Wednesday, December 30, 2015

ለኢትዮጵያ ተማሪዎችና ሁሉም ወጣቶች ሀገራዊ ጥሪ/ Finote radio


ለኢትዮጵያ ተማሪዎችና ሁሉም ወጣቶች ሀገራዊ ጥሪ
በአሁኑ ጊዜ ያለውን የሀገራችን አሳሳቢ ሁኔታ በማጤን ለወሳኝ የህብረሰብ ክፍሎች ሁሉ የትግል ጥሪን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ በቅድሚያ ለለውጥ አምጪዎችና የሰፊው ህዝብ ወገኖች ለሆናችሁት ወጣቶች የትግል ጥሪ እነሆ እናሰተላልፋለን። የኢትዮጵያ ወጣቶችን የትግል ቅርስና ታሪክ መሰረት በማድረግ።
ለኢትዮጵያ ተማሪዎችና ወጣቶች በሙሉ ፤
እናታችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በከባድ አደጋ ላይ ናት። ጠላቶቿ 25 ዓመታት ሙሉ ሊያጠፏት ሲሸረሽሯትና ሲቦረቡርዋት፤ ሕዝቧም ሲከፋፍሉና ሲያሳድዱ፤ ሲያፈናቅሉና ሲገድሉ፤ ትግራይ ወይ ሞት በሚል ቀሪዋን ክፍል ሲያፈራርሱ፤ ከጠላቶቿ ገጥመው ጥፋት ሲያደርሱ ከርመዋል። ይህን የማያውቅ ወጣት የልም ብንል ስህተት አይሆንም። ወያኔ በትኩረትና በትጋት በተለይ ወጣቱን ሊከፋፍል ተዋድቋል። ወጣቱ በሰበብ አስባቡ ከተከፋፈለና በአልባሌ ጠባዮች ተይዞ ወደ ትግል የሚያዞረው ህሊናው ከበደነ ወያኔ ከአደጋ ነጻ እሆናለሁ ብሎ ትውልድን --ራሱ እንደሚለው--ለማምከን ያልፈነቀለው ድንጋይ አልንበረም፤ አሁንም የለም። በተለይ ብሔርተኛነትን መሰረት አድርጎ ተማሪዎችና ወጣቶች ከፋፍሎና አፈራቆ ቆይቷል። ቅጥረኞቹን አሰልፎ ደግሞ ትግል ከንቱ መሆኑን ለማሳመን ያለፈው የታገለው ትውልድ ብልህ አልነበረም፤ ስልጡን ፖለቲካ አላወቀም፤ ተጨረሰ፤ ተፈጀ በሚል የሽንፈትን አቅጣጫ ለማስያዝ በሰፊው እየጣረ ነው። ባለፈ ታጋይ ትውልድ ላይ የተከፈተው ሰፊ አሉታዊና ባለጌ ዘመቻ ኢላማው የተሰዉት ሳይሆኑ አሁን ያለውና መጪው ትውልድ ነው፡፡ ይህን መገንዘብ ግዴታችሁ ነው። መልዕክታቸው አትታገሉ ነው። ያን ትውልድ ሲያወግዙና ለሀገር መሰዋት ስህተት ነው ሲሉ በሌላ በኩል ደግሞ የአርበኞቹንም የትውልዱንም ታሪክ የከሸፈ በሚል ጸያፍ ድምዳሜ በማቅረብ ቀቢጸ ተስፋ እንዲወራችሁ፤ ግለኝነት እንዲያሰምጣችሁ፤ ፍርሃት እንዲያፍናችሁ፤ ዘረኝነት ምርጫችሁ እንዲሆን፤ ስለ ሀገር ደንታ እንዳይኖራችሁ ለማድረግ ነው ዓላማቸው። በከፊል እንደሰራለትና በዚህም ስምሪቱ ከታሪክ መማር ያቃታቸው ጠባቦች እንደተባበሩት የሚታወቅ ነው።
ወጣቶች ሆይ፤
በጣሊያን ወረራ ጊዜ ወጣት አርበኞች የነበራቸው ታሪካዊ የጀግንነት ሚና በታሪክ ተመዝግቧል። የሙሶሊኒ ፋሺስታዊ ጦርም ትኩረት ሰጥቶ ስንቱን ምሁር እንዳረደ የሚታወቅ ነው። ጥቁር አንበሳ ብለውና ሪፑብሊክም ይመስረት በሚል ተደራጅተው የአቅማቸውን የታገሉ ወጣቶች ነበሩ። የአጼውን ኋላቀር ስርዓትም መስዋዕትነትን ከፍለው በቅድሚያ የታገሉት የሕዝብ አለኝታ የሆኑት ተማሪዎችና ወጣቶች ናቸው። የደርግንም አረመኔ ስርዓት የተፋለሙት ወጣቶች ነበሩ--ኢሕአፓዎች በተለይ። ለዴሞክራሲ፤ ለሀገርና ለሕዝብ ደማቸውን ገብረዋል፤ የሽብር ሰለባ ሆነዋል። ለዚህም ነው እስከዛሬ የደርግ መሪዎችና ርዝራዦች በድርጅቱ ላይ ዘምተው ወጣቱ በዚያ ትግል መንገድ እንዳይጓዝ ሊያደርጉ፤ ሊያስፈራሩ እየጣሩ ያሉት።
በአሁኑ ጊዜ ይህ በወያኔ አበረታችነት የተጀመረው ዘመቻ ግቡ ወጣቱን ከኢሕአፓና ካመረረ ትግል ለማራቅ ነው። ለትግል በተነሳችሁበት ወያኔ በተቻለው የአፈና ክንድ ሊደቁሳችሁ ሲሞክር ዓመታት አልፈዋል። ደማቸውን ያፈሰሱ ወጣቶች ቁጥርም ቀላል አይደለም። ይህ ሁሉ ግን የሚያመለክተው የትግሉ አማራጭ አንድና አንድ ብቻ መሆኑን ነው። ወያኔን መውጫ ቀዳዳ በማይሰጥ ትግል፤ በሁለገብ ትግል ማስወገድ ብቻ ነው። ከወያኔ መደራደር በሚል ዛሬ ቅዠት በሆነ አማራጭ ሊያደክሟችሁ የሚጥሩትን ወግዱ ማለት አለባችሁ። በወሳኙ ትግል እንዳትሰማሩ ይህን አማራጭ ጊዜው ያለፈበት፤ ያልሰለጠነ፤ የማይሰራ፤ አስፈጂ፤ ከዱላ ይሻላል መላ ወዘተ በሚል ጩኸት ለሚያደነቁሩዋችሁ ጆሮ አትስጡ። መላው ዱላ ነው በሚል ጸንታችሁ በሁሉም መስክ፤ በሁሉም መንገድ፤ በሁሉም መሳሪያ ወያኔን ለማጥቃትና ለመጣል መዋደቅ እንዳለበችሁ መገንዘብ አስፈላጊ ነው። የለም ሊሏችሁ የሚፈልጉት ኢሕአፓ ከጎናችሁ አለ። ብትፈልጉ ታገኙታላችሁ፤ እሱም ይፈልጋችኋል። ከኢሕአፓ መወገን መሰለፍ ይጎዳችኋል፤ ያስጠፋችኋል ብለው ቡታ ለሚረጩትም ትግሉ ነው ሕይወቴ፤ ህይወቴም ነው ለሀገሬ በሏቸው። በትኩረት ግን ወጣቱ አንድነትን እንዲያቅፍ ባላችሁ አቅም ሁሉ መጣር አለባችሁ። ከባድ ስራ ነው፤ የወያኔን መርዝ ጠርጎ ጠራርጎ ማስወገድ ማለት ነው። ስለዚህ ሳትታክቱና ተስፋ ሳትቆርጡ፤ በዘረኝነትም ሳትብከሉ መሰማራት አለባችሁ። ከሙስሊም ወገኖቻችን ትግል ተሰለፉ፤ ተሳተፉ። በአምቦ በወለጋ፤ በጎንደር ወዘተ ሕዝብ ሲያምጽ አመጹን አጅቡት። የሰርቶ አድሩ ሕዝብ በየአቅጣጫው ትግሉን እንዲያፋፍም ቀስቅሱ፤ ጥረቱንም አግዙ። ወጣቱ ነው ግንባር ቀደም፤ የለውጥ አዋላጅ፤ ቀስቃሽና አታጋይ፤ የድርጅቶችም የጀርባ አጥንት። እናንተ ማለት ነው። ሀገርን ከረሳችሁ፤ ወያኔ ለሚያሰራጨው አልባሌ ልምዶችና ጠባዮች ሰለባ ከሆናችሁ ሀገር አድን ትግሉ ይዳከማል፤ ወደፊት አይሄድም። በስልት ተደራጁ፤ አምጹ አሳምጹ ነው ጥሪው።
ለምን ለእናንተ ለወጣቶች ጥሪ ማድረግ አስፈለገ? ወጣት የነብር ጣት የተባለውን አትርሱ። ከሕዝባችን አብዛኛውም ቁጥር ወጣቶች ናችሁ። ወጣቶች--ወንዱም ሴቱም--በትግሉ ካልተሳተፋችሁ ድል መገኘቱ አጠራጣሪ ነው። አዛውንት ያልናቸውም ትግልን አዳፋኝ ሞራል ሰባሪ፤ ሽንፈት አስፋፊ፤ ቀቢጸ ተስፋ አንጋሽ ሆነው አሉና የወጣቱ በመድረክ ብቅ ማለት ቀነ ቀጠሮ የሚሰጠው አይደለም። ለወለደችና ለአሳደገች ሀገር መሰዋትን የመሰለ ክብር የለም። የኢትዮጵያ ወጣቶች ታሪክ የፍርሓት፤ የክህደት፤ የባንዳነትና የአድርባይነት አይደለምና ይህን አጢናችሁ ወደ ትግል ጎራ እንድትገቡ ጥሪያችን ጠንካራ ነው። ኢሕአፓ በቅድሚያ የቆራጥ ወጣቶች ነጸብራቅ ነው። ግንባሩን ያላጠፈ ትውልድ የመሰረተው። ሀገሩን የወደደና ያስቀደመ ትውልድ የገነባው። ሕዝባዊነትን ዓላማው ያደረገ ትውልድ ያጠናከረው። ያኔ ታዲያ በፈሪዎችና ከሀዲዎች ጎዳና የነጎዱት ሁሉ --እንደዛሬዎቹ የወያኔ ተለጣፊዎች--ከፋሺስቶቹ ገዢዎች ጋር አብረው በህዝብ ላይ ወንጀል ከፈጸሙ በኋላ ዛሬ የናንተን ትግል ለማደናቀፍ ደፋ ቀና እያሉ መሆናቸውን ተረድታችሁ ጥረታቸውን ከትቢያ መደባለው ግዴታችሁ ነው። ወጣት ሴቶች በተለይ የህዝባዊ ትግል ክብሪትም ፈንጂ አፈንጂ ናችሁና እምቢኝ ለሀገሬ ብላችሁ ከተነሳችሁ ትግሉ ይህ ነው የማይባል ጥንካሬን ያገኛል፤ ታጋዩ በአጠቅላይም በሁሉም መስክ በእናንት የትግል እስትንፋስ ያታደሳል። ወጣት ሴቶች ወደ ትግሉ እንድትመጡ ጥሪያችን ጠንካራ ነው። በሴቶች ላይ በተለምዶ የሚተረኩ ማንኳሰሻዎች ሁሉ ውድቅ ናቸው። ግማሹ ሰማይ በሴቶች የተደገፈና የቆመ ነው የሚለውን እንመርጣለን።
ተማሪዎችና ወጣቶች ሆይ፤
አር አያ የሚሆኗችሁ ማጣታችሁ ይገባናል--ሊሆኑ የሚችሉትን ታሪክ ደግሞ አቆሽሸው የሚተርኩላችሁ በዝተዋል። ሊታገሉ ቀርቶ ትግልን የሚያኮላሹም በዝተዋል። ምጸት ነው። ግን ታጋይ ነኝ ባዩ ስለታጠፈ ትግል አይረባም አያስፈልግም ማለት አይደለምና ድክመትና አስወግዶ ስህተትን አርሞ ወደፊት መጓዙ በእናንተ ላይ የተጫነ ግዳጅ ነው። የሀገር አድን ትግሉ የጀርባ አጥንት በቅድሚያ እናንተ ናችሁ። ከውጭ መጥቶ ነጻ የሚያወጣን ሀገራዊም ሆነ የባዕድ ሀይል ይኖራል ማለት ዘበትና ራስን ማታለል መሆኑን እሳክሁን ስትገነዘቡት አልቀራችሁም። የራሳችን ነጻ አውጪ እኛው ራሳችን ነን የሚለውን መፈክር መያ ማስቀደም ይኖርባችኋል ማለት ነው። ስንቴ መጣንላችሁ ብለው ቃል ገቡላችሁ፤ ስንቶቹ የወራት ቀጠሮስ ለነጻነት ሰጧችሁ? ሁሉም ከንቱ። ኢሕአፓ የሚዋሸው ነገር የለም። መልዕክቱ ለናንት ለሀገር ለወገን ብላችሁ እናንተ ካልተነሳችሁ ስርየት የለም የሚል ነው። ትግልም ቀላል አይደለም፤ መራራና እልህ አስጨራሽ፤ የደም ግብር ጠያቂ ነው። ተጨባጭ ጦርነትም ( ከአፋዊው ዘመቻ ባሻገር) መራራ ነው፤ ሌላ አማራጭ ቢኖር በተተወ ነበር። ግን አማራጭ የለም። ሀገርን በምለላና በምኞች ማዳን አይቻልምና። ስለዚህ ለማይቀረው ፍልሚያ ራሳችሁን አዘጋጁ። ለአመጽ ተነሱ። ሕዝብን ቀስቅሱ፤ ደግፉ፤ አደራጁና በወያኔ ላይ በጋራ ለመነሳት ጣሩ። ሌላ አማራጭ የለም። መቶ ሚሊዮን አይሰደድምና ዜጋ መታገሉ የግድ ነው--መብቴና ሀገሬ ብሎ። ይህ ከሆነ ወያኔ ይደቃል፤ ይደቆሳል፤ ድምጥማጡም ይጠፋል።
ወጣቶች ሆይ ሀገራችንን ኢትዮጵያን ለማዳን ለትግል ተባባረን እንነሳ ነው የእኛ መልዕክት።
በትግሉ መድረክ እንፈላለግ።

No comments:

Post a Comment