Monday, February 29, 2016

አባቶች በበሉት የልጆች ጥርስ አይለቅ / ቢንያም ግዛው ከኖርዌይ ኦስሎ

                                                    ቢንያም ግዛው ከኖርዌይ ኦስሎ

አባቶች በበሉት የልጆች ጥርስ አይለቅ

<<ለሚተኩቱ ሀገረ ይቅርላቸው>>
አምባገነኑ ቡድን ለራሱ ስልጣን ሸልሞ በኢትዮጵያ ላይ ቁብ ያለ ቡድን ነው። ትውልድ እንዲያቀረቅር እና አንገቱን ሰብሮ በለሆሳስ እንዲራመድ የኢትዮጵያዊውን መብት ገፍፎ በጫንቃው ላይ የጎጠኝነትን ቀንበር ጭኖበታል። የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ሀገር ወዳድ ልጆች የመስዋትነት ውሎ እና አዳራቸውን የሚያንቋሽሽ፣ፍፁም የአንድነት ስሜት የተለየውና ታሪካችንን የሚያናንቅ  የክህደት ተግባር እየፈፀመ ይገኛል። ይህ ግፍ አድራጊ የወያኔ ቡድን ካልተገረሰሰ፤በእያንዳንዱ መስመር እና አቅጣጫ ሀገራችን ፈፅማ እስክትቆስል እና እስክትደማ ድረስ  በበቀል ዱላው ትመታለች።  ስለሆነም  ምድራችንን ከዚህ ወረርሽኝ ማዳንና ማትረፍ የሚቻለው በጋራ ትግል ነው። መክሮ መታገል፣ በተሞክሮ ከአባቶች በመማር በአንደነት ዘብ መቆም።

የትግሉ ኦሜጋ እና ወሳኙም ምዕራፍ መተማመን፣መያያዝ እና መቀራረብ  ብቻ ነው።  ጠላታችን ስልጣን ከያዘበት ቀን አንስቶ በክልል፣በጎሳ፣በባንዲራ ለያይቶን በጥምረት እንዳልፋለመው መከፋፈልን በሁሉ ላይ አብቅሎ ለምዝበራው እንዲያመቸው አራርቆናል።   እንዲህ አይነት ሥነ-ልቦና እና አምለካከት ይዘን ሀገር ልንገነባም፣ልናለማም፣ነፃ ልናወጣም ከቶ አንችልም፡፡ በፅሞና መግባባት፣ መተማመንእና መወያየት ካልፈጠርን፤ብሎም አንድ ሀገር እንዳለው ወገን በዳይ ተበዳዩን ይቅርታ ጠይቆ ወያኔ የረጨውን መርዝ ለማርከስ እና ለማምከን እርስ በእርስ ይቅርታን በመቀባበል ጎሳችንን ለመገንባት ሳይሆን ለሀገር ቅድሚያ በመስጠት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የሆነው ጥንታዊት  ባንዲራችን በሁላችንም አደባባይ  ላይ  ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ  ክንዳችንን የምናስተባብርበት ጊዜው አሁን ነው። ይህ ካልሆነ ግን በደለኞች ነን። ይህም እያንዳንዱ ዜጋ በኢትዮጵያ ላይ የፈፀመው ትልቅ በደል ነው።ያለመቀራረብ እና ያለመመካከር በሽታ።

የኢትዮጵያ ግፋዊ አገዛዝ ኢትዮጵያውያንን በቋንቋና በክልል ከፋፍሏል። በዚህ የከፋፍለህ ግዛ ግፋዊ ሥትራቴጂውም ህዝቡን በተጨባጭተቆጣጥሮታል። በዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንም መካከል ሰርጎ የመግባት  ሥልቱን ቀጥሎበታል።በማህበራዊ መገናኛዎች ላይ አንድ ግለሰብ በተለያየ የብዕር ስም እና በበርካታ የማስመሰያ የፌስ ቡክ አካውንቶች ኦሮሞውን ከትግራይ ተወላጅ አማራውንም እንዲሁ ከሌላው ብሔር እርስ በእርስ በማጠላላት ደረጃ በተለይም በሀይማኖት ተቋማት ዘንድ ከፍተኛ መናቆር እንዲፈጠርና የኢትዮጵያን አንድነት በመሸርሽር፤ተቃዋሚ ፓርቲዋችንም እርስ በእርስ ተቃቅረው  ጠንካራ ተቃዋሚዎች ሳይሆኑ  ቁጥራቸውን  ለማመናመን እና ለማዳከም   የወያኔ ጆሮ-ጠቢዎችና ደጋፊዎች ኢትዮጵያውያንን ሥልታዊ በሆነ መንገድ ከፋፍለዋቸዋል። እንዲህ ተቋስሎ የተከፋፈለው የኢትዮጵያማኅበረሰብ የአገር ቤቱ አገዛዝ ውጤት እና ሥራ ነው። ክፍፍሉ ማኅበረሰቡን ለሌሎች በርካታ ችግሮች ተጋላጭም አድርጎታል። እየተከሰቱ ባሉማኅበራዊ ችግሮች ለምሳሌ ትምህርት ማቋረጥ፣ ሥራ አጥነት፣ እንደ እፅና ወንጀል፣ እንዲሁም አስከፊ የሆነ ተስፋ መቁረጥ እና የሀገር ፍቅር መቀዝቀዝ እንዲንሰራፋ ወያኔ በውስጥም ሆነ በዲያስፖራው መሀከል በረጫቸው መርዝ ተሸካሚ አስመሳይ ገፀባህሪያቶቹን ለብሰው በተሰለፉ ደጋፊዎቹ በጥልቀት ተሰማርቷል። 

የዳያስፖራው ፖለቲካዊ ሚና በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው ወያኔ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካእንዲሁም በአረብ ሀገራት ወ ዘ ተ . . . የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰቦችን ቆራቆስ የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው። የስራ በር እያመቻቸ፣የሀሰት የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በማሰልጠን፣ተማሪዎች፣ ጎብኚዎች በሚል ስምና እንዲሁም ግለሰባዊ የፖለቲካእንቅስቃሴዎችንና የማኅበረሰቡን መሪዎች በተመለከተ መረጃ ለማቀበል የሚያገለግሉትን ከኢትዮጵያውያን ማኅበረሰቦች መካከል በመመልመልጭምር ደጋፊዎቹን በሁሉ አቅጣጫ ሰግስጎ ኢትዮጵያዊውን እያባላው ይገኛል። ይህ አካሔድ ግን እውነተኛ የህዝባችን ባህሪ አይደለምና እያደር ሁሉም ነቅቶበታል እየነቃበትም ነው። 
በአለምም ዙርያ ስለ ኢትዮጵያ  ህዝብ የሚታወቀው  ትልቁ አስደማሚው ሀቅ አንድነታችን ብቻ ነው። ኦሮሞው ከትግራይ መዋለዱ፣ አማራው ከአፋር ዘር ማፍራቱ፣ ሰሜኑ ሲጠቃ ደቡቡ ዘብ መቆሙ፣ ሀረሪው ከጉራጌው ተጋብቶ ዘር ማብዛቱ፤ይህ ነው ኢትዩጵያዊነቱ። 

የነበረው ጥምረት እና አንድነት በወያኔ ሴራ ተንዶ ምድራችን እና ትውልዳችን ባለ ብዙ ጥላቻ ባለቤት እየተደረገ ነው። የባንዲራ ብዛት በአንዲት ሀገር ላይ ያለቅጥ ተውለበለበልን፣በየእለቱ በረሀብ እና በእርዛት የሚያልቀው ወገን  በየጊዜው ቁጥሩ ሲያሻቅብ ፣ ገበሬው መሬቱ እየተነጠቀ ለባዕድ ሲቸር፣ አዛውንቶች ሲጣሉ፣ ሴቶች ሲደፈሩ፣ህፃናት በጨቅላነታቸው ሲቀጩ፣ አንዱ ብሔር ብቻ በተለያዩ የግልና መንግስታዊ በሆኑ ተቋማት ላይ ሲፈናጠጥ፣መገለሉና አድሎው ነግሶ የተማረው እንዳልተማረ መንገድ ዳር ወድቆ ያልተማረው ፊደል ሳያውቅ የፕሮፌሰርነት ሹመቱን ሲጭን ወ ዘ ተ. . . የሆኑ ክፋቶች ሲከወኑ ፤ ከዚህ በላይ አገር መቀማት ከወዴት አለ? ይህ ወያኔ በኢትዮጵያ ላይ የዘረጋው የበቀል ዱላ ነው።  

በተለያየን እና መራራቃችን በየወቅቱ በጨማረ ቁጥር በሰምበራችን ላይ  ወያኔ የአርጩሜ  ማህተም ጀርባችን ላይ  እየመታ እንዲገዘግዘን እየተስማማንም ነው።  ከሁሉም በላይ እና አሳዛኙ ድርጊት በእቅፋችን ውስጥ ያሉ ህፃናት እና ቀጣዩ ትውልድ እኛ እያለፍንበት ባለው ጭቆናእንዲያልፉ፤በመለያየታችን ጠንቅ ምክንያት ሁኔታዎችን እያመቻቸን እንደሆነ በጽሞና መገንዘብ ያስፈልገናል።  ኃላፊነቱም የአሁን ጊዜ ነዋሪዎቹ የእኛ ነው፡፡
አባቶች በበሉት ፍሬ የልጆች ጥርስ ማለቅ የለበትም። ልጆች ባልበሉት በማያውቁት ዳፋ ያልኖሩበትን ዘመን እዳ ቀፍቃፊ በመሆን በአለም ሀገራት የታሪክ ማህደር ከተመዘገበችውና ከምትታወቀው ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ሌላ ፀጉረ ልውጥ ትውልድ በምድራችን ሳይበቅል ስለ ተከታዩ እና ሀገር ተረካቢው ትውልድ እንቀባበል፣እንዋሀድ፣እንስማማ እንማከር። 

ነብር በቆዳው ቢዥጎርረጎር በውጫዊነቱ እንጂ ፤በውስጡ ግን አንድ ነው። ይህንን ነው ከኢትዮጵያ ጋር መፅሐፉ አነፃፅሮ ያስቀመጠው።ኢትዮጵያም የብዙ ጎሳ የብዙ ቋንቋ የደጋግ ቤተሰብ ክምችት ብትሆንም ሁሉን አጋብታ አዋልዳለችና ለመገንጠልም፣ለመለየትም ፣ለመክፈልምእጅግ አዳጋች ነው። ዥንጉርጉርነታችንም በውስጣችን ተዳፍኖ የተቀመጠውን አንድነት ሊደብቀው ከቶውንም አይችልም። ብዙዎች ስንሆንአንድ ነን።እንደዚያ ተሰርተናልና ሊገነጥሉን ሲያስቡ የሚያመን ህዝቦች ሆነናል። ስለ አፍሪቃ አንድነት የምታወራ አንዲት ኢትዮጵያ ትላንት በመጣ ጠላት ልትቆረስ እና ልትመዘበር ታሪኳ ተረት ተረት ሊሆን ከቶውንም የተገባ አይደለም። 
ከባእዳን ወራሪዎች ጋር ለዳር ድንበሯ የተዋደቀ ህዝብ የነበራት ኢትዮጵያ እና በሌሎች አገሮች ያሉ ነዋሪዎች በመተማመን፣ በመቀራረብታግለው የጭቆና ሥርዓቶችን መገርሰስ ከቻሉ ፤ ዛሬም እንደ ጥንቱ በአንድነት ታግለን ከወያኔ ምድራችንን ነፃ ለማውጣት የማንችልበትምንም አይነት ምክንያት አይኖርም፡፡ የትግራይ ነፃ አውጪ ብሎ ራሱን የሰየመው ጎጠኛ ቡድን በትግራይ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን እና በተቀረው ዜጋ መሀከል ቁርሾን ያዘለ የበቀል ጊዜን ብቻ በሚጠብቅ መልኩ የትግራይ ወንድሞቻች እና እህቶቻች ውስጥ የነበረውን የኢትዩጵያዊነት ስሜት አላሽቆት የክልል ፍቅር የጎሳ እና የመደብ አፍቅሮት ውስጥ ነክሮአቸዋል። ይህ በትውልድ ላይ የተሴረ የባቢሎን ድብልቅልቅ ዘመን እና በሌላውም  በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ የፈፀማቸው በደሎች ሰምበር ሁልጊዜም የሚያመን ቁስል ነው፡፡ታግለነው ግን እንፈወሳለን  የዳነ እና ከእዳ ነፃ የሆነ ምድር ለልጆቻችን እናስረክባለን።  

ስናብር የምናስረው ጠላት አለ። ከዚያም ለታሪክ ፀሀፍት አሳልፈን እንሰጠዋለን።ወያኔ አስፀያፊ ታሪክ ሆኖ ይቀራል። በቅድሚያ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ድርሻ ሊሆን የሚገባው  የተገረፍንበት የወያኔ ጅራፍ ባሰመረልን ሰንበሮቻችን እና ቁስላችን ላይ መወያየት፣ ከችግሮቹምእንዴት መፍትሔ እንደምናገኝ  ነፃነታችንን  እንዴት እንደምንጎናፀፍ ከተሞክሯችን ዘዴ መዘየድ።ይህ ‹‹ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ›› ሊሆንይገባል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ  ከሁሉም አስቀድሞ በራሱ ወርቃማ ፈር ቀዳጅ የለውጥ ሃዋርያነት ብሎም የታሪክ ፈርጥነት ሊያምንይገባዋል፡፡ በትግሉ መደምደሚያ ላይ ከዚህ ቀድሞ እንደሆነው ሁሉ የለውጥ አልፋና ኦሜጋ ሕዝብ እንጂ ጥቂት የፊት ተቀማጭ ፖለቲከኞችሊሆኑ አይችሉም።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቃት ያለው ጀግና ህዝብ ነው።በተደጋጋሚ ወራሪዎችን ተፋልሞ አስደማሚ ታሪክ አስመዝግቧል።  ሊገዙት ካሰፈሰፉት ጋር ሁሉ  ግብግብ ገጥሞ አሳፍሯቸው ያውቃል፡፡ ከዚህ ሁሉ ከተፈፀመበት የጭቆና፣የመገነጣጠል፣ የአፈና ዶፍ እና ዝርፊያ  በኋላየኢትዮጵያ ሕዝብ ማቁን ጥሎ ትቢያውን አራግፎ እንደሚነሳ ለአፍታም እንኳን ማንም አይጠርጥር።

ከተስፋ መቁረጥ ጋር የምንፋታበት ጊዜ ላይ ነን።  ጥቂቶች ለመታገል ሲነሱ ወኔያችው ሞልቶ እንዲትረፈረፍ የምንደግፍ እንጂ ተስፋቆርጠው እንዲቀመጡ የምንመካከርበት ጊዜ አባጅቷል።የኦሮሞ ወንድሞቻችን ጠላት አማራው አይደለም ከትግራይ ተወላጅ ጋር ደቡቡም ሆነ ጉራጌው አልያም ሌላው ብሔር ጠላትነት የለውም። ለሁላችንም ከወያኔ በቀር ጠላት የለንም። ሁላችንም ተያይዘን ምድራችንን የሚሸረሽረውን አሳች በመፋለም ለልጆቻችን ብሔራችንን ሳይሆን አንዲት ኢትዮጵያን እናስረክብ። እኛ ችግሮቻችን ፈትተን ለነፃነት ትግልስንነሳ የሚቦለቦለው  የችጋርና የጭቆና የመለያየት እሳተ ገሞራ ይቀዘቅዛል።በብርቱ አንድነታችን የነፃነት ትግል ማድረግ ስንችል ደግሞ ንዳዱ ከእሳትነት ወደ ክስለት ከዚያም አልፎ የጠላታችን እሳት የአመድ ቁልል ይሆናል።  የዛን ጊዜ የትውልድ ደማቅ የፀደይ ቀናት የሀገር ተረካቢ ውብ ዘመናት ተግተልትለው በኢትዮጵያ ምድር ላይ ይመጣሉ፣ይዘከራሉ፣ይከበራሉ። የጭቆና ሰንበሮቻችን ሁሉ ፈፅመው ይሽራሉ፣ ይፈወሳሉ፣ይከስማሉ፡፡እንግዲህ ልጆች ባልበሉት ፍሬ ጥርሳቸው እንዳያልቅ ለተተኪው ትውልድ በእኛው ዘምን ታግለን አንዲት ኢትዮጵያን እናስተላልፍላቸው። የዚያን ጊዜ እስካሁን ያልቀረፅነው እና ከቅርሶቻችንን ሁሉ የላቀውን ታላቅ ሀውልት በአንድነት በምድራችን ላይ እናቆማለን። ይህ ነው የውስጣችን ማህተም። የነፃነት፣ የእኩልነትና  የወንድማማችነታችን  ሀውልት በሁላችን ዘንድ ለመታሰቢያነት በልባችን የሚቆመው። 
ኢትዮጵያዊነት ያብባል!!! 
እናቸንፋለን!!!

No comments:

Post a Comment