Wednesday, February 24, 2016

ያለማወቅ ጉዳትና የግንጠላ መዘዙ. Finote Radio !

ያለማወቅ ጉዳትና የግንጠላ መዘዙ
ከመናገር በፊት ማወቅ መመራመር የሚለው ዘንድሮ ተረስቶ እንዳመችና አፍ እንደመጣ መናገር መተቸት፤አልፎም ማውገዝ ተለመደና አያሌ ጽንሰ ሀሳቦች፤ክስተቶችና መፈክሮች ወይም መርሆዎች ድብልቅልቃቸው ወጣ ። መገንጠል የሚለው መርህ አንደኛውና ዋናው ነው ቢባል ትክክል ነው ።
ለለውጥ የታገለውን ትውልድ ሀገር አስገነጠ ብለው አሁንም ማውገዝ የሚቀናው አሉ ። ያለማወቅ ጉዳት ነው ተንኮል አዘል ባልሆነበት ። የኢትዮጵያን የብሄረሰብ/ ኤርትራን ችግር የፈጠረውና ያባባሰው ያ የታገለው ትውልድ ሳይሆን ስርዓቶቹ ናችው ። የኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ለስር ነቀል ለውጥ ሊታገል የተነሳው መሬት ለአራሹ መፈክርን አንግቦ ሲስለፍ ማለትም በ1958/1965  ነው ። ከዚያም በኋላ ድሀው ይማር፤ድህነት ወንጀል አይደለም፤ የመብት እገዳው ይወገድ፤ በአርሶ አደሩ ላይ ጎጂ ግብር አይጣልበት ወዘተ ብሎ ከተሰለፈ በኋላ ነው ችግር ሆኖ የመጣውን የብሔረሰብ ጥያቄ መልስ ሊስጥ የሞከረው ። ከዚህ ሁሉ በፊት፤ራሱ የተማሪው እንቅስቃሴ የሥር ነቀል ለውጥን አማራጭ ከመያዙ በፊት ማለትም በ1960 (በአውሮጳውያን አቆጣጠር) ጀምሮ የኤርትራ ነጻ አውጭ ግንባር ቅኝ ግዛት ነን ብሎ የትጥቅ ትግሉን ጀምሮ ነበር ። በባሌ፤በኦጋዴንም ብሄረሰብ ጥያቄን የሚጠቅሱ አመጾች ነበሩ ። አንድ አደራጅ ድርጅት መስርቶ ወደፊት ለመጓዝ ይህንን ከፋፋይ ጥያቄ ምላሽ መስጠቱ ቅንጦት ሳይሆን ግዴታ ነበር ማለትም ይቻላል ። ከኤርትራ የመጡ ተማሪዎች የኢትዮጵያ ጉዳይ አይመለከተንም እያሉ ከሰልፎች የሚርቁበት ጊዜ ነበር ። የኦሮሞ የሜጫ ቱማ እንቅስቃሴ (ቦምብ የፈነዳበት በአዲስ አበባ ና እነ ማሞ መዘምር የተሰቀሉበትም) አንደምታው ቀላል አልነበረም ። ዛሬ የታሪክ በራዦችና ያለፈን ካጆች ምንም ጭቆና አልነበረም ሊሉን ቢቃጡም ያፈጠጠና ያገጠ ልዩነት ነበር ።ኢትዮጵያ ለቡዝሃኑ እስር ቤት ሆነ ሲባል  ባዶ ቃል ድርድረና ቃለ አጋኖነትም አልነበረም ። ዓይን ያለ ይይ፤ጆር ያለው ይስማ በተባለው መሰረት ወጣቶች ዓይን ጆሮአቸውን ከፍተው የወገንን ሰቆቃ ሰሙ፤ መከራውን አዩለት ። ለችግሩ መፍትሔ ሊሰጡ ሲነሱም ፍለጋቸውን የነበራቸው ርዕዮት ቢቃኘው የሚያስገርም አይሆንም ።
ይህን ሁሉ ቢነገሩ ቢነገሩ መረዳት የተሳናቸው ግን ተማሪዎች፤ ያ ትውልድ፤ ኢሕአፓ ሀገር አስገነጠሉ ይላሉ --ኤርትራና ያስገነጠለው ወያኔ፤ለግንጠላ ያመቻቹት ደግም ቀደም ያሉት አገዛዞች መሆናቸውን በመካድ ። ተማሪዎችና ወጣት ተማጆች ለምን ወደ ግራ አዘነበሉ? ለምንስ የቀኙና የአሜሪካ አናቂዎች ደክማ ሆኑ? ይህ  የሚመለሰው በዛሬ መነጽር ሳይሆን የነበረውን ሁኔታ በዜው ክልል በመመርመር ነው ። በዚያን ጊዜ ዕራቡ ዓለም የብዝበዛና ጭቆና ማዕከል፤ የአፓርቴድና ዘረኝነት ደጋፊ፤ የአፍሪካ አምባገነኖች ቀኝ እጅ በመሆኑና በተጻራሪው ደግሞ የሶሻሊስቱ ጎራ ጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግሎችን ይደግፉ ስለነበር ለውጥና ነጻነት ፈላጊዎች በአስተሳሰብ ወደ ሶሻሊዝም/ማርክሲዝም ማዘነበላችው የሚጠበቅ ነበር ። ቬትናም/ኢንዶቻይና ትግሎች፤ የኩባ ትግል ድል፤ በደቡብ አሜሪካ የነበሩ ጸረ ኢምፔሪሊስት ትግሎች፤ ካብራል ሞንድሌን፤ሉሙምባ ንክሩማህ፤ አልጄሪያ የመን፤ ፓለስታይን፤ ማኡ ማኡ በኬንያ፤ ፌሊክስ ሙሜና ዩፒሲ በካሜሮን ወዘተ ዘተ በየአቅጣጫው የሕዝብ የነጻነትና የመብት ትግል ። አሜሪካ የደቡብ አፍሪካ ሕዝብን ትግልና ራሱን ማንዴላን ሽብርተኛ የምትልበት ዘመን ማለት ነው ። ማን ሉሙምባን አስገድለ? ካብራልን ? ማሼልን? ሙሜና ዩዋንዴን? ኪማቲን? ዘመኑ የሕዝብ አመጽና የጸረ ቅኝ አገዛዝን ጸረ ኢምፐኢሪያሊስግል ዘመን ነበርና ወደ ግራው ርዕዮት ያዘነበሉት ተማሪዎችና ወጣቶች--ወይም ያ ትውልድ-- ለብሄረሰብ ችግር የሰጠው መልስ በርዕዮቱ መሰረት ሆኖ እስከ መገንጣል የሚለውን መብት ማወቅ የሚለውን አጠቃለለ ። ይህን መብት ማወቅ ግን መገንጠልን በደፈናውና በግድ መደገፍ አይደለም የሚለውን መርህ የዛሬዎቹ ተቺዎች ባይረዱትም ተገንጣዮቹ ግን--በተለይ ሻዕቢያ--የመገንጠል መትን ማወቅ ነጻነታችንን መደገፍ ማለት አይደለምና ኢሕአፓ ነጻነታችን ተጻሯል በማለት ሲያወግዝ የነበረውን በቅርቡም ዳግም ገልጾታል ። ሶማሊያም መስፋፋት አቅዋሟን ድርጅቱ ስላወገዝ ስላልተቀበ በጠላትነት ፈርጃ እነ ወያኔን ረድታለች ። በአጭሩ ተገንጠሉ ተበታተኑ  አልተባለም ። ወያኔም በ1967 ልገንጠል ና ነጻን ትግራይን ልመሰርትየሚል መርሃ ግብር ሲያወጣ ኢሕአፓ ተቃወመው እንጂ አልደገፈውም ። ወደ ደርግ ውድቀት ገደማም ድርጅቱ ባወው የአዋም መግለጫ የፌዴራልን መፍትሄ አቅርቦ በሻዕቢያም በወያኔም ትምክህተኛ ብሎ መወገዙ በስሁፍ ሳይቀር የሰፈረ ነው ። በአጭሩ ክስ ደረዳሪዎች ያለማወቅና ወይ አውቆ የማደናገር ተውሳክ የተጠናወታቸው ናቸው ማለት ይቻላል ።
ግንጠላ መዘዙ ብዙ ነው ። እራባውያን ይህን አማራጭ የሚገፉት ሀግሮችን ለማዳከምና ለመበታተን ነው ። በሶቬት ህብረትና በዩጎዝላቪያ ላይ ተሞክሮ ያደረሰውም ጉዳትና መዘዝ የሚስተው የሚያውቀው ይኖራል ማለት የሚቻል አይደለም ። ወደ ቅርባችን መለስ ስንል ኤርትራና ደቡብ ሱዳንን እንደ ምሳሌ መጥቀስ እንችላለን ። ጸሓይና በሪኻ ብሎ የጨፈረው ኤርትራዊ ሁሉ ዛሬ ደረቱን በሀዘን እየደቃ መሆኑ ግልጽ ነው ። በቅርቡ እንድ ታዋቂ ኤርትራዊ ምሁር ኤርትራ ሞታላች ገዳይዋም ቀባሪዋም ሻዕቢያ ነው ያለው ሀቅን መሰረት ያደረገ ግምገማ ነው ተብሏል ። ብዙ ሀተታ ሳናበዛ ኤርትራ ተገንጥላ ያገኘችው ጥቅም አንዱን አምባገነን በባሰ መተካት እንጂ ሌላ አለሆኑን ሞትን በስደት የሚጋፈጡ ወጣቶች በአቅዋማቸው እያረጋገጡ ናቸው ። መገንጠሉ ጎዳ እንጂ አልጠቀመም፤ስድስት ሚሊዮን ሕዝብን ወደ እንጦርጦስ ከተተ እንጂ ገነት አላገባቸውም ። ይህንን የመገንጠል ሂደት ምዕራቦች--በተለይም አሜሪካና እንግሊዝ--እንደደገፉ ደግሞ የሚታወቅ ነው ። ካፈርኩ አይመልሰኝ ካልሆነ ዛሬ ያለን ሁኔታ ጽቡቅ ነው የሚሉ ኤርትራውያን ብዙ አለመሆናቸው የሚገመት ነው ።  በሳምንት በሺ ደረጃ  ሰው ሲሰደድ አለምክንያት አይደለም ። ሞት መኖሩን እያወቁ ሲሰደዱ ቢብስባቸው ነው ። ትግሉ መራን ያሉ ዛሬ በብረት ኮንተይኔር/ሳጥን ታጉረው ይሰቃያሉ ፡፤ የሞቱትም ብዙ ናቸው ። ያ የተዘፈነለት ሐርነት መና ቀርቷል ። ጸሓይ ጠለቀች እንጂ አልወጣችም ለኤርትራ።
ወደ ደቡብ ሱዳን ስናይ ደግሞ የደቡብ ሱዳን ሕዝብ በሰሜኖቹ ከኒሜሪ እስከ በሺር ባሉ አሀዛዞች መሰቃየታቸውና ዜግነትም መነፈገቻው በገቢር የሚታወቅ ነው ። አረቦቹ ደቡቦቹን ሕይዋኒን/እንስንሳት ያሉ ያደረሱባቸ ጥቃትና ውርደት ወደ ግንጠላ ቢገፋቸው  የሚያስገርም አልነበረም ። የካርቱሙን  አገዛዝ የጠሉት አሜሪካና አጋሮቹ--በተለይም እስራኤልና እንግሊዝ-- የደቡብ ሱዳን አመጽ ወደ መገንጠል ጎዳና እንዲገባ የተቻላቸውን አድርገዋል ። ምዕራባውያን በአፍሪካ ገዘፍ ያሉ ሀገሮችን (ናይጄሪያ፤ኮንጎ፤ኢትዮጵያ፤ሱዳን ወዘተ) መከፋፈልና ማዳከም ይጠቅመናል ብለው የተያያዙት ስምሪት በመሆኑ ደቡብ ሱዳንን መገንጠል ይሁነን ብለው የያዙት ተልዕኮ ነበር ። ይህን በመቃወም ደረጃ የአማጽያኑ መሪ ኮለኔል ጆን ጋራንግ የተባባረች አዲስ ሱዳንን መመስረት የሚል ግብ ይዞ በመቆየቱና ከሉም በመያዙ በሄሊኮፕተር አደጋ (እንግሊዝ፤ዩጋንዳና አሜሪካ ባሉበት ሴራ) ተገደለና ለአሜሪካው ሎሌ ለሳላቫ ኪር ቦታው ተዘጋጀ ። የደቡብ ሱዳንም ሆነ የኤርትራ ልዩ የጋራ ብሔራዊ ማንነት ራሱ--ከዲንካ ኑዌር፤ከትግራዊ በኒአምር ለሚለው በተለየ--ደማቅ ህልውና ያለው መሆኑ አከራካሪ በመሆኑ ደቡብ ሱዳን ከጎጥ/ብሄረሰብ አልፎ ሀገራዊና ብሔራዊ ማንነት ሊከሰት ባለመቻሉ እነሆ ጎሳን መሰረት ያደረገ ጦርነትና ግድያ ተፋፍሞ አለ ። በዚህ ላይ ደግሞ ደቡብ ሱዳን ቤንዚንና የለም መሬት ባለቤት በመሆኗም ውሷ መባባሱ አልቀረም--እንደ ዛይር/ኮንጎ ። ደቡ ሱዳን እንደ አንድ ሀገር ህልውና ይኖረዋል ወይ ለሚለው ጥያቄና ስጋት የሚያረጋጋ ምላሽ ለመስጠት ማንም የሚደፍር የለም ።
የተነሳንበት ዋና ቁም ነገር መገንጠል ጠቃሚ ሳይሆን ጎጂ ነው/ነበርም የሚለውን ጫና ሰጥቶ ለማቅረብ ነው ። የአፍሪካን ሆነ የሌሎቹንም ተመክሮና ተጨባጭ ሁኔታ ማንሳት የተገደድነው ለዚሁ ነው ። ይህ በዚህ እንዳለና ሀቅ ሆኖ እየተገኘ እንደ ኦነግ አይነቶቹ አሁንም መገንጠል በሚል አጓጉል አባዜ ተይዘው መቆየታቸው የሚያሳዝን ሆኖ ይገኛል ። ወያኔም ትግራይን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ ለብቻ ለማድረግ አሊያም ከኤርትራ በትግራይ ትግሪኚ ደረጃ ለማዋሀድ የሚመኘው ከንቱ ሆኖ የሚቀር መሆኑ ከወዲሁ የሚታወቅ ነው ። ኤርትራ  ተገንጥላ ተመቻት ጫጫች? ዜጎቿ አለፈላቸው ወይስ የባሕር ሰለባ ሆነው አለቁ? ደቡብ ሱዳን በራስ አገዛዝ መቆየትን ትታ በ ባእዳን ግፊት ተገንጥላ ሀገር ሆነች ወይስ ሕጻናቷን ሳይቀሩ የምትጨፈጭፍ ጉድ ሆነች? መልሱ ለማንም ህሊና ያለው ዜጋ ግልጽ ነው ።


No comments:

Post a Comment