Monday, June 20, 2016

በፍኖተ ራዲዮ የተነበበ ሀተታ (ያልተባበረ ተጠቅቶ ቀረ !)

                                         
    
                                ያልተባበረ ተጠቅቶ ቀረ !
የተፈጥሮና   የታሪክ ሂደት ነውና ፤ ያረጀ ያፈጀው እየሄደ፤  በአዳዲስ ክስተትና ትውልድ መተካቱ የሚቀር አይደለም ።   እንደ ማቱሳላ፤ 900 ዓመት  ለመኖር በመመኘት፤  ዕቅድ  አውጥቶ የሚንቀሳቀሰው ሁሉ፤  ባላሰበውና ባልተዘጋጀበት  ወቅትና ፍጥነት  እንዳልሆነ ሆኖ ይወገዳል ። ኅልውናው ይከስማል።  ደብዛው   ይጠፋል።  መቃብሩ ይፈልሳል ።   በህይወት ዘመኑ፤ ባሳየው ድርጊትና  ምግባር፤ ታሪኩ ይወሳል ይሞገሳል፤ ይከበራል።  ስሙና ታሪኩም ከመቃብር በላይ ህያው ሆኖ ይኖራል።
ይህ ዕድል  የተነፈገው ደግሞ፤ ይነቀፋል፤ ይወቀሳል ። ይረገማል።   " ሲራክ በመግባሩ ጠፋ መቃብሩ  "  ስለሆነ ፤ ስሙ ከነመግባሩ ይጠፋል   
   "  ምንም ትቢያ  ቢሆን  አፈሩ ቢያለብሰው ፤
      ስሙ አይቀበርም  መልካም የሰራ ሰው ! "    የተባለውን  መውድስ -ቅኔ አያገኝም ።

 ካለፈ በኋላ፤ በጥሩም ይሁን በመጥፎ  የሚታወስበት ታሪኩ የሚወሰነው ፤  በሕይወት ዘመኑ በፈፀመው ድርጊትና ባሳየው ምግባር  ነው። ይህንን ዕውነታ ተገንዝቦ  መቆየት፤ ምንኛ በልኅነት ነው? ነገር ግን፤  " ሰው  ስጋ-ለባሲ በመሆኑ"  የዕለቱን ጥቅም እንጅ፤ የኋላውን ማየት አይሞክርም   በአመዛኙ አይሆንለትም ።
" አወይ የኔ ነገር ጤፍ ይዤ በወንፊት፤
  ልብ በኋላ እንጅ አይገኝ ወደፊት    "
የሚባለው ስንኝ   የተቀረፀው ፤ የኋላ-ኋላ  የሚከሰተውን   ፀፀት  ለማስታወስ  ይመስላል 
የመንግሥት ሥልጣን ይዞ፤ ሀገር  የጎዳና ሕዝብ የበደለ ሁሉ፤  የሰራውን አውቆና ተግንዝቦ በጊዜው እራሱን ከዚህ ድርጊት   ካላሸሸ፤  የሚጠብቀውን መጠበቅ አይሆንለትም። ለጊዜው  በልቼ፤  ጠጥቼ ፤ ተደስቼ፤ ገዝቼ- ነድቼ፤ አመሮብኝ ፤ አልፎልኝ፤ ብሞት ግድ የለኝም  የሚለው አስተሳሰብ ፤በቅርብ ጊዜ የተፈራረቁት   የኢትዮጵያ  ገዥዎች የጋራ  ዕምነት ሆኖ ቀርቷል ። አለመታደል ነው ! 
የመንግሥት ሥልጣን የያዘ ቀርቶ፤ የቤተሰብን  ኃላፊ የተሸከመም  እንኳ  ቢሆን፤ ለልጆቼ፤  ለልጅ-ልጆቼ  ብሎ  ማሰብ ተገቢ ነበረ።  ከእኔ በኋላ፤ የሀገሬ  ዕጣ -ፈንታ፤ ምን  ሊሆን ይችላል ? የሕዝቤስ ሁኔታ እንዴት ይሆናል ? ብሎ  አለማስብ፤  " እኔ ከሞትኩ ስርዶ አይብቀል "  እንዳለቸው እንስሳ መሆን ነው ።   ይህ ደግሞ፤  ሰውን  ከሰውነት ተራ  የሚያወጣ ብልሹነት ነው ። ከንቱነትም ነው !
 "ከእኛ በኋላ ፤ የኋላ ልጅ  ይጨነቅበት! " ያሉ መሪ እንደነበሩ፤   የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑ አዛውንት ፤ በፀፀትና በሀዘን የናጋራሉ ይባላል ፤ ዛሬ! የነበሩት መሪ፤ ይኽንን  በእርግጥ አሉ አላሉ ሌላ ጉዳይ ቢሆንም፤ ሀገሪቱና ሕዝቧ አሁን  ለደረሰባቸው ችግር ግን መፍተሄ አልሆነም። ወደፊት ለሚመጡ መሪዎች ግን ፤ " የሄዱትን ያየኽ ተቀጣ" የሚል ማስጠንቀቂያ ለመንገር ይረዳ ይሆናል   አርቆ አሳቢና ብሩኅ አዕምሮ  ለተሰጠው !
አለመታደል እየሆነ ነው መስል፤ የሚመጣው ሁሉ ግን ከታሪክ  መማርን አልፈለገም፡፡ ሀገሪቱንና ሕዝቧን ወደ ተሻለ ዕድል ለመምራት፤ አዲስ  ምዕራፍ ቢከፈትለትም እንኳን ፤  ቅድሚያ የሚሰጠው ለራሱ ክብርና ሥልጣን እንጅ፤  ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም አይደለም።   የኢትዮጵያ መንበረ ሥልጣንን፤ የቱን  ያኅል ጣፋጭ ቢሆን ነው?  በሀገራችን ሥልጣን የጨበጠው ሁሉ ፤ ከያዘው ሥልጣን ፤ካለሞተና ካልተባረረ በስተቀር፤ ለምን   ፈቅዶ በሠላም የማይወርደው ? ።  ይኽ ጥያቄ፤  ሁሉን ዜጋ  የሚያስገርም  ከሆነ ቆይቷል  ። መልስ ግን አልተገኘለትም።  መሪ ሆኛለሁ የሚለው ሁሉ፤ በሠላም ሥልጣኑን ላለመልቀቅ የሚሰጠው ምክንያት ደግሞ ፤ ራስን  ለመታለል መሠረት ያደረገ ግብዝነት ነው ።
 ለአለፉት አምሳ  ዓመታት   በኢትዮጵያ የፖለቲካ መልከዐ ምድር  የተፈራረቁት አገዝዞች፤ወደ ሥልጣን ለመምጣትና ለመቆየት የየበኩላቸውን ምክንያቶች አቅርበዋል። እነዚህን ምክንያቶች፤ ለሥልጣናቸው ማጠየቂያ ( ) ተጠቅመውባቸዋል ።    ምክንያቶቻቸው እንደሚከተሉት ተመዝግበዋል 
አንደኛው፤   የመንግሥትን   ቅብዐ -ቅዱስ ፤ ከመለኮት እጅ ተቀብቻለሁ። እንደ ልቤ አንቀጥቅጨ፤ እስክሞት እንደጋዛም  ተፈቅዶልኛል ። የሚል ነበር። ያ ሥርዓት ግን አማሟቱን እንኳ ሳያሳምር፤ ዘር ሳያስቀር ፤ ሀገር ሳያተርፍ ፤  ከሰመ ።   
ሁለተኛው ፤   የታሪክ ግዴታ  ተሰጥቶኛል ።  ግዴታየን  እስክወጣ፤  ሕዝብ ጨርሸ፤ ሀገር አጥፍቼ፤  እቀጥላለሁ እንጅ፤ ከሥልጣኔ አልወርድም   ብሎ ሲወራጭ፤  ሀገሪቱን ለሌላ አጥፊ ቡድን አስረክቦ ሸሸ። የሞት ሞት ሞተ። በዕስመ  ዐብዮት፤ ኅልቁ መሳፈርት ትውልድ መትሮ ሄደ። ኣጥፍቶ ጠፋ ። የታሪክ ምፀቱ ግን፤ ዛሬ፤ በዚህ አስከፊ ሥርዓት ወስጥ የነበሩ ወንጀለኞች፤ አንዳቸውም  ለፍርድ አልቀረቡም፡፡
ሦስተኛው ፤  የብሄር ነፃ  አውጭነት ውክልና አግኝቻለሁ ብሎ ፤  የብሄርን ለምድ በመልበስ ፤ ከተፈለፈለበት  ጎሬው  መጣ ። በዕስመ- ብሄር ነፃነት ፤ ሀገር እየሸጠ፤ ሕዝብ እየከፋፈል፤ ዳር ድንበር እያስደፈረ፤ ሀብት ንብረት እያሸሸ፤  ዜጎች እያሰረ፤ እየገደለ፤ እያሳደደ፤ እያሳቃየ፤ አገዛዙን አንሰራፍቷል ።  የሀገሪቱና የሕዝቧ መከራና ስቃይም በአስከፊ ሁኔታ ቀጥሏል።   ከአምሳ ዓመታት ጀምሮ  የቀጠለው የሀገራችን ሁኔታ በአደገኛ  ፍጥነት እየተባባሰ  በመሄድ ላይ ይገኛል   የዚህ ምክንያቱ  ተፈራራቂ አገዛዞች ያመጡት ጥፋትና ጠንቅ ነው ። እንዲያውም፤ አሁንማ፤ የሀገሪቱ ኅልውና ጥያቄ አሳሳቢ ደርጃ ደርሷል ።
እነኝህ አጋዛዞች፤ በተጠቀሙባቸው  ማታለያ መክንያቶች የተነሳ፤  ዕድሜ ልክ በሥልጣን መቆየታችው ብቻ  ሳይሆን ፤ ገደብ -በለለሽ አምባገነንነት፤   ያሻቸውን ለማድረግ ማጠየቂያ ( ) እየሰጡ ሕዝቡን አታለሉት።፤   ሁሉም፤ በሕዝብ አመፅ   የሚወገዱ መሆናቸው ባያጠራጥርም፤  ጦሳቸው  ግን በቀላሉ አይወገድም። ጠባሳቸው ለሀገርና ለሕዝብ ተርፏል።   ጦሳቸው ወደ ተተኪው ትውልድ እንዳይተላለፍ፤ ምን መድርግ እንዳለበት ተብሎ ለማስብ ደግሞ አይቻልም።  ምክንያቱም፤ በወቅቱ ያለው ዜጋ፤ ራሱን ከችግር ለማውጣት ስለሚፍጨረጨር፤ ስለተተኪው  ትውልድ  ለማሰብ አይሆንለትም።  " ራስ ሳይጠና፤ ጎተና ! "  እንደሚባለው፤  ለራሱ  የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ፤ መጠለያና መጠጊያ የሌለው ሕዝብ፤ እንዴትስ ለነገው ትውልድ ያስባል ተብሎ ይታሰባል ?
ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ፤  ራዕይ ያለው መሪ ስለማያገኝ ፤  ተተኪው   ሥርዓት ምን መሆን አለበት ? የሚለውን ጥያቄ  ለመመለስ ይቸገራል ።  ለነገው  ዕድል ዛሬ ካልታሰበበት  ደግሞ፤ የትላንቱን ችግር ወደ ነገው ማስተላለፍ ነው።  የዛሬን ችግር ዛሬ ካልቀረፈቱት ፤ ዕዳን፤ ወደ ዞረ ድምር  ማወራረድ ይሆናል  ። ይኽ ደግሞ  ሀገራችን ኢትዮጵያ  "ኣድሮ ጥጃ " ከመሆን አያስመልጣትም ። ዕድሜ-ልኳን ፤ ዝንተ-ዓለሟን፤  ከዘለዓለም  ችግሯ  መውጣት አለባት ከተባለ፤ ለመፃዒ- ዕድሏ ዛሬ ሊታሰብላት ይገባል ። ይህ ኃላፊነት ደግሞ፤ የሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች እንጅ፤  ለተውሰኑ ድርጅቶችና ቡድኖች ብቻ የሚተው አይደለም።  የሀገርን  ዕጣ- ፋንታ፤ ለሞግዚት አይሰጥም ።  
 " ሀገር  የጋራ ናት " እስከተባለ  ድረስ ፤ የሀገር ኃለፊነትና ግዴታ፤ መሥዋዕትነቱም ጭምር የያንዳንዱ ዜጋ ድርሻ  ከመሆን አያልፍም     አንዱ በሌላው ላይ ጣት ቢጠቃቆም፤ ሌላውም አንዱን ለመጥለፍ  ቢጣጣር፤  የጋራ ጥፋትን እንጅ፤ የሀገር  ደኅንነትን  አያመጣም  ። ዕቅጩን እንናገር ከተባለ፤ እስካሁን የተሄደው ሂደት ከዚህ ተግባር ነፃ ያወጣ ነበር ለማለት አይቻልም። እኛ፤ ከአጉል ይሉኝታ ይልቅ፤ ዕውነቱን ተናግሮ ከማሸበት ማደርን መርጥናል ።  ሁሉንም ፤ታሪክ ይፍረድ  !
 ለኅሌና ዳኝነት የተሰየመ፤  ፈርድ ለግጫ ነውና፤   ለግጫ ይፍረድ !  ሀቀኛ ልሣን ያለው፤ ሀቁን ይናገር !  የኅሊና ብይን የሰጠና ሀቁን የተናገረ፤  ራሱን  ከኅሊና ወቀሳ ነፃ ያደርጋል  ። ኢትዮጵያ ሀገራችንም የምትፈልገው፤ የኅሊናቸው ተገዥ የሆኑትን ዳኞችንና መሪዎችን ነው። ይህንን ዕድል ያላገኘ ሕዝብ፤ መላ ህይወቱን ከመከራ አይላቀቅም ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤ቀደም ብለው የነበሩትን ሁለት አገዛዞች ለመጣል  መራራ ትግል አካሄዶ ያመጣቸውን ለውጦች፤ሳይጠቀምባቸው ቀረ። አልተዘጋጀም ነበርና ! ባለመዘጋጀቱም ዕድሉን ለወራሪዎች አስረከበ። በቀጣፊዎች ተታለለ።  በብልጦች ተበለጠ። በእበለ- ባዮች ተጠለፈ።  ባለመንጠቀቁ ምክንያት ያገኘውን  ሕዝባዊ ድሉን ተነጠቀ።  
 ሁለቱ አገዛዞች፤  (የሆናሉ ተብሎ አልተገመተም እንጅ)፤  በዕርግጥም፤ ለሀገርና  ለሕዝብ አሳቢዎች ሆነው ቢሆን ኖሮ፤ የተገኘውን ለውጥ፤  ለራሳቸው  ከንቱ ሥልጣንና ክብር ማዋላቸው ቀርቶ፤ ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም አውለውት ቢሆን ኖሮ ፤  ታሪክ፤ ልዕልና የሚያጎናጽፋቸውን ክብር  ባገኙ ነበር።  ያ ሳይሆን  ቀርቶ፤    " ለአህያ ማር አይጥማትም  ! "   ሆነና፤ " ከአልጋ ሲሏቸው አምድ ላይ ተንከባልለው "  ቀሩ ።  ዛሬ እኛን የሚያስጨንቀን ፤ እነርሱ  አመድ መሆናቸው ሳይሆን፤ የሀገራችን ዕጣ -ፈንታ  አሁን ከደረሰበት ደረጃ መውደቁ  ነው ።   
ያልተደራጀ፤  ያልተዘጋጀ፤  ያልተጠነቀቀ፤ የልተባበረና ያልተሳሰበ ሕዝብ፤ የውስጥ አምባገነኖችና የውጭ  ባዕዳን ተጠቂ ከመሆን አይድንም።  የኛም ሀገርና ሕዝብ ፤ የዚህ ሁኔታ ተጠቂዎች ናቸው።  ከዚህ መከራ የሚወጡበት ብልኀቱ ጠፍቶባቸዋል ። መፍተሄው ተሰውሮባቸዋል  ። መፍተሄው ደግሞ ያለው በዕጃቸው ነው ። ጨቋኝ ሥርዓትን፤ በአመፅ ማሰወገድ የሚፍተሄው የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው ።  ይህ ምዕራፍ ካልተከፈተ፤ የተስፋው ጭላንጭል አይገኝም ። ያን ለማግኘት ደግሞ ፤ በመራራ ትግል ላይ  የተመሰረተ መሥዋዕት  መክፈልን ይጠይቃል። "ያለ መሥዋዕት፤ ስርዕየት አይገኝምና !  "    
የኛ ጭንቀት-ጥበታችን፤፤ ዕንቅልፍ ማጣታችንና  ቁጭታችን፤፤  ይበልጡኑ ከበድ  የሆነብን፤ ያ ሁሉ  መሥዋዕት ተከፍሎ፤  የሀገራችን  ኅልውና ዛሬ አጠያያቂ ሆኖ መቅረቱ ነው። የሀገሪቱ ታጋይ ሠማዕታት አልቀው፤ ምድረ ተገንጣይና አስገጣይ በለስ ቆንቶት ሀገራችንን ሲቆራርሳት ማየት ፤ ከምንችለው በላይ ሆኖብናል። ትግሉ መቀጠል አለበት የምንለውም ከዚህ መሠረታዊ  ዕምነት በመነሳት ነው 
የፋሺስት ኢጣልያ ወረሪ ሠራዊት፤ ከሀገራችን ከተባረረ ከ 1933  ዓም ጀምሮ  እስክ 1966 ዓም  ድረስ  የነበረው ትውልድ፤ ለመላው  የኢትዮጵያ ሕዝብ በለውለታው መሆኑን ተግንዝቦ፤ ከደረሰበት ችግር ለማላቀቅ፤ ከባድ መሥዋዕት ከፍሎ በለውለታ መሆኑን አስመስክሯል ። ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ፤  እየራበው ሳይበላ ፤ እየተራዘ ሳይለብስ፤ እየተጠማ ንጹህ ውሃ ሳያገኝ፤  ለህመሙ  ህክምና ሳያገኝ፤  መንገድና መጓጓዣ ሳይኖረው፤ ያን  ትወልድ፤ የመንግሥት ግብር እያከፈለ በነፃ አስተምሯል። ከአንደኛ ደረጃ  እስከ  ዩኒቨርስቲ ድረስ  አስተምሯል  ። በልዩ ልዩ የትምህርት ተቋማት በሚሰጠውን  ሙያ እንዲሰለጥን አድርጓል ። ጫማና ልብስ እየቸረ በአዳሪ ትምህርት ቤቶች  አስግብቷል ። ይኽ ሁሉ ሲኖን፤  እርሱ ራሱ ግን ከሙታን በላይ ከኅያው በታች  በሆነ ኑሮ እየኖረ ነበር። የገጠሬውን አስከፊ ኑሮ  በሚገባ የሚገነዘበው  ከገበሬው ጋር  የኖረ ብቻ ነው።
ይኽ ታላቅና ለጋስ ሕዝብ፤   ሳይተርፈው  የለገሰ ፤ ሳይኖረው የቸረ፤ ተብድሮ ያስተማረ፤  ቸር ሕዝብ ነው። ከድኅነት፤ ከረሃብ፤ ከበሽታና ከማይምነት  መላቀቀ አለበት ብሎ የተነሳው ፤ ያ ትውልድ፤ ውለታውን ለመክፈል ተንስቶ ሕዝባዊ ፍቅሩን   በመሥዋዕት አስመስክሯል   አንድ ትውልድ፤ ለሚወደው ሕዝቡ ሊከፍለው የሚችለውን  ከፍተኛ ውለታ የሚገልጸው፤ የህይወት ዋጋ እስከመክፍል ድረስ ነው።  ያ ትውልድ፡ ይህንን አድርጓል 
በ1966 ዓም  ታላቁ  የኢትዮጵያ አብዮት ሲፈነዳ፤ የህዝቡ ደጋፊ-ተሳታፊ ለመሆን፤ በመላው  ዓለም ሀገሮች ባሉ ዩኒቨርስቲዎችና  ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት  ሲማር የነበረው ወጣት ሁሉ ወደ ሀገሩ ተመለሰ።  ሕዝቡን ለማገልገል ።  ሀገርን ለመጥቀም ከያለበት ወደ  ኢትዮጵያ ጎረፈ።  ለሕዝብ ሲል እንደ ቅጠል ረገፈ።  ፀላዒ- ኢትዮጵያም ግን፤ ተደሰተ። ጮቤ ረገጠ። አንድ ትውልድ ሲመተር ፤ የሀገራችን ጠላቶች ዕልል አሉ !
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሲማሩ የነበሩ ጠባብ ብሄረተኞች ግን  የመላውን ሕዝብ ዓላማ በመክዳት ፤ ወደ ትግራይ በመሄድ ፤ ለዕኩይ ተግባራቸው ማስፈፀሚያ ተንኮለቸውን መጎንጎን ጀመሩ። ለዕቅዳቸው መሳካትም  የተፈጠረውን ግርግር ተጠቅመው ሀገራችንን ለመገንጠልና ለማስገንጠል በቁ ። ሰኔነና ሰኞም ገጠመላቸው። 
የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን፤ ይህ አደጋ የከሰታል ብሎ አላሰበም። የትግራይ ልጆቻችን ፤ ኢትዮጵያን ይከዷታል፤ ይጎዷታል፤  ይገነጥሏታል ብሎ አላሰበም ነበር።  የሆነው ግን ይኽ ነበር ! ባለመዘጋጀቱ፤ ተዘናጋ ። ባለመንጠንቀቁ፤  ተበለጠ ። ባለመደራጀቱ ተጠቃ ። መሪ ባለማውጣቱ፤ ድሉን ተነጠቀ።   ባለመተባበሩ ተዳከመ።  ተዳክሞ ስለአገኙት፤ ተገንጣይ-አስገንጣይ ግባቸውን መቱ።
ከአምሳ ዓመታት በኋላስ ዛሬ ሀገራችን በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለች? ያለችበትን ተጨብጭ ሁኔታ ሁሉ ዜጋ ስለሚያውቀው  ፤ መልሱን ለመዘርዘር፤ አስፈለጊ አይሆንም። ግን አንዳንድ ኩነቶችን  ለማስገንዘብ   ግድ ሊሆንብን ነው።
1ኛ.  ሕዝባችን፤ ዛሬም  እንደትላንቱ፤ በብቃት ተደራጅቶ፤ የተቃጣበትን የኅልውና አደጋ ለመከላከል  በሚችልበት ደርጃ ላይ አይደለም ።
2ኛ.  ለምን የሚባሉትን  ምክንያቶችን፤ በጥልቀት፤ መመርመርና መፍተሄ መፈለጉ ይዋል ይደር የሚባልበት አልሆንም። የመፍተሄው ፍልጋ ሂደት ግን ፤ ለወቅታዊ ስብስባ ፍጆታና ከየግል ድርጅቶች ጠቅሜታ በላይ ሊሆን ይገባል 
3ኛ.  ዞሮ ዞሮ፤ የፖለቲካ ጥያቄ የሚፈታው፤ ሰጥቶ በመቀብልና ተናግሮ በማዳመጥ፤ ተቻችሎ በመግባባት ፤ እንጅ፤ ጥሎ በማለፍ፤  ገጭቶ በመጥለፍ፤  ሮጦ  በመቅደም፤ በብልጣ -ብልጥነት አይደለም ፡ ይህ ሁሉ እስካሁን ተሞክሮ ፋይዳ አላመጣም ።    ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ፤ የመጨረሻው ወሳኝ ግን ፤ የኃይል ሚዛን ጉዳይ  ነው ተብሎ ይገመታል።
4ኛ. የሀገርንና የሕዝብን ታማኝነት ማዕከል  ያላደረግ ማነኛውም እሳቤና  ድርጊት የትም  አያደርስም   በመላዕክት ቋንቋ እየተናገሩ፤ የአጋንንትን  ድርጊት መፈፀም፤  የሕዝብን ርግማንና ጥላቻ ከማትረፍ በቀር  እርባና  የለውም 
 5ኛ.   ቀደምቱን  የትግል ታሪክ ፤  እያጣጣሉና እያንኳሰሱ  መገኘት ብቻውን ለአዲሱ  ትውልድ ማስተማሪያ አያገለግልም። አፍራሽ ሚና ግን ይጫወታል ።ወገንተኛ የሆነ ሁሉ አፍራሽ ሚና እንዲጫወት አይጠበቅበትም 
5ኛ  " ጠላቱን በሚገባ ያወቀ፤ 100 ጦርንቶችን ሳይቸነፍ  መዋጋት ይችላል ።"   እንደተባለው፤   የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ዕውነተኛ  ወዳጁንና ጠንቀኛ ጠላቱን አውቆ   ካልተረዳ፤ ምን ጊዜም ቢሆን፤ የተሟላ ነፃነቱን አያገኝም ። መጀመሪያ  ራስን ማወቅ፤ ጠላትን ለማወቅ ይጠቅማል ።
6ኛ.  ለሕዝብ ያልቆመ ፤  ለኢትዮጵያ ያልሆነ፤   በሕዝብ የተተፋ  ሥርዓት፤  በሕዝባዊ አመፅ መደምሰሱ አይቀሬ ነው። ድምሰሳውን ለማጣደፍ ግን ፤ በብቃት ተደራጅቶ መገኘት ወሳኝ መሆኑ መረሳት የለበትም ።
ወያኔን  ለማስወገድ ፤ ተባብሮ ከመታግል የተሻለ አማራጭ  የለም!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኖራለች  !
         


No comments:

Post a Comment