Tuesday, May 24, 2016

የቅኝ ገዢዎች ቀን (ቢንያም ሙሉጌታ ከኖርዌ )


በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አገዛዝ ቀኔ የሚለውን ግንቦት 20 ሊያከብር ከካድሬዎች ጋር ቀና ደፋ እያለ ነው። ለአንድ ብሄር የቆመ እንደሆነ ከጅምሩ ይፋ ያደረገው ወያኔ ለ25 ዓመታት አንድ አይነት አቁዋም በመውሰድ በቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ ያለው መሆኑን በይፋ እያሳየ ይገኛል። ይህንን እኩይ ተግባር ስልጣን ከያዘ በኃላ እስከ ዛሬዋ ቀን በስራ ላይ በማዋል ላይ ነው። ታዲያ ይህንንም የወያኔ ታላቅ ሴራ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን የተደበቀ አይደለም።

የተወሰኑ የሕወሀት(ወያኔ) ቡድን አመራሮች ስልጣን ሙሉ በሙሉ ይዘው የሚያሽከረክሩት ከአንድ ጎሳ የመጡ ግለሰቦች የዘረኝነትንት መርዝ ነዝተው ሀገሪቱን በማበጣበጥ የስልጣን ጥማቸውን እየተወጡ ይገኛል። ይህንንና እርኩስ ራዕያቸውን ስራ ላይ ማዋል የጀመሩበትን ግንቦት 20 ሊያከብር በመሯሯጥ ላይ ናቸው።
በዘር መርህና በመከፋፈል የሚመራው ወያኔ ዛሬ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያን የመበታተንና የመከፋፈል ጉዞ የጀመረበትን ቀን ሊያከብር በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የህዝብ ገንዘብ መድቦ አሸሼ ገዳሜ ሊል ዝግጁን አጠናቁዋል። በሀገራችን ውስጥ የብሄረሰቦች እኩልነት ሳይኖር ሰላም ሳይሰፍን በሀገሪቷ በተለያዩ ከልሎች ውስጥ የተለያዩ አስጨናቂ ሁኔታዎችና ነውጦች ነግሰው ባለበት ሰአት እነርሱ ሆዳቸውን ሊሞሉ ሻምፓኛቸውን ሊራጩ ከጫፍ ደርሰዋል።
ወያኔ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ጋዜጠኞችን፣ የተቃዋሚ አባላትን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ጠንከር ያለ ሂስና ትችት የሚሰነዝሩበትን ዜጎች በማሰርና ደብዛቸውን በማጥፋት እንዲሁ በማሸማቀቅና የፀረ ሽብር ህግ እያለ ዜጎችን እየከሰሰ ሲሻው የሀገርን ሰላም በማደፍረስ እያለ ሲያሻው ህገመንግስት ስርአቱን ለመናድ እያለ ሲያሰፈልገው ዘር በማጥፋት ወዘተ የሚሉ ወንጀልና ክሶችን በማቅረብ አላማቸው ግልፅ የሆነና ዜጎችን ማጥቂያ አድርጎ የሚጠቀምበትን ጠላቶቼ ናቸው ብሎ በሚያስባቸው ኢትዮጵያውያን ላይ መከራን የሚያዘንብበትን ስልት ተጠቅሞ እየገዛ ይገኛል።
በአንድ ጎሳ የበላይነት የተገነባው ሰራዊት የግፍ ቋት የሞላባቸው የሀገራችን ህዝቦች በጠንካራና በአንድነት መንፈስ ተደራጅተው ለሚያቀርቡት ጥያቄ ምላሹ ጥይት ነው። የወያኔንም ስርዓት በተቻለው መንገድ ሁሉ እየታገለ ብዙ የደም ግብር ከፍሏል ኢትዮጵያዊ ዜጋ።
አሁን ላይ ግንቦት 20 ሊከበር ባለበት ወቅት ነፃነት፣ ዲሞክራሲ፣ ፍትህ፣ እኩልነት በሀገር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ደብዛቸው ጠፍቱዋል። የኑሮ ውድነት ጣራ ነክቶ ስራ አጥነት ተባብሶ ዜጎች ተስፋ ቆርጠው በተሽከርካሪ በእግርም የሀገሪቱን ድንበሮች አቁዋርጠው የሚሰደዱ በየመንገዱ የሚሞቱ ዛሬም ቁጥራቸው በአሳሳቢ ደረጃ ጨምሩዋል። ግንቦት 20 እኮ ለማን?
ወያኔ በኦሮሚያና በአከባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችን አፈናቅሎ መሬት ዘረፋ ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ማድረጉ ግልፅ ነው። ህዝብን ጠርቶ ሳያወያይ የተቀናጀ የጋሪ ማስተር ፕላን በሚል ለአርሶ አደር ምንም ጥቅም በማያስገኝበት ሁኔታ በግዳጅ ወደ ተግባር በመግባት አርሶ አደርን ከነቤተሰብ ለችግር ዳርጎታል ታዲያ ይህንንም የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን በመቃወም በሁሉ የኦሮሚያ ክልል የሚገኝ ወጣቶችና ተማሪዎች ባደረጉት ተቃውሞ ውድ ሒወታቸውን በወያኔ ታጣቂዎች ተቀጥፈዋል።
በሌላ በኩል ባለፉት አመታት የሙስሊሙ ማህበረሰብ ሰላማዊ መንገድን በመጠቀም ድምፃቸውን ለማሰማት ባደረጉት ሙከራ እስክ አሁንም ድረስ እያሰማ ያለውን ድምፅ ወያኔ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል። ታድያ የሙስሊም ማህበረሰብ የሰላማዊ ስልቶችን ተጠቅሞ ድምፁን ለማሰማትና የሚፈፀሙትን ህገወጥ ድርጊቶች እንዲቆም ለማስደረግ ሲጥር ቆይቷዋል።
በቀላሉ ከአንዱ ወደ ሌላው የሚዛመትና ለወያኔም ጠንካራ መልክቶችን የሚያስተላለፍ የትግል ስልቶችን ተጠቅመዋል ሆኖም ወያኔ መስሚያዬ ድፍን ነው በማለት የብዙሃኑንን ጥያቄ ንቆ ይልቁንም የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ ሌላ ስም በመስጠት ማንም በማያየውና በማይሰማው የቴሌቭዥን ጣቢያው ቅጥፈታዊ ሃረካቱን አስተላለፉዋል። ለኢትዮጵያውያን የሙስሊም ማህበረሰብስ የሚከበረው የወያኔ የግፍ በዓል ግንቦት 20 ምኑ ነው?
ወያኔ ወልቃይት ጠገዴ በትግራይ ክልል ስር በግድ እንዲተዳደሩ ማድረጉ በነዋሪዎችም እምቢተኛነት መቀጠሉ የሚታወቅ ነው። የገዢው ቡድን ይህንን አቋሙን አፅንቶ ቀጥሏል በነዋሪዎችም ሲነሳ የቆየው ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ እንዳለ አለ። በአከባቢው ዛሬም ድረስ ውጥረት ነግሷል። የወያኔ የፀጥታ ሀይሎች በስፋት ሰፍረው ይገኛሉ በዚህ የማንነት ጥያቄ ብዙዎች ለእስር ተዳርገዋል ብዙዎች ተፈናቅለዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ውስጥ ወያኔ እረጅም እጁን በማስገባት ባለፉት ጊዜያት በታሪካዊ ገዳማት ላይ በልማት ስም በገዳማውያን አባቶች ላይ እየፈፀመ ያለው እንግልትና መፈናቀል በቅድሳን መናኸሪያነታቸው በመናንያን መሸሸጊያነታቸው የሚታወቅና ከ1600 ዓመታት በላይ እድሜ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ክብራቸውና ሞገሳቸው ተጠብቆ የቆዩ እንደ ዋልድባ ገዳም በልማት ስም ወያኔ ክብራቸውን ደፍሩዋል።ታሪክነታቸውን አስረስቶ ለስኳር ፋብሪካነት በሚል ቦታውን እያረሰ ገዳማዊያኑ እንዲሰደዱ አድርጉዋል። ወያኔ የገዳማዊያን መብት ማክበርና ማስከበር ቅርስና ታሪክን በክብር መጠበቅ ሲገባው ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ነው የወያኔ ነገር።
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ግድ የማይለው ስርአቱ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት ክምችት ያላቸውን ድንበር አካባቢ የሚገኙ መሬቶችን ቆርሶ ለጎረቤት ሀገር ሱዳን አሳልፎ ሰጧል። ወያኔ የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም የሚፃረር የለም መሬት ነጠቃንና ወረራን ላለፉት 25 ዓመታት በማን አለብኝነት ሲዘርፍ ሲያዘርፍ ቆይቱዋል።
ወያኔ ስለጣን ከያዘ ጀምሮ ህዝባችንና ሀገራችን ቃላት የማይገልፀውን መከራ አስተናግደዋል። ግንቦት 20 የሚያስታውሰን የመከራ ዘመናችን ምን ያህል እንደተጏዘ ነው። ፀረ ኢትዮጵያውያን ስርዓት ከስሩ ነቅለን ጥለን ሉዓላዊነቷና የግዛቷ አንድነት የተከበረባት እኩልነት፣ የህግ የበላይነትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት የበለፀገች ሀገር መስርተን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ በአንድነት እንነሳ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

Monday, May 16, 2016

በቅድሚያ የላብ አደሩ መብት ይከበር ( ቢንያም ሙሉጌታ ከኖርዌ)በቅድሚያ ላብ አደሩ መብት ይከበር ቢንያም ሙሉጌታ ከኖርዌ
በሀገር ውስጥ ሜዳ ላይ ያለው ስርዓት የሲቪክ ማህበረሰቡን አዳክሞ አገሪቱን ለመበዝበዝ የራሱን ዘማቾች አዝምቶ ያሻውን እያሰረ ያሻውን እየፈታ ይገኛል። ዛሬ ዛሬ በሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ ለዜጎች ሰርቶ ማደር በጣም ብዙ መስዋዕት የሚያስከፍልም ፈታኝ ጉዳይ መሆኑ ግልፅ ነው። ከእስካሁኑ በባሰ ሁኔታ ወያኔ አሁን ላይ በሀገሪቱ የሚገኝ የስራ
ዘርፎችን ከሁሉም ዜጋ ነጥቆ የግሉ አድርጎታል። ከዚህም የሚብስ ዜጎችን የሚያዋርድ ተግባር የለም ቢባል አልተጋነነም።
አባቶቻችን ኢትዮጵያን ለባዕድ አንሰጥም በማለት በታላቅ ተጋድሎ መስዋዕት በመሆን ያቆይዋትን አገራችንን፤በውጭ ሀይል የሚደጎመው ሀገር በቀሉ ጠላት ትውልድ አልባ፣የተዛባ ታሪክ ባለቤት ሊያደርገን ቆርጦ ተነስቷል። ወያኔ የሱ ቅጥረኛ የሆኑትን ካድሬዎቹን እንዴት ሀገር እንደሚዘረፍ አስተምሮአቸዋል። ይህንንም አይን ያወጣ ውንብድና የተቃወሙ ዜጎች በመሪር ስቃይ ውስጥ እያለፉ አንዳንዶቹም ለሞት ሌሎቹም ደግሞ ደብዛቸው እንዲጠፋ እና ስየል እንዲቀበሉ ሆነዋል።
በሀገራችን ውስጥ ያለው ላብ አደር ጉልበት እያለው እና የእውቀት ባለቤት ሆኖ ሳለ በሀገር ላይ ምንም ነገር መስራትም ሆነ መንቀሳቀስ የተሳነው እንዲሆን መብቱ ተግፏል። ከዚህ የተነሳ በጠቅላላ በሀገሪቱ ላይ የሚገኘው ላብ አደር በተስፋ መቁረጥ ተውጦ ይታያል። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የስርዓቱ አካል በምድሪቷ ላይ ከራሱ ወገን እና ብሔር በስተቀር ሌላው ዜጋ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጨምሮ የወደፊት ህልም እና ራዕይ እንዳይታየው በቅኝ ግዢ ባርነት ውስጥ ጥሎታል።
የወያኔ ውሽት እና ቅጥፈት በህዝብ ዘንድ ጥርስ ውስጥ አስገብቶት ባለበት በዚህ ወቅት በተጨማሪም ላብ አደር የሆነው ወገን ሰርቶ ራሱን እና ቤተሰቡን ማኖር ባቃተው ሰዐት አደግን ተመነደግን እያሉ የውሸት ፕሮፖጋንዳቸውን ቀጥለውበታል ። ይህም ለምንወዳት ሀገራችን እና ለምንወድው ህዝባችን አደጋ ሆኖ 25 አመታትን አስቆጠረ።
በቀበሌዎች እና በገበሬ ማህበራት እንዲሁም በመሳሰሉት ተቋማት ለብ ለብ በሆነ ስልጠና ወደ ስራ የሚሰማሩ ጥቂት የወያኔ ካድሬዎች ካልሆኑ በስተቀር በሀገሪቱ ላይ ተምረው ስራ ያላገኙ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ ማየት እና ማግኘት አዲስ ነገር አይደለም።
እንደ ባዕድ ወራሪ ኢትዩጵያውያንን በጥይት የሚፈጀው ወያኔ የተማረው ህዝብ ባልተማረበት የጉልበት ስራ እንዲሰማራ እና ከትላልቅ የትምህርት ተቋም ምረቃ በኋላ ሴቶች በዓረብ ሀገር የሰው ቤት ሰራተኛ ግፍ ተቀባይ እንዲሆኑ እና በተለያየ እድሜ ክልል ያሉ ዜጎችም በበረሀ ቀርተው የባህር ሲሳይ ቢሆኑ ምንም ሰብዓዊነት ይሰማዋል ብሎ ማንም አይጠብቅ። ይህ እንዲሁ ሳለ ላብ አደሩ በሀገሩ ላይ የመስራት እና የድካሙ ፍሬ በጨቋኙ አገዛዝ ተረግጦበት የላብ አደሮች (የሰራተኞች) ቀን ብሎ በማክበር የህዝብ ላይ የሰለጠነበትን ወንጀል ወያኔ ምን ያህል የሌባ አይነ ደረቅ መሆኑን ያስመሰከረበት ሂደት ነው።
ትክክለኛ የሆነ የስራ እና የሙያ ክፍፍል ሳይኖር በየአመቱ የሰራተኞች ቀን እየተባለ የላብ አደሩን መብት የሚያከብር ስርዓት ሳይኖር የማስመሰያ በዓል ማክበሩ ዜጋው የሚሰማውን የበቀል ስሜት ይልቁንም እንዲጨምር ከማድረጉ በላይ በሁሉም አቅጣጫ የተፋፋመውን የተቃውሞ ማዕበል ያቀጣጥለዋል። የላብ አደሩ መብት ተጨፍልቆ የላብ አደሩን ቀን ማክበር ምን የሚሉት በህዝብ ላይ ማፌዝ ነው?
page1image21368

የሰለጠነ አመለካከት በሚራመድበት አደጉ በሚባሉት ሀገራት ላይ የላብ አደሩ መብት ተከብሮ ባለበት ሁኔታ በየአመቱ በዐሉን ከሰራተኛው ጋር መዘከሩ አግባብ ነው። በአንፃሩ ደግሞ ወደ ኢትዩጵያችን ተመልሰን የምናየው እውነታ ከዚህ የሚቃረን ነው። ዜጋው እንኳን በላቡ ሰርቶ ሊያድር ቀርቶ በነፃነት ድምፁን ማሰማት እንኳን ፈፅሞ አይችልም። ሁን የተባለውን፣ስራ የተባለውን እና ክፈል የተባለውን ከመክፈል ውጪ ያለው ሌላ አማራጭ ወህኒ ነው።
ታድያ ይህ የህብረተሰብ ክፍል ዛሬ ዛሬ እንኳን በላቡ ሰርቶ ሊያድር ይቅርና በሰላም ንጽህ አየር መተንፈስ ተስኖት በላቡና በወዙ ያፈራውን እና አለኝ የሚለውን ንብረቱን ተቀምቶ እና ተፈናቅሎ ቤተሰቡን በትኖ ያ ጎበዝ ላብ አደር ዛሬ መብቱ ተረግጦበት አንገት ደፊ ተደርጓል? እውነት ለኢትዮጵያዊው የላብ አደር ቀን ምኑ ነው?
የስርአቱ መሪዎች ለግል ትርፋቸው በባርነት ወደ አረብ ሃገራት የሚቸበችቡዋቸው ዜጎች ባሉበት ስፍራ እንኳን የመግባትም ሆነ የመውጣት ነጻነት የተነፈጉ ሆነው ባሉበት በሙስና የተጠቀጠቀ ስርዓት በሰፈነበት እና የላብ አደሮችን ቀን ማክበር ምን ሊፈይድ ይጠበቃል? ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ይሏል ይህ ነው።
የመማር እድል ተነፍገው ወደ የማያውቁት አገር እና ወደ ማያወቁት ቀዪ በለጋ እድሜያቸው ተሰድደው ከአቅማቸው በላይ መከራን የሚቀበሉ ሴቶችና ህጻናት ቁጥር ዛሬም ላይ እጅግ ብዙ ነው። በዚህ አይነት መከራ ውስጥ እንዳሉ ከአቅም በላይ በሆነ የሰራ ጫና ህይወታቸውን የሚገብሩ ህጻናት ብዙ ናቸው ታድያ በኢትዮጵያ ውስጥ የላብ አደሮች ቀን የሚወክለው የትኛውን ላብ አደር ነው?
በኢትዮጵያ ውስጥ በላቡ ሰርቶ ከሚያድረው ይልቅ በሙስና የሚያድረው በየቀኑ እየበዛ እና እየጨመረ መጥቷል። ሙስና የሀገሪቱ የስራ ባህል እስከ መሆን ድረስ ተንሰራፍቶ ባለበት በየዓመቱ የአይቅርብኝ ማስመሰያ የላብ አደሮች ቀን ወያኔ ሊያከብር መሰለፉን ልንቃወመው ይገባል። ይልቁንም መቅደም የሚገባው የሰራተኛው መብት እና አድሎአዊነት የሌለው የስራ ክፍፍል በሀገሪቷ ላይ ማስከበርን ነው። ቢሆንም ወያኔ እያለ ይህ ይሆናል ብሎ መጠበቅ ላም አለኝበሰማይ... ይሆናል።
በእውቀቱ እና በችሎታው ተሰማርቶ በላቡማደርተስኖትተመጽዋችየሆነውንዜጋ፤እንዲሁም በሰው ሃገር በአሰቃቂ ሁኔታ አማራጭ ጠፍቶአቸው በግዞት ህይወታቸውን የሚገፉ ሴቶች እና ህጻናቶችን ከእንዲህ አይነት ብሄራዊ ውርደት ዜጎቻችንን መታደግ የሚቻለው አስቀድመን ለዚህ ሁሉ መንስኤ የሆነውን አምባገነን ቡድን በሁለ ገብ ትግላችን በመፋለም ነው። ወያኔ ሲገረሰስ በእርግጥም ስርዓቱ ይፈወሳል።
ዜጎች በሃገራቸው በነጻነት ሰርተው መኖር የሚችሉባትን ትክክለኛ የሆነ የላብ አደሮች ቀን የሚከበርባትን ኢትዮጵያን መገንባት የሁላችንም ሃላፊነት ነው ታድያ ለዚሁም ኢትዮጵያ ሃገራችን እንደ ሃገር እንድትቀጥል እና ወደ ተባባሰ ችግር ውስጥ እንዳትገባ ያለውን ስርዓት ከስሩ ነቅሎ ለመጣል በትግል ተሞክሮዋቸው ፋና ወጊ ከሆኑ የኢትዮጵያ አንድነት እና ሉዋላዊነት እንቅልፍ ከሚነሳቸው የበሰለ አመራር አምድ ካላቸው፤ከጅማሬያቸው የህዝብ አለኝታ ከሆኑ እስከዛሬዋ ቀን ድረስ በጽናት ለቃላቸው ታማኝ ከሆነ ትላንትም ዛሬም አስከፊ እመቃና አፈና ቢካሄድባቸውም በቁርጠኛነት የኢትዮጵያ ሃይልና ተገን ሆነው እየታገሉ ያሉ ቃል ኪዳናችውን የጠበቁ የፖለቲካ ፓርቲ ጎን በመሰለፍ አገራችንን እናድን። በእርግጥም የሚቀጥለውን ዓመት የላብ አደሮች በዓል ስናከብር፤ በተባበረ ክንዳችን የወያኔን ስርዓት ገርስሰን ያለ ገደብ መብቱ የተከበረለት ላብ አደር ለተሻለ ምርታማነት ነፃ እስከሚሆን ድረስ በሁለገብ ትግላችን እንታገላለን።
እናቸንፋለን!!! 

Tuesday, May 10, 2016

የእይታ ብልሽት... http://www.finote.org


የእይታ ብልሽት

የቫይታሚን A ጉድለት የጥቁር ዓይን ሽፋንን አድርቆ የደበዘዘ እይታ ወይም ትናንሽ ነጠብጣቦችን በማሳየት ይገለጣል። ይህ ከውልደት ጀምሮ በቫይታሚን ዕጥረት የተጠቃ ህፃን በጊዜው የህክምና ዕርዳታ ማግኘት ካልቻለ ዓይነ ስውር እስከመሆን ይደርሳል። ይህ አይነቱ በሽታ በጨለማ ጊዜ የማየት ችሎታን ይቀንሳል። በዚህ ጊዜ ዳፍንታም የመሆን ዕድል ይገጥመዋል። ዳፍንታም ማለት በቅጡ ማየት የተሳነው ማለት ነው። ታዲያ! ይህንን ሀቅ ስንመነዝረው ስንቱ ኢትዮጵያዊ ነው። በተገቢው መልክ ቫይታሚኖችን እየተመገበ ያደገው / የሚያድገው? የዚህ በሽታ ችግር በኑሮ ሁኔታው ላይ የሚጎሳቆለው ክፍል በገጠርና በከተማ አኗኗር መሃል መጠነኛ የሆነ ልዩነት ቢኖርም አጠቃላዩ ህይወት ሁሉንም የሚመለከት ይሆናል።
ሁኔታዎችን ስናይ ይህ የዳፍንት በሽታ ስር የሰደደ ለመሆኑ በአንዳንድ ድርጊቶች ላይ ይስተዋላል። ታሪክን አንሸዋሮ መመልከት ከዚህ አይነቱ ዕድገት ሁኔታ የተገኘ ይመስላል። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ነገስታት አንድ ወጥ ጎሳን የሚወክሉ ናቸው ተብሎ በጎጥ አቀንቃኞች ሲጠቀስ በተለይ የዐፄ ምኒልክ ዘመንና የዐፄ ሀይለስላሴ ዘመን በአማሮች የተያዘ ነበር ተብሎ ነው። ሀቁ ግን ራሳቸው ነገስታቱም ሆኑ የስልጣን ተካፋዮቻቸው ዛሬ ጎጠኞች ከሚጠይቁት የተለዩ ነበሩ። የዐፄ ምኒልክና ከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸውን ታሪክ ለጊዜው እንኳ ብናልፈው፣ ቅርብ ከሆነው የዐፄ ሀይለስላሴ
ዘመን ሹመኞች መሀል ብንመለከት አማራው የትኛው ነበር። ለነገሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሁሉም ጎሳ አባል ነው። ይህ የዘር ትርጓሜ የመጣው በከፋፋዮችና የውጭ ጠላቶች ወኪል በሆነው ወያኔና መሰሎቹ ነው። ያም እንኳ ቢሆን በዳፍንት አመለካከት የተስተዋለ እንጂ ብሩህ የሆነ እይታ ያስገኘው እንዳልሆነ ግልፅ ነው።
- ብላታ ዴሬሳ አመንቴ የጠቅላይ ሚኒስትር ምክትል ሚኒስቴር
§  ሜጀር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ የክብር ዘበኛ ዋና አዛዥ
§  ክቡር አቶ ይልማ ዴሬሳ በዩናይትድ ስቴትስ ባለሙሉስልጣንና የገንዘብ ሚኒስቴር ወዘተ.
§  ክቡር አቶ አማኑኤል አብርሃም የፖስታና ትራንስፖርት ሚኒስቴር ወዘተ.
§  ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ የኤሉባቡርና የጎምጎፋ ገዥ
§  ደጃዝማች ፍቅረስላሴ ሀብተማርያም የወለጋ ጠቅላይ ገዥ
§  ደጃዝማች ካሳ ወልደማርያም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ወዘተ.
§  ደጃዝማች ሽፈራው ባልቻ የጅጅጋና የኦጋዴን አበጋዝና የወለጋ አውራጃ ገዥ
§  ሜጀር ጄኔራል አበበ ገመዳ የሁለተኛው ክፍለጦር አዛዥ
§  የተከበሩ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የገንዘብ ሚኒስትር ምክትል ሚኒስቴር ወዘተ.
§  ጀኔራል ታደሰ ብሩ የፖሊስ ሰራዊት ፈጥኖ ደራሽ አዛዥ
በተለይ ደጃዝማች ከበደ ብዙነሽና ሊጋባ በቀለ ሆርዶፋ ስመ ጥር የሆኑ አርበኞች ሲሆኑ የተሰጣቸው ስፍራ ግን መንግስትን የሚያስተች ነው። አርበኛን ወደሁዋላ ባንዳን ወደፊት
ያደርጋል ተብሎ በህዝብ የሚተቸው መንግስት ደጃዝማችን የክብረ መንግስትና የናዝሬት አውራጃ ገዥ ብላታን ደግሞ የንጉሰ ነገስቱ ዋና ሊጋባ በማድረግ ሾመዋቸዋል።
ትውልድ! ይህን መሰሉን ሀቅ አጋልጦ፣ በወዳጅነትና በቤተሰብ እጅ ወድቆ ሊገዛ የማይገባው ህዝብ ነው ብሎ ቆርጦ የታገለ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የዳበረ ታሪክ ያለውና ዘመኑም በፈቀደው መጠን የተማረ ትውልድ ያፈራ ነው። ይህ አይነቱ ፈር የለቀቀ አድልዎና የህዝብን መብትና ነፃነት የነጠቀ አስተዳደር በህዝባዊ መንግስት መተካትና መስተካከል አለበት ብሎ ነው ትውልድ የታገለው። የጎጥን ፖለቲካ አያቀነቅንም። በኢህአፓ ውስጥ ተሰልፎ የታገለና ህይወቱን ለትግሉ የሰጠ የአማርኛ ተናጋሪው ወጣት በርካታ ነው። ለጎጥ ብሎ ሳይሆን ለዕውነት ሲል። ለቆመለትና ለሚገኝበት የመደብ ክፍል ሲል። ታግሎ የወደቀው፣ በእስር በስቃይ የተንገላታው ኢትዮጵያን የሚያፈቅረው ወገን ጠላት ተብሎ ሊጠቀስ አይገባም። የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የኢትዮጵያ ወጣት የወገኑን በደል የሚያውቅ፣ በጋራ ሆኖ ስለመብቱ የጠየቀ/የሚጠይቅ እንጂ! ብዙና ጥቂት የተማረ ሀይል ያለው ህዝብ፣ የተማረና ያልተማረ ወጣት ያለው ህዝብ፣ ይህንንና ያንን ቋንቋ የሚናገር ህዝብ፣ እያለ አይሸነሽንም። ህዝቦች የሚል ቃል የፈጠረው ወያኔ፣ ህዝቦቹን ከሚፈልግበት ይፈልግ እንጂ! የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ህዝብ ነው። ወጣቱ እንደ ወያኔ አይነቶቹን ሀገር አጥፊ ቡድኖች በፊትም በኢህአፓ ተደራጅቶ ታግሏቸዋል። አሁንም ከዚህ የጋራ ጥያቄ ተነስቶ ጎጠኞችን ይታገላቸዋል። ጎጠኞች እንደሚያወሩት ኢትዮጵያ የተከፋፈለች አይደለችም። የኢትዮጵያ ወጣት ይህ የጎጠኞች አላማ የትም እንደማያደርስ አውቆታል። ከዚህ በሁዋላ ወጣቱን ማጭበርበር አይቻልም።
ይህን የመሰለውን እውነታ የማይመለከቱ ሰዎች የዳፍንት ችግር አለባቸው ቢባል ሀሰት አይደለም። ምክንያቱም የጎጠኞች ፖለቲካ የተዋቀረው በተንሸዋረረ የፖለቲካ አመለካከት ላይ በመሆኑ ነው። አማራው የተለየ ስልጣን ኖሮት አያውቅም። እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የመደቡ ተጠቃሚ ሆነ ሊሆን ይችላል። እንጂ! ለአማራነቱ ዋቢ ቆሞ አያውቅም። የጎጠኞቹ አለቃ (አባይ ስብሀት) አማራና ኦርቶዶክስ አከርካሪያቸው ተመቷል ሲል፣ ወጣቱ ኢትዮጵያዊነቱን ከማንፀባረቅ ውጭ ሌላ ወንጀል እንደሌለበት ለማየት ዳፍንት አስቸግሮት ሊሆን ይችላል። አለበለዚያ መንግስታት የራሳቸውን መደብ አባል እንጂ! ደሃውን አማራ፣ ደሃውን ኦሮሞ፣ ደሃውን ጉራጌ፣ ደሃውን ወላይታ፣ አፋርን፣ ሲዳማን፣ ከምባታን፣ ሀድያን፣ አኝዋክን፣ ሙርሲን ወክለው አያውቁም። የወያኔ አይነቱ የዘር ፖለቲካና የጠላትነት አመለካከት ጥያቄ ቀደም ሲል ባነሳነው የቫይታሚን A ዕጥረት ከሚፈጠረው ዳፍንት የተነሳ ሊሆን ስለሚችል ትክክለኛውን እይታ ለማየት ተቸግሮ ዓይኑ ከታወረ ምርኩዙን ተቀብሎ መምራት የህሊና ግዴታ ይሆናል።

አንድነት የኢትዮጵያ ህዝብ መገለጫ ነው።
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!