Sunday, July 19, 2015

ወያኔን፣ መንግሥት ነው ማለት ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው !

ዴሞክራሲያ ቅፅ 40 . 9
ሰኔ 2007 .

ወያኔን፣ መንግሥት ነው ማለት
ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው !
ኢትዮጵያ ሀገራችን እንደማንኛውም ሀገር ብዙ ነገሮች ወደፊት እየገሰገሱ ባሉበት የ21ኛው ክ/ዘመን ውስጥ ትገኛለች። አዎ ከምንቆጥርበት የጊዜ ስሌትና የለውጡና የእድገቱ ተጠቃሚ ከሆኑ የሌሎች አገር ዜጎች ከሚያስቡት ውጭ ማሰብ ስለማንችል ለኛም ዘመኑ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ነው። ውስጡ ያረጀ ቤት ነገ እንደሚፈርስ እየታወቀ ላዩን በቀለም እንደሚያሳምሩት ሁሉ በሕዝባችን ላይ በገዥነት የተሰየሙባት ፤ ለዓይን የሚስብ የሃያ አንደኛው ክ/ዘመን ቀለም የተቀቡ "መንግሥት" ተብየዎች አስተሳሰብና ተግባር ግን ቀደም ብለው ከነበሩት መሳፍንትና ኋላ ቀር አምባገነኖች ጋር የሚመሳሰል ነው ። አምባገነናዊ መሳፍንቶች ናቸው እንበል? ይህንን ደግሞ እንዲሁ ለማለት ብቻ የሚቀርብ ሳይሆን ቀደም ባሉት አገዛዝም ሆነ በተለይም ባለፉት 24 ዓመታት በግልጽ ወገናችን በዐይኑ በብረቱ ያየው፣ በደም ባጥንቱ የኖረው ጉዳይ ነው።
ታዲያ የሚያሳዝነው፣ አሁን ያለው የወያኔ አገዛዝ በተወሰነ ደረጃ የመሳፍንት ዘመኑን አንድምታን
የሚያንጸባርቅ በአብዛኛው ግን የሰሜን ኮሪያው "መንግስት" ተብየው ትክክለኛ ግልባጭ ሁኖ ሳለ አንዳንድ ክፍሎች የዴሞክራሲያዊነት ካባ አልብሰው እንደመንግሥትም ቆጥረው ሲያሽሞነሙኑት ማየታችን ነው። ከልብ ቀረብ ብሎ ወያኔን ላየው ግን ባህሪው የመንግሥትነት ባህርይ የሚበዛበት፤ ያንድ ሕገ ወጥ ወንጀለኛ ቡድን ባህርይ ነው ። ይህንን ወረድ ብለን እናብራራለን።
የወያኔ ባለሥልጣናት ከ21ኛው ክ/ዘመን (ዘመናዊ) መንግሥታት ተርታ ራሳችንን አስቀምጠናል ብለው የሚፎክሩበት ልክ እንደቤቱ ቀለም የበሰበሰውን ውስጣዊ አካል ለማቆንጀት የሚያገለግሉ ሁኔታዎች በሀገራችን ተከስተዋል። "እያደግን ነው" የሚለውን ዘፈን ለመዝፈን የሚያገለግሉ በመስተዋት ያሸበረቁ ሕንፃዎች፤ የመጨረሻ ሞዴል መኪናዎች፤ በከተሞች ውስጥም ሆኑ ክፍለ ሀገራትን የሚያገናኙ ዘመናዊ የመኪና መንገዶች ፤ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ፤ በምዕራቡ ዓለም የተሰሩ የልብስና የጫማ ሞዴሎች፤ የቤት ዕቃዎች - ከውጭ የሚገቡ ቤት ማሸብረቂያዎች፤ ኮምፕዩተር፤ ኢንተርኔት፤ ሞባይል፤ ስልክ፤ አብረው የሚሄዱት የማህበራዊ ሚዲያዎች (ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ እስካይፕ፣ ...ወዘተ)፣ የመሳሰሉት በሀገራችን ይታያሉ። ትላልቅ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች፣ ውሃን በቧንቧ አገልግሎት የማቅረብ፣ ወዘተ፣ ...ወዘተ እያሉ ሌሎችንም መዘርዘር ይቻላል። ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉ ምን ያህል የሀገሪቱን የአብዛኛውን ሕዝብ ኑሮ እያንጸባረቁ ነው? ለሚለው ጥያቄ ያለው መልስ በርካታው ሕዝባችን ዛሬም በገሌ ብሎ በድህነት ይኖራል የሚል ነው። በከተማም ያለው ምንም ሳይበላ የሚያድርበት ሻል ካለም ጉርሻ የሚገዛበት፣ ቀደም ብሎ በመካከለኛ ኑሮ ላይ የነበረው ወደታች የወረደበት ሁኔታ ላይ መሆናችን ግልጽ ነው።
ሕገ-መንግሥት ተብዬ ተቀርጿል፤ ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ቻርተር ተለቅመው የተካተቱም ነገሮች አሉበት፤ ፍርድ ቤት አለ፤ በደል ሰሚና የሰብዓዊ መብት ድርጅት፣ ተብየዎችም አሉ። እነዚህ በሀገራችን አሉ የሚባሉት ዘመናዊውን ዴሞክራሲያዊ የሆነ የመንግሥት ሥርዓትን ገላጭ የሆኑ ሰነዶች፣ ተቋማት፣ ወዘተ... በዴሞክራሲያዊ ሀገራት የሚሰጡትን ትርጉምና አገልግሎት በሀገራችን እየሰጡ አለመሆናቸው ግልጽ ነው። ምዕራቡ ዓለም በብዙ መቶ ዓመታት ነው ለዴሞክራሲ የታደለው፣ በእኛም አገር ዴሞክራሲ በሂደት ላይ ስለሆነ እነሱ ላይ ለመድረስ ረዥም ጊዜ ያስፈልጋል" የሚለውን የወያኔን የአጭበርባሪ ካሴት ደጋግመን ካልሰማንና በዚህም ራሳችንን ካላሞኘን በሀገራችን ያለው ሐቅ የአፈናና የወንጀል እንጅ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አይደለም። እዚህ ላይ ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምንነት ባጭሩም ቢሆን መጥቀሱ ተጨማሪ ግንዛቤ ይሰጣል። በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ዜጎችን በሕግና በሥርዓት አብረው የሚኖሩበት ሁኔታን ለመፍጠር የግድ በበላይነት የሚያስተዳድር መንግስታዊ ተቋምና መዋቅር መመሥረት ያስፈልጋል። በአንድ አገር ውስጥ ያለው መንግሥት ከሁሉም በላይ የሆነ ሕግና ደንብ የሚያወጣ፤ ያወጣውን ሕግና ደንብ በኃይልና በሥርዓት ሥራ ላይ የሚያውል ተቋም ነው። ዴሞክራሲያዊ መንግሥታት የሚባሉት የሚቋቋሙት በሕዝብ ፍቃድና ስምምነት ላይ በመመስረት ሲሆን ተቋማቱና መዋቅሮቹ በአንድ ግለሰብ ወይም ቡድን ቁጥጥር ሥር የሆኑ ሳይሆን ነጻና ገለልተኛ ሁሉንም በእኩልነት የሚያገለግሉ ናቸው። ነጻነታቸውንና ገለልተኛነታቸውን ዘወትር ለመቆጣጠር ነጻ ሚዲያና ሕዝባዊ ድርጅቶች እንደመሣሪያ
ያገለግላሉ። የአገሪቷ የበላይ ሕግ- ሕገ መንግስት - በሕዝቡ ውሳኔ ጸድቆ ሥራ ላይ ይውላል፤ በየጊዜው ህጎችንና ደንቦችን የሚቀርጹ ዋና ዋና ሀገራዊ ውሳኔዎችን በሕዝብ ስም የሚወስኑ የሕዝብ ተወካዮች በነጻና በርቱአዊ ምርጫ በሕዝብ ይመረጣሉ። የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ የሚያገለግል፤ ፍትሀዊ በሆነ የአሠራር ደንብን ተከትሎ የሚዳኝ የፍርድ ተቋም፤ ሕግን የሚያስከብር የጸጥታና የፖሊስ ተቋም ነጻና ገለልተኛ በሆነ መንገድ ይቋቋማሉ። የአገሪቷን የአስተዳደር አካል ለተወሰነ ጊዜ ተረክቦ በሕዝብ ስም የሚያስተዳድር በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ይመረጣል። በየአገሩ ያሉት የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሥርዓት መዋቅሮችና የአስተዳደር ስልቶች የተለያዩ ቢሆኑም ሁሉም አንድ ዓይነት ጠባይና መልክ አላቸው። ይኸውም መንግሥታዊ ተቋማት ገለልተኛና ነጻ በማንም ግለሰብ ወይም ቡድን ቁጥጥር ስር ያልሆኑበት፤ ሕግ የበላይ የሆነበት፤ የሕዝብ መብቶችና ነጻነቶች በማንም ቡድን ወይም ግለሰብ የማይደፈሩና የማይገረሰሱበት ሥርዓትን የሚያስተናግዱ ናቸው። በአገራችን ግን ይህ የለም። በወታደራዊ ኃይል ሥልጣን የያዘው ወያኔ ሁሉንም መዋቅርና ተቋም እንደግል ሀብት በቁጥጥሩ ስር አድርጎ እንዳሻው እየፈነጨባቸውና እያሽከረከራቸው ይገኛል።
ኢሕአፓ ቀደም ሲል ጀምሮ ከዚህ ወንጀለኛና ዘረኛ ቡድን የሚጠበቅ ሀገራዊም ሆነ ዴሞክራሲያዊ ነገር የለም ብሎ ነበር። በመሠረቱ አንድ ጠባብና ሀገራዊ ወገንተኝነት የሌለው፤ ከሕዝቡና ከሀገሩ ይልቅ ለውጭ ሀገሮች በተለይም ለኢትዮጵያ ጠላቶች ህይወቱን ለመስጠት ቃል የሚገባ፤ የሀገሩን መሬት በፊርማ ውሰዱ እያለ የሚሞግት፤ ከድሃዋ ሀገርና ሕዝብ በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብትን እየዘረፈ በማሸሽ በውጭ የሚያከማች፤ አጥፊ ቡድን እንዴት ሁኖ ነው ያንድ ሀገር መንግሥት ነው የሚባለው? - እንዲያው ዘመናዊነቱ ይቅርና?! ወያኔን ባጭሩ ማለት የሚቻለው፣ ያንድ ጠባብ ቡድንን ፕሮግራም ወይም መርሓ ግብር በዘመናዊ ሰነዶችና ተቋማት ቀለም ቀብቶ ለምዕራቡ ዓለም ፍጆታ ያቀረበ አምባገነናዊ ስብስብ ነው። ኢሕአፓ ይህን ያጋለጠው ገና ከጠዋቱ ከጅምሩ ሲሆን ዛሬ ደግሞ የዚህ ጠባብ ቡድን አባል ነበርን ከሚሉት ጀምሮ ወዳጁና አድናቂው ነን እስከሚሉት የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ምሁራን ድረስ ባደባባይ የሚመሰክሩት ሁኗል።
ዛሬ የወያኔ መንግሥት ተብየው ቀደም ብሎ እንደተባለው፣ በሩ ሆነ መስኮቱ አንድ ሐሙስ የቀረው፣ ጣሪያው አንድ ክረምት የማያሻግር፣ ግርግዳው አንድ የክረምት ወጀብ የሚደረምሰው ባማረ ቀለም ተጀቡኖ ቆሞ እንዳለ አስመሳይ ቤት ዓይነት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ቤት ግርግዳ፣ በር፣ መስኮት፣ጣሪያ ወዘተ... ለስሙ ተገጥመውለታል እንጂ ቤት ሊባል የሚችል አይደለም። በሀገራችን መንግሥት ነኝ ባዩ ወያኔም መንግስት የሚለውን ስያሜ ወዳጆቹ ይሸልሙት እንጅ መንግስት ሊያሰኝ የሚችል አንዳችም ባህርይ የለውም።
ወያኔ የወንጀለኞች ቡድን የተባለው አለምክንያት አይደልም። የወንጀለኛ ቡድን ሀገር የለውም። በዚያ በቡድኑ ዋና ቁንጮ ክበብ ውስጥ ላሉትና በዙሪያው ለተኮለኮሉት ጥበቃን እየሰጠ ሕጋዊ ያልሆነን የገንዘብ ዘረፋን እንዲቀጥል የሚያደርግ እንጅ ለሀገርና ለወገን የቆመ አይደለም። ወያኔ እንደ ወንጀለኛ ቡድን አንድ አለቃ ይፈልጋል፤ ነበረውም። አሁንም ልክ ማፊያ እንደሚባለው የወንጀለኞች ቡድን አንዱ ቁንጮ በሆነ ምክንያት ሲሞት ወይም በሌላ ሲገደል የሱን ፈለግ ይዘው በሚቀጥሉና የለም የራሳችንን ቁንጮ ፈልገን ቡድን መሥርተን እንከብራለን በሚሉ መካከል ሽኩቻው ይጦፋል። በወያኔም ውስጥ ቁንጮው ከሞተ በኋላ ምን እየሆነ እንዳለ እየታዘብን ነው።
የወያኔ ወንጀለኛ ቡድን ራሱን ለማስመሰል ከሚቀባቸው ቀለሞች መካከል አንደኛው ምርጫ የሚባለው ቀለም ነው። በትክክለኛው የዓለም አቀፍ መስፈርት መሠረት ትክክለኛና ፍትሃዊ ምርጫን ስናወራ ቅድመ ሁኔታዎቹ በተሟሉበት ሁኔታ የሚካሄድ ምርጫን ለማለት ነው። ከሁሉ በፊት ሕዝቡ በሁሉም መስክ መብቱ ያለገደብ ተከብሮ በነጻ የሚኖርበት ሀገር ያስፈልገዋል። ያሰበውን የሚተነፍስበት፣ የሚጽፍበት፣ በነጻ የሚደራጅበት፣ የሚሰበሰብበት፣ የሚንቀሳቀስበት፣ እንደልቡ በሀገሩ ተዘዋውሮ የሚሠራበት፣ ...ወዘተ ነጻነት ያስፈልገዋል። ሀገሩም በሕግ ፊት ሁሉም ዜጋ ዕኩል ነው የሚለው በተግባር የሚተረጎምባት የፍትህ ሥርዓት ያላት መሆኑን ማመን፣ ማየት አለበት። ከሕግ ውጭ መታሰርን፣ መንገላታትን፣ መገደልን የማያይባት ሀገር ሊኖረውም የግድ ይላል። አስመራጭ ኮሚቴ ሆነ ኮሚሽን የሚባለውም ከሕዝቡ የኔም ነው የሚል ዕምነት የተቸረው መሆኑ የግድ ነው። ፖሊስና ፍርድ ቤቱ በዜጎች መካከል ተገቢው የኑሮ፣ የሕግ ሥርዓት በትክክል እንዲከበር ያለ አድልዎ ለማገልገል ለሕዝብ የቆሙ መሆናቸውን ማየት ይኖርበታል። ወታደሩና የጸጥታው ክፍል የሀገርን፤ የሕዝብን ደህንነት በተለይም ከውጭ ጠላት የሚሰነዘረውን ጥቃት ለመከላከል የተቋቋሙ መሆናቸውን በተግባር ማስመስከር አለባቸው።
ታዲያ የእስከዛሬውየወያኔውየምርጫቲያትር "እነዚህከላይየሠፈሩትእውንበሆኑበት፤ሕዝብምእውን መሆናቸውን አምኖ በተቀበለበት፤ የሕግ የበላይነት በተግባር በሰፈነበት፤ መብቶች በተከበሩበት ሀገር ውስጥ ነው ወይ የተካሄደው?" ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው። በ1997 .ም የውጭ ሀገራት ወዳጆቹ ግፊትና እንዲሁም የማፊያው ቡድን ቁንጮ ሕዝቡን በኪስ አደርገዋለሁ ከሚል ከንቱ ምኞትና እምነት ተነስቶ ሁኔታውን በመጠኑም ቢሆን ከፈት በማድረግ እንዲካሄድ ያደረገው ምርጫ ሕዝቡ መብቱን ተጠቅሞ ማፊያውን እንዳደባየው አይተናል። ወያኔ ወንጀለኛ ዘረኛ ቡድን ወንበዴ ነውና የገንዘብ ምንጩ ሲደርቅ፤ በሀገሪቱ ባሉት ተቋማት የሚዘርፍበት ሁኔታ የሚዘጋበትና የሚያከትም መስሎ ስለታየው ወዲያው በወንበዴው አለቃ ትዕዛዝ በህዝብ ላይ የደረሰው ግፍ በግልጽ በማይፋቅ ቀለም ተጽፎ ይገኛል። ስንጠቀልለው በወንጀለኛው ወያኔ ሥር ምርጫ የሚባል ነገር ማንሳትስ ለምን ያስፈልጋል? የሚል ጥያቄ ቢነሳ አግባብነት ያለው ነው። ወያኔ ብዙ ዘራፊና ወንጀለኛ ድርጅቶች እንደሚያረጉት፣ ዘረፋውን የሚያጠናክርበት፣ የሚጠብቅበት ልዩ ልዩ ሽፋን የሰጣቸው ህጋዊ መሰል ተቋማት አሉት። ወያኔ ባንክ አለው፤ የትራንስፖርት (የሕዝብ ማመላለሻ) ተቋማት፣ የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭ፣ የሲምንቶ፣ የቢራ፣ የልዩ ልዩ ኢንጂኔሪንግ ተግባራትን የሚኮናተሩ፣ የሕክምና አገልግሎት ሰጭ፣ ...ወዘተ ተቋማት አሉት። ህንጻዎችን ገንብቶ ያከራያል። የሀገሪቱ መሬት እንዳለ በጁ ነው። እንደፈለገው ለፈለገው ይቸበችባል። እነዚህን መሰል ነገሮች ጨቋኞች በገነኑባቸው ቦታዎች ሁሉ ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት በሚልም ሲሰራባቸው የቆየ ቴክኒክ፣ ሽፋን ነው። በትክክል በዚህም መልክ ባይሆን ልዩ ልዩ ሕጋዊ ሽፋን እንዲያገኙ ተደርገው በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሥር፣ ወይም በባለኢንዱስትሪዎች ስም፤ ልዩ ልዩ ሥራ ተቋራጮች ስም (ኮንትራክተርስ ስም)፣ ባለ ትላልቅ ዘመናዊ አሳ አጥማጆች፤ ገበሬዎችና ነጋዴዎች ስም ... ለምሳሌ በሲሲሊ ለረጅም ዓመታት ለሕዝቡ የቆሙና አገልግሎት ሰጭ መስለው መቆየታቸውን እንገነዘባለን። ገንዘብ አበዳሪና ማኅበረሰቡን ደግፎ ያዥ፣ በችግሩ ደራሽ መስለውም ሲታዩ ኑረዋል። የሲሲሊው ማፊያ፣ አሁን እስኪዳከምም ድረስ እኔ ከሌለሁ ሁልሽም
ድህነት ውስጥ ትወድቂያለሽ፤ ሰላምሽም አይጠበቅም፤ ሁከት ይሰፍናልእያለ ሕዝቡን በመያዣነት ጠፍሮት መክረሙን ማስተዋል ያስፈልጋል። ይህ የጥፋትና የወንጀለኛ ድርጅት ከዋና ዓላማው ማለትም ገንዘቡን ከማሳደግና ከማበራከት ተጻረው የሚቆሙትን ሁሉ ያጠፋቸዋል። እነዚህ ተጻራሪዎቹ በገንዘብ የሚገዙና አፋቸውን ዘግተው የሚቀመጡ ካልሆነ መጨረሻቸው ቅርብ ነው። ይህ በአገዛዙ ውስጥ ቦታ ያለው ሆነ ተራ ግለሰብ እንዲሁም ጋዜጠኛ ሆነ ነጋዴ ለወንጀለኛው ቡድን ካልታዘዘ፤ ለዓላማው እንቅፋት ነው ብሎ ካመነ ሊያጠፋው አያቅማማም።
ወያኔም ጠበብ ሲል ለትግራይ ሕዝብ ሰፋ ሲል ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስተላልፈው መልእክትና በተግባር የሚያረገውም ይህንኑ ነው። እዚህ ላይ እንደገና ማስመር የሚያስፈልገው ወያኔ ሀገር የሌለው፣ ገንዘብ ማካበቱ ነው ዓላማዬ ብሎ የያዘ መሆኑን ነው። ገንዘብን በሆነው ዓይነት መንገድ መዝረፍ መሰብሰብ ዋና የሚንቀሳቀስበት ሞተሩ ነው። ልክ እንደለየለት ወንጀለኛ ለዚህ እንቅፋት የሚሆኑትን ሁሉ የራሱ አባላት ይሁኑ አይሁኑ እያጠፋቸው፣ እያሰቃያቸው፣ እያሰደዳቸው፣ ሰላም የሌለው ኑሮ እንዲገፉ እያረጋቸው ይገኛል። በትግራይ ስም በኤፈርት ተብየው የሚዘረፈው ገንዘብ ስንት ነው? የሀገር መከላከያ ተብየው ስም የሚዘርፈውስ? ከውጭ የዕርዳታ ገንዘብ በገፍ ይገባል የት ነው የሚደርሰው? በዓለም አቀፉ ሙስና ይጥፋ በሚል የሚታገለው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ህብረት (ዘ ግሎባል ኮኤልሽን አጌንስት ኮረፕሽን) ይፋ ሁኖ እንዳየነው፣ አንዴ 11 ሌላ ጊዜ 14 ቢሊዮን የአሜሪካን ብር ሕጋዊ መሰረት በሌለው ሁናቴ ከሀገር ወጥቷል። ወርቁ ባሌስትራ መስሎ መጫኑንም አስተውለናል። የኢትዮጵያ ቴሌኮምዩኒኬሽን እንዲደኸይ ዘራፊው ቡድን ጎን ለጎን የሚያንቀሳቅሰው በህጋዊነት ስም ተመሳሳይ አገልግሎት በሚሰጠው ድርጅቱ እንዲከብር ሲደረግ ታዝበናል። ያንዱ ኩባንያ የሲሚንቶ ምርት ከገባያ እንዲጠፋ ተደርጎ የመሶቦ ሲሚንቶን ሕዝብ አፍንጫውን ተሰንጎ በግድ እንዲገዛ የተደረገበትን፣ የሚደረግበትን የማፊያ ሥርዓት ሕዝባችን ኖሮታል እየኖረውም ነው። በትግል ላይ ሳለሁ ከኔ ካዝና አውጥቸ ለሕዝብ የመድኃኒት አገልግሎት የሰጠሁበት 11 ሚሊዮን ብር ይከፈለኝ ብሎ የሕዝብን ሀብት በጠራራ ፀሐይ ሲዘርፍም በዓይናችን በብረቱ አይተናል። ለሕዝብ ታገልኩ የሚለው ቡድን፣ "መንግሥት" ይዣለሁ ካለም በኋላ ሕዝብ ከሚገለገልበት የህክምና በጀት ይከፈለኝ ብሎ መጠየቁና መውሰዱ፣ ምን ያህል ወንበዴነቱ ባደባባይ እንደወጣ በወቅቱ ተተችቶበትም ነበር። ብቸኛ የማዳበሪያ አስመጭ ሁኖም ምን ያህል ገንዘብ ከድሀው አርሶ አደር እንደዘረፈና፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘም የነበረውን ቅሌት የምናስታውሰው ነው። ማዳበሪያውን ሻጩ የኖርዌይ ድርጅት ለመለሰ ዜናዊ የድርጅቱን ልዩ ሽልማት እንዳጠለቀለት፣ ገንዘብም እንደመደበለት ባደባባይ ተጋልጧል።
ትላልቅ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎችን ገነባሁ ለሚለው ኮንትራቱን ለጨረታ ሳያቀርብ እያስኬደ መሆኑ ሳይጠቀስ የሚታለፍም አይደለም። በጣም ከፍተኛ ገንዘብ እየወጣባቸው የሚገነቡ ተቋማት እንዴት ነው በጠረጴዛ ሥር በሚደረጉ የወንበዴዎች ስምምነቶች የሚካሄዱት ብሎ መጠየቁ አግባብነት ያለው ነው። በሀገር ውስጥ ተራ ነጋዴው ያቅሙን ሠርቶ ማለትም ነግዶና ቸርችሮ እንዳያድር ልዩ ልዩ ተፎካካሪ የወያኔ አባል ነጋዴዎች ከቀርጥ ነጻ የማድረግን ጨምሮ የተለያዩ ዕርዳታ እየተቸራቸው እንዲሰሩ አድርጓል።
በዚህም ስንቱ ነጋዴ ነው ከጨዋታው ውጭ የተደረገውና ወደ ድህነት የተገፋው? ቤቱ ይቁጠረው። ወያኔ በሀገር ያሉት የገንዘብ ማስገቢያ ድርጅቶቹ ሳይበቃው በውጭ ሀገርም ልዩ ልዩ የንግድ ተቋማትን፤ ገንዘብ አዘዋዋሪ ድርጅቶችን ከፍቶ ይሠራል።
ይህንን ሁሉ ማንሳታችን ለምንድነው? እንደገና ወደተነሳንበት እንመለስ። ስንነሳ፣ ቤት ሊባል የማይበቃ ቤት በቀለም አሸብርቆ ቤት ይባላል ወይ ብለን ነበር። ወያኔም መንግሥት ለመባል የማይበቃ በስምና በልዩ ልዩ የመንግሥትን ስም የሚያላብሱ ተቋማት፣ የሕገ-መንግሥት ቀለም ተቀባብቶ የሚንቀሳቀስ የማፊያ/ወንጀለኛ  ቡድን ነው የሚለውን በግልጽ ለማሳየት ነው። የወንበዴ ቡድን ገንዘብን ማካበት ከሆነ ዓላማው ወያኔም ከዚያ ውጭ ምን የሚያረገው አለ? የሚታዩት ህንጻዎች ሆኑ መንገዶች ወይም ትላልቅ ግንባታ ተብየዎች ከወንበዴው ቡድን ዓላማ ጋር ተያይዞ ከሚካሄዱ ነገሮች የተገኙ ውጤቶች አድርጎ መመልከቱ ተገቢ ነው። ወንበዴው ወያኔ ባንክ አለው ያበድራል፤ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክስ የሚወጡ ብድሮችን ማነው የሚያዛቸው? ኤፈርት የማንም ቁጥጥር የሌለበት የብዙ ገንዘብ አስገቢ ተቋማት ባለቤት ነው። ባለቤትነቱ የጸረ ሕዝቡ ወያኔ ነው። ከባንኮች እንደልቡ ገንዘብ ያገኛል ሕንጻ ገንብቶ፤ ወይም የግንባታ ሥራዎችን ተቋርጦ ይሠራል፣ ያከራያል፣ ይሸጣል። መከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱ ነው የሚለውን ወደጎን ትተን፤ እነማን አብዛኛውን ያዛዥነት ቦታ ይዘዋል የሚለውንም ባደባባይ የምናውቀውን በልባችን ጥፈን፤ ዛሬ ለሚካሄዱ የግንባታ ሥራዎች የኢንጂነሪንጉን ኮንትራት እየወሰደ ማን እንደሚሠራ በግልጽ እየታዘብነው ያለ ጉዳይ ነው።  ከዚህ ኮንትራት የሚገባው ገንዘብ የማነው? ይህም ብቻ ሳይሆን ወያኔ የዘራውን የሰሊጥ ሆነ ሌላም የውጭ ገንዘብ አምጭ እህል ምርቱን የሚያሰበስበው በወታደሩ ነው። ሰሊጡ ወይም ቦሎቄው ተመርቶ ወደውጭ ሲሸጥ ገቢው የማነው? ወታደርና ትጥቅን ካነሳን አይቀር የወንበዴው ቡድን ይኸው ዓላማው በምንም ዓይነት እንዳይደናቀፍበት ከመከላከያው፣ ከፖሊስ ኃይሉ (የፌደራሉን ጨምሮ) ውጭ ያሰናበታቸውን በርካታ አባላቱንና ደጋፊዎችን በሲቪል የሚኖሩ ካድሬዎችን አስታጥቆም እየተጠበቀ ነው። ለመሆኑ በጅቡቲ ሳይሆን በፖርት ሱዳን ወደ ትግራይ የሚገቡትን ሸቀጦች እንደሀገር የሚያስተናግዳቸው ጉምሩክ ሆነ ሌላ ተጠያቂ መሥሪያ ቤት አለ? - ለነገሩ የጅቡቲውንስ ቢሆን ማነው አዛዥ ናዛዡ እንዲያው ለማሳየት አነሳነው እንጂ?
ወያኔ ዛሬም የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር በሚል ስም ሀገሪቱን ይዟል፤ ሀብቱም የሚገባው ለዚሁ ድርጅት ነው - ይህ ምን ይባላል? ለኢትዮጵያ ሀገራችን ቅንጣት ያህል ደንታ የሌለውን፤ በየጊዜው የኢትዮጵያዊውን ልብ የሚያቆስል ጸረ-ኢትዮጵያ ሥራ የሚያከናውነውን ይህን የማፊያ ቡድን ኢትዮጵያዊ መንግሥት አርጎ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት ትክክል አይደለም። መንግሥት ያለ ይመስል ፍትህን፣ ነጻ ሚዲያን፣ ምርጫንበየጊዜው እያነሳን ብንወቅጥ - "ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ" ነው የሚሆነው።
በዓለም አቀፍ ተቋማት እንደመንግሥት ሆኖ መቀመጥ ወይም አለመቀመጥ ምንም ማለት አይደለም፤ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ ይኸው በመሆኑ። ነፍስ ገዳይ ወንጀለኛ ሆነ አምባገነን፣ አክራሪ ሆነ አልሆነ አንድ ወንበር ይሰጠዋል። የሚደነገጉ ሕጎች ፍትኃዊ የሕዝብን ፍላጎትና የሀገር ደህንነትን ያገናዘቡ ሆኑ አልሆኑ በነሱ ዘንድ ከቁም ነገር የሚገባ አይደለም።ኃያል የሚባሉት ሀገሮች ማን የነሱ ጫማ ላሽ ሁኖ የሚያገለግላቸው መሆኑን ማረጋገጥ እንጂ ሌላው የሕዝቡ ነገር ደንታ አይሰጣቸውም። እነሱ የሚጠሉት ከሆነ ሲያስፈልጋቸውም በቀጥታ ካልሆነ ልዩ ልዩ መንገዶችን ተጠቅመው ሊጨፈልቁት ይሞክራሉ። ለነሱ አገልጋይ ከሆነ ደግሞ ወንበዴ ይሁን፤ ዘራፊ ፤ አምባገነን ይሁን ወንጀለኛ የነሱ ጉዳይ አይደለም።
አዎ በዓለም በተለያዩ አህጉራት በተለይም በአፍሪካ አምባገነን አገዛዞች እንደአሸን ፈልተዋል። ሥልጣን ለመያዝ ወይም በሥልጣን ለመቆየት ህዝብን ሊፈጁ፣ ብዙ ጉዳትም ሊያደርሱ ይችላሉ። ነጻነትንም ይገድባሉ፣ ለሥልጣናቸው አደገኛ ስለሆነ። ለግል ስልጣናቸው ሲሉ ወንጀል ቢፈጽሙም በሀገራቸው ማንነት፣ የመጣ ነገር ላይ ሽንጣቸውን ገትረው፤ አንገታቸውን ቀና አርገው ነው የሚከራከሩት። መጓዝ እስከሚችሉት ተጉዘው የሚቻላቸውን ሁሉ አርገው የሀገራቸውን ሉዓላዊነት አያስነኩም፤ አንዲት ቅንጣት
መሬት አላግባብ እንዲነካባቸው አይሹም። ይህ መሬት የኔ አይደለምና እባካችሁ ውሰዱልኝ (ውሰዱብኝ) ብለው አይፈርሙም።
ለሥልጣን የደረሰ አንድ ኃይል የሀገሪቷ ወይም የሕዝቧ መንግሥት ሊባል የሚችለው ሕዝብ የመረጠውና ለሕዝብ ተገዢነቱ የተረጋጋጠ ሲሆን ብቻ ነው። በሕዝብ ላይ ራሱን ጭኖ፤ ሕዝብ መወገዱን እየፈለገ ሥልጣኑን በጉልበት የቀጠለ፤ ሕዝብን የፈጀና ሀገርን የበደለ ቡድን የሀገር መንግሥት ሊባል አይገባውም በጉልበት ገዢ ነውና አገዛዝ መባሉ ተገቢ ስያሜው ነው። ወያኔ በጥቂቶች የሚደገፍ፤ ብዙሃኑ የጠላው፤ ኢትዮጵያን የከዳ፤ ሕዝብን ያስለቀሰና ሀገርን የዘረፈ የወንበዴዎች ጥርቅም በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ብሎ መጥራቱ ኢትዮጵያን መስደብ ማዋረድ ከመሆን ሌላ ምንም ትርጉም የለውም። ወያኔ በየአምስት
ዓመቱ ምርጫ የሚለውን እጅ እጅ ያለ ቲያትር እዩ ቢለንም፤ መቶ በመቶ ወንበር መያዙን ቢያረዳንም ጸረ- ሕዝብ አገዛዝ ሆኖ በመቀጠሉ መንግሥት የሚል ከበሬታን ሕጋዊነት ሊሰጠው የሚችል አይደለም፤
የፋሽስቶቹ ቁንጮዎችን (መንግሥቱና መለስ-) አንቱ የሚሉም ያከበርነው ቦታውን ነው ሊሉ ቢቃጡም የዘረኛ መንጋና ሎሌዎቹ አንቱታን ሊያገኙ አይችሉም። አይገባቸውም። ወያኔ ከተራ አምባገነንነት ባሻገር ሀገርን ያህል ክቡር ቅርስ ለግንጠላ የዳረገና ጉዳት ያደረሰም በመሆኑ ኢትዮጵያዊ ሊባልም የሚገባ አይደለም። በደሉን የሚረሳ ሕዝብ የተጫነበትን ቀንበር ፈላጊ ነው የሚለው አነጋገር ትርጉም አልባ አይደለም። ኢትዮጵያን ያስለቀሰው ቡድን ዘረኛ አለቃ በአጭሩ ሲቀጭና የቋመጠላትን ሕይወት ሲያጣ በአንድ በኩል ሀገር ወዳድ ነን ባዮች ዜጎች ሊያለቅሱለትና ደረት ሊደልቁ ሲንጋጉ ማየቱ አሰቃቂ ክስተት ሆኖ
ያስቸግረናል። እሰየው በ'ወይኔ፣ ወይኔ' መለወጡ ምን ያህል አልቃሾቹ ሚዛናዊ ግምት እንዳጡ አሳይቷል። አገዛዝን መንግሥት ማለት ከባድ ግድፈት ነው።
ወያኔ የሕዝብ መንግሥት ስላልሆነና በሕዝብ ህጋዊነትን የተነፈገ በመሆኑ ውድቀቱን በሁሉም መንገድ
ማፋጠን የዜጎች ግዴታ ሆኖ ይገኛል። ሕገ-መንግሥት የሚለውን የወያኔ ሕግ አለመቀበል ሕገ ወጥ ያሰኛል ብሎ ወያኔ የሚለፍፈውን በመቀበል፣ ተቀብለናል ብለን ፈርመን እንኮልኮል የሚሉትና ይህን ሕግ ካልተቀበሉ ጋር አንሰለፍም ብለው የሚለፍፉ ራሳቸውን ተቃዋሚ ብለው የሚጠሩት ሐቁ ሲነገር ሰልፋቸው ከሕዝብና ከሀገር ጥቅምና መብት ጎን አይደለም። ወያኔን ዘረኛ ስንለው ከመሠረቱ እስካሁንም ዘረኛ በመሆኑ ነው። ወያኔን አፋኝ ፋሺስት ስንለውም የሆነውን ለመግለጽ ነው ። ወያኔን ባንዳ ከሀዲ ስንለውም በመሆኑ ነው። ያልሆነውን ሆነ አላልነውም። መንግሥት አይደለም ሲባልም በደፈናውና አለምክንያት ለመሰረዝ ለማጣጣል ሳይሆን ሐቁን ለማስረገጥ ነው። አካፋን ዶማ ማለት ራስንም ማደናገር ነው። ከዚሁ በተያያዘ ለምሳሌ ድርጅቶች ላይ የክፍፍል ሴራቸውን የሚያካሂዱና ጉዳት የሚያደርሱ አንጃ ሲባሉ ስድብ ሳይሆን ድርጊታቸውንና ይዘታቸውን ለመግለጽ ነው ።
ማንም በዓለም ላይ ያለ ሀገር ለኛ ብሎ ይህንን መንግሥት የማይባል ሀገር አጥፊና ሕዝብን በዳይ ቡድን መንግሥት አይደለም እንዲልልን አንጠብቅም። በሌላ በኩል ቡድኑ እንደ መንግሥት እንዲታይ ገንዘባቸውን እያፈሰሱ የምርጫ ቲያትር እያዳነቁ፤ አልፎ አልፎ የሰው መብትን የጣሰ መንግሥት እያሉ የቀልድ ሪፖርት በመጫር አሁንም መንግሥትነቱን ሊያስረግጡልን ሲሞክሩ አሌ ማለቱ የኛ ሀገራዊ ግዴታና ኃላፊነት ነው። ወያኔ ሀገራችንን መቀመቅ እየከተተ ያለ አደገኛ፣ ዘረኛና ወንጀለኛ ቡድን መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል። ያንንም ተቀብሎ በትብብር ለመጣል መነሳትና መንቀሳቀስ ጊዜው ነው። እንደምናስታውሰው
ቁርጠኛ ያገሪቷ ዜጎች (ዳኞች፣ አስተማሪዎች፣ ተማሪዎች፣ ቄሶች፣ ሼሆች፣ ወታደሮች፣ ፖሊሶች፣ የተደራጁ
ማኅበራት፣ ...) በአካባቢያቸው የሰፈነውን ወንጀለኛ ለማምከን ተንቀሳቅሰው ከባድ መስዋዕትነትን ከፍለዋል። ኢሕአፓም ካለ መስዋዕትነት ሥርየት የለምና ይህንን አደገኛ ሀገር አጥፊ ወሮበላ ቡድን በጋራ ታግለን እናስወግድ ይላል። ለዚህ ግን የተቻለውን ሁሉ ለማረግና የሚፈለገውን መስዋዕትነት ለመክፈል አሁንም ቃል ይገባል።
ወንጀለኛው ወያኔ በኢትዮጵያውያን ትግል ያከትማል !

No comments:

Post a Comment