Tuesday, July 7, 2015

ውሃ ውሃው ሄዶ፤ አለቱ ይቀራል... ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ


ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ
Finote Democracy Voice of Ethiopian Unity
Efdpu@aol.com www.Finote.org
የፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሀተታ ሰኔ 25 ቀን 2007 .. የተላለፈ
ውሃ ውሃው ሄዶ፤ አለቱ ይቀራል
" ጣሊያን በአደዋ፤ በማይጨው ፤ እንግሊዝ በመቅደላ ፤ መጥቶ ተመለሰ ፤ ቱርክም በዘይላ፤ ግብፁም በቀይ ባህር፤ ድርቡሽ በመተማ፤ መጥቶ ተመለሰ ፤ ሶቪየትም በደርጉ፤ መጥቶ ተመለሰ ፤
ምዕራቡ መጣእንጅ ከነወያኔጋር ደም እያፈሰሰ፤

ዜጋንአሰድዶ፤ አገር አስቆርሶ፤ሕዝብእየጨረሰ ። " ሰቆቃወ ወሰቆቃ ዘ/ለ ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ፤ በረዥሙ ታሪኳ ፤ በኅልውናዋ ላይ የተቃጡባትን ፈተናዎችን ተቋቁማ ፤ ባላንጣዎቿንም ሁሉ አቸንፋ እስከ ዛሬ ደረስ ሳትጠፋ መቆይቷን ከላይ፤ የተጠቀሱት ስንኞች በመጠኑም ቢሆን፤ ሊገልፁ ይችላሉ ። እስከዛሬ ደረስ፤ ሀገራችንን ሊያጠፏት የሞከሩ፤ የውጭ ባዕዳን እንደነበሩ፤ ሁሉም ዜጋ ይገነዘበዋል። ሁሉም የሰሩትን እየሰሩ በመጡበት እግራቸው ተመልሰው ሄደዋል። ጊዜ ያመጣቸው አልፎ-ሃጅ ጎርፍ ስለነበሩ ሁሉም ነጥፈዋል። ደርቀው ቀርተዋል። ሀገራችን ግን እስካሁን አለች። ወደፊትም ትኖራለች። ሕዝቧም አለ ወደፊትም ይኖራል።
አለቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ መሠረቱን ሳያናጋ አስክዛሬ ቆይቶ ነበር ። እንደ ጅብላርታ ቋጥኝ፤ መከራውን ሁሉ ተቋቁሞ እስካሁን መቆየቱ፤ የሀገራችን በነፃነት የመቆየት ቋሚ ምስክር ነበር። ይህ ማንነትና ጥንካሬ ወደፊት እንደተጠበቀ ይቆያል ብሎ ማለት ከማይቻልበት ደረጃ እየደረሰ መምጣቱን የሚሰጉ ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም ። እኛም የስጋቱ ተካፋዮች ነን ።
ዛሬ ሀገራችን፤ የበግ ለምድ የለበሰ ቀበሮ፤ ወስጠ-አዋቂ የሆነ፤ የገበያ ግርግር ኪስ አውላቂ፤ የባዕዳኑን ጥቅም አስጠባቂ
መጥቶባታል ። የሀገሩን ታሪክ ናቂ ፤ የራሱን ሕዝብ አዋርዶ ፤ የውጭ ባኅልን አድናቂ የሆነ ቡድን በትረ -ሥልጣን ይዟል ።
ዛሬ፤ ነገር- ዓለሙ ሁሉ፤ ለሰሚው ግራ ሆኗል። ሁሉም ግራ የተጋባው ፤ ይህንን እንቆቅልሽ መፍታት ባለመቻሉ እንደሆነ ብዙ ታዛቢዎች ይስማሙበታል ። ታዛቢዎቹ ደግሞ እንቆቅልሹን ሊፋቱ የሚያስችላቸውን ብልሃት እንኳን አላገኙም።
ሁሉም ዜጋ፤ የሀገሩን ችግር የሚያስወግድበትን ዘዴ አላገኘም። ራሱ ለራሱ በራሱ መፍተሄ ፈላጊ መሆኑ ቀርቶ በጠራራ ፀሀይ የፋኑስ መብራት ይዞ ሰው ይፈልጋል። ሁሉም በየአቅጣጫው ሙሴን ፍለጋ ይሯሯጣል! ተፈላጊው ሰው ግን እስካሁን አልተገኘም ። ተወደደም ተጠላ፤ ዘገየም ፈጠነም ሰው መገኘቱ/ መምጣቱ ደግሞ የማየቀር ታሪካዊ ሃቅ ነው። ያ ዕውን እንዲሆን ከተፈለገ ደግሞ ፤ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ሥራ መስራት ገድ ይላል። ሳንታክት በተደጋጋሚ እንደገለፅነው ሳይገሉ ጎፈሬ፤ ሳይሰው ነፃነት፤ ሳይሟገቱ ስርዔት፤ ሳይታገሉ ፍትኅ-ርትዕ ፤ ምን ጊዜም ማግኘት አይቻልም ።
ኅብረት ሃይል መሆኑን ሁሉም ተረድቶ ካልተባባረ ፤ ሃይል አይገኝም፡፡ ሃይል ከልተያዘ ደግሞ ለውጥ ሊመጣ አይችልም። እንዲያው፤ ተናግሬ ነበር ለማለት ካልሆነ በስተቀር፤ " ኅብረት ሃይል ነው፤ ኅብረት ከሌለ ሃይል አይመጣም " እየተባባሉ
የቃላት መለዋወጥ ጨዋታ መጫወት፤ " የዶሮና ዕንቁላል " ተረት እየተረቱ ከመኖር የዘለለ እርባን አያመጣም ። የታሰበውን ውጤት ለማስመዝገብ በግድ ቆራጥ ውሳኔ መውሰድ ያስፈልግ ነበር። እስካሁን ደረስ ግን ቆራጥ ወሳኔ የውሃ ሽታ እየሆነ ቀርቷል ። እስከ አፍንጫው የታጠቀን ፀረ- ሕዝብ ጠላት፤ በሰላማዊ ሠልፍ፤ በስብሰባ ወሳኔ፤ በግጥምና ውርድ- ንባብ፤ በቀረርቶና ፉከራ፤ በደጅ-ጥናትና ልመና ማስወገድ እንደማይቻል፤ የትግል ተመክሯችን አስረድቶናል ።
የሀገር ተወላጅ ወራሪ ኃይል፤ ቆዳችንን ቆዳው፤ ቋንቋችንን ቋንቋው ያደረገ ሀገር- በቀል፤ ሃሳዊ- ሚሲኅ የሆነ ጽሐፍ- ፈሪሳዊ፤ ሀገሪቷን ተቆጣጥሮ ዜጎቿንም፤ ከፋፍሎና በታትኖ፤ አደህይቶና አስድዶ እንደ ገል እየቀጠቀጠ፤ እንደ ሰም እያቀለጠ አንቀጥቅጦ ይገዛል ።
ይህን ቁጭትና ጥቃት የተሰማው ሕዝብ፤ ሰማይ ምድሩ ተደፍቶበት፤ የሚያደርገው፤ ቅጥ-አምባሩ ጠፍቶበታል። ለሙከራው ያቀረበውን አማራጭ ሁሉ ጨርሷል የትግል አቅጣጫውን እስከ ማጣት ደርሷል። በሠላማዊ መንገድ፤ በህጋዊ ርምጃ የሚባሉትን ሁሉ ሞክሮ፤ ይኸው ላለፉት 24 አመታት ፍላጎቱንና ምኞቱን የሚያንፀባርቅለት ለውጥ ሊያይ አልቻልም። ተቃዋሚ ሃይሎች ነን የሚሉትንም "ተበብራችሁ ኅብረት ፍጠሩና ከዘረኞች አገዛዝ ነፃ አውጡኝ " ብሎ ቢጮኽም ስሚ አላገኘም ።
እነርሱ ደግም፤ እንኳን ሕዝብ ነፃ ሊያወጡ ቀርቶ፤ የራሳቸውንም ኅልውና ቢሆን ማስከበር አልቻሉም። አንዳንዶቹማ በመክሰም ላይ ናቸው። " የቸገረው እርጉዝ ያገባል " እንደሚባለው፤ በራስ ትግል መተማመን አቅቶት፤ በባዕዳን አማላጅነት የወያኔን በራፍ ማንኳኳትን እንደ ምርጫ መወሰዱንም ታዝበናል ። ወያኔ ደግሞ ፤ በሩን ከፍቶ ሊያስገባው ይቅርና ፤ አጮልቆ ሊያይበት የሚያስችለውን ትንሽ ቀዳዳ እንኳን ገርገብ አድርጎ አልሰጠውም። " ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ" ብሎ ቀርቷል ወያኔ ! ይባስ ብሎ፤ ለወሬ ነጋሪ ሊሆን የሚችል አንድ ተላላኪም ቢሆን አልተወለትም ። የንቀቱ ንቀት፤ መቶ- በመቶ ( 100 % ) ምርጫውን አቸንፊአለሁ ብሎ፤ የቃሪያ ጥፊውን ሰንዝሮ ሁሉንም አንገቱን አስደፍቶታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በረዥም ዘመን ታሪኩ፤ እንደ ወያኔ የናቀው ቡድንም ሆነ ገዥ አጋጥሞት አያውቅም ። " ሀገር ሲያረጅ፤ ጃርት እንደሚያበቅል " ባንስተውም፤ " የተናቀ ሕዝብ በአህያ መወረሩን " ግን እስካሁን ማመን አቅቶናል ። የሆነው ግን ያው ነበር። የአናብስት ሀገር የነበረቸው ኢትዮጵያ፤ ማን እንደወረራት፤ ሕዝቡ፤ እያንገፈገፈው ቢሆን ለማየት ተገድዷል ። ባጭሩ፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ ፤ እንደ አሁኑ ዓይነት የራሱን ሀገር የሚያጠፋ ሥርዓተ አጋዛዝ አጋጥሟት አያውቅም ብሎ ማለፉ ይበቃል ።
ሀገሪቱን ከገባችበት አዘቅት የማውጣት ኃላፊነትና ግዴታ፤ የዚህ ትውልድ ብቻ መሆኑን ተረድቶ አዲስ የታሪክ ውጤት ካላስመዘገበ፤ ሀገሩን አጥፍቶ እርሱም ጠፍቶ እንደሚቀር ማወቅ አለበት። ሀገሪቱን አጥፍቷል ሲባል፤ የጥፋቷ ቀጥተኛ ተካፋይ ነበር ለማለት ሳይሆን፤ እየጠፋች መሆኗን ተረድቶ፤ እንዳትጠፋ አንዳችም ጥረት ባለማድረጉ፤ ከተጠያቂነት አይድንም ለማለት ነው። ለነገሩማ፤ ቀስ በቀስ ሳያውቅውና ሳይገነዘበው በሄደት እየጠፋ መሆኑን፤ ሕዝቡ አላወቀውም ማለት አይቻልም። ሕዝቡ የሀገሪቱን በሂደት እየጠፋች መሆኗን ቢገነዘብም፤ ኃይልና ጉልበት አግኝቶ ሀገሩን ከጥፋት ለማዳን አልተቻለውም ። እርሱ እራሱ ካላዳናት በቀር፤ ማንም ሌላ ሊያድናት የሚችል የለም ። ፈፅሞ ዛሬ መሪና-ተመሪ፤ አቅጣጫ ሰጭና ተቀባይ ፤ ተገናኝተው የትግል አዝማች/ መሪ ኃይል ሊያፈሩ አልቻሉም ። አዝማች ከሌለ ደግሞ ዘማች አይገኝም ። አዝማች ለመሆን ደግሞ፤ የዘማቹን አመኔታና አክብሮት ማትረፍ ብቻ ሳይሆን፤ ከጥርጣሬ ነፃ የወጣና ከብክለትም የፀዳ የሞራል ልዕልና ይዞ መገኘት ያፈልጋል ። ይህ ሁኔታ ባለመከሰቱ ፤ ተቃዋሚ ኃይሎች ፤ ተዋውቀው፤ ተስማምተው ፤ተማምነው፤ ህብረት ሊፈጥሩ አንዳልቻሉ ተነግሮ ተነግሮ ሰሚ ያጣ ጉዳይ ሆኖ ቀርቷል።
የጅብ መንጋ እርስ-በእርሱ ስለማይተማመን፤ ፊትና ኋላ ሆኖ ሊሄድ አይችልም። አውራ አውጥቶ መሪና ተከታይ ሆኖ መሄድ ተፈጥሮው አይፈቅደለትም። በፊት ለፊት የሚሄደው ጅብ፤ በኋላው ያለውን ጅብ ስለሚጠራጠረው፤ አምኖት እንዲከተለው አይወድም። ምክንያቱም፤ በኋላ የሚከተለው፤ መቀመጫውን ይቦጭቀኛል ብሎ ስለሚፈራ ነው። ይህ ለጅብ የተሰጠው ምሳሌ፤ እስካሁን ድረስ፤ ኅበረት እንፍጠር ብለው ሲንገላቱ ለነበሩት ተቃዋሚ ክፍሎች ቢሰጥ፤ ከዕውነት የራቀ ነው ብሎ ለመከራከር ድፍረት ያለው ሊገኝ የሚችል አይገኝም ።
ኅብረት በሚፈጠረበት ወቅት፤ ሙሉ በሙሉ ተማምኖ መገኘት ይገባል፤ የሚለው ምኞት፤ ምናልባት ቀቢፀ - ተስፋ ነው ለማለት ቢቻልም፤ ኅብረቱን ፈጥሮ፤ ቀስ- በቅስ- በሂደትና በጋራ ተግባር፤ እየተዋወቁና እየተስማሙ ሲኬድ፤ የመተማመኑ ጉዳይ እየመጣና እያደገ ይሄዳል ብለው የሚያምኑ አያሌ የፖለቲካ ተዛቢዎች አሉ። ከዚህም በቀር፤ ሰው ሰውን አምኖት፤ አብሮ መኖር ካልቻለ፤ ታዲያ ከማን ጋር አብሮ መኖር ይቻለዋል? በማነኛውም ሀገር የሚኖሩ ህዝቦች፤ የአብሮነት ህይወት በጋራ ሊመሩ የሚችሉት፤ በጋሪዮሽ በሚመሰርቱት ሀገራዊ ተቋም ( Institutions ) ሲተዳደሩ እንደሆነ፤ በርካታ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል። በጥንታዊቷ ሀገራችንም ቢሆን፤ ሕዝቡን አስተብብረው በጋራ ሀገሩ በአንድ ላይ እንዲቆይ ያስቻሉት ባኅላዊና ሃይማኖታዊ ተቋማት ነበሩ። እነኝህ ተቋማት ዛሬ እየከሰሙ በመሄድ ላይ ናቸው። በአንፃሩ ደግሞ፤ የአብሮነት ዕድልን ሁሉ የሚያጠፉ ተቋማት እየተስፋፉ በመሄድ ላይ ይገኛሉ።
" የአሣ ግማቱ ከአናቱ " እንደሚባለው፤ በሀገራችን ላይ ለወደቀው መሰረታዊ ችግር፤ ዋናው በሽታ ወያኔ " ሕገ መንግሥት " ብሎ የተከለው ከፋፋይ ሥርዓት ለመሆኑ የሚያከራክር አይደለም ። በዚህ መርዘኛ ከፋፋይ ሥርዓት ላይ የተመሰረቱት ተቋማት ሁሉ አንጀት- ጉበታቸው ጤናማ ስላይደለ፤ የሀገራችንን ህይውት በክለውታል። የሚከተሉት ለዓብነት ይጠቃሳሉ።
1. ዘረኝነትን መሠረት ያደረገው የወያኔ ሥርዓተ- ትምህርት ( Curriculum ) በዚህም ላይ ተመርኩዞ የተቀረፁት መማሪያ መጻሕፍት( Text Books )። ይህ ደግሞ ተማሪዎቹ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ስሜትን እንዲክዱ አድርጓቸዋል ።
2. ወያኔ ያውቀረው ጦር ሠራዊት፤ የሀገሪቱ መከላካያ ሠራዊት መሆኑ ቀርቶ በአንድ ብሄር አባላት የተማከለ በመሆኑ፤ የኢትዮጵያንና የሕዝቧንም ጥቅም የማስጠበቅ ግዴታ አለመኖሩ ። የጦሩም የውጊያ ዕምነት (Doctrine) ከብሄረተኝነት ስሜት ያልዘለለ መሆኑ ነው።
3. የኢኮኖሚ ተቋማቱ፤ የገንዘብና ፊናንስ አስተዳደሩና አሰራሩ፤ ከጎጥና ከሸንተረር በላይ የማያስብ መሆኑ፤
4. ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን በሁለት መከፈሏና፤ የእስልምና ሃይማኖት ተቋም ችግር ላይ
መውደቁ፤
5. ከላይ ከአንድ እስከ አራት የተጠቀሱት ዋና ዋና የሀገር አንድነት ምሶሶዎች፤ ማለትም፦ የትምህርት፤ የመከላካያ፤ የኢኮኖሚና የሃይማኖት ተቋማት ሁሉ፤ በዘረኛ ሥርዓት ቁጥጥር ስር መውደቃቸው፤ የሀገሪቱን መጥፋት አደጋ አመልካቾች ናቸው።
የዚህ ሁሉ ጠንቅ መንስዔው፤ የወያኔው "ሕገ መንግሥት" ተብየው ነው። ይሀ የሀገር ጠንቅ፤ መውገድ አለብት ብለን የምንታገለውም በነዚህ ዓይነተኛ ምክንያቶች ነው። ተፈራራቂ መንግሥታዊ ሥርዓቶች ሁሉ ያልፋሉ ይከስማሉ። የሥርዓቶቻቸው ቁንጮዎችና አራማጆቹም ይጠፋሉ። በእኛው ዕድሜ ያየናቸውም እንኳ፤ በሙሉ ጠፍተዋል ። ይህ የዛሬው መርዘኛ አገዛዝም፤ ከነ መርዙ እንደሚጠፋ ቅንጣት ያህል ብዥታ ሊኖር አይችልም። ይህን ፀረ ሀገር፤ ፀረ ሕዝብ ብሄረተኛ ቡድን ለማስወግድ ግን፤ ኢትዮጵያዊ የሆኑና ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ የሚዋደቁ ድርጅቶች የተባበረ ኃይል ወሳኝ ነው ብለን እናምናለን ። ዘወትር የተባበረ ኃይል አስፈላጊነትና ወሳኝነት፤ ያለመታከት ማንሳት የማናቋርጠው፤ እንዲያው ለግብር- ይውጣ ወይም ደግሞ፤ ይህንን ብለን ነበር ለማለት ሳይሆን፤ በጉዳዩ ስለምናምንበት ብቻ ነው። ይህንን ለማለት የሚያስችል በቂና አንገብጋቢ ምክንያቶች አሉን። ዋና ዋናዎቹን እንጥቅሳለን።
1. ጥልቅና ክባድ ፤ ውስብስብና በርካታ ችግር ያለባትን ሀገር መፍትሄ ለመምጣት የሁሉም ትብብር አስፈላጊና ወሳኝ በመሆኑ፤
2. በመፍተሄው ፈላጊ፤ ዛሬ በትግሉ ሂደት ሁሉም ተሳታፊ ከሆነ ፤ ከወያኔ ውድቀት በኋላ ለሚከፈተው የዴሞክራሲ ምዕራፍ ሁሉም የሂደቱ ተጓዥ መሆን ስለሚችል፤ በሽግግሩም ወቅት ብቻ ሳይሆን፤ በቋሚው የሀገራችን ሥርዓተ-መንግሥት ምስረታም ጭምር ቢሆን አስተማማኝ ሁኔታዎችን ሊያረጋግጥ ይችላል ብለን ስለምናምን ነው።
3. የዞረ ድምር ፈላጊዎችና የታሪክ ቁርሾ አውጠንጣኞች፤ ሀገራችን ሠላምና መረጋጋትን አግኝታ ወደ ዕድገቷና ልማቷ እንዳታተኩር ስለሚፈልጉ፤ ለነዚህ ባላንጣዎች ዕድል ላለመስጠት ይጠቅማል ብለን ስለምንገምት ነው።
4. ዞሮ ዞሮ፤ ሀገር የማስተዳደር ኃላፊነት፤ የፖለቲካ ሥልጣን ጉዳይ ስለሚሆን፤ በዴሞክራሲ ሂደቱ ሁሉም ሙሉ ተሳታፊ ስለሚሆን የበይ ተመለካች ሆኖ የመገኝት እድል አይኖርም ብለን እናምናለን ።
5. ከዚህም በላይ፤ እንደ ኢትዮጵያ የብዙሃን ብሄረስብ መኖሪያ ለሆነች ሀገር፤ ሁሉም ድርጅቶችና የኅብረተስብ ክፍሎችን የሚያሳትፍ ሂደት ቋሚና ዘላቂ ሠላምን ያስገኛል ብለን እናምናለን።
ይህ ኅብረት ፈጥሮ በጋራ የመታገል ዐቢይ ጉዳይ፤ ለነገ- ተነገወዲያ የሚያስተላልፉት ተግባር አይደለም። ወይንም ደግሞ፤ አጋጣሚን እየፈለጉ የሚያነሱት- የሚጥሉት የትግል አጃንዳ ሊሆን የሚገባው አይደለም። ወራትን እየጠበቁ አፍለኛ አድርጎ
በማቅረብ፤ ከዓመት አንድ ቀን በሚመጣ የስፖርትና የሃይማኖት በዓላትን በመጠቀም፤ ስብሰባ የሚቀመጡበት ጉዳይ ሊሆም አይገባም። የሀገራችንን ችግር ለአንዴና ለማጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ካስፈለገ ችግሩ አስካልተወገደ ደርስ እንቅልፍ ሊኖር አየገባም ። ገና ለገና፤
" ለልደት ለጥምቀት ያልዘፈንች ቆንጆ ፤
እንጭት ካብ ስደዷት ለአህያ መናጆ ። "
የተባለውን ትችት ለማስወግድ ብቻ ተብሎ፤ የሚደረግ ሙከራ፡ እስካሁን የትም እንዳላደረሰን ሁላችንም እናውቀዋለን። የኢትዮጵያን ችግር በጥልቀት የተረዱ ሀገር -ወዳድ ሊሂቃንና የኅብረተስብ ክፍሎች እንዳሉ በሚገባ እንገነዘባለን። የማይናቅ ጥረትም እንደሚያደርጉ በቅርብ እንከተተላለን ። እናደንቃቸዋለን። እንተባበራቸውማለን !
አምባገነን አገዛዞች አላፊ ጠፊ መሆናቸውን እናውቃለን። እንደ ጎርፍ ደራሽ ቢሆኑም፤ እንደ ውሃ ፈሳሽ ሆነው ደርቀው እንደሚቀሩም እንገነዝባለን ። ሀገራችን ኢትዮጵያና ዜጎቿ ግን የማይነቃነቁ አለቶች ናቸው ። እንደ እማይበገረው የጅብላርታ
አለት! ኢትዮጵያሀገራችንለዘለዓለምትኖራለች !
4

No comments:

Post a Comment