Wednesday, March 2, 2016

Finote Democracy Voice of Ethiopian Unity Satellite Radio News

Finote Democracy Voice of Ethiopian Unity Satellite Radio News
የካቲት 22 ቀን 2008 ዓ.ም.ዜና (March 01, 2016 NEWS)
Ø ለአራት ወራት የቀጠለውን የሕዝብ ተቃውሞና ቁጣን ለማስታገስ የወያኔ መሪዎች የራሳቸውን ከፍተኛ ካድሬዎች መስዋዕት በማድረግ ከስልጣንና ከኃላፊነት በማባራር ድርጅታዊ ብወዛ መጀመራቸው ታውቋል። በዚህ መሠረት የወያኔው ኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበረው ዳባ ደበሌ ከስልጣኑ ተነስቶ የተባረረ ሲሆን በምትኩ በወያኔው ኦህዴድ ውስጥ ታማኝነቱ አያጠራጥርም የተባለው በከር ሻሌ ተመድቧል። ከዚህ ቀደም በከር ሻሌን በጉምሩክና ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ውስጥ ይሰራ እንደነበር ታውቋል። በናዝሬት ለተወሰነ ጊዜ ከንቲባ እንደነበረ ተገልጿል። የወያኔው መሪዎች በኦህዴድ ውስጥ ከስራ የማገድ የማባረርና የማዛወር ሥራን በሰፊው ያካሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህ በዚህ እንዳለ ቴድሮስ አድሃኖም የዓለም የጤና ድርጅት ሀላፊ በመሆን ለመመረጥ ፍላጎት እያሳየ ስለሆነ ግለሰቡ ኃላፊነቱን ከለቀቀ የደቡብ ህብረቱ ዮናስ ዮሴፍ እንዲተካው ሀይለማርያም ደሳለኝ እየለመነለት ነው ተብሏል።
Ø የወያኔ ቡድን መሪዎች በአዲስ አበባ ታክሲ ሹፌሮችና ማህበራት ላይ ያወጡትን ህግን ተከትሎ በትናንትናው ዕለት የታክሲዎች የስራ ማቆም አድማ በመደረጉ የወያኔ የትራንስፖርት ባለስልጣኖች የህጉን ግንዛቤ ማስጨበጫ ጊዜ ለማራዘም በሚል ህጉ እስከሚቀጥሉት ሶስት ወር ድረስ ተባራዊ እንዳይሆን መወሰናቸው ታውቋል። የወያኔው ትራንስፖርት ባለስልጣኖች ያወጡትን የህግ መዘግየት መግለጫ ተከትሎ የተወሱን ታክሲዎች በመንገድ ላይ መታየት መጀመራቸው የታወቀ ሲሆን የወያኔ መሪዎች መሰረታዊ የሆነው የታክሲ ሹፌሮችና ማህበራቱን ጥያቄ በአግባብብና በትክክለኛ መንገድ እስካለመለሱ ድረስ ትግሉና አድማው በማናቸው ጊዜና ወቅት ሊቀጥል እንደሚችል ለታክሲ አሽከርካሪዎችና ማህበራት ቅርበት ያላቸው ምንጮች እየገለጹ ነው። ሌሎች ወገኖች ደግሞ የወያኔ ቡድን መሪዎች ህጉን ለሶስት ወር እንዲዘገይ ያደረጉት በኢትዮጵያ ያለው የፖሊቲካ ትኩሳት እስኪበርድና ትንፋሽ መግዣ ጊዜ ለማግኘት መሆኑን ጠቅሰው የታክሲ ሹፌሮችና ማኅበራት ይህን ታሳቢ በማድረግ በማናቸውም ጊዜና ሁኔታ አድማቸው ለመቀጠልና መብታቸውን ለማስከበር ዝግጁ ሆነው መጠበቅ እንዳለባቸው ይናገራሉ። በተያያዘ ዜና የአዲስ አበባ ታክሲ ሹፌሮች አድማን ተከትሎ በሌሎች ከተሞችና ስፍራዎች የሚገኙ ታክሲዎችና ባጃጆች የሥራ ማቆም አድማ ያደረጉ ሲሆን ይህም ሆለታንና ሰላሌና አርሲ እንደሚጨምር ታውቋል ታውቋል። በናዝሬት የወያኔ ኦህዴድ ባለሥልጣኖች የታክሲ ስራ ማቆም አድማ እንዳይዛመት በማለት በማንኛውም መልኩ አድማ ማድረግ አይፈቅድም በማለት መግለጫ አውጥቷል።
Ø የወያኔ ቡድን መሪዎች በሁሉም አቅጣጫ የተነሳባቸውን ተቃውሞ ቁጣ ለማስታገስና የመልካም አስተዳደርና ስራ እየሰራን ነው ለማለት ከአዲስ አበባ ከተማ በመሬት አስተዳደር ቢሮ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ስልሳ አንድ ሹሞችን ይዞ ማሰሩን ይፋ አድርጓል። አገዛዙ ከትናንንት በስቲያ በድንገተኛ መንገድ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሹሞች ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ መሬት እየሸነሸኑ መሸጣቸው ካርታ እያዘጋጁ በይዞታነት ያረጋግጡ ነበር የሚል ውንጀላ ያለባቸው ሲሆን ከአስሩም ክፍለ ከተማ ውስጥ መያዛቸው ተብራርቷል። በርካታ የሕግ ባለሙያዎች የሹሞቹ መታሰር የዘገየ መሆኑንና አሁንም ከሹሞቹ ጀርባ የጥቅምና ተካፋይነትና አይዞህ ባይ የወያኔ መሪዎችና ባለስልጣኖችን ሳይነካ ሹሞቹን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ ፍትሓዊ አሰራር ሳይሆን የሕዝብ ቁጣን ማስተንፈሻ ነው በማለት ይተቹታል።
Ø የወያኔ ቡድን መሪዎች ከ 80 በላይ ኢትዮጵያውያን የሆኑ የወርቅ ማዕድን ፈላጊዎች በሻዕቢያ ታግተዋል በማለት በአስቸኳይ እንዲለቀቁና ካልተለቀቁ ግን ተመጣጣኝ እርምጃ እንወስዳለን በማለት በኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ በኩል መግለጫ ከሰጠ ወዲህ ታገቱ የተባሉት ኢትዮጵያውያን የወርቅ ማእድን ፈላጊዎች በነጻ መለቀቃቸውን የወያኔ ኮሚኒኬሽን ቦሮ ተናግሯል። ይሁን እንጅ የወያኔው ቢሮ ታጋቾች ስንት እንደሆኑና እንዴት እንደተለቀቁ የገለጸው ነገር የለም። የወያኔ አገዛዝ ከቀናት በፊት ዛቻ አዘል ማስጠንቀቂያና ስለ አጸፋው እርምጃ ይናገር እንጅ ምን ዓይነት የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስድ አላስታወቅም ነበር። ለዲፕሎማቶች ቅርብ የሆኑ ምንጮች እንደገለጹት ከሆነ የሱዳን መንግስት ታጋቾቹ እንዲለቀቁና በሱንዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ የሽምግልና ጥረት ማድረጉን እየገለጹ ሲሆን የሱዳን መንግስት ግን አደረገው ስለተባለው የሽምግልና ጥረት የእምነትም ሆነ የክህደት ቃሉን አልሰጠም።
Ø በአዳራሽ ውስጥ የ1500 ሜትር ሩጫ አሸናፊ የነበረችውና ከጥቂት ጊዜ በፊት በጋብቻ ምክንያት የስዊድን ዜግነት ያገኘችው አበባ አረጋዊ የአካል ጥንካሬን የሚሰጥ ዕጽ መውስዷ በምርመራ ስለተጋለጠ ከስፖርት ውድድር ታግዳለች ። እስካሁን ድረስ በዚህ መንገደ የተከሰሰ ከእሷ በቀር አንድም ኢትዮጵያዊ አለመኖሩ ታውቋል።
Ø የጉጂ ሕዝብ በ ሼክ አላሙዲ ሚድሮክ የወርቅ ማዕድን ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደርግ መቆየቱ በተደጋጋሚ የተገለጠ ሲሆን ደርባ የሚገኘው የሚድሮክ ሲሚንቶ ፋብሪካው እንዲሁ ከፍተኛ ተቃውሞ አጋጥሞታል ። ሕዝቡ በሼኩ ላይ ጠንካራ ተቃውሞውን እየገለጸ ያለው ሼኩ ለአገሪቱ መክፈል ያለበትን በርካታ ገንዘብ ካለመክፈሉ በላይ ሰራተኞችን በአነስተኛ ክፍያ እየበዘበዘ ነው በሚል ነው። ይህ በዚህ እንዳለ ብሔራዊ የዘይት የኢትዮጵያ ኩባንያ የተባለው የሼኩ ተቋም በጅቡቲ ያለውን የሊቢያ ኦይል የሚባለውን ድርጅት መግዛቱ ተነገሯል።
Ø የጅቡቲ አምባገነናዊ አገዛዝ በተቃዋሚዎች ላይ እያካሄደ ያለው አፈና የቀጠለ ከመሆኑ በላይ በታጁራህ ታስረው በተለያይ የማሰቃያ መንገዶች ሲሰቃዩ ከነበሩት መካከል ሁሙድ እስማኤልና አብዶ አህመድ ሞሚን ሕይወታቸው ያለፈ መሆኑ ተነግሯል። ኦቦክ በሚባለው ቦታ ታስረው ከነበሩት መካከል ኦማን መሀመድ ቦዴ፤አሊ ሁሴን አሊ፤ከድር መሃመድ አይዳሂስ ና መሀመድ አሊ ሃጉስ በከፍተኛ ድብደባ ተሰቃይተው የሞቱ መሆናቸውን የጅቡቲ የሰብዓዊ መብት ተከላካይ ኮሚቴ ገልጿል ።
Ø ከጥቂት ቀናት በፊት ወያኔ ወደ ሶማሊያ ጦሩ መላኩን መዘገባቸን የሚታወስ ሲሆን ይህ ወደ ሶማሊያ የተላከው ውጋግን ሬጅመንት በመባል የሚታወቀው ጦር በቁጥር 600 መሆኑና የሚመራው በኮሎኔል ታደሰ ወረደ ተስፋዬ በተባለ ግለስበ የሚመራ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ጦሩ የሚሰማራው በደቡብ ሶማሊያ ሲሆን የኪስማዮን ወደብ ለመጠበቅ ነው ተብሏል። የወያኔ፤የዩጋንዳና ኬንያ ጦሮች ሽብርተኛ የተባለውን አል ሸባብን በማዳከም በኩል ውጤት አግኝተናል ቢሉም ቡድኑ ሰሞኑን በሞቃዲስሾ ጥቃት ሰንዝሮ በርካታ ሰዎችን መግደሉ ይታወሳል ።
Ø ከሰባት ዓመታት በፊት በደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ላይ ዴሞክራቲ አሊያንስ በሚባለው የተቃዋሚ ቡድን ቀርበው የነበሩት 738 ክሶች በፍርድ ቤት እንደገና ቀርበው ይታያሉ የሚል ዜና ከሰሞኑ ተሰምቷል። የፕሬዚዳንቱ ቢሮ ክሱን በጽኑ የሚከላከል መሆኑን ጠቅሶ በ2001 ዓም በወቅቱ የነበረው አቃቤ ህግ ክሶቹ ወደ ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ ማድረጉ ትክክል ነበር የሚል ማብራሪያ ሰጥቷል። ክሱን ያቀረበው ተቃዋሚ ክፍል ያን ጊዜ የነበረው አቃቤ ህግ በፖሊቲካ ምክንያት ክስ እንዳይመሰረት አደረገ እንጅ ክሶቹ ትክክል ነበሩ የሚል መከራከሪያ አቅርቧል። ከተዘረዘሩት ክሶች ውስጥ አንደኛው በወቅቱ የጸጥታ ኃላፊ የነበሩት የአሁኑ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ በብዙ ቢሊዮን ዶላር በተደረገው የመሳሪያ ግዥ ከፍተኛ የሆነ የጉቦ ገንዘብ ተቀብለዋል የሚል ነው። ዴሞክራቲክ አሊያንስ የተባለው የተቃዋሚዎች ህብረት የአገሪቱ የታችኛው ምክር ቤት በፕሬዚዳንቱ ላይ እምነት የሌለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ድምጽ እንዲሰጥ የውሳኔ ሀሳብ ያቀረበ መሆኑ ታውቋል። በምክር ቤቱ ከፍተኛ የመቀመጫ ብዛት ያለው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግሬስ የተባለው የገዥው ፓርቲ ሲሆን የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ ያደርገዋል ተብሎ ይገመታል።
Ø ሰኞ የካቲት 21 ቀን 2008 ዓም በምስራቅ ኮንጎ በምትገኝ አንድ መንደር ውስጥ ራሱን “የመከላከያ ኃይል ህብረት” በሚል መጠሪያ የሚጠራ የታጠቀ ቡድን አባሎች የመንደሩ ነዋሪ የሆኑትን 12 ሰዎች መግደላቸውን አንድ የሰብአዊ መብት ድርጅት ተቋም ከአካባቢው የአገኘውን ዜና ዋቢ በማድረግ ገልጿል። መቀመጫቸው በኡጋንዳ ወሰን አካባቢ የሆነው ታጣቂዎች ግድያውን የፈጸሙት በያዙት ቆንጨራ ሲሆን ምግብና የቤት እንስሳት ዘርፈው የሄዱ መሆናቸው ተነግሯል።
To Listen PART 1: http://finote.org/March01EVE_Hr1.mp3
To Listen PART 2: http://finote.org/March01EVE_Hr2.mp3
FINOTE.ORG

No comments:

Post a Comment