Wednesday, March 16, 2016

በጠላት የተከበበ ሠራዊት፤ በሕዝብ የተተፋ ሥርዓት( የፍኖተ ራዲዮ ሀተታ)

                      
 
                በጠላት  የተከበበ  ሠራዊት፤ በሕዝብ  የተተፋ ሥርዓት
 በሁሉም አቅጣጫ ዙሪያውን በጠላት የተከበበ ሠራዊት፤ የቆሰለን አውሬ ባኅርይ ያስያል።  በጭንቀትና በፍርሃት ድባብ ውስጥ ይቅለበለባል። ዙሪያው ገደል፤ ቀኑ ጨለማ፤ ይሆንበታል።  በጭንቀት ሥነልቦና ባኅርይ ይዋኛል። በዚህ ምክንያት በጦር አዛዦች መካከል መስማማት፤ መደማመጥ፤ መነጋገርና መተማመን ይጠፋል። ሠራዊቱም ኣዛዥና መሪ ያጣል። ወታደራዊ ሥነሥርዓት አፈር-ድሚ ይበላል። ከፍፍል ይመጣል። የመንፈስ አንድነት (Esprit de corps) ይጠፋል፤ የግልና የቡድን ክኅደት ይከሰታል። ክዳት ይከተላል። ስልታዊ ማፈግፈግ፤ ወታደራዊ አሰራር መሆኑ እየቀረ፤ ለሽሽትና ለነፍስ-አውጭኝ፤ ሽፋን ይሆናል። ለሠራዊቱ መበተን ማጠየቂያ  ይደረጋል ።    
ከዚህ  በኋላ፤ ይህ ሠራዊቱ፤  የውጊያ ተነሳሽነቱንም ሆነ የመመከት አቅሙን ያጣል።  ወኔው ይከደዋል።  በዝቅተኛ የሞራል  ውድቀት ላይ  የሚገኝ ሠራዊት  ደግሞ  ፋይዳ-ቢስ ነው።  እዚህ ደረጃ በሚደረስበት ጊዜ፤ የዚህ ሠራዊት አዛዥ  ሁለት  ምርጫዎች  ለመውሰድ ይገደዳል ።
1ኛ.  የሀገር ወዳድነት ስሜትን በጥቂቱም ቢሆን የተላበሰና ለሕዝብ አክብሮት ያለው ሰራዊት የጠላቱን ከበባ ስብሮ በመውጣት፤ ጠላቱን እየረፈረፈ በመጨረሻ የጀግና ሞት እየተቀበለ ክንዱን ተንተርሶ ያሸልባል።  የሀገሩን ክብር እያስከበረና መሠዋዕትን እየከፈለ ማለፍን ይመርጣል ።  እጅን ለጠላት አለመስጠት  ደግሞ  ለኢትዮጵያውያን ባኅርያቸው ስላይደለ፤ የሠራዊቱ አዛዥ ይህንን ቢመርጥ አያስገርምም  ይልቁንም ይህንን ማድረጉ ያስመሰግነዋል። የታሪክም ፍርድ አይጨክንበትም።
2ኛ.  ሁለተኛ ምርጫው፤  ነጭ ጨርቅ እያውለበለቡ ከተከበቡበት በመውጣት ተማርኮ  እጅ መስጠት ይሆናል።
   ከዚያ በኋላ የሚሆነውን ከስተት የሚያቅ ያውቀዋል። በደርግ አወዳደቅ ጊዜ  የተከሰተውን ለመዘርዘር የዚህ ሐተታ ዓላማ  አይደለምና ወደዚያ አንሄድም ። ገና ያልሻረውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ቁስል መንካት አግባብነት ያለው ማስሎ አልታየንም። እግረ መንገዳችንን ግን አንድ ሃቅ  ጠቅሶ ማለፍን አንሻለን።
የደርጉ ቆንጮ የነበረው ግለ- ስብ፤  " ከሳሃራ በታች፤ ተወዳዳሪ አልነበረውም " የተባለለትን የሀገሪቱን መከላካያ ሠራዊት ለብተና አጋፍጦና  ከድቶ  ጥሎ ሲሸሽ፤ የሀገሪቱ መከላካያ ሠራዊትም ያለ መሪ ቀረ። ተበተነ። ውለታውን እንኳ የሚያስታውስለት  ሳይገኘ ቀረ። ይህ አልበቃ ተብሎ፤ በየመንገዱ፤ የዕለት ምፅዋዕት መለምኑን ቀጠለ። ይህ አሳዛኝ ሁኔታ፤ ለኩሩው ሕዝብም ሆነ ለሀገሪቱ ታሪክ አሳፋሪ ሆነ። " ወይ ነዶ ! "
  ከዚያ በኋላማ፤ ገንጣይና አስገንጣይ ሀገሪቱን ቀለዱባት፤ ተጫወቱባት። ሕዝቡንም አዋረዱት። ጎዱት። ለብዙ ጊዜ ሲመኙት  የቆዩትን  ከይሲ ዓላማቸውን ፈፀሙበት። ከዚያ በኋላ የሆነውን ሁሉም ስለሚያውቀው ወደ ዝርዝሩ መግባት አያስፈልግም ።  " ዝርዝር ኪስ ይቀድዳል"  እንዲሉ!
ከላይ  በአጭሩ የተጠቀሰው ሁኔታ በወታደራዊ የጦርነት ታሪክ ሂደት የነበረና ያለ ወደፊት የሚኖር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤  የዚህ ከስተተም  በተመሳሳይ መልኩ የአምባገነን አገዛዝ በሚያራምዱ መሪዎችም ላይ የሚፈፀም ሀቅ ነው።  ይህ ጉዳይ በግልፅ  የሚታየው በዛሪይቱ ኢትዮጵያ ላይ ሆኗል። አሁን በምኒልክ ግቢ መሽገው በተቀመጡት ወያኔዎች ላይ በግልፅ ጎልቶ ይታያል። በጠላት እንደተከበበ ሠራዊት በጭንቀት ላይ እንደሚገኙ ማንም ሳይነግራቸው እነርሱ  እራሳቸው ያውቁታል ።
በአሮጌው ግንብ ውስጥ ብቻዋን እንደምትቅበዘበዝ ድንቢጥ የጭንቀት ማዕልትና ሌሊት እንደሚያሳልፉ፤ ከራሳቸው የበለጠ የሚረዳ የለም። በመጨረሻዋ ሰዓት የሚወስዱትን  ርምጃ ለመከናውን ግን ለመወሰን ተቸግረዋል። ይህ ማለት ግን ወደፊት ሊወስዱት በሚፈልጉት ርምጃ ላይ  ምንም አያስቡም ማለት አይደለም። የደርግ የመጨረሻ ዕድል፤ ምን እንደነበረ  በሚገባ ያጤኑታል። ያ ዕድል  እንዳይገጥማቸው የተቻላቸውን ያህል ይጥራሉ። እንደ ደርግ መሪዎች  በአስራ አንደኛው ( 11)ኛው ሰዓት እንዲርበተበቱ  ጮሌነታቸው  አይፈቅድላቸውም።  በሥልጣን ለመቆየት ሲሉ፤ የአንድ ቀን  ዕድሜም እንኳን ቢሆን ለማግኘት የሚፍረጨረጨሩትን ያህል፤ ከሕዝቡ ቁጣና ቅጣት ለመዳን ደግሞ ያንኑ ያህል ጥረት ከማድረግ ይቆጠባሉ አይባሉም ። 
ወያኔዎቹ፤ በአሁኑ ወቅት  ጎን -ለጎን  በሚያከሂዷቸው ሁለት ተግባራት ላይ ያተኮሩ  ይመስላል።
1ኛ.   የቀናት -የሳምንታት  ዕድሜ  ለመቀጠል ሲሉ፤ በሥልጣናቸው ላይ ለመቆየት የሚያስችላቸውን ጥረት ሁሉ የደርጋሉ።
  • በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች የተነሳሳባቸውን ሕዝባዊ አመፅ በተቻላቸው መጠን ለመቋቋም ይጥራሉ ። ከተቻለ፤  ተቃውሞውን ማዳፈንና መደምሰስ  ይመኛሉ።
  • ይህንን ለመድረግ የመጀመሪያ እርምጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ግድያውንና አፈናውን ማፋፋም ይሆናል ።
  • የፀጥታውንና፤ የፕሮፓጋንዳውን ተቋማት  አዋኅዶ እስከ መጨረሻው  ኃይልና ጉልበት ከመጠቀም ወደ ኋላ አይሉም።
  • በሀገሪቱ ውስጥ ስፋት ያላቸውን ሁሉት ታላላቅ  ብሄሮች ካሁን በፊት እንዳደረጉት ሁሉ እንዳይስማሙ በስፋት መጣር፤ አንዱ በሌላው ላይ የተነሳ አስመስሎ ፍጅት እንዲቀሰቀስ  ማድረግ። በሃይማኖቶች መካከል ጠብ ለመጫር እንዲመቻቸው፤ የራሳቸውን ወገኖች  ለዕኩይ ተግባር  ያሰማራሉ ።
  • የጎረቤት ሀገራት ኢትዮጵያን ወረሯት በሚል ሰበብ፤ የሕዝቡን የትኩርት  አቅጣጫ  አስለውጠው ትግሉን ለማኮላሸት ይፍጨረጨራሉ ።
  •  ይህ የተጀመረው  ሕዝባዊ የተቃውሞ የሕዝብ እንቅስቃሴ፤ " ፀረ- ትግሬ እንቅስቃሴ በመሆኑ ሕዝብ ትግራይ " እራሱን ከጥፋት ማዳን አለበት በሚል ርካሽ ፕሮፓጋንዳ ተጠቅመው፤ የትግራይን ህዝብ ድጋፍ ለማግኘት ይለፋሉ።  የትግራይ ህዝብ ግን ከወያኔዎቹ በላይ ስለሚያስብ፤ ትግሉን ከወገኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ተሰልፎ በሀገራዊው ሕዝባዊ አመጽ ጎን ተሰልፎ ድርሻውን ይወጣል።  ቅብዝብዞቹ  ወያኔዎች ግን  እማህል መንገድ ብቻቸውን ይቀራሉ ።
ታሪክና ሕዝብ ግን ፦
" ከእኛ  ቤት ቀላወጥሽ፤ እዚያም ሄደሽ በላሽ፤
  ሰው ታዘበሽ  እንጅ ሆድሽን  አልሞላሽ  " ።
ብሎ ይተፋቸዋል። ያባርራቸዋል።
ከላይ የተዘረዘሩት  ጥረቶች ግን የሕዝቡን አመፅ አንደማይገቱት  የታወቀ ነው ። .                       
2ኛ   ወያኔ፤ ጥረቶቹ  እንዳልተሳኩለት ከተረዳ፤ የሕዝቡን ዕሳተ-ገሞራ መቋቋም እንደማይችልም  ይገነዘባል ። በመሆኑም፤ በሚከተሉት የጥፋቶች ላይ  መሰማራቱን በይበልጥ ያፋፍማል።
  • በአንድ ብሄር ተዋፅዎ ላይ የተደራጀውን ጦርና  የፀጥታ ኃይል አስባስቦ የመጨረሻውን የአልሞት ባይ - ተጋዳይ  ጥረት  እንደሚሞክር መጠራጠር አይገባም 
  • በእልህና  በቆጭት አቆማዳ ውስጥ የቋጠረውን የአጥፍቶ- መጥፋት ሙከራ ሊያደርግ እንደሚችል አለመገመት የዋኅነት ይሆናል።  ሥረዓተ-አልበኘነትን ፈጥሮ በግርግር  የማምለጫ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ይጥራል 
  • ላለፉት ሠላሣ ዓመታት ያዘረፈውን የሀገሪቱን ሀብትና ንብረት ወደ ውጭ ሀገር አውጥቶ ስለአገባደደ፤ ያንኑ እየበላ ለመኖር፤ ወደ ምዕራባውያን አለቆቹ ሀገር የመኮብለል እቅዱን ይፈጽማል። ምዕራባውያን ዐለቆቹ ደግሞ፤ ለዚህ ተግባር እንደሚተባበሩ ግልፅ ነው። እነርሱ፤ ይኅንንም ትብበር እንኳንስ ለጭፍራቸው ለወያኔ ቀርቶ፤ ለመንግሥቱ ኃይለማርያምም  አድርገዋል።
  • ወያኔዎቹ፤ በኢትዮጵያ ላይ ስር የሰደደ ጥላቻ ስለአላቸው፤ እነርሱ ከሄዱ በኋላ፤ ሀገሪቱና ሕዝቧ  እንጦሮጦስ ወረዱ አልወረዱ ደንታ የላቸውም።
ሻዐቢያዎቹ፤ ለለበጣም እንኳን ቢሆን፤  ከኢትዮጵያ ሲገነጠሉ ፤
" ድሃን ኹኒ  ኢትዮጵያ ካብ ቕድም  መስራስኺ " ትርጉሙም አንች ኢትዮጵያ፤ ከመፍረስሽ በፊት ደህና ሁኚ ! ብለዋታል።  አጥፊዎቿ ወያኔዎቹ ግን የመልካም መግለጫ ስንብት አያደርጉላትም።  ከእነርሱም ይህ አይጠበቅም ።
በመሆኑም " ዉሃ ዉሃው ሀጂ ዐለቱ ቀሪ "  እንዲሉ፤  ቀሪውና ነዋሪው  የኢትዮጵያ ሕዝብ፤  አንድነቱን ጠብቆ ፤  ኀይሉን  አስተባብሮ፤ ጉልበቱን  አጠንክሮ፤  ምሥጢሩን በጉያው ቋጥሮ፤  በመሃሉ የተሰገሰጉትን  የወገን ጠላቶች መንጥሮ፤  ትግሉን  አስተባብሮ በመነሳት  ይህንን አጥፊ ዘረኛ ቡድን ማስወገድ የቅድሚያ አጀንዳው ሊሆን ይገባል ።
አሁን በመላው ሀገራችን  የተዠመረው ሕዝባዊ ኣመፅ ፤ በምልዑነት ተቀናጅቶ፤ አንድ ማዕከላዊ ፤እዝ- አመራርና አስተባባሪ እንዲኖረው መገንዘብና ከተግባር ማዋል የግድ እያለ ነው።   የኢትዮጵያ  ሀገራዊ ትግል፤ የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ትግልና ድል እንዲሆን   ከተፈለገ፤ ትግሉ በብሄርና በጎሣ ሊካፋፈል አይገባውም ። ዘረኛው ወያኔ በተለመው  የጎሣ  ክልል ፤ የሕዝቡን ትግል ሊከልሉ የሚፈልጉ ክፍሎች፤ የወያኔን ዘረኛ  ሥርዓት፤ በአዲስ መልክና ቅርፅ እንዲቀጥል የሚመኙ መሆን አለባቸው ።  ዛሬ፤ ይህንን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ  ጭራሽ አይፈልገውም።
"  ከአላበደ በቀር ዱባ ቅል አይጥልም ፤
   የወታደርን ሚስት ባላገር አይደፍርም  ። "   እንደተባለው፤
ከእንግዲህ ወዲህ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ በዘርና በሃይማኖት ለመከፋፈል መሞከር እብደት ነው ! ምክንያቱም ወያኔም ሞክሮ አልተሳካለትምና ! በመሆኑም፤ ይህ አሁን የተቀጣጠለውም ሕዝባዊ አመፅ ፤ በሀገራዊ ደረጃ በኅብረት መቀጠል ይኖርበታል ።     
 በጠላት የተከበበ ሠራዊት መጨረሻው አንደማያምር ሁሉ፤ በሕዝብ ዘንድ የተተፋ ሥርዓትም በመጨረሻ ጊዜ ተመሳሳይ ዕደል ይገጥመዋል። ዘለዓለም ሕዝብን አፍኖ፤ በኃይል  ረግጦ፤ መግዛት አይቻልም። የገዥዎች ጦር መሳሪያ እየዛገ፤ ጥይታቸው  እየመረተ፤ ክንዳቸው እየዛለ፤  ልሳናቸው እየሰለለ  የሚይዙት  ሠራዊት እያገዳቸው  ወደ ሕዝቡ ጎራ የሚቀላቀልበት  ጊዜ መምጣቱ አይቀርም።  ያ ቀን አስኪመጣ ድረስ ግን፤  እጅ- እግር አጣጥፎ መቀመጥ ፤ ውጤቱ ፀፀት ሆኖ ይቀራል። በመሆኑም፤ የሚከተለውን  ምልክታ ለማስተላለፍ እንገደዳለን ።
1ኛ.       ሌላው ሁሉ እንኳን ቢዘገይ፤ ቢያንስ የተቃዋሚው ክፍል (የአንድነት ኀይል የሚባለው) በአንድ ምዕራፍ ላይ መገኘት አለበት ።
2ኛ.  የኢትዮጵያ በቀጣይነት መኖር  አለመኖር የሁሉም ዜጎቿ ውሳኔ  መሆኑን አምኖ መቀበል፤ የራስንም ኅልውና እንደመጠበቅ ይቆጣራል።
3ኛ. ሁሉም ተባብሮ ሀገሩን ካላዳነ ሁሉም ተያይዞ  እንደሚጠፋ ብልህነት መሆኑን ማወቅ አለበት።
4ኛ እርስ በእርስ ተጠፋፍቶ፤  ሀገሪቱንም ከምትጠፋ ፤ ወያኔን አጥፍቶ ኢትዮጵያን  ማዳን አያከራክርም  ለድረድርም አይቀርብም።
  ኢትዮጵያ  ለዘለዓለም  ትኖራለች   !

         

No comments:

Post a Comment