Wednesday, February 3, 2016

አብዮቶች ሁሌም ይቸነፋሉን? የግብጽ አብዮትና ሽንፈት፥ http://www.finote.org

አብዮቶች ሁሌም ይቸነፋሉን?
የግብጽ አብዮትና ሽንፈት፥ለፍትህ፥ ለመብትና ለእኩልነት የሚካሄዱ ትግሎችን በበጎ አይን የሚመለከቱ ሁሉ ከህዝባዊ አብዮቶች ድክመትና ስህተት ይማራሉ እንጂ ለለውጥ የተደረጉ ተጋድሎዎችን አያወግዙም። አብዮት የራት ግብዣ አይደለም እንደተባለው ትግል እሾኽና አሜከላ የበዛበት ጠመዝማዛ ጉዞ ነው። በሌላ በኩል ያንድን ሀገር ህዝብ ዳር ከዳር  የሚያነቃንቁ ህዝባዊ አብዮቶች የሚከሰቱት ከተራዘመ የህዝብ ስቃይና መከራ በኋላ በመሆኑ አብዮተኞች አጋጣሚውን ላለማጣት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግና የሚሰጡት አመራር ህዝብ የተመኘውን የተሟላ ድል ለማጎናጸፍ ብቃት ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። በርግጥ ህዝባዊ አብዮት በመላው ህ/ሰብ ተሳትፎ የሚካሄድ ትግል ነው። ይሁን እንጂ ትግሉ በጠንካራ ድርጅት መመራቱ ደግሞ ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ ነው። እዚህ ላይ ድርጅቶች ትግሉን በማደራጀትና አቅጣጫ በማስያዝ በየደረጃው የሚጠይቀውን አመራር ይሰጣሉ ሲባል ህዝብን ይተካሉ ለማለት አይደለም። የድርጅቶች ጥንካሬም ከህዝቡ የትግል እድገት ደረጃ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም።       
 የህዝባዊ አብዮቶች ድልና ሽንፈት ሁሌም ከድርጅቶች ጥንካሬና ድክመት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ስለመሆኑ ከመጀመሪያው የላባደሮች መንግስት (ፓሪስ ኮሚዩን) እስከ ቅርቡ የአረቡ ዓለም አብዮትና የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮትን ጨምሮ በመካከሉ የነበሩትን ትግሎች ታሪኮች ማጤን በቂ ይሆናል። 
የቀደሙቱን ትተን የቅርቡን የግብጽ አብዮት እንኳ ብንመረምር ከመነሻው መላውን ህ/ሰብ ያሳተፈ ታላቅ ቁርጠኝነት የታየበት የዓለምን ህዝብ ቀልብ የገዛ እንቅስቃሴ ነበር።  የግብጹ አብዮት አምባ ገነኑን ሙባረክ እስካስወገደ ድረስ መላው ግብጻዊ ጉዳዬ ብሎ ብቻ ሳይሆን የምዕራባውያንን አብዮት የማክሸፍ ስልት ተቋቁሞ የዘለቀ ሴቶች ህጻናትና አረጋውያንን በየሰልፉ በንቃት በማሳተፍ ግርማ ሞገስ የተላበሰ ድንቅ ህዝባዊ አመጽ ነበር። ይሁን እንጂ እንደ ብዙዎቹ ያልተሳኩ አብዮቶች  አንድን አምባ ገነን በሌላ አዲስ አምባገነን በመተካት ተጠናቋል። `አምባ ገነንን በማውረድ አምባገነንነትን ማስቀጠል` የሚለው የምዕራባውያን አብዮት ማኮላሻ ስልት ግብጽም ላይ ሰርቷል። ዛሬ የመብት ጥያቄን በተመለከተ ግብጻውያን የሚገኙበት ሁኔታ ከአብዮቱ በፊት ከነበረው ቢብስ እንጂ የተሻለ አልሆነም። ሁሌም እንደሚሆነው አብዮቶች ተነሰተው በወደቁ ቁጥር ሁሉም እንደየፍልስፍናውና እንደየአመለካከቱ የየራሱን ትንታኔና ምክንያት ያቀርባል። ምዕራባውያንና ሎሌዎቻቸው ባንድ በኩል የግብጹን አብዮት እንደተሟላ ድል ሊያቀርቡት ሲሞክሩ (ሙባረክ ተወግዷል በሚል) በሌላ በኩል ደግሞ ሊከሰቱ የሚችሉ ቀጣይ አብዮቶችን ቅስም ለመስበር የአብዮትን ውድቀት አይቀሬነት ያስተጋባሉ። ትግሉን በተመልካችነት ያሳለፉ ሀሞተ ቢሶችና የሽንፈት ደላሎችም `ብለን ነበር` የሚለውን አጭበርባሪ ማምለጫ ይሰብካሉ። 

ሳይመን ጀንኪንስ የተባለው ጸሐፊ ለምሳሌ አብዮቶች ለምን እንደሚሸነፉ ሲገልጽ `
`ተራው ህዝብ ህብረተሰብን የመምራት ብቃቱ ስለሌለው ነው`
`አብዮቶች ሁሌም ማፍረስ እንጂ መገንባት አይሆንላቸውም` ሲል ጽፏል።

ሁለቱም አመለካከቶች የተሳሳቱ ናቸው። በመሰረቱ አምባ ገነንነትን መታገል በራሱ የሚከበር ግዳጅ ሆኖ ሳለ ትግሉ ግቡን ስላልመታ ብቻ ሙከራውን ማራከስ ቢያንስ ቢያብስ ከሞራል አንጻር ትክክል አይደለም። ባለመታገል መሳሳትን ማምለጥ ይቻላል፣ ጭቆናና የመብት እጦትን አሜን ብሎ መቀበል ነው እጅግ አሳፋሪው ተግባርና  ሰው የመሆን ምልክትም ያልሆነው።  በሌላ በኩል የግብጹ አብዮት ድል አድራጊ ነው የሚለውም አባባል እንዲሁ ከእውነቱ የራቀ ነው። ግብጻውያን የሙባረክን መወገድ የትግላቸው አልፋና ኦሜጋ ቢያደርጉት ኖሮ ዛሬ ድረስ የዘለቀና ምሬት የተቀላቀለ የእንቢተኝነት ቀጣይ እንቅስቃሴ ማካሄድ ባላስፈለጋቸውም ነበር።  የአንድ ህዝባዊ ትግል ድል የሚለካው በተወገደው ሀይል  ምንነት ብቻ ሳይሆን በሚገነባውም ስርአት ምንነት ጭምር ነውና ሙባረክን ማስወገድ የድሉ የመጀመሪያ ምዕራፍ እንጂ በራሱ የፍጻሜው ድል አልነበረም።  የግብጽ ህዝብ የታገለው አምባገነን ጄነራል የሚመራውን መንግስት ለስልጣን ማብቃት እንዳልሆነ ማንም የሚስተው አይሆንም።  

ያለአግባብ `የፌስ ቡክ አብዮት` የሚል ስያሜ የተሰጠው የግብጹ ህዝባዊ አብዮት ለመጨረሻው ድል የሚያበቃውን መጣኝ ድርጅት አላገኘም ሲባል ትግሉ ተጀምሮ እስኪያልቅ መሪና አሰባሳቢ አካል ያልነበረው ፌስ-ቡክ ላይ የተሰባሰቡ ሰዎች አንድ ቀን ድንገት ያካሄዱት አመጽ ነው የሚል አንድምታ ለመፍጠር አይደለም። አንድ አደባባይ ላይ የተለያዩ የአፈናና ጨካኝ የግድያ እርምጃዎችን ተቋቁሞ ለ19 ቀናት በቁርጠኝነት የዘለቀ እንቅስቃሴን ያለ ድርጅት እውን ማድረግ የማይታሰብ ነው። በተጨማሪም ትግሉ በተለያዩ ከተሞች የተለያዩ የህ/ሰቡን ክፍሎች ያሳተፈ መሆኑና በቅንጅትም የተከናወነ መሆኑ ከፌስ ቡክ ያለፈ መሬት ላይ ያለ ድርጅት መጠየቁ የሚያጠራጥር አይደለም። በርግጥ ፌስ ቡክና መሰል ማህበራዊ ሜዲያዎች መልእቶክችን በማሰራጨት ህዝቡን ከማደራጀት አኳያ ጠቃሚ ሚና ተጫውተዋል። ይሁን እንጂ ትግል ፌስ ቡክ ላይ ተጀምሮ እንደማያልቅ መረዳቱ ከስህተት ያድናል።  የግብጻውያን አብዮት እንደማንኛውም አብዮት ሁሉ ተጨባጭ የሆኑ ኤኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች የፈጠሩትና ይህ ሁኔታ የፈጠረውን ብሔራዊ ችግር በማስወገድ ዙሪያ የተደራጀ ትግል እንጂ አንዳዶች እንደሚሰብኩት  `ፌስ ቡክ` ላይ የተጀመረ እንቅስቃሴ አይደለም። የዚህ አሳሳች ድምዳሜ ሰለባ የሆነ አንድ የሰሜን አሜሪካ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ ቁጥራቸው በዛ ያለ የፌስ ቡክ ተከታዮች አሉኝ በሚል አብዮት አደባባይ እንገናኝና እናምጽ የሚል የተደጋገመ ጥሪ ማቅረቡን አስታውሳለሁ። ያላደራጀውን ህዝብ! ትግል በድርጅት፥ በህግና በስርአት እንጂ እኔም ልሞክረው በሚል በነሲብ የሚመራ የሆነ ቅን ሰዎች ሰብሰብ ሰብሰብ በሉ ተባብለው የሚያካሂዱት ጉዳይ አለመሆኑን ካለመገንዘብ የመጣ ስህተት ነበር።  
   
ኢትዮጵያውያን የግብጻውያንን ለመብት መከበር ያካሄዱትን ትግልና የከፈሉትን መስዋእትነት ስናደንቅ ከሽንፈታቸው ደግሞ ለመማር መሞከራችን እያስገመገመ ላለውና አይቀሬ ለሆነው ሁለተኛው የሀገራችን አብዮት ስንቅ ስለሚሆነንም ጭምር ነው። ለግብጽ አብዮት ግብ ያለመምታት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ አያሌ ምክንያቶችን መዘርዘር ቢቻልም መሰረታዊ የሆነው ምክንያት ግን ትግሉ በጠንካራ ድርጅት ያለመመራቱ ነው።  እንደ እውነቱ ከሆነ ከላይ የተጠቀሰው የግብጻውያን ትግልና ሽንፈት ታሪክ በተለያየ መልኩ እስከ ዛሬ የተካሄዱና ለግብ ያልበቁ ህዝባዊ ትግሎችን ሁሉ ያስተጋባ ነው ቢባል ከእውነት የራቀ አይደለም።  በተለይም የ1966ቱን የኢትዮጵያ አብዮት ተሳታፊ ለነበረውና አሁንም ለቀጠለው ትውልድ የግብጹ አብዮት ጉዞ ብቻ ሳይሆን ፍጻሜውም ምን ሊመስል እንደሚችል ከሞላ ጎደል ግምቱ ነበረውና የሆነው ሁሉ ያልተጠበቀ አልነበረም።          

   
አብዮት ያረገዘባት ሳይሆን እጅግ በጣም በዘገየባት ኢትዮጵያችን `አብዮት` የሚለው ቃሉ ራሱ ለአመታት ህቡእ ገብቶ ከግዞት አምልጦ ብቅ ያለው ወያኔ ሰራሹና `ሰላማዊ ሽግግር` የተባለው የ`መላ` ፖለቲካ ቅዠትና ውዥንብር ማጭበርበሪያነቱ አላዋጣ ከሚል ደረጃ በመድረሱና የወያኔውም ቡድን አፍአዊ `ዴሞክራሲ` ገጽታ እርቃኑን በመቆሙ ሲሆን የጋንዲና ማርቲን ሉተር ኪንግ ወራሾች ነን የሚሉ `የሰላማዊ ትግል` አባወራዎች ድንገት አብዮተኞች፥ የትጥቅ ትግል ወይም ሞት! ፊት አውራሪ ሆነው ብቅ ሲሉ ነው። የአረቡ አለም የጸደይ አብዮት መቀጣጠልም ይህንኑ ስሜት ግፊት እንደሰጠው አይካድም።   ኢህአፓን ከመሰሉ ጥቂቶች በስተቀር `ወያኔ` `አንድነት` እና `ኢትዮጵያ` ከተባሉት ቃላት ባልተናነሰ ሁኔታ`አብዮት` የሚለውን ቃል  ላለመጥራት ተቃዋሚ ነን የሚሉ ክፍሎች የዳያስፖራዎቹም ጭምር ወያኔን ላለማስቀየም በራሳቸው ላይ የሳንሱር ማእቀብ ጥለው እንደነበር የምንዘነጋው አይደለም።  ሁኔታው እዚህ ደረጃ እንኳ ለመድረስ ምን ያህል እንደተጓዝን አመላካች ነው። ነገርን በስሙ እንዲጠራ ለማድረግ እንኳ ትግል ጠይቋል። 
በሀገራችን አሁን ትግሉ በደረሰበት ደረጃ የአብዮትን መከሰት አይቀሬነትን ማንም አሌ ሊለው ከማይችልበት ደረጃ የደረሰ ቢሆንም ከትግሉ ታክቲክና ስትራቴጂ መራራቅ ባልተናነሰ የድርጅትንም ሚና በተመለከተ እንዲሁ የሰፋ ልዩነት ይታያል። አንዳንዶቹ ሕዝባዊ አብዮት በድርጅት መመራት የለበትም ሲሉ ሌሎች ደግሞ የድርጅት መሪዎች ከድተው የሕዝብን አብዮት ሊያስነጥቁ ይችላሉና ድርጅቶች ሊታመኑ አይችሉም ይላሉ።  ባሳለፍናቸው ጊዜዎች  የህዝቡን ትግል ባደባባይ የሸጡ ግለሰቦችንና ድርጅቶች እንዲሁም የክህደት ጉዞዎች የመሰከርን ቢሆንም በአብዮት ወቅት  ድርጅት ሊጫወት የሚችለውን  የመሪነት ሚና ፍጹም መካድ አይቻልም። 

ትግሉ በጠንካራ ኢትዮጵያዊ ድርጅት መመራት አለበት ስንል ሁሉንም የህብረተሰብ ጥያቄዎች ያካተተና ያስተባበረ  አይነት ትግልን ለሚከፋፍል ለማናቸውም ዓይነት የተናጥል (ሴክታሪያን) አካሄድ ቀዳዳ የማይሰጥ መሆኑን ማረጋገጥ ማለት ነው። ይህን ለማለት ያነሳሳኘ በሰሞኑ እየተካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ ሊያስወግደው የሚገባውን ለመጠቆምና ህዝባዊና ሁሉን አቀፍ የጋራ የትግል ሀይል ሆኖ መውጣት እንደሚጠበቅበት ለማሳሰብም ነው። 

በዘመናችን የህዝባዊ አብዮቶች ሌላኛው ተግዳሮት ከሚታገሉት የራሳቸው አምባ ገነን ባሻገር በምዕራባውያንና መሰል የባእድ ሀይሎች ጣልቃ ገብነት የሚካሄደው አብዮቶችን የማኮላሸት ሂደት ሲሆን ይህም በግብጽና በሌሎች የከሸፉ አብዮቶች ተሞክሮ ተስተውሏል። ይህንን አይነቱንም እኩይ የባእዳን ሴራ  ለማሳካት ራሳቸውን ያዘጋጁና የተባሉት የውጭ ሃይላት ያሰለጠኗቸው ጥብቅ ቅጥረኞች የት የት እንዳሉ ሁሉ ማንም የሚስተው አይደለም። በተለያዩ የአሜሪካን ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪነት ሽፋን እንደ ወታደር የስምሪት ጊዜያቸውን የሚጠባብቁ ቀጣይ ርግማኖች መኖራቸው ድብቅ አይደለም። ይህ ሁኔታ በሀገራችንም የማይደገምበት ሁኔታ ባለመኖሩ ከራሳችንም ከሌሎችም ውድቀት መማሩ የህዝቡን ትግል በሀላፊነት የተሸከሙ ሁሉ ግዳጅ ነው።  

ታጋይና አታጋይ ድርጅቶች በትግል ተወልደው በትግል ሜዳ የሚያድጉ እንጂ ከጂን ሻርፕ ንባብ ወይም አንድ ሰሞን እንደታዘብነው በሴሚናርና ስልጠና የሚገኙ አይደሉም። ጠንካራ ድርጅት ሲባልም በተጋድሎ ታሪኩ በታገለላቸውና በሚታገልላቸው ህዝባዊ ጥያቄዎችና መሪዎቹ ከዳር ተቀምጠው ሳይሆን የትግሉ ግንባር ቀደም ሆነው ራሳቸውን ለመስዋእትነት ያዘጋጁ ሲሆኑ ማለት ነው። 

አብዮቶች ለጊዜውም ቢሆን ተደጋጋሚ ሽንፈት ገጥሟቸዋል ወደፊትም ሊገጥማቸው ይችላል። ይህ ግን የህዝብን የመብትና የፍትሀዊ ስርአት ግንባታ ተጋድሎና የማታ ማታ ድል አይቀሬነት አይቀይረውም። 
ግፍ ለዘለዓለም አቸናፊ ሆኖ ሊኖር አይችልም። ግፍ እስከቀጠለ የግፍ አገዛዝን ለማስወገድ የሚካሄደው ትግል መቀጠሉ ተፈጥሮአዊ ነው። ምክንያቱም ህይወትን የሚወዱ ነጻነትን ግን አጥብቀው የሚሹ ሞት አይፈሬዎችን ህዝብ በትግሉ አምጦ ይወልዳልና የጸረ ደርጉና የጸረ ወያኔው ተጋድሎ ታሪክ ለዚህ ህያው ምስክሮች ናቸው።

የተባበረ ህዝባዊ ትግል አቸናፊ ነው!  
 ህሊና ከቶሮንቶ!

No comments:

Post a Comment