Friday, June 17, 2016

በአንድ ዘር ጎራ ሀገር ስትመራ፤ በአንድ ዘር ጎራ ሀገር ስትበላ (ቢኒያም ሙሉጌታ ከኖርዌ)


ኢትዮጵያ ሀገራችን በራሷ ልጆች በኢትዮጵያ ደምና አጥንት የተገነባች ሲሆን በሁሉ መስፈርት ያለ ዜጋ ከታናናሽ ዜጎች እስከ ታላላቅ ዜጎች ንጉሰ ነገስት ድረስ ያሉ ዜጎች ዋጋ ከፍለው አቆይተዋታል። ዛሬ ላይ ግን ያለው ስርዓት ማንም የሚደፍራት ጋለሞታ አድርጏታል።
ሕወሀት(ወያኔ) የስልጣን መንበሩን ከተቆናጠጠ ወዲህ ከሚፈፅማቸው ለነጋሪ ከማይመቹ አንዱና ዋናው ሙስና ነው። ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ የሚመዘብረው የሀገር ሀብት የወያኔ ፓርቲ ቀንደኛና ዋንኛ ልሳኖች እንዲሁም የወያኔ ሚዲያ ተቋማት ጉዳዩ የሀገሪቱ ታላቅ ስጋት እንደሆነ አድርገው ሲያቀርቡና ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ ይታያሉ። ይሁን እንጂ ስልጣን ላይ ያለው ቡድን ባህር የሆነውን የኢትዮጵያን ህዝብ አዋርዶና ንቆ ከአንድ አከባቢ በመጡ ግለሰቦች ዝርፊያውን ተያይዞት ይገኛል። በዚህ ሀገር አጥፊ ቡድን ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች ተደጋግሞ እንደሚነገረው ማንኛውንም አይነት ንግድ ያለ ቀረጥ ይነግዳሉ ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ያሻቸውን ያደርጋሉ።
በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ጭምር ከታችኛው ጀምሮ እስከ ላይኛው መኮንኖች ድረስ ዋና ዋና ቦታዎች የሚገኝ ከአንድ ጎሳ የተሰበሰቡ የሀገሪቱ ሀብት በማን አለብኝነት እንደፈለጉ ሲያደርጉ እነሱ የሚያዩት የአገዛዙን ጥቅም የሚወክል ብቻ መሆኑን ነው። ወያኔ ራሱ ከሚመዘብረውና ከሚያደርሰው ጥፋት ባሻገር የሀገሪቱን ንብረት ሀላፊነት በጎደለው መልኩ ለሆዳም ካድሬዎች የህዝብ የሆነውን ንብረት እንደመደለያ ይጠቀሙበታል።
በአንድ ዘር ጎራ ሀገር ስትመራ፤ በአንድ ዘር ጎራ ሀገር ስትበላ እያየን 25 ዓመት ሞላን።
ታዲያ ይህ ሀገር አጥፊ ቡድን እርሱ የሚያደርሰውን እንዲሁም የሚመዘብረውን ምዝበራና ጥፋት በረጅም እጁ ወደ ሌሎች ሲጠቁም ይታያል። ሲያሰኘው በሀገሪቱ ላይ የተስፋፋውን ሙስና በተመለከተ ጥቂት ባለ ሀብቶች እያለ ሲወነጅል ሲሻው የተወሰኑ ሹመኞች እያለ ሲል ካስፈለገውም የሀገሪቱ ደላሎች እያለ ይከሳል፤ እንዲሁ በሀገርና በህዝብ ላይ እየቀለደ እራሱንም ልማታዊ መንግስት አድርጎ አስቀምጧል።
እነዚሁ የወያኔ ሹመኞች በሀገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች ከህዝብ ዘርፈው ያቋቋሟቸው ድርጅቶች በአሁኑ ሰዓት በነፃነት ስራቸውን መስራት ተስኗቸዋል። ለዚሁም ዋንኛ ምክንያት ህዝብ እንዴትና ከየት ገንዘቡ መጥቶ እንደተቋቋመ ስላወቀ ነው። የዜጎች ጭንቀት እየሆነ የመጣው በሀገሪቱ ላይ የሰፈነው ሙስናና ዘረፋ ሀገሪቱን እንደሚጎዳና እንደሚያጠፋ በመረዳቱ ያለውን ስርዓት ከስር መሰረቱ ለመናድ ህዝቡ ቆርጦ ተነስቷል።
ሀገራችን በነዚህ ገዢዎች ክራንች ውስጥ ከገባች ጊዜ ጀምሮ ህዝብን በዲፕሎማሲ ሳይሆን በሀይልና ጠመንጃ እየገዙትና በረቀቀ መልኩ ሀብት ንብረቱን እየዘረፉ ይገኛሉ። አሁን የህዝቡ ትግል ምን ያክል እንደጠነከረ ዜጋ ሁሉ የሚያውቀው ነው። በትግሉ ሜዳ ላይ ተሰማርቶ ለሀገርና ለህዝቡ ይህ ነው የማይባል መስዋዕት እየከፈለ ነው።

የዲሞክራሲ ስርአት የተራብን እኛ ተስፋችን እውን እንዲሆን በሚደረገው የትግል ሂደት ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን አለብን። ታዲያ አሁን ስጋቱ ኢትዮጵያዊነታችን ከተወረወረበት ሀገራችን ኢትዮጵያ ከወደቀችበት ማንሳት ነው።
ነፃነትና እኩል የሀብት ክፍፍል በሌለበት ሁኔታ የዲሞክራሲ ድርቅ አብሮን የተወለደ እስኪመስል ድረስ በዚህ ሁሉ ቸነፈር መመታታችን በተፈጥሮ ያገግኘነውን ነፃነት በጉልበተኞች ጠመንጃ መቀማታችን ሊቆጨን ይገባል።
አምባገነኑ ወያኔ ነፃነት ወዳድ የሆነውን ህዝባችንን ጭካኔ በተሞላው መንገድ እንዲሁም አግባብ በሌለው ሁኔታ ሁለንተናውን ባዶ አድርጎት ይገኛል። ታዲያ ይህ ጎሰኛ ቡድን የህዝባችንን አንድነት የሀገራችንን ሉዓላዊነት እያናጋ ይገኛል። ማህበራዊና ኢኮነሚያዊ ቀውስ በሀሪቱ ላይ ተስፋፍቶ የሚገኘው ይኸው ስርዓት በሚፈጥረው ችግር ነው። ይህ ሁኔታ በታሪክ አጋጣሚ ዛሬ ያለን ሰዎች የምንመሰክረው ሀቅ ነው።
ኢትዮጵያ ሀገራችን ካልበታተነ እረፍት እንደማያገኝ የሚሰማው ይህ ቡድን ከትናንት ዛሬ በዛች ሀገር ላይ እያደረሰ ያለው መጠነ ሰፊ ችግር ተባብሶ ኢትዮጵያን የኩራት መታወቂያ መሆኑን እያስረሳ ይገግኛል።
አሁን ላይ ከራሱ አልፎ የዜጎችን ስነ ልቦና በርካሽ ባህልና ሙስና እየበከለ ያለው ይህ ስርዓት ይህንን ፀያፍና ሀፍረት የተሞላበትን እርምጃ ለሀገርና ለወገን የማይጠቅም ተልእኮውን በተደራጀ መልኩ እያሳካ ይገኛል። የውጭ ሀይሎችም ተባባሪዎችም በግልም በቡድንም ሀገር የሚያደክም ዘመቻ ላይ ናቸው።
እብሪተኛው ገዢ በሁሉ መልኩ ህዝባዊ እፎይታ በሀገራችን ላይ እንዳይሰፍን ባለ በሌለ ሀይሉ ይታገል። በሀገሪቱ ላይ ከግለሰብ እስከ ቤተሰብ ከቤተሰብ እስከ ማህበረሰብ ባሉ ዜጎች ላይ ሰላም እንዳይሰፍን ማድረግ የወያኔ ዋነኛ አጀንዳ ነው።
ወያኔ ዘመኑን መከታ በማድረግ ወገንንና ሀገርን በስውርም በግልፅም በቀንና በማታ እየሸጠ ይገኛል። የዚሁ ቡድን ካድሬዎች ሲጀመርም ስለ ሀገራቸውና ስለህዝባቸው ጨንቋቸው አያቅም። ከእውነት ጋር የቆሙ አይደሉም። ሆዳቸው ከሞላ ህዝብ ከጠላው ስርዓት ጋር እጅና ጉዋንት ሆኖ መቀጠልን እንደ ጀግንነት የሚያዩት ጊዜ ይፋረዳቸዋል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!! 

No comments:

Post a Comment