Sunday, March 13, 2016

ዴሞክራሲያ ቅጽ 41 ቁ 5 የካቲት 2008 ዓ.ም የካቲት 1966--ድገመና !


ዴሞክራሲያ ቅፅ 41 . 5 የካቲት 2008 ..
የካቲት 1966--ድገመና !
page1image2136
የካቲት 66 አብዮት ከተከሰተ 42 ዓመታት አልፈዋል። የኅብረተሰብ ሂደት ሆነ እድገት አንድ ወጥ አይደለምና በዚህ ረጅም ጊዜ ሀገራችን ብዙ ለውጦችን አሳይታለች። በዚያውም ልክ መከራዋና ችግሯ፤ ህመሟና ቅጥቃጤዎቿ አሁንም እንደቀጠሉ አሉ። ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ወደ መቶ ሚሊዮን ተጠግቷል፤ አብዛኞቹም ወጣቶችና ሴቶች ናቸው። ዘመን ተለውጦ የአካባቢውና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ እንደቀድሞው አይደለም። የዚህ ሁሉ አንደምታ እንዳለ ሆኖ ግን የየካቲት 66 መሠረታዊ መንስዔዎች ዛሬም ወቅታዊነትን እያንጸባረቁ አሉ ።
የካቲት 66 .. በግብታዊነት ፈነዳ ቢባልም የቅድመ የካቲት ሁለገብ ትግሎች ውጤት ለመሆኑ የሚያከራክር አይደለም። የካቲት 1966 .ም በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ ታሪካዊ ቦታ አስመዝግቦ አልፏል። አብዮት እንደተካሄደባቸው እንደ ሌሎች ሀገራት ሁሉ፤ የኢትዮጵያ አብዮትም የራሱ የሆነ መንስዔና ምክንያቶች፤ እንቅስቃሴና ሂደት ነበረው። የተሟሉ ግብዐቶችና የተጓደሉ ሁኔታዎችም ነበሩት። የተሟሉ ግብዓቶች የተባሉት፣ ነባራዊ ሁኔታዎች ተሟልተው በመገኘታቸው ነበር። የተጓደሉ የተባሉት ደግሞ፣ ሕዝባዊውን እንቅስቃሴ ፣ በቂ አቅምና ችሎታ ኖሮት፣ አመራር ሊሰጥ የሚችል ፤ የተዘጋጀና የተደራጀ መሪ ኃይል ባለመኖሩ ነበር ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያውያን ፤ በስድሳ ስድስቱ የየካቲቱ አብዮታቸው ይኮሩበታል። ያሞግሱታል። በረዥሙ አኩሪ ታሪካቸው ላይ ተጨማሪ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ስለከፈተላቸውም ልዩ ቦታ ይሰጡታል። የየካቲት አብዮት፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የጭቆና ማህጸን ተጸንሶ፤ በሕዝባዊ አመጽ የተወለደ በመሆኑ ልዩ ቦታ አለው። በሁለንተናዊ መስፈርት ሲለካ፤ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ በውጭ ኃይል ያልተበረዘ፤ ያልተከለሰ ያልተዳቀለ፤ ነበር። እንደሸቀጥ ዕቃ ከውጭ በነጋዴዎች አልመጣም። የኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድነቱም ነጸብራቅ ነው - ታክሲ ነጄው፣ ወታደሩና ዝቅተኛ ማዕረግ መኮንኖች፣ ተማሪና አስተማሪዎች፣ የቢሮ ሠራተኞችና የሠራተኞች ማኅበር፣ ሴቶችና ሙስሊም ክርስቲያኖች የተሳተፉበት ታሪካዊ ትግልና አብዮት ነበር።
1966ቱ የካቲት ሕዝባዊ አመፅ ፣ አንድ ታሪካዊ ክስተትን በመመዝገብ ፤ የኢትዮጵያን አንድነት እንደገና አስረግጦ ፤ የማይጠፋ ማኅተሙን አሳርፎ ሄዷል። ለዚህ ዕውነታ ቋሚ ምስክር የሚሆነውም፤ በወቅቱ የነበረው ሕዝባዊ ዐመፅ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ ዕምነት ሳይከፋፈል ፣ ባንድነቱ ፀንቶ በመቆም፤ ሁሉም ያንድ ሀገር ዜጋ ሆኖ የኖረ መሆኑን ለዓለም ማሳወቁ ነበር። ተፈራራቂ ገዥዎቹ ፣ ለአገዛዛቸው ማጠንከሪያ እንዲመቻቸው ሕዝቡን በልዩ ልዩ ዘዴ ለመከፋፈል ቢሞክሩም፤ የተመኙት አልሆነላቸውም። ወደፊትም ቢሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ የመከፋፈሉ ሴራ የሚሳካ አይሆንም። ይህን የማይታበል ሐቅ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶች ሊረዱት ይገባቸዋል። የየካቲት ስድሳ ስድስት ሕዝባዊ አመፅ ያነሳቸው አምስት መሠረታዊ- ሀገራዊ ጥያቄዎች ነበሩ። እስካሁን ድረስ ማነኛቸውም ምላሽ አላገኙም።
1. የሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄ ፡
ከጉልታዊ አምባገነን ሥርዓት ተላቆ ፤ በሕዝብ ምርጫ የተመሠረተ መንግሥት ማቋቋም፤ የሕዝቡ የመጀመሪያው ጥያቄ ነበር፡፡ይህ መሆኑ ቀርቶ ፤ ጥያቄው የሥልጣን ጥም ባሰከራችው በጥቂት የጦር መኮንኖች ተደመሰሰ። የፊውዳሉ አምባገነን ሥርዓት በወታደራዊ አገዛዝ ተተካ። ፋሽስታዊ ሥርዓት ተመሠረተ። የ66ቱ ዐብዮት መሠረታዊ ዓይነተኛ ጥያቄ የውሃ-ሽታ ሆኖ ቀረ። ለአለፉት 38 ዓመታት በኢትዮጵያ፤ ዴሞክራሲ፣ ነፃ ምርጫ፣ የፍትኅ ሥርዓት የሚባሉ ሁሉ ደብዛቸው ጠፋ። ይህ ጥያቄ እስካሁን ደረስ ምላሽ አላገኘም። የሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄ አሁንም ህያው ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የዴሞክራሲ መብቱን ተቀዳጅቶ፤ የሚፈልገውን ሕዝባዊ መንግሥት እስከሚመሠርት ድርስ ጥያቄውን በይደር አያቆየውም። በምፅዐተ-ዳግማዊ የካቲት እንደገና ተነስቶ የማያዳግም መልስ ያገኛል።
2. የመሬት ለአራሹ ጥያቄ ፡
አሁንም ይህ ጥያቄ አልተመለሰም። የመሬት ባለቤትነት ከጥቂት የፊውዳል ከበርቴዎች እጅ ወጥቶ ወደ ገዥው ፓርቲ ተቆጣጣሪነት ተዘዋወረ እንጅ፤ ወደ አርሶ-አደሩ ባለቤትነት አልተዘዋወረም። ገበሬው፣ የራሱ መሬት ላይ የባለቤትነት መብት አግኝቶ፤ የግሉ ሀብት ሆኖለት፤ በግሉ የመያዝ ፣ የመሸጥ፣ የመለወጥ፣ የማውረስ፣ በወለድ- አገድ የማሲያዝ መብቱ አልተከበረለትም። የኢትዮጵያ ገበሬ፣ ከጥንቶቹ የመሬት ከበርቴዎች ተጠማኝነት፤ ወደ መንግሥት ከበርቴ ተጠማኝነት ተዘዋውሯል። የመሬት ጥያቄ የኢኰኖሚ ጥያቄ ጭምርም ነው። 85% ከመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ደግሞ በግብርና ምጣኔ-ሀብት ላይ የተገነባ እንደ መሆኑ፤ የመሬት ይዞታ መሠረታዊ ለውጥ ማግኘት እንዳለበት የሚያከራክር አልነበረም። አይሆንምም።
ከዚህም በላይ መሬት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከማንነቱ፣ ከታሪኩ፣ ከባህሉ፣ ከአብሮነቱ፣ ከዕምነቱና ከነፃነቱ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ፤ ከኤኮኖሚ ጠቀሜታው ባላነሰ ደረጃ ክብርና ቦታ አለው። መሬት ለኢትዮጵያዊነቱ፣ ለሀገራዊ ኩራት- ጌጡ፣ ትውልድ ቆጥሮ፤ ታሪክ ጠቅሶ፤ ከአባት -ከአያት ወርሶ ለተተኪው ትውልድ የሚያወርሰው ዘለዓለማዊ ተቋም ጭምርም ነው። የመንግሥት አገዛዝ በተለዋወጠ ቁጥር፤ በገዥዎች ፍላጎትና ትዕዛዝ የሚለዋወጥ ሊሆን አይችልም። በርዕዮተ-ዓለም ፍልስፍና ሰባኪዎችም የሚወሰን አይደለም። መሬት ከአርሶ-አደሩ የዕለት-ተዕለት ኑሮውና ህይወቱ ጋር በብዙ ሀብል የተሳሰረ በመሆኑ፤ ማንም ያበደ- የተንደገደገ አምባገነን እንዳሻው ሊቆርሰው - ሊሸነሽነው፣ ሊመትረው ፣ ሊያዝዝበትና ሊናኝበት የሚችለው አይደለም። ይህ ሁሉ ተዳምሮ ሲታይ ፤ አሁንም የመሬት ለአራሹ ጥያቄ - በየካቲት 66 ዋና የሆነው - ምላሽ ሳያገኝ ቆይቷል። መልስ ይጠብቃል።
3. የዴሞክራሲ ጥያቄ ፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ በረዥም ዘመን ታሪኩ፤ ዴሞክራሲያዊ መብትን አይቶም- አሽትቶም - ቀምሶም አጣጥሞም ስለማያውቅ፤ የዴሞክራሲ ጥያቄ ዓይነተኛና ግምባር-ቀደም ጥያቄ ነበር። በየካቲት 66 ዓብዮት ማግስት ጭላንጭሉን ለማየት ዕድል አግኝቶ ነበር ለማለት ቢቻልም ፤ ወዲያው ከመቅፅበት ተዳፈነበት። ጥያቄውን አጠንክሮ ቢቀጥልም፤ ምላሽ ሳያገኝ እስከዛሬ ድረስ ልሳኑ እንደተዘጋ ቆይቷል። ጠብ-መንጃ ባነገቱ ተፈራራቂ ገዥዎች ዕብሪተኛነትና ጭካኔ ምክንያት፤ አቅም ባለማግኘቱ፤ አንገቱን ደፍቶ፣ ሞራሉን ሰብሮ ያለውድ-በግድ የአምባገነኖች ተገዥ ሆኖ ቀርቷል። ሀሳቡን በነጻ የመግለጽ፣ የመጻፍ፣ የመሰብሰብ፣ ሠላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ መብቱ ተጨፍልቋል። የዕምነት-የኅሊና ነፃነቶች ሁሉ ወህኒ ቤት ገብተዋል። የሰው ልጅ የኅሊና ነፃነቱ ከተገፈፈ፤ ሰብዓዊ ፍጡር ነኝ ብሎ ራሱን ሊያታልል አይችልም። አሳዛኙና አስገራሚ የሚሆነው ነገር ደግሞ፤ ገዥዎቹ ዴሞክራሲ አምጥተንልሃልና እኛን አምነህ ተቀበል ፤ አሜን ብለህ ተገዛ፤ ተነዳ ለማለት መሞከራቸው ነው። ገዥዎች ራሳቸውን ለመደለል ይችሉ ይሆናል። የሕዝብን የማስብ ችሎታም ሆነ ስብዕና ዝቅ አድርጎ መገመት ግን የድንቁርና ድንቁርና መሆኑን አለመገንዘብ ፤ ከማስገረም አልፎ በምጸት ደረጃ ያስቃል ። ሕዝቡ፤ እያረረም ቢሆን ለመሳቅ ቢሞክርም፤ የዴሞክራሲ ጥያቄው አስካልተመለሰለት ድረስ ጥያቄውን አንግቦ መታገሉን ይቀጥላል። የሕዝብ ጥያቄ፤ በሕዝቡ አመፅ መልስ ያገኛል ! የዴሞክራሲ ሥርዓት በሀገራችን እስካልሰፈነ ድረስ፤ የዴሞክራሲ ጥያቄ አይዳፈንም።
4. የብሔር-ብሔረሰቦች ጥያቄ ፡
ሕዝባዊው አመፅ ካነሳቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች መካከል፤ የብሔሮችና የሃይማኖት እኩልነት ይከበር፤ መብቶቹም በሕግ ይታወቁ የሚል ነበር። የዜግነት ነፃነት፣ የብሔር፣ የሃይማኖትና የዕምነት እኩልነትን ተቀብሎ፤ በሕግ አስከብሮ በተግባርም እንዲተረጎም ካላደረገ ፤ የተሟላ ነፃነት ሰፍኗል ማለት አይቻልም። ሀገራችን መልከ-ጉራማይሌ ልትሆን የቻለችው፤ የብዙ ብሔር-ብሔረሰቦች መኖሪያ በመሆኗ ነበር። ይህም መልኳ፤ ውበቷን ብቻ ሳይሆን ጥንካሬዋንም ጭምር አጉልቶ የሚያሳይላት ነው። ይህንን መልከ-መልካምነቷንና ጥንካሬዋን ወደ ጥላቻና ድክመት እየለወጡ ፤ ሕዝብን ለመከፋፈልና ሀገርንም ለማፈራረስ ተግቶ መሥራት ማለት የብሔር-ብሔረሰቦች መብት ተከብሯል ማለት አይደለም። የግለሰብ መብትና ነፃነት መከበር፤ ለብሔር-ብሔረሰብ መብት መከበር ፤ መቅደመ- መብት መሆኑ፤ መዘንጋት የለበትም። የየካቲት 66 ዓም ሕዝባዊ ጥያቄ ዒላማ ያደረገው በሁለንተናዊ ገፅታው ጸረ- ሕዝብ የነበረውን ጨቋኙን አገዛዝ ማስወገድ ነበር። ተከታዩና ቀጣዩ ተግባር ደግሞ፤ የተወገደውን ሥርዓት በዴሞክራሲያዊና ሕዝባዊ መንግሥት መተካት ነበር። በዚህም ተባለ በዚያ፣ ዞሮ-ዞሮ የዴሞክራሲ ሥርዓት መስፈን ጉዳይ በመሆኑ፤ ቅድሚያ የሚሰጠው ዜጎቹን የዴሞክራሲ ባለቤቶች እንዲሆኑ ማድረግ ነው። ያ እስካሁን አልሆነም። በጎሳ ላይ የተመሠረተ የክልል ፌዴራላዊ ሥርዓት ፤ የብሔር-ብሔረሰብን ችግር ሊፈታ አይችልም። የወያኔ አገዛዝ እስካለ ደረስም ተፈፃሚነት አያገኝም። በአሁኑ ወቅት የብሔር-ብሔረሰቦች መብት መከበሩ ቀርቶ አንዲያውም በከፋ መልኩ፤ ወደ ዘር ማጥፋት ደረጃ እየተለወጠ በመሄድ ላይ ይገኛል። በጋምቤላ በአኝዋክና፣ በዐማራውና ኦሮሞው፣ በኦጋዴን፣ ... ወዘተ በዜጎች ላይ የሚፈፀመውን የዘር ዕልቂት ማየቱ ብቻ በቂ ሆኗል። በነገደ-ዐማራ ላይ የሚካሄደው የዘር ማጥፋት ወንጀል፤ ለታሪክ ተመዝግቦ ተቀምጧል ። ካንድ ብሔር ብቻ የተውጣጡ የአገዛዙን ሥልጣን በእጃቸው አስገብተው፤ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የወታደሩንና የጸጥታውን አውታሮች ሁሉ ተቆጣጠሩ ማለት የብሔር- ብሔረሰቦች መብት ተከበረ ማለት አይደለም። በዚህም መስክ እኩልነትና ዴሞክራሲን በተመለከተ የየካቲት 66 ሕዝባዊ አመፅ ያነሳው ጥያቄ አልተመለስም። መልስ ይጠብቃል።
5. የሀገሪቱ ኅልውና ፤ ብሔራዊ ሉዓላዊነትና የፖለቲካ ነፃነት ጥያቄ ፡
ይህ ጥያቄ፣ የሕዝባዊ ጥያቄዎች ሁሉ ማሳረጊያ እንደነበር አብዮቱ መዝግቦት ያለፈ መሪ ጥያቄ ነበረ። ዛሬ ኢትዮጵያ ነፃ ሀገር አለመሆኗ ብቻ ሳይሆን ፤ በሀገር ደረጃም የራሷ ኅልውና አደጋ ላይ ወድቆ፤ በመኖርና ባለመኖር መካከል የምትጠራሞት ሀገር ሆና ትገኛለች። ተወደደም ተጠላ ሀገሪቱ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ወድቃለች። ሁለት ኃይላት በተቃራኒ አኳኋን ተፃርረው ቆመዋል። አንደኛው ኢትዮጵያ እንደ ሀገር መቀጠል አለባት ህያው ናት ብሎ የቆመው ያንድነት ኃይሉ ጎራ ሲሆን ፤ ሁለተኛው ደግሞ፤ ኢትዮጵያ የምትባለው ተረት -ተረት ነች፤ እንደ አንድ ሀገር ሆና መቀጠል የለባትም ብሎ የተነሳው ፤ ፅንፈኛውና አክራሪው የብሔረተኛ ቡድን ነው። ይህንን ጽንፈኛ ቡድን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሆኑ ባዕዳን፣ ሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብር ይሰጡታል። በአንጻራዊ መልኩ ሲታይ፤ ጠንካራ ነኝ ብሎ እራሱን ይገምታል። ከዚህ ግምጋሜ በመነሳትም የአጥቂነት ባህርዩን ለማሳያት ይሞክራል። ቀስ በቀስ በሚያደርገው እንቅስቃሴም የዓላማው ተጻራሪ የሆነውን የአንድነቱን ኃይል በመከላከል ደረጃ እንዲወድቅ አድርጎታል። ሁለቱ ተፃራሪ ኃይላት ፤ አንዱ በአጥቂ ሌላኛው በተከላካይ ደረጃ እንዳሉ ይገመታል። ይህ ግምት ደግሞ፤ ከዕውነት የራቀ ነው ማለት አይቻልም። ምክንያቱም፤ የአንድነት ኃይል ነው ተብሎ የሚገመተው ወገን ፤ የተጠበቀውን ያህል የተሰባሰበና የተቀራረበ ባለመሆኑ። ይህ ደግሞ የጥንካሬ ሳይሆን የድክመት ምልክት ሆኖ ቆይቷል። የማይበገር ኃይለኛ ደጋፊና ተባባሪ ሊሆንለት የሚችለውን የኢትዮጵያን ሕዝብ አሰባስቦ- አደራጅቶ በራሱ ጎራ በበቂ ሊያሰልፍ ባለመቻሉ የድክመቱ ዋነኛ ምክንያት ሆኖበታል። ይህ የአንድነት ጎራ፤ ይህንን ድክመት አስወግዶ፤ ከወጣ በአቸናፊነት እንደሚገኝ መጠራጠር አይቻልም። የሀገሪቱ ሉዓላዊነትም ሆነ ኅልውና ጥያቄ መልስ ሊያገኝ የሚችለው ከዚያ በኋላ ይሆናል። ያ ስለተባለ ግን ፤ የኃይል ሚዛኑ ወደ አንደኛው ወገን አዘነበለለት ተብሎ ቢገምትም እንኳ፤ የሀገራችን ችግር በቀላሉ ይፈታል ማለት አይደለም። በብሄር- ብሔረሰቦች መካከል የነበረ ቁርሾና ሀዘን፣ በደልና ጥቃት፣ መበዳደልና መጎዳዳትን አምኖ በመቀበል ዕርቅና ሠላም መምጣት አለበት። በኢትዮጵያ የሀገር ግንባት ሂደት፤ ያልበደለና ያልተበደለ አልነበረም ብሎ ሃቁን አምኖ መቀበል ይገባል። እስቲ በታሪክ ሂደትና በሀገር አንድነት ግንብታ የነበሩትን ታሪካዊ ክስተቶች እንመልከት። በዚያን ጊዜ ኃይል የአንድነት አዋላጅ ነበረ።
የሩሲያውን ንጉሥ ታላቁ ጴጥሮስ ሰፊውን የሩሲያ ሀገርና ግዛት መመሥረቱ፤ (1672 እስከ 1725) ታላቁን የሩሲያን ኢምፓየር የገነባ (ዛር) የቄሳር መግሥት መሪ ነበረ።
  •   የኢጣልያኑን -ጂዮሴፒ- ጋሪባልዲ፤ (1807 እስከ 1882 ) ደካማዋንና የተከፋፈለችውን ኢጣሊያን ግዛቷን አዋህዷል። ሕዝቡን አንድ አድርጓል። ከዚያ አልፋ ተርፎ ኢጣሊያ ተዋህዳና በርትታ፤ ሀገራችንን ለመውረር ብቃት አግኝታለች። የኢጣሊያ ጠንቅ አሁንም በሀገራችን ላይ አለ።
  •   የጀርመኑን ኦቶ ቫን ቢስማርክ ፤ ከ1860 እስከ 1890 ባለው ዘመን፤ የተከፋፈሉትን ግዛቶች አዋኅዶ አንድ በማድረግ በአውሮጳ ሰፊ ግዛትና መንግሥት ያላትን ታላቅ ሀገር የሆነቸውን ጀርመንን ፈጥሯል።
    በኢትዮጵያም የተፈፀመው የታሪክ ሂደት፤ የሀገር ግንባታ ጥረት፤ በተለየ መልኩ ሊታይ አይገባውም።
    የካቲት 66 ም ትምህርትን ሰጠን ብንል በቅድሚያ የሕዝብን አንድነትና ኃያልነት ማረጋገጡ ይሆናል ። የየራሳቸውንም ሆነ የጠቅላላውን ጥያቄ ያነሱ የህብረተሰቡ ክፍሎች በመሰረታዊው ኢትዮጵያዊነት ላይ ቅንጣት ጥያቄ ሳይኖራቸው እንደ ኢትዮጵያዊ መታገላቸው ለጥንካሬያቸው መሠረት ሆኗል። ይህ ነው ዋናው ትምህርት። አንድነት ኢትዮጵያዊነት። ከዚያም የከተማዎችን ዋና ሚናም አሰረግጧል። ላባደሩም በጠቅላላ የሥራ አድማ የሚኖረውንም ከባድ ሚና አስመስክሯል። የስዳሳ ስድስቱ የካቲት ዐብዮት ያነሳቸው ሕዝባዊ ጥያቂዎች እስከዛሬ ማናቸውም አልተመለሱ። መልስ ይፈልጋሉ። ይህንን መመለስ የሚችለው ፤ በሕዝብ የተመረጠ ፤ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሲመሠረት ብቻ ይሆናል ። ለዚህ ክስተት ምክንያት የሚሆነው ደግሞ የዳግማዊ የካቲት ዳግም ምፅዐት ብቻ ነው። ያ መምጣቱ ደግሞ አይቀርም። ድገመና የካቲት የምንለውም ለዚህ ነው።
    የካቲት 66 የሕዝብ የረጅም ቀዳሚ ትግል ተከታይ ክስተት ነው ብለናል። ግብታዊ ቢሆንም ሊጠበቅ የሚገባው ነበር-- በሥልጣን ያለው አገዛዝ አብቅቶለት ነበርና። የአጼው አገዛዝ ለጥገና ለውጥም ቢሆን ምንም ፈቃደኛነት ማሳየት ስላቃተው አብዮት የግድ ነበር። “ያ አገዛዝ ለምን ወደቀ?” ብለው ለሚቆጩ ግልጽ መሆን ያለበት ይህ ነው--አብዮት በራሱ ላይ ያመጣው ሥርዓቱ ራሱ ነው--ግትር ሆኖ፤ ለውጥ አልቀበል ብሎ። ካሁኑ የቀደመው አገዛዝ የካቲትን ማጅራት መትቶ ለሥልጣን ሲበቃና የሕዝብን ድል ሲቀማ ተኪው ደግሞ የባሰ ሆኖ ጸረ የካቲት ጸረ ኢትዮጵያ በመሆን ጫንቃችን ላይ ሰፍሯል። ዛሬ የካቲት 66 ጊዜን ወስዶ 42 ዓመት ሆኖታል። ገና 25 ዓመት ሲሞላው ግን የሚከተለውን ብለን ነበር - በየካቲት 1991-
    "የካቲት 66ን አብዮትና የሕዝብ ታሪካዊ ትግል 25ኛ ዓመት ስንዘክርም አንዱን የካቲት ሸኝቶ ሌላውን ሊቀበል የከረመው የሀገራችን ሕዝብ ዕጣው ከጅብ ጎሬ ወደ ጅብ ዋሻ ቢመስልም በትግሉና በመስዋዕትነት ሊመዘገብ ነው። ታሪክን መቃኘቱ፤ ማደሪያውን--ዕጣውን--ሊለውጥ ሊያሻሽል መዋደቁን ለመመዝገብ ነው። የገዢዎች ዜና መዋዕል መሠረትነቱ ተሰርዞ አንጀቱን በድግ ጠፍሮ--አስሮ ከተፈጥሮም ከባለሥልጣኑም ተጋትሮ ይህቺን ሀገር በላቡና በደሙ ማንነቷን የለገሳት፤አሻራውን አሳርፎባት ሀገር ያደረጋት ብዙኃኑ ጭቁን ሕዝብ “ትንሽ ምላጭ ሀገር ትላጭ” እንደሚባለው በተናቀው ክንዱ የጀመረው ጉሸማ-ትግል የሥርዓቱን ለውጥ ወልዷል። በየካቲት 66 ሕዝባዊ ትግል በግንባር ቀደምትነት ከተሜው ጎልቶ ቢታይም ሥርዓቱ የሕዝብን እንቅስቃሴ እንዳያኮላሽ እንቅፋት የሆነበት የትግሉመፈክሮች፣ ዋነኛ ጥያቄዎች፣ የሕዝብን መሠረታዊ ብሶትንና ፍላጎትን ያስተጋቡ መሆናቸው ነው። የወቅቱ ታጋይ ምሁራን የነበራቸውን ሚና የፈረጁት በሕዝብ አንደበትነት በመሆኑ “መሬት ለአራሹ!” ብለው ሲፋለሙ፤ እኩልነት ብለው ሲዋደቁ፤ ሠራተኛው ሕዝብ ባለመብት ይሁን ብለው ሲሰለፉ ዕድሉ ለተነፈገው ግና ግሮ ጥሮ ለአስተማራቸው ሰፊ ሕዝብ ላንቃ ሆኑት እንጂ፤ መፈክሩን አነገቡለት እንጂ ሌላ ዓላማ ሆነ ግብ አልነበራቸውም። የየካቲት አብዮት ሲገመገም ኋላ የተከሰተው መርገም ግንዛቤን የሚለውጥ መሆን የለበትም። አብዮቱ በእርግጥም የሥርዓትን ለውጥ ያስከተለ ትግል ነበርና ከተሳታፊዎቹ የየግል ይዞታና እምነት ባሻገር የጭቁኑን ሕዝብ ታሪክ ሠሪነት፣ አለሁ ባይነት ያስመዘገበና ያንን የገለማውን--ግን በዕብሪትና በግፍ የጨቀየውን--ሥርዓት ያዋከበና የደረመሰም ነበር። የካቲት አብዮት በደርግ ተብዬው ማጅራቱን ቢመታም አዲሱ የገዢ መደብ ቤተ መንግሥት ከመግባቱ በፊት የበሰበሰውን ሥርዓት አስወግዷል። የየካቲት አብዮት ደርግን አልወለደም። በዝባዡን የአጼውን ሥርዓት ግን ቀብሯል።"
በዚያው ጽሁፍ ላይ የሚከተለው ሀሳብ ሰፍሮ ነበር፡-
"የየካቲት አብዮት በተወሰነ ወቅትና የኅብረተሰብ ዕድገት ደረጃ የተከሰተ ቢሆንም በድጋሚ መምጣቱ፤ ከወቅቱ ጋር የተጣጠመ ዓላማና መፈክር ይዞ መደገሙ የግድ ነው። ያለንበት ደረጃና የኅብረተሰብ ይዘት ፤ የቅራኔዎች ጠባይና የወዳጅ ጠላት አሰላለፍ የተለየ ቢሆንም ያን አብዮት የግድ ያደረገው መሠረታዊ ሁኔታ አሁንም አለ። ተጨባጩ ሁኔታና በህሊናዊ ደረጃ በአደረጃጀት ሆነ ኅብረት የሚከሰተው መቀናጀታቸው ዛሬም ወሳኝ ነው። በመሠረቱ ብዙኋኑ ተጨቁኗል፤ እየተበዘበዘ ነው፤ ዘረኛ የጥቂቶች አገዛዝ በሥልጣን ተሰይሟል፤ የሕዝብ መብት ተረግጧል፤ የሕግ የበላይነት ተክዷል፤ የሀገሪቷ ህልውና ራሱ ለአስከፊ አደጋ ተጋልጧል፤ የዕኩልነት ጥያቄ ምላሽ አላገኘም፤ ... ወዘተ የካቲት ሁለተኛ ዙር የግድ ሊወለድ እየተፈራገጠ ይገኛል። አዋላጁ ከተገኘ፤ ዝግጁ ከሆነ ለማለት ነው።"
የካቲት ይደገም ስንል የ1966ቱ አብዮት በነበረው መልኩ ይከሰታል ብሎ መጠበቅ ሳይሆን ዓላማውን ይዞ፤ መፈክሮቹና ጥያቄዎቹ ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉበት ሁኔታን መፍጠር ነው። በተለይም የጋራና የአንድነት ትግል ነጸብራቅ ሆኖ ማለት ነው። ስላለውና ስለሚኖረው ተጨባጭ ሁኔታ ብዥታን ባለማስተናገድ ይህን የሚከተለውን ከዓመታት በፊት ጽፈን ማሳሰቢያ አድርገን ነበር፦
"ዛሬ የዚያን ትውልድ፤ለውጥ ብሎ የታገለውን ተራማጅ ክፍል ማብጠልጠል እንደ ብልጠትና ብሰለት ተቆጥሮ ነገሮችን ነገሮችን ሊያዛባ ቢቃጣም የየካቲቱ ትውልድ ሀገር ወዳድነቱን በደሙ ያስመስከረ ነው ። ዛሬ እንደምናየው ኢትዮጵያዊነትን በጭምብል ደረጃ ወስዶ ሲሆን ሲያመቸው የሚለብሰው ሳይሆን የሚጥለው አልነበረም። ከሁሉም በፊትና በላይ ሀገሩን የሚወደው ያ ትውልድ ለሀገር ይበጃል ብሎ ባመነበት ጸንቶ ታግሏል ። ሀገሩን ለጭራቆች፤ክብሩን ለባዕዳን ሸጦ የተዋረደ ትውልድ አልነበረም። ከየካቲት ወዲህ የመጡትን የታሪክ ጭንጋፎችና የሥልጣን ባለቤቶች ስንመለከት ምንኛ ያ ትውልድና የካቲት ራሱም ታሪካዊ እንደሆኑ እንደገና እንገነዘባለን። ሌላው የየካቲት ዕንቁ ትምህርት ለሀገሩ ሊሞትላት የተዘጋጀ ትውልድ እስከሌለ ድረስ ሀገር ለባዕዳን ጥቃትም ሆነ ለሀገር ውስጥ ተውሳኮች ጉዳት ተጋልጣ እንደምትጠቃ ነው ።"
ይህም ተብሏል ።ሌላም እንዲሁ ;፡ የካቲት 66ን ስንዘክረውና ስናስታውሰው ይህን ሁሉ በግንዛቤ አስገብተን ነው። መደምደሚያችንም ቀደም ካልነው የሚለይበት በቂ ምክንያት የለውም ።
" የየካቲት ዋና ዋና መፈክሮች አሁንም ሕያው ናቸው። በትግል ያገኘናቸው ድሎች የማይካዱ ቢሆኑም የታገልንላቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ዛሬም ትግልን፣ ምላሽን ይጠይቃሉ። ከመቸውም ጊዜ የከፋው ሁኔታ ደግሞ ከሥልጣን ጥማት ሌላ ሀገርን ማጥፋት ተልዕኮው የሆነ ቡድን ለቤተመንግሥት መብቃቱ ነው፡፡ ሀገርን መጠበቅና ከጥፋት ማዳን ወሳኝ በሆነበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ለዚህም ነው የካቲት አብዮትን በተመለከተ ከታሪኩ በጥሞና ተምረን፤ የነበሩ ጉድለቶችን አስወግደንና በስፋትና በጽናት ተባብረን በጋራ ጠላት ላይ መረባረብ የሚጠበቀብን። የካቲትን በትግል መዘክራችን ተገቢ ነው። የካቲት ማለት ትግል፤ ቆራጥነትና ሀገር ፍቅር ማለት ነበር፤ ነውም።"
ከዚህ በተያያዘስ የኢሕአፓ አቅዋም ምን ይሆናል? ያልነውን ለመድገም፤
" ኢሕአፓ ታሪኩ ከየካቲት አብዮት ጋር የተቆራኘ እንደመሆኑ መጠን ለሕዝብ የገባውን ቃል ኪዳን በማክበር በየካቲት የአመጽ መንፈስ ዛሬም ጸንቶ ለሀገርና ለሕዝብ ትግሉን ቀጥሏል። በባሩድ ሳይታጠን፤ በተፋፋመ ትግል ሳይታጀብ በሰላምና ዕልልታ የካቲት አብዮት የሚዘከርበት የሕዝብ ጊዜ፣ ሕዝባዊ ሥርዓት እስኪመጣም ይህ ትግሉ ይቀጥላል።"
ይህ ነው፣ የኢሕአፓ መልዕክት፤ ድገመና የካቲት የሚለው ጥሪውም። የየካቲት አብዮት በትግል ይዘከራል !
በተባበረ ትግል የሕዝብ ባለሥልጣንነት ይከበራል !!
ኃያልና አቸናፊ ሕዝብ ነው !!! 

No comments:

Post a Comment