Monday, June 6, 2016

ሆዳም ሀገሩ ሆዱ ነው (አሚናት ኢብራሂም ከኖርዌ)


ሆዳም ሀገሩ ሆዱ ነው
አሚናት ኢብራሂም ከኖርዌ
በኢትዮጵያ ሀገራችን ውስጥ ለ 25ተኛ ጊዜ ወያኔ ሊያከብር የተዘጋጀው እርሱ ለህዝባችን ያለውን ንቀት የሚያሳይበት በሱ አጠራር የነፃነት ቀን ብሎ የሚጠራውን ለኛ ኢትዮጵያውያን ግን የባርነት ጊዜ የሆነውን ግንቦት 20 ለመደገስ ሽርጉድ እያለ ነው። በተለይ ለሴቶች ከአረመኔው ደርግ አገዛዝ በሁዋላ በባሰ ሁኔታ መብታችንንና
ነፃነታችንን ነፍጎ ወያኔ በባርነት ወደ ተለያዩ ሀገሮች ለሽያጭ አቅርቦን መከራ ተቀባይ ነፃነት ናፋቂ አድርጎናል። ግንቦት 20 ለኛ ለሴቶች የክብር ቀን ሳይሆን የውርደት ቀን ነው። ማክበሩስ መደገሱስ ለማንና ለምን?
ሴቶች ለአፍታ እንኩዋን ነፃ የመሆን ስሜት ተሰምቶን በማያውቅበት ሁኔታ ወያኔ ነፃ ናችሁ ብሎ ሊነግረን ወገቡን ታጥቆ ተንስቱዋል። የኛ ሴቶች የመብትና የነፃነት ጥያቄያችን የቀናት አለመሆኑ ግልፅ ነው። እውነት እንነጋገር ከተባለ እኛ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ጥያቄያችን እንደ ትንሽ ጥያቄ የሚታይ አይደለም። ብዙዎች ኢትዮጵያውያን ሴቶች እስካሁንዋ ሰአት ድረስ ውድ ሂወታቸውን የከፈሉባት የነፃነትና የእኩልነት እንዲሁም ሳንወድ ተገደን የምንገባበት ስርኣቱ ያመጣብን ዘመን ያስቆጠረ ጭቆናና መከራ ይቁም ነው የምንለው። እርሱ ወያኔ የፖለቲካ እምነቴ የዜጎች መብት፣ እኩልነት ምናምን እያለ ሲለፈልፍ ቢደመጥም ሀቁ ያለፈ ግን ይህ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅቆ ያቀዋል።
የሴቶች ክብርን በሚነካ መልኩ በሀገር ውስጥ በየእስር ቤቱ የሚማቅቁ እንዲሁም በአደባባይ ወያኔ የፀጥታ ሀይሎቼ በሚላቸው የመብትን ጥያቄ የሚያነሱ ሁሉ በጥይት ሲደበደቡ ማየት የተለመደ ነው። ለወያኔ ዜጎችን በጥይት መግደል የጉርሻ ያህል ቀላል ነው። አረንጉዋዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩን ባንዲራችን በማዋረድ የጀመረው ስርአቱ ዛሬም ሴቶችን፣ ወንዶችን፣ ህፃናትን፣ አዛውንትን፣ ሀገርን እራስዋን ጨምሮ አዋርዶና ንቆ ለውጪ ወራሪ ለባእዳን አስንቆ የነፃነታችን ቀን ብሎ ሊያከብር መነሳቱ ያማል። በአንድ ወንበዴ ቡድን ወያኔ በሚባል የምትመራው ሀገራችን ዛሬ ለሴት ልጆችዋ እንዲሁም ለዜጎችዋ እንዳትመች ተደርጋለች። ይህ ለዚህ ሁሉ ግፍና ምንጭ የሆነው ስርአቱ እዛው በሀገር ውስጥ ስለሆነ ነው። ለዚህም ነው በሚሊዮኖች የሚሆኑ ሴቶች የሚሰደዱት በሰው ሀገር ላይ ብዙ አይነት ሰቆቃ የሚቀበሉት። ለዚህ ሁሉ ምንጭ በሀገር ውስጥ በሴቶች ላይ ባለው ስርአት የሚፈፀመው የአስተዳደር በደል ነው። ይህ በደል ብዙ አመታትን አስቆጥርዋል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ከገባንበት የስነ ልቦና ችግር ለመውጣት ከብቃትም በላይ ብቃት እንዳለን ግልፅ ነው። በርግጥ እኛ ኢትዮጵያውያን ሴቶች መንፈሰ ጠንካሮች መሆናችን በዚህ ሁሉ ዘመናት የሚደርስብንን መከራና ችግሮች ተቁዋቁመን ዛሬም ለለውጥ መዘጋጀታችን ለዲሞክራሲና ለሰብአዊ መብት መከበር የምናደርገው አስተዋፅኦ አንዱ ምስክር ነው። በሀገራችን ውስጥ የምናያቸው ችግሮች እንዲሁ በቀላሉ የሚወሩ አይደሉም።
የሴቶች መብት ጉዳይ ለሀገር ዋልታና ማገር ነው። ሆኖም ግን የኛ የሴቶች ጉዳይ ተረስቶ ባለበት ሁኔታ ወያኔ እንደሚፈልገው በደብል ዲጂት ያደገው ኢኮኖሚያችን ሳይሆን የኛ የኢትዮጵያውያን መብት ረገጣና የባርነት ሽያጭ እንደሆነ ግልፅ ነው። ይህም የአምባገነንነቱን ደረጃ ጥግ መድረሱን ያሳያል። የአምባገነንነቱ አንዱ መገለጫ ሴቶችን አፍኖ በመያዝ በሁሉም መስክ ምንም አይነት የጎላ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ማድረግ ነው። ከዚህም የተነሳ እኛ ሴቶች ሀገራችንን ጥለን የመጥፋት ፍላጎታችን ከፍተኛ ነው። በሌላ አገላለፅ ባለን ችሎታ ተሰማርተን ኑሮዋችንን ለማሸንፍ የምንችልበት እድል የለንም። ይህ የወያኔ ቡድን ያምባገነንነት ደረጃውን አድጎ የደረሰበትን ደረጃ እንድናይ የሚረዳን ነው። የኛ የሴቶች መብት ረገጣ ከፍተኛ ከሚባለው ደረጃ አልፎ መጨረሻ ደረጃ ላይ
page1image21920

ደርስዋል። ያለ ሴቶች ተሳትፎ ውጤት መጠበቅ ከባድ ነው።
ወያኔ ስልጣን ለመያዝ ከያዘም በሁዋላ የሚጫወተው ጨዋታ የሴቶች መብት ጉዳይ ነው። የሴቶች መብት አስከብረናል እያለ የሚዘፍነው ዘፈን አለው፤ ከተግባር የራቀ ማምታቻና ፕሮፕጋንዳ ነው። የዲሞክራሲ ትልቁ መሰረት ሴቶች ሲሆኑ፤ በርግጥ ዜጎችን እንደ ባህሪያቸው መንከባከብ አንዱ የዲሞክራሲ መገለጫ ነው።
የሴቶች መብት ሲባል የሁሉም ዜጎች መብት ማለት ነው። በስልጣን ላይ ያሉ ንክኪ ያላቸው ከቁጥር የማይገቡ እናውጣና ከዛ ሌላ ያለነውን የኛ የሴቶች መብት ጉዳይ የሁሉም ዜጎች ጥያቄ ነው። ዛሬ ላይ ወያኔ ግን ይህን ሁሉ የሴቶችና የዜጎች መብት ደፍጥጦ ባለበት ሰአት ግንቦት 20 ብሎ በሚጠራውና እርሱ የነፃነታችሁ ቀን ሲለን እኛ ደግሞ የባርነታችን ቀን እንደሆነ የምናቀው እርሱ ለራሱ ደግሶ ለሚበላው ድግስ እየተዘጋጀ ነው። ሆዳም ሀገሩ ሆዱ ነው። በደብል ዲጂት ያሳደገው ወንጀል አልበቃ ያለው ቡድን ብሎ ብሎ በንደዚህ አይነት አሳፋሪና እርካሽ ስራ ተወጥሩዋል። በሀገራችን ውስጥ በህግ የበላይነት በዲሞክራሲ መሰረት ላይ የታነፀ የሴቶች ተቋም እንዲፈጠር ስርአቱ አይፈልግም።
ብዙ አቅምና እውቀት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ህዝብ የሚውዳቸውና የሚያከብራቸው ብሎም የሚሰማቸው ሀገራዊ ተምሳሌት ያላቸው በታሪክ አጋጣሚ የሚገኙ እንደነ አበራሽ በርታ የመሳሰሉ ብዙ ጠንካራና ጎበዝ ሴቶች ደብዛቸውን ሲያጠፋና ሲገድል ከርሙዋል። ኢትዮጵያ ሀገራችን በአባቶቿ ተጋድሎ ለዘመናት ተከብራ የኖረች በቀኝ አገዛዝ ስር ያልወደቀች ብቸኛዋ ሀገር ናት፤ አሁን ግን ተራዋ ደርሶ ከራስዋ በወጡ ቀኝ ገዢዎች ስር ወድቃለች። ታዲያ እነዚህ ቀኝ ገዢዎች ሀገርን ትውልድን ሴቶችን ወጣቶችን ያመክናሉ ሀይማኖትንም ከሀይማኖት ያጋጫሉ። ለቀጣዩ ትውልድ በነሱ አስተሳሰብ መቼም የማይፈታ የቤት ስራ ይሰጣሉ። በርግጥ ያለው ስርአት ሆዳም ነው። ሆዳሞች ደግሞ የሚታመኑና ተስፋ የሚደረግባቸው አይደሉም። ለዚህም ነው ዜጎች የሚናፍቁትን ነፃነት፣ ዲሞክራሲ ፍትህና ብልፅግና በሌለበት ሀገሪቷ ለ 25 አመታት በሆድዋ ብዙ ችግሮች ይዛ ነፍሰ ጡር ሆና ምጥ ላይ እያለች ወያኔ በየአመቱ ከችግሮችዋ በሰላም እንደተገላገለች እየሰበከ ብቻውን እልል እያለ ያለው በሀገራችን ውስጥ ስላለ የሰብአዊ መብት ችግር ብዙ ማለት ይቻላል ግን አሁን ወያኔ ሀገሪቷን ሽጦ ህዝባችንን በትኖ ያሻውን እያደረገ ይገኛል። ይህ ጉዳይ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያንን የሚመለከት ነው። ለመፍትሄው መሮጥ መትጋት ያስፈልጋል ልጆቻችንን መከራ እንዳይወርሱ ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትና ህብረት በሁላችንም ዘንድ ይጠናከር።
እናቸንፋለን!!! 

No comments:

Post a Comment