Sunday, February 14, 2016

ዝምታ ለበግም አልበጃት!.... ዴሞክራሲያ ቅፅ 41 ቁ. 4


ዴሞክራሲያ ቅፅ 41 . 4
ጥር 2008 ..
ዝምታ ለበግም አልበጃት!
page1image2136
አምባገነኖች ሥልጣንን ለመቆናጠጥ የሕዝብን ፈቃድ ወይም ድጋፍ ፈልገውና ጠይቀው አያውቁም። የሚፈልጉት የሕዝብን ታዛዥነትና ጸጥ -ለጥ ብሎ መገዛትን ነው። የሕዝብን ፍላጎት ሰምተው፤ የልቡን ትርታ አዳምጠው፤ ፍላጎቱን ተከትለው፤ አግባብተውና በጋራ አቅጣጫ ላይ ተመሥርተው ማስተዳደርን አያውቁበትም። የበታችና የበላይ ሰልፍን የሚያረጋግጡት በኃይል ወይም በጠብ-መንጃ ብቻ ነው። በኃይል በመቀጥቀጥ ካልገበርክ፤ ተቃውሞህን ካላቆምክ፤ የባሰ ይመጣብሃል በማለት “ ማሸማቀቅ” ሰብዓዊ ክብርን መግፈፍና ማዋረድ የአምባገነኖች ተፈጥሯዊ መለያችውና ባህሪያቸው ነው።
በዚያን ዘመን የተፈጠረው ተራማጅ ትውልድ ፤በቁጭትና በቆራጥነት ተደራጀቶ ለመታገል የተነሳው፤ ኢትዮጵያ ሀገሩ፤ ከጥገኘነት ፤ከምፅዋተኝነት፤ከድኽነትና ከኋላ ቀርነት ተላቅቃ በሠላምና በእድገት ጎዳና እድትራመድ በመመኘት እና የአዲስ ሥርዓትን ምሥረታ አስፈላጊነትን በማመን ጭምር ነበር። ይህ የ1960ዎቹ ተራማጅና ለውጥ ፈላጊ የተማሪዎች እንቅስቃሴ፤ ጭቆና ፤ብዝባዛና የግፍ አገዛዝ ከሚወዳት እናት አገሩ ተወግዶ፤ ሕዝባዊ የሆነ ሥርዓት ተመሥርቶ ፤ሕዝቡ ፤ ለተሻለውና ለሚገባው ኑሮና ክብር እንዲበቃ ለማድርግ ብሔር፤ ፆታ፤እድሜና ሃይማኖት ሳይገድበው፤ በአንድነት የተሰባሰበ ትውልድ ነበር።
ለአገሩ ቀናዒ ፤ለሕዝቡ አሳቢ የነበረውን የዚያን ጀግና ትውልድ ሕዝባዊና ሀገራዊ እንቅስቃሴ ለመግታት ሲል በወቅቱ የነበረው አገዛዝ መሪዎቹን አስሮና ገደሎ ፤የተማሪውን አመፅ ፅጥ! ቀጥ! አድርጋለሁ በሚል እብሪት ተወጥሮ ነበር። ይሁንና የኢትዮጵያ ሕዝብ የግፍ ጽዋ ሞልቶ በመፍሰሱ የተነሳ፤ በዩኒቨርስቲና በሁለተኛ ደረጃ ት/ ቤት ተማሪዎች ተቀስቅሶ በአዝጋሚነት የተጀመረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጭምር በመቀጣጠሉ፤ የሕዝቡ ብሶት ገንፍሎ የአገዛዙን ግብዐተ-መሬት እንዲፋጠን አድርጎታል።
የአፄውን አገዛዝ የተካውና የየካቲቱን ሕዝባዊ እንቀሰቃሴ ያጨናገፈው አምባገነኑ ወታደራዊ ቡድን፤ የራሱን ሥልጣንና ኢትዮጵያን ለይቶ ማየት የተሳነው ፤ፍፁም የሥልጣን ጥማቱ ዓይኑን የጋረደው ስለነበረ ፤የደርጉ መሪ፤ ሀገር ጥሎ እስከፈረጠጠበት ቀን ድረስ ለሥልጣኔ ያሰጋኛል ያለውንና ፤ በሀገራችው ምድር የፓለቲካ፤ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፍትህን እውን ለማድረግ ተደራጅቶ የታገለውን ተራማጅና ለውጥ ፈላጊ ትውልድ በጭካኔ መትሯል ። ርዝራዦቹ ዛሬም ወንጀላቸውን ደብቀውና ክደው በጥፋት ጎዳና ተሰማርተው ይገኛሉ ።
ደርግን የተካው ዘረኛው ወያኔም፤ መሠረተ-ዓላማው ዘር፤ ጎሳና መንደር በመሆኑ፤ የአገሪቱን አንድነትና ሉዋላዊነት በፅኑ ከማስደፈሩም ሌላ ተጋብቶ፤ ተዋልዶ፤ ተዛምዶና ተጎራብቶ ለዘመናት የኖረውን ሕዝብ በጎጥ፣ በክልልና በሃይማኖት በመከፋፈል ፍራቻና ጥላቻ እንዲነግሥ አድርጓል። ቃልና ተግባሩ ለየቅል የሆነው ጠባብ ብሔርተኛው ቡድን በዴሞክራሲ ስም አፈናን፤ በእኩልነት ስም ጭፍን አድሎዎን፤ በአንድነት ስም ክፍፍልን ፤ በፍቅር ስም ጥላቻን፤ በሀገሪቱ በማንገስ በዓለም ዙሪያ አቻ በሌለው ደረጃ ጎጠኛና ጭፍን አምባገነንነቱን በተጭባጭ አስመስክሯል።
የኢትዮጵያን የኅብረተሰብ ታሪክ ስንመረምር ፤ እስካሁን ድረስ፤ መንግሥት የተባለው ተቋም የሕዝቡን መሠረታዊ መብቶች እየገፈፈ ፤ ሕዝቡ መብቱን ማጣት ብቻ ሳይሆን፤ ባለመብት መሆኑን ጭምር እንዳያውቅ ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ኃይልን መሠረት ያደረገው የሥልጣን ለውጥም መንግሥት ነኝ ለሚል እብሪተኛ ሁሉ የበላይነትና ፤ፍጹማዊነትን ሲያከናንብ ተመልክተናል። የአንድ መንግሥት የሥልጣን መሠረቱ የሕዝብ ፈቃድና ምርጫ መሆን አለበት የሚለው መሠረታዊ መርሕ በአምባገነኖችና ጎጠኞች እየተጨፈለቀ ቀጥሏል። በመሆኑም፤ በሀገራችን የሕዝብ የፖለቲካ ሚና፤ ከአምባገነን አገዛዝ ነፃ የሚያወጣ አመፅ ብቻ እንደሆነ አምኗል። እንኳን ሕዝብ ሳይፈልገውና ሳይመርጠው የተሰየመ ኃይል ይቅርና ሕዝብ ራሱ የመረጠውንም መንግስት ቢሆን ሙሉ አመኔታና ፍጹም ሥልጣን ሊሰጠው አይገባም ። ሥልጣን ብዙዎችን ያበላሻልና መቆጣጠር መቻል የሕዝብ ኃላፊነትና ግዴታም ነው ።
ዛሬ በአገራችን እየተካሄደ ያለው የሕዝብ አመፅ/አምቢተኛነት የወያኔ ቱባ ቱባ መሪዎችና ካድሬዎቹ እንደሚወተውቱት ”በጥቂቶችና በአሽባሪዎች የተጠነሰሰ ሴራ” ሳይሆን ፤መብቱ የተረገጠውና የተገፋው ሕዝብ በተፈጥሮ የተጎናጸፋቸውን መሠረታዊ የሆኑ የማይገረሰሱ የሰብአዊ እና የዴሞክራሲያዊ መብቶቹን ለማስከበር የሚያደርገው ሕጋዊ ትግል አካል መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። ከጥገኝነት ከምፅዋተኝነት፤ ከድኽነትና ከኋላቀርነት ለመላቀቅ ከተፈለገ፤ እድገት መኖር አለበት። እድገት ደግሞ ከሰላም በፊት አይመጣም። ሰላም ደግሞ በወያኔ ቸርነት አይወርድም። የሰላም ጠንቅ የሆነውን ወያኔን ለማስወገድ ኢትዮጵያን ለሚሉ ሁሉ አንድነት የግድ ያስፈልጋል። የአንድነትም ሆነ የአብሮ መኖር ቁልፉና መሠረቱ ፅንፈኝነትን አስወግዶ ሕዝቡ ርስ በርሱ በእኩልነት፤ በወንድማማችነት /(በእህትማማችነት) ና በዴሞክራሲ ተቻችሎ አብሮ መጓዝ ሲችል ነው።
ዛሬ በአገራችን መልከዓ-ምድር የሚደረገው ትግል በሕዝቡና በጥቂት ጎጠኞችና የሥልጣን ጥመኞች መካከል ያለ የሕግ የበላይነትንና የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነትን ለማረጋገጥ የሚደረግ ትንቅንቅ ነው ። የዚህ ሕዝባዊ ተጋድሎ ማሳረጊያው ደግሞ የአገር ሉዓላዊነትና የሕዝብ እኩልነት የሰፈነባት ዴሞክራሲያዊና ሕገመንግሥታዊ ኢትዮጵያን በትግል እውን ማድረግ ነው። ዴሞክራሲን ለማስፈን ፤ የሕዝብን ወሳኝነት፤ የሕግ የበላይነትና የሀገር ሉዓላዊነት እንዲኖር የግድ ይላል። የመንግሥት ዓይነት፤ የመንግሥት ሥልጣንና የመሪዎች ሥልጣን ዘመን ፤ በሕዝብ የሚወሰን እንጂ፤ መንግሥት በሕዝብ ላይ ተወዝፎ ሲያሰኘው “መብት” ሲያሰኘው “ጥይት” እያለዋወጠ እንዳሻው እየወሰነ ፤ የሕዝቡን ጥቅም እየሽጠ፤ የሕዝቡን ፍላጎትና መብት እየረገጠ ሊገኝ አይችልም። ዴሞክራሲ በሕዝብ ልዕልና እንጂ ባልተመረጡ አልኩ ባይ ሞግዚቶች የሚገለጥ አይደለም ። በተጨባጭ እንደሚታየው የሕዝብ ወሳኝነትና ልዕልና በአፍ ጢሙ ተደፈቷል። ያለፈውም ሆነ ያለው አገዛዝ በሕዝብ ስም የሚገዙ አምባገነን አገዛዞች ነበሩ፣ ናቸውም ማለት ትክክል ነው ።
ዛሬ በኢትዮጵያ የሚታየውና የሚሰማው የዲሞክራሲና የጎህ ብሥራት ሳይሆን ፤ የአስከፊ አምባገነናዊ ‘አለሁ! ምን ትሆናላችሁ?’ የሚል የሰቆቃ ደወል ነው ። ዴሞክራሲ “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ” እንደሆነ አለ ።ወያኔ ሁሉን እንዳሻው ወሳኝ፤ መብትን ገዳቢ እኔ በቀደድኩላቸሁ ጎዳና ብቻ ተራመዱ ባይ ነው። ዛሬም እንደትናንትናው ሕዝቡ ከፖለቲካው መድረክ ፤ ከወሳኝነትና ከባለሙሉ መብትነት እንደተነጠለ ነው። ለመበቱም ካልታገለ፤ ወያኔ በያዘው የጥፋት ጎዳና ቀጣይ እንጂ የሚታረም አለመሆኑ ለሁሉም ዜጋ ግልጽ ነው። የሕዝብ የመቃወም መብት ሊከበር የሚችለው ተቃውሞን/ መብትን የነፈገውን አገዛዝ በመቃወም ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ እየተፈራረቁ የብረት ቀንበር ሲጥሉበትና ቁብ ሲሉበት የነበሩትን አምባገነኖች መሸከሚያ ጫንቃ አጥቷል። ባርነትን ያጸደቀ ትግሥትን፤ ውርደትን የተከናነበ ሠላምን ተቀብሎ መገኘት የሚጠብቅብት አይደለም ። በአጭሩ መብቴ ተገፈፈ በቃኝ፣ አልቻልኩም፣ አሻፈረኝ ያለ ሕዝብ ማመጽ መብቱ ብቻ ሳይሆን ግዴታውም ነው።
የሕዝብ የተቃውሞ መብት በትግል እንዲከበር በቅድሚያ ሕዝቡ የመንግሥት ሥልጣንና መሠረት እሱ ራሱ ሕዝቡ መሆኑን መቀበልና በመንግሥት የተቀማውን መብት “ቅዱስ መብቴ” የሚለውን ለማስመለስ ቆርጦ መነሳትን የግድ ይላል። “ ከመንግሥት ማን ተጋፍቶ!?” ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ” " ያለ አቅም መፈራገጥ ለመላላጥ” ወዘተ... እያሉ መብቱን የቀማውን ሕገ-ወጥ አገዛዝ ፈርቶ የመብቱን መገፈፍ ተቀብሎ መኖር፤ የአገዛዙ ባሪያ ከመሆን ማምለጥ አይቻልም።
ዛሬ ሕዝቡ በወያኔ ላይ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መብቱን ለማስከበር ነቅቶ የተነሳበት ወቅት ነው ማለት ይቻላል። ወያኔም ተደፈርኩ በሚል የሕዝቡን አመፅ ለማፈን የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛል። ወያኔ የሕዝብን ሥልጣን ቀምቶ በአፋዊ ሽንገላ ተሰማርቶ የተለየ ሐሳብን ያቀረበ፤ ተቃውሞን ያሰማ የሚያሳድድ የሚያፍንና የሚፈጅ መሆኑን ከቋራ እሰከሞያሌ፤ ከአራካ እስከግዋኔ፤ ከአርባጉጉ እስክ ጋምቤላ፤ ከሎቄ እሰከ ዲላ፤ከጎሞጎፋ እሰከ ሱሉልታ፤ ከአርሲ እስክ ሐረር፤ ከባሌ እስክ ወለጋ፤ ከኢሊባቦር እስክ ጎጃም፤ከከፋ እስክ ጎንደር፤ የፈሰሰውና ዛሬም እየፈሰሰ ያለው የንፁሐን ዜጎች ደም ህያው ምስከር ነው። ሕዝቡ በየጊዜው በወያኔ ላይ የሚያነሳቸው ተቃውሞዎች በተግባር የሚያሳየውና የሚያረጋግጠው ሕዝቡ በመሠረታዊ መብቱ ከቡር መሆን ማመኑንና ይህን የማይገረሰሰ መብትና ነፃነት ለማንም አሳልፎ ለመስጠት አለመፍቀዱን ነው። በመሆኑም ሕዝቡ በተቃውሞ እንቅስቃሴ መሰማራቱ የተገፈፈ ስብእናውን ለማስከበር እንጂ ሌላ ምክንያት ኖሮት አይደለም።ይህን ብዙ በደሎችን እንደ ምክንያት አቅፎ የተነሳን ሰፊ የሕዝብ ተቃውሞ በተወሰነ የግዛትም፤የብሔረሰብ ደረጃ ወስነውና አሽገው የደገፉ መስለው ሊያዳክሙ የሚጥሩ በወያኔም ሆነ በባእዳንም ኃይሎች መሰማራታቸውንም እናያለን ። ጠንቀቅ የሀገሬ ልጅ ማለቱ ወቅታዊና አስፈላጊም ነው ። የሕዝብን ትግል ገንጣዮች ሲጠቀሙበት ከዚህ ቀደም አይተናልና ።
የወያኔ መሪዎች ፍላጎት ሀ ና ፐ ወይም “አልፋና ኦሜጋ” ብቸኛ የመንግሥት ሥልጣን ባላቤት ሆነው እሰከወዲያኛው ለመኖር ነው። ወያኔዎች ጠብ-መንጃ ጨብጠው የያዙት ሥልጣን በኢትዮጵያዊያን ፈቃድ ተጠብቆ ሊቆይ እንደማይችል ጠንቅቀው ያውቃሉ። የሚያውጧቸው ሕጎችም እነሱ ሌሎችን ለመከፋፈል፤ ለማሰርና ለመግደል የሚገለገሉባቸው እንጂ ሕጋዊነትንትን ለማስከበር የሚያግዙ፤ ሕዝብን በሰላም ለማስተዳደር የሚያገለግሉ አይደሉም። የኢትዮጵያዊ ዜግነትን መብት በየጊዜው እየጨፈለቁ የገነቡት የዚህ ሕግ አልባ ሥርዓት መሠረቱ ነፍጣቸውና በየጊዜው ቆስቁሰው የሚያራግቡት ዘረኝነት ጭምር ነው። ኢትዮጵያዊነትን በዘር እርከን እየሸነሸኑ በተዋረድ የፈጠሩዋቸው ድንበሮች የሁሉም ብሔረሰቦች አስተዳደራዊ መልከዐ- ምድር ሳይሆኑ፤ አንዱ በሌላው ላይ በጥላቻ እንዲነሳ ለማድረግ ሆን ተብለው የተወጠኑ የጥቅም ልዩነቶች የሚደረጉባችው የዘረኝነት ወጥመዶች ናችው። “ያለዘሩትን አያበቅሉ” ያላበቀሉትን አያጭዱ” እደሚባለው ዛሬ በተጨባጭ ወያኔ እየደገሰልን ያለው ድግስ ማሳረጊያው ዋይታ የሞላበት ቤት እንዳይሆን ከወዲሁ ማርከሻውን ማሰናዳት የግድ ነው። ማርከሻውም ወያኔ በቀደደው ቦይ(በጎጥ) ተከፋፍሎ መፈሰስ/መታገል ሳይሆን እንደ የካቲት 1966ቱ ጎጥ ፤ሃይማኖትና ፆታ ሳይገድቡን በኅብረትና በአንድነት ተሰባስቦ መታገል ነው።
የሕዝቡም የተቃውሞ እንቅስቃሴ ፍሪያማ እንዲሆን ከተፈለገ፤ በየካቲት 1966 እንደታየው ሁሉንም ሕዝብ ወይንም አብዛኛውን የኅብረተስብ ክፍል ለማቀፍና ለማሳተፍ መቻል አለበት። ስፋቱ፤ ጥልቀቱና ቀጣይነቱም መረጋገጥ ይኖርበታል። ትግሉ በየፈርጁ ተካሂዶ ሊከሰት እንደሚችል የወቅቱ የኢትዮጵያም ሁኔታ እየጠቆመ ነው። ቀደም ሲል በአዲስ አበባና በአገሪቱ ትላልቅ ከተሞች የተደረገው የወረቅትና የተነፉ ፊኛዎች/ባሉኖችን የመበተን ተግባር፤ ብልጭ ድርግም ሲሉ የነበሩትን የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች፤ በሃይማኖት ተቋማት አካባቢ ሲካሄድ የቆይው የሃይማኖት ነፃነት ትግልና በቅርቡ ደግሞ፤ ያለማቋረጥ የቀጠለው በአዲስ አበባና በሌሎችም የአገሪቱ ከተሞች የሚታየው የወያኔን የመሬት ነጠቃ (የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን) በመቃወምና ፍትሃዊ አስተዳደርን በመፈለግ የተነሳው የሕዝብ ተቃውሞ ወዘተ..፣ የሚጠቀሱ ናችው። እነዚህን የሕዝብ ተቃውሞና እምቢተኝነት አስተሳስሮና አማክሎ ሕዝቡን ለወሳኙ ሕዝባዊ አመጽ እንዲነሳ ማድረግና ፤በተበታተነ ሁኔታ የሚስተጋባውን ሕዝባዊ ጥያቄ፤ ማኅበራዊ ፤ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ ቅርጽ አላብሶ ማታገል የሐቀኛ ፖለቲካ ድርጅቶች ኃላፊነት መሆኑን ኢሕአፓ በፅኑ ያምናል ።
የአገዛዙን እድሜ ለማሳጠር ጥንቃቄና ዘዴ በተመላበት መንገድ ፀረ- ወያኔ መፈክሮችን በየግድግዳው መፃፍ ፤ወያኔ በሚጠራው ስብሰባዎች አለመገኘት፤ የወያኔ አባላትና ደጋፊዎች ከሆኑ ንግድ ቤቶች አለመግባት ፤ አለመሽመት፤ አጠቃላይ ወያኔን በሁሉም መስክ በሚጎዳ መንገድ እቀባን ማድረግ፤ ሕዝብን የሚቅሰቅሱ የወያኔን ገበና የሚያጋልጡ ፅሁፎችን ማስራጨት፤ በየመሥሪያ ቤቱ የተሰገሰጉ ከሀዲዎችንና የአገዛዙን አገልጋዮች ማግለል፤ድርጊቶቻችውንም ማጋላጥና ሕዝብ እንዲያውቃቸው ማድረግ ወዘተ... ተገቢ ነው። ከዚሁ ጋር ጎን ለጎን የተቀናጀና ሥፋት ያለው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍን ማድረግ፤ ስፋት ያለው የተጠናና የተቀናጀ የሥራ ማቆም አድማ ማድረግም የሚጠቀስ ነው። የተማሪዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከአስተማሪዎች ጋር ተደጋግፎ፤ የመንግሥት ሠራተኛው ከላብ አደሩ ጋር ተቀናጅቶ ፤ ሁሉም የሃይማኖት አማኞች በአንድነት የጸሎት ጉባኤ ተባብረው ሀገራዊ ይዘት ያለው ትግል እንዲያካሄዱና ሕዝብ ተባብሮ በአገዛዙ ላይ በአንድነት እንዲነሳ ማድረግ ያስፈልጋል ። ሕዝብ ተባብሮ ክንዱን ካነሳ የሚበገረው ባለመሳሪያ አለመኖሩን ሩቅ ሳንሄድ ከራሳችን ከየካቲቱ ሕዝባዊ አመፅ መማር እንችላን። የሕዝብ ትግል ግን አንድነትን ካጣ፤ለወያኔና ለጠባቦች በር ከተከፈተ፤ የጋራ ትግልን ትቶ በጎጥ ደረጃ መክፋፍል ከሰፈነ መጨረሻው ከቶም የማይያምር መሆኑን ያየነውና ወደፊትም የምናየው ነው ። ድርጅቶች በ1983 የወያኔን የዘረኛ ፖለቲካ ጭራ ይዘው ሊጓዙ ሞክረው ያደረሱትን ጉዳትና የደረሰባቸውንም ውድቀት ማስታወስ ተገቢ ይሆናል ።
ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ የተጠላ፤ ደም የተቃባና በዚህም ምክንያት በጠብ-መንጃው ድጋፍ ብቻ ገደል አፋፍ ላይ ተንጠልጥሎ ያለ ድንጉጥ አውሬ ሆኗል። የሰብዓዊ መብት ረገጣው እያስነሳበት ያለውን የሕዝብ ተቃውሞና አመጽ ባዕዳን ጌቶቹ እንኳን ሊሽፍኑለት ከብዷቸዋል። በሥልጣን ላይ ያለ አምባገነን አገዛዝ በኃይል፤በፕሮፓጋንዳና በጥቅም ሕዝብ እየለያየ ለመግዛት የዘራው የክፍፍል መርዝ በአገሪቱ አንድነት ላይ የሚያጠላው ጥላ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ስለሆነም ይህ ዓይነቱን አምባገነናዊ ጎጠኛና አገር አፍራሽ አገዛዝን ለዘለቄታው ለማስወገድ አገር ወዳድ ዜጎች ሁሉ ያልተቋረጠና ያላሰለስ ትግል ማድረግ እንዳለባቸው ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የሌለባችው መሆኑን ኢሕአፓ ዛሬም በአፅንኦት ያሳስባል። በእብሪት ለተወጠረው አገዛዝ መፍትሔው ሕዝባዊ ትግል እንጂ ዝምታ አለመሆኑን ታሪክ በተደጋጋሚ አስተምሮናል።አስመስከሯልም።
በታሪካዊ ወቅቶች ላይ ሲደረስ ምን ላይ መጣን? ምንስ ማድረግ አለብን በሚል ጥያቄዎችን አቅርቦ ሐቁንና ተጨባጭ ሁኔታውን መሠረት ያደረገ ምላሽ መስጠት ይጠበቅብናል ። በምኞትና በጭፍን ወደፊት ለመሄድ አቅጣጫን ለመምረጥ አይቻልምና ። ያለፉት 24 ዓመታት ብቻ ሳይሆን ትግል በረጅሙ ለምንና እንዴት ተደናቀፈ፤ ለወያኔ ሥልጣን መምጣትና መደላደል እነማንስ ጉዝጓዝ ሆነው ተገኙ፤ቀጠሉ ብሎ መጠየቅም የግድ ይሆናል ። ዘረኛው ወያኔ ትግሌ ጸረ አማራ ነው ሲል በሚጋልበው የክፍፍል ጋሪ ላይ የወጡለት ሳይውል ሳያድር ለወያኔ ፍጹም ሥልጣን ሰለባ ሆነው አስከፊ ውድቀትን ተከናንበው እስካዘሬም ማንሰራራት አልቻሉም ። በመሆኑም ከስህተታቸው ተምረው በአንድነቱ ትግል ለመሳተፍ ከመጣር ፈንታ በሕዝብ ትግል ላይ ሊፈናጠጡና አቅጣጫ ሊያስቱ መጣራቸው ውጤት አልባ ሆኖ የሚቀር ነው ። በተግባርና በሚደረግ ትግል ዙሪያ የድርጅት ህልውና ሊከሰት ሲገባው ማንነቱ የሚገለጸው ከእኛ በላይ ታጋይ ለአሳር በማለት ድንፋታ ብቻ ከሆነ የሕዝብም ትግል ብዙ አመርቂ ውጤትን አያገኝም ።
ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ማለቱ እዚህ ላይ አግባብ ያለው ይሆናል ። የሚታገል ሕዝብ ለድል የሚያስፈልገውን አቅዋም፤ ዘዴና መሳሪያ ራሱ ማወቅ አለበት ። ድርጅቶችም የዚህ ግንዛቤ አራማጅ ወይም አስጨባጭ መሆን አለባቸው ። የሕዝብ የጋራ ትግል ማርከሻውና የሚጥለው መሆኑን በመረዳት ወያኔ ሕዝብን ከፋፍሎና አቃርኖ ሲገዛ ቆይቷል ። ትግሎችም ተነጣጥለው ብቅ እያሉ በተናጠል ተጠቅተዋል ። በቅርቡ እንኳን ሙስሊም ወገኖቻችን ያደረጉትን ረጅም ትግል ሌላው ክፍል ሊያጅበው ባለመፍቀዱ ወይም ባለመቻሉ ትግሉ የተጠቃው በእኛው ድክመት መሆኑን ማመን ይኖርብናል ። ለወያኔ መድኃኒቱ ለመከፋፈል ሲባዝን ክፍፍልን የሚያጠናክር ጩኸት ማሰማት ሳይሆን ማበርና አንደነትን ማጠናከር ነው ። ትግልን በጋራ ማካሄድ ነው ። ሁሉም በየፊናው ለራሱ ብቻ በሚለውና ዛሬ ጽንፈኞች የሚያሰሙት ጩኸት ለወያኔ ጮማው ነው፤ ይጠቅመዋል ። በጋምቤላ፤ በሸዋ፤በጎንደር፤በአዋሳ፤ ወዘተ ትግሎች ተፋፍመዋል። ግን አንዳንዶች የተደራጀ ትግል እያካሄድን ነው በሚል ቢዋሹም የተቀናጀና አንድነትን የያዘ ትግል አለመሆኑ የሚደበቅ አይደለም ። ወያኔ ይህን ክፍተት አግኝቶ ክፍፍልና መነጣጠልን ሊያሰፋ ሲጥር በዚሁ ከይሲ ዘመቻው ጀሌው ሆነው እያጀቡት ያሉ አሉ ። ምን ማድረግ አለብን ስንልም በየጎጣችን መወሰንና መብላላት ሳይሆን በዋናው ጠላት ላይ ማበር ነው። ይህን ወሳኝ ተልዕኮ የሚያደናቅፉ ሁሉ ወደዱም ጠሉም ሰልፋቸው ከወያኔ ጎን መሆኑን ቢክዱትም ሐቅ ሆኖ የሚያወግዛቸው ነው ።
በሕዝብ መሐል ያሉ ቅራኔዎች ዋነኛ ሳይሆኑ መለስተኛና በዴሞክራሲያዊ ውይይት የሚፈቱ መሆናቸውን በመካድ ወያኔ የእርስ በርስ ቅራኔን ተክሎ ውሃ እያጠጣ ተራራ ሊያሳክል ሲጥር ዓመታት አልፈዋል ። ጉዳቱንም ያነውና እያየነው ነው ። ቅራኔዎች የሚፈቱት በዴሞክራሲ እንጂ አርባጉጉና አሶሳ በደኖን ለመደጋገም በመምኘት ወይም በመጣር አይደለም ። ስለሆነም ዘሬ የሕዝብ ወገን የሆኑ ድርጅቶች ሚና መሆን ያለበት የሕዝብን አንድነት አጠናክሮ በዋናው ጠላት በወያኔ ላይ መረባረብ ነው፤ ከውሱን ጥያቄዎች ወደ ሀገር አቀፍና መሠረታዊ ጉዳዮች መሸጋገር ነው ፤ መተባበርና ማበር ነው፤ ወያኔን በጋራ ጥሎ የሕዝብን መብት የሚያስጠብቅና ሕዝብን ወደ ሚወክል ስርዓት ለመሄድ ሰላማዊ ሽግግር ማድረግ ነው። ከዚህ ውጪ አለ የሚባል መፍትሔ የለም ። የኢትዮጵያ ጠላቶች ሕዝብን በመከፋፈል፤እመጹን ውሱን አድርጎ በመከለል ለወያኔ ሊጠቅሙ ተነስተዋል። ተነሱ ታገሉ ስንል ቆይተናል ፡፤ ሕዝቡ ወያኔ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ ሲታገል መቆየቱ ደግሞ የታየ ነው። ምንም እንኳን አመጹ በተፈለገው ግለትና ስፋት ባይካሄድም የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ሕዝብ ወይም ወጣቱ እንደተኛ ተደርጎ የሚነገረውም ትክክል አለመሆኑ ሲገለጥ የቆየ ነው ። ወያኔን ብርክ እያስያዘ የመጣ ተቃውሞ በአሁኑ ወቅት በመካሄድ ላይ ስለሆነ ቀደም ብሎ እንዳቀረብነው ይህም እንዳይመታና እንዳይከሽፍ መደረግ ያለበትን ሁሉ በጊዜ መረዳቱና ተግባራዊ ማድረጉ አስፈላጊና አማራጭ የለሽ ነው ። ለዚህም ነው ትግሎቹ ይተባበሩ፤አንድነት ይስፈን፤ይቀናጁ ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የሚታገሉ ሁሉ በአንድነት ይታገሉ የምንለው ። ለዚህም ነው ይህን አቅዋምና አማራጭ የሚቃወሙና ከዚህ በፊትም ገብተንበት ከነበረው ማጥ ሊከቱን የሚቃጡትን በግልጽ የምንቃወመው። አለበለዚያ ተጠቃሚው ወያኔ ይሆናል። ተንገዳግዶ የነበረው ተመልሶ የሚቆምበትና ሕዝብን ሀገርን ማጥፋቱን የሚቀጥልበት ሁኔታ

ዴሞክራሲያ ቅጽ 41 4 ጥር 2008 .
ይፈጠራል። ወያኔ ሲሸፈንለት የቆየው ገበናው በአደባባይ ተሰጥቷል ። እኩልነትን አመጣ የተባለው ልብ ወለድ መሆኑ ታውቆበታል ። የኤኮኖሚ ዕድገትን አምጥቻለሁ በማለት ያሰራጨውን ፕሮፓጋንዳ ወደ 20ሚሊዮን የደረሰው ረሃብተኛ ውሸት ብሎ አጋልጦታል ። ሕዝቡ ደግፎታል ብለው ለሚዋሹትም ወያኔ በሥልጣን ላይ ያለው በአፈናና በግድያ እንጅ ሕዝብ ፀረ ወያኔ መሆኑን በማያወላውል መንገድ አሳይቷቸዋል ። ለሀገራችን አዲስ ብሩህ ምዕራፍን የሚከፍት አጋጣሚ አለልን ። አያያዛችን ውጤቱን ይወስናል ማለት ነው ። ከመንታ መንገድ መድረስ ዓይነት ነው--ወደ ተፈለገው መንደር ወይም ወደ አውሬ መፈንጫ ? ጉዞ በየት? አያያዝ እንዴት? የሕዝብ አመጽ ድሉን ሊቀማ እንደሚችል ለማወቅ የራስችንን የካቲትና በቅርቡም የግብጽ ሕዝብን ሰቆቃ ማየት ለምንችለው ግልጽ ነው ።
የተባበረ ትግል ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ! ወያኔ ላይ እንረባረብ !
ጠባቦችና ትምክህተኞችን እንቋቋም !
አመጽ ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ !! 

No comments:

Post a Comment