Tuesday, April 12, 2016

የሴቶች ተሳትፎ ለትግሉ ወሳኝ ነው ዴሞክራሲያ ቅጽ 41 ቁ.6


የሴቶች ተሳትፎ ለትግሉ ወሳኝ ነው
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት የታገለላችውና ክቡር ህይወቱን የገበረላችው መሠረታዊ የመብት ጥያቄዎች ዛሬም ምላሽ አላገኙም። ወያኔና ባዕዳኑ በኢትዮጵያ ሰላም ሰፈነ፤ የኤኮኖሚ እድገት ተመዘገበ፤ ማሀበራዊ ጭቆናዎች ተወገዱ በማለት ቢሳለቁም፤ ሕዝቡ ሰብዕናውንና ክብሩን ፤ የዜግነት መብቱን ለማስጠበቅና ዕውን እንዲሆኑ ለማድረግ በሚችለው መንገድ ሁሉ አምባገነኖችን ከመታገል አላቆመም። ከተማሪው እንቅስቃሴ ጀምሮ ተራማጅ ምሁራን በተለይም በኢሕአፓ ዙሪያ የተሰባሰቡትና መሠረታዊ ለውጥን ያቀነቀኑት ወጣቶች ካነሷቸው ዓቢይ መፈክሮች ውስጥ አንዱና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ አካል የሆነው የሴቶች የፆታና የእኩልነት ጥያቄ ዛሬም ምላሽ ሳያገኝ ወቅታዊነቱን እንደተላበሰ ይገኛል።
ዴሞክራሲ ስንል የብዙኅኑ መብት አለምንም ገደብ መከበሩን ማመልከታችን መሆኑ በሚገባ ሊታወቅና ከፍ ብሎ ሊስተጋባ ይገባል። ከዛሬ 44 ዓመት በፊት ኢሕአፓ የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች አለገደብ ይከበሩ የሚለውን መፈክር አንግቦ ሲታገል በቅድሚያና በዋናነት ደረጃ የኅብረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑት የብዙኅኑ ሴቶች የፆታና የእኩልነት መብት መከበርና መረጋገጥን ጭምር የሚያካትት ነበር። ዛሬም ነው። ጥቂቶች ባለመብት ሆነው ብዙኅኑ መብት አልባ በሆነበት ሁኔታ ዴሞክራሲ አለ ማለት ዓይን ባወጣ መንገድ ማታለል ወይንም ተጨፈኑ ላሞኛችሁ ማለት ነው።
በየካቲት 1966ዓ.ም ሕዝባዊ አብዮት ወቅትም የኢትዮጵያ ጭቁን ሴቶች ከዳር እሰከዳር አንግበው የተነሱት የመብት ጥያቄና ለመሠረታዊ ለውጥ እውን መሆን በቆራጥነት ያደረጉት ሁለገብ ትግል ሁሌም የሚዘከር ታሪክ የመዘገበው ሐቅ ነው። በጣሊያን ወረራ ወቅት ፋሽስትን ከአገር ለማበረር በተደረገው ግብግብ እና በየካቲት አብዮት፤ ደርግን ለማሰውገድ በተደረገው ትግል ሴቶች በገጠርም በከተሞች ሙሉ ተሳትፎን በማድረግ አለሴቶች ተሳትፎ ፤ የሀገር ነፃነትን አንድነትንና ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ የማይቻል መሆኑን አስረግጠዋል። ያ ደማቅ የትግል ተሳትፎአቸው ዛሬ ሊደገም ባለመቻሉ የትግላችንን ደካማ ጎን የሚጠቁም ሆኖ ይገኛል። የዴሞክራሲ እውን መሆን ማለት በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ክልልን በመፍጠር የሚገለጽ አይደለም። ይልቁንም በፖለቲካው በኢኮኖሚውና በማኅበራዊው መስክ ሙሉ የሆነ የመብት መከበርን/መረጋገጥን ይመለከታል። ሴቶች የመብታቸው ተጠቃሚና በመብታቸውም ያለምንም ተጽዕኖ ተገልጋይ መሆን ይኖርባቸዋል። በኢትዮጵያ ታሪክ ሴቶች የተጫወቱት ሚና በጣም ከፍተኛ እንደነበር የማይካድ ነው።ጀግና ተብሎ ከሚደነቀው ወንድ ጀርባ ሁሉ አያሌ ጀግና ሴቶች ነበሩ። ዛሬም በርካታዎች አሉ። ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ግፍና ጭቆናን አሻፈረኝ ብሎ በመታገልና ከቡር ህይወታቸውን ጭምር ለሕዝብና ለሀገር ሲሉ መሰዋዕት አድርገዋል። እዚህ ላይ ለምሳሌ በአደዋ ላይ ድል ያደረጉትን ገድል ያስታውሷል። ዛሬም ከፍተኛ መስዋዕትነትን እየከፈሉ ይገኛሉ። ሴቶች የእድገት ቀያሽ፤ የታሪክ ገንቢ፤ አምራችና አምራች ኃይልን የሚያፈሩ እናቶች ጭምር በመሆናቸው በአንድ አገር የኤኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላቸው ድርሻ ሁለገብ የሆነ ሚናን በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዲጫወቱ አድርጓቸዋል። ሴቶች ግማሽ ሰማይን ደግፈው አቁመውታል የሚባለው ለይስሙላ አይደለም።
ሴቶች ዴሞከራሲያዊ ሥርዓት ባልሰፈነበትና የሰብዓዊ መብቶች ባልተከበሩበት ሁኔታ ውስጥ ለአገራቸው ኤኮኖሚና ልማት ከሚያበረከቱት አስተዋጽኦ አንጻር ሲታይ የሚደርስባቸው ባህላዊና ኤኮኖሚያዊ ተጽአኖ እጅግ የከፋ በመሆኑ መብታችው ተከበሮ የድካማቸው ፍሬ ውጤት ተጠቃሚ ሆነው አያውቁም። ለዚህም ተጨባጭ ማስረጃ የሚሆነው ሴቶች ለአገራችን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚያበረክቱት አስተዋፆኦ በቀን በአማካይ ከ17 ሰዓታት በላይ በአድካሚ ሥራ ላይ የሚጠመዱ ለመሆናቸው ከጥናቶች ከተገኙ መረጃዎች ለማወቅ መቻሉ ነው። በተለይ በገጠሩ (በእርሻው) ክፍለ-ኢኮኖሚ የተሰማሩ ሴቶች ከላይ ለመጥቀስ ከሞከርነው ሰዓታት በላይ አድካሚና ለጤና ጠንቅ በሆኑ የሥራ መስኮች ጭምር ተሰማርተው ይገኛሉ። ተፈጥሮ ባጎናጸፈቻቸው የሴትነት (የእናትነት) ተፈጠሮ የተነሳ የሀገሪቱ የወደፊት ብሩህ ተሰፋን ተረካቢ የሆነውን አዲስና ወጣት ትውልድ የሚያፈሩ በመሆናችው ከእርግዝና ጊዜ አንሰቶ እሰከ ወልዶ ማሳደግ ድረስ ባለው ሂደት ውስጥ የነቃ ተሳትፎ ስላላቸውም በልጅ ማሳደግ ሂደት ውስጥ ጥሩም ሆነ መጥፎ ባህሪን ለልጆቻቸው የማስተላለፍ ወሳኝ የሆነ ሚናን ይጫወታሉ። ሴቶች በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ የሚያደርጉት ማኅበራዊና ባህላዊ ተሳትፎ እጀግ ከፍተኛ በመሆኑ የተነሳ በአሉታዊም ሆነ በአዎንታዊ መልኩ የሚያደርጉዋቸው አስተዋጽኦዎች የሚኖራቸው እንደምታዎች በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርነው ይህንን ከባድ ሃላፊነትና ድርሻን የተሸከሙት የኅብረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑት ሴቶች ከሚደርስባቸው ኢኮኖሚያዊ ባኅላዊና ፖለቲካዊ ተጽእኖ የተነሳ ከወንዶች እኩል የአገራቸው የጥቅም ተቋዳሽ ለመሆን አልቻሉም። ሴቶች በአጼውና በወታደራዊው የደርግ አገዛዞች ከደረሱባችው ባኅላዊና ኢኮኖሚያዊ በደሎች በከፋ ሁኔታ በጎጠኛው የወያኔ አገዛዝ የሚደርስባቸው ግፍና በደል እጀግ የከፋና የመረረ ነው። ቀደም ሲል በሀገር ደረጃ በተደራጁ እንደ ሠራተኛ ማኅበር፣ መምህራን ማኅበር ወዘተ... ውስጥ ሲያኬዱት የነበረው ትግል ዛሬ በወያኔ ጎጠኛ ፖሊሲ እንዲጠፋና እንዲደበዝዝ ሆኗል። ስለሆነም ሴቶች በሁሉም መስክ መብታቸው ተረግጦና በሥርዓቶቹ ተጨቁነው እንደቆዩ ማንም ሊክድ አይችልም ።
ኢትዮጵያዊያን ዛሬ ከወያኔ የጥፋት ተግባርና የዘረኝነት ተውሳክ ለመላቀቅ በሚያደርጉት ትግል ውስጥ የሴቶች ጉልህና ቀጥተኛ ተሳትፎ መኖሩ ለትግሉ መሳካትና ግብ መምታት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን አንገብጋቢ ጭምር ነው። የኅበረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑት ሴቶች ያልተሳተፉበት ሕዝባዊ ትግል ለድል መብቃት እንደማይቻል ሊሰመርበት ይገባል። በኅበረተሰቡ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎና የእኩልነት መብት መከበር በሕግ መደንገግና በተግባርም መረጋገጥ ይኖርበታል። ስለዚህም ሴቶች በሴትነታቸው ጎጥና ክልል ሳይገድባችው በአገር አቀፍ ደረጃ በፆታችው/ በሴትነታችው የመደራጀት መብታችው መከበር አሰፈላጊ ነው። ያለምንም ገደብ በነፃ መደራጀት የሴቶች የራሳቸው ሥራና መብት ሲሆን ለዚህም ጥረታችው ተግባራዊነት ከኅብረተስቡ ያላሰለሰ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል። ኢትዮጵያዊያን ሴቶች በክልልና በጎጥ ባለተገደበና ነፃ በሆነ ማኅበር ስር ለመደራጀት የሚያደርጉት ትግል ከአገዛዙ ጋር ሲያጋጫቸውና ቅራኔ ውስጥ ሲከታቸው መቆየቱ ዛሬ አሌ የሚባል አይድለም። ስለዚህም ከአገዛዙ በደልና ጭቆና ጭፍን ቁጥጥር ለመላቀቅ ሴቶች ምስጢራዊ አደረጃጀትን በመጠቀም ለመብታቸው አልፎም ለአጠቃላዩ አገራዊ ትግል ሊሰለፉ ይችላሉ። በፓለቲካውም መስክ የሴቶችን ትግል ለማጎልበት ያላሰለሰ ትምህርትና ቅስቀሳን መስጠት አስፈላጊ ሲሆን ሴቶችን የሚጎዱ ሕጎች ሁሉ እንዲሰረዙ የሴቶችን መብት የሚያስከብሩ ድንጋጌዎች እንዲወጡ መታገል ለእኩልነት የቆሙ ዜጎችን ሁሉ ይመለከታል።
ድኽነት በአገራችን ምድር ሥር ሰዶ ዛሬ በገጠርም ሆነ በከተማ ህዝቡ በችጋር አለንጋ እየተጠበሰ ይገኛል። በተለይ በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል የሚኖሩ አዳጊ ህጻናትና የሚያጠቡ እናቶች በከፍተኛ ሁኔታ ለረሀቡ ሰለባ ሆነዋል። የአርሶአደሩ የኤኮኖሚ ዋልታ የሆኑት የቤት እንሥሳትም በውሃና በግጦሽ ሳር እጥረት ምክንያት በአሰቃቂ ሁኔታ እየሞቱ የአሞራና የዱር አራዊት ሲሳይ መሆናቸው ቀጥሏል። ለዚህ አደጋና ችግር በዋናነት መንስኤው አገዛዙ የሚከተለው የተሳሳተ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተጓዳኝ የጤና አገልገሎት፤ የንጹህ መጠጥ ውሃና የማኅበራዊ ግልጋሎቶች አለመስፋፋት ሁኔታውን የበለጠ እንዲከብድና እንዲስፋፋ አድርገውታል። በየጊዜው ሳያቋርጥና እያደባ የሚጎበኘንን ረሀብ ከሚያባብሱት ሁኔታዎች መካከል አንዳንዶቹን ለመጥቀስ፤ የአካባቢ መጎዳት፤ ተገቢ ያልሆነ የመሬት አጠቃቀም (በሚገባ ያልተጠኑ በባዕዳን ባለቱጃሮች የሚገነቡት ኢንዱስትሪዎች፤ ሰፋፊ እርሻዎችና የማዕድን ቁፋሮዎች) የአፈርና የውሃ ሀብታችንን እየበከለውና እያባከነው ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር ሳይጠቀስ የማይታለፈው ደግሞ ከማገዶና ከግንባታ ፍላጎት ማደግ ጋር ተያይዞ ደን በአስደንጋጭ ደረጃ እየተመነጠረ መሆኑ ነው። በጋምቤላ የደረሰው ብቻ ለዚህ በቂ ምስክር ይሆናል። እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ ከባድ የሆነ የአየር ብክለትና የአካባቢ ጉዳት በሀገሪቱ ሕዝብና ተፈጥሮ ሀብት ላይ እያደረሱ ይገኛሉ። የትላልቅ ግድብ ግንባታም ሃላፊነት በጎደላቸው ፣ ከሕዝቡ በተነጠሉና ኪሳቸውን ለማደለብና ስማቸውን ለማጉላት ሲሉ ብቻ በቆሙ የሀገር መሪዎች መገንባታቸው የአካባቢ ደህንነት ጠንቅ ነው ከተባለ ቆይቷል። በነዚህም ጥፋቶች የተነሳ በግንባር ቀድምትነትና በአብዛኛው ሰለባና ተጎጂ የሚሆኑት አዳጊ የሆኑ ህፃናትና ሴቶች ናቸው።
ዛሬ በገሀድ እንደሚታየው በአገራችን ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ በየጊዜው ቁጥራቸውን በአሃዝ ለመጥቀስ በሚዘገንን መልኩ በርካታ ህጻናትና ወጣት ሴቶች በጉዲፈቻ ሥም ለባዕዳን በወያኔ መልካም ፈቃድና ይሁንታ እንደሸቀጥ ይሽጣሉ፤ ይለወጣሉ። የወያኔ ባለሥልጣናትና ካድሬዎች ከአረብ አገር ደላሎች ጋር በመመሳጠር ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ወጣት ሴቶችንና ህጻናትን ከፍተኛ ገንዝብ እየተቀበሉ በቦሌ በየጊዜው ያስኮበልላሉ። ከዚህ በተጨማሪም ከአገዛዙ ካድሬዎች ጋር በመመሳጥር ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ሴቶች የተሻለ ኑሮና ሥራ ፍለጋ በሚል ከሚወዱዋቸው ወላጆቻቸውና ውድ አገራቸው ተነጥለው የአገራቸውን ድንበር በእግራቸው አቋርጠው ወደባእድ አገር ይሰደዳሉ። ከሚሰደዱት ውስጥ አብዛኛዎቹ በስደት ጉዟቸው ፤ የዱር አራዊት ሲሳይ፤ የባህር ላይ ሰለባም ይሆናል። ከዚህም ሌላ ፤ በየበረሃውና በሥደት በሚገኙባቸው የአረብ አገራት እየተደፈሩ፤ በአሰቃቂ ሁኔታ ለሞት ሲዳረጉ ፤ የተቀሩት ደግሞ በባእዳን እሰር ቤቶች እንዲሰቃዩና ለአእምሮ በሽታም እንዲጋለጡ ተደርገዋል።
የኅበረተስቡ ግማሽ አካል የሆኑት ሴቶች በሁለተኛ ደረጃ ዜግነት ተፈርጀው ለአደጋ ተጋልጠው እያለ ሀገር ደህንነትና እድገትን አታገኝም። ከጠቅላላው ኅብረተሰብ ቁጥር ግማሽ የሚሆኑ ሴቶች ሆነው በየትኛውም የትምህርት ተሳትፎ ከወንዶች ጋር ሲነጻጸር የሴቶቹ ቁጥር እጅግ ያነሰ ነው። በሴቶች ላይ በባህልና በሃይማኖት የሚደርሰው ተፅእኖ እንደትናንቱ ዛሬም እንደቀጠለ ነው። አገራችን በሁለገብ እድገት ልታዝመዘግብ የምትችለው ሴቶች ከአድሎ ፤ ከኋላ ቀርነትና ከፆታ ተፅእኖ በተላቀቀ ሁኔታ ከወንዶች እኩል እድል ተሰጥቷቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሲደረግ ጭምር ነው። ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ዛሬ በከተማ ውስጥ የሚገኙት ሥራ አጥ ሴቶች ቁጥር ፤ ከወንዶች ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ ሲሆን ፤ በገጠር ደግሞ ከአራትና አምስት እጥፍ በላይ ነው። በአገራችን የአምራች ሴቶች ጉልበት የሚፈሰው በአብዣኛው አድካሚ በሆነው በግብርናው የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው። ሴቶች በዚሁ በእርሻው የምርት ሂደት ውስጥ ባላቸው ተሳትፎ - እንስሣትን በማለብ ፤ የእንስሣት በረትን በመጥረግ፤ ኩበትን ለማምረት እበትን በመጠፍጠፍ ፤ ማገዶ በመልቀም፤ በአረም ፤ በጉልጓሎና በአጨዳ፤ ... ወዘተ - ከፍተኛውን ኤኮኖሚያዊ ሚና ይጫወታሉ።
ከእርሻ ሥራውም ባሻገር በገጠር እህል በመፍጨት፤ ውሃን ከረጅም እርቀት ቀድተው ተሸክመው ለቤት በማቅረብ ፤ ምግብ በማብሰል፤ ሲደክሙ ይታያል። ዛሬም እንደትናንቱ በከተሞች በማምረቻና ማከፋፈያ እንዲሁም በአገልግሎት መስጫ ድርጀቶች ውስጥ ለተመሳሳይ ሥራ ከወንዶች ባነሰ ደሞዝ የሚቀጠሩት ሴቶች ናቸው። ወያኔ የሚያናፋለት “የለውጥና ትራንስፎርሜሽን” (አገርን ለባዕዳን ከበርቴዎች የመሽጥ) ፖሊሲው በዋናነት ሰለባ የሆኑት ሴቶች ናቸው። ዛሬ የሀገራችን የገጠር ለም መሬቶችና ሰፋፊ የከተማ ቦታዎች የተያዙት በባዕዳን ቱጃሮች ነው። በእነዚሁ ባለሀብቶች በተያዙት የእርሻ ተቋማትና ፋብሪካዎች ውስጥ በገፍ ጉልበታቸው የሚበዘበዘውና ለማኅበራዊ ቀውሶች የተጋለጡት በአብዛኛው ሴቶች ናቸው። ከእነዚሁ ውስጥም በአመዛኙ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ በዝቅተኛ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ናቸው። የእለት ኑሮአቸውን ለማሽነፍ ሲሉ የወለዷችውን ህፃናት ልጆቻቸውን በጀርባቸው እንዳዘሉ ለጤና እጅግ ጠንቅ የሆኑ ኬሚካሎችን በሚጠቀሙ የሥራ ዘርፎች በአበባ እርሻዎች፤ በቆዳና በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች... ወዘተ ተሰማርተው የሚሰሩ እናቶችና ወጣት ሴቶች የጤና ዋስትና የሌላቸው ሲሆን ፤ የሚያገኙት ክፍያም በጣም ዝቅተኛ ነው። አገዛዙ በሚያራምደው የተሳስተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተነሳ በቀጥታ ጉልበታችው ከሚበዘበዘው ሴቶች ቁጥር ባልተናነስ ሁኔታ ለተሻለ ሥራና ለተሻለ ገቢ በሚል ከገጠር ወደ ከተማ በመፍለስ ለሴተኛ አዳሪነትና ለአደንዛዥ እፅ የተጋለጡት ሴቶች ቁጥር ካለፉት ሥርዓቶች ጋር ሲነጻጸር እጀግ አስፈሪና አስደንጋጭ ነው። በዚሁ ማኅበራዊ ጠንቅ የተነሳ ከትዳር ውጪ የሚወልዷቸውን ሕፃናት ብቻቸውን ለማሳደግ የሚገደዱት ሴቶች ቁጥር በርካታ ሲሆን ፤ የእነዚህም ህጻናት የወደፊት እጣ ፋንታ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመቱ አስቸጋሪ አይሆንም። የሀገራችን የጤና ይዞታ እጅግ ደካማ ከመሆኑ የተነሳ በቀላሉ መከላከልና መወገድ የሚቻሉ ተላላፊ የሆኑ እንደ ኤች አይ ቪ ኤድስ፤ የሳንባ ነቀርሳ፤ የወባ በሽታና ፤ ኮሌራ.... ወዘተ በመሳሰሉት በሽታዎች ተጠቂዎቹና በአብዛኛው ለሞት ሰለባ የሆኑት ወጣት ሴቶችና እናቶች ናቸው።
በአገራችን ዛሬ ከሚሞቱት እናቶች ከመቶ አሥራ ሰባት (17%) የሚሆኑት በወሊድና ከወሊድ ጋር በተያያዙ ምከንያቶች ነው። በተላላፊነቱና በገዳይነቱ የሚታወቀው የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ በማገርሽቱ የተነሳ የበርካታ እናቶችንና ወጣት ሴቶችን ህይወት ስቃይ ከፍ እያደረገና እየቀጠፈም ይገኛል። ዛሬ በአገራችን በረሀብ የሚጠበስው ሕዝብ ቁጥር ከአሥር ሚሊዮን በላይ መሆኑን የውጭ ብዙሃን መገናኛዎች በስፋት የዘገቡት ሲሆን ፤ እሰከመጪው ሚያዚያ ወር ድረስ በቂ የሆነ የምግብ እርዳታ ካልደረሰ በሰው ህይወት ላይ በተለይም በእናቶችና በህጻናት ላይ ሊደርስ የሚችለው አደጋ አሰቃቂ እንደሚሆን እየተነበየ ነው። ተደጋግሞ መነገር ያለበት ደግሞ፣ ለዚህ ሁሉ በሕዝብ ላይ ለደረሰውና ለሚደርሰው መከራና ሥቃይ ተጠያቂው በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ የሚከተለው ብልሹ ፖሊሲ መሆኑ ነው።
ወያኔ በሚያራምደው የጎሳ ፖለቲካ በዋናነት ሰለባ የሆኑት ሴቶች ናቸው ስንል ያለ ምክንያት አይደለም። ወያኔ ብዙኅኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ በጎሳ ከፋፍሎ ጥላቻና ፍራቻን በማስፋፋት የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓቢይ እሴት የሆነውን መተሳሰብንና መተማመንን ሸርሽሯል። የማኅበረሰብ ዋልታና መሠረት የሆነውን ቤተስብ ጭምር እንዲናጋና እንዲናድ አድርጓል። በአጠቃላይ በሥልጣን ላይ ያለው አናሳ ቡድን፣ ከፍጥረቱ ጎጠኛና አምባገነናዊ በመሆኑ የሕዝብን መሠረታዊና ዴሞክራሲያዊ የሆኑ ጥያቄዎችን በአግባቡ ሊያስተናግድ ቀርቶ የዴሞክራሲ ጠረን ሸቶትም ስለማያወቅ፤ የሴቶችን መብትና የእኩልነት ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ያለው ባህሪ አይፈቅድለትም። ስለሆነም የሴቶች መብት ይከበር፤ የእኩልነት መብታቸው ይረጋገጥ፤ ሴቶች የሥልጣን ባለቤትነቱን በዕኩልነት ይካፈሉ ፤ ብሎ መታገል ወቅታዊ፣ ተገቢና፣ አንገብጋቢም ነው ብሎ ኢሕአፓ ዛሬም ያምናል። በድርጅቱ የፖለቲካ መርሃ ግብር/ፕሮግራም/ ላይ እንደሰፈረው ሴቶች በኢትዮጵያ በማኅበር የመደራጀት መብት መከበር፤ በፖለቲካው፣ በማኅበራዊ ኑሮ፣ በትምህርት፣ በባህልና በጤና አገልግሎት መስክ የሴቶችን ሙሉ መብት ማስጠበቅ ወሳኝ ጉዳይ ነው። በአጠቃላይ ሕዝብና አገርን ለመታደግ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በፀረ ወያኔው ትግል መሳተፍ እንዳለበት ይታመናል። ብዙኅን ስንልም በቁጥርም ሆነ በኅብረተስቡ ውስጥ ባላቸው ቁልፍ ቦታና ሚና ዓቢይ የሆኑትን ሴቶች ልንዘነጋ አንችልም። ኢትዮጵያን የማዳኑ ተጋድሎ በወንዶች ብቻ የሚካሄድ አይደለም። በተጋድሎው ሴቶች በሥፋትና በቀጥታ ካልተሳተፉ እናት ኢትዮጵያ መጨረሻዋ አያምርም። ሴቶችም ትምክህት በደቀነባቸው ችግርና ጋሬጣ ሁሉ ሳይደናቀፉ ስብዕናችውን አስረግጠው ለሀገር ያደረጉትን ተጋድሎ ዛሬም በማደስ ለመብታቸውና ለሀገር ሥርየት ግንባር ቀደም ሆነው መደራጀትና መታገል ይጠበቅባቸዋል።
ኢሕአፓ ከምሥረታው ጀምሮ የሴቶችን መሠረታዊ መብት መከበር ዓቢይ ዓላማ አድርጎ የተንቀሳወሰ ሲሆን ተግባራዊ ሆኖ ሴቶች ሙሉ በሙሉ መብታቸውን የሚቀዳጁበት ሁኔታ እንዲፈጠር እስካሁን ትግሉን ሳይቋርጥ ይገኛል። ፋሽስቱና ሰው በላው የመንግሥቱ ኃይለማርያም አገዛዝ ሴቶችን ጨፍጭፏል፤ ማኅበራቸውን አፍርሶ በቅጥረኞች ማኅበር ተክቷል፤ ብዙዎችን ለስደት ዳርጓል፡፡ ወያኔ ባሰ እንጂ በግብሩ አልተናነሰም። ስለ ሴቶች መብት እየለፈፈ ሴቶችን መብት አልባ አድርጎ እየቀጠቀጠ ከመሆኑም በላይ ለዘመናዊ ባርነትም እየሽጣቸው ነው። ዘረኛ አገዛዙ አማራ፣ ኦሮሞ፣ አኝዋክ፣ ሶማሌ፣ ... ወዘተ በሚል ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የትግራይ ሴቶችንም (በካድሬነት ለሱ ከሚያገለግሉት በቀር) መብት አልባ አድርጎ መቀጠሉ የሚታይ ነው። ሕጻናትንም ለጉዲፈቻ እየሸጠ ትርፍ አካብቷል። የባህል ዝቅጠትን ሲያሰፍንና ድህነትንም ሲያስፋፋ ሴቶችን ለአደጋ ማጋለጡን ቀጥሎበታል። ለባለጌ ሼኮችና ለሌሎች ባለጌ የውጭ ዜጎች ወጣት ሴቶቻችን ሰለባ አድርጓል ብንል ስህተት የለውም። ወያኔ ጸረ-ሕዝብ ነውና ጸረ ሴትም ነው።
በፋሺስቱ ደርግ ጊዜ የሴቶች አስተባባሪ ኮሚቴን በማቋቋም ትግሉን ለማጠናከር የተደረገው ጥረት ይታወሳል። ወያኔም የድርጅትን ጠቀሜታ ስለሚያውቅ ሴቶችን በነፃ የመደራጀት መብት ነፍጎ የራሱን ጸረ-ሕዝብ ካድሬ ሴቶችን ለይስሙላ በመድረክ አውጥቶ እያሳየ መሆኑን እያየን ነው። የአንድ አገር ዜጎች ነፃነታቸውንና መብታቸውን ለማስከበር ለሚያደርጉት ትግል መደራጀታቸው አስፈላጊ ሲሆን ሴቶች ደግሞ የሚደርስባቸው በደል ድርብ ድርብርብ ስለሆነ በሴትነት መደራጀታቸው ወሳኝ ነው። እንደ ሕዝብ ይጨቆናሉ፤ እንደ ሴቶችም የወንዶች ሁሉ ወይም የአብዛኞቹ (አሉታዊ በሆኑ ባህላዊ ወጎች) ጭቆና ተበዳይ ናቸው። መብታቸውን ለማስጠበቅ በሴትነታቸው የመደራጀት መብታቸው ይከበር የሚባለውም ለዚህ ነው። ለሴቶች መብት መከበር ድርጅት ወሳኝና ቀዳሚ ሆኖ ስለሚገኝ።
በወያኔ አገዛዝ ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱትን መድፈር ወይም ማባለግ፤ ለባዕዳን ብቻ ሳይሆን ለወያኔ ባለስልጣናትም የተተወ ነው። ይህ አሳፋሪ ክስተት የቀነሰ ይምስል እንጂ በተለይ በገጠር ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ሕፃናትን ለጋብቻ መዳረጉ አሁንም አልቆመም። ሴቶች የአካላቸው ባለቤት መሆናቸውም ገና ጊዜን ጠባቂ ነው። የወያኔ አጫፋሪዎች በጤንነት መስክ ሴቶች ሁኔታቸው ተሻሽሏል ቢሉም በመሬት ላይ ያለው ሐቅ ግን ሌላ ነው። በግርዛት አካል መምተሩ፤ በልጅነት መዳሩ፤ ጠለፋ ማካሄዱ ወዘተ... ዛሬም እንዳለ አለ። የሀገራችን አብዛኛው ሕዝብ ወጣት በሆነበት፣ ከነዚህም ብዙዎቹ ሴቶች መሆናቸው ራሱ የመብት ረገጣው ብዙኅኑን ሴቶች እንደሚያጠቃ የሚገልጽ ነው። በጉዳዩ ላይ ለዓመታት ብዙ የተባለና ትግል የተካሄድበት ቢሆንም መብታቸውን የማስከበር ክቡር ዓላማ ግቡን ሊመታ የሚችለው ሴቶች ከሁሉም በላይ እራሳቸው ሲንቀሳቀሱና ሲታገሉ ነው። ይህ ደግሞ በቅድሚያ እንደሴት መደራጀት፤ በታጋይ ድርጅቶች ውስጥ ገብቶ የትግሉ አካል፣ ምሰሶ መሆን ማለት ነውና ሌላ መፍትሔ መሻቱ ፋይዳ አይኖረውም። ሕዝብ ራሱን ነጻ ማውጣት አለበት እንደሚባለው ሁሉ ሴቶችም የመብታቸውን ጥያቄ ራሳቸው ካልያዙትና ካልተንከባከቡት ውጤቱ አያምርም። ሀገራት እራሳቸውን ነፃ አወጣን ቢሉም (በርግጥም ከቅኝ ገዥነት እራሳቸውን ነፃ ያረጉ የአፍሪካም ሆነ የላቲን አሜሪካ እንዲሁም የእስያ ሀገራት ቢኖሩም) የሴቶች መብት ዛሬም በዝቅተኛ ደረጃ ያለባቸው ሀገራት ናቸው። በተቃዋሚ ድርጅቶች ውስጥም ቢሆን የሴቶች ሚና እየደከመ መምጣቱ እንዲሁ ሊያሳስበን የሚገባ ጉዳይ ነው። ብቅ ያሉት ሴቶች በወንዶች ተጠልፈዋል፤ መጠቀሚያም ሆነዋል። ፖለቲካ የወንዶች ክበብ ሆነ የሚባለው አለምክንያት አይደለምና ይህም መቀየር አለበት። ያለ ሴቶች ተሳትፎ ሀገራዊ የሆነው ትግላችን ለድል አይበቃም የተባለውን እናቶች እህቶቻችን ደማቸውን አፍሰው አስመስክረዋልና ከቶም መረሳት የለበትም።
ይህን በተመለከተ ከዓመታት በፊት እንዲህ ብለን ነበር ለማለት ሳይሆን ያኔም ያልነው ዛሬም ሊባል የሚገባው ይኸው በመሆኑ ነው በመጠኑ እንጠቅሳለን ። በ1966 ያልነውና ዛሬ የምንለው ቢመሳሰል ጥፋቱ ከእኛ ሳይሆን ከአገዛዞቹ ነው-- ሁኔታውን መቀየር አልቻሉምና!
ምን አልን ስለ ሴቶች መብት በወንዶችና በሴቶች መሃከል የእኩልነትን መብት ማስከበር፤  በፖለቲካ፣ በኤኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ኑሮና በባህል፣ በትምህርት፣ በጤና አገልግሎት፣ ... ወዘተ በወንዶችና በሴቶችመሃከል እኩልነት እንዲኖር ማድረግ፤  ለተመሳሳይ ሥራ እኩል ክፍያን ማረጋገጥ፤  የሴቶችን በማኅበር የመደራጀትን መብት ማረጋገጥ፤  ለማኅበረሰብ ዕድገትና ነጻነት የሚስማሙ የጋብቻና የቤተሰብ ሕጎችን ማውጣት፤ በዚሁ ሕግ በሚወሰነው መሠረት ለአቅመ ሔዋን ዕድሜ ያልደረሱ እንዳያገቡ ማገድ፤ ሴቶች ወሊድን ለመቆጣጠር ያላቸውን መብት ማስከበር፤ሴተኛ አዳሪነትን ለማስቀረት ለሴተኛ አዳሪነት መስፋፋት ምክንያት የሆኑትን ሁኔታዎች ለማስወገድ መጣር፤ለሴተኛ አዳሪዎች ትምህርትን ለመስጠት መጣር ፤  በኢትዮጵያ ገጠሮች ውስጥ የሴቶችን ህይወት ለማሻሻል አስፈላጊ የሆኑት የመጠጥ ውሃ ቧንባዎችን ወይንም ጉድጓዶችንና የመስኖ ውሃ ቦዮችን ፤ የወፍጮ ተከላዎችንና የማገዶ አቅርቦቶችን በቅድሚያ መስጠት፤ የሴቶች መብት መከበሩን ማረጋገጥይህን ሲልም በባህል፣ በሃይማኖት፣ ... ወዘተ ሽፋን የሴቶችን መብት የሚገደቡትን ሳያወላውል ተቃውሟል፤ አሁንም በመቃወም ላይ ነው። የሴቶች መብት ያልተከበረበት ሀገር ዴሞክራሲያዊ ነው ሊባል መቼም አይቻልም። ሴቶችን ጨቁኖ መብት ተከበረ ማለት ዘበት ነው። በርግጥ ነውናም የሀገራችን ሴቶች ሙሉ መብት እንዲከበር ኢሕአፓ ትግሉን ይቀጥላል። ሴቶችም ለመብታቸው ተደራጅተው እንዲታገሉ የቆየ ጥሪውን ዛሬም ያስተጋባል ግዴታውም ይሆናል።

  • የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ይከበር !! ድርብ ጭቆና ያክትም !!
    ጸረ ወያኔ ትግላችን በጋራ ይፋፋም !!

page6image8904

No comments:

Post a Comment