Friday, June 24, 2016

የፖለቲካ አክሮባት አቅጣጫን ለማሳት፤ የፕሮፓጋንዳ ግብዐት፤ ውሸትን ለመንዛት ፤ ( የፍኖተ ራዲዮ ወቅታዊ ሀተታ )


የፖለቲካ አክሮባት አቅጣጫን ለማሳት፤
የፕሮፓጋንዳ ግብዐት፤   ውሸትን ለመንዛት
ባለፈው ሳምንት፤ እንደልማዳቸው፤ የሻዐቢያና የወያኔ አበጋዞች፤ የፕሮፓጋንዳ ኩዴታ አካሂደው ጊዚያዊ ውዥንበር ለመፍጠር ሞክረው ነበር ።  ሊወናበድ የሚፈልገው ሁሉ  ስለተወናበደላቸው ፤ ምናልባት ፤ ጊዚያዊ  ስኬት እንዳገኙ  ቆጥረውታል።  ሆኖም፤ ከሰሞነኛ ወሬ ሊያልፍ የሚችል እርባና ግን አላመጣላቸውም። የሁለት  ወንድማማች ዜጎችን  አብሮነትን  በማፋለስ የአካባቢ ሠላምና መረጋጋት እንዳይኖር ማድረግ፤ ከሕዝብ የሚመጣባቸውን አደጋ ለመከላከል ይረዳናል ብለው አስበው ከሆነ፤ ያም፤ አልተሳካላቸውም ።  ዜጎችን  እያጋጩና እያለያዩ  መቀጠል  ለሥልጣናቸው  ማራዘሚያ ዘዴ ሊጠቀሙበት  መከጀላቸው እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አልነበረም።  ሻዕቢያዎቹ 200  የወያኔ  ወታደሮች ገድለን፤  ከሦስት  መቶ  በላይ  ወታደሮችንም  አቁስለናል   ብለው  ቢለፍፉም ፤  ወያኔዎቹ ግን   " በቆረጣ ውጊያ የሚችለን የለም። " ከሚሉት የጉራ ደንፋታ ያለፈ መግለጫ ሲሰጡ አልተደመጡም።
 በቆረጣ ውጊያ፦---
 ደርግን ወግተነዋል።
ሻብዕያን፤ አግዘን ጀብሃን ገጥመነዋል ።
በፕሮፓጋንዳውም፦
ዐረቦች ነን ብለን ዐረብ አታለናል።
ምሥራቁን ሸውደን  ለምዕራቡ ሰግደናል፤
የዐማራን ቅስም ሰብረን፤  ደቡቡን  ገዝተናል ።
በፖለቲካውም፦-
"ሀገር ተወረረ፤ ብለን ቀልደናል፤
 ዳር ድንበር ተጣሰ፤ ብለን ሸውደናል፤
 ክተት አዋጅ ! ብለን  ህዝብ  አጭበርብረናል፤
 ሀገር  ለማታለል ብቃት አሳይተናል፤
የመጣው ቢመጣ ማን ያስለቅቀናል ?
ምዕራቡ እያለ፤  ማንስ ይደፍረናል ?
     ይልቅስ፤
ሰጥ ለጥ ብለህ  ብትኖር ይሻለሃል ። "
በሚል ሥነልቦናዊ ህዋው ውስጥ  በሚኖሩ ገዥዎች ስር ያለች ሀገር ሆናለች ።  የዛሬይቱ ኢትዮጵያ !

 ሆነም -ቀረ፤ በሁለቱም ወገን የሚያልቀው ዜጋ፤ ሁላችንንም ያሳዝነናል።  ያሳስበናል። ያስቆጨናል። ያለፈው ደም መፋሰስ ይበቃ ነበር ! ሁለቱም፤ ወንድማማች  ሕዝብ ናቸው። የልጆቻቸውን ሬሳ እየቆጠሩ- እየቀበሩ ሊኖሩ አይገባም። ወደፊት በአብሮነት የተሻለ ዕድል ፤ ሠላምና  ብልፅግና  ይጠብቀናል ብለው  ይመኛሉ። ይጠብቃቸዋልም !  ያላስፈላጊ  ጦርነትና  ዕልቂት ፤ መቆም  ይገባዋል !  ይኽ የቆየ ርግማን ፤ አንድ ቦታ መቆም አለበት።  ጦርነትና ፍጅት፤ ለሚቀጥለው ትውልድ ሊተላለፍ ከቶ አይገባውም !
በአካባቢያችንም ሠላምና ፀጥታ ሰፍኖ ዜጎች መልካም ህይወትን እየኖሩ እንዲኖሩ እንፈልጋለን።  የዚህ ፍላጎታችን መሠረቱ ግን  የዴሞክራሲ  ሥርዓት መስፈን እንደሆነ እናውቃለን። ያ ደግሞ እስካሁን ደረስ ዕውን ሊሆን አልቻለም ።  ሊሆንም አይችልም ። ምክንያቱም፤ በሁለት አምባገንን ሥርዓቶች  በሥልጣን ለመቆየት መርበትበት  ምክንያት፤ የሚደረገው ጥፋት፤ የዴሞክራሲን ሥርዓት ለማምጣት ስለማይችል ነው።  አምባገነን  ሥርዓትን፤ ሁሉም ዜጋ  የሚያወግዘው  ነው።  የሚያውግዙት ሁሉ ግን ፤ በውግዘት ብቻ አይወገድም።  ውግዘት፤ ማስወገድን  ካላስከተለ፤ የሚያወግዙት ሁሉ፤ እንዲሁ አይጠፋም። የሚያወግዙትን ካላጠፉ ደግሞ፤  የገዥዎች ፕሮፓጋንዳ ሰለባ እየሆኑ፤ መኖር ነው። ያ ደግሞ፤ መኖር ሳይሆን፤ ህይወት ዐልባ መሆን ነው። ህይወት ዐልባ ከተሆነ፤ ታዲያ፤ ለተተኪው ትውልድ፤ ማን፤  ምን  ማውረስ ይቻላል ?  ኢትዮጵያ፤  አውራሽና ወራሽ፤  አስረካቢና ተረካቢ፤ የሌላት ሀገር  እየሆነች  መምጣቷ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል ።
 " ሙታንን፤  ሙታን ይቅበሯቸው"  እንዳንባል፤ ገዳዮቹን አጥፍተን ፤ ሀገራችንን ኢትዮጵያን  በህይወት እንድትኖር ማድረግ አለብን  !
ከጎጅ ሥርዓት ለመገላገል ሲባል፤ ሀገሩን እየጣለ የሚሄደው ወጣት ሁሉ፤ ገሀነመ-ዕሳት ውስጥ እየገባም ቢሆን፤ ስደትን መርጧል።  ባለፈው ሳምንት ብቻ ቁጥራቸው  በውል ያልታወቀ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች፤ በዕቃ መጫኛ የጋለ በርሜል  (Container)  ውስጥ ተደብቀው በመግባት ለማምለጥ ሲሞክሩ፤ ታፍነው መሞታቸው የዓለም ዐቀፍ የዜና አውታሮች መርዶ አሰምተዋል። ይህ መርዶ  የተሰማው በአንድ አካባቢ ስለሞቱት ወጣቶች ብቻ እንጂ፤ በተለያዩ አካባቢዎች፤  ተመሳሳይ አደጋ የሚያጋጥማቸውን ኢትዮጵያውያንን ቁጥር ማወቅ ከቶ፤  የሚቻል አይደለም ።  
ይህ አሳዛኝ ዕድል ፤ በኤርትራውያን  ወጣቶችም  ላይ  እየተፈፀመ  እንደሆነ  የዘወትር  መርዶ  ( መርድዕ ) መሆኑ  እንደቀጠለ ነው ።  የሀዘናቸው   ተካፋዮች  ነን ።  ወንድሞቻችን-  እህቶቻችን  ናቸውና ! ሻዕብያዎቹ ፤ ይህንን ሲሰሙ ፤ " አብ ሀውይ እተው !   "  ዕሳት ወስጥ ግቡ "  እንደሚሉ  ይሰማናል ። ከእነርሱ፤ ከዚህ የተሻለ አይጠበቅምና  አንገረምም !   ረጋሚዎቿ  እየረገፉ፤ ኢትዮጵያ  ግን ፤ ዘለዓለማዊት ሀገር መሆኗን  ትቀጥልበታለች  !
 ይኽንን የወጣቶችን  ህይወት  መጥፋትም ሆነ፤  ሌሎች ተመሳሳይ  ወንጀሎችን ለመደበቅ ታስቦ፤  የወያኔና የሻዕብያ ተላላኪዎች፤ ባለፈው ሣምንት፤ በናይሮቢ  ከተማ፤ ከአንዲት የኬንያ ቴሌቪዚዮን ጋዜጠኛ ጋር ቃለ- ምልልስ ተለዋውጠዋል።  የተጠየቁትን መመለስ አቅቷቸው፤ እጅግ በሚያሳፍር መልኩ ያልተጠየቁትን ሲቀባጥሩ ታይተዋል። እንኳንስ ተመልካቹ፤  ጋዜጠኛዋም ሳትቀር፤ አፍራለች።   "አምባሳደሮች "  ናቸው ተብለው የቀረቡት እነኝህ ሁለት ሰይፈ-ጃግሬዎች፤ የዲፕሎማት ስብዕናም ሆነ የዲፕሎማቲክ ችሎታና ዕውቀት  እንደሌላቸው  በግልፅ አሳይተዋል ።  የዲፕሎማቲክ ቋንቋም ሆነ አነጋገር ሳይሆን፤ የካድሬ  አብዚሎ - ቀብዚሎ ፤ ጫጫታ አሰምተው ነው  የሄዱት ። እንኳን ሌላው ቀርቶ፤ አለቆቻቸውም ሳያፍሩባቸውም አልቀሩ ። ምክንያቱም እነርሱንም ሳይቀር አጋልጠዋቸዋልና !
 
 " አስቀድሜ ባለማወቄ ፤ ነው። "  ወይም፤  " ሌሎች አሳስተውኝ  እኮ ነው  ። " የሚል ሰበብ፤ ከታሪክ ተጠያቂነት አያድንም ።  በታሪክም ሆነ፤ በህግ ፊት፤ ሁሉም በየፈርጁ የየግል ተጠያቂነት አለበት። በስውርም ሆነ በግልፅ፤ በጋሪዮሽም ሆነ በግለሰብ፤  በመንግሥት ደረጃም ይሁን፤  በግል  የሥልጣን ሽፋን የተፈፀመው  ወንጀል ሁሉ፤ ጊዜው ሲደርስ መጋለጡ አይቀርምና፤ ከሕዝብ ቁጣና ቅጣት ማምለጥ አይቻልም ። ታዝዤ- ተገድጄ  ነው ይህንን ወንጀል የፈፀምኩት ማለት አይቻልም ። አዛዡም -አስገዳጁም ፤ ከተገደደውና  ከታዘዘው  ጋር ሆኖ፤ በአንድ ቁና አብሮ  መሰፈሩ አይቀርም ። ይኽ ደግሞ ፤  የህግ ፍልስፍና  መሠረታዊ መርህ ነው። 
የዛሬ 26 ዓመት በሎንዶን ከተማ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በስተጀርባ የተፈፀመው፤ ሀገራዊ ክኅደት፤ አሁንም፤ በአደገኛ ሁኔታ ሀገራችንን እያጠፋ ይገኛል። ወንጀሉም እንደቀጠለ ነው። የሎንዶኑን ጎባዔ ያዘጋጁት በዕዳንና ተባባሪዎቻቸው፤ ሀገራችንን ወደጥፋት  አዘቅት እንደጨመሯት አልተገነዘቡትም። ጉዳያቸው አይደልምና ! ኢትዮጵያ ሀገራችን እየተጠራሞታች ብትሆንም፤ ጨገሬታው ግን አለ። ዕስትንፋሷም በቀላሉ ፀጥ የሚል አይደለም። ኣጥፊዎቿ ግን እየጠፉ ናቸው።  ማስረጃ ፦
1 በ1960 ዎቹ (እ አ አ) የግብፅ መሪዎች ፦  ጋማል አብደል ናስር፤ አብደል ሀኪም ዐመርና አንዋር ኤል ሣዳት  ካይሮ ላይ ተገንጣዮቹን ስብስበው  ጀብሃን መስርተው ኤርትራን  ለማስገንጠል መሠረት ጣሉ። እነርሱ ግን ጠፉ። ለጥቂት ጊዜያት በካይሮ ሥልጣን ጨብጠው የነበሩት የሙስሊም ወድማማቾች በገሃድ በኢትዮጵያ ላይ ሲዶልቱ በቴሌቪዥን መስኮት ታይተው የነበሩት ባለሥልጣናትም የዚሁ እጣ ተካፋዮች ሊሆኑ በቅተዋል።  ሀገራቸው  ግብፅም፤ ዛሬ በምን ሁኔታ እንደምትገኝ  መዘርዘር የለብንም ። ለሁሉም ግልፅ ነውና !
2.  የሊቢያው መሪ የነበረው ፤ ሙዐመር ኻዛፊ በበኩሉ፤  ኢትዮጵያ እንድትዳከምና ኤርትራ እንድትገነጠል እድሜውን ሙሉ ድክሟል።  በመጨረሻ ራሱን ማዳን አቅቶት ተዋርዶ ጠፋ። አይሞቱ- ሞት፤ ሞተ ። በተለይ ደግሞ፤ ሻለቃ አብደል-ሠላም  ጃሉድ የተባለው የካዛፊ ምክትል የነበረ ሰው፤ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ፤ ጉዳዩን በቅርብ  የተከታተለው ሁሉ የሚያውቀው ነበር።   ሊቢያም ዛሬ እንደ ሀገር መቅጠል አቅቷታል። ሕዝቧም እርስ በእርሱ  ከመፋጀቱ ሌላ የክርስትና እምነት ባላቸው የግብፅና የኢትዮጵያ ስደተኞች ለአንገት መቀላት መዳረጋቸውም የሚታወስ ነው።  
3. ኢራቅና ሦርያ ፤ ኢትዮጵያን በመጎዳት በኩል ተዘርዝሮ የማያልቅ በደል ፈጽመዋል ።  ተገንጣዮቹን፤  በማሰልጠን፤- የደፈጣ ውጊያ  በማስተማር፤ የገንዘብ፤ የቆሳቆስ፤ የዲፕሎማቲክና የፖለቲካ ርዳታ ሁሉ ለግሰዋል።  ዛሬ ሦርያና ኢራቅ ያሉበትን ሁኔታ ዓለም ሁሉ ስለሚያውቀው ፤ ያንን በመዘርዘር  መድከም የለብንም።
4. የቀድሞዎቹ የየመን መሪዎችም፤ አቅማቸው  የፈቀደላችውን ሁሉ በማድረግ ፤ ለኤርትራ ተገንጣዮች ትብብር አድርገዋል። ዛሬ የመን እራሷ እንደ ሀገር መቆየት እንኳ አልቻለችም 
5. ሳውዲ ዐረቢያ ፤ ኻታር፤ ዐረብ ኢሚሬት ፤ ኦማን፤ ባኅሬን፤ የፔትሮ ዶላር ሀብታቸውን ለኤርትራ መገንጠል አፍስሠዋል። ሀገራችንን ጎድተዋል ። ይዘገያል እንጅ በሰፈሩበት ቁና መሰፈራቸው ግን አይቀርም 
6.  ጎረቤታችን ሱዳን  በበኩሏ፤ ኢትዮጵያ እንድትበታተን ያደረገችውን ሁሉ ለመዘረዘር ቦታ አይበቃንም ።   " በመስታዎት ቤት ውስጥ የሚኖሩ፤ ድንጋይ ለመወርወር ፤ የመጀመሪያዎቹ መሆን የለባቸውም፡፡ "   የሚለውን ይትብኃል ባለማወቃቸው፤  የሱዳን  መሪዎች ደቡብ ዱዳን ሲገነጠል ዐይናቸው ጉድ አይቷል ። የምሥራቁን ግዛታቸው  ዳርፉርን መቆጣጠር አልቻሉትም ።  ኢትዮጵያን ያስገነጠሉ ሁሉ እነርሱም መገንጠላቸው አይቀርም  !
ይኽንን ሁሉ የምንጠቅሰው፤ "ኢትዮጵያን የበደሉ/የሚበድሉ ሁሉ ዋጋቸውን ያገኛሉ።" ከሚል የግብዝነት-ስሜታዊ አነጋገር " እንዲመስል አይደለም። ሀገራችንን ከውጭ የሚቃጣባትን ጥቃት ለመከላከል እስካሁን ድረስ የረባ ሥራ አለመፈፀማችንን ለመጠቆም ነው።  ወደፊትም፤ በዚህ አኳያ የሚጠብቅብንን መፈፀም ካልቻልን፤ የቀረችዋን ኢትዮጵያን ለማዳን ምንም ዋስትና እንደሌለ፤ መረዳት ይገባናል። ስለ አለፈው ምፀት ብቻውን ዋጋ አይሰጠንም።  " ያለፈው ቅራና ፤ የሚሚጠው መጭኛ " መሆኑን መርሳት አይገባንም ።
የወያኔ የነፈሰበት ፕሮፓጋንዳ  ቲያትር፤ ፤ የተበላ ዕቁብ ፖለቲካ ጨዋታ ፤ ብዙ ምዕራፍ የማያስኬድ  መሆኑን ተረድተን፤  ኃይላችንን በማስተባበር የአገዛዙን አምባገነናዊ ሥርአት ማስወገድ መቻላችንን በተግባር ማሳየት አለብን።
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኖራለች  !             
 
                 
         

No comments:

Post a Comment