Monday, April 25, 2016

ጉንዳን ሳይገባ አመድ ነስንስ ( Finote radio )


በረዥም ዘመናት ታሪኳ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ ጥቃት የደረሰባት፤ በአመዛኙ፤ ከባዕዳን ኃይሎች በበለጠ በሀገር ውስጥ ከሃዲያን ነበር ቢባል፤ ስህተት አይሆንም።  የውጭ ወራሪ  ኃይሎች ነፍጥ አንግበው  ሲመጡባት፤ የውስጥ ባንዳዎች ስጋጃ አንጥፈው ተቀለዋቸዋል።  ዋገምት ደግነው፤  ደሟን እየመጠጡ፤ ለበዕዳን ወራሪ ኃይሎች  አስተላልፈውላቸዋል ። የሀገሪቱን ውስጠ ምሥጢር እያሾለኩ አቀብለዋቸዋል። የሚገርመው ደግሞ፤ ይህንን የክኅደት ተግባር የፈፀሙት ፤ በአብላጫው፤ ገበሬዎችና ተራ ዜጎች ሳይሆኑ፤ ሹማምንቱና በኃላፊነት ቦታ የተቀመጡ ሰዎች ነበሩ።
ስማቸውን መጥቅስ፤ የዚህ ሐተታ ዓላማ ባለመሆኑ፤ ወደዚያ አናዘነብልም። ባንዳዎችና ሌሎች የጠላት ተባባሪዎች፤ በሀገሪቱ ላይ ያደረሱት  ጉዳትና ጥፋት በቀላሉ የሚገመት አልነበረም። አሁንም ያው ነው። የሕዝብና የሀገር ጠላት በአገዛዝ ደረጃ እስካለ ደረስ፤ ሰላይና ባንዳ፤ እንደ አሽን ክታብ መፈልፈሉ አይቀርም ። ጉንዳኑ ሳይገባ ፤ አመድ ሊነሰንስ ግዴታ ነው።  ያልነሰነሰ ተደመሰሰ! ያልጠረጠረ ተመነጠረ ! እንዳይሆን ሁሉም በያለበት ነቅቶ እራሱን እንዲጠብቅ እናሳስባለን !
 የሀገር ውስጥ ቀበኞች ቁጥራቸው እጅግ አነስተኛ ቢሆንም ቅሉ፤ ያስከተሉትና  ዛሬም እያስከተሉት ያለው  ጉዳት ግን  እንዲሁ በችልታ ሊታለፍ አይገባውም ።  ምክንያቱም ይህ ጥፋት፤ አሁንም በተጠናከረ መልኩ እንደቀጠለ  በመሄዱ ነው ። የጠላት ተባባሪዎችን ጥፋት ሊያቆመው ቀርቶ፤ አደጋውን እንኳ  በቅጡ  ሊገነዘብ የቻለ ማንም ኃይል  እንደሌለ  ስለምንገነዘብ፤ ሁኔታው በእጅጉ ያሳስበናል።  
 በየትኛውም ኅብረተስብ ውስጥ፣ በየአንዳንዱ 12ት ኀዋርያት፤ አንድ አንድ ይሁዳ ስለሚገኝ፤  በሀገራችንም የካሃዲያን መኖር አያስደንቅም። የግል ጥቅምን ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅም  በላይ  በሚያስቀድም ኅብረተስብ  ውስጥ ፤ ሰብዕናቸውን  ለአላፊ-ጠፊ  ጥቅማ-ጥቅም የሚለውጡ ዜጎች እንደሚበረክቱ የታዘብነው ጉዳይ ሆኗል ።
 " አንድ ሎሌ ለሁለት ጌቶቹ  በዕኩል ታማኝነት ማገልገል እንደማይችል" ሁሉ፤ የመርኅ  ሰው ነኝ የሚልም ግለሰብ፤  የመርኅና የጥቅም ተገዥ ሊሆን አይችልም። አንዱን መርጦ፤ ሌላውን መተው  ይገባዋል ።  በሁለት ካራ  እየተበላ ብዙ ጊዜ መቆየት የሚቻል አይሆንም።  
ይህ ክስተት በኅብረተስቡ ውስጥ መኖሩን ከተገነዘብን ፤ በሕዝቡ ውስጥ ጉንዳኑ ከመግባቱ በፊት አመድ መነስነስ፤ እንደ መጀመሪያ የመከላካያ መስመር ሆኖ ሊያገልግል ይገባል። አመድ መነስነስ፤ ጉንዳን እንዳይገባ የሚረዳ ብልሃት ከሆነ፤ ሰላዮችም ሰርስርውእንዳይገቡ አስቀድሞ  ሰርሳሪዎቹንና ያሰማራቸውን  ኃይል  ጠንቅቆ  ማወቅ   አስፈላጊ  ነው ። 
የእነርሱን ማንነት ማውቁ  ብቻውን  ደግሞ በቂ አይደለም ። ሰላዮቹን የሚያሰማራችው ኃይል  በጉልህ  ማወቁ  አስቸጋሪ ላይሆን ይችል ይሆናል ።  ለስለላ የሚሰማሩትን  ሁሉንም ማወቁ ግን ቀላላ አይሆንም ። ምክንያቱም፤ የሚያሰማራቸው ኃይል፤ ከበቂ በላይ ገንዘብና መመሪያ ስለሚያፈስስላቸው፤ በኅብረተሰቡ ውስጥ ሕዝቡን መስለው ተመሳስለው፤ በልተው እያበሉ፤ ጠጥተው እያጠጡ፤ ስቅው እያሳቁ፤ አልቅሰው እያስለቀሱ፤ ድርና ማግ ሆነው ስለሚኖሩ፤ ሕዝቡን የማዘናጋት ዕድላቸው ሰፊ ነው ማለት ይቻላል ።
የዕለት ጉርስ፤ የዓመት ልብስ  የአረረበት ኅብረተስብ ደግሞ ፤ የሰላዮችና የወስላቶች መፍንጫ -መጫዎቻ  መሆኑ አያስገርምም።  በመሆኑም፤ ፀረ-ሕዝቦች ማንነታቸውን ሳያሳውቁ፤ እኩይ ድርጊታቸውን እየፈፀሙ ላልተወሰነ ጊዜ ለመቆየት የሚያግዳቸው ስጋት አይኖራቸውም ።  በመጨረሻ ሊነቃባቸው ቢችልም፤ እስከዚያው ድረስ  የሚያደረሱት ጉዳት ግን ቀላል አይሆንም ። ከዚያ ወዲያ፤  " ጅብ ከሄደ፤ ውሻ ቢጮኽ "  ምን ይጠቅማል  ?
ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ ተሽቀርቅራ ተፈጥራ ግና ተጎሳቁላ የምትኖር ሀገር ነች። በሁሉም ገጽታው ሲመለከቷት፤ ቁስቁልናዋ የትየለሌ ነው። በአሳለፈችው ትዝታ ብቻ ለመኖር  እየፈለገች፤ አሁን ያለችበትን አስከፊ ሁኔታ ለማየት ተስኗታል ።   አሁን ያለውን ሁኔታ በቅጡ አለማየቷ ደግሞ፤ የወደፊቱን አጋጣሚ ተዘጋጅቶ ለመጠበቅ አልተሰናዳችም ። ትከሻ ሊሸከመው፤ ኅሊና ሊቀበለው፤ የማይችል ጥፋትና በደል እየተፈፀመባት፤ ከዚህ አሳርና መከራ ሊያላቅቃት የሚችል ኃይል  እስከሁን አልተፈጠረላትም።  የበደሏን ፅዋ ሊቃመሱላት የሚፈልጉ መሪዎች አላጋጠማትም  ። ይልቁንም ፤ " ኃጢአተኛ  ሳያሳድዱት ይሮጣል ። " እንደሚባለው፤ በፈታኝ ጊዜ፤ ለበላዒ- ሰብ እያጋለጧት ይሸሻሉ። ወንጀለኞች፤ ወንጀላቸው እያሳድዳቸው ይጠፋሉ።   ሀገር አጥፍተው እስኪጠፉ ደርስ ግን ጊዜና  ዕድል ሊሰጣቸው አይገባም ። ተባብሮ እነርሱን ማጥፋት ጊዜ ሊሰጠው አይገባም።
 ነዋሪዎቿም፤ "ትዕግስት ውቅያኖስን ያደርቃል። ተራሮችም በንነው ይጠፋሉ።"  የተሰኘውን ብኂል እያስተናገዱ፤  በቀቢፀ- ተስፋ መኖርን  ይመርጣሉ።  ሊሂቃኑና የፖለቲካ  ጠበብቶችም፤  " ብልጥን ማታለል ትርፉ ቂም ነው " የሚለውን ይትበሃል፤ እየዘነጉ፤  የሕዝቡን ፍቅር ፤ በሽንገላ  ምላሳቸው  ለመግዛት ይመኛሉ። ይህ ግን አይሆንም። ምክንያቱም ፤ የሕዝብን ፍቅር፤ ልብና አዕምሮ ማቸነፍ የሚቻለው ፤ መሥዋዕት  ከፍሎ  በማስመስከር እንጅ፤  ማር በተቀባ አታላይ ፕሮፓጋንዳ  አይደለም ።
ፕሮፓጋንዲስቶች፤ ሞታቸውን ማዘግየት ይችሉ እንደሆነ እንጅ፤ ማስቀረት ስማይሆንላቸው፤ እየሞቱ ይኖራሉ እንጅ፤ ሀገርንና ሕዝብን ከሞት ሊያድኑ አይችሉም። አጥፍቶ መጥፋት ደግሞ፤ የቅርብ ጊዜ የሀገሪቱ መሪዎች አሳፋሪ ታሪክ እየሆነ አልፏል ። " ውሻ ሊበላ ያልቻለውን  ይቀብራል ። " እንደሚባለው ፤ የኢትዮጵያ መሪዎች፤ ያላግባብ ያግበሰበሱትን ሥልጣን መሸክም እየተሳናቸው፤ ከነሥልጣናቸው ተቀብረው ይቀራሉ።  ፊውዳሎችና  ፋሽስቶች፤  ካግበሰበሱት ሥልጣናቸው ጋር ወደ ማይቀርላቸው  ከርሰ-መቃብር መውረዳቸውን  መገንዘብ፤ ለወደፊቱ ይጠቅማል። ወያኔዎቹም የፊተኞቹን ፈለግ እየተከተሉ ይጠፏታል።  ከሕዝብ አመፅ፤ ማንም ምድራዊ ኅይል ሊያድናቸው ከቶ አይችልም።
  የኢትዮጵያ  ሕዝብ  በባኅሉ ፤ መንግሥት የሚባለውን ተቋም ማክበሩ፤ በታሪክ የቆየ  ዕምነቱ ነበር ።  
" የሀገር ያለህ ! የመንግሥት ያለህ ፤
  በህግ አምላክ ! በመንግሥት አምላክ ! "
እያለ፤ እርስ በእርሱ እየተዳኘ፤ እየተስተዳደረ የኖረ ሕዝብ  ነበር።  ዳኝነት፤ ፍትኅ-ርትዕ ፤ የኅሊና ፍርድ፤ ሚዛናዊ መስተዳደር፤ የራሱ የግሉ ባኅሉና ታሪኩ ነበር። ይህ ደግሞ፤ ከጥንት-ከጧቱ ሲወርድ-ሲዋረድ የመጣ እንጅ፤ ዘመን አመጣሽ ፖለቲከኞችና የሥልጣን- ጥመኞች የሚያቀነቅኑት ረጋ-ሠርሽ፤  እንደ ዕንግዳ ደራሽ ፤  አይደለም።  
ሁሉ ጊዜ በታዛ ስር የበቀለ ሀረግ ሬሳ፤  ራሱን ችሎ ቆሞ አያውቅም። በራሱ ያልቆመ ደግሞ፤ ለሌላው ይጠቅማል ተብሎ አይታሰብም። ወያኔ የቆመው በምራባዉያኑ ድጋፍ ነው። የድጋፉ መሠረት ደግሞ፤ የጌታና ሎሌ ግንኙነት ነው። ይህን በውጭ ኃይል የሚደገፈውን አገዛዝ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕጋዊ  ዕውቅና አልሰጠውም ። በህግ ያለቆመን ሥርዓትና አጋዛዝ በኃይል ማስወገድ ደግሞ አግባብ ብቻ ሳይሆን፤የሞራል ህግም ይደግፈዋል። " ጅብ ከሚበላህ ፤ ጅብ በልተህ ተቀድስ  "  ስለሆነ፤ ወያኔ ሀገሪቱን  አጥፍቶ ከመጥፋቱ በፊት አስቀድሞ እርሱን ማጥፋት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪካዊ ተልዕኮው ከሆነ ቆይቷል ። አጥፊን መቅጣት፤ በመንፈሳዊና ዓለማዊ ህግ የተደገፈ ነው።  የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ የሞራል  ልዕልና ስለአለው፤ ሞራለ-ቢሶችን ለማስወገድ ግዴታ አለበት ተብሎ ይጠበቃል  ።
 መንግሥትና  ሕዝብ ፤ ድንበራቸውን ተካልለው፤ ሚዛናቸውን ጠብቀው፤ አቅማቸውን አመዛዝነው ፤  ባኅሪያቸውን አጣጥመው፤ ሚናቸውን አውቀው፤ ግዴታቸውንና ኃላፊነታቸውን ተገንዝበው  እስካልተገኙ ድረስ፤ በሠላም ለመኖር አይችሉም።  በጋራ ስምምነት ላይ የተመሰረተ አብሮነትን አክብረው መኖር ካልቻሉ፤ በአንዲት ሀገር መቆየት አይሆንላቸውም።  እዚያ ደረጃ ከደረሱ፤ በአጥፊና-ጠፊ  ጎራ  ተሰልፈው ፤  አንዱ  የሌላውን  መውደም  ለማየት  ይፈልጋል። " ዝሆኖች ሲፋተጉ፤ ሳሩ  ይደቅቃል  " ነውና፤  መንግሥትና ሕዝብ ሲራኩቱ፤ ሀገር ትጎዳለች ።  ይህ ደግሞ ለማንም  አይበጅም። ያ ስለተባለ ግን፤ ሀገርና ሕዝብ ዘለዓለማዊ መሆናቸው ዕርግጥ ነውና፤ እነርሱ እየኖሩ፤ ስምምነቱን ያበለሸው  መንግሥት መጥፋቱ አይቀሬ ነው ። ሀገርና ሕዝብ ምን ጊዜም ቢሆን አይጠፉም።
 ከዚህም በላይ፤ ኃላፊነት  የሚሰማቸውና አርቆ አስተዋይ የሆኑ ዜጎች ይህንን እድል ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው አይመኙም።  በትግል የተሰማሩ ሀገር ወዳድ  ኃይሎችም ቢሆኑ፤ ትግላቸው ፤ ትዕግስት አስጨራሽ-  ተስፋ አስቆራጭ፤  ሊሆን የሚችል መሆኑን ቢገነዘቡትም፤ ከአድማስ ባሻገር እየተመለከቱ፤ ከሸለቆው መጨረሻ ብርሃን እንዳለ ያምናሉ። ብርኅታዊነትን ሰንቀው ይጓዛሉ። የድል ተስፋን አንግበው ይታገላሉ። የመጨረሻው አቸናፊዎች እንደሚሆኑም ያምናሉ። ኢትዮጵያ ሀገራቸው፤ የማንም ከሃዲ መጫወቻ ሆና አትቀርም በማለት በዕልኽ መታገላቸውን ይቀጥሉበታል ። 
እነርሱ ያላመኑበትን ለመቀበል እንደማይፈቅዱ ሁሉ፤  ሌላውም ሳያምንበት እንዲቀበል አይሹም፡፤ አያስገድዱም።  አይችሉምም።  ህይወት፤ ለማንም  ሙሉ በሙሉ የሰመረች ሆና አታውቅም ።  በየጊዜ መራራ ገፅታዋ ይከሰታል  ። የሕይወት መራራን፤ እየጎመዘዘም ቢሆን እየተጎነጩ መታገል የመጨረሻውን ድል ለመጎናፀፍ ያስችላል።  
ከሚገባው በላይ የጠነከረ  ዓላማ ፤ ምናልባት ወደ ጭካኔ እንዳያመራ ጥንቃቄ የሚያደርጉ፤ ብፁዓን ናቸው ባይባሉም ፤ ከአርቆ አስተዋዮች ደረጃ  ይመደባሉ። አክራሪ ብሄረተኝነትን   የሚያራምዱ ሁሉ  አወቁትም አላወቁትም ፤ ወደ ፋሽስት በኅርይ እንደሚለወጡ  በጊዜው  ሊገነዘቡት  ይገባቸዋል ። ይህንን ካልተገነዘቡ፤ አገር አጥፍተው እነርሱም ይጠፋሉ ። ይህንንም ከሙሶሊኒ  ፋሽዝም ና  ከሂትለር   ናሲዝም  ታሪክ ቢቀስሙ ይሻላቸዋል ። 
የዕይታ ልዩነት፤ የአስተሳስብ ልዩነት ሊያስከትል ስለሚችል ፤ ልዩነትን እያሰፉ ከመሄድ ይልቅ፤   እያጠበቡ ተቻችሎ መኖሩ ይመረጣል። ይኽች የብዙ ብሄር -ብሄር ስብ መኖሪያ የሆነች ሀገር፤ የሁሉም የጋራ እንድትሆን ከተፈለገ፤ ተቻችሎ ከመኖር የተሻለ ምርጫ አይኖርም። የእኛም ምርጫ ይኽው ነው፡፡  
በደልንና ጥፋትን፤ በአርምሞ መመልከት፤  ለጥፋቱ ተባባሪ እንደመሆን ስለምንቆጥረው  በሀገርና በሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን  በደል እየተከታተልን  ለሕዝብ ማሳወቁን እንቀጥልበታለን ።  
ጉንዳኑ ሳይገባ አመድ እንዲነሰንስበት  ለሁሉም ጥሪ እናስተላልፋለን  ! 
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኖራለች !

No comments:

Post a Comment