Tuesday, May 10, 2016

የእይታ ብልሽት... http://www.finote.org


የእይታ ብልሽት

የቫይታሚን A ጉድለት የጥቁር ዓይን ሽፋንን አድርቆ የደበዘዘ እይታ ወይም ትናንሽ ነጠብጣቦችን በማሳየት ይገለጣል። ይህ ከውልደት ጀምሮ በቫይታሚን ዕጥረት የተጠቃ ህፃን በጊዜው የህክምና ዕርዳታ ማግኘት ካልቻለ ዓይነ ስውር እስከመሆን ይደርሳል። ይህ አይነቱ በሽታ በጨለማ ጊዜ የማየት ችሎታን ይቀንሳል። በዚህ ጊዜ ዳፍንታም የመሆን ዕድል ይገጥመዋል። ዳፍንታም ማለት በቅጡ ማየት የተሳነው ማለት ነው። ታዲያ! ይህንን ሀቅ ስንመነዝረው ስንቱ ኢትዮጵያዊ ነው። በተገቢው መልክ ቫይታሚኖችን እየተመገበ ያደገው / የሚያድገው? የዚህ በሽታ ችግር በኑሮ ሁኔታው ላይ የሚጎሳቆለው ክፍል በገጠርና በከተማ አኗኗር መሃል መጠነኛ የሆነ ልዩነት ቢኖርም አጠቃላዩ ህይወት ሁሉንም የሚመለከት ይሆናል።
ሁኔታዎችን ስናይ ይህ የዳፍንት በሽታ ስር የሰደደ ለመሆኑ በአንዳንድ ድርጊቶች ላይ ይስተዋላል። ታሪክን አንሸዋሮ መመልከት ከዚህ አይነቱ ዕድገት ሁኔታ የተገኘ ይመስላል። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ነገስታት አንድ ወጥ ጎሳን የሚወክሉ ናቸው ተብሎ በጎጥ አቀንቃኞች ሲጠቀስ በተለይ የዐፄ ምኒልክ ዘመንና የዐፄ ሀይለስላሴ ዘመን በአማሮች የተያዘ ነበር ተብሎ ነው። ሀቁ ግን ራሳቸው ነገስታቱም ሆኑ የስልጣን ተካፋዮቻቸው ዛሬ ጎጠኞች ከሚጠይቁት የተለዩ ነበሩ። የዐፄ ምኒልክና ከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸውን ታሪክ ለጊዜው እንኳ ብናልፈው፣ ቅርብ ከሆነው የዐፄ ሀይለስላሴ
ዘመን ሹመኞች መሀል ብንመለከት አማራው የትኛው ነበር። ለነገሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሁሉም ጎሳ አባል ነው። ይህ የዘር ትርጓሜ የመጣው በከፋፋዮችና የውጭ ጠላቶች ወኪል በሆነው ወያኔና መሰሎቹ ነው። ያም እንኳ ቢሆን በዳፍንት አመለካከት የተስተዋለ እንጂ ብሩህ የሆነ እይታ ያስገኘው እንዳልሆነ ግልፅ ነው።
- ብላታ ዴሬሳ አመንቴ የጠቅላይ ሚኒስትር ምክትል ሚኒስቴር
§  ሜጀር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ የክብር ዘበኛ ዋና አዛዥ
§  ክቡር አቶ ይልማ ዴሬሳ በዩናይትድ ስቴትስ ባለሙሉስልጣንና የገንዘብ ሚኒስቴር ወዘተ.
§  ክቡር አቶ አማኑኤል አብርሃም የፖስታና ትራንስፖርት ሚኒስቴር ወዘተ.
§  ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ የኤሉባቡርና የጎምጎፋ ገዥ
§  ደጃዝማች ፍቅረስላሴ ሀብተማርያም የወለጋ ጠቅላይ ገዥ
§  ደጃዝማች ካሳ ወልደማርያም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ወዘተ.
§  ደጃዝማች ሽፈራው ባልቻ የጅጅጋና የኦጋዴን አበጋዝና የወለጋ አውራጃ ገዥ
§  ሜጀር ጄኔራል አበበ ገመዳ የሁለተኛው ክፍለጦር አዛዥ
§  የተከበሩ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የገንዘብ ሚኒስትር ምክትል ሚኒስቴር ወዘተ.
§  ጀኔራል ታደሰ ብሩ የፖሊስ ሰራዊት ፈጥኖ ደራሽ አዛዥ
በተለይ ደጃዝማች ከበደ ብዙነሽና ሊጋባ በቀለ ሆርዶፋ ስመ ጥር የሆኑ አርበኞች ሲሆኑ የተሰጣቸው ስፍራ ግን መንግስትን የሚያስተች ነው። አርበኛን ወደሁዋላ ባንዳን ወደፊት
ያደርጋል ተብሎ በህዝብ የሚተቸው መንግስት ደጃዝማችን የክብረ መንግስትና የናዝሬት አውራጃ ገዥ ብላታን ደግሞ የንጉሰ ነገስቱ ዋና ሊጋባ በማድረግ ሾመዋቸዋል።
ትውልድ! ይህን መሰሉን ሀቅ አጋልጦ፣ በወዳጅነትና በቤተሰብ እጅ ወድቆ ሊገዛ የማይገባው ህዝብ ነው ብሎ ቆርጦ የታገለ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የዳበረ ታሪክ ያለውና ዘመኑም በፈቀደው መጠን የተማረ ትውልድ ያፈራ ነው። ይህ አይነቱ ፈር የለቀቀ አድልዎና የህዝብን መብትና ነፃነት የነጠቀ አስተዳደር በህዝባዊ መንግስት መተካትና መስተካከል አለበት ብሎ ነው ትውልድ የታገለው። የጎጥን ፖለቲካ አያቀነቅንም። በኢህአፓ ውስጥ ተሰልፎ የታገለና ህይወቱን ለትግሉ የሰጠ የአማርኛ ተናጋሪው ወጣት በርካታ ነው። ለጎጥ ብሎ ሳይሆን ለዕውነት ሲል። ለቆመለትና ለሚገኝበት የመደብ ክፍል ሲል። ታግሎ የወደቀው፣ በእስር በስቃይ የተንገላታው ኢትዮጵያን የሚያፈቅረው ወገን ጠላት ተብሎ ሊጠቀስ አይገባም። የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የኢትዮጵያ ወጣት የወገኑን በደል የሚያውቅ፣ በጋራ ሆኖ ስለመብቱ የጠየቀ/የሚጠይቅ እንጂ! ብዙና ጥቂት የተማረ ሀይል ያለው ህዝብ፣ የተማረና ያልተማረ ወጣት ያለው ህዝብ፣ ይህንንና ያንን ቋንቋ የሚናገር ህዝብ፣ እያለ አይሸነሽንም። ህዝቦች የሚል ቃል የፈጠረው ወያኔ፣ ህዝቦቹን ከሚፈልግበት ይፈልግ እንጂ! የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ህዝብ ነው። ወጣቱ እንደ ወያኔ አይነቶቹን ሀገር አጥፊ ቡድኖች በፊትም በኢህአፓ ተደራጅቶ ታግሏቸዋል። አሁንም ከዚህ የጋራ ጥያቄ ተነስቶ ጎጠኞችን ይታገላቸዋል። ጎጠኞች እንደሚያወሩት ኢትዮጵያ የተከፋፈለች አይደለችም። የኢትዮጵያ ወጣት ይህ የጎጠኞች አላማ የትም እንደማያደርስ አውቆታል። ከዚህ በሁዋላ ወጣቱን ማጭበርበር አይቻልም።
ይህን የመሰለውን እውነታ የማይመለከቱ ሰዎች የዳፍንት ችግር አለባቸው ቢባል ሀሰት አይደለም። ምክንያቱም የጎጠኞች ፖለቲካ የተዋቀረው በተንሸዋረረ የፖለቲካ አመለካከት ላይ በመሆኑ ነው። አማራው የተለየ ስልጣን ኖሮት አያውቅም። እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የመደቡ ተጠቃሚ ሆነ ሊሆን ይችላል። እንጂ! ለአማራነቱ ዋቢ ቆሞ አያውቅም። የጎጠኞቹ አለቃ (አባይ ስብሀት) አማራና ኦርቶዶክስ አከርካሪያቸው ተመቷል ሲል፣ ወጣቱ ኢትዮጵያዊነቱን ከማንፀባረቅ ውጭ ሌላ ወንጀል እንደሌለበት ለማየት ዳፍንት አስቸግሮት ሊሆን ይችላል። አለበለዚያ መንግስታት የራሳቸውን መደብ አባል እንጂ! ደሃውን አማራ፣ ደሃውን ኦሮሞ፣ ደሃውን ጉራጌ፣ ደሃውን ወላይታ፣ አፋርን፣ ሲዳማን፣ ከምባታን፣ ሀድያን፣ አኝዋክን፣ ሙርሲን ወክለው አያውቁም። የወያኔ አይነቱ የዘር ፖለቲካና የጠላትነት አመለካከት ጥያቄ ቀደም ሲል ባነሳነው የቫይታሚን A ዕጥረት ከሚፈጠረው ዳፍንት የተነሳ ሊሆን ስለሚችል ትክክለኛውን እይታ ለማየት ተቸግሮ ዓይኑ ከታወረ ምርኩዙን ተቀብሎ መምራት የህሊና ግዴታ ይሆናል።

አንድነት የኢትዮጵያ ህዝብ መገለጫ ነው።
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!


No comments:

Post a Comment