Wednesday, February 17, 2016

ዓለምና ዘመን ፊታቸውን ያዙሩባት ሀገር ! (ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምፅ ራዲዮ ሐተታ)

   
ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምፅ
   ራዲዮ ሐተታ  የካቲት 2008 ዓ.ም 

ዓለምና ዘመን  ፊታቸውን  ያዙሩባት ሀገር !
በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ አምባገነን አገዛዝ በኢትዮጵያ ከተንሰራፋ ፤ይኸው ሠላሣ ዓመታት  እያስቆጠረ  ነው።  በዘመን ስሌት ሲቆጠር ቀላል  ጊዜ አይደለም ። የአንድ  መሥዋዕታዊ ትውልድ ዘመን አሳልፎ ሌላ ትውልድ እየተካ  ይገኛል  ። ይህ ዘመን ፤ በሀገራችን ታሪክ  ዜና መዋዕል፤ የመከራ፤ የውርደት፤ የሀፍረት፤ የጥፋት፤ የጥቃት፤  ሀገር የመቆራረስና  ሕዝብ የመከፋፈል ሀቅን መዝግቧል ።  በዚህ ዕኩይ ዘመን፤  የሀገሪቱ ዳር-ድንበር ተደፍሯል  ። ሃገራዊ ወሰኗ የት ላይ እንደሚቆም እንኳን ገና አልታወቀም !  
የተፈጥሮ የባህር በሮቿ ተዘግተዋል። የቆዳ ስፋቷ ተጨራምቷል። የረሀብ ፤ የቸነፈር፤  የእስራትና  ግድያ ፤  የዕልቂትና የስደት ዘመን ሆኗል ። ለምልዐተ- ሕዝቡ   ዓመተ-ፍዳ፤ ዘመነ መርገም ሆኖበታል ።  ይህ ዘመን፤  ለአጥፊዎቿ ሀሴትን፤ ለዜጎቿ  መከራንና ስቃይን አምጥቷል ። " የጨነቀው በአባቱ መቃብር ያፍራል " እንደሚባለው፤ ኢትዮጵያን የጠሉና   በኢትዮጵያዊነታቸው  ያፈሩ  ሁሉ ከድተዋታል ። ታዲያ ዓለምና  ዘመን  በኢትዮጵያ  ላይ ፊታቸውን  አዙረውባታል ቢባል  ምን ያስገርማል  ?  "  ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ፡፤ ባለዕዳ ይቀበለዋል " ብሎ ማሰብስ እንዴት ይቻላል ?
                     "  አይጣል ይሏል እንጅ   የእሳትን መከራ ፤
                        ቤተክርስቲያን  ያቃጥላል እንኳን  የሰው ገላ ። "  እንዲሉ፤ 
ዘመንና ዓለም ተባብረው ፊቷን የዞሩባት ሀገር፤  የራሷ ለጆች  ከከዷት፤ ታዲያ ማን ሊደርስላት ይችላል ? በአደጋ ላይ የወደቀው ህልውናውን  ለማትረፍ   የትኛው ኃይል ነው  ሊታደጋት  የተዘጋጀው  ?  ሆነም - ቀረ ፤  ይህንን  ጥያቄ  በአግባቡ  መመልስ ያለበት   የአንድነት  ኃይሉ  መሆን   እንደሚገባው    ኢትዮጵያ  መዳን   አለባት  የሚለው   ዜጋ  ሁሉ     ጓጉቶ   ይጠብቃል ።  " ፖለቲካ ማለት፤ መሆን የሚችለውን የማየት ጥበብ ነው ።  ከተባለ፤ የአንድነት ኃይሉ ማን ነው?  ለመሆኑ ይህ ኃይል አሁን በብቃት ተሰባስቦ  ይገኛል  ወይ ?  ከሌለስ እንዴት ይፈጣራል ? ማንስ ይፈጥረዋል ?  እነኝህንና  ሌላች ተመሳሳይ   ጥያቄዎች ከመመለሳቸው በፊት ግን ፤አንድ ሌላ አጣዳፊና ወሳኝ ጥያቄ መልስ ሊያገኝ ይገባዋል ።   የዚህ ጥያቄ ምላሽ ካልተገኘ ፤ እውነተኛ ኅብረት ይፈጠራል ማለት ዘበት ነው ።
ይኽውም፤ የአንድነት ኃይል  ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚቆጠረው ሁሉ፤ሊስስማማበት በሚችለው መሠረታዊ - ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ  ለመነጋገር ችሏል ወይ ?  ይህ መሠርታዊ ጉዳይ ደግሞ፤  የሀገሪቱ ኅልውና  ጥያቄ  ነው ። ኢትዮጵያ እንደ  ሀገር መቀጠል አለባት የሚለው ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መምጥቱን አለመገንዘብ፤ ወቅታዊውን  የሀገሪቱን   ተጨባጭ  ሁኔታ በቅጡ አለመረዳት ይሆናል  ። የአንድነት ኃይል ነው  ተብሎ የሚገመተው ሁሉ፤ በኢትዮጵያ ኅልውና ላይ ቁርጠኛ  ውሳኔ አድርጎ  ከአንድ ስምምነት ላይ ካልደረሰ፤ ሀገሪቱን ማዳን ቀርቶ እራሱንም በህይወት  ለማቆየት የሚችል አይሆንም።  በመሆኑም፤ ከማንምና ከማንኛውም በላይ ይህ ጥያቄ የማያወላውል  መልስና ውሳኔ ሊያገኝ ይገባዋል 
 እስካሁን ድረስ፤ ሁሉም በየፊናው - በተናጠል የየግሉን መግለጫና  አቤቱታ ከማቅረብ  የዘለለ፤ ፋይዳ ያለው  የጋራ ተግባር ሲፈጽም አይታይም ። ለአለፉት አምሳ  ዓመታት ፤ በኢትዮጵያ  የፖለቲካ ምኅዳር  የታየው እንቅስቃሴ፤ ሕዝብ ለመብቱ እንዲታገል ከማድረግ አንጻር ጎላ ያለ አስተዋጽኦ ያደረገ ቢሆንም  ግብዓት አግኝቶ የግስጋሴ ርምጃ ማሳየት አልቻለም  ቢባል እንደ ተስፋ አስቆርጭ ሊቆጠር አይገባውም     የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሻለ አስተዳደር ለማግኘት አይከፍሉ መሥዋዕት ከፍሏል። ዐርበኛና ጀግኖች ልጆቹን አጥቷል። በዚህም አንጀቱ አርሮና ለጊዜው አንገቱን ደፍቶ ለመኖር ቢገደድም የሚከፈለውን መሥዋዕት ሁሉ ክፍሎ  ውጤትን ለማየት ይፈልጋል  !  ያንን የሚጠበቅ ውጤት ለማስመዝገብ ግን፤ በግድ  የኅብረት ትግል  እንደሚያስፈልግ ከልብ ይገነዘባል !   ወያኔም፤ ኅብረት እንዳይፈጠር የታቸለውን ሁሉ ያደርጋል  ። የተቃዋሚውን ተሽከርካሪ ባሌስትራ ይስብራል። ተቃዋሚውም በበኩሉ በየጊዜው የሚተነፍስበትን ጎማ ሳልዳሬ በማድረግ  እየተጠራሞተ ይገኛል ።
 እንደ  ኢትዮጵያ  ውስብስብ ችግሮች ያሉባትን  ሀገር ህልውናዋን ለመጠበቅ ካስፈለገ፤ የጋራ ጥምረት፤  የእርስ በእርስ ትብብርና  የዕምነት  ትስስር ወሳኝ መሆኑን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል ።  በራስ አቅምና ብቃት ላይ የተመሰረተ ትግል ማካሄድ የሚቻለውም፤  በጋራ ዓላማ ላይ የተመሰረተ የኅብረት ትግል ሲያካሂዱ ብቻ ነው።   ኅብረት-ኅብረት ስለተባል ብቻ ኅብረት በራሱ ፈቃድ እንደማይመጣ፤ ያለፈው  ተመክሮ በገሃድ አስመዝግቧል ።  ህብረትን ለመፍጠር፤ ሁሉም  ተቃዋሚ ሃይል ወያኔ ብሄራዊ ጠላት መሆኑን ከልብ አምኖበት፤  አስፈላጊውን መስዋዕት ለመክፈል ቆርጦ መነሳት አለበት። ከለበጣና ከይስሙላ በላይ በተጨባጭ ተግባር ላይ ካልተሰማሩ ሕብረት ሊመጣ አይችልም።
ይህ ሃቅ እንዳለ ሆኖ ግን   ወያኔ አራት ኪሎ ከመሸገ በኋላ  ፤ ልዩ ልዩ  ተቃዋሚ ድርጅቶች፤ ኅብረት ፈጥረው ለመታገል ሙከራ አላደረጉም ማለት አይቻልም። ለታሪክ ግንዛቤና ለወደፊቱም ማጠያቂያ ሊሆን የሚችል ከሆነ፤ ዋና ዋና  ሙከራዎቹን መጥቅሱ አግባብነት ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል።  እነርሱን እንዳመጣጣቸው በቅደም -ተከተል እንመዘግባለን 
1ኛ.  ወያኔ ገና ወደ አዲስ አበባ ከመግባቱና የደርግ ቁንጮ  የነበረው፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለአደጋ አጋልጦ ከመፈርጠጡ በፊት ፤  በሀገሪቱ ላይ ያንዣበበውን አደጋ የተገነዘቡ አምስት ድርጆቶችና ሀገር ወዳድ ዜጎች ተስባስበው፤ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች  ቅንጅትን  (  ኢዴኃቅ  ) መሰረቱ።
2ኛ.   ፓሪስ አንድና ፓሪስ  ሁለት የተሰኙ ሁለት የኅብረት ሙከራዎች ተደረጉ።
3ኛ.   የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ኅብረት ( ኢተፖድኅ ) ተብሎ፤ ሌላ የኅበረት ጥረት ተሞከረ ።
4ኛ .  የአማራጭ ኃይሎች  የሚል ስያሜ የተሰጠው በአዲስ አበባ ግዮን ሆቴል  ስብሰባ ተደርጎ ኅብረት ፈጥሮ ተነሳ ተባለ ።
5ኛ. በመጨረሻ ደግሞ ፤ ከሁሉም በላይ ፤ ብዙ ታስቦበትና ሁለት ዓመት የፈጀ ከፍተኛ  ርብርቦሾ ፤ ገንዘብንና ዕውቀትን የጠየቀ ሥራ ተሰርቶ፤  አስራ ስድስት ( 16)   የፖለቲካ  ድርጅቶችን  ያካተተ ፤ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት  ( ኢዴኃኅ ) ተመስርቶ በመልካምና ብሩኅ ተስፋ ተግባሩን ቀጠለ። ለተወሰነ  ጊዜም ቢሆን፤ ለሕዝብ ከፍተኛ ተስፋና መነሳሳት አምጥቶቷል። የማይናቅም ውጤትን አስምዝግቦ እንደነበር የሚካድ አይደለም። ቢያንስ ተቃዋሚዉ ኃይል ከተደራጀ፤  አርዕድ- አንቀጥቅጥ ኅይል ሊሆን እንደሚችል  በተጨባጭ አሳይቷል።
ከላይ እንዳመጣጣቸው በጊዜ  ቀመር ቅደም- ተከተል የተፈጠሩት የኅብረት ድርጅቶች፤ በወቅቱ ለተነሱት ሕዝባዊ ጥያቄዎች፤ ከሞላ ጎደል ፤ ምላሽ ለመስጠት ጥረት ቢያደርጉም፤ ከስትራተጂያዊ ራዕይ አኳያ ግን፤ የሀገሪቱን ዘላቂ መፍተሄ ለማስግኘት  አልታሳካላቸውም    ከነዚህ  መካከል ፤ አንዳንዶቹ፤  እንዲያውም ከናካቴው፤ ስምምነቱ የተጻፈባቸው  ቀለሞች ገና ሳይደርቁ  የውሃ ሽታ  እየሆኑ ቀርተዋል። ጥቂቶች ደግሞ የተሰጣቸውን የሃላፊነት ቦታ እንኳን በቅጡ ማስረከብ ይቅርና እንዲያውም ስሙን ቀምተው የወያኔ ፓርላማ ወንበር  ለመያዝ ተጠቀሙበት። እንዲሁም ሌሎች ብዙ ተመሳሳይ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻል ነበር፣ ሆኖም ግን ይህ ለምን ሆነ ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ፤  የዚህ ሐተታ ዓላማ ስለአይደለ፤ ለታሪክ ተከታታዮች እንተወዋለን   
በእኛ ዕምነት ፤ በአሁኑ ወቅት ፤ ጠንካራ የተቃዋሚዎች ኅብረት ለመፍጠር፤ በመጀመሪያ  የጋራ ብሔራዊ  ራዕይ መኖር አለበት እንላለን ።  ቀጥሎም ሰፊው ትብብር በዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ላይ የማያወላዳ አቋም ሊኖው ይገባል። እስካሁን ይህ ባለመኖሩ፤ ጠንካራ የተቃዋሚ ኃይል ኅብረት ለመፈጠር ሳይቻል  ቀርቷል ።  ይህ የጋራ ራዕይ ማለት፤ የሀገሪቱን ኅልውና በመጠበቅ ዙሪያ ሊያሰባስብ የሚችል ብሔራዊ አጀንዳን የያዘ ዓላማ ያለው  እምቅ ኀይል ማለት ነው። ኢትዮጵያን ከጥፋት ለማዳን የሚችል ዕምቅ ኀይል እንዳለ የማይካድ ቢሆንም፤ እምቅን ኀይል ወደ ተንቀሳቃሽ ኀይል መለወጥ መቻል አለብን ነው ዋናው ቁም ነገር።  ለዕምቅ ሃብትማ፤ ከኢትዮጵያ የበለጠ ማን ሀብታም አገር ይኖራል ? የሀገራችን ሁለንተናዊ ዕምቅ ሀብት ፤ማለትም፤  የሰውና የተፈጥሮ ኀብት ተደምሮ ተጠቃልሎ ወደ ተንቅሳቃሽ ኀይል ከተለወጠና ሥርዓት ባለው  ሁኔታም   መጠቀም ከተቻለ፤ የፖለቲካውም ሆነ፤ የኢኮኖሚው ችግራችን ይፈታልናል የሚል ብሩኅ ተስፋ አንግበን ካልታገልን፤ አድሮ ጥጃ ከመሆን አናልፍም   
በጋራ አጅንዳ ላይ የተገነባ ኅብረት ፈጥሮ፤ ሀገሪቱ ከገባችበት ማጥ ለማውጣት የህብረት ትግል  አስፈላጊ መሆኑ በዕርግጥ ሁሉ ካመነበት፤ የሚከተሉት አምስት ጉዳዮቹን መሠረት ማድረግ ያስፈልጋል  
1ኛ.  ማነኛው ድርጅት/ ስብስብ ወደ ኅብረት  ጉባዔው  ለመሄድ ሲሰናዳ፤ የስብሰባው ቅደመ- አጀንዳ ፤ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም  ማዕከል ያደረገ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት ።
2ኛ. ይህ ማለት፤  የኢትዮጵያ ኅልውና፤ የግዛቷ ልዕልና፤ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የዜጎቿ አንድነትና ነፃነት፤ እንዲሁም የዴሞክራሲ ሥርዓት ማለት ይሆናል 
3ኛ.  በተራ ቁጥር አንድና ሁለት የሰፈሩትን  መሠረታዊ ዕምነቶች አምኖ መቀበል የመጀመሪያው ርምጃ ብቻ ሳይሆን፤ ለድረድርም የሚቀርብ አይሆንም ። ይህ ደግሞ  የእኛ አልፋ-ዖሜጋ ብቻ ሳይሆን፤ የማንነታችን መግለጫና  መርኋችን ሆኖ ቆይቷል ።  ወደፊትም ይኖራል ።
4ኛ. ድርጅትን ድርጅት የሚያስብሉ፤ መስፈርቶችን አሟልቶ መገኘት፤ለኅብረት ኀልውና  መሠረት  ነው። በዘለቄታውም ፤ በአብሮነት ያገለግላል። በጉባዔ ለመገኘት ብቻ ሲባል  ወይንም እኔስ ለምን ተለይቼ እቀራለሁ ከሚል እሳቤ ብቻ በጉባዔ ላይ መገኘት፤ ድርጅታዊ ህልውና በሌለበት ለስም ብቻ  ገብቶ መኮፈሱም ፋይዳ አያመጣም ። እስካሁንም እንደታየው ምንም ያስገኘው እርባና  አልነበረውም ። ትብብሩ (ህብረተቱ) ለትግል ቆርጠው የተነሱ ድርጅቶችን መያዙ ወሳኝ ስለሚሆን መሠረቱ በሀገር ውስጥ መሆኑ ሚዛኑን ከፍ ያደርገዋል።
5ኛ.  የጋራ ብሄራዊ  ራዕይ ያለው የጋራ ኅብረት መፍጠር፤ ቢያንስ  ሦስት ዐበይት ጠቀሜታዎች ይኖሩታል ።

      ሀ.   ያለተቋረጠና ያልተቆጠበ ሕዝባዊ  ዕምነትና ድጋፍ ይኖረዋል 
     ለ.    ለአምባገነን ገዥዎች  ሰልባ ከመሆን ራሱን ያድናል ። በራስ ኃይል ይተማመናል  ። በራሱ የሚተማመን ደግሞ የሕዝብ ከበሬታና ድጋፍ   ያገኛል ። ተአማኒነትንም ያተርፋል ፡፡ የሕዝብና የሀገር መከታ ይሆናል ።
      ሐ .   በራስ ኀይል ተማምኖ፤ የሕዝብንም ሁለንተናዊ ድጋፍ አግኝቶ ስለሚታገል፤ የአምባገነኖችን ዕድሜ ባጭሩ ይቀጫል ።
ይህንን  ዘረኛና ዘራፊ  የገዥ ቡድን ፤ ከነሥርዓቱ  ከስረ- መሠረቱ ፈነቃቅሎ ለማስወገድ ሲባል ፤ ለአለፉት ዓመታት የተደረገውን ጥረት በሚገባ መርምሮ፤ በአዲስ ስልትና ፈርጀ-ብዙ የኅብረት ትግል ማካሄድ የወቅቱ ወሳኝ ጥያቄ ሆኗል  ። ወደ ፊትም ኅብረቱ ካልተመሰረተ፤ ሕዝባዊና ወቅታዊ ጥያቄ እንደሆነ ይቆያል 
 ይንን ሕዝባዊ ጥያቄ ለመመልስ፤ የሚቻለው ደግሞ፤ የጋራ ብሄራዊ ራዕይ ያለው ኃይል ሲፈጠር ብቻ ነው።  ቅድሚያ ለብሄሬ እንጅ  " ኢትዮጵያ  ለእኛ  ሁለተኛ   ደረጃ  ነች  ከሚሉና አልፎም ስሟን መጥራጥ  ዳገት ከሆነባቸው ፅንፈኞች"   ጋር ኅብረት መፍጠር አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የአሸዋ ላይ ግንብ ከመሆን አያልፍም ። አሁንም ሁኔታው አልተለወጠም ።  የወያኔ ሰለባ የሆኑ ሁሉ፤ ሊያስቡበት የሚገባው፤  ከሁሉ በፊት የመጀመሪያው ዒላማ  ፤የሁሉም የጋራ ጠላት በሆነው አገዛዝ ላይ መሆን  አለበት። ይህ ደግሞ፤ ለማንኛውም ብሩኅ አዕምሮ ላለው ሁሉ  የሚሰወር አይደለም ። ለሁሉም  የጋራ የሆነችውን ሀገር በጋራ ከጥፋት አድኖ፤   ሁሉም የሀገሪቱ  ዜጋ ፤ በጋራ ተጠቃሚ  በምትሆነው ሀገር ላይ  ዴሞክራሲያዊ  ሥርዓት  መስርቶ አብሮ ከመኖር የበለጠ ሌላ አማራጭ እንደሌለ የማይናውጥና ዘመን የማይሽረው  አቋማችን መሆኑን ሁሉም ሊያውቀው ይገባል  ። ወገናችን የሆነው ብዙሃኑ የትግራይ ሕዝብም በዚህ እንደሚስማማ  አንጠራጠርም ። ይህ የፖለቲካ ሀቅ ግን ወያኔን ሲያስጨንቀው ኖሯል ።  ወደፊት መሆኑ አይቀርም ብሎ  ስለሚያስብ ፤ ሁልጊዜ እያባነነው፤  እንቅልፍ- አልባ   እንደሆነ ይቆያል 
ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባልቆረጠው ዱላ እየተመታ፤ ባልሰየመው ዳኛ እየተረታ፤ባልመረጠው " መንግሥት "  እየተፈታ የቁም-ስቃዩን እየከፈለ   ይገኛል ። ሀገራችንንም  ዓለምና  ዘመንም  ረስተውታል  ። ከስቃይ ያወጡኛል  የሚላቸው  ኃሎችም አልተባበሩለትም። ከቀዳሚው ትውልድ ያገኝው ህልውናም ጥያቄ ውስጥ ገብቶበታል  ።የወረሰውን ኢትዮጵያዊነትም ለሚቀጥለው ትውልድ ለማውረስ ከሚችልበት ደረጃ አይደለም። ወጣቱ ትውልድም የሚወርሰውን ፤ የሚያወርሰው እያጣ ነው ። ከአባቱ ያልወረሰውን ደግሞ ከአያቱ መውረስ ይቸግረዋል ።  በዚህ ምክንያት፡
               " የባት  ዕዳ ለልጅ ይባል ነበር ዱሮ፤
                ባያት  እዳ ገባሁ እኔማ ዘንድሮ ። "  እያለ ይማልላል!
የተቃዋሚው ክፍል፤ ኢትዮጵያን በሚመለከት ፤ የዓለምን አስተያየት መለዋጥ ባይችልም፤   በራሱ ላይ ለውጥ አድርጎ ፤ የሀገሩን  አስጊ ሁኔታ  ለውጦ ፤ ብሩኅ ጊዜን  ለማምጣት እንዲችል ጥሪያችንን አናስተላልፋለን  !


ኢትዮጵያ  ለዘለዓለም  ትኖራለች  ! 

No comments:

Post a Comment