Friday, January 15, 2016

ባርነት የለመደ ፤ በህልሙ ድንጋይ ይሸከማል ( በፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ)


ባርነት የለመደ ፤ በህልሙ ድንጋይ ይሸከማል
በተጨማሪም " የማንነት መሠረት ያጣ፤ በአጥር ውስጥ ይሸሸጋል " ተብሏል ። በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ የኖረ/ የሚኖር ዜጋ ሁሉ ፤ የማንነት ችግር ስለሌለው ፤ መሸሸጊያ አያስፈልገውም ። የነፃነት ባለፀጋ በመሆኑም፤ ከባርነት ነፃ ለመውጣት ሲል፤ ድንጋይ ለመሸክም አይጎነበስም ። ዱሮውንም ቢሆን ነፃ ሕዝብ ነበርና ! የጋራ ሽንፈትን ስለማይቀበልም ፤ ለጋራ ድል ይታገላል እንጅ ፤ የባዕዳንን ርዳታና ድጋፍ አይጠብቅም ።
በራስ መተማመንን የሚተካው አለመኖሩን ስለሚገነዘብ ፤ ከሕዝቡ፤ ከወገኑና ከትግል አጋሮቹ ፤ ጋር ሆኖ ፤ አምባገነኖችን እየታገለ ማንነቱን ከማስመሰከር በቀር፤ የሌሎቹን ይሁንታ አይጠይቅም። አያሻውምም ። በጋራ ተባብሮ ጠላቶቹን ድል ይነሳል እንጅ፤ እየተበደለ በጋራ አያለቅስም ። በጋራ እያለቀሱ መኖር ፤ ውርደት ስለሚመስለው፤ ለጋራ ድል ተባብሮ ይታገላል ! ደሙን እያፈሰሰም የወገኖቹን እምባ ያደርቃል ። የሕዝቡን የነፃነት ጥማት ለማርካት ይታገላል ። ይሰዋል።
በራሱ የሚተማመን ፤ የሕዝብን ከበሬታና ድጋፍ ያገኛል ። ባላንጣውን ያስደነግጣል ። ባዕዳንም ቢሆኑ ይጠሉታል እንጅ አይደፍሩትም ። ዛሬ ፤ የኢትዮጵያን ማንነትና ምልዑነት፤ ወደ ሽርፍራፊ የጎሳና የዘር ፖለቲካ ዕሳቤ ለመለወጥ የሚደረገውን ደባ፤ በፅናት የሚቃወመውም ከዚህ መሠረታዊ ዕምነትና ማንነት በመነሳት ነው ። ኢትዮጵያዊ ማንነትን፤ ሀገራዊ እሴትንና ብሄራዊ ኩራትን የተላበሰ ትግል የሚያካሂድ ሁሉ፤ በመጨረሻው ስዓት ድል አድራጊ መሆኑ ፤ የታሪክ ሃቅ ነው ።
ለሥርዓት ለውጥ መታገልና ፤ ለውጥን ለግንጠላ ማመቻቸት ፤ እጅግ የተለያዩ ናቸው ። ለመገንጠል ሲባል ብቻ ፤ ለውጥን የሚያራግቡ፤ የሀገር ህልውና ተፃራሪዎች መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋል ። በለውጥ ስም የሀገር ጥፋት፤ በዴሞክራሲ ስም የሕዝብ ጉዳት፤ በሥልጣኔ ስም የባኅል ብክለት እንደተፈፀመ የሀገራችን የቅርብ ትዝታ ነው ። ያ እንዲደገም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ጭራሽ አይፈልግም።
ከዚህ ተመክሮ በመነሳት፤ ለውጥን ፤ ለሀገር አንድነትና ለሕዝብ ነፃነት ማስገኛ ማዋል ካልተቻለ ፤ ትርፉ ኪሳራ ነው። ኪሳራ እንዳይመጣ ከተፈለገ ፤ የኢትዮጵያ አንደነት ኃይሎች ፤ የለውጡን ሂደት እየተቆጣጠሩ ሊመሩት ይገባል ። ከተባበሩ ደግሞ ፤ ክህሎትና ኃይል ይኖራቸዋል ። መላው ሕዝብም ከጎናቸው ይቆማል ። የመላውን ሕዝብ ድጋፍ ያገኘ ትግል ደግሞ የመጨርሻ ድል አድራጊ መሆኑ አይቀርም ።
በዛሬ ወቅት ፤ የብሄር ድርጅቶችና ኅብረ-ብሄር ድርጅቶች በመስቀለኛ መንገድ ላይ መሆናቸውን ሊገነዘቡት ያስፈልጋል ። ሁለት ምርጫዎች እፊታቸው ቀርበዋል ።
1ኛው ሳይተባበሩ ቀርተው ሀገሪቱ እንድትፈራርስ ማድረግ፤ እነርሱም መና ሆነው መቅረት። ያለዚያ ፤
2ኛው ተባብረውና ተስማምተው ሀገሪቱን ከመበታተን አድነው፤ በጋራ አብሮ መኖርን ማረጋገጥ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ብቸኛውና ዓይነተኛው ምርጫ ሁለተኛው ነው !
page1image20648 page1image20808 page1image20968 page1image21128
1
በአንዲት ሀገር ፤ አብሮ መኖር ፤ የጋራ ሀብትን በጋራ እየተጠቀሙ እንዲኖሩ ያስችላል ። ሀብትና ጉልበት፤ ሥልጠኔና ዕድገትም የሚገኘው አብሮ በመኖር ነው። የዛሬው ዓለም አብሮ ተባብሮ ከመኖር በሚያገኘው ትርፍ፤ ተጠቃሚ መሆኑን በተግባር እያሳየ ይገኛል ። ወያኔን እናሰወግዳለን ብለው የተነሱ ኃይሎች ሁሉ ፤ አብሮ የመኖርን ጥቅም በሚገባ ተረድተው ፤ አብሮ የመታገልንና ለድል መብቃትን ተገንዝበው፤ አስቸኳይ የሆነ ወሳኝ ርምጃ ሊወስዱ ሁኔታው ያስገድዳቸዋል ።
" ሁኔታውን እያየን ወደ አደላው እናዝንብል " የሚለው ስሌት፤ እበላ-ባይነት እንጅ፤ ውጤት አያስገኝም ። ራስን አዋርዶ፤ ሀገርን ከመበታተንና ሕዝብን ከመከፋፈል በቀር እርባና አያስገኝም። ወያኔም እንደዚህ ያለውን ሁኔታና አካሄድ በሚገባ ተጠቅሞበታል ። አሁንም ሁኔታውን ለመጠቀም ፤ እየተፍጨረጨረ ይገኛል ።
ሀገራችን እንደ አንዲቷ ኢትዮጵያ ፤ ዜጎቿም ፤ እንደ አንድ ሀገር ዜጎች ሆነው እንዳይቀጥሉ ሲባል ለአላፉት ሩብዕ ( 1/4) ምዕተ- ዓመት ፤ ተገንጣይና አስገንጣይ ሥራውን ሲሰራ ቆይቷል ። ዛሬም በአዳዲስ ዘዴዎች እየተጠቀመበት ነው ። ለከርሳቸው ያደሩ እስካሉ ድረስ ደግሞ ፤ እበላ ባዮችን በገፍ ማግኘት አይቸግርም ።
"እበላ ባይ በዝቶ፤ዳኛውነገርሰሚ፤
እኛስ ሄድንላችሁ ይብላኛ ለከራሚ ።
"
እያሉ ተስፋ በመቁረጥ ሀገርን እየጣሉ መሰደድ፤ መፍትሄ አልሆነም ። የሚበጀው፤ ወያኔን እየተጋፈጡ፤ ለውጥ ማምጣት ነው ። ለውጥ ደግሞ ያለ መሥዋዕት አይመጣም ። አይገኝም ።
የሰሞኑ ሕዝባዊ አመፅ ዓላማ ፤ ያተኮረው በዘረኛው አገዛዝ ላይ መሆኑ ባይካድም ፤ ኢትዮጵያን ለመበታተን ፍላጎት ያላቸው ክፍሎች ግን ፤ የየራሳቸውን ትርጉም ሊሰጡት ይሯሯጣሉ ። የወያኔው አንቀፅ 39 በተግባር ለመተርጎም ጊዜው እየደረሰ ነው ብለውም ይመኛሉ ። የሀገራችንን ኅልውና በሚመለከት፤ በእነርሱና በወያኔ መካከል፤ የዓይነትና የዓላማ ልዩነት የለም። በአስገንጣይና በተገንጣይ መካከል፤ ምንስ ልዩነት ሊኖር ይችላል ?
እዚህ ላይ ያለውን የፖለቲካ ዳማ ጨዋታ፤ በሦስት ረድፎች ተፋጠው የቆሙ መሆናቸውን ማስተዋል ተገቢ ነው እንላለን ።
1. መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ 2. ወያኔ እና
3. ተገንጣይ ክፍሎች ናቸው ።
. የኢትዮጵያ ሕዝብ ለውጡን የሚፈልገው፤ የኢትዮጵያና የሕዝቧ አንድነትና ነፃነት ተጠብቆ፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሰፍኖ ፤ በሠላም መኖርን ነው። በሠላም መኖር ከተቻለ ደግሞ፤ ዕድገትና ብለፅግና መምጣቱ አይቀርም ።
. ተገንጣይ/ አስገንጣይ ክፍሎች፤ የኢትዮጵያ መኖር አለመኖር ጉዳያቸው አይደለም። የሕዝቧ አብሮ መኖር/ አለመኖር አያሳስባቸውም ። የመገንጠል ዓላማቸው ግቡን እስከመታላቸው ድረስ፤ የኢትዮጵያ ጉዳይ ፤ አያስጨንቃቸውም ። እንዲያውም፤
"ኢትዮጵያ፤ ጥቁርውሻውለጅ " ብለንስንረግማት፤ ርግማኗ ደርሶ ሄደናል ጥለናት ።
እያሉ ይጨፍራሉ ።
. ወያኔም፤ የመጨረሻው እቅዱ እንዲሳካለት ይፍጨረጨራል እንጅ ፤ ለኢትዮጵያ እንደ አንድ ሀገር መኖር አለመኖር ቅንጣት ያህል አያስብም ፡፡ አይጨነቅም ። እንዲያውም ፤ ይግረማችሁ ብሎ፤
" ድሃን ኹኒ አቲ አዲ ፤ኻብ ቕድም መፍራስኺ" አንች ሀገር፤ ከመፍረስሽ በፊት ደህና ሁኚ ። ብሎ ይሸመጥጣል ። ይኮበልላል። " ኢህአዴግ መራሹ " ሲሉለት የነበሩ አሽቃባጮቹም ፤ ያጨበጭባሉ ።
ሻዓቢያ የመገንጠል ተስፋው እውን የሆነለት ፤ በኢትዮጵያ መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ ወይም ሺግግር መካሄድ በነበረበት ወቅት እንደነበር፤ የትላንት ትዝታ ሆኖ ቀርቷል። " መሃሉ ሲደፈርስ ፤ ጠረፉን አስወስድ " በሚል ስሌት ፤ ገንጣይና አስገንጣይ ተባብረው ኢትዮጵያን ቆርሰው ፤ ግባቸውን መትተዋል ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን፤ የበይ ተመልካች፤ የፀፀት አንጓች፤ የጥቃት ሰለባ፤ የሀዘን እምባ አፍሳሽ ሆኖ ቀርቷል ። ይህ እንዳይደገም ከተፈለገ፤ " የኢትዮጵያ አንድነት ኃይሎች ናቸው " የሚባሉት ክፍሎች ሁሉ ተሰባስበው ግልፅና ቆራጥ አቋምን ይዘው አንድ ቁም ነገር መስራት ይጠብቅባቸዋል ። ኢትዮጵያን ከአደጋ ለማትረፍ የመጀመሪያ ርምጃ ሊሆን የሚገባው፤ የአንድነት ኃይሉ መሰባሰብና ኅብረት መፍጠር መሆኑ አከራካሪ አይሆንም ።
ይህ ካልሆነ፤ ያለፈው ተመሳሳይ ደባ ላለመፈፀሙ ምን ዋስትና ይኖራል ? በአሁኑ ወቅት የትኛውስ የአንድነት ኃይል ነው ሀገሪቱን ሊይድናት የሚችለው ? እረ ለመሆኑ፤ የተጠናከረና የተዋሃደ ፤ የኅብረት ኃይል አለ እንዴ ? ተብሎ ቢጠየቅ፤ አዎንታዊ መልስ ማግኘት ይቻላልን ?
የሕዝቡን አመፅ፤ " ብረቱ ሲግል ቀጥቅጠው " በማለት ለመንገጠል ያሰፈሰፉት ሁሉ፤ ላይና ታች እያሉ በመፈራገጥ ላይ ናቸው። ወያኔና ሻዕቢያም፤ " ለአንድ መቶ ዓመት የመደብንላቸው የቤት ሥራ ፤ ገና በሩብዕ- ምዕተ-ዓመት ውስጥ፤ እየተጠናቀቀ ነው " ብለው ጮቤና ጓይላ እየረገጡ ይገኛሉ ። ልክ "በኩርናውን በጭብጥ ምስር እንደለወጠው " ከንቱ ልጅ ፤ ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን በጎሳ ለምድ ለመለወጥ የሚሯሯጡም እንዳሉ እየታየ ነው። ነገ ከነገ ወዲያ፤ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል እያቆበቆቡ ያሉት ሁሉ ፤ ጊዚያችን ደርሷል በማለት ላይ ናቸው ።
ይኅንን በሚገባ ያልተረዱና ያልተገነዝቡ ሌሎች ክፍሎችም ፤ በውቂው -ደብልቂው ቀውስ ራሳቸውን ለማስገባት እየሞከሩ ይገኛሉ፡። የሚያስከትለውን አደጋ ግን በቅጡ የተረዱት አይመስልም ። ኢትዮጵያዊውን ሕዝባዊ አመፅ ፤ ዜግነታቸውን ለካዱ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዲመች ለማድረግ መሞከር ፤ " አየ በሬው ሞኙ፤ ሳሩን አየህ እንጅ ገደሉን ሳታይ ! " እንደሚባለው፤ ሀገሪቱን ወደ ባስ አደጋ ከመጣል የተሻለ ሊሆን አይችልም ። ያ ግን የሚሆን አይመስልም።
ምክንያቱ፤ ምንም እንኳን፤ ዛሬ ፤ ይህ እንዳይሆን የሚከላከል የተደራጀ የአንድነት ኃይል አለ ለማለት ባይቻልም፤ መላው የሀገሪቱ ሕዝብ ግን ፤ ኢትዮጵያ እንድትበታተን ይፈቅዳል፤ ይስማማል ማለት አይደለም ። እጅ እግሩንም አጣጥፎ ዝም ብሎ ያያል ማለት አይደለም።
ይህ ስለተባለ ግን፤ የሀገሪቱ የፖለቲካ ኃይል ሚዛን፤ ወደ አንድነት ኃይሉ ማድላት ካልቻለና የወያኔ አገዛዝ መዋቅሮቹ እስካልተሽመደመዱ ድረስ ፤ የሀገራችን ህልውና በአደጋ እንደተከበበ ይቆያል። ሕዝብ ካልተደራጀ በቀር፤ በጀግንነቱ ብቻ አስተማማኝ ውጤት ሊያስመዘግብ አይችልም ።
የአንድነት ኃይሉ፤ ማዕካላዊ ሚና የሚጫወትበት ሁኔታ ካልተፈጠረ፤ ወያኔ የፖለቲካ ድራማውን ከማሽከርከር ወደኋላ አይልም ። የሕዝቡን አመፅ ፤ በማዕከላዊ ዕዝና ቁጥጥር፤ በቀጣይነትና በሁለገብነት የሚመራው ኃይል እስከሌለ ደረስ ፤ ፋይዳ ሳያመጣ ተንገጫግጮ እንደሚቀር ያለፈው ተመክሮ አሳይቷል።
ይህንን ሕዝባዊ አመፅ፤ በሀገር-አቀፍ ደረጃ ሊመራው የሚችል የአንድነት ኃይል መኖሩ አንገብጋቢና ወሳኝ ነው። የተናጠል መግለጫዎችና ውግዘቶች ብቻቸውን ውጤት አያስመዘግቡም ። ወያኔ ሊንበረከክ የሚችለው ፤ በቀጣይነት
በሚካሄድ ሕዝባዊ አመፅ ብቻ ነው። ይህንን አመፅ የሚመራው ኃይል መኖር አለበት። ይህ ኃይል ደግሞ፤ የኢትዮጵያ አንድነት ኃይል ብቻ ነው!
ይህ ሳይሆን ቀርቶ ፤ የሕዝብን ግብታዊ አመፅ በመመልከት ብቻ ፤ ወያኔ ሊወድቅ ነው ! ይችን ዓመት አያልፋትም ! በሚል አጉል ተስፋ መብተክተክ ውጤት አያስገኛም ። ይልቁንም ትጥቅ አስፈች ሊሆን ይችላል። ለዚህ ፍቱን መድኅኒት የሚሆነው፤ የኢትዮጵያ አንድነትና ዴሞክራሲያዊ ኃይላት ተሰባስበው፤ ኅብረት በመፍጠር፤ የሕዝቡን አመፅ አስተባብረው የመሪነቱን ሚና መጫወት ሲችሉ ነው። ይህ እውን እንዲሆን፤ አሁንም ያልታከተ ጥሪያችንን አናስተላልፋለን !
ኢትዮጵያን ማዳን የሚቻለውም ፤ የተባበረ ትግል ሲካሄድ ለመሆኑ ማንም አይጠራጠር
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኖራለች

No comments:

Post a Comment