Wednesday, April 6, 2016

ሀገር በታኙን ቫይረስ ለማምከን / ቢንያም ሙልጌታ ( ከኖርዌይ )

ሀገር በታኙን ቫይረስ ለማምከን

ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ታሪክ ናት፡፡ይህም በዜጎችዋ አንደበት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም እውቅና በመስጠት የሚናገሩት ነው። ጥንታዊና ታሪካዊነቷ ለጉብኚዎቿ አይን መስህብ የሚሆኑ ዘመናትን ያለፉት ቅርሳ ቅርሶች ብቻ ሳይሆኑ ህዝቧ በራሱ የተለየ ስብዕና ባለቤት ነውና ብዙዎች ይደነቁበታል። ፍቅሩ፣ ደግነቱ፣ መከባበሩ፣ ችሮታው፣ ወኔው፣ ጀግንነቱ፣ያለውን ተካፍሎ መኖሩ እና ከሌላው ትውልድ ለየት የሚያደርገው ብዙ ብዙ ተፈጥሮው ወ ዘ ተ . . . ያስደምማል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሀገር ወዳድ የሆኑ ጀግኖች የፈለቁበት ሀገር በመሆን፤እንኳን ዳር ድንበርን አፍሩ እንዳይቆነጠር የታገሉ ሴት እና ወንድ ታጋዩች የሞሉባት ሀገር ናት። በአገራችን ረጅም ታሪክ ውስጥ ህዝቦቿ በርካታ
ውጣ ውረዶችን ያለፉና ዘውዳዊው ተሽሮ ወታደራዊ አገዛዝ ሲተካ የሚደርስበትን የተለያየ እንግልት እና በደል ዋጥ ስልቅጥ አድርጎ የእርስ በእርስ የነገድ እና የብሔር ብሎም የሀይማኖት ልዩነቶች ሳይበግሩት እና ሳይከፈፍሉት የኖረ ህዝብ ነው።
በዚህች ጥንታዊና ታሪካዊ አገር ብሶት የወለደው ብሎ ለአንድ ብሔር የታገለው አምባገነን ቡድን ከሀያ አምስት አመት በፊት ምሊኒክ ቤተ መንግስት ሲከትም ለዜጎች በእናስብላችኋለንና እናውቅላችኋለን ማስመሰያ ተሸብቦ ከጊዜ ወደጊዜ ለአፍሪቃ እንኳን ምሳሌ በመሆን አንድነቷን እና ድንበሯን በማስጠበቅ የተፈራችውን ሀገር ሊመዘብራት ተነሳ። አሁን ላይ የአገዛዙ ሌብነት እና በደል በጉልህ በሁሉ ዘንድ ፀሀይ የሞቀው ጉዳይ ሆኗል። የኢትዮጵያ ህዝብ መብት እና ነፃነት ክፉኛ ተደፍጥጦ ህዝባችን ወሳኝ ሳይሆን ውሳኔ ተሸካሚ ብቻ በመሆን በፈላጭ ቆራጭ ዘረኛ ስር በመውደቅ ምድሪቷ የመከራ በትር እየደቆሳት እንደሆነ ከሁላችንም የተደበቀ አይደለም፡፡ ወያኔ ወደ ስልጣን ከመጣበት ከ ሀያ አምስት አመት በፊት የነበረውን ስርዓት ብንመዝነው እነዛ ዘመናት ለአገራችን ጭቁን ህዝቦች በመሪርነታቸው ፍፁም የማይረሱና አገራችንን ወደ ኋላ የጎተቱ በሁሉም ልብ ተፅፈው የሚገኙ የቁጭት ዘመናት ቢሆኑም የአሁኑ ዘመን ጭቆና እና በህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍ ከየትኛውም የማይገጥም ነው። ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ በየግዜው መልኩን እና ግፋዊ ስርዓቱን በተለያየ ቅርፅ እየቀያየረ በሀገሪቷ ላይ ከቶውንም ያልታየ ፋሺስታዊ ድርጊቱን አቀላጥፎታል።
በኢትዮጵያ ምድር ላይ ህዝብን ከህዝብ፣ወገንን ከወገንን፣ሀይማኖትን ከሀይማኖት አንዱን ብሔር ከሌላው ብሔር በማናቆር እና በቂም በቀል ህዝብ እንዲጠላላ የሚያደርግበት የወያኔ ቫይረስ በሀገሪቱ ዳር እስከመሀል ድረስ በሁሉ ዘንድ ተውሳኩ ተዛምቷል። ቫይረሱንም ለማምከን ኢትዩጵያዊነት በትውልዱ ስብዕና ላይ እንደገና ይገነባ ዘንድ ማንም ሳያፈገፍግ ሊስማማበት የሚገባ አንገብጋቢ መፍትሔ ነው። ለኦሮሞው መበደል አማራው ካልጮኸ ለአኝዋኩ ጉራጌው ካልተነሳ ወያኔ ወደ ግቡ ወደ ስኬቱ ይገሰግሳል ይፈጥናል። ኢትዩጵያዊነትን የማጥፋት ስኬት እና ጉዞ። የቂም በቀልና የዘረኝነት ደመና አገሪቷን በሸፈነበት በዚያን ወቅት፣ በጎንደር ክፍለ ሃገር ጭካኔ በተሞላው አካሔድ የወያኔ አጋዚ ታጣቂዎች ህዝብን በማፈን እና በማፈናቀል እና በዘራቸዉ ምክንያት ዜጎች ይጠቁ ዘንድ የሚገፋፋ ርካሽ ቅስቀሳ በስፋት እየተገበሩ ነው። ኢትዮጵያዊው ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ በአንክሮ ሲታይ ሆን ተብሎ በገዢው ክፍል አንድን ብሔር ከማጉላት አንፃር የሚደረግ መሆኑን ማንም ሊስተውም አይገባም። የሚያስደንቀዉ ነገር ግን በኦሮሚያ ክልልሎች እና በአማራው ክልል የሚኖሩ አበዉና ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችን ተሰብስበዉ ... ለዘመናት አብረን ኖረናል። ተዋልደናል። ተጋብተናል። የነርሱ ልጆች የኛ ልጆች ናቸዉ። እነርሱን ማጥፋት እኛን ማጥፋት ነዉ... ብለዉ ፍቅርንና አንድነትን እንዳይሰብኩ የወያኔ ቫይረስ ከትውልዱ ላይ ኢትዮጵያዊነትን እያሳሳው ለሀገር ሳይሆን ለብሔር ዘብ መቆምን እያስተማረ ይገኛል።
በተለያዩ የአለም ህብረተሰብ ዘንድ ከዘረኝነት አልፎ በጋራ መሥራት በተጀመረበት በዚህ የስልጣኔ ወቅት፣ በአገራችን ባሉ ዜጎች መሀል የሀይማኖት መሪዎችንም በሚያካትት ሁኔታ ይህ አይነት ከዘር ጋር የተገናኙ
page1image24184

ችግሮች መፈጠራቸዉ እጅግ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነዉ። ይህም ወደ አስከፊ ደረጃ ላይ እየደርሰ ይገኛል። በተለያየ የትምህርት ተቋም ውስጥ የሚማሩትን ሳይቀር ይኸው የወያኔ የዘረኝነት ተውሳክ ትውልዱን ለሀገር ቀናኢ መሆኑን እየሰረቀው ይገኛል። የተማረው ወገን የበለጠ መብሰልና ማገናዘብ ሲገባው፣ በሰይጣን መንፈስ የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ግለሰቦች ለግል ጥቅማቸዉ የሚያናፍሱትንና የሚቆሰቁሱትን የጥላቻና የዘረኝነት ፖለቲካን በማስተናገድ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ለጥቂቶች መጠቀሚያ እስክንሆን ድርስ ማስተዋል መጥፋቱ እጅግ አሳዛኝ ከመሆኑም ባሻገር ትልቅ የሆነ በስልጣን ላይ መባለግን እና እንዲሁም ደግሞ ወያኔ የኢትዩጵያ ጠላት እና አጥፊዋ እንጂ ገንቢዋ እንዳለሆነ በግላጭ የታየበትም ሆኗል።
በምድራችን ላይ ፍቅርና ሰላም ቢኖር ኖሮማ፣ አሁን በስልጣን ላይ ያሉ አምባገነን ባለሥልጣናት በጋዜጠኞች በብሎገሮች እና ጦማሮች እንዲሁም ግፉና ጭቆናው ይብቃ ድምፃችንም ይሰማ በሚሉ ኢትዮጵያዉያን ላይ የሚያራምዱትን የእልህና የግፍ ፖለቲካ ባስወገዱ ነበር፣ በጥያቄ የተሞላውን ህዝብ በመጠጋት ከሁሉ ኢትዮጵያዊ ጋርም በትህትና የአገራችንን ችግር ለመፍታት ቢነጋገሩ ፣ በውጭ ሀገር በተለያየ ምክንያት በስደት የሚኖረውን ዜጋ እንደ ሰይጣንከማየትና ከማጥላላት ይል ቅንነት ያለበት ንግግር ቢጀመሩ እና የምዕራባውያንን ፍርፋሪ ንቀው ዲያስፖራውን ዉጭ አገር ከሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የዉጭ ምንዛሪ መሰብሰብ ይቻል ነበር። እጅግ አያሌ መልካም እና ለሀገር የሚበጅ ነገራት በጋራና በአንድነት ማከናወን ይቻል ነበር።ዳሩ ወያኔ ከደደቢት ጀምሮ የተለከፈበት አጋንንት የሚገድል የሚሰርቅ የሚያጠፋ ሆነና ለኢትዮጵያችን መርገም ሆነ። የበረሐው ልክፍት ለሚያስተዳድረው ህዝብ፣ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ እንዲያሟላ አላስቻለውም ገና ከጥንስሱ በሀገር ልማት አልተመሰረትም እና ህዝብ የሚኖረው ኑሮ ከበረሐ ተለይቶ ሊታይ አይችልም። የህዝብን ኑሮ ባዶ በረሐ። የሚያቃጥል፣ የሚያነድ በረሐ ሆኗ - ኃለፊነቱን ያልተወጣ መንግስት ደግሞ ህዝብን ለእንግልት ለስቃይ እና ለሞት አሳልፎ ይሰጣል። እየሰጠም ነው።
በተለይም በአሁን ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ብሔር እና ጎሳዎች ትልቅ በደል እየተፈፀመባቸው ባለበት በዚህ ከባድ ወቅት የሚከተለውን ማጤን አስፈላጊ እንድሆነ ተናግሬ ሀሳቤን ለዛሬው ልደምድም። በሀገራችን ላይ የተበደለው እና የተጠቃው አንድ ብሔር አይደለም፣ የተፈናቀለውም አማራው አሊያም ኦሮሞው አይደለም ቤጌምድር ለትግራይ ሲሸነሸን ወልቃይቶች ተሰደዱ ተሰቃዩ የሚለው መገለጫ ሊሆንም ከቶ አይገባም። ኢትዩጵያዊው ወገን ነው በጨቋኝ አገዛዝ እየተሰቃየ ያለው። ስናብር በእርግጥ የምናስረው ነገር አለ ኢትዩጵያዊነት በሁሉ ዜጋ ላይ ይታተም!
ሀገራችንን እና ትውልዳችንን በመለያየት ቫይረስ በመበከል በዜግነታችን ለትውልድ እንዳንታገል ያደረገንን የወያኔን ተውሳክ አምክነን ሰሜኑ ለደቡቡ ምስራቁ ለምዕራቡ ይጮህ የሚገባበት ስልጣኔ እና እውቀት ላይ እንድረስ። በተለያዩ ውብ እና ማራኪ ባህል የተላበስን ኢትዩጵያዊ ህዝቦች ነን። ተከብራ የኖረች ሀገራችን ለተተኪው ትውልድ ተላልፋ ዜጋው የሚለማባት እና በሰላም የሚኖርባት ሀገር እንድትሆን እንደ ኢትዮጵያዊ የምንወስደው አማራጭ አንድ እና አንድ ነው፤ የሀገራችን ምድራዊ አቀማመጥ አመቺ በመሆኑ ከወደ አሥመራም ሆነ ከወደ ካይሮ የሚያስመሽገን ምንም ምክንያት የለም ወቅታዊው የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታም የሚያሳየን ይህኑኑ ዕውነታ ነው። ወያኔን በሁለገብ ትግል አንድነትን አጠናክሮ ለህዝብ ከቆሙና ታግሎ ከሚያታግሉ እንደ ኢህአፓ ያሉ ሕብረ ቤሄርና የብዙ ትግል ተሞክሮና በቆመለት ዓላማና በአገራችን ቤሄራዊ ጥቅም አይደራደሬ በመሆናቸው ልንደገፋቸውና በየቦታው የተበተታተነውንና መሪ ያጣውን ትግል እንዲመሩና ሕዝባዊውን ትግሉእንዲያጥናክሩትና እንዲያፋፍሙት በያለንበት ሆነን ጥሪ ልናቀርብላችውና እንዲሁም ከጎናቸው በመቆምና በማጠናከር እና እንደዚሁም ደግሞ ለህዝብ ነፃ መውጣት መስዋዕት ለመሆን ከቆረጡና በኢትዮጵያ ህልውናና ሉዓላዊነት ላይ ምንም ብዥታ ከሌላቸው የተለያዩ የህዝብ ክፍሎች ጋር በማበር እና በመያያዝ የወያኔን ሀገር በታኝ ቫይረስ ለማምከን በኢትዩጵያዊነት ስሜት እና ሞራል እንነሳ! እንደራጅ! ኢትዮጵያ ከወያኔበቀር ሌላ ጠላት የላትም። አንዱን ጠላት በተባበረ ክንዳችን እናድቀው!!!
እናቸንፋለን!!! ቢንያም ሙሉጌታ
Binimoja@yahoo.com 

No comments:

Post a Comment