Friday, June 10, 2016

ግንቦት ፳ እና ፈንጠዝያዉ.... አርሴማ መድህኑ ከኖርዌይ

ግንቦት ፳ እና ፈንጠዝያዉ

አርሴማ መድህኑ ኖርዌይ ግንቦት 19/2008
በደም የተገነባ፣ በደም የተለወሰ፣ በደም የሚያበራ፣ በደም የሚታደስ፣ ደም ግብሩ የሆነ ቀን ሲከበር የሚከፋችሁ ለምንድን ነው? ደም፣ ደም፣ ደም..... "ያለምንም ደም፣ ኢትዮጰያ ትቅደም" ተብሎ ተጀምሮ በደም ተቋጨ። "ካሁን በኋላ ጠላታችን ድህነት ብቻ ነው፣ ሰላማችንን የሚነካው የለም" በሚል ስብከት ተጀምሮ ይኽው አሁን ድረስ ደም እየተገበረ ነው። አሁን ባለው አያያዝ የግንቦት 20 ወዳጆች ደም የሚጠግቡ አይመስልም፣ገና ብዙ ደም ለማፍሰስ የተዘጋጁ ይመስላል። ክብር ለተስፈነጠሩት ባለ "ራዕዩ" መሪ!!
በዚህ ቀን ዋዜማ ይህንን ጽሁፍ ሳዘጋጅ "የጫካውን ዘመን ሳናስብ 25 ዓመት ለመማር አይበቃም? "ብዬ ራሴን ጠይቄ ነበር። ተማር ያለው ከሌሎች ሲማር፣ የግንቦት 20 ባለቤቶች ለምን ለመማር ፈቃደኛ አይሆኑም? ከቶውንም ሊገባኝ የማይችል ጉዳይ ነው። ይልቁኑም "የግንቦት 20 አንጸባራቂ ድሎችን የነካ፣ በአይኔ የመጣ!! " በሚል መመጻደቅ ይቀናቸዋል። ቃታ መሳብና መግደል ያስደስታቸዋል። ቀን የሰጣቸዉ ጀግኖች!!
እነዚህ ወገኖች ቢመጻደቁ ፣ ጠግበዋልና ድሆች ላይ ቢያገሱ፣ ቢታበዩ፣ ቢያብጡ፣ በትምክህት ናላቸው ቢወጠር፣ ያለ እኛ ጀግናና ተኳሽ የለምቢሉ፣ ውስኪና ሻምፓኝ እየገለበጡ ቢያሽካኩ አያስደንቅም።
ለምን? ቢባል፣ ዘርፈዋል፣ ገንብተዋል፣ ገንዘብ በዉጭ ሃገር ባንኮች ሳይቀር አከማችተዋል፣ እስከ አፍንጫቸው ታጥቀዋል፤ ከሁሉም በላይ አይነ ልቦናቸው የተጋረደባቸው አደግዳጊ ባሮች አሉዋቸው። በርካታ ወንደሞቻቸውን፣ እህቶቻቸውን፣ ወገኖቻቸውን፣ እናቶቻቸውን፣ አባቶቻቸውን ወዘተ የሚገርፉ፣ የሚያስሩ፣ የሚሰልሉ፣ የሚያሰቃዩ፣ የሚገሉ ህሊና ቢሶች አሉዋቸውና!!
የግንቦት ሃያ ግብዞችን ማን አለብኝነትና አልጠግብ ባይነት ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልምና የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ ወደሆነዉ ቁምነገር ላምራ።
በብሔር በሔረሰቦች ስም የሚምለውና የሚገዘተው የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር፣ እዚህ ላይ አንድ ማሳሰቢያ አለኝ። ብዙዎች ይህንን ስማቸውን አይወዱትም። ጫካ እያሉና ፣ አሁንም ትልቅ ሃገር እየገዙ ስማቸውን
ያልቀየሩት እነሱ ሆነው ሳለ "ወያኔ" አትበሉን የሚል ቀረርቶ ያሰማሉ። በእኔ አመለካከት በሃገር ቤትና በዉጭ ሃገራት ያሉ ሚዲያዎች አቋም በመያዝ በትክክለኛ ስማቸው ማለትም የትግራይ ነጻ አዉጭ ወይም ወያኔ ሃርነት ትግራይ ብለዉ በወጥነት እንዲጠሩዋቸው በዚህ አጋጣሚ ጥሪ አቀርባለሁ። ስማቸው ወያኔ ሆኖ እያለ ፣ ሳይመረጡ አገር በጠብ መንጃ እየገዙ መሆኑ እየታወቀ፣ "የኢትዮጵያ መንግስት፣ ወይም ህብረ ብሄር ድርጅት ሆኖ ለመታየት ኢሕአዴግ ብሎ መጥራት ለመጪው ትውልድ ስህተት ማስተማር ይመስለኛል ።
ወያኔ የሃገራችን ገዢ ከሆነ በኋላ እንደ ኩበት ጠፈጠፎ የሰራቸው ባሪያ ድርጅቶች በባንዳነት ላለፉት 25 ዓመታት የኢትዮጰያን ህዝብ እየዘረፈና እየገደለ እንዲጋልብ ፈቅደውለታል። አብዛኞቹ ባንዳና ፍርፋሪ ለቃሚ የመሆናቸው ብቻ ሳይሆን የባርነታቸው ዘመን ሲጠናቀቅ የሚጣሉ መሆናቸውን ቢረዱም የሚቆጠቡ አይደሉም። አፈር አቡክተው ያደጉበትን ቀዬና ጓደኞቻቸውን በትርፍራፊ ይለውጧቸዋል። እንዲህ ያሉ ከሰውነት ደረጃ የወረዱ ዜጎች በማፍራት የሚታወሰው ግንቦት ሃያ ሲከበር በፈቃደኛነት የሚዘሉና የሚያሽካኩ ሁሉ የወያኔ ባሮችና፣ ሃገራቸዉን የከዱ ባንዶች ናቸው።
"በሃገሬና በአይኔ ቀልድ የለም" የሚሉ ተውልዶችን አምጣ የወለደች አገር ዛሬ የባንዶች ምድር ሆናለች። ጥንት በቅኝ ግዢ ያለተያዘች አገር ዛሬ በተወሰኑ ጠባብ ሃይሎች ተወራለች። እነዚህ በትግራይ ንጹህ ህዝብ ስም የሚነግዱ ወረበሎች የባህር በሯን ዘግተው ሳትሞት ቆልፈውባታል። አንጡራ ሃብት መሬቱዋን በሳንቲም እየቸረቸሩ የተፈጠሮ ሃብቱዋን አውድመውታል። በተሳሳተ ፖሊሲ / ምሁራን እንዳረጋገጡት/ ግብርናው አንድ እርምጃ መራመድ አቅቶን ረሃብ ዜጎችን እያረገፈ ነው። በቀን ሶስቴ ትበላለህ የተባለ ህዝብ አንዴም አቅቶት ገንዳ ውስጥ ቆሻሻ እየለቀመ ነው። ይህ ነው አንግዲህ አንዱና ዋናው የግንቦት ሃያ ፍሬ፣ ግብዞች የሚደግሱለትና የሚፈነጥዙበት።
በወያኔ አገዛዝ ዴሞክራሲና ሰብአዊ መብት የሚከበሩ ባለመሆናቸው ኢትዮጵያዊያን መብት የሌላቸው ሆነዋል። የጻፉና የተቃወሙ አሸባሪ ተብለው ታስረዋል። የተከራከሩና ራሳቸውን አማራጭ አድርገው ያቀረቡ ፖለቲከኞች ቤታቸው ወህኒ ሆኗል። ያልተያዙም ተሰደዋል። ምሬቱ ልክ ስላለፈ ስደቱ መንገድ የሚያስመርጥ አይደለም። ወያኔዎች ነጻ ፕሬስን ስለሚፈሩ ነጻ ሆነው የሚያገለግሉ ሚዲያዎች ከስመው በምትካቸው "ቅምጥ" ጋዜጠኞችና ሚዲያዎች በባርነት ተቀጥረዋል። እንዲህ ያሉ የውርደት መለኪያዎች ላይ ደርሰን ነው
በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ፈሶ ግንቦት 20 የሚዘከረው። ድንቄም ዝክር!!
የግንቦት 20 ፍሬዎች ቢዘረዘሩ ራስን ከማስደፋት የዘለለ ፋይዳ የላቸውም። አንድ ወዳጄ " ግንቦት 20 በቲቪ ደስ ይላል" ያለው ታወሰኝ። የጠፉትን ሳይጨምር ኮንዶሚኒየሞች ተገንብተዋል። መንገድ ተዘርግቷል። ሌቦቹ ያሰሩዋቸው ህንጻዎች በያደባባዩ ተገተረዋል። ሁሉም ያምራሉ። በቲቪ ሲታዩ ቀልብን ይስባሉ። ዶ/ር መረራ ጉዲና እንዳሉት በተግባር ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ስትታይ ግን ጉዱ ሌላ ነው። እዚህ ላይ ከውጪ አገር አበዳሪዎች የተነከርንበት እዳ በስንተኛው ትውልድ ተከፍሎ ይጠናቀቅ ይሆን የሚለውን ጥያቄ ማስታወስ ግድ ይላል። ተዘርፎ በውጪ ባንክ የተቀመጠው በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ ... ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል። ህዝብ ሁሉንም ያውቃል። ለህንጻዎቹ ስም ሰይሞ ቀን እየጠበቀ ነው።
የቀን እንጂ የድርጅት ጀግና የለውም ተብሎ የለ!!
ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ያጡዋቸውን በርካታ ጉዳዮች መዘርዘር ዋጋ የለውም፣ "ግንቦት 20 አንጸባራቂ የድል ቀን

ነው" በሚል በበላችሁት መጠን ለምታሽካኩ ጊዜ መልስ ስላለው ብዙ የምለው ነገር አይኖረኝም። በባርነት ወያኔዎችን የምታገለገሉ ግን ዋ!! ኩማ ደመቅሳ ውህዳኑን ደግፈሃል ተብለው በተወረወሩበት ወቅት "ተራ ሰው ሆኖ ለቅሶ መድረስና ንፍሮ መቃም እንዴት ያስደስታል። ከሃላፊነት በተነሳሁ ጊዜ ይህንን ተረድቻለሁ...." በማለት የተናገሩት ተመልሰው ቢዘነጉትም የልብ ውስጥ ጭንቀት ንግግር ነውና በቀላል የሚታይ አይደለም። ሌሎችም በተመሳሳይ የምታስቡ እንዳላችሁ እገምታለሁ። የኦሮሞ ልጆች ደም ሲፈስ፣ የኦሮሞ እናት ልጅዋን ስትነጥቅና ስተገደል የምትቃጠሉ እንዳላችሁ ይታመናል። ክህደትና ባርነት ያንገሸገሻችሁ ጥቂት እንዳልሆናችሁ ይታመናል። ግና እስከመቼ ? 25 ዓመት አይበቃም? ጊዜው የመለየት ነው። ጊዜ ይከንፋል። እድሜም አጭር ነው!! ይህ መልዕክት ለኦህዴድ ብቻ ሳይሆን ለአማራ፣ ለደቡብ፣ ለሶማሌ፣ ለቤኒሻንጉል፣ ለጋንቤላ፣ ለአፋር፣ ለትግራይ፣ ለሶማሌው እንዲሁም በመላው ዓለም ላላችሁት ሁሉ ነው።
ወያኔዎችን ለማስደሰት ሌት ተቀን የምትተጉ፣ ስትተኙ እንኩዋን ማጎብደድ የማታቆሙ ባንዶች ጊዜ መልስ ሲሰጥ፣ እናንተ መልስ የላችሁምና ከወዲሁ አስቡ። የግንቦት 20ን ፍሬዎች ረጋ በሉና ገምግሙ። ጊዜውንም
አስተውሉ። ያለውን የህዝብ ስሜትና ቁጣ ግለት ለኩ። ሳይመሽ ፍሬ አልባ የሆነውን ቀን ማምለክ አቁሙ። ወደ ወገኖቻቸሁ ተመለሱ። በዚህ የክሽፈት ድምር ቀን ከክሽፈት መንገድ ራሳቸሁን አቅኑ። የወራሪ ካስማና ምሶሶ በመሆን ዘመናችሁን አታጠቃሉ። ህዝብ መሃሪ ነውና ወደ ህዝብ ተመለሱ።
ሃዘን፣ ድህነት፣ ረሃብ፣ ምሬት፣ በደል፣ ጣሪያ ደርሱዋል። ሁሉም በየቤቱ በጎሸ ስሜት ውስጥ ነው። የግንቦት ፳ መዘዝ ያልነካው ደጅ የለም። የዘር ፖለቲካው ጦዞ ዙሩ ከሩዋል። አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ አያስደስትም። በግራም በቀኝም የሚሰማው ሃዘን ነው። የመብት ጥያቄው በየአቅጣጫው ተቀጣጥሏል። ስጋት አንዣቧል። የምታመልኩት ወያኔ ቋንቋው ጥይት ብቻ በመሆኑ የበቀል ስሜቱን አንሮታል። በቀል በየአቅጣጫው እየፋመ ነው። የበቀል እሳት ሰደድ ነው። አንዴ ፈር ለቆ ከተነሳ ለማስብ ጊዜ አይሰጥም። ስለዚህ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ራሳቸሁን ከዚህ ሰው በላ አገዛዘ በመለየት ህዝባዊ ይቅርታን ተጎናጸፉ። በፖለቲካ ዓለም ነገሮች ሲቀያየሩ ትንፋሽ የሚወሰድበት ጊዜ አይኖርም። ሁሉም የሚያልፍ ነውና የማያልፍ ታሪክ ስሩ። ቢያንስ ልጅ ለጆቻቸሁን ከባነዳነት ታሪክ ነጻ አውጡ። እየነፈረች ያለችውን አገርና ምስኪን ህዝብ ታደጉ።
በወያኔ በኩል የሚታየው አካሄድና ስልት ዓላማ ያለው እንደሆነ ድሮ አብረው የነበሩ በሰነድ አስደግፈዉ ነግረውናል። ትናንት የተፈበረከ ድርጅት ተረክባችሁና በስሩ ታቅፋችሁ ህዝብን የምታስረግጡ እባካችሁ ስሙ። የግንቦት ፳ ፍሬ ከእሬትም መሯልና ይብቃችሁ!! እኛም ይብቃን!! አገሪቱም ይብቃት!! መጪው ትውልድም ከበቀል የጸዳ ይሆን ዘንድ ህዝብ በሚፈልገው ይተዳደር ዘንድ ታገሉ። የማይቀር ቢሆንም በእናንተ ዘመን ይህን በማድረግ በታሪክ ስትወደሱ ኑሩ!! ተራ የቀበሌ ነዋሪ በመሆን ያለ ስጋት የምትኖሩባት አገር ትኖራችሁ ዘንድ ዛሬ ወስኑ። መለስ ድንገት ይሞታል ብሎ ያሰበ አልነበረም። “መንገዱን ጨረቅ ያድርግላችሁ” እያሉ ሲዛባበቱ ድንገት ሾለኩ። እድሜ ይስጠንና ታሪካቸው ሲጎለጎል እንሰማለን። ዛሬ ረሃብ የሚያቃጥላቸውን ወገኖቻቸንን ጉሮሮ ለማበስ እህል ማስገቢያ አጥተን በርበራ፣ ካርቱም፣ ሞምባሳ እያልን ወደብ ፍለጋ እንዋትታለን። ሃፍረት የማይሰማቸው ወያኔዎች እንዲህ ያለውን የታሪክ ልቅላቂ አጽም “ውርስህን እናስቀጥላለን” እያሉ ህዝብ ላይ ይሳለቃሉ። ትንሽ የሚቃወማቸው ሲነሳ በዚሁ መንፈስ እየማሉ ይረሽናሉ። በደም ተነክረው የመኖር አባዜያቸው የሚለቃቸው አይመስልም። ገና ሊገሉ ቃታ ላይ ናቸው። ግንቦት ፳ የዚህና የዚህ መሰል ውርደቶች ዝክረ ቀን ነውና እናንት የህዝብ ወገኖች ተለዩት!! ተጠየፉት!! ከደም ፖለቲካ ውጡ!! 

No comments:

Post a Comment