Thursday, February 4, 2016

ብንተባበር እስከምን ባንተባበርስ?!! http://www.finote.org


                                                                                                                                                       

                                    ብንተባበር እስከምን ባንተባበርስ?!!

      
በርካታ ኢትዮጵያውያን መተባበርን ጫና ሰጥተው ይተቻሉ። ሀሳቡ የተቀደሰ ነው። ያለ ህብረት ምን በጎ ነገር አለ?። ያለ ህብረት ብልፅግና፣ ያለ ህብረት ድል የለም። ወያኔ በጫካ ህይወቱ ከሻዕቢያ ጋር ተባብሯል። መተባባሩ ክፋት የለውም። ምን አይነት ትብብር የሚለው ግን ወሳኝ ነው። ወያኔና ሻዕቢያ ሲተባበሩ ያተኮሩት በመንግስት ግልበጣ ላይ ነው። መንግስትን ገልብጦ ሌላ የራሳቸው መንግስት ማቆም። የሀገርን ችግር ለመፍታት የሚለው የዘለቄታ ትልም አልነበራቸውም። ለህዝብ የሚለው ሰበብ ለዕርዳታ ማግኛ ሲያደርጉት አክትሟል። ዕርዳታው ቢገኝም ትግሉ የሌላ ሆኗል። ሻዕቢያና ወያኔ በዐረብ ሀገሮችና በአውሮፓውያን ዕርዳታ የሚፈልጉት ደረጃ ላይ መድረስ ቢችሉም የሚፈልጉትን ለማድረግ ግን አልበቁም። ትግሉ በዕርዳታ ገንዘብ ተሸጧል። የሌላን ትግል ነው የታገሉት። በመሰረቱ የጠራ ራዕይን ሳይዙ መጓዝ የሚያመጣው ችግር ይኸ ነው።

       ምክንያታቸው ህዝብ ቢሆንም፣ የተረዱበትን ቃል ለመፈፀም ሀገርን ለውጭ ሀይል አሳልፎ መስጠትን፣ ህዝብን መክዳትን አስከትሏል። እርስ በርስ ማጋጨትን ዓላማ አድርገው መያዛቸው ግባቸውን ለማስፈፀም ነው። ያም ሆኖ ግን በትብብራቸው አልዘለቁም። በፍቅራቸው አልፀኑም። ለስልጣን ለሀብት ክፍያ እርስ በርስ ተራኩተዋል። የጉዳዩ ባለቤቶችም ይበልጥ የሚያገለግሏቸውን ለመምረጥ ዕድል አግኝተዋል። አንዱን ሸልመው ሌላውን በማዕቀብ ቀጥተዋል። "ተወደድኩኝ ብለሽ አትበይ ጠምበር ገተር – እኛን አንድ ሰሞን እንዲህ አርጎን ነበር።" አባብሏቸዋል። ሻዕቢያ በመቀጣቱ ወያኔዎች ተኩራርተዋል። የሰው ዕቃ መሆናቸውን ዘንግተው በራሳችን እንወስን ብለው ተወራጭተዋል። እናም "ሁለት ባለ ትከል አንዱ ቢሰበር ባንዱ ተንጠልጠል" በሚል ቻይናን ሁለተኛ ወዳጅ ለማድረግ ውስጥ ውስጡን አሲረዋል። ቻይናና አሜሪካንን በፈረቃ ለመጠቀም ከጅሏቸው። "ዶሮ ገመዷን ረዘም ሲያደርጉላት የለቀቋት ይመስላታል" እንደሚባለው ማለት ነው። 

       ያን ጊዜ ጉድ ፈላ። ፊትም የታሰሩበት ሰንሰለት መክፈቻውም፣ መበጠሻውም፣ ማሳጠሪያውም በነሱ እጅ ስላልሆነ በርቀት እንዲበጠስ ሆነ፣ ማጣፊያው አጠረ፣ የትም ማምለጥ አልተቻለ። ቀጣዩን ለማሰር በሚበቃ አይነትም ለክተው ገመዱን ቆራረጡት፣ መንዛዛትን አሳጠሩት፣ ማንም! ሊያጉረመርም አይችልም። ያለ ስምምንት ያለ ውለታ የተፈፀመ አይደለማ!  ”ጥንቱን ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ – አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ " የሚባልበት ጉዳይ ሆነ። ስለዚህም ወያኔ እራሱን ገደብ የሌለው ባርነት ውስጥ በድጋሜ አስገባ። ለስልጣን ላበቁት ባዕዳን ሁሉ በውለታው መሰረት ለመፈፀም ተገደደ። ስለዚህም የህዝብን መሬት እየነጠቀ ለነሱ አከፋፈለ።  ለራሱም ሞነቸፈ። አዲዎስ! የህዝብ ትግል ማጭበርበሪያ ሆኖ ቀረ። ሱዳንም ለውለታዋ ሰፊ መሬት ተቸራት። ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ተከታዩን ሁሉ ማኖ አስነክቶ፣ ጥላቻን፣ ውርደትን፣ ተጠያቂነትን ሁሉንም አውርሶ ነጎደ። " ሸንኮራ ገዳ ቢሰጡኝ አጤ - መምጠጤን ጥዬ ምነው መላጤ" ሲል ስንኝ ቋጠረለት። ባዕዳን በጅልነቱ ሳቁ! ተዘባበቱ፣ በተሰጣቸውም ተደሰቱ። ይኸ ሁሉ ነገር ሲደረግ ተነሳንለት ያሉት የህዝብ ዓላማ ውሸት እንደነበረ ተጋለጠ። ቆምንለት ያሉትን ህዝብ መሬቱን ለመነጠቅ፣ ለድብደባ፣ ለእስር፣      ለእንግልት፣ ለአሰቃቂ ሞት ዳረጉት። ወያኔ እራሱን በቪላ፣ ዘመዶቹን በኮንዶምኒየም፣ ልጆቹን በስኮላርሺፕ አንበሸበሸ። ለድሃው የትግራይ ህዝብ ተረፍ መረፍ የደረሰው ለማስመሰል ቅንጥብጣቢ ጣለለት። የነሆለለውም በሌለ ነገር እንዲኩራራ፣ በባዶ ልቡ እንድታብጥ ተቀሰቀሰ። "ከወርቁ ዘር በመወለዴ እኮራለሁ" ሲል መለስ ዜናዊ ባደባባይ ተናገረ። ልክ " "ዶች ላንድ ኡበር አለስ"  ብሎ እንዳለው ሂትለር። መደለያ መሆኑ ነው።

        የትግራይ ህዝብን ማጭበርበሪያ መሆኑ ነው። ግራም ነፈሰ ቀኝ፣ ሰዎቹ ቃል የተገባላቸውን መሬት ወስደዋል። የቀረበት ህዝብ ነው። የተንገላታው ሁሉንም ያጣው ህዝብ ነው። ወያኔ ወገኑ መስሎት እየደገፈ ያስገባው ህዝብ ነው እየተረገጠ ያለው። በህብረት እንዳያድም ከጎረቤቱ ከኖረበት ቀዬ የተባረረው ህዝብ ነው የጨለመበት። በምትኩ የገዥው ዘመዶች ናቸው በቦታው የሰፈሩበት። ከጋምቤላ፣ ከጎንደር፣ ከወሎ፣ ከሸዋ፣ ከአዲስ አበባ፣ ከሁሉም ስፍራ ነዋሪው ህዝብ ጊዜ በሰጣቸው ጎጠኞች ተወርሷል። ቦታው በውጭ ባዕዳንም፣ በገዥው መደብ ዘሮችም ይፈለጋላ!። እናም መላሹ ማነው? የትግራይ ህዝብ ደልቶኛል ብሎ ይቀበላል ወይስ ከወገኖቹ ጋር አብሮ ይቆማል?  ወያኔ የሚያሳስት አይደለም፣ ዘረኛ፣ ወንጀለኛ፣ ሀገር ገዳይ ነው። ማንነቱን ለማወቅ ጊዜው እስኪደርስ መጠበቅም አያስፈልግ።

       የሳውዲ ሀብታሞች፣ አረቦች፣ ህንዶች፣ ሁሉም በነፃ መሬት ታድሏቸዋል። አለያም ከዶላር ባነሰ ካሬ ሜትሩን ቸብችቦላቸዋል። ምንቸገረው ባንዳ፣ አልደማበት አልቆሰለበት። ባዕዳን መሬቱን አረሱ፣ ምርቱንም ሰብስበው ወደ ሀገራቸው አሳፈሩ። ማን ተዉ! ይላቸዋል፣ ቀድመው ነዋ! ቃብድ የከፈሉት። ህንድም አረብም ድርሻውን ተቀራመተ። ምስኪን የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ከወራሪዎች ጋር ያደረገው ተጋድሎ በባንዳ ልጆች ተነጠቀ። ወራሪዎች አንጀታቸው ራሰ። የሀገሩ ዜጋ ቤቱን መሬቱን ተቀማ!  ቦታ ልቀቅ ተባለ። አዱኛ ብላሽ!  አዳዲስ ሀብታሞች መጥተዋል ከሜዳ፣ ሲበሉ የሚሮጡ፣ ሲጠጡ የሚራገጡ መጥተዋል።

        የኢትዮጵያ ህዝብ መጠኑ ይብዛ ይነስ እንጂ በኖረባቸው ዘመናት በሙሉ ከመከራ ተላቆ አያውቅም። እናም ዘወትር እራሱን ይጠይቃል  "መሬት ይዤ ውስጡ አረንጓዴ -  ለምን ይሆን የራበው ሆዴ"  እንዳለው ቴዲ አፍሮ። ትክክል ነው። ድርቅና ጠኔን የኢትዮጵያ መለያ ለማድረግ ሲጥሩ የኖሩት ባዕዳን ለአድራጎታቸው ምክንያት ቢኖራቸውም፣ በራሳቸው ሞክረውት ያልተሳካ በመሆኑ ዳግመኛ በዚያ መንገድ ሊሄዱበት አልፈለጉም። ይልቁንስ ለያይተውና ገነጣጥለው ማዳከምና በዓለም አደባባይ እራሱዋን የማትችል ተጠዋሪ ሀገር አድርጎ ማስቀመጥ የሚቻለው በራሱዋ ሆድ አደር ዜጎች አማካይነት መሆኑን በማመን ለማስፈፀም መንደፋደፉን መርጠዋል። ለዚህም ተግባር ያሰማሯቸው የጎሳ ድርጅቶች አሉ። ከነዚህም መሃል ቀንደኛው ደጋፊያቸው ወያኔ ነው። ስለወያኔ ማንነት ከ91 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ሲነገር የቆየ በመሆኑ፣ መደጋገም አያስፈልገው ይሆናል። ነገር ግን በፍርሀትና በጥቅም ተይዞ በግምባር ተሰልፎ እኔን ግደሉኝ እያለ የሚሞግተውን የዋህ ዜጋ ነፃ ለማውጣት መደጋገሙ አስፈላጊ ይሆናል።

       ምንም አይነት ፍላጎት ቢኖራቸው ተለጣፊ ገዥዎች በአፍሪካ ውስጥ ህዝብን ማስደሰት አይቻላቸውም። ምክንያቱም የተሰማሩበት ተግባር ይህን እንዲያደርጉ አይፈቅድምና። መለስ ዜናዊ አፉ ዳጥ ዳጥ ሲል "የሰው በልቶ አይተኙም ተኝቶ" የተባለውን ረስቶት ይሆናል። ለሚዘነጋ ደግሞ ማረሚያም አለ። ለቅብጠትም ቅጣት። አሁንም በዚያው መንገድ እንጓዝ ለሚሉ ግን አያዋጣውምና በጊዜው ታረሙ ማለቱ ተገቢ ነው። በራስ መንቀሳቀሻው መንገድ የተሳተ ይመስላልና። ያለህልማቸው የሚያልሙ፣ ያለመንገዳቸው የሚነጉዱ እንዳሉ ተስተውሏልና።  ለድል የጓጉ፣ የወያኔ ግፍ ያንገፈገፋቸው፣ ህብረትን ከልብ ቢሹ ተገቢ ነው። ግን አብሮ መታየት ያለበት " ብንተባበር እስከምን – ባንተባበርስ?” የሚለው ነው።

                                      ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!
      
                                                                                                                                                      

                                                                                                                                                                                                                                                                                                         
 

No comments:

Post a Comment