Tuesday, May 24, 2016

የቅኝ ገዢዎች ቀን (ቢንያም ሙሉጌታ ከኖርዌ )


በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አገዛዝ ቀኔ የሚለውን ግንቦት 20 ሊያከብር ከካድሬዎች ጋር ቀና ደፋ እያለ ነው። ለአንድ ብሄር የቆመ እንደሆነ ከጅምሩ ይፋ ያደረገው ወያኔ ለ25 ዓመታት አንድ አይነት አቁዋም በመውሰድ በቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ ያለው መሆኑን በይፋ እያሳየ ይገኛል። ይህንን እኩይ ተግባር ስልጣን ከያዘ በኃላ እስከ ዛሬዋ ቀን በስራ ላይ በማዋል ላይ ነው። ታዲያ ይህንንም የወያኔ ታላቅ ሴራ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን የተደበቀ አይደለም።

የተወሰኑ የሕወሀት(ወያኔ) ቡድን አመራሮች ስልጣን ሙሉ በሙሉ ይዘው የሚያሽከረክሩት ከአንድ ጎሳ የመጡ ግለሰቦች የዘረኝነትንት መርዝ ነዝተው ሀገሪቱን በማበጣበጥ የስልጣን ጥማቸውን እየተወጡ ይገኛል። ይህንንና እርኩስ ራዕያቸውን ስራ ላይ ማዋል የጀመሩበትን ግንቦት 20 ሊያከብር በመሯሯጥ ላይ ናቸው።
በዘር መርህና በመከፋፈል የሚመራው ወያኔ ዛሬ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያን የመበታተንና የመከፋፈል ጉዞ የጀመረበትን ቀን ሊያከብር በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የህዝብ ገንዘብ መድቦ አሸሼ ገዳሜ ሊል ዝግጁን አጠናቁዋል። በሀገራችን ውስጥ የብሄረሰቦች እኩልነት ሳይኖር ሰላም ሳይሰፍን በሀገሪቷ በተለያዩ ከልሎች ውስጥ የተለያዩ አስጨናቂ ሁኔታዎችና ነውጦች ነግሰው ባለበት ሰአት እነርሱ ሆዳቸውን ሊሞሉ ሻምፓኛቸውን ሊራጩ ከጫፍ ደርሰዋል።
ወያኔ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ጋዜጠኞችን፣ የተቃዋሚ አባላትን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ጠንከር ያለ ሂስና ትችት የሚሰነዝሩበትን ዜጎች በማሰርና ደብዛቸውን በማጥፋት እንዲሁ በማሸማቀቅና የፀረ ሽብር ህግ እያለ ዜጎችን እየከሰሰ ሲሻው የሀገርን ሰላም በማደፍረስ እያለ ሲያሻው ህገመንግስት ስርአቱን ለመናድ እያለ ሲያሰፈልገው ዘር በማጥፋት ወዘተ የሚሉ ወንጀልና ክሶችን በማቅረብ አላማቸው ግልፅ የሆነና ዜጎችን ማጥቂያ አድርጎ የሚጠቀምበትን ጠላቶቼ ናቸው ብሎ በሚያስባቸው ኢትዮጵያውያን ላይ መከራን የሚያዘንብበትን ስልት ተጠቅሞ እየገዛ ይገኛል።
በአንድ ጎሳ የበላይነት የተገነባው ሰራዊት የግፍ ቋት የሞላባቸው የሀገራችን ህዝቦች በጠንካራና በአንድነት መንፈስ ተደራጅተው ለሚያቀርቡት ጥያቄ ምላሹ ጥይት ነው። የወያኔንም ስርዓት በተቻለው መንገድ ሁሉ እየታገለ ብዙ የደም ግብር ከፍሏል ኢትዮጵያዊ ዜጋ።
አሁን ላይ ግንቦት 20 ሊከበር ባለበት ወቅት ነፃነት፣ ዲሞክራሲ፣ ፍትህ፣ እኩልነት በሀገር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ደብዛቸው ጠፍቱዋል። የኑሮ ውድነት ጣራ ነክቶ ስራ አጥነት ተባብሶ ዜጎች ተስፋ ቆርጠው በተሽከርካሪ በእግርም የሀገሪቱን ድንበሮች አቁዋርጠው የሚሰደዱ በየመንገዱ የሚሞቱ ዛሬም ቁጥራቸው በአሳሳቢ ደረጃ ጨምሩዋል። ግንቦት 20 እኮ ለማን?
ወያኔ በኦሮሚያና በአከባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችን አፈናቅሎ መሬት ዘረፋ ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ማድረጉ ግልፅ ነው። ህዝብን ጠርቶ ሳያወያይ የተቀናጀ የጋሪ ማስተር ፕላን በሚል ለአርሶ አደር ምንም ጥቅም በማያስገኝበት ሁኔታ በግዳጅ ወደ ተግባር በመግባት አርሶ አደርን ከነቤተሰብ ለችግር ዳርጎታል ታዲያ ይህንንም የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን በመቃወም በሁሉ የኦሮሚያ ክልል የሚገኝ ወጣቶችና ተማሪዎች ባደረጉት ተቃውሞ ውድ ሒወታቸውን በወያኔ ታጣቂዎች ተቀጥፈዋል።
በሌላ በኩል ባለፉት አመታት የሙስሊሙ ማህበረሰብ ሰላማዊ መንገድን በመጠቀም ድምፃቸውን ለማሰማት ባደረጉት ሙከራ እስክ አሁንም ድረስ እያሰማ ያለውን ድምፅ ወያኔ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል። ታድያ የሙስሊም ማህበረሰብ የሰላማዊ ስልቶችን ተጠቅሞ ድምፁን ለማሰማትና የሚፈፀሙትን ህገወጥ ድርጊቶች እንዲቆም ለማስደረግ ሲጥር ቆይቷዋል።
በቀላሉ ከአንዱ ወደ ሌላው የሚዛመትና ለወያኔም ጠንካራ መልክቶችን የሚያስተላለፍ የትግል ስልቶችን ተጠቅመዋል ሆኖም ወያኔ መስሚያዬ ድፍን ነው በማለት የብዙሃኑንን ጥያቄ ንቆ ይልቁንም የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ ሌላ ስም በመስጠት ማንም በማያየውና በማይሰማው የቴሌቭዥን ጣቢያው ቅጥፈታዊ ሃረካቱን አስተላለፉዋል። ለኢትዮጵያውያን የሙስሊም ማህበረሰብስ የሚከበረው የወያኔ የግፍ በዓል ግንቦት 20 ምኑ ነው?
ወያኔ ወልቃይት ጠገዴ በትግራይ ክልል ስር በግድ እንዲተዳደሩ ማድረጉ በነዋሪዎችም እምቢተኛነት መቀጠሉ የሚታወቅ ነው። የገዢው ቡድን ይህንን አቋሙን አፅንቶ ቀጥሏል በነዋሪዎችም ሲነሳ የቆየው ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ እንዳለ አለ። በአከባቢው ዛሬም ድረስ ውጥረት ነግሷል። የወያኔ የፀጥታ ሀይሎች በስፋት ሰፍረው ይገኛሉ በዚህ የማንነት ጥያቄ ብዙዎች ለእስር ተዳርገዋል ብዙዎች ተፈናቅለዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ውስጥ ወያኔ እረጅም እጁን በማስገባት ባለፉት ጊዜያት በታሪካዊ ገዳማት ላይ በልማት ስም በገዳማውያን አባቶች ላይ እየፈፀመ ያለው እንግልትና መፈናቀል በቅድሳን መናኸሪያነታቸው በመናንያን መሸሸጊያነታቸው የሚታወቅና ከ1600 ዓመታት በላይ እድሜ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ክብራቸውና ሞገሳቸው ተጠብቆ የቆዩ እንደ ዋልድባ ገዳም በልማት ስም ወያኔ ክብራቸውን ደፍሩዋል።ታሪክነታቸውን አስረስቶ ለስኳር ፋብሪካነት በሚል ቦታውን እያረሰ ገዳማዊያኑ እንዲሰደዱ አድርጉዋል። ወያኔ የገዳማዊያን መብት ማክበርና ማስከበር ቅርስና ታሪክን በክብር መጠበቅ ሲገባው ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ነው የወያኔ ነገር።
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ግድ የማይለው ስርአቱ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት ክምችት ያላቸውን ድንበር አካባቢ የሚገኙ መሬቶችን ቆርሶ ለጎረቤት ሀገር ሱዳን አሳልፎ ሰጧል። ወያኔ የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም የሚፃረር የለም መሬት ነጠቃንና ወረራን ላለፉት 25 ዓመታት በማን አለብኝነት ሲዘርፍ ሲያዘርፍ ቆይቱዋል።
ወያኔ ስለጣን ከያዘ ጀምሮ ህዝባችንና ሀገራችን ቃላት የማይገልፀውን መከራ አስተናግደዋል። ግንቦት 20 የሚያስታውሰን የመከራ ዘመናችን ምን ያህል እንደተጏዘ ነው። ፀረ ኢትዮጵያውያን ስርዓት ከስሩ ነቅለን ጥለን ሉዓላዊነቷና የግዛቷ አንድነት የተከበረባት እኩልነት፣ የህግ የበላይነትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት የበለፀገች ሀገር መስርተን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ በአንድነት እንነሳ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

No comments:

Post a Comment