Tuesday, January 26, 2016

FINOTE RADIO


oፍኖተ ዴሞክራሲ ራድዮ  አጫጭር ዜናዎች
o ረሀቡ ህፃናትን እየፈጀ ነው፡፡
o በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝባዊ አመጽ እንደቀጠለ ነው፡፡
o ባሳለፍነው ሳምንት የግል ባንኮች ድንገተኛ የብር እጥረት ውስጥ እንደገቡ ታወቀ፡፡
o የድንበር ማካለሉ በዚህ በያዝነው አመት እንደሚጠናቀቅ በሱዳን እየተነገረ ነው፡
o ከሙስሊሞች እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የታሰሩት ተፈረደባቸው
o ወያኔ በአሜሪካ የሚኖሩ ተቃዋሚዎች ተላልፈው እንዲሰጡት ለአሜሪካ ሰነድ እንዳዘጋጀ ተወቀ፡፡ o የወያኔ የመዋጮ ወረርሽኝ ሠራተኞችን እያማረረ ነው
o የአውሮፓው ፓርላማ ውሳኔዎችን አሳለፈ
o የቀድሞ የናይጄሪያ ባለስልጣኖች 9 ቢሊዮን የአገሪቷን ሀብት መዝረፋቸው ተነገረ
o የደቡብ ሱዳን የአንድነት መንግስት እንዲመሰረት የተያዘለት ቀነ ቀጠሮ ሳይከበር ቀረ
  •   ባሳለፍነው ሳምንት በሐዲያ ወደ ሆሳዕና እና ወደ ተለያዩ ከተሞች የሚደረጉ የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች ለአንድ ቀን ዝግ ሆነው መዋላቸውንና በኋላም መጀመራቸውን ከአካባቢው ከተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል። ትራንስፖርት ሊቋረጥ የቻለው የአካባቢው ባለስልጣኖች የጣሉትን ተጨማሪ የቅጣት መመሪያ በመቃወም አሽከርካሪዎች አድማ በመምታታቸው ሲሆን መመሪያው የተነሳ መሆኑ ሲገለጽ የትራንስፖርት አገልግሎቱ የጀመረ መሆኑ ታውቋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በሃዲያ ዞን ከሚገኘው ከዎቻሞ ዪኒቨርስቲ ተይዘው የተወሰዱት 8 ተማሪዎች የት እና በምን ሁኔታ ላይ መሆናችው ስላልታወቀ ቤተሰቦቻቸው በከፍተኛ ሀሳብና ጭንቀት ላይ የወደቁ መሆናቸውን ከአካባቢው የተገኙ ዜናዎች ገልጸዋል። በዲላም ዩኒቨርስቲ ውስጥ ከተማሪዎቹ እኩል ቁጥር ያለው የአግአዚ ጦር ተሰማርቶ ጥበቃ እያካሄደ ሲሆን በተማሪዎቹ ላይ ከፍተኛ በደል ከመፈጸሙ ባሻገር የእጅ ስልኮቻቸውንም የቀማ መሆኑ ታውቋል።
  •   ጥር 11 ቀን 2008 ዓም በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች የጥምቀት በዓል በደመቀ ሁኔታ የተከበረ ሲሆን የአዲስ አበባ በዓል አከባበር ላይ በወያኔ የደኅነነት ኃይሎች ተጥለቅሎ እንደንበር ከስፍራው የመጣው ዘገባ ገልጿል። ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነና የሲቪል ልብስ የለበሱ የወያኔ የደህንነት ተቀጣሪዎች አስተናባሪ የሚል ባጅ ደረታቸው ላይ ለጥፈው ታቦቱን አጅቦ ወደ መንበሩ ለማስገባት ከሚንቀሳቀሰው ሕዝበ
ጥር 15 ቀን 2008 ዓ.ም
dollar
ክርስትያን ጋር በመቀላቀል ሲያስፈራሩ የነበሩ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል። በአዲስ አበባ እና በአካባቢዎ ባሉ አንዳንድ ቦታዎች ተቃውሞ የሚያሰሙ ወጣቶች የተደበደቡና ተይዘው የታሰሩ መሆናቸው የታወቀ ሲሆን በተለያዩ ከተሞችም የጥምቀት በዓሉን አስታኮ በወያኔ አገዛዝ ላይ ተቃውሞ ሲሰማ መዋሉ ተነግሯል። በማግስቱ ጥር 12 ቀን 2008 ዓ/ም በአዲስ አበባ ተከብሮ በዋለው የቃና ዘገለሊላ በዓል ላይ የበዓሉ ታዳሚ በነበሩት ምዕመናንና በፖሊስ መካከል ግጭት ተነስቶ ለግዜው ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች በአካላቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸውና በፖሊስ ታፍነው የተወሰዱ መሆናቸውንም ከስፍራው የደረው ዘገባ ገልጿል። በተለምዶ ሾላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውን የየካ ቅዱስ ሚካኤል ታቦትን በማጀብ ወደ መንበሩ ለማስገባት ተሰባስበው የነበሩ ምዕመናን ባህላዊ ዘፈኖችና ጭፈራዎች እያደረጉ በሚጓዙበት ወቅት ለጭፈራ ማድመቂያ የያዙትን ዱላ በተለያዩ ስፍራዎች ቆሞ ይጠብቅ የነበረው የወያኔ የፖሊስ ኃይል ለመንጠቅ ሙከራ ሲያደረግ ከፍተኛ ግብግብ መከሰቱና ዱላቸውን የተቀሙት ወጣቶች እንደጀመራችሁ ጨርሱን በማለት ፖሊሶችን ማጥቃት በመጀመራቸው ግጭት ተፈጥሮ በርካታዎች የመፈንከት አደጋ እንደደረሰባቸውና አንዳንዶቹ ሲሮጡ የእግር ወለምታ አጋጥሟቸው ጉዳት እንደደረሰባችው ተያይዞ የመጣው ዜና ይገልጻል። ብዙዎች ታስረው በመኪና ተጭነው ወደ አልታወቀ ቦታ የተወሰዱ ሲሆን ከፖሊስ አባላት መካከልም ጉዳት የደረሰባችው እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሳሳቢነቱ እየጨመረ የሄደው ሊምፎማ በመባል የሚታወቀው በሰውነት ውስጥ የሚገኙ የሊምፍ አካላትን የሚያጠቃና የደም መበከልንና መመረዝን የሚያስከትለው በሽታ አርሶ አደር ገበሬዎችን በወረርሽኝ መልክ እያጠቃ መሆኑን ከሀኪሞችና በጤና ላይ ምርምር ከሚያካሄዱ ወገኖች መረዳት ተችሏል፡፡ ከጥቁር አንበሳና ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባዎች ለህክምና የሚመጡ አብዛኛዎቹ ገበሬዎች ሊምፎማ በተባው በሽታ የተጠቁና የበርካቶቹም ሁኔታ ወደ የደም ነቀርሳነት ያደገ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል፡፡ ይህ በሽታ ሊከሰት የሚቸው በዘር፣ ከቀዶ ህክምና በኋላ እንደ ጡት ነቀርሳ የመሰለው፣ ጡቱ በቀዶ ህክምና ከተወገደ በኋላ የተለመደ ሲሆን በአረም ማጥፊያ አሲድም ሊከሰት እንደሚችል ይታወቃል፡፡ እንዲህ ያለውን በሽታ ሊያስከትሉ የሚችሉ የአረም ማጥፊያ አሲዶችን ከይዘታቸው መለየትና እንዳይገቡ እግድ ማውጣት ሲገባ ወደ አገር ውስጥ በወያኔ የንግድ ድርጅቶች አማካይነት እንዲገቡ መደረጋቸውና ገበሬው በግዴታ እንዲገዛና እንዲጠቀም መደረጉ ለዚህ ለገዳዩ ሊምፎማ በሽታ እንዳጋለጣቸው ማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ ደግሞ ለተቃውሞ የወጡ ዜጎችን ከመረሸን በላይም የከፋ መሆኑን ከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎች በመቆጨት ያስረዳሉ፡፡
ከገሙ ላይቀር ብስብስ ነው እንዲሉ ወያኔን እንደ ጋማ ከብት እያገለገለ ያለው ኃይለማርያም ጥር 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ከመንግስት ተብየው ካዝና ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት ልጁ ሀናን በቤተ መንግስት መዳሩ ታወቀ፡፡ ይህን ወጪ የሰርጉ እድምተኛ የነበረው የሳዑዲው ደላላ አላሙዲ ወጪውን ሙሉውን የሸፈነ መሆኑን ከቅርብ ምንጮች ተረድተናል፡፡ አስቀድሞ ከወያኔው ገንዘብ ሚንስትር የወጣውን ገንዘብ የወያኔ ቁንጮዎች ለመቀራመት እንዲያመቻቸው ወደ “መለስ ፋውዴሽን” የዘረፋ ቋት እንደሚገባ መወሰኑ ታውቋል፡፡ ይህ ሁኔታ በ1997 ዓ.ም. ሟቹ መለስ ዜናዊ የጋጠ ወጥ ልጁ የሰመሀልን 12ኛ ክፍል ማጠናቀቅ አስመልክቶ በሸራተን ሆቴል የነበረውን የውስኪ ግብዣ ያስታውሳል፡፡ የመለስ ልጅንም ወጪ የሸፈነው አላሙዲ መሆኑ በወቅቱ ይነገር እንደነበር ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡ ዘረኛ አምባ-ገነኖች በመጠሪያ ስማቸው ቢለያዩ እንጂ በምግባራቸው ያው እንድ ናቸው።

File Photo
File Photo
 በወያኔ መገናኛ ብዙሀን እስከ ዛሬ ድርቁን የዝናብ እጥረት፣ እርሀቡን የምግብ እጥረት በማለት በሕዝብ ስቃይና ሞት ላይ ለፖለቲካ ትርፍ ብቻ በማሰብ የቃላት ጨዋታ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ ከአምስት መቶ ሺ በላይ የተለያዩ ከብቶች በድርቁ ምክንያት እረግፈዋል፡፡ ህፃናት እርሀቡና ጥሙ ጠንቶባቸው ዋይ ዋይ እያሉ እንደዋዛ፣ እንደ ቅጠል እየረገፉ ነው፡፡ ወያኔ ነጋ ጠባ እያሰላ ያለው ከርሀቡ የሚገኘውን ትርፍ ነው፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት ከተለያዩ አገራት የተውጣጣ የህፃናት አድን ድርጅቶች ቡድን እርሀቡ ህፃናትን፣ ነፍሰጡርና የሚያጠቡ እናቶችን በከፍተኛ ሁኔታ እያጠቃ መሆኑን መገንዘብ ችለዋል፡፡ ህፃናትና ነፍሰጡር እናቶች በርሀቡና በጠኔው እየረገፉ ነው፡፡ የርሀቡን አስከፊነትን የታዘበው የህፃናት አድን ድርጅቶች ቡድን በመጨረሻ ያሰማው 1.4 ቢሊዮን ዶላር በአስቸኳይ ከለጋሽ አገራትና ከግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ማግኘት ካልተቻለ የርሀቡ ግድያ ከመልቀም ወደ ማጨድ ሊሸጋገር እንደሚችል ስጋታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ከዚህ ከተጠየቀው የገንዘብ መጠን መገንዘብ የሚቻለው እርሀቡ እጅግ ዘግናኝና ከግምት በላይ እንደሆነ ነው፡፡ በርሀብ አለጋ እየተገረፉ ያሉትን ገበሬዎች የወያኔ የንግድ ድርጅቶች የማዳበሪያ እዳ ከርሀቡ የተረፉ ከብቶቻቸውን ሽጠው እንዲከፍሉ እያስገደዷቸውና እያንገላቷቸው መሆኑን አውቀናል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የማዳሪያ እዳ ያልከፈለ አባወራ እርዳታ እንዳይሰጠው መታገዱ ይታወቃል፡፡ በንጉሡ ዘመን ድርቅ ሰብሉን ክው አድርጎ አድቆት ያዘረዘረው እንኳ ከአፈር ተደባልቆ እየታየ ባለ እርስቶቹ ገበሬው የግድ እንዲገብር ያስገድዱት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ይህንን ግፍ ወያኔ ደገመው፡፡ እርሀቡ አድማሱንና መከራውን እያሰፋ ነው፡፡ ወያኔ ደግሞ ከረሀቡ የፖለቲካና የገንዘብ ትርፉ ለማካበት እየማሰነ ነው፡፡
በተያያዘ ዜና ካሪታስ ኢንተርናሽናል የተባለው የካቶሊክ የአርዳታ ሰጭ ድርጅት ባለስልጣኖችን በወቅቱ እርዳታ ካልተኘ በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ከፍተኛ የሆነ እልቂት ሊከተል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ድርቁ ባጠቃቸው አካባቢዎች ከ90 ከመቶ በላይ በመቀነሱ ምክንያት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ በድርቅና ረሃብ እየተጠቃ መሆኑን ባለስልጣኖቹ ገልጸው ካሁኑ ጀምሮ በእርዳታው ላይ መረባረብ ካልተቻለ የዛሬ ሰላሳ አመት ተፈጥሮ የነበረው ዓይነት የእልቂት ሁኔታ ሊደገም እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
በሌላ በኩል ለእርዳታ የመጣውን እህል በተለያየ መንገድ በመዝረፍ ላይ ያሉት የወያኔ ባለስልጣኖች ሕዝቡን እያስመረሩት መሆኑ እየተስተዋለ ነው። በዚህ ሳምንት ባገኘነው ዜና መሰረት በመቂና በሞጆ ከተሞች መካከል በሚገኝ የህብረት ስራ ማህበር መጋዘን ውስጥ ተከማችቶ የነበረ ስንዴ ጨለማን ተገን በማድረግ አስራ አምስት በሚሆኑ በበቅሎ በሚጎተቱ ጋሪዎች ተጭኖ ወደ ጥቁር ገበያ ለሽያጭ ሲወጣ የተመለከቱ መሆናቸውን በአካባቢው የነበሩ የአይን እማኞች የገለጹ ሲሆን የስንዴው ብዛት እስከ ሁለት ሺህ ኩንታል ሊጠጋ እንደሚችል ተናገረዋል። ድርቅና ረሃብ ያጠቃቸው ወገኖች እርዳታ በማጣታችው ወደ አዲስ አበባ እየፈለሱ መሆናችውም እየታየ ነው። ሰሞኑኑ ዘጋቢያችን በመርካቶ ራጉኤል ቤተክርስትያን አካባቢ ያነጋገራቸው ወገኖች ከትግራይና ከወሎ ቦረና የመጡ መሆናቸውን የገለጸሉት ሲሆን የእርዳታ ስንዴ እንሰጣችኋለን ከሚል ተስፋ በስተቀር የተሰፈረልን እህል ባለመኖሩ ልጆቻችን ሲሞቱ ከማየታችን በፊት በራችንን ዘግተን መምጣቱን መርጠናል ብለውታል።
  •   ወያኔ በማን አለብኝነት የደነገገውን የአዲስ አበባን የቆዳ ስፋት እሰከ አንድ መቶ ሃያ ኪሎ ሜትር ድረስ ለመለጠጥ መደንገጉን በመቃወም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያለ ማቋረጥ በተካሄዱ አመጾች ወያኔ ለይስሙላ ድንጋጌው መነሳቱን ቢለፍፍም የተጀመረው አመጽን ሊገታው እንዳልቻለ የታወቀ ነው፡፡ ወያኔ በርካታ ህጻናትን፣ ወጣቶችን፣ ገበሬዎችን፣ ሴቶችን ገድሎ ሲያበቃ የማስተር ፕላኑ መሰረዙን ማውራቱ ለሕዝብ ያለውን ንቀት ሚያሳይ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ ወደ አምስት ሺ የሚጠጉ ሰዎች በየእስር ቤቶች በግፍ እየማቀቁ ባለበት የማስተር ፕላኑ መሰረዝ ከፖለቲካ ቧልትነት አይዘልም የሚል አስተያየት እየተሰማ ነው፡፡ አሁን እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ ወያኔ እራሱን እንጂ ሕዝብን አያታልልም የሚል መንፈስ የተላበሰ መሆኑን መገንዘብ ችለናል፡ ፡ የማስተር ፕላን መሰረዝ በግብር መገለጽ ይገባዋል የሚሉ ወገኖች እንደሚሉት የንፁሀንን ደም ያፈሰሱ የአጋዚ ጦር አባላት ለፍርድ ሲቀርቡና ቤተሰቦቻቸው ለተገደሉባቸው ቤተሰቦች ተገቢ የህይወት ካሣ ሲከፈል፣ የታሰሩት በአጠቃላይ ሲፈቱና ተገቢ ካሣ ሲከፈላቸው መሆኑን አበክረው ያስረዳሉ፡፡ ለዚህ ነው ሰሞኑን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሕዝባዊ አመጹ እየቀጠለ ያለው፡፡
  •   በዚህ በዘረኛው ወያኔ ዘመን አብዛኛው ሥራ የሚከናወነው ጥናት ላይ ተመርኩዞ ሳይሆን እንዲሁ በደፈናው ነው፡፡ አንዳንዶች በጥናት ላይ እንደተመሰረቱ የሚነገርላቸው ቢሆኑም ዝም ብለው አረጋ ሰራሽ በመሆናቸው ጥናቱን አካሄደ የሚባለው ክፍል እራሱ መጠናት እንዳለበት የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ባለፈው ሳምንት ምንጩ ከዓለም የገንዘብ ድረጅት የተገኘ ብድር እንደሆነ የሚነገር የውጪ ምንዛሪ በመገኘቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በድንገት በፋብሪካ ሥራ ለተሰማሩ ድርጅቶች ምንዛሪ እንደሚሰጥ በማሳወቁ የግል ብንኮች ላይ ከፍተኛ ቀውስ እንደፈጠረ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የባንክ ባለሙያዎች እንደሚሉት እንዲህ ዓይነቱ የግድየለሽነት አሰራር ከበስተጀርባው ተንኮል ያዘለ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ የባንኮችን በነፃነት የመፎካከር ሁኔታን በእጅጉ ያውካል፡፡ ለምሳሌ ከአንድ የግል ባንክ ብቻ በአንድ ቀን 1.3 ቢሊዮን ብር እንዲወጣ መደረጉ ለግል ባንኮች ከፍተኛ ፈተና መሆኑን ባለሙዎቹ ያስረዳሉ፡፡ በአንድ ቀን ከተለያዩ ባንኮች ወጪ ተደርጎ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲገባ የተደረገው ገንዘብ 4.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን ይህን ያህል ገንዘብ በአንድ ጊዜ ማውጣት የባንኮቹን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እንዳወከው ተውቋል፡፡
ethiopia sudan Boarder
  •   ወያኔ በተደጋጋሚ ከሱዳን ጋር ምንም ዓይነት ድንበርን ለማካለል የተካሄደ ድርድር መኖሩን ቢክድም በሱዳን በኩል ግን በማስረጃ እየቀረበ መሆኑን መረዳት ተችሏል፡፡ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር 725 ኪሎ ሜትር እርዝመት ያለው ድንበርተኛ መሆኗ ታወቃል፡፡ ወያኔና የአል በሺር መንግስት በሟቹ በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ከሁለቱ አገራት የተውጣጣ ጉዳዩን የሚያጠና የቴክኒክ ቡድን ተመስርቶ አንደነበር የሱዳኑ ጋዜጣ “ሱዳን ትሪቡን” የተሰኘው ዘግቧል፡፡ ይህ የተጀመረው ጥናት እንዲቀጥል አል በሺር 2014 ዓ.ም. የወያኔ የይስሙላውን መሪ ኃይለ ማርያምን ማሳሰቡን አስታውሷል፡፡ ሱዳን ከኢትዮጵያ ይገባኛል የምትለው መሬት ሰቲት፣ አትባራ እና ባላሳም የተባሉ ወንዞች የሚፈሱበት 600 ሺ ሄክታር ስፋት
ያለው፣ እየታረሰ ያለ ለም መሬትን አንደሆነ ጋዜጣው አትቷል፡፡ ይህ ቦታም ለገደሀሪፍ አዋሳኝ የሆነ ሲሆን አል-ፋሻጋ በመባል የሚታወቅ እንደሆነም ሱዳን ትሪቡን ጠቁሟል፡፡ ይህ የተጠቀሰው ስፋት የአዲስ አበባን ስፋት ከአስር እጅ በላይ እንደሚያጥፍ የስነ-ምህዳር አዋቂዎች ያስረዳሉ፡፡ ወያኔ አገር አጥፊ ነው ሲባል አገርን ይሸጣል ማለት ነው፡
  •   “ድምጻችን ያሰማ” የሚሉ ሕዝበ ሙስሊሙ በወያኔ ላይ በአንድነት እንዲነሳ የሚቀሰቅሱ ጽሑፎችን በትነዋል፣ የታሰሩትን የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን ለማስፈታት ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ 16 የእስልምና እምነት ተከታዮች ተፈረደባቸው፡፡ ማክሰኞ ጥር 10 ቀን 2008 ዓ.ም. የወያኔ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንወጀል ችሎት በተከሳሾቹ ላይ እጃቸው ከተያዘበት አንስቶ የሚታሰብ 7 አመት ጽኑ እስራት ፈረደባቸው፡፡ ተከሳሾቹ 15 ወንዶችና አንዲት ሴት ሲሆኑ እነሱም ኤልያስ ከድር፣ ሙባረክ ከድር፣ ቶፊቅ መሐመድ፣ ፌይሰል አርጋው፣ አብዱልመጂድ አብዱልከሪም፣ እስማኤል ሙስጠፋ፣ ሬድዋን አብደላ፣ አንዋር ሱልጣን፣ አብዱላዚዝ ፈቱዲን፣ ጃፋር ደጋ፣ ፋሩቅ ሰይድ፣ መሪም ሀያት፣ መሐመድ አሊ፣ መሐመድ አይለየን፣ አክበር ስልጣን እና ሙአዝ ሙደሲር ናቸው፡፡ የወያኔው አቃቤ ህግ ያተተባቸው በአዲስ አበባና በወልቂጤ፣ የታሰሩትን የሙስሊሙ ህብተሰብ ችግሮችን ለመፍታት የተቋቋመው ኮሚቴ አባላት፣ በወያኔ በመታሰራቸው እነሱን ተክቶ ለመሥራት በህቡዕ በመንቀሳቀሳቸው እንደሆነና በየመስጂዱ ውስጥ ውስጡን ሕዝበ ሙስሊሙ በወያኔ ላይ እንዲያምጽ በመቀስቀሳቸው በመሆኑን አትቷል፡፡ ወያኔ በየጊዜው ሙስሊሞችን ያስራል ትግላቸው ግን እንደቀጠለ ነው፡፡ ይህ የሙስሊም ኢትዮጵያውያንን ትግል ሕዝበ ክርስቲያኑም እንደሚደግፈው የታወቀ ነው፡፡
muslim addis
  •   ወያኔ በአሜሪካ የሚኖሩ ተቃዋሚዎችን አድኖ ወደ ሀገር ቤት የአሜሪካ መንግስት እንዲልክለት እረቂቅ ሰነድ አዘጋጅቶ ማጠናቀቁን ከውስጥ አወቆች መረዳት ተችሏል፡፡ ከዚህ ቀደም በሌሉበት እስራት የፈረደባቸውና በ”ሽብርተኝነት” የወነጀላቸውን ሁሉ አሜሪካ እያሰረች እንድትልክለት መሆኑን ከሰነዱ መረዳት እንደሚቻል እነዚሁ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ ይህ ድርጊት አወቅሽ አወቅሽ ሲሏት መጽሐፍ አጠበች እንደሚባለው ያለ መሆኑን የሚገልጹ የዓለም አቀፍ ህግ አዋቂዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከወያኔ የደህንነት ምንጮች የተገኘው ጉዳዩ የሚያነጣጥረው በተለይ በኢሕአፓ አባላት ላይ እንደሆነና በተለያዩ ጊዜያት የተቃውሞ ሰልፎችንና ስብሰባዎችን በመምራትና በመስተባበር የሚታወቁትንም ያካትታል፡፡ በተለይ በአሜሪካ በወያኔ ኤምባሲ የወያኔን ባንዲራ አውርደው የኢትዮጵያ ባንዲራን የሰቀሉትን፣ በስብሀት ነጋና በሬድዋን ላይ የተቃውሞ ድምጽ ያሰሙት ተላልፈው እንዲሰጧቸው ከሚጠየቁት በመጀመሪያው እረድፍ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
  •   ደርግን በመዋጮ ብዛት ይኮንነው የነበረው ወያኔ መዋጮ በግዳጅ የሠራተኛውን ጉሮሮ እያነቀ በመውሰድ ተወዳዳሪ አልተገኘለትም፡፡ የዓባይ ግድብ መዋጮ አላቆም በማለቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በመርገምነቱ እንጂ በሲሳይነቱ መታየት አቁሟል፡፡ ከዚህ ከጥር ወር ጀምሮ የሚቀቆረጠው የጤና
መድንም እዬዬ እያሰኘ ነው፡፡ ህክምና ወደ ሸቀጥነት በወረደበት አገር በገንዘብ ያልተገኘ ህክምና በመድንማ ዘበት እንደሚሆን የተፈታ ህልም ነው፡፡ አብዛኛው ሰው እንደሚለው ወያኔ በመድን ስምም የሚሰበስበው ለዛው ለመከረኛው ዓባይ ገድብ እንደሆነ ነው፡፡ የዛሬ አስር ወር ግድም ወያኔ ምርጫ ተብዬውን አስታኮ የደሞዝ ጭማሪ እንደሚያደር ቀለምዶ ሲያበቃ እንኳን ጭማሪው ወሬውም የለም፡፡ ሠራተኛው እንዳይተፍስ በስብሰባ ስም አበል እየፈለ አፉን ማስያዝ የሚል ዘመቻ ተይዟል፡፡ የወያኔ አባላትም በተጣለባቸው የግዴታ የአባልነት መዋጮ እየተማረሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም በፈቃደኝነት ከ50 እስከ መቶ ብር ይከፍሉ የነበረው ቀርቶ በደሞዝ መክፈያው ላይ በመትከል አራት ከመቶ ከደሞዛቸው እንዲቆረጥ በመወሰኑ ቅሬታቸውን በማልጎምጎም እየገለጹ መሆኑንም ተረድተናል፡፡ የውሀ፣ የመብራት ታሪፍ በቅርቡ ጨምሯል፡፡ በተመሳሳይ መልኩም የዕለት ተዕለት የምግብ ሸቀጦች ዋጋ እየናረ ይገኛል፡፡
 ባለፈው ሳምንት የአውሮፓው ህብረት ምክር ቤት (ፓርላማ) ሰሞኑን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የሕዝብ አመጽ አንተርሶ ጠንካራ ውሳኔዎች ማስተላለፉ ተገለጿል። የአውሮፓው ሕብረት ምክር ቤት ባለፉት ሁለት ወራት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በመቃወም ተካሄዱትን ሕዝባዊ አመጾች ለመግታት ወታደሮች ከ140 ሰዎች በላይ መግደላቸውን፤ የአዲስ አበባ መስፋፋት ብዙ አርሶ አደሮችን ያፈናቀለ መሆኑን፣ በአካባቢው የሰብአዊ መብት ጥሰት መኖሩን፤ የወያኔ የጸጥታ ኃይሎች አሸባሪዎች ናቸው በሚል በርካታ ሰልፈኞችን ማሰሩን፤ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎችን ጋዜጠኞችንና ጦማሪያንና ይዞ እያሰቃየ መሆኑና አንዳንዶቹንም በሽብረተኞች ክስ በማፈረድ በእስር ቤት ማሰቃየቱንና በአንዳንድ አካባቢዎች የሚያካሄደው ጦርነትና ጭፍጨፋ አስከፊ መሆኑን የተረዳ መሆኑን ገልጿል። በተጨማሪ የወያኔ አገዛዝ ባለፈው አመት ግንቦት ወር ላይ ያካሄደው ምርጫ በአፈናና በማስፈራራት የተካሄደ መሆኑና አርሶ አደሮች ለም ከሆነው መሬታቸው ላይ ተነቅለው መሬታቸው ለባዕዳን መሰጠቱን ምክር ቤቱ መረጃ የደረሰው መሆኑን በመጠቆም ጉዳዩ ያሳሰበው መሆኑ አብራርቷል። ወያኔ በሕዝብ ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ረገጣና አፈና እያካሄደ በየአመቱ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ማግኘቱ አግባብ አለመሆኑን ምክር ቤቱ ገልጾ በርካታ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።፡ በውሳኔውም ኦሮሚኛ ተናጋሪዎች በሚኖሩበትና በሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶች የወያኔ ወታደሮች በዜጎች ላይ ያካሄዱትን ገደብ የለሽ ግድያ፤ የሰብአዊ መብት ረገጣ፤ ህገ ወጥ እስራትንና ሰቆቃዊ ድርጊቶች፤ የመናገርና የመጻፍ መብት መታገዳቸውን እንዲሁም ወንጀለኞች ለፍርድ ሳይቀርቡ በነጻ መለቀቃቸውን አውግዟል። በመንግስት የጸጥታ ወታደሮች እየተደረጉ ያሉት የአፍናና የግድያ ተግባሮች ባስቸኳይ እንዲቆሙና መብታቸውን በመጠቀም ድምጻቸውን በማሰማታቸው ብቻ የታሰሩ ተማሪዎች፤ አርሶ አደሮች የፖለቲካ ተቃዋሚዎች፣ ምሁራን ጋዜጠኞችና ጦማራውያን በሙሉ ባስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል። በተደረጉት ግድያዎች ላይ ነጻና ገለልተኛ በሆነ መንገድ ምርመራና ማጣራት እንዲካሄድና ጥፋተኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጥሪ አስተላልፏል። ወያኔ የዓለም አቀፉንና የአፍሪካ ህብረትን የሰብአዊ መብት ቻርተርና ድንጋጌን ማክበር ያለበት መሆኑን ገልጾ በሚዲያ ላይ እያካሄደ ያለውን የሞገድ አፈናና እንዲያነሳና ነጻ የሆኑ ሚዲያዎች ስራቸውን በነጻ የሚሰሩበት ሁኔታ እንዲፈጠር ጠይቋል። አልአግባብ እየተካሄደ ያለው የሰፈራ
ፕሮግራም ምክር ቤቱን ያሳሰበው መሆኑን ገልጾ በአካባቢዎቹ የሚደረጉት የልማት ስራዎች ሕዝብ ጋር ተመካክሮና ተስማምቶ መሆን እንደሚገባው አሳስቧል። የአውሮፓ አገሮች ለልማት ስራዎች ለወያኔ የሚሰጡት እርዳታና ብድር ከአገሪቱ የሰብአዊ መብት ሁኔታ ጋር መመጣጠን ያለበት መሆኑን ገልጾ የአውሮፓው ኅባረትና አባል አገሮች በንጹሐን ዜጎች ላይ እየተወሰደ ያለውን ርምጃ ኮንነው ድርጊቱን ለማስቆም አስፈላጊውን ተጽእኖ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል።
  •   የናይጄሪያ የማስታወቂያ ሚኒስትር ትናንት ሰኞ ጥር 9 ቀን 2008 ዓም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ የናይጄሪያ አገረ ገዠዎች፤ ሚንስትሮች የንግድ ተቋም ባለቤቶች ፤ የባንክ እና የመንግስት ባለሥልጣኖች 9 ቢሊዮን ዶላር የአገሪቷን ገንዘብ አለአግባብ የዘረፉ መሆናቸውን ገልጸዋል። የተሰረቀው ገንዘብ 1.35 ትሪሊዮን የናይጄሪያ ናይራ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸው ይህም 36 ሆስፒታሎች ለመስራት ወይም 4000 ተማሪዎችን እስከዩነቨርስቲ ድረስ ለማስተማር የሚያስችል ገንዘብ እንደነበር ገልጸዋል። ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑን ገልጸው ባሁኑ ወቅት አስፈላጊው ርምጃ መወሰድ አለበት ብለዋል። ሚኒስትሩ የተዘረፈውን ገንዘብ ዝርዝር መረጃም አቅርበዋል። ገንዘቡ ተዘርፏል የተባለው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ2006 እስከ 2013 በአብዛኛው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ሲሆን የቀድሞ የጸጥታ አማካሪ የነበሩት ሚስተር ዳሱኪ 2 ቢሊዮን ዶላር ዘርፈዋል ተብለው መወንጀላቸው ይታወሳል። በአሁኑ ወቅት የናይጄሪያ ተቃዋሚ ፓርቲ የሆነው ፒፕልስ ዴሞክራቲ ፓርቲ የአሁኑ እርምጃ የፓርቲውን አባላት ለማጥቃት ሆን ተብሎ በስልጣን ላይ ባለው ኦል ፕሮግሬሲቭ ኮንግሬስ በተባለው ፓርቲ የተጠነሰሰ ሴራ የሚል ውንጀላ ሲያቀርብ ባለስልጣኖቹ ደግሞ የአገሪቱን ገንዘብ የሰረቀ የማንኛውም ፓርቲ አባል ለፍርድ ይቀርባል ብለዋል።
  •   በደቡብ ሱዳን ከሁለቱም ተጻራሪ ወገኖች በተውጣጡ ወኪሎች እንዲመሰረት ስምምነት ተደርሶበት የነበረው ጊዜያዊ የአንድነት መንግስት በተግባር እንዲውል የተሰጠውን ቀነ ቀጠሮ ያሳለፈ መሆኑ ተገለጸ። የአንድነት መንግስቱ እንዳይመሰረት እንቅፋት ከሆኑት አቢይ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የስልቫኬር መንግስት ከስምምነት ውጭ የአካባቢ አስተዳደሮችን ከ10 ወደ 28 ከፍ ማደረጉንና 28 አስተዳዳሪዎች መሾሙን በሪክ ማቻር የሚመራው የአማጽያን ኃይል በመቃወሙና ባለመቀበሉ መሆኑ ታውቋል። በዕቅዱ መሰረት ከሁለቱም ተጻራሪ ኃይሎች የተውጣጣ የአንድነት መንግስት ከጥር 13 ቀን 2008 ዓም በፊት መመስረት ነበረበት። ለስምምነቱ መፍረስ ሁለቱም ወገኖች እርስ በርሳቸው የተወነጃጀሉ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ ሁለቱም ተጻራሪ ኃይሎች ጦርነቱን በማስፋፋት እንዲሁም በጦር ሜዳዎች የጅምላ ርሸና በማካሄድ፤ የያዟቸውን ዜጎች ዱካ በማጥፋት፤ በቡድን ሴቶችን በመድፈር፤ ለወሲብ አገልግሎት ሴቶች አግቶ በመያዝ ፤ አስገድዶ ጽንስን በማስወረድና የመሳሰሉ ወንጀሎችን በመፈጸም በኩል ሁለቱም ወገኖች ተጠያቂዎች ናቸው ብሏል።
 ባለፈው ሳምንት በምዕራብ ፓኪስታን በቻርሳዳ ከተማ በሚገኘው ባቻ ከሃን ዩንቨርስቲ ላይ ታጣቂዎች ባካሄዱት የቦምብ ጥቃት 19 ሰዎች መገደላቸውና ከ50 በላይ መቁሰላችወን የፓኪስታን ፖሊስ ገልጿል። አጥቂዎቹ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ተኩል ሲሆን የዩኒቨርስቲውን የጀርባ አጥር በመዝለል ጥቃቱን መሳሪያ በመተኮስና ቦምብ በማፈንዳት መፈጸማቸው የተገለጸ ሲሆን ከዩኒቨርስቲው የጸጥታ አባላት ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል። አንድ የታሊባን ወታደራዊ ኮማንደር ጥቃቱ የተወሰደው በታሊባን መሆኑን ጠቅሶ እርምጃውም በቅርቡ የፓኪስታን ወትደራዊ ኃይል ለወሰደው ጥቃት የአጸፋ እርምጃ ነው ብሏል። በሌላ በኩል የታሊባን ቃል አቀባይ የሆነው ለቢቢሲ የዜና ወኪል በሰጠው ቃል ድርጊቱ ከሙስሊም ሃይማኖት ትእዛዝ ውጭ የተደረገ የሚወገዝ ድርጊት በማለት ታሊባን እንዳልፈጸመው አስተባብሏል።

No comments:

Post a Comment