Friday, February 26, 2016

ፌደራሊዝም ማለት ዴሞክራሲና ለዜጎች ቅርበት ማለት ነው!! Finote Radio.

ፌደራሊዝም ማለት
ዴሞክራሲና ለዜጎች ቅርበት ማለት ነው!!
ከዝግጅት ክፍላችን
ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ በሳተላይት የሚሰራጭ የራዲዮ ፕሮግራም
http://www.finote.org
Finote 


የፌደራሊዝም ሥርአት ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ የሥልጣን ባለቤት በሁለመናው መልኩ እንዲሆኑ ዋስትና የሚሰጥ ነው። ማንኛውም ዜጋ በተለማመደደት፤ በሚያውቁት አካባቢ በማንኛውም የማህበራዊ ሥራ ተካፋይ ለመሆንና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ለማሳደር የሚችሉት የፌደራል ሥርአት ከዴሞክራሲ መርሆዎች ጋር ተቆላልፎ በሚገኝበት ሁናቴ ነው። ፌዴሬሽን ከፖለቲካ ቅርፅ በላይ ማለትም ከዜጎች ፍላጎት መግለፅ በላይ የሚሄድ ነው። ባጭሩ ፌዴሬሽን ማለት ዴሞክራሲና ለዜጎች ቅርበት ያለው ሥርአት መኖር ሲሆን፡ ፖለቲካ ደግሞ የወቅቱን ሁናቴ እድሜ ማራዘም ሳይሆን ስለ ወደፊቱ ፕላንን መቅረጽና ለተግባራዊነቱ  ጥረት ጥረት ማድረግ ነው።
ስለ ፌደራሊዝም ምንነት የወያኔ አገዛዝ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱና ተራ ካድሬዎቹ ሳይቀሩ በቁጥጥራቸው ሥር ባደረጉት የዜና ተቋማት ላለፉት በርካታ አመታት  መጠነ ሰፊ ፕሮፓጋንዳ ያላካሄዱበት ቀን በጣም ጥቂ እንደሆነ መግባባት የሚቻል ይመስለናል። በተለያዩ ርዕሶችና  የፌደረሊዝም መርህና ተግባር ነክ በሆኑ ጥያቄዎች ላይ ጥናታዊ ውይይት ማድረጋቸውንና ተመክሮ የተገበያዩበት በርካታ ስብሰባዎች በክልል ከተሞችም ሳይቀር ማድረጋቸውን ከመግለፅ የቦዘኑበት ቀን የለም ቢባልም ያስኬዳል። ሕዝቡን በዚሁ ተመርኩዞ ውይይት አድርጎ አመርቂ ግንዛቤ ማግኘቱንም እንዲዚሁ ሲናገሩ አመታት አልፈዋል። አልፎ ተርፎም ለሌላ ሕዝብ ተመክሮ ለማካፍል የሚያስችላቸው ግንዛቤ ማግኘታቸውንም ካድሬዎቻቸው በኩራት ሲገልጹ ተደምጠዋል።  ይህን በተመለከተም የፃፉትንና በተለያዩ ድረ ገጾች ያወጧቸውንም ትንተናዎች ይፋ አድርገዋል።  
ይህ ሁሉ ጥረታቸው ግን አምባገነንነት የተጠናወታቸው በመሆኑ የዴሞክራሲ ካባ ሊያላብሳቸው አልቻለም። አይችልምም። ስለሆነም መልከ ጥፉ በስም ይደፉ ይባላልና የወያኔ አገዛዝ  በርካታ የሕዝብ ሀብት በማፍሰስና መጠነ ሰፊ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት የራሱን ገፅታ ለማቆነጃጀትና በአለም አቀፍ ማህበረሰብ እውቅና ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ማድረጉ የሚጠበቅ ነው። ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚንቀሳቀስ ነውና ከነዚህ ኃይሎች ውስጥ የተወሰኑቱ ቢደግፉት የሚደንቅ አይሆንም። ግን ዘላቂ ሊሆን አይችልም።  ይህ የወያኔ የፌዴሬሽን ቀመርና አካሄድ የኢትዮጵያን ብዙሃን ሕዝብ የልብ ሙሉ ድጋፍ ያላገኘ እንዲያውም በሀገሪቱ ያንሰራፋው ሥርአት በዘረኝነት የተለወሰ የአንድ ድርጅት አምባገነንነትና ከፌደራልዝም መርህ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው መሆኑን በመገንዘብ ሊገረሥሠው የሚታገለው መሆኑ በበለጠ በገሃድ እየታየ ነው።
ዛሬ በወያኔ የበላይነት ከላይ በሕዝብ ላይ የተጫነው ወያኔያዊ የፌደራል ቀመር ከሰርተ አመታ ተመክሮ በኋላ ኢትዮጵያዊያን ያልገበዩት እውቀት፤ ያለገኙት ተመክሮ የለም ቢባል ሀቁን መናገር ነውና የሚሟገተን ሊኖር አይችልም። ነፃነትን የተላበሰ መብት የሚከበርበት የፖለቲካ ምህዳር ቢኖር ኖሮ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን የወያኔን የፌደራል ቀመር በዴሞክራሲያዊ ውይይት እርቃኑን ለማስቀረት በቻሉ ነበር። ይህ ብቻ አይደለም። እነዚህ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን የሚደርሱበትንም ጥናታዊ ውጤት በተለያዩ የሀገሩ አካባቢዎች ከሕዝቡ ጋር በነፃ ለመወያየት ቢችሉ፤
. ሕዝቡም ጥናት አቅራቢዎቹም የበለጠ ትምህርትና ተመክሮ ሊገበዩበት እንደሚችሉ በርግጠኝነት መናገር የሚቻል ነው።
. የወያኔ ባለሥልጣናት አሁን እያደረጉ እንዳሉት እንዳሻቸው እንዳይደነፉ አደብ ማስገዛት ይቻል ነበር።
. ባዕዳኖች ሲናገሩት እውነተኛ፤ ኢትዮጵያዊያን ሲያወሩት ስህተተኛ የሚል የባዕድ አምላኪነት የተጠናወታቸውን የአገዛዙን አባላት ጠመንጃ ስላነገቡ ብቻ ሁሉን አዋቂ ሆነው ለመገኘት የሚያደርጉትን ጥረት ባዶነታቸውን ባጋለጠ ነበር።
. በወያኔ አገዛዝ አማካኝነት ስለተገነባው ሥርአት አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ውጤቶቹ መስካሪ ባዕዳኖች ሳይሆኑ በዋናነት የሚመለከተው ሕዝባችን መሆኑን በሚገባ ማስረገጥ በተቻለ ነበር። ሌላም ሌላም።
ይህ ሁሉ ግን የመቀበሪያቸውን ጉድጓድ መቆፈር ስለሚሆንባቸው የሚፈለግም፤ የሚመኙትም ሳይሆን ጨርሶውኑ እንዲነሳም የሚሹት አይደለም። በሥልጣን ጥቅም በመታወራቸው ምክንያት የጊዜ ጉዳይ መሆኑ አልገባቸውም እንጂ ከታሪክ ትቢያ መጣላቸው የሚከሰት ለመሆኑ እነሱም እኛም በቅጡ የምናውቀው ነው። የታሪክ ሂደት ነውና። ለማንኛውም ስለ ፌዴሬሽን ሥርአት አስመልክቶ በቴሌቪዥን መስኮት የተለቀቀውን ውይይት ተመልክቶ ላዳመጠና ለተገነዘበ የተለያዩ ትችቶችን ያዘሉ ጥያቄዎችንና አግራሞቶችን ያስከተለ መሆኑን እንገነዘባለን።
በበኩላችን በአሁኑ ወቅት ቢያንስ 24 አመት የወያኔ አገዛዝና በርካታ አመታት የወያኔ ፌዴሬሽን ተብዬ ተመክሮ በኋላ የፌደራሊዝምን መነሻና ፅንሰ ሃሳባዊ የፖለቲካ ፍልስፍና ታሪካዊ አመጣጥ አስመልክቶፌዴሬሽን ሲሉ ፌዴሬሽን ስንልበሚል ርዕስና በሌሎችም ቀደም ብለን ገና ከመጀመሪያውኑ በርካታ መጣጥፎችን ያቀረብንበት መሆኑ የሚታወስ ነው። ስለሆነም ባሁኑ ወቅት ሕዝባችን በቂ እውቀት አለው ብለን ስለምንገምት ወያኔዎች እያደረጉ ስላሉት ጫጫታ ትችቶችን ማቅረብና እንካ ሰላንቲያ መግጠም የምንሻ አይደለንም።  ባሁኑ ወቅት የወያኔ አገዛዝና ባለሟሎቹ የፈለጉትን ቢቀባጥሩ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ያለው የአስተዳደር አወቃቀር ፌዴራላዊ የመንግሥት ሥርአት፡ የሥልጣን ተዋረዱም ያልተማከለ ሲሆን፡ ብሔር፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መሰረት ያደረገ ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ባለቤትነታቸውን ያረጋገጠ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር በኢትዮጵያ ተገንብቷል እየተባለ የሚነገረው በርግጥም ዛሬም ውሃ የማይቋጥር ፕሮፓጋንዳ ከመሆን አላመለጠም። የፌደሬሽን ሥርአት  በቴሌቪዥን መስኮቶችም ሆነ በአደባባይ ባሕላዊ ዘፈኖችንና ዳንኪራዎች በማሳየት የሚገለፅ አይደለም። ከዛ በላይ የሚሄድ ነው። ለምን?
1. በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ ስለ ዴሞክራሲና ስለ ሰብአዊ መብቶች መከበር ጠግበን ቋቅ እስከሚለን እንዳንቆረቆረልን ሁሉ ስለ ፌዴሬሽን ምንነትና ይዘትም ተመሳሳይ ትረካ ባለፉት አመታት ማድረጉ የሚታወስ ነው። አሁንም ካለፈው በበለጠ ይኸው ፕሮፓጋንዳ በቀጣይነት እየተሰበከልን ነው። ታዲያ የሚያወራውንና ተግባራዊ አደርጋለሁ የሚለውን በተጨባጭ ለመፈተን የሞከሩና፡ የፍትህና የመልካም አስተዳደር እጦት ታክሎበት በተጨባጭ የማስመሰያ ዘዴ መሆኑን ያረጋገጡ በርካታዎች ብቻ ሳይሆን  ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል። ይህ ገሃድ አልዋጥ ያለው የወያኔ አገዛዝ ግን የተለያየ ሥም እየለጠፈባቸው ይገኛሉ። በዚህም የተነሳ ውድ ሕይወታቸውን ከማጣት ጀምሮ ለእስር፤ ለተለያዩ እንግልቶች፡ ስቃይና በደል ተዳርገው አካለ ጎደሉ የሆኑ፡ ሕሊናቸው የተቃወሰ፡ ኑሯቸው የተበላሸ፡ ለስደት የተዳረጉ ዜጎቻችን ቁጥራቸው በርካታ ነው። ይህ ኢሰብአዊ የሆኑ ድርጊቶቹ አሁንም በቀጣይነት እያካሄዳቸው ያሉ ጉዳዮች ናቸው። 
በዚህም የተነሳ ሕዝባችን የተገነዘበው አንድ ሀቅ ቢኖር ማውራትና፡ ማስመሰል፡ በገቢር ደግሞ ሆኖ መገኘት የተለያዩ መሆናቸውን ነው። በወያኔ አገዛዝ የተጫነበት ሥርአት ከሰብአዊና ደሞክራሲያዊ መብቶች፡ ከዜግነት፡ ከነፃነት፡ ከሕግ የበላይነት፡ ከሀገርና ከሕዝብ ሉአላዊነት መከበርና ማስከበር አንፃር ሲታይ በብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት ማስከበር ሥም የተሸፈነ ካለፉት ሥርአቶች ሊለይ ያልቻለበት ፀረ ዴሞክራሲ የሆነ፡ አልፎ ተርፎም የአንድ ድርጅት አምባገነናዊ ሥርአት የተጠናከረበት ሁኔታ መከሰቱን ነው። ቀናቶች በወራት፡ ወራቶች በአመታት እየተተኩ በሄዱ ቁጥር መብቶች በርግጠኝነት ሲከበሩ ለማየት አልተቻለውም።
ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ አይከበሩለትም። የፖለቲካ ባለሥልጣንነቱ ተረግጦበታል። የአንድነቱ ዋልታ ከሥረ መሰረቱ ተቦርብሮበታል። የተወሰነ አካሉ ተቆርጦበታል፡ ፍትህና የሕግ የበላይነት የውሃ ሽታ ናቸው። ሙስና በጣም ተስፋፍቶበታል። ኤኮኖሚው አድጓል እያሉ ቢለፈልፉለትም የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ ኑሮዉን ክፉኛ አጎሳቅሎበታል። የሀገር ባለቤትነቱ ተሽሮበታል። ሕዝባዊ አንድነቱ ተቃውሶበታል። ኢትዮጵያዊ ዜግነቱ ተቦርብሮበታል።  ፍቅርን ሳይሆን አላስፈላጊ የርስ በርስ ጥላቻ በመካከሉ ተዘርቶበታል። የተዘራ ነው የሚታጨደውና ይህን መጥፎና አሰቃቂ አደጋን የሚያስከትል ቅስቀሳ አቁሙ ተብለው ቢመክራቸውጆሮ ዳብ ልበስ መልሳቸውን ለግሰውታል። ክፉኛ አሳዝነውታልም።
ከአደረጃጀት አንፃርም ሕገ መንገሥቱና ተግባራዊነቱ፡ በፌዴራሉም ሆነ በክልል ደረጃ ስለተደላደለው የሥልጣን ክፍፍል፤ ክልሎች ራሳቸውን ለማስተዳደር ስላላቸው ችሎታ፤ ሚዛናዊና የተመጣጠነ የህብት ክፍፍልና የገቢ ምንጮችን በፍትህ መርህ መደልደል ስለመኖር፤ በፖለቲካው የውሳኔ ሂደት የሚኖራቸው ተካፋይነት፤ ስለ ነፃ የዳኝነት መኖር፤ በማዕከሉ የአስተዳደር ተቋማት ውስጥ ሆነ በክልሎች መካከል ወይንም ደግሞ በተቋማቱ መካከል ሊፈጠሩ የሚችሉትን ችግሮችን ስለመፍታት፡ በጠቅላላ ሀገሪቷም ሆነ በክልሎች ውስጥ የመድበለ ፓርቲ ሥርአት መኖር በነዚህና በሌሎችም መሰረታዊ በሆኑ ርዕሶችን አስመልክቶ በወያኔ ተገነባ የሚባለውን የፌደራል ሥርአት ስናጤነው የምናገኘው አንድና አንድ ውጤት ብቻ ነው። እሱም በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካገኙ የፌዴሬሽን መርሆዎች ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ነው።
ፌዴሬሽን በአሁኑ በምንገኝበት ወቅት በመርህ ደረጃና በመልካም አማራጭነት  የሚድገፍ እንጂ የሚነቀፍበት ምክንያት ባይኖርም ተግባራዊ አፈጻጸሙ ከፍተኛ ጥንቃቄ ካልታከለበት ዞሮ ዞሮ አምባገነናዊነት የሚጠናወተው መሆኑ በርካታ ተመክርዎች የሚያረጋግጡት ነው በማለት ቀድሞውኑ ገልፀን ነበር። የተከሰተውም ደግሞ ይኸው ነው። የወያኔ ፌዴሬሽን ቀመር የዴሞክራሲንና የነፃነት መርሆዎችን ያልተላበሰ ከመሆኑ ሌላ ሕዝብ መክሮበት፤ ዘልቆበት፡ ያዋጣኛል፡ ችግሬን ይፈታልኛል በማለት አምኖ የተቀበለው ሳይሆን በታሪክ አጋጣሚ ከሥልጣን በተቆናጠጠው ወያኔና የሱ ተለጣፊ በሆኑት ድርጅቶች አማካኝነት ብቻ ከላይ ወደታች በሕዝብ ላይ የተጫነ በመሆኑ በነበሩት ችግሮች ላይ ሌሎች እየተደራረቡ በሰው ሕይወትና በሀገር ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት፡ በሕዝቡም ከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት አስከትሎ ይገኛል። በሂደት ይታረማሉ በማለት ትዕግስቱን ቢለግሳቸውም በተላላነት በመውሰድ ምላሻቸው እብሪት መሆኑን አረጋገጡለት። ከሰላማዊ የትግል ሥልት ባሻገርም ሞክረን ብለው መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ ሲሉም ተሳለቁበት።
2. የወይኔ የፌዴሬሽን ቀመር ጥፋቱ እንደ ዴሞክራሲ ሁሉ ከልቡ በፍፁም የማያምንበት በመሆኑ ነው። ይህ ብቻ አይደለም። ከመጀመሪያውኑ የወያኔ አላማ የኢትዮጵያን ሕዝብ በጠቅላላ ባለሥልጣንነቱን ለማወቅና ለማክበር ሳይሆን በሱ አጠራርብሔር፡ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  ብቻ ለይቶ የሥልጣን ባለቤት በማረግ የራሱን ብቸኛ የአንድ ድርጅት ወደኋላ እንደታየውም የአንድ ግለሰብ አምባገነንነትን ሕጋዊነት ለመስጠት ነበር። አንቀጽ 8 1. በሕገ አገዛዙ የሰፈረበት ዋና ምክንያትም ይህንኑ የሚያመላክትና በምሳሌነት ሊወሰድ የሚችል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው የኢትዮጵያ መሬትና በከርሰ ምድሯ ውስጥ ያለውን የማዕድንም ሆነ የተፈጥሮ ሀብት የጠቅላላ ሕዝብ ነው በማለት በራሱ ሙሉ ቁጥጥር ሥር አድርጎ በአሁኑ ወቅት ለመገንዘብ እንደሚቻለው ለም የሆነውን የርሻ መሬት እንዳሻው ለባዕዳኖች እየቸረቸረና ቀዬውን ሕዝብ እያፈናቀለ ለከፋ ችግር እየዳረገ የሚገኘውም በዚሁ ምክንያት ነው።
3. በወያኔ ሕገ አገዛዝ አንቀጽ 47 1. የብሔረሰቦችና ብሄሮችን ራስን በራስ ማስተዳደር በሚል ሳቢያ ኢትዮጵያን በቋንቋ (በዘር ማለቱ ይሻላል) በማዕከላዊና በክልል አስተዳደር እንድትከፋፈል አድርጎ የፌደራል መርህ የሚከተል ለማስመሰል ቢጥርም ሀገሪቷና ሕዝቦቿ በጠቅላላ በአንድ ድርጅትና በሱ ተለጣፊዎቹ ሙሉ ቁጥጥር ሥር ያደረገና ሕዝብን አግላይ የሆነ ፖሊሲ ነው። የሥልጣን ክፍፍል ለባዕዳን የመሸንገያ ቃል ከመሆን አላለፈም። ይህ ሁኔታ የኋላ ኋላ ከፍተኛ አደጋ ያስከትላል ተብሎ በበርካታ ሀገር ወዳድና ለሕዝብ ቀናኢ ኢትዮጵያዊያን ቢገለፅም ሥልጣኑንና የበላይነቱን የሚሽርበት ሆና ስላገኘው ሊቀበለው አልተቻለውም። የመጨረሻው ምርጫ ተብዬ ውጤትና ሕዝብን ለማጃጃል የሚሰጣቸው ምክንያቶች የዚሁ ውጤቶች ናቸው። የፖለቲካ ፍላጎት ግንባታን ለብቻው እየቀረፀና እየወሰነ ያለውም የዚሁ ነፀብራቅ ነው። በተለይ ይፋ ባልሆኑ የውሳኔ አወሳሰድ በወያኔ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሥር ያለ መሆኑ ሥልጣን የት እንዳለች ግልፅ የሚያደርግ ነው። በነሱ በድብቅ የተወሰነው ውሳኔ ተግባራዊ የሚሆነው በወያኔ ካድሬዎች ነው። የወያኔ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ በኢሕአደግ ሽፋን ነገር ግን በፓርቲው አባላት ተፈፃሚ ተደርጎ የነበረው የአምስት አመት ፕላንም ሆነ አሁን ደግሞ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ የተሰኘው የተጠነሰሱትና ተግባራዊ እንዲሆን የተወሰኑት በዚሁ አካሄድ ነው።
4. ለፌደራሊዝም ሥርአት መኖር አስፈላጊ የሆነው የሥልጣን ክፍፍል በሀገሪቱ ውስጥ በወያኔ የበላይነት ተግባራዊ ሆኗል ተብሎ መጠነ ሰፊ ፕሮፓጋንዳ ቢነዛም ዛሬ 24 አመት በኋላ የተረጋገጠውና በተጨባጭ ሰፍኖ የሚታየው ብሄር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እየተባሉ የሚቀለድባቸው ዘፈንና ዳንኪራ በአደባባይና በቴሌቪዥን መስኮት ከማሳየት ውጭ የተቀዳጁት የፖለቲካ ሥልጣን አለመኖሩን መካድ የሚቻል አልሆነም። ወያኔ በሚመፃደቅበት ሕግ አገዛዙ ውስጥ የሰፈሩት መብቶች የተፃፉበትን ወረቀት ያህል እንኳ ክብደት የሌላቸው፤ ባሳኘውና በፈለገው ጊዜ በክልሎቹ የውስጥ ሁኔታ ጣልቃ እየገባ የሚሽራቸው ሆነው ነው የተገኙት። በክልል ተካለው የሚገኙት ዜጎቻችን በነፃ ያለ ምንም የወያኔ ጣልቃ ገብነት የራሳቸውን በጀት ለማውጣት፡ የራሳቸውን መሪዎች ለመምረጥ፡ የፍርድ ተቋሞቻቸውና ውሳኔዎቻቸውን ተግባራዊ ለማስደረግ የሚችሉ እንዳልሆኑ በራሳቸው ተመክሯቸው የተረጋገጠ ነው። ለምሳሌ በጋምቤላ ክልል አንድ የቀድሞ ርዕስ መስተዳድርን በዋስ ፈትታችኋል በሚል ምክንያት በክልል መስተዳድሩ ትዕዛዝ ችሎት ላይ ተቀምጠው የነበሩ ዳኞች መሳሪያ በታጠቁ ወያኔዎች ወደ እስር ተወስደው ለወራት የታሰሩት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በጉልህ ምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል ነው።
5. የወያኔ አገዛዝ በመዲናዋ በአዲስ አበባ ዋና መቀመጫውን አድርጎ ሕዝብን በማነቆ የመያዣ መረቡን ግን በመላው ሀገሪቷ ዘርግቶና አስፋፍቶ በኤኮኖሚ፡ በልማትና በእድገት መስክ ራሱ ባመቸውና ለሱ በሚጠቅመው ሁኔታ እቅድ የማውጣትና የማስፈፀም ሥልጣኑን በራሱ ሙሉ ቁጥጥር አድርጎ ሲያላግጥ የሚታይ ነው። የሱ ተለጣፊና በሱ ሙሉ ቁጥጥር ሥር ያሉ ቡድኖችን በየክልሉ በአስተዳዳሪነት ቢሾማቸውም፤ በራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ተመሳሳይ ተግባር ሊሰሩ ይችላሉ እያለ ቢያጃጅላቸውም በተጨባጭ ዋና አቀናባሪና አስፈፃሚ ራሱ ብቻ መሆኑን በተደጋጋሚ አረጋግጧል።
እነዚህን የክልል አስተዳዳሪ ተብዬዎች አሰኝቶት እንደሾማቸው ሁሉ እንዳሻ የሚሽራቸው ናቸው፡፡ በተሰጣቸው ቦታ ተረጋግተው የራሳቸውን መሰረት አበጅተው ከአጥር እንዳይዘሉ ለማድረግ፡ በሥራቸው የራሱን ሰላይና ተቆጣጣሪዎችን በሥራቸው የኮለኮለባቸው ናቸው። ዋና ባለሥልጣናቱም እነኚሁ ናቸው። ባጭሩ የክልሎች መስተዳድሮች ከፌደራል መስተዳድር ጋር በእኩልነት የሚተያዩ ሳይሆኑ በማናቸውም ረገድ የበታች አካላትና ከሕዝብ ፍላጎት ይልቅ የገዢውን ፍላጎት በአስፈፃሚነት የተቀመጡ ናቸው። ሥርአቱ የራስ አስተዳደርንና የጋራ አስተዳደርን አጣምሮ የያዘ አይደለም።
ነፃነት ዛሬም የሕልም እንጀራ እንደሆነች ትገኛለች። ክልሎች ያላቸው ሚና በወያኔ የታቀደውንና የተወሰነውን እቅድ በተግባር የመፈፀም ብቻ ነው። ላለፉት 24 አመታት በራሱ ሕይወትና የቀን ተቀን ኑሮው ወሳኝ ተመክሮ ያካባተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀርቶ በርካታ ምሁራኖችም ጭምር የወያኔ ፌደራሊዝም የአፋዊ ፌደራሊዝም፡ የባሕል ብዛትነት መኖርን የሚያሳይ እንጂ የሥልጣን ባለቤትነታቸውን ያረጋገጡበት፡ የፖለቲካ መድበላዊነትን የሚያንፀባርቅ አይደለም በማለት ትችታቸውን እየሰነዘሩ የሚገኙት። ለዚህም ነው በወያኔ ግንዛቤና በሕዝብ ትክክለኛ ስሜት መካከል ለዘብ ባለ አገላለፅ ከፍተኛ ርቀት ያለው ክፍተት የተፈጠረውና ለመጥበብ የማይችል በቅራኔ የተሞላ ነው። ይህ ቅራኔ ሊፈታ የሚችለውም ወያኔን በማስወገድ ብቻ ነው ተብሎ በፅናት የሚገለፀውም በዚሁ ምክንያት ነው።
6.  በተመሳሳይ ሁኔታም በትምህርትም ሆነ በጤናም መስክ የሚንፀባረቁት የዚሁ ፖሊሲ ውጤቶች ናቸው። ወያኔ ለክልሎች ሰጠሁ የሚለውን ስልጣን በተከታታይ እየጣሰ የራሱን አላማ ብቻ ሲያስፈጽምና አሁንም እያስፈፀመ ያለ መሆኑ በገሃድ የሚታይ ነው። ወያኔ 1994 .. በትምህርት መስክ፡ 1997 .. ባህልን አስመልክቶ  የወሰዳቸው እርምጃዎች ይህንኑ የሚያረጋግጡ ናቸው። በፍርድ ተቋሙም ሥልጣን ላይ ከተቆናጠጠ ጀምሮ እየወሰደ ያላቸው በሙሉ የመቆጣጠር ድርጊቶች ፍትህና የሕግ የበላይነት በክልልም ሆነ በማዕከላዊ ደረጃ እንዲሰፍኑ ሳይሆን እንዲያውም በዜጎች ሕይወት ላይ ማላገጫ እየተደረጉ ለመሆናቸው ማስረጃ አምጡ ብሎ ደፍሮ የሚጠይቅ በፍፁም ሊኖር አይችልም።
7. የገቢ ምንጭ እመዳደብም ሆነ በቀረጥ አሰባሰብም ቢሆን ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚገኝበትን የገቢ መሰብሰቢያ መስኮች በራሱ ቁጥጥር ሥር አድርጎ ከላይ በሚሰጠው ትዕዛዝ እቅድ ማስፈፀሚያ ግን አስፈላጊውን የገንዘብ አቅም ክልሎች እንዲያገኙ አይደረግም። ክልሎች በተሰጣቸው አስተዳደራዊ ተግባርና በሚሰበስቡት ገቢ መካከልም ያለው ግንኙነት ያልተመጣጠነና የክልሎችን ጥገኝነት ብሎም ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደርያላቸው ችሎታ በታም ዝቅተና መሆኑን የሚያሳይ ነው። የቀረጥ ገቢ አሰባሰብና የገንዘብ ድልደላ ድርጊቶችን ስንቃኝም የሚያሳየው የወያኔ(ፌደራል) የበላይነት የሚያረጋግጥ ነው። ባጠቃላይ መስክ የሚገኙ አስተዳደሮች የስልጣን አደላደላቸው ሙሉ በሙሉ ወደ ወያኔ ያደላና አምባገነንነት የሰፈነበት ሥርአት በመሆኑ እኩልነትን ከሚያረጋግጥና ለዴሞክራሲ መዳበር ዋና መሰረት ከሆነው ከፌዴሬሽን መርህ ጋር በጣም የሚጣረስ እንደሆነ ምስክር መጥራት አያሻውም።
ሌላው 2002 .. የተጀመረው ለወረዳዎች የተወሰነ ሥልጣን እንዲያገኙ ለማድረግ ተብሎ የወጣው ለውጥ/ማሻሻያ ሕግ ነው። የለውጡ ዋና እምብርትም ወረዳዎች የበጀት ሥልጣን እንዲኖራቸው ለማድረግ የታሰበ ነው። ይህ የማሻሻያ ሕግ እስከሚወጣበት ድረስ ወረዳዎች ለአስተዳደር ተግባር የሚሆናቸውን በጀት የሚደለደልላቸው በክልሎቻቸው ነበር። 2002/2003 .. .. ጀምሮ ግን በአራት ክልሎች(አማራ፡ ኦሮሚያ፡ ደቡብ ሕብረትና ትግራይ) ድጎማ በክልል እየተሰጣቸው ድልደላውን በሚመለከት ራሳቸው ይወስናሉ። ይህ ለወረዳዎቹ 50 እስከ 80 በመቶ የሚሸፍን የድጎማ አሰጣጥ የክልሎቹን የፖለቲካ መጫወቻ ምህዳር እንደሚያጠብባቸው ግልፅ ነው። ይህም በበኩሉ የክልሎቹን ሉአላዊነት፡ የሥልጣን ባለቤትነታቸውን የሚገደብ፡ የፌዴረሽንን ዋና መርህ የሚጥስ ለመሆኑ ከጥያቄ የሚገባ አይደለም።
8.  በወያኔ ሕገ አገዛዝ አንቀፅ 53 መሰረት ሁለት ምክር ቤት እንዲመሰረቱ የሚፈቅድ ቢሆንም በአንቀፅ 61 መሰረት ግን ሁለተኛው ምክር ቤት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተብዬከብሔር፡ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችብቻ እንዲወከሉ የተደረገ በአንቀፅ 62 መሰረት ደግሞ የዚህ ምክር ቤት ሥልጣን በዋናነት ሕግን የመተርጎም ሲሆን በክልሎች መካከል ለሚነሱ አለመግባባቶችን የመዳኘትና እንዲሁም ለአስተዳደር ተግባራት የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ለክልሎች በመደልደል ብቻ የተወሰነ ነው። አጠቃላይ በጀት የመወሰን ሥልጣን ጨርሶ የሌለው፡ ሕግ የማውጣት ሂደትም የራሱን የሕግ አውጪ የመሆን፡ ወይንም ደግሞ ፌደራል አስተዳደሩ በሚያወጣቸው ሕጎች ላይ የማገድ ሥልጣን የሌለው በመሆኑም የፌደራሉ የበታች አካል እንጂ በሁለተኛ ምክር ቤት ለመወሰድ የሚቻል አይደለም። የወያኔ ሕገ አገዛዝ የመተርጎም ሥልጣን የተሰተውም ለዚሁ ነፃና ገለልተና ላልሆነ ምክር ቤት ነው። ይህም በመሆኑ የሥልጣን ክፍፍል መርህ ከመጀመሪያዉ የሌለ መሆኑን ገላጭ ነው።
9. ፍትህ፡ መልካም አስተዳደር፡ ዴሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች መከበር የተሰኙ ሕሊናን የሚያነሆልሉ ቃላቶች ሕገ መንግሥታችን በሚሉት ሰነዳቸው ቢያካቱቷቸውም በእሴቶቹ ላይ የይዘትና የአተገባበር ልዩነቶች ቢኖሩንም ዋናው ችግሩ ሕዝቡ በነሱ ላይ እንኳ ተመርኩዞ እንዲያዳብራቸው ለማድረግ በተግባር መረጋገጥ አለመቻላቸው ነው። የራሳቸው አፈቀላጤዎች እንኳ ሳይቀሩ ተግባር! ተግባር እያሉ የሚገኙት በዚሁ ምክንያት እንጂ በሌላ አይደለም። ለዚህም ነው የተጻፉበትን ወረቀት ያህል እንኳ ክብደት የሌላቸው ናቸው ተብለው የሚገለፁት። ይህም በመሆኑ ነው የወያኔ አገዛዝ በሕዝብ ትግል ሲደመሰስ ሕገ አገዛዙም አብሮ የሚደመሰሰው። ይህ ስኬታማ ሲሆን ደግሞ በአዲስ መልክ ሌላ በህዝብ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ የሚቀረጽ ሕገ መንግሥት ይደነገጋል ተብሎ የሚነገረው። ያኔ በዚሁ ሕገ መንግሥት በመመርኮዝ ዴሞክራሲን በበለጠ የሚያዳብር የፌደራል መርህ ተግባራዊ ይሆናል። በህዝብ ፍላጎት ላይ የሚመሰረት ስለሚሆንም ሰላም ይሰፍናል። ግልፅነት፡ ተጠያቂነት፡ መልካም አስተዳደር የመሸንገያ ቃላቶች መሆናቸው አብቅቶ የሕዝብ መገልገያ ይሆናሉ።
10. ለማጠቃለል የወያኔ የፌዴሬሽን ቀመር የአስተዳደር አመቺነትንና ኤኮኖሚያዊ ትሥሥርን ግምት ውስጥ ያላስገባ፡ ልዩነትን በአንድነት ለማጣጣም ቢልም ለከፋፍለህ ግዛ አመቺ እንዲሆን የተደረገ፡ ዋናው መሰረቱ የሕዝብ ፈቃደኝነት ሳይሆን በግዴታ ከላይ የተጫነበት፡ ለሁሉም ዜጋ በጋራና በእኩልነት የሚያገለግል ነፃ የዳኝነት ተቋም የሌለበት፡ ያልተማከለ አስተዳደር ገንብቻለሁ ቢልም የጠበቀ ከላይ ወደ ታች ትዕዛዝ ውስጥ ለውስጥ በባለሟሎቹ የሚተገበርበት፡ የቋንቋ፡ የማንነትና የባሕል መብቶች በእኩልነት ተከብሯል ተብሎ ቢለፈፍም በቴሌቪዥን መስኮት ከመታየት ያላለፈ መሆኑ፡ ተመጣጣኝ የሀብት ክፍፍልን መሰረት ያላደረገ የኤኮኖሚ ግንኙነት የተዘረጋበት፡ የሁሉንም ወገኖች ሚዛናዊ ተሳትፎ ባላረጋገጠ ሁኔታ ማዕከላዊ አገዛዙን ያሰፈነበት ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ የወያኔ የፌዴሬሽን ቀመር የነፃነትን፡ የዴሞክራሲንና የእኩልነትን መርህ ያልተላበሰ፡ በሰብአዊ መበቶች መከበር ላይ ያልተመሰረተ፡ የሕዝብን አንድነት ተፃርሮ የሚገኝ፡ ዜጎች ለሕይወታቸው ዋና መሰረት የሆነውን ከአደጋ የመታደግ ዋስትና የማይሰጥ፡ ፍትህ በሙስና እየተረገጠች ያለችበት ነው። ዋና መለያውም አምባገነናዊ ሥርአት ነው። ይህንን የወያኔን ሥርአት አጥብቆ በመታገል በምትኩ በሕዝቡ ፍላጎት ላይ የሚመሰረት ዴሞክራሲያዊና ፌደራላዊ አስተዳደር መመስረቱ የማይቀርና አማራጭ የሌለው ነው። የፕሮፓጋንዳ ጋጋታ ለተወሰነ ጊዜ የሚሆን አየር መተንፈስ ነውና ይህ በቀጠለ ቁጥር ራሳቸው በራሳቸው አንገት ላይ ያጠለቁት የመታነቂያ ገመድ እየጠበቀ ሄዶ የማይቀረውን ሞት ማስከተሉ የማይቀር ነው። ይህ ስኬታማ እንዲሆን ደግሞ በበኩላችን ማናቸውንም ከማድረግ ወደኋላ እንደማንል እንገልፃለን። ያለ መብቶች መከበርና ያለ ነፃነት እውቅና ፌደራሊዝም ውጤቱ አምባገነንነት ነው።

ነፃነትን ለተላበሰ ፌዴራላዊ ሥርአት እንዲገነባ መታገል ሀገራዊ ግዴታ ነው።
http://www.finote.org

No comments:

Post a Comment