Sunday, January 31, 2016

ወተት ይሸፍታል እንኳን ሰው ሲበደል....ዴሞክራሲያ ቅፅ41 ቁ. 3 ታኅሣስ 2008 ዓ.ም ወርሃ ታኅሣሥ--


ዴሞክራሲያ ቅፅ41 . 3 ታኅሣስ 2008 .
ወርሃ ታኅሣሥ-- ወተት ይሸፍታል እንኳን ሰው ሲበደል
በኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ውስጥ የታኅሣሥ ወር የአመጽና ለውጥን አብሳሪ የሆኑ ትግሎች ሲከሰቱባት መቆየቷ የሚታወስ ነው። ዛሬም ቢሆን ታኅሣሥ፣ ሕዝባዊ አመጽን አስተናግዳለች። ዞር ብለን ግን ለአገራቸው ራሳቸውን የሰጡትን ሰማዕታትን ስንዘክር ገዝፎና ሚዛን ደፍቶ የምናገኘው የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ መሆኑ የሚረሳ አይደለም - ታኅሣሥ 20 የተማሪዎች እንቃስቃሴ ሰማዕትን መዘከሪያ ቀን መሆኑን ያስታውሷል።
page1image4536
የታኅሣሥ ቅርስ ግን በቅድሚያ የንዋይ ልጆችን--መንግሥቱና ገርማሜን--እና የሌሎችንም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ያስታውሰናል፡፡ አንዳንዶች የዚህን ክስተት ክብደት መረዳት ተስኗቸው የታኅሣሥ ግርግር ብለው ሊያንኳስሱት ቢሞክሩም የመንግሥቱና የገርማሜ ንዋይ እንዲሁም የጓደኞቻቸው ጥረትና እርምጃ አዲስ የትግል ምዕራፍ የከፈተ ለሕዝባዊ ትግሉ ጭላንጭል ብርሃን የፈነጠቀ አቢይ እርምጃ ነው። ከዛሬው ጋር ስናስተያየው ለምሳሌ፡ ለወያኔ ካደሩ መኮንኖችና ባለስልጣናቱ አንጻር በሥርዓቱ ከፍተኛ ቦታ የነበራቸው መኮንኖችና ምሁሮች የሕዝቡን ብሶትና እሮሮ ተገንዝበውና ሰምተው ለውጥ ብለው ሲነሱ የሚደርስባቸውን ጉዳት ሳያውቁ ሳይሆን ለሀገር ሲሉ ሞትን ደፍረው ነው። ሞተዋልም። ራሳቸውን የገደሉት ብቻ ሳይሆን ተይዘው የተፈረደባቸውም እነ መንግሥቱ በየአደባባዩ ተሰቅለዋል ፤ ለእስርም ተዳርገዋል፡፡ ለምን ታገላችሁ፤ ለውጥን ለምን ፈለጋችሁ፤ ... ወዘተ ያላቸው አልነበረም - መስዋዕትነታቸው ተከበረ እንጂ፤ ምሳሌ ሆነ እንጂ። የታኅሣሡ የመፈንቅል ሙከራ ዋናው አንደምታው በተማሪዎች እንቅሳቃሴ ላይ ያደረገው ተጽዕኖ ነው ቢባልም ስህተት አይደለም። ቀደም ብሎ ተማሪዎች የጥገና ለውጥ አቀንቃኝ ነበሩና ለአጼው መንግሥት የምለላ ደብዳቤ እየጻፉና እየተማጸኑ አንዳንድ ለውጦች እንዲደረጉ ሲጠይቁ እንደነበሩ የሚታወቅ ነው። ለውጥ ከገዢዎች በጎ ፈቃድ የሚጠበቅ ነበር። ታኅሣሥ 1953 ግን ይህን ሁሉ ቀየረውና የአጼው ሥርዓትና ተማሪዎች ተቆራረጡ። ሥር ነቀል ለውጥም ተፈላጊና ተቀንቃኝ ሆነ።
ከዚያን ጊዜ እስከ የካቲት የተደረገው ጉዞ ውጣ ውረድ የሞላበት እንደነበር ሊረሳ የሚገባውም አልነበረም። ከተማሪዎች በፊት የኢትዮጵያ ሠራተኞችም ታግለዋል። ልዩ ልዩ የአርሶ አደሮች አመጾችም ተካሂደዋል። በሕግ የተደነገገ ጪሰኝነትን የሚያጸድቅና የአርሶ አደሩን ምርት ከሦስት ሁለት እጅ (ሁለት ሶስተኛ ምርት) ለባለመሬቶች የሚሰጥ የገባርነት/ጪሰኝንት ሥርዓት ነበርና የተጠቃው አርሶ አደር ከጊዜ ወደ ጊዜ አምጾ ተሰውቷል። ትግሎቹ ግን የተቀናጁና ስልታዊ ስላልነበሩና የአጼው አገዛዝ የአፈና ተቋሞች ዘመናዊና ጨካኝ ስለነበሩ አመጾቹ መቸነፋቸው የሚጠበቅ ነበር። በንጉሡ የበላይነት የሰፈነው ሥርዓት ፊውዳል ወይም ይባል እንደነበረው ባላባታዊ ስለነበር መሠረታዊ ቅራኔው አገዛዙ ከሠፊው አርሶ አደር ሕዝብ ጋር ቢሆንም ከጅቡቲ ኢትዮጵያ (ቀደም ፍራንኮ ኦትዮጵያ ይባል የነበረው) ባቡር ሃዲድ መዘርጋት ጋር ተያይዞ ላባደሮች ብቅ ብለው ነበር። ከብዙ ችግርና ትግል በኋላ በመጋቢት 5/1947 የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ሠራተኞች ማኅበር (ሲንዲካ ደ ሼሚኖት ኢትዮጵያ) በሚል ስም ተመሠረተ። ይህ በዚህ እንዳለና ማኅበራቸውንም አለፍቃድ የመሠረቱ ቢሆንም ብዝበዛን በመቃወም በዚያ ዓመት ያደረጉት የሥራ ማቆም አድማ የተሳካ መሆኑ ለሌሎችም ምሳሌ ሆኗል። በ19051908 ዓመታት ባዕዳን ባንኮችን በመክፈታቸው የቢሮ ሠራተኞች ቁጥር ተበራከተ። የፋብሪካዎች መቋቋምም እንዲሁ የላባአደሩን ቁጥር እያሳደገው መጣ። ኤርትራ በፈደሬሽን ስትደዳድር በነበረበት ጊዜም የሠራተኛ ማኅበር ማቋቋም የተፈቀደ ስለነበር መንግሥት ሲያስፈልገው የሠራተኛ ማኅበራትን ሊያፈርስ/ሊሰርዝ ይችላል የሚል አንቀጽ በወጣው አዋጅ ውስጥ በመካተቱ የኤርትራ ሠራተኞች ይህን በመቃወም ያደረጉት ጠቅላላ የሥራ ማቆም አድማ የተሳካ ሆኖ ሠራተኞቹም ከቀሪው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ጋር በማኅበር ሊያያዙ መቻላቸው ትግላቸውን በቁጥርም በተመክሮም አዳበረው። ሠራተኛው ለመብት--በተለይም አታጋይ ማኅበርን በጋራ ለመመሥረት ያደረገውን ትግል ታሪክ በዚህ ለመዘርዘር ባንቃጣም በ1950ዎች መጀመሪያ ላይ በእነ አቶ አበራ ገሙ (ቃጫ ፋብሪካ)ና የሞዝቮልዱ የእንጨት ሥራ ድርጅትና ሌሎች (ዲያባኮ ጥጥ ፋብሪካ፣ የኢትዮጵያ ተሽከርካሪ አግልግሎት፣ ቫስኪንና ዳርግስታድ) በምስጢር ግንቦት 20 ቀን 1953 .ም ደጃዝማች ባልቻ ሜዳ ተሰብስበው የጋራ ድርጅት ለማቋቋም መስማማታቸው መጠቀስ ያለበት ነው። መጋቢት 3 ቀን 1954 .. በቃጫ ፋብሪካ ሠራተኞች ሊቀመንበር(ነት) የተካሄደው ስብሰባም አንድ ቋሚ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር እንዲቋቋምና በኮንፌዴሬሽን መልክም ኢንዱስትሪዎችን፣ ፋብሪካዎችንና የኅብረት እርሻዎችን ሁሉ እንዲያቅፍ ተወስኖ በመቀጠልም በሰኔ 1954 ዓም 3ኛው የተወካዮች ስብሰባ ሲደረግ የምድር ባቡር ፣ የድሬዳዋ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ በዘረኛ ሆላንዶች ሥር ይሰቃዩ የነበሩት የወንጂና ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞችና ሌሎችም ሊሰባሰቡ ቻሉ። ሚያዝያ 1 ቀን 1955 ም የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበር ሊቋቋም ቻለ። በሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር ሥር ማኅበራት መመዝገብ አለባቸው በሚል ሥርዓቱ ማኅበሩን ሊቆጣጠር ሲጥር አጋሩ አሜሪካም በራሷ የሠራተኞች ድርጅት አማካይነት ወጥመዷን ዘረጋች። በሠራተኛው ማኅበር ላይ ከባድ ተጽዕኖ ተደርጎ የክብር ፕሬዚዳንቱ አቶ አበራ ገሙ ራሱን ገደለ ተብሎ ቢለይም ማኅበሩ ለብዙ ሥራ ማቆም አድማዎች አደራጅና አዋላጅ ሆኖ ቀጥሏል - ከተቋቋመ በአራት ወሩ የጠራው አድማ በተደረገው አፈና የተነሳ ባይሳካም።
እይታችንን ወደ ሠራተኞች ማኅበር ዞር ያደረግነው ቀደምም ትግል ማካሄዳቸውን ለመጥቀስና ቀጥሎም ከተማሪዎቹና ከአስተማሪዎቹ እንቅስቃሴ ጋርም በመቀናጀት ለየካቲት 66 ስፋትና ጉልበት የሰጡ መሆናቸውን (የእንዳልካቸው መኮንን ካቢኔ ከሥልጣን እንዲወርድ ጠቅላላ የሥራ ማቆም አድማ ያደረገው አስተዋጽኦ
እንደምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል) ለማስታወስም ነው። የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴም ሲጀምር የተማሪውን ሁሉ ድጋፍና ተሳትፎ ያገኘ አልነበረም። ጃንሆይ ምን አጠፉየሚሉ ጥቂቶች ካለመሆናቸው በተጨማሪም የተማሪው የንቃት ደረጃም በጣም ደካማ ነበር ቢባል ስህተት አይሆንም። ከዩኒቨርሲቲው አስተማሪዎች የነበሩት ባዕዳንም -- በተለይም የሰላም ጓድ ተብለው የተሰማሩት አሜሪካውያንና ሚሲዮናውያን -- ተማሪው በፖለቲካ እንዳይነቃና እንዳይደራጅ፤ እንዲከፋፈልም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ጥቂቶች ቢሆኑም ጊዜው የደረሰን ወይም የመጣለትን ጽንሰ ሀሳብና አቅዋም ይዘው ከተነሱ ብዙሃኑን ሊሰበስቡ ይችላሉ በተባለው መሠረት ጥቂት የነቁ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በምስጢር ተሰባስበው፤ ንቃታቸውን እያዳበሩ፤ በተለያዩ መንገዶች የአብዛኛውን ተማሪ የአስተሳሰብ አድማስ ለማስፋትና ለማበልጸግ ቻሉ። የእነኃይሉ ገሞራውና የእነጸገየ ወይን (ደብተራው) ግጥሞች (በረከተ መርገም፣ ናስተማስለኪ፣ . . . )፤ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በግልጽ የሚደረጉ ውይይቶች በተማሪው ማኅበር ጋዜጦችና በተባራሪ ወረቀቶች በሚደረጉ ጽሁፎች ተማሪዎች ስለአገራቸውና ስለዓለም አቀፍ ሁኔታ ያላቸውን ግንዛቤ አሳደጉ። በአመለካከትና በአስተሳሰብ ግልጽነትም አስፈላጊ እየሆነ የመጣውንና መሠረታዊ የሆነውን ጥያቄ -መሬት ለአራሹን- እንዲሁም ሌሎች አገራዊ ጥያቄዎችን በማንሳት ተከታታይ ሰልፎችን አካሄዱ። ጥያቄው ሥርዓቱን የሚያናጋ በመሆኑ አገዛዙ ለተማሪዎቹ የሰጠው ምላሽ የኃይል እርምጃ ሆነ። በሰልፋቸው ከአገዛዙ ጋር ተጋጩ ። በቅድሚያ ተነስቶ የነበረው የመሬት ጥያቄ የአጼውን አገዛዝ ምሰሶ የሚነቀንቅ በመሆኑ አገዛዙ በሰልፈኞቹ ላይ የኃይል እርምጃ ወሰደ፤ መሪዎች ናቸው ያላቸውን ዘጠኝ ተማሪዎች (ሟቹ ኃይሉ ገበረዮሐንስ- ገሞራውን- ጨምሮ) ከዩኒቨርስቲው አባረረ። ቀንዲሉ፣ እሳቱ ተለኩሷልና አልጠፋ ማለቱ የሚጠበቅ ነበርና በተከታታይ ዓመታት ተቃውሞውና ሰልፉ ቀጠለ።
የኋላ መብራት ፈዘዝ፤ ወደ ኋላ ዕይታ ጨንበስ የሚል አይደለምና በዚያን ጊዜ ድርጅቶች የነበራቸው ድክመት፣ ጥንካሬ፣ ትግልና መስዋዕትነት፣ ምርጫ፣ ስልትና መፈክሮችንም በተመለከተ የሚሰጠው ፍርድና ትችት አስፈላጊ የሆነውን ግምገማን ከጊዜው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ማቆራኘትን የሚቀበል አይመስልም። ስለዚህም ትችቱ የሐቅ ደኻ እና ገለባ ሆኖ ቆይቷል። ለጨለማ መብራት፤ ለወገንም ኩራት ሆኖ ያለፈውን ትውልድ መዝለፉ አወቅን ባዮች ሥራዬ ብለው ተያይዘውት ቆይተዋል። ለካፒታሊዝም ከመሰዋት ለሠርቶ አደሩ ሕዝብ ሥልጣንና ዴሞክራሲ መሰዋት ይበልጥ የተከበረ መሆኑን የሚስቱት ምሁራን ተብየዎች የተማሪዎች እንቅስቃሴ ግራ ክንፍ ነበር ብለው በደፈናው ሊያወግዙ ይነሳሉ። ሐቁ ይነገር ከተባለ ደግሞ፣ ለሰው በላና ለበዝባዥ ሥርዓት ከመሞት ለሠርቶ አደሩ ሕዝብ ሥልጣንና ለዲሞክራሲ መሰዋት ይበልጥ የተከበረ ነው። ተማሪዎችና ምሁሮች ወደ ግራና ወደ ሶሻሊዝም ያዘነበሉበትም ምክንያት የነበረውን ጨቋኝ አገዛዝ በሁሉም መስክ ሊፋለሙ ሲነሱ የርዕዮት ትጥቅ ሊሆናቸው የሚችለው ይህ ብቻ ስለነበር ነው። የካፒታሊዝም አገዛዝ ቁንጮ የሆነችው አሜሪካ የአጼው አጋር ሆና የተሞከረውን መፈንቅል ያከሸፈች ከመሆኗ በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃም ኢምፔሪያሊስት ተብላ ሕዝባዊ ትግል ያነጣጠረባት፤ የደቡብ አፍሪካን አፓርቴይድ የምትደግፍና ዘረኛ ሀገር ነበረች። ለማንም አርዓያ የማትሆን የግፍ ሀገር። ተማሪዎችና ምሁሮች ዕይታቸውን ወደ ሌላ አቅጣጫ ማድረጋቸው አንድም በዚህ ምክንያት ሲሆን በሌላም በኩል ሥር ነቀል ለውጥ ፈላጊውና አሜሪካ ሆድና ጀርባ በመሆናቸው ነው። ለነገሩ ዛሬም ይህ ሐቅ ሆኖ ያለ ነው።
ጊዜውን መመርመር ባልነው መሠረት ደግሞ የተማሪው እንቅስቃሴ ደምቆና አምርሮ በተነሳበት ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ጸረ ኢምፔሪያሊስትና ጸረ-ቅኝ ገዢዎች ትግል በአፍሪካ፣ እስያና ደቡብ /ላቲን አሜሪካ ተፋፍሞ ነበር። በሀገራት ደረጃ ቪየትናም፣ ላኦስ፣ ካምቦዲያ፣ ሞዛምቢክ፣ አንጎላ፣ ጊኒ ቢሳው፤ በታጋዮች ደረጃ ቼ ጉቬራ፣ ካብራል፣ ሞንድሌን፣ ማሼል፣ ሆቺ ሚንህ፣ ማንዴላ፣ ሉሙምባ፣ ቤን ቤላ፣ ... ወዘተ የሚባልበት ጊዜ ከመሆኑ ሌላ የትግሎቹ አጋሮች ደግሞ የሶሻሊስቶቹ ጎራ (ሶቭየት ህብረት፣ ቻይና ፣ ኩባ፣ ... ወዘተ ) ነበሩ። በ1966 ኢሕአፓ መሆን ከወጣቱ የሚጠበቅ ሆኖ እንደተገኘው ሁሉ ከዚያ ቀደም ባለው ጊዜ ግራ ክንፍ አለመሆን ኋላ ቀር ያሰኝ ነበር ብንል ትክክል ነው - የነበረ የወቅቱ ዕውነታ ነው።
ስለዚህም ያ ትውልድ ግራ ክንፍ የሆነው ለኢትዮጵያ ችግሮች በዚህ መልክና መንገድ መፍትሔ አገኛለሁ በሚል ነው እንጂ የሀገሩን ባህልና ወግ በደፈናው ሰርዞና ለባዕድ አድሮ አልነበረም። እውነቱ ሲነገር እንቅስቃሴውም ሆነ ኋላ የተቋቋመው ኢሕአፓ ለማንም ባዕድ አንገዛም፣ አንጎነበስም በማለታቸው ጉዳት ደረሰባቸው እንጂ ከሀዲዎቹ እንደሆኑት እንደነ ወያኔ አልተጠቀሙም። ያን ትውልድ ወደ ግራና ወደ ስር ነቀል ለውጥ ፍለጋም የገፋፋው ራሱ ሥርዓቱ ነው። ጉድ ይሰማል ጆሮ፣ ሆኖ ዛሬ የአጼውን ዘመን ጭፍን ጭቆና ሲክዱ የሚሰሙ ያሉ ቢሆንም ያ አገዛዝ ለሚሊዮኖች እስር ቤት፣ የመከራ፣ የስቃይና የፍዳ፣ የልዩነትና የበደል አገዛዝ እንደነበር የሚካድ አይደለም። ደከም ያለ ለውጥ እንኳን ለማድረግ አጼውም ተከታዮቻቸውም ዝግጁ አልነበሩም። ሕዝብን ንቀውና ቀጥቅጥው መግዛት የለመዱ ነበሩና፤ እኩልነትን ነፍገው፤ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ሁሉ አፍነው፤ ስዩመ መለኮት ነን በሚል ዘለዓለማዊነትን ከጅለው (የዛሬውን የትግራይ ወያኔዎች፣ ጠባቦች በሚመስል ደረጃ) ነበርና ለተማሪው መልስ ምላሻቸው አፈናና ግድያ በመሆኑ ሁኔታው እየተባባሰ መሄዱ የማይቀር ሆነ።
በልዩ ልዩ ቦታዎች አመጾች መቀጠላቸው ፤ ሠርቶ አደሩ ማመጹ፤ አስተማሪዎችና የቢሮ ሠራተኞች መነሳታችው፤ የእነ ደጃዝማች ታከለ መገደልና፤ መፈንቅሎች መሞከራቸው፤ የተማሪውም ትግል ማየሉና አልቋረጥ ማለቱ ውሎ አድሮ ለየካቲት 66 መከሰት በሩን ከፈተ፤ ድልዳል ሆነ። የካቲት የግብታዊነት ውጤት ነው ፤ የሕዝብ አመጽ ድርጅትና ትግልን አይጠይቅም የሚሉት ይህን ሐቅ መረዳት የተሳናቸው መሆኑም በግልጽ ያታያል። ችግሮቹንም የነበሩት ሥርዓቶች ፈጠሯቸው እንጂ ተማሪዎች የሌለውን ችግር አለ ብለው ለተቃውሞ እልተሰለፉም። ይህን መሠረታዊ ሐቅ የዘነጉ ክፍሎች ችግር ፈጣሪውን ሥርዓት ትተው ተማሪዎች በጠበጡ፤ ሀገር አስገነጠሉ፤ . . .ወዘተ ሲሉም ይደመጣሉ።
በተጨባጭ ታኅሣሥ 20 የተማሪ ሰማዕት መዘከሪያ ቀን የተባለውም በዚህ ቀን በርካታ ተማሪዎች በመገደላቸው ነው። የተማሪው እንቅስቃሴን የሚከሱ ክፍሎች መረዳት ወይም መቀበል የተሳናቸው ከአንድ አፈና ደረጃ ወደ ከፍተኛ ጥቃት የተሸጋገረው ሥርዓቱ መሆኑን ነው። የተማሪው እንቅስቃሴ መፈክሮች ሲመረመሩና በተለይም ከዛሬው የተሰበጣጠረ መፈክር ጋር ሲነጻጸሩ በዚያን ጊዜ ተማሪዎች ሲያነሷቸው የነበሩ መፈክሮች ለሀገሪቷ ችግሮች መፍትሔን ጠቋሚ ነበሩ። ከመፈክሮች ውስጥ አንደኛው መሬት ለአራሹየሚለው ነው። የዚህ መፈክር ጥፋቱና ጎጂነቱ በተለይም ለጭሰኛውና ገባሩ ምንድ ነው የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል? የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብት ይከበር የሚለው እስከዛሬ ያልተመለሰ የሕዝብ ጥያቄ ነው። መብት ለሠርቶ አደሩ ሕዝብድህነት ወንጀል አይደለምየሀገራችን ሉዓላዊንት ይከበርእና መሰል መፈክሮች ያኔ የቀረቡና ያታገሉም ናቸው። ሕዝባዊ መንግሥት ይቁቋምደግሞ ዛሬም ሊስተጋባ የሚገባውና የሕዝብን መሠረታዊ ፍላጎትም የሚያንጸባርቅ ነው። የሃይማኖት ልዩነቶች ተወግደው ነጻነታቸው ይጠበቅ፤ የሴቶች መብት ይከበር የሚሉት ጥያቄዎች ዛሬም መሠረታዊ ናቸው። ተማሪዎችና ተራማጁ የኤርትራም ጥያቄ በሰላማዊና ዴሞክራሲያ መንገድ ይፈታ በማለት ሲያሰሙ የነበሩት ጩኸት አድማጭ አግኝቶ ቢሆን ኖሮ አሁን የተከሰተው ችግር በአጭር በተቀጨም ነበር። የኢትዮጵያ ትግል ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማድረጉ፣ ባከተመ ነበር። በወቅቱ የተደረጉት ሰልፎች በአገሪቱ ውስጥ ተከስተው የነበሩትን ሕዝባዊ መፈክሮች ይዘው መሆኑን ማንም ሊክድ አይችልም።
ጥላሁን ግዛው ተገደለ። በቀጣዩ ሰልፍና ተቃውሞም በደብረ ብርሃን እነ ሺፈራው ከበደና ሊሎችም ተረሸኑ። መኮንን ሀጎስና ሊሎችም በሐረር ፣ እንዲሁ። በጥላሁን ቀብር ላይ እነጀማል፣ ስብሓት፣ አበበና ብዙዎች በግፍና በገፍ ተገደሉ ፤ ታኅሣሥ 20 የሰማዕት ቀን የተባለውም በዚህ ነው። ያ እንቅስቃሴና ትውልድ ለሀገራችን ችግር ያቀረበውን መፍትሔ የሚመጣጠን እስካሁን ካለመቅረቡ ሌላ አሁንም ሰማህ አልሰማሁም፤ አየህ አላየሁም ባዮች ያን የከሰረውን ሥርዓት ሂደት መፍትሔ ብለው ያን ትውልድ እያወገዙ ማላዘኑን መርጠው ይገኛሉ። የቀድሞ ሰማዕትን ስንዘክርና የየካቲትንም ክስተት መሠረቱን ለመግለጽ ስንጥር በተለይም ዛሬ የሕዝብ ትግል ከሚያሳየው ድክመትና ስህተት አንጻር ከተመክሮ መማር ይቻል ነበር፤ አሁንም ይገባል ለማለት ነው ። ማለትም፡
  •   የተማሪው እንቅስቃሴ ግቡን የሚያውቅ ነበር - ዴሞክራሲና እኩልነት ለኢትዮጵያ።
  •   የተማሪው እንቅስቃሴ ብቁ አመራር የሚሰጡት የነቁ አባላት/መሪዎች ነበሩት።
  •   ያነሳቸው መፈክሮች በሞላ የሕዝብና በሕዝብ የተደገፉ ነበሩ።
  •   በጎጥ ወይም ብሔረሰብ ፣ በሃይማኖት የተከፋፈለ አልነበረም። ምንም እንኳን የተወሰኑ የኤርትራን ግንጠላ ይደግፉ የነበሩ (በኤርትራ የተወለዱ ተማሪዎች) የተማሪው ትግል አይመለከተንም ብለው ራሳቸውን ከእንቅስቃሴው ቢያገልሉም ብዙዎቹ ግን በእንቅስቃሴው ተካፍለው በዚያም ጊዜ ሆነ በየካቲት መስዋዕትነትን ከፍለዋል።
  •   የተማሪው እንቅስቃሴ በስልት ከሌሎች የኅብረተሰቡ ክፍሎች ጋር ሊቀናጅና ትግሉን ሀገር አቀፍ ሊያደርገውም መቻሉ ውጤቱ በየካቲት 66 ሊታይ ችሏል ዛሬ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በጥሞና ስናየው ያኔ የነበረው ሁኔታ እንደሌለ መቀበል እንገደዳለን። ወያኔ ለሥልጣን የበቃው በወደቀው ፀረ-ሕዝብና ቀይ ሽብርተኛ አገዛዝ የተነሳ መሆኑን ማንም የሚክደው ወይም የሚዘነጋው አይደለም። እብሪተኛውና ፈርጣጩ ኮሎኔልና የወንጀሉ ተባባሪዎች የሆኑት ጓደኞቹ ሀገር ወዳድ ትውልድን ጨፍጭፈው ለገንጣይ ኃይሎች ድል መሠረት መጣላቸው ይታወቃል። ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችም ሊረባረቡ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሮ የደርግ ከፍተኛ ባልሥልጣን ከነበሩት የባዕዳን ሰላዮችና ሠራተኞች የነበሩባቸው መሆኑም ተጋልጧል። የቀጠለውን ሁኔታ ሕዝብ ያውቀዋልና ሀተታን ባይጠይቅም፤ ሀገራችንን ለቅርጫ ወያኔ ሲያቀርብ ተባባሪዎች ከየጎራቸው ብቅ ብለው አጫፋሪ ሆነውታል። ተማሪዎች ለአንዴም ለመጨረሻም ሊባል በሚችል ሁኔታ ወያኔን ተቃውመው ቢሰለፉና ቢሰዉም በጋራ እንዳይሰለፉና እንዳይቃወሙ ወያኔና ጠባቦች የተንኮል ሴራቸውን ጠንስሰው ተግባራዊ አደረጉ። ሕዝቡንም ወጣቱንም በጎጥ፣ በክልል፣ በብሔር፣ በቋንቋ፣ ...ከፋፈሉ። ይህ ሁኔታ በስፋት ሰፍኖ የሕዝብ አመጽንና ትግል አደናቅፎ እስካሁን ቆይቷል። የታኅሣሥ መንፈስና የሰማዕቱ ቅርስ ተኗል ለማለት ባንችልም ችግሩ ግን ግልጽ ነው ለሁላችንም።
ለጋራ ሀገር ለኢትዮጵያ መታገል ቀርቶ ለክልልና ለጠባብ ግብ መቆሙና ይባስ ብሎ ኢትዮጵያዊነትን መካዱም ያለ ሆኗል። የተሰው ተማሪዎችና ወጣቶች ጀግኖች፣ ተራማጆች አጥንታቸው ይገላበጥብናል። ተማሪዎችና ወጣቶች የለውጥ አንቀሳቃሾች መሆን ሲገባቸው ተከፋፍለው መቆማቸው ምስጢርም አይደለም። የሚነሱት መፈክሮች ሀገራዊ ሳይሆን ጠባብና ውሱን ናቸው። ድርጅቶቹ የኢትዮጵያን ነጻነትና የሕዝቧን ዴሞክራሲ የሚሹ ሳይሆኑ ግንጠላን የሚያቀነቅኑ ስለሆኑ ሕዝባዊ ትግልንም ሊመሩ የሚችሉ አይደሉም--አያምኑበትምና። ትግል ተብሎ የምናየው አንድ ግብ ያለው ባለመሆኑ በመከፋፈሉም ገዢውን ክፍል በጋራ ሊያጠቃ አልቻለም። ገዢው ክፍል ላይም፣ አንድ ወጥና ለአገዛዙ ተጻራሪ የሆነ አቅዋም አልከሰት ብሎ ከርሟል። ግማሹ በሰላም እንደራደር ሲል፤ ሌላው አብዮት ቃሉን እንኳን መጠቀም ስህተት ነው ብሎ ራሱን ለትዝብት ሲዳርግ፤ ቀሪው የግንጠላ አንቀጽን ይዟል በሚል የወያኔን ሕግ ሕገ-መንግሥታችን ነውና ይከበርልን በማለት ጥያቄ ሲያቀርብ፤ በዚህ ውጥንቅጥና ውዥንብር የተነሳ ወያኔ ከውድቀት እየዳነ መቀጠሉን ሁሉም በምጸት እየተገነዘበው ነው ማለት የሚቻል አልሆነም። ያን ትውልድና ያን ሀገራዊ ቁርጥ አቅዋም የምንናፍቅበት ጊዜ መምጣቱ በራሱ ምንኛ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዳለን የሚጠቁም ነው። ካለፈው መማር ሲቻል ያለፈውን የሕዝብ ደምና መራራ ተመክሮ ማክቸልቸል ፤ ለሕዝብና ለሀገር ጠላቶች ሰለባ መሆን መጨረሻው ጎጂ ለመሆኑ አስተማሪ አያሻውም። መደራጀት ወሳኝ ነው፤ ትግሉ ለኢትዮጵያ መቆምና የጋራም መሆን አለበት፤ ክፍፍል ማክተሙ አስፈላጊ ይሆናል፤ በሕዝብ ላይ ሳይሆን በባዕድ ላይ መተማመኑ ማብቃት ይገባዋል። እንዲሁም ወያኔ በወደደው ቦይ መፍሰሱ ኢትዮጵያን የሚጎዳ መሆኑ መቀበል የተገባ ሲሆን ለትምክህተኞችም ሆነ ለጠባቦች መድረኩን መልቀቅ ደግሞ ሊታሰብ አይገባውም። ከራሳችን ተመክሮ ከተነሳን ለራሳችን የጋራ ታሪክ ክብር ከሰጠን ወደሚፈለገው ጎህ ለመድረስ እንችላለን። የታኅሣሥ ሰማዕትም በከንቱ አልሞቱም ማለት የምንችልበት ሁኔታ ይከሰታል ማለት ነው።
ያኔ ትግሉ ለኢትዮጵያ ነበር። የጋራ ነበር። በሥርዓቱ ላይ ሕዝብ በጋራ የተነሳበት ነበር። ዛሬ አፍን ሞልቶ ይህን ማለት አይቻልም። ያኔ የነበሩት ድርጅቶች፣ በዴሞክራሲና በእኩልነት፤ በሀገርም አንድነት ጉዳይ ላይ ልዩነቶች አልነበሯቸውም። እነ ወያኔ የጋራውን ሰልፍ ሊበታትኑ ሲነሱም አድማጭ አልነበራቸውም። ትግሎች ቀስ በቀስ የተቀነበባሩ ነበሩ እንጂ በየፊናቸው አልነጎዱም። ከሁሉም በላይ ተማሪዎችና ወጣቶች በአንድነት ተደራጅተው ቆዩ እንጂ በየብሔራችን ብለው አልተለያዩም። ምሁሮችም በአጠቃላይ ሀገራዊ ተልዕኮ እንጂ ሕዝብን በጎጥና በሃይማኖት የሚከፋፍሉ አልነበሩም። የጊዜ ጎማ ግን ያን ድንቅ ቅርስ ረጋግጦ ቀይ ሽብርተኞችና ፤ ጠባብ ነፍሰ ገዳዮች ሰው የሚባሉበትን ጊዜ ስላመጣብን ከገባንበት ረግረግ ለመውጣት ወደ ኋላ መለስ ብለን ሀገርን የዴሞክራሲና የመብት ባለቤት ለማድረግ የተደረገውን የጋራ ተጋድሎ ማስታወሱ የግድ ይሆናል። እያንዳንዱ ትውልድ የራሱን ግዳጅ መቀበልና መስቀሉንም መሸከም እንዳለበት ሲታወቅ ባለፈው ታጋይ ትውልድ ላይ በአሉታዊ መረባረብ የራስን ግዳጅ ያለመቀበልን ጥፋት የሚሸፍን አይሆንም። ካለፈው ተመክሮ ጠቃሚውን ሁሉ ቅርስ አድርጎ አሁንና ዛሬ በሚጠይቀው መንገድ መታገሉ ነው ዋናው። ስለ ትግል ወሬው ደርቶ ትግል ደብዛው ከጠፋ፤ ያው ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡን ያመጣል እንጂ የሚፈይደው ነገር አይኖርም። በኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ላይና አከታትሎም በኢሕአፓና በዚያ ጀግና ትውልድ ላይ ዛሬ የሚደመጠው መረን የለቀቀ አሉታዊ ትችት የሕዝብ ትግል ጠላት በሆነው ወያኔና መሰሎቹ የሚራገብ፤ ያሁኑ ወጣት ትውልድ ካለፈው እንዳይማር ለማድረግ መሆኑን የምንስተው አይደለም። በመሆኑም ነው ቅርሳችንን በተደጋጋሚ ለማሳወቅና የአሁኑ ባለፈው የኅብረትና የዕኩልነት፣ የኢትዮጵያዊነት ጎዳና እንዲጓዝ ለመጥራት እየሞከርን ያለነው።
ጊዜ ተለውጧልና በጨቋኞች ላይ ብረት ማንሳቱ ጊዜው አልፎበታል የሚሉም እንዳሉ የምናውቀው ነው። በዚያው ልክ ግን ለውጥ በአመጽና በብረት ትግልም እንደሚመጣ በዓለም ደረጃ እያየነው ከመሆኑ ሌላ ሕዝብም ደምቶና ታግሎ ድሉን በታጠቁ እንዳይቀማ (የካቲትን ያስታውሷል! ግብጽን ይመለከቷል!) ድርጅትና ኃይል ያስፈልገዋል። ሁሉን ኃይሎች ያቀፈ የሽግግር ሂደት ይኑር በሚል የቀረበውን አብዮት አድን አማራጭ ያኔም ሥልጣን ቀሚዎቹና ዛሬም እርዝራዦቻቸው በአሉታዊ ቢተቹትም ይህን ሕዝባዊ አማራጭን ዕውን ለማድረግ መንገዱ ምለላ ወይም ባዕዳንን ልመና እንዳልሆነ ግልጽ ሊሆንልን ይገባል። የድርጅቶቹንም ይዘትና ተመክሮ በሚገባ መመርመሩ የሚታለፍ ወይም ቸል የሚባል ግዳጅ አይደለም - ነጋ ጠባ የፖለቲካ ቁማርተኞች ሰለባ እያደረጉን ወደ ክስረትና ቀቢጸ ተስፋ እንዳይከቱን ማለት ነው። ደግሞ ደጋግሞ የሚታለል ሰው የሚታዘንለት ሊሆን አይችልም ተብሏልና እየተስተዋለ እንላለን። ጥላሁን ተባለ ጀማል፤ ደመቀ ተባለ አበበ፤ ጀሚላ ተባለች አስቴር ፤ አበራ ገሙ ተባለ ገ/እግዚአብሔር ... ወዘተ ከአንድ ብሔር የተወለዱ ሳይሆኑ ለኢትዮጵያ ብለው የታገሉና የሞት ጽዋንም የጠጡ ጀግኖች ናቸው። አርዓያዎች። ከደርግ ሽብርተኞችና ከወያኔ ዘረኞች የተለዩ፤ የተቃረኑ። ተባብረው የታገሉ፤ ፍርሃትን አሽንፈው ሞትን የተጋፈጡ፤ የአፍ ሳይሆን የተግባር ታጋዮች፤ ኢትዮጵያንም መውደዳቸውን ውድ ህይወታቸውን ሰጥተው ያስመሰከሩ። የታኅሣሥን ሰማዕት፤ የተማሪውና የሠራተኛውን፣ የአርሶ አደሩና የወታደሩን፣ የአስተማሪውን የሴቱን፣ ...ወዘተ ትግል ስንዘክር ያ ኢትዮጵያዊነት፤ ያ ቆራጥነት፤ ያ ኅብረት ህያውነቱ ይታደስ ዘንድ በመፈለግ ነው።
ለሕዝብና ለሀገር የተሰዉ ሁሉ በትግላችን ህያው ይሁኑ ! ኢትዮጵያዊነት ያቸንፋል !!

No comments:

Post a Comment