Friday, July 31, 2015

ወርቁ ቢጠፋ ፤ ሚዛኑ ጠፋ ?

ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ
Finote Democracy Voice of Ethiopian Unity
Efdpu@aol.com www.Finote.org 
ወርቁ ቢጠፋ ፤ ሚዛኑ ጠፋ ?


ዛሬ፤ ሕዝብን በሀገር ፤ ገበሬን በዕርሻ፤ ስብልን በማሳ፤ እህልን በጎተራ ፤ እንስሳትን በሜዳ፤ ህፃናትን በትምህርት ቤት፤ ቀሳውስትን በቤተ-መቅደስ፤ ሸኹን በመስጊድ፤ ራባዩን በምኩራብ፤ ወታደሩን በጠረፍ፤ ማግኘት ከማይቻልበት ሁኔታ ተደርሷል ። ላወቃቸው፤ ሁሉም የሀገር ቅርሶች ነበሩ። ክብራ ቸውንና ጥቅማቸውን በሚገባ ለተረዳ ዜጋም ፤ ዋጋቸው ከወርቅ፤ ከአልማዝና ዕንቁ፤ ከከበረ ድንጋይም ይበልጥ ነበር ።
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ግን እነኝህ ሁሉ የተከበረ ቦታ አልተሰጣቸውም ። እንዲያውም ቅስማቸው እየተሰበረ እንዲከስሙ እየተደርጉ ናቸው ። ማር ለአህያ እንደማይጥመው ሁሉ ፤ የሀገርን ጥቅም ፤ የሕዝብንም ክብር ፤ የማያውቅ ሥር ዓት አራማጅም እንዲሁ ፤ ለታሪክና ባህል ዋጋ አይሰጣም ። የራስ ማንነት ገላጮች ስለሆኑ ለሀገር ቅርሶች ደንታ አይኖረውም ። ሁሉንም ያጠፋቸዋል። ለታሪክ ቅርስነት እንዳይቆዩ፤ ያፈልሳቸዋል። ለተተኪው ትውልድ ለማሰረጃ እንዳያገለግሉ ደብዛቸውን ያጠፋዋል ።
ይህንን የሚያደርገውም፤ ጥንታዊቷና ታሪካዊቷን ኢትዮጵያን አጥፍቶ፤ ቅርሷና መልኳ፤ ማንነቷናም ባልታወቀች ሌላ ሀገር ስም ለመተካት ታስቦ ነው። ነገር ግን፤ ይህ አጥፊ ቡድን ፤ አንድ ያልተገነዘበው ጉዳይ ቢኖር ፤ ወርቁ ቢጠፋም ፤ ሚዛኑ ያልጠፋና የማይጠፋም መሆኑን ነው ። እኛ ደግሞ፤ የተወለድነው፤ ያደግነውና እየታገልን የምንሰዋው፤ ለዚያች ታሪካዊትና ዘለዓለማዊት ለሆነችው ኢትዮጵያ ብቻ ነው። ይህ የኅልውናችን፤ የትግላችንና የመሥዋዕታችን አልፋ- ኦሜጋ ሆኖ፤ በደማችንና አጥንታችን ውስጥ ተዋኅዶ ይኖራል ። እስከ ዘለዓለሙ ! እስከ ምፅዐቱ ! እስኪያልፍ ያለፋል እንጅ፤ መከራው አልፎ ብሩኅ ቀን እንደሚመጣ ግን አንጠራጠርም !
ወያኔን ተፃርረን የምንታገለው መሠረታዊው ምክንያት ይህ ነው ። ይህንን መሰረታዊ ምክንያት አንግበን ለመታገል የማንንም ምክር፤ ፈቃድና ርዳታ አንጠይቅም ። ኢትዮጵያዊነታችን፤ ከምንምና ከማንም በላይ ስለሚበልጥብን፤ በሀገራችን ብሄራዊ ጥቅም ላይ አንደራደርም ። ያንዱ ኃያል መንግሥት መሄድና የሌላው መተካት፤ ይህንን ፅኑ እምነትና አቋም አይለውጠውም ። አንደ በተሃ (?) አፍለኝነት፤ እንደ እስስት ተለዋዋጭነት፤ እንደ እባላ- ባዮች ጥቅመኝነት፤ እንደ ፀሀፍ (?)- ፈሪሳዊ አስመሳይነት፤ ባህርይ የለንም። ለመኖር ብቻ ሲባል ለመኖር የትግላችን መርኅ አይፈቅድልንም ። ይኸው ባህርይና ሰብዕና የመላውን ሕዝብ አመኔታ አትርፎልናል ብለን አናምናለን ።
ምክንያቱም፤ ወርቁ ቢጠፋም ሚዛኑ ስለአልጠፋ ነው ። ሚዛኑ ደግሞ ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማለት ነው ። ሚዛንን ከሕዝቡ ጋር ለማዛመድና አንድም ሁሉትም ናቸው ብሎ ለመናገር የሚያስችለው፤ የበለፀገ ታሪክ፤ የዳበረ ባህል ያለው በመሆኑ፤ አባይ ያልሆነ ሚዛን አለው ። ሁሉ-አቀፍ መሥተጋብርና ትክክለኛ የኅሊና ፍርድ ስጭ ሕዝብ በመሆኑ የማይናጋ ሚዛን ባለቤት ሕዝቡ ነው ። እንደ በተሃ ጠጅ አፍለኛ ያልሆነ ፤ እንደ ብረድስት ሽሮ በቀላሉ የማይገነፍል፤ ለመጣው ሁሉ የማይሰግድ፤ ሥልጣን ለጨበጠ ሁሉ የማያጎበድድና አሜን ብሎ የማይገዛው ፤ በጥቅመኞች ስብከት የማይታለል ፤ በፍየል ወጠጤዎች ድንፋታ የማይደነብር ፤ በእበላ-ባዮች ወከባ የማይበገር መሆኑን አረጋግጧል
።በዚህ ምክንያት፤ ሚዛኑን አስከብሮ ይኖራል ። ወርቁ ቢጠፋበትም ሚዛኑን አላጣም ። ማንም ሊያሳጣው አልቻለም ። ሕዝቡ፤ ልዕልናውንና ስብዕናውን ከኅሌና ሚዛኑ ጋር አዋኅዶ ቆይቷል። ዛሬም በዚሁ ሁኔታ አለ። ሚዛኑንን ለማንም ሳያስነካ ወደ ፊት መኖሩን ይቀጥላል ። ወርቁን ቢያጣም፤ ሚዛኑን አላጣም ። " ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ ጠፋ ? የተባለውም እኮ ለዚህ ነበር !
የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ የደርግን ጭካኔ ተቋቁሞ የተሻለ አስተዳደር ለማምጣት ሲል ከፍተኛ መሥዋዕት ከፈለ። ግን ፤ ለባሰ አስከፊ ሥርዓት ተጋለጠ እንጅ፤ የከፈለውን መሥዋዕት የሚመጥን ነፃነት እንኳን አላገኘም ። ያም ሆኖ ግን፤ ሚዛኑን ሳያናጋ ክብሩን ጠብቆ ለነገው ብሩኅ ተስፋ ይታገላል ። የሀገር ውስጥ፤ የአካባቢና የዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ተባብረው ኅልውናውን ለማጥፋት ቢጥሩም ፤ ሀገራዊና ሕዝባዊ ሚዛኑን ሊያናጉበት አልቻሉም ። ወደፊትም ቢሆን ይደክማሉ አንጅ፤ ኢትዮጵያዊ ሚዛኑን ለማናጋት፤ ችሎታ አይኖራቸውም ። ያም ስለተባለ ኢትዮጵያዊ ሚዛኗን ጠብቃ የምትቀጥለዋን ሀገር አድርጎ ለማቆየት የሚደረገው ጥረት ሁሉ ቀላል ይሆናል ማለት አይቻልም ። ለዚህም በቂ ምክንያቶች አሉ ። የሚከተሉትን እንደ ማስረጃ መጥቀስ ይኖርብናል ።

1. የሀገሪቱን ችግሮች በሚገባ አለመረዳት ዋነኛው እንደሆነ ይታመናል ።
2. ሀገሪቱ ችግር ያለባት መሆኗ ቢታወቅም፤ እንኳ ፤ ጥልቀቱ፤ ስፋቱና ክብደቱ እስካሁን በቅጡ አልታወቀም ።
3. ችግሩ በሚገባ ካልታወቀ ደግሞ መፍትሄውን ማግኘት አይቻልም ።
4. የሀገሪቱ ዋና ችግር ፈጣሪ የሆነው፤ የሀገሪቱ ተወላጅ በመሆኑ፤ የባዕዳንን ሙሉ ትብብርና ድጋፍ ማግኘቱ፤ ችግሩን ውስብስብና ይበልጥ አስቸጋሪ ማድረጉ ። የባዕዳን ወራሪ ኃይል ባለመሆኑ ምክንያት፤ የውጭ ዕርዳታ ለማግኘት ከባድ መሆኑ ።
5. መፍትሄ ፈላጊ ነኝ የሚለው ክፍል አለመተባበሩ። ይልንቁም፤ ዕርስ በዕርሱ በመከፋፈልና እንዲያውም ለመፍትሄው ፍለጋ ደንቃራ መሆኑ።
6." የጨነቀው ሙቅ አነቀው " እንዲሉ፤ የሀገሪቱ ዜጎች ራሳቸው መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ፤ ምዕራባውያን መፍትሄ ያማጡልናል ብለው ቀቢፀ -ተስፋን ተስፋ እያደረጉ መጨነቅ፤
7. የኢትዮጵያን ሕዝብ ዕውነተኛ ማንነት ፤ ባኅርይ፤ ጠባይና ሥነልቦና በሚጋባ ያለመረዳት ችግር፤ እንታገላለን ብለው በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ወስጥ መኖሩን መካድ አይቻልም ። ለዚህም ይመስላል፤ ብዙዎቹ፤ ኅብረት ፈጠርን ካሉ በኋላ፤ የተፈራረሙበት ሰነድ ላይ ያስቀመጡት ፊርማ ሳይደርቅ ወደ መፈራረስና ወደ ጠብ የሚሄዱት ።
የኢትዮጵያን ሕዝብ በሚገባ ባለማወቃቸው፤ ሕዝብን ወደ ማታለልና እራሳቸውንም ወደ መደለል ተግባር ይሰማራሉ ። ይህ ደግሞ ሕዝቡን በሚገባ ያለማወቅ ችግር ወጤት ነው ። እኛ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጠባይና ባኅርይ በሚገባ እናውቃለን የሚል ግብዝነት ባይኖረንም ፤ ማወቅ የምንቸለውን ያህል ግን በመጠኑም ቢሆን እንረደዋለን ። ሕዝብን በሚገባ ያለማወቅ ችግር፤ ከባድ ቸግር እንደሆነ የትግል ተመክሯችን አስተምሮናል ።
ከብዙ በጥቂቱ፤ እነኝህ ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው ብለን እንገምታለን ። ችግሮቹ በቀላሉ እሳካሁን ሊቀረፈቱ ያልተቻሉት፤ የችግሩ ፈጣሪዎች አምባገነኖች ብቻ ሳይሆኑ፤ እነርሱን ለማሰወገድ የሚችል ኃይል ለመፍጠር አለመቻላችን ጭምር ሆኖብናል ። ይህንንም አውቆ በድፍረት አለመናገር ደግሞ ራሱን የቻለ ሌላ ተጨማሪ ችግር እየሆነብን ቆይቷል ። እያንዳንዱ ዜጋ የራሱን ስኅተት እያወቀ የችግሩ አካል መሆኑን በድፍረት ካላመነ በስተቀር፤ እናም ለመፍተሄው ፍለጋ የራሱን ድርሻ እስካልተወጣ ድረስ፤ የሀገራችንን ችግር ማንም ባዕድ መጥቶ ይፈታልናል ብሎ መጠበቅ ግብዝነት ነው። " እራሳችን ያቀለልነውን አሞሌ፤ ሌላ ባለ ዕዳ ሊሸከምልን አይችልም ። ስህተተን አምኖ መቀበልና ፈጥኖ ማረም ፤ ብሎም፤ ይቅርታ መጠየቅ የታላቅነት ምልክት እንጅ፤ የድክመት ነፀብራቅ አይደለም !
የማነኛውም ሀገር መሪ መጀመሪያ ተጠያቂነቱና ኃላፊነቱ ለራሱ ሀገርና ለመረጠው ሕዝብ መሆኑን ሳንገነዘብ ፤ ፕሬዝደንት እከሌ ዋይም ጠቅላይ ምኒስትር እከሌ ሊረዳን ይችላል ብሎ መተማመን፤ የዓለምን ፖለቲካ ጠባይና አካሄድ አለመረዳት ብቻ ሳይሆን፤ የዋህነትም ጭምር ይሆንብናል ። ፕሬዝደንት ኦፓማ በቆዳቸው ጠይምነት የተንሳ ኢትዮጵያን ይረዳሉ ብለው ያመኑ ብዙ የዋሆች እንደነበሩ የቅርብ ትዝታችን ነው:፡ የሰው ልጅ ለምኞት ባይከለከልም፤ ጠይሙ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ፤ የተመረጡት የአማሪካንን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠብቅ መሆኑን ቃለ መሃላ ወስደው ነው። የኣሚሪካ ህግ ተገዥ በመሆናቸውም የሚያገለግሉትም ለአሜሪካ ህግና ደንብ ነው። የአሜሪካ ወታደራዊ- የኢንዱስትሪና ሁል-አቀፍ ጥቅምን ( American- Military - Industrial- Financial Interest ) ለመጠበቅና ለማስጠበቅ መሆኑን ማጤን ይግባናል ። እራሱ ያረረበት የሌላውን የሚያማስል ሞኝ የለም ። ቢፈልጉትም አይገኝም ። እየባከኑ መኖር ብቻ ነው ትርፉ ።
የሰሞኑን የኦባማ ኢትዮጵያን መጎብኘት አስመልክቶ ብዙ ቲያትሮች ሲውጠነጠኑ ታዝበናል ። የእርሳቸው አዲስ አበባ መገኘት፤ የወያኔን ልብና አዕምሮ ይለውጠው ይመስል፤ እስረኛች ይፈታሉ፤ ወያኔ የዘጋውን በር ለተቃዋሚዎቹ ይከፍታል ። የዴሞክራሲ ጭላኝጭል በሀሪቱ የፖለቲካ መልከዐ- ምድር ላይ መንዣበብ ይጀምራል፤ ሠርግና ምላሽ ሆኖ ሕዝቡ በደስታና ሀሴት ይፈነድቃል ወዘተ ተብሏል ። የሀገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ በቅርብ የሚከታተሉ ተንታኞች ያላቸው ግንዛቤ ግን ከዚህ ምኞት የተለየ ሆኗል ። የሚከተሉት ግንዛቤዎች ያስቀምጣሉ ።
1. የኦባማ ጉብኝት የአሜሪካንን ጥቅም በበለጠ ከማስጠበቅ የተለየ ትኩረት አይኖረውም ።
2. ታማኝ አገልጋይነቱን በተግባር ያስመሰከረላቸውን ወያኔን አበጀህ በርታ ከማለት ያለፈ ለሕዝቡ የሚጠቅም ፋይዳ አያመጣም ።
3ኛ የወያኔ አገዛዝ የሚ ጠነክርበትንና በሥልጣኑ ተደላድሎ የሚቀጥልበትን በበለጠ ከማጠናከር በቀር፤ ለሕዝብ የሚጠቅም ያመጣል ተብሎ አይጥበቅም ። የጠበቀም ካለ እንደናቱ ጡት ርሳው።
4. ኢትዮጵያ፤ የአሜሪካ ሀረግ ሬሳ ሪፑብሊክ ( Banana Republic ) መሆኗን የሚያረጋግጥ ይሆናል ።
5. ምናልባት ከእንግዲህ በኋላ፤ ተቃዋሚው ሁሉ፤ አሜሪካ ይረዳናል የሚለውን ተስፋ ሁሉ አሟጥጦ አንድ ላይ ለመተባበር በር ይከፍትለት ይሆናል።\
ይህንን የሚሰማ ሁሉ፤ ( " እባካችሁ አታስጎምጁኝ ") ሊል ይችል ይሆናል፡ ፡

ያም ተባለ ይህ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ሁሉንም ታዝቦ ጨርሶታል ።
አንቱ ባራክ ኦባማ ያማሪካ ዕንግዳ፤
ጎራ ብለው ነበር በምኒሊክ ግቢ፤ በወያኔ ጓዳ፤
እኛስ መስሎን ነበር እስረኛ ሊያስፈቱ ፤
ፍትህ ከጠፋበት ከወህኒ ቤቱ
ፍዳውን ሊያስቆሙ ረሀብ ርዛቱ
አንቱ ባራክ ኦባማ ያማሪካ ዕንግዳ፤
ሌላ ጉዳይ ነበር ለካ ያመጣዎ ፤
ወያኔን መርቀው እኛን ለመርገምዎ፤
ጩኸታችን ንቀው ጥለው መሄድዎ ፤
መላው የጦቢያ ሕዝብ እንዴት ታዘበዎ ።
ይብላኝ ለርስዎ እንጂ፤ እኛስ አንጎዳም፤ ኢትዮጵያም አትጠፋም፤
ይህንን ለማየት ግን ይቆዩ በሠላም ።
ብሎ ተችኝቶባቸዋል ፤ ለአሚሪካው ፕረዝደንት !
ወትሮውንም ቢሆን በታሪክ፤ ከራሱ በቀር በማንም የማይተማምነው ሕዝብ፤ዛሬ እንደገና ያንን ዕምነቱን በድጋሜ የሚያጠነክርለት ዕድል አግኝቷል ። ሁሉም ነገር ግልፅ ሆኖለታል ። ይኽውም ፤እራሱ ታግሎ ራሱን ነፃ ካላደረገ ፤ ማንም መንግሥት ሆነ ፤ ሀገር ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅት ወይም ሰብዓዊና ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ነፃ የማያደርጉት መሆኑን እንደገና አረጋግጧ
። ሁሉንም አማራጮች ሞክሮ ሞክሮ ስላልተሳካለት፤ አንድ ምርጫ ብቻ ቀርቶታል ። ይኸውም፤ በሁሉን አቀፍ ትግል የታጀበ ሕዝባዊ ኣመፅ! አካሄዶ፤ የራሱ ድል መጎናፀፍ ይሆናል ። ይህ እንዴት ይሳካል ? ማንስ ያሳካዋል ? የሚባሉትን መሪ ጥያቄዎች መመለስ ግን ወሳኝ ነው ።፡
የፖለቲካ ትግል በድል እንዲጠናቀቅ ካስፈለገ፤ የኃይል ሚዛኑን በራስ እጅ ማስገባት አስፈላጊ ይሆናል ። የኃይል ሚዛኑን የሕዝባዊ ወገን ለማደረግ ፤ የፀረ - ሕዝብን አከርካሪ አጥንትና የኃይል ስበት ማዕከል ማስበር የመጀመሪያው ዒላማ ሊሆን ይገባል ። " ዝርዝር ኪስ ይቀዳል " እንዲሉ ፤ ዝርዝር አፈጻጸሙና አካሄዱ በሙያው የተካኑ ብቁዎች የተግባር ድርሻ ይሆናል ። ይህ በቃል እንደሚያወሩት ቀላል ስላይደለ ፤ ብርቱ ተግባርንና ከባድ መሥዋዕትን መጠየቁ አይቀሬ ነው ። ለዚህ ደግሞ ቁርጠኝነትን ቀጣይነትንና ቆራጥነትን የሚጠይቅ መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ይህንን ሳያሟሉ በጥድፊያ የሚደረግ ሸተክ- በተክ፤ ሠላማዊውን ሕዝብ አስፈጅቶ -አስጨርሶ " ዘቅዝቆ ሮጠ ወደ ቦንጋ ወንዝ ! " የሚል ትችትንና ፌዝን ከማትረፍ በቀር ፋይዳ አያመጣም ። አስቀድሞ ማሰብ፤ ከታላቅ ጥፋት ያድናል !
ወቅታዊቷ ሀገራችን የሚከተሉትን መልክ ይዛለች ።
1. የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፤ ሁሉ እያላት ሁሉንም እንድትጣ የተደረገች ሀገር ሆናለች ።
2. ይህ ሁኔታ የ ዓለም ተመፅዋዕች ሀገር አድርጓታል ።
3. መላው ሕዝቧም ፤ " የመጀመሪያው ምርጫህ ምን እንዲሆን ትፈልጋለህ ? " ተብሎ ቢጠየቅ፤ ያላንዳች ማመንታት ፤ሁሉ፤ ከሀገሩ መውጣትን ያስቀድማል ። ወያኔና ተባባሪዎች ግን፤ ለእነርሱ ብቻ ምድረ-ገነት የሆነችው ሀገር ሰለሆነችላቸው ፤ ሌላውን እያባረሩ እነርሱ ይኖሩባታል ።
4. ዛሬ፤ የሀገሪቱን ስታራተጂያዊ/ ዘላቂ ጥቅም የሚያስጥብቅ ኃይልም ሆነ ማዕከል አለመኖሩ ፤ መፃዒ- ዕድሏ ወዴት አቅጣጫ እንደሚያመራ መተንበይ አልታቻለም ። ሕዝቧ፤ በሜሶፖታሚያ ሀገር፤ በሀረግ ተንጠልጥሎ እንደነበረ የአትክልት ቦታ እየዋለለ ይገኛል ።
5. የተቃዋሚው ክፍልም ፤ መልኅቅ ስለሌለው ፤ በከንቱ ይንሳፈፋል ። በመሆኑም የጋራ ስትራተጅ ነድፎ ለመታገል አልቻለም ። ሕዝቡም መሪ አጥቷል ። ተስፋ ቆርጧል ። በተፈራረቁበት ሦስት ሥርዓት ባጋጠመው የጭቆና አገዛዝ ምክንያት ፤ መንግሥት የሚባለውን ተቋምም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሊያምን አልቻለም ። አይፈረድበት !
6. የሀገራችንን ያልተነካ ጥሬ ሀብት ለመዘረፍ ባዕዳኑ መልካም አጋጣሚ አግኝተዋል። ያላንዳች ቁጥጥር፤ ይዘርፉታል ። ያሸሹታል።
ኢትዮጵያ ሀገራችን ዛሬ አንድ መሠረት ብቻ ይዛ ቀርታለች። ሚዛኑ ያልተዛባ ጨገሬታዋ ብቻ ! በመሆኑ፤ " ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ ጠፋ ? " እያለች ለመቆየት ተግድዳለች !


ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኖራለች !

No comments:

Post a Comment