሞላ እና የኢትዮጵያዊነት ጠላት።

         ይህ ሀሳብ ከመዘጋቱ በፊት በድጋሚ አንድ ነገር ይመከራል። በታሪክ እንዳየነው በሀገራችን ውስጥም ሆነ በውጭ ተነስተው የነበሩ ጨካኝ መሪዎች መካከል ያልወደቀ እና ያልተሻረ አምባገነን መንግስት ፈፅሞ የለም። ህዝባዊ ትግል እና ቀን ጥሎአቸው ሁሉም መሪ የተባሉቱ የህዝብ ጠላቶች ጥቁር ታሪክ ሆነው አልፈዋል። ወያኔም የታላቅ ወንድሞቹን አወዳደቅ እና ቅጣት እንደትምህርት በመውሰድ እየገሰገሰ እንደደራሽ ወንዝ የመጣበትን የህዝብ ቁጣ እና ትግል በማጤን ከወዲሁ ተፀፅቶ በ24 አስጨናቂ አመታት ውስጥ ስላደረሰው በደል ኢትዮጵያውያንን ይቅርታ እንዲጠይቅ ይመከራል፤ይህን የሚያስተውል ልብ ከሌለው ከፊት ለፊቱ ስለተዘጋጀለት ፍርድ እና ቅጣት ዝግጁ ሊሆን ይገባል። በርግጥ የወያኔ ውድቀት እና መንኮታኮት በቅርብ ነው፥በደጅ ነው ።

እውነት ምንግዜም ያቸንፋል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
No comments:

Post a Comment