Thursday, March 10, 2016

የጤና መድህን ክፍያ ታግዷል ትርኢቱ ቆይቶ የሚጫን ዕዳ ነው።የጤና መድህን ክፍያ ታግዷል ትርኢቱ ቆይቶ የሚጫን ዕዳ ነው።

page1image2016
ባለፉት 25 ዓመታት የተከሰተው የአፈና፣የግጭት፣የድሕነት፣ የውርደት፣ የዘረፋ፣የሙስና፣----ወዘተ የስርአቱ አውዳሚነት እንኳንስ ቀዳሚ ተጠቂ የሆኑት መምህራን ይቅርና በወያኔ የሐሰትና የተንኮል ፕሮፓጋንዳ ከጭቆና እንደወጡ ቆጥረው ጮቤ የረገጡ ግለሰቦችና ቡድኖችም ሳይቀሩ ደባውን ስለተረዱት ለመጸጸት ተገደዋል።የወያኔ አገዛዝ ሲፋጅ በማንኪያ ሲበርድ በእጅ እንዲሉ የሕዝብ ቁጣ በሚያይልበትና በሚጋጋልበት ወቅት ሁኔታውን ለማቀዝቀዝና ራሱን ለማጠናከር የማይፈጥረው ተውኔት አያጣም። ለዚህ አንዱ ማስረጃ በ2002ዓ.ም በአረብ አገሮች በግብፅና በቱኒዚያ ከተነሱት የሕዝብ አመጾች ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ የህዝብ አመጽ ኣንዳይነሳ አቅጣጫ ለማስቀየር በጥድፊያ የተቋቋመው የአባይ ግድብና የተፈጸመው የአገርና የህዝብ ንብረት ዝርፊያ አንዱ ነው። በሌላ በኩል ለታሪክ ፣ ለባህል፣ለፍትህና ለሰላም ከበሬታ የሌላውና በተቃራኒ መቆሙ ገሀድ የወጠው አገዛዝ ንጹሀንን በእስር እያማቀቀ የአካልና የአእምሮ ማሳቃያዎችን እያራቀቀ ራሱ የሰየማቸውን ሽማግሌ ተብዬዎች ተላላኪ አድርጎ እስረኞች ይቅርታ እንዲጠይቁ የሚጠይቅበት ስልት “ ራሴን መትተው እግሬን ቢያሻሹኝ መች ሊገባኝ” ዓይነት ነው።
በሲቪል ማህበራትና በፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ሰርጎገቦችን በማስገባት ሕዝባዊ ውክልና ያላቸውን እያሳደደ የተለያዩ ቅጥያ ስሞችን በመለጠፍ ውዥንብር የመፍጠር ተግባሩን እየደጋገመ ስለሚተውን አካሄዱ የተበላ ዕቁብ የሚል ስያሜ ወጥቶለታል።የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ ለቀረበው የሕዝብ ጥያቄና ለተፈጠረው ሕዝባዊ ተቃውሞ እቅዱ ታግዷል እንደተባለው መምህራንና ሠራተኞች በግዴታ ከደመወዛቸው ለመቁረጥ የተጣለባቸውን 3% የጤና መድህን ክፍያ አምርረው ስለተቃወሙት ለጊዜው ታግዷል መባሉ ሌላ ትዝብትና ጥርጣሬ አጭሯል።
በመጀመሪያ ደረጃ በነፃ የመደራጀት መብታቸውን ተገፈው በማህበራቸው አማካይነት የሚያቀርቧቸውን ሕጋዊ ጥያቄዎች መስተናገድ ከማይቻልበት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።ወያኔ በራሱ አምሳል ጠፍጥፎ የሰራው ተለጣፊ ማህበር የፍየል ጅራት አካል አይከድን ከብርድ አያድን ዓይነት ሆኖ የበቀለ አጉል ነገር ነው። እንዲሁም በመምህራን መካከል ተሰግስገው የሚሰልሉ የአንድ ለአምስት ጥርነፋ አባላትን ለማሰማራት የሚመች ማዕከልነቱ እየጎላ መጥቷል። የመምህራንን ሕልውና ስናስብ የትምህርቱም ጉዳይ ፊት ለፊት ይጋፈጠናል። የትምህርቱ ስርአት ትውልድ ገዳይነቱ ለትምህርት ባለሙያዎች ይቅርና ለአጠቃላዩ የህብረሰብ አካል ሳይቀር ለትምህርት ጥራቱ ማሽቆልቆል ከበቂ በላይ ግንዘቤ አግኝቷል።
መምህራን በአገራቸው የኢኮኖሚ፣የፖለቲካና የማህበራዊ ጉዳዮች ድርሻቸውን በበቂ እንዳይወጡ ማህበራቸውንና ንብረታቸውን ወርሶ የአንድ አምባገነን ፓርቲ ተቀጽላ ስላደረገው እንደቀድሞው ሁሉ የሕዝብን ብሶት በማስተጋባትና ለፍትህ የመቆም ተልዕኳቸውን እንዳይወጡ ሸብቦታል። መምህራን ግን የአገራቸውን ሕልውናና የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመታደግ መታገላቸውን ቀጥለዋል። ድሉንም ያቃርቡታል።ከዚህ በፊት በወጣው መግለጫ በመምህራንና በሌሎች ሠራተኞች ላይ የተጣለው ሕገወጥ የጤና መድህን ክፍያ ተቃውሞ የገጠመዉ መሆኑን አሳይተናል።አሁን ደግሞ ለጊዜው ስለመታገዱ መረጃ ደርሶናል።ለዚህ የወያኔ የማፈግፈግ ርምጃ መንስኤው የመህራንና የሌሎች ሠራተኞች ቁርጠኛ ትግል ውጤት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።
ዳሩ ግን ይህ የትግሉ የመጨረሻ ምዕራፍ አይደለም፤ አይሆንምም።መምህራን በርካታ ያልተመለሱ የመብት ጥያቄዎቻቸው እየተንከባለሉ ከ20 ዓመታት በላይ ዘልቀዋል።በነፃ የመደራጀት ጉዳይ፣የትምህርት ጥራት፣የሙያ ክብር፣ የመምህራን ኑሮ ---ወዘተርፈ ጉዳዮች ፍታዊ ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ እልህ አስጨራሽና መስዋዕትነት የሚጠይቁ የትግል እርካኖች ከፊታችን ተደቅናዋል።እነዚህ እውን እንዲሆኑ ሕዝባዊ ሥርዓት ማስፈን የግድ ስለሚል ትግሉ የዚሁ አካል እንደሆነ ይታመናል።
መምህራን በግዴታ በጤና መድህን ስም የተጨነባቸውን የዝርፊያ እቅድ በትግላቸው እንዲቆም ከማድረጋቸውም ባሻገር የራሳቸውና ባጠቃላይ የሕዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በአገሪቱ ባሁኑ ጊዜ በየአካባቢው የተከሰቱትን ሕዝባዊ እምቢተኝነት በመቀላቀል ክልልተኝነት የተጠናወታቸውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ መልክ በማስያዝ ብሔራዊ መፈክሮችን በመቅረጽና ብሔራዊ ገጽታ በማላበስ ሕዝባዊ ትግሉን አድማስ በማስፋት ረገድ የመምህራን ሚና በአዎንታዊነት ስለሚጠበቅ የትግሉ ፊታውራሪ እንድንሆን ግድ ይለናል።ከዚህ አንፃር የሕዝብ አመጾች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሰሜን ወልቃይትና ጠገዴ፣ በምዕራብ ቤንሻንጉል፣ ሐረርጌ፣ ወለጋ፣ አርሲ፣ አዲስ አበባ ...ወዘተ የሚታዩት እንቅስቃሴዎች እንዲቀናጅ በማድረጉ በኩል መምህራን የድርሻቸውን እንዲወጡ በሰደት የኢትዮጵያ መምህራን አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ ጥሪ ያቀርባል። ለኢትዮጵያ አንድነትና ለዴሞክራሲያዊ ግንባታ የሚታገሉ ኃይሎች በጋራ አጀንዳ ላይ መክረው ሕዝቡን እንዲያታገሉም ይጠይቃል።
ትግሉና ሕዝባዊ አመጹ ይፋፋም!! ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!! 

No comments:

Post a Comment