Saturday, February 6, 2016

መልኅቅ እንደሌላት መርከብ የመሆን አደጋ / http://www.finote.org

ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሀተታ ጥር 18 ቀን 2008 ..የተላለፈ
መልኅቅ እንደሌላት መርከብ የመሆን አደጋ 
ስለ ኢትዮጵያ መናገር የሚፈልጉ ባዕዳኑም ይሁኑ የሀገሪቱ ተወላጆች፤ ሊስማሙ የሚችሉበት አንድ ነገር አለ ማለት ይቻላል ። ይኽውም ፤ የሀገሪቱ ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕንቆቅልሽ እየሆንባቸው መምጣቱ ነው ። ለዚህ አባባል፤ የሚከተሉትን ሀቆች ያጤኗል ፡፡ የሀገሪቱንም ሁኔታ ያስተውሏል፡ -- 
1. የተፈጥሮ ሃብቷ ሞልቶ ተትረፍርፎ ፤ ዜጓቿ በርሃብና ጠኔ የሚረግፉባት ሀገር ሆናለች። 
2. ልሂቃንጠቢባን ሞልተው ተትረፍርፈው፤ ደናቁርትና ቁማርተኞች የሚመሯት ሀገር ሆና ቀርታለች ። 
3. የአፍሪካ አኅጉር የነፃነት ዓርማ እንዳልነበረች ሁሉ፤ ዛሬ ራሷ በአዲስ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ስር ወድቃለች። 
4. ሀብቷ ንብረቷ ለዜጎቿ መጠቀሚያ መሆኑ ቀርቶ፤ የውጭ ሀገር ሀብታሞች እየዘረፉት ይገኛሉ ። የራሷ ልጆች ግን የበይ ተመልካች መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፤ በአሁኑ ወቅት፤ ከ 15 ሚሊዮን በላይ የሚቆጠሩት ዜጎች በረሃብ አለንጋ የሚገረፉ ሆነዋል ። 
5. ዳር ድንበሯን፤ የግዛት አንድንቷንና ሉዋላዊነቷን ለማስከበር የተሰዋ ሕዝብና መሪዎች እንዳልነበሯት ሁሉ፤ ዛሬ ፤ ከግቢ ተቀምጠው ፤ በፊርማቸው ሀገሪቱን ቆርሰው የሚሸጡ ከሃዲያን ከሥልጣን ላይ ተቀምጠዋል ። 
6. በባዕድ ወረራ ጊዜ የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ መዋረድ አናይም በማለት የተሰዉላት ጀግኖች አርበኞች እንዳልነበሯት ሁሉ ፤ ዛሬ ብሄራዊ ዓርማችንን ብጣሽ ጨርቅ ነው ብለው የሚያንቋሽሹ ነውረኞች ""መንግሥታዊ ሥልጣን ይዘው ተቀምጠዋል ። 
ዘርዐይ ደረስ፤ አብዲሳ ዐጋና፤ ሌሎቹንም ዕልፍ አዕላፍ ጀግኖች ሰማዕታትን መዘከር አግባብነት ይኖረዋል። 
7. ሕዝባዊ መንግሥት፤ የሚባለው ቃል ፤በታሪክና በሕዝብ ዘንድ ፤ የተከበረየታፈረና የከፍተኛ ተቋም መግለጫና መታወቂያ እንዳልነበረ ሁሉ ፤ ዛሬ የስርቆትና የሙስና የዝርፊያና የግድያ፤ የሀገር ሃብት ማሸሻያና የውንብድና ድርጅት ሆኗል ።
በመሠረቱ፤ የህግና ፍትኅ-ርትዕ ፤ ድንብ፤ ሥርዓትና የመልካም አስተዳደር ማስፈፀሚያ መሆኑ ቀርቶ፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ የማፊያዎች-ወንበዴዎች ና የዘራፊዎች ድርጅት ሆኖ ቀርቷል ። 
8. በታሪክ፤ ሌሎች ህዝቦች በየሀገሮቻቸው በደል ሲፈጸምባቸው ፤ ወደ ኢትዮጵያ እየተሰደዱ በሠላም ተጠግተው ይኖሩ ነበር። በሃይማኖትና በፖለቲካ፤ በጦርነትና በረሃብ ችግር ምክንያት፤ ክፉውን ዘመን በኢትዮጵያ በደስታና በሰላም አሳልፈው ወደ ሀገሮቻቸው ይመለሱ ነበር ። 
የነበዩ ሙሐመድ ቤተስቦችና ተከታዮች ፤ በዕምነታቸው ምክንያት ከሀገራቸው ሲሳደዱ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንደቆዩና በኋላም በሠላም መመለሳቸው እንደ አብነት እየተጠቀሰ የሚኖር የታሪክ እውነታ ነው። 
የአርመን ክርሲያኖች፤ በኦቶማን ኢምፓየር መውደቂያ ዘመን ሲጨፈጨፉ፤ በብዙ ሽ የሚሆኑ አርመናውያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ፤ተጠግተው ሃይማኖታቸውን ጠብቀው በሠላም ኖረዋል። ኢትዮጵያ ለእነርሱ ፤የልጅ-ልጅ ዐይተው ፤ ወልደው-ከብደውና ሀብት ንብረት አፍርተው በሠላም የኖሩባት ሀገር ነበረች። 
በአንፃሩ ግን ዛሬ፤ ኢትዮጵያውያንበሀገራቸው በሠላምና በነፃነት ለመኖር ባለመቻላቸው ፤ በአራቱም የዓለም ማዕዘናት መጠጊያ ለመፈለግ በመሰደድ ላይ ይግኛሉ። ብዙዎቹም በየበረሃውና በየባህሩ የአሞራና የአሳ ነባሪ ቀለብ ሆነው ቀርተዋል ። በብዛት መሰደዳቸው አሁንም አላባራም ። 
እረ ለመሆኑ፤ ባለፈው ዓመት፤ በሊቢያ ምድረበዳ በአረመኔዎች ጭካኔ ሰይፍ የታረዱትን ሠላሣ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን እንዴት መርሳት ይቻላልበታሪክ የሌሎች ሀገሮች ስደተኞችን በሠላም ስታስተናግድ የቆየች ሀገር፤ ዛሬ በሃያ አንደኛው ክፍለ-ዘመን፤ እንዴት የራሷ ዜጎች ከሀገራቸው እየተሰደዱ መድረሻ መዳረሻ ፤ መጠጊያ መጠለያ ያጣሉ እነኝህንና ተመሳስይ ጥያቄዎችን መመለስ ያለበት ሁሉ ዜጋ ነው ብለን እናምናለን ። ስለሆነም ሀገርን የማዳን ኃላፊነት የሁሉም ዜጋ ድርሻ መሆኑ መዘንጋት የለበትም 
9. " ሀገረሐበሻ የፍትኅና የሠላም ምድር ነች። ወደ እርሷ ሂዱ። ትቀበላችኋልችም ። በሠላምም ትኖሩባታለችሁ ። እንዳልተባለላት ሁሉ ፤ የገዛ ራሷ ዜጎች፤ ዛሬ እንዴት በሠላም፤ በገዛ ሀገራቸው መኖር ሳይቻላቸው ቀረ 
10. የሌሎች ሀገራትን ነፃነት፤ ሰላምና የግዛት አንድነትን ለማስከበር፤ የበኩሏን ኃላፊነት የተወጣች ሀገር፤ እንዴት ዛሬ የራሷን ዳር-ድምበር፤ ለማስከበር አልቻለችም ኅልውናዋስ በምን ምክንያት ከስጋት ላይ ለመውደቅ በቃኢትዮጵያ የሚለው ስሟ እየደበዘዘ እንዲሄድ ማድረግና ፤ በየብሄር ስሞች የመተካት ሙከራስ ለምን አስፈለገ የሚያኮራውንና ታሪካዊ የሆነውን ስም መጥላትስ ፤ ከምን የመጣ የሥነአዕምሮ በሽታ ነው?
ከሞላ ጎደል፤ ከአንድ አስከ አሥር የተጠቀሱትን እነኝህ የሀገራችን ዕንቆቅልሾች የመጡት በተፈጥሮ ምክንያት ሳይሆን፤ በሰውሠራሽ መንሥዔ መሆኑ ለክርክር የሚቀርብ አይመስለንም። እነኝህን ዕንቆቅልሾች የፈጠሯቸው ፤ ለዘመናት በሀገራችን የተፈራረቁትየሚፈራረቁት ሥርዓቶችና ሥርዓቶችን ለማገልገል የተፈጠሩትየሚፈጠሩት ተቋማት ናቸው ቢባል ፤ ስህተት አይሆንም ። ሥርዓትና የሥር ዓት መገልገያ እንዲሆኑ የሚፈጠሩት ተቋማትና ድርጅቶች፤ በሀገራች ውስጥ ስለሚገኙት ክስተቶች በቀጥታም ይሆን በእጅ አዙር ተጠያቂዎች ናቸው። ሥርዓቶቹም ይሆኑ አጋልጋዮቻቸው እንዲሆኑ የተፈጠሩት ተቋማት ደግሞ የሚወጡትየወጡት ፤ ከሀገሪቱ ኅብረትሰብ ለመሆኑ አሌ የሚባል አይደለም። 
የዐፄ ኃይለ ሥላሴን አገዛዝ የፊውዳሉ ሥር ዓት ፈጠረው። የደርግ ወታደራዊ አምባገነን አገዛዝም ከዐፄ ኃይለ ሥላሴ ፈላጭቆራጭ አገዛዝ ማህፀን የወጣ ነበር። የወያኔ ዘረኛ ሥርዓትም ቢሆን፤ የትግራይን ሕዝብ ድህነት ፤ ችግርና ሰቆቃ መሰረት አድርጎ በሻዕቢያ አዋላጅነት የተወለደ ነው። 
የሦስቱም ተፈራራቂ ሥርዓት አራማጆች ፤ የአመጣጣቸው ወቅትና ሁኔታ ይለያያል ከልተባለ በስተቀር፤ ለኢትዮጵያ ሀገራችን ባህርይና ሁኔታ እንቁቅልሽ መሆን፤ የየራሳቸውን አስተጋብዖ ተክለዋል። እንቆቅልሾቹ እንዳይከሰቱ ከማደረግ ይልቅ፤ እንዲያውም ሆን ተብሎ ነገሮቹ ሁሉ እንዲባባሱ የየበኩላቸውን አጥፊ ሚና ይጫወታሉ። 
ብዙሃኑ ተገዥ ዜጋም ፤ ከዕሳት ወደ ረመጥ ይሸጋገራል ። ትሻልን እየሰደደ ትብስን ይቀበላል ። ይህ ሂደት ደግሞ ፤ የሀገራችንን የዕንቆቅልሽ ባኅርይ ይበልጥኑ ውስብስብ ያደርገዋል ። ይህም ውስብስብነት በበኩሉ ፤ ለችግራችን መፍትሄው ፍለጋ በምናደርገው ጥረት ሁሉ መዳህኒቱን እንዳናገኝ አስቸግሮናል ። ዜጎቿ ሀገር ወዳድና ብልህ መሪዎችን ማግኘት እስክሁን አልቻሉም ። 
ይኽም በመሆኑ እስከ ዘሬ ድረስ ባለው ታሪካችን ፤የፖለቲካ ሥልጣን፤ በደም የሚነጠቅና በደም የሚመለስ የአምባገነኖች የግል ንብረት ሆኖ ቆይቷል። በዚህ ልምድና ሥርዓት የተነሳ፤ አንድ መሪ ወይም ቡድን፤ በሚሞትበት እና በሚወርድበት ወቅት ፤ ከእርሱ ጋር ተባብሮ የነበረው ክፍል ሁሉ የበቀል ዱላ ይታወጅበታል ። አጥፊውን ከአልሚው፤ ንፁሁን ከወንጀለኛው ፤ ለሀገር የሚጠቅመውን፤ ከማይጠቅመው ለይቶ ማየት የማይቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል። ሌላው ቀርቶ፣ አዲሱ አስተዳደር ባለፈው ስርዓት ከጥፋት የዳኑት ጥቂት የኢኮኖሚ መሠረቶች ላይ መቀጠል ሲገባው እንዲያውም አጥፍቶ ሀ ብሎ መጀመር ጭራሽ ስልጣኔ እየመሰለ ሄዷል። 
አገዛዞች ወደ ሥልጣን ሲወጡና ሲወርዱ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍዳውን ሲከፍል ኖሯል ። በዚህ የተነሳ ሳይወድ በግድ፤ ከማያውቁት መላዕክ ፤ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል ከሚል ምርጫ እንዲገባ ይገደዳል ። እንደ ዕውነቱ ከሆነ፤ የሀገራችን ሕዝብ ከዚህ ምርጫ ውስጥ እንዲገባ ሊገደድ አይገባውም ነበር ። መላዕክትን ባይጠብቅም እንኳ ፤ ቢያንስ ፤ መልካም ሰብዕና፤ አስተዋይ አዕምሮ፤ ሩኅሩኅ ልብ ያለውና ፤ አርቆ ተመልካች መሪዎች እንዲያገኝ ይፈልጋል ። የዚህ ዓይነት ሰዎች ደግሞ፤ የሚመጡት ከሕዝቡ ውስጥ ብቻ ነው። ሕዝብ እነርሱን መፍጠር ካልቻለ፤ ማነኛው ህብረተስብ የሚገባውን መንግሥት ያገኛል ። ብሎ ከ 100 መቶ ዓመት በፊት አንድ የፖለቲካ ፈላስፋ የተናገረውን ማረጋገጥ ይሆናል ።
መሪዎችንና መንግሥትን የመምረጥ ሥልጣንና ኃይል የሕዝብ እስካልሆነ ድረስ ፤ ስለ ዴሞክራሲያ፤ ፍትኅ ርትዕ ነፃነትና መብት፤ ሠላምና ልማት ማሰብ፤ የኅልም እንጀራ ሆኖ ይቀራል ። ሕዝብን፤ በእርጎ ባኅር እንዲዋኝ ማድረግ ደግሞ፤ የቀጣፊ ፖለቲከኞች ዓይነተኛ ተግባር መሆኑ መረሳት የለበትም ። 
ዛሬ ሀገራችን ኢትዮጵያ ፤ ልክ መልኅቑ እንደጠፋበት መርክብ፤ አቅጣቸዋ የተሰወረባት ሀገር ሆናለች ቢባል ማጋነን አይሆንም። ዜጎቿም ያጋጠሟቸውን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት ከማይችሉበት ደረጃ ደርስዋል ። የዚህም ዋና ምክንያት፤ ችግሩን ወደ ጎን አስቀምጦ፤ ወያኔ በዘረጋው ዘረኝነትና የክፍፍል ወጥመድ መያዝ በመሆኑ ነው። ለጊዜ ጥቅምና አገልግሎት ቅድሚያ ጭራስ አልተሰጠውም ብንል ስህተት አይሆንም። 
የሀራገችንን የፖለቲካ ተፎካካሪዎችን ደካማነት፤ በጥልቀት የተገነዘቡት የውጭ ባዕዳን ፤ በረቀቀ ስልታቸው፤ ሀገራችን እድትምሰቃቀል በስውር እየተከታተሉ ሥራቸውን ይሰራሉ ። የውጭ ኃይሎች በሀገራችን ውስጥ ጣልቃ ገብነት ከ 16ኛ ክፍለ-ዘመን ጀምሮ እንደተከሰተና ውጤቱም አጥፊ እንደነበረ የታሪክ ድርሳናት ያረጋግጣሉ ። ይህ ክስተት ዛሬም ቢሆን መልኩን እየለወጠ ቀጥሏል ። ይህንን ቀውጢ ሁኔታ ተገንዝበን፤ ለሀገራችን፤ ብሩኅ ተስፋ የሚያስገኝ ጊዜ ማምጣት ካልቻልን የምናጠፋው ጊዜ እኛኑ መልሶ አንዳያጠፋን ስጋታችንን እንገልፃለን ። 
የጊዜን ጠቀሜታ በጊዜ መጠቀም ካልቻልን ደግሞ ፤ የዐረቦችን ምሳሌ ለመጥቀስ እንገደዳለን ። የዐረቦች ተረትና ምሳሌ እንዲህ ይላል። ጊዜ ልክ እንደ ሠይፍ ነው። አንተ ካልቆረጥከው፤ እሱ ይቆርጥሃል ። ሀገራችን የገባችበትን አደገኛ የኅልውና ጥያቄ መመልስ እንድንችል የዘወትር ጥሪያችንን እናስተላፋለን 
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር !

No comments:

Post a Comment