Friday, July 8, 2016

ባለፈው ታሪክ ብቻ የሚኖር ፤ በወደፊቱ ላይ ማተኮር ይሳነዋል ! በፍኖተ ሬዲዮ የተነበበ

                   
ባለፈው ታሪክ  ብቻ  የሚኖር ፤
                                በወደፊቱ ላይ  ማተኮር ይሳነዋል  !

   ኢትዮጵያ፤ እንደማነኛውም  ሀገር፤ የራሷ መጥፎም ሆነ መልካም ታሪክ  ነበት/ አላት።  የጥቃትና የድል፤ የጥጋብና ረሀብ፤ የስፋትና የመጨራመት፤  የመከራና ሀሴት ዘመናት ሁሉ ተፈራርቀውባታል ። የተለያዩ ሥርዓተ- ማኅበራትንና ገዥዎችን ሁሉ አሳልፋለች።   ድንበሯ  ያልተደፈረ ፤ ታሪኳ የተከበረ ፤  ላዊነቷ  ያልተገሰሰ ፤  የንግድ መናሃርያዋ ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ  የተዘረጋ፤ ኃያል ሀገር ነበረች ።  የጦርና  የንግድ  መርከቦቿም   በውቅያኖሶችና  ታላላቅ  ወደቦች  ይንሳፈፉ ነበር። ያ ሁሉ ዛሬ፤  ነበር ሆኖ  አልፏል ! " የነበር ሲያወሩት ይመስላል ያልነበር፤ የኢትዮጵያ ጠረፍ ውቅያኖስ ነበር !  " እያሉ መናገር፤ የዕለት -ተዕለት ቁዘማ ሆኖ ቀርቷል !  ታሪካዊና ነባራዊ ሀቆች ግን እነኝኽ ናቸው ! 
ዜጎቿም በነኝህ ተፈራራቂ ሥርዓተ- ማኅበራትና ስልተ-ምርቶች ሂደት ተጉዘዋል። ያም ሁሉ ሆኖ እስካሁን ደረስ፤ የራሳቸው ዕድል ባለቤቶችና ወሳኞች አልሆኑም። በዚህ በያዝነው 21ኛው ክፍለ-ዘመን  እንኳ፤ የዴሞክራሲ ጭላንጭልን  ሊጎናጸፉ አልቻሉም ።  የነፃነትና ፍትኅ-ርትዕ  ዕጦት አሉባቸው። የጉስቁልና ኑሮ የህይውታቸው መቆያ፤ ረሀብና ስደት፤ የማንነታቸው መለያ መሆኑን ድፍን  ዓለም አውቆላቸዋል ።  እነርሱ ግን ወዴት እንደሚሄዱ ብቻ ሳይሆን፤ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እንኳን የተገነዘቡት አይመስልም።
ርሃብን  በስደት፤ ጭቆናን  በሽሽት፤ ድኅነትን በምፅዋዕት፤ ቁጭትን  በብስጭት፤  እያፈራረቁ ማስተናገድ፤ ዘላቂ መፍሄ አላመጣልንም ። ለችግራችን ሁሉ ማስወገጃ የሚሆን መድሃኒት ለማምጣት፤ ቆራጥ ውሳኔ ለመውሰድ  ፤ እስካሁን አልተሳካልንም ። ሌላው  ዓለም ፤ የየራሱ ችግር ስለአለበት፤ ከችግሩ ለመውጣት ፍጨረጨራል እንጅ፤ ስለ እኛው ችግር ለማስብ፤ ጊዜውም፤ ደንታውም፤ ላጎቱም  የለውም ። ማነኛው ሀገር፤ ለሌላ ችግር ቅድሚያ አይሰጥም ። ለራሱ እንጅ !
 እኛው በኛው፤ ለእኛው መፍሄ ካላገኘን፤ ስለኛ ሆኖ ለኛ አስቦ፤ የኛን ችግር የሚፈታልን ሌላ ማን እንደሌለ አውቀን፤ ቆርጠን  መነሳት  አለብን ። ዕድያችን ሲደርስ፤ የናታችንን ጡት መጥባት ቆርጠን እንዳምነው ሁሉ፤ በውጭ ርዳታ፤ ችግራችን ይቆረጣል የሚለውን ምኞት ቆርጠን መጣል አለብን!  የራሳችንን ችግር ራሳችን ፈችዎች መሆናችንን ካስመስከርን፤  ዓለም ሁሉ ያከብረናል ። በየጊዜው ከ 10 እስከ 20  ሚሊዮን ረሃብተኛ ሕዝብ እያመረትን፤  ምፅዋዕት ጠያቂዎች  መሆናችን  ግን ያስንቀናል እንጅ አያስከብረንም ። ከ 1966 ዓም ጀምሮ፤  እስከ ዛሬ 2008 ዓም  ድርስ ያለው ዘመን ታሪካችን፤ የረሃብተኛ ዜጋ  ፈጣሪዎች  እንጅ፤  የኢዱስትሪ ውጤት አምራች አላደረገንም ። አሁንም ይህ ችግራችን እንደቀጠለ ነው።  በውቅቱ ያለው ዘረኛ አገዛዝም፤ ተግባራዊ ፖሊሲዎቹ እንደሚያመላክቱት የችግሩ ምንጭና አባባሽ እንጅ፤ የመፍሄ አካል ሊሆን አይችልም።
ኢትዮጵያ ሀገራችን ፤ ወዳጆቿን እያጣች፤ ጀግኖቿን እያጠፋች፤ አጥፊዎቿን እያነገሰች ፤ ዐርበኞቿን እየቀበረች፤ ቀባሪዎቿን  እያቀፈች፤ ልጆቿን  አስከፍታ እያሰደደች ፤ ራሷ ግን፤ ቀስ በቀስ፤ በሂደት  የምትጠፋ ሀገር ሆናለች !  እስከ  መቼ ?   
ኢትዮጵያ፤  በራሷ ዜጎች ፍላጎትና ውሳኔ  ላይ የተመሠረተ  ኢትዮጵያዊ  ሥርዓተ-  መንግሥት እስካላገኘች ድረስ፤ ሁልጊዜ ሕዝቦቿ፤ በዕርጎ ባኅር እየዋኙ ከመኖር በቀር ሌላ ተስፋ አይኖራቸውም። ኢትዮጵያዊ መንግሥት ማለት፤ በትውልድና በዜግነት  ብቻ ኢትዮጵያውያን የሆኑ መሬዎች የሚመሩት መንግሥት ማለት ሳይሆን፤ መሪዎቿ፤ የሀገርንና የሕዝቡን ሁለንተናዊ ጥቅም ጠብቀው የሚያስጠብቁ ፤ የሀገርን ክብር አክብረው የሚያስከብሩ፤  ለሀገራቸው ነፃነትና ሉዐላዊነት የሚሰዉ ማለት  ነው ። 
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  የተፈራረቁ  " መሪዎች " ፤  ይህን   መስፈርት   አሟተው   አልተገኙም ። " መወለድ ቋንቋ ነው ። "  እንደሚባለው ፤ ዜግነት ብቻውን፤ ኢትዮጵያዊ  መንግሥትን  ለመምራት ብቁ አያደርግም ።    በሰው ልጆች ታሪክ ሂደት፤  በሕዝቦች ላይ በተለያዩ ስሞች ብዙ ግፎች ተፈፅመዋል ። በሥልጣኔ ስም ፤ በይማኖት ስም፤ በሶሻሊዝም ስም፤  በብሄር ነፃ አውጭ ስም   ተዘርዝሮ የማያልቅ ግፍና በደል፤ በሕዝቦች ላይ ተፈፅሟል። ኢትዮጵያም በልዩ ልዩ ስሞች ብዙ   ተቀብላለች ። ኅልውናዋ አደጋ ላይ እስኪወድቅ ድረስ  አያሌ ፈናዎችን አልፋለች ። ዛሬም ከዚህ አደጋ አልወጣችም።
 የኦቶማን ኢምፓየር፤ በግዛት ማስፋፋት ሰበብ፤ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሞክሯል። ግብፅና ሱዳን ተባብረው በዐባይ ወንዝ ምክንያት ፤ የሀገራችንን ኅልውና ተፈታትነዋል።  ያ፤ ጠንቅ  አሁንም አልጠፋም።  ምዕራባውያን በበኩላቸው፤ ( እንግሊዝ፤ ፈረንሳይ፤ ጣሊያን) ኮሎኒያሊስቶች  ተባብረው፤ ኢትዮጵያን፤ በመቀራመት ከአፍሪካ  ካርታ /ገፅ  ለማጥፋት ከፍተኛ ጥርት አድርገዋል።   ደርግ በሶሻሊዝም ስም  በሀገርና በህዝብ ላይ የፈፀመውን ወንጀል ለመዘርዘር የዚህ ሐታታ መነሻ አይደልምና  በዚያ ላይ አናተኩርምም ።  ወያኔ እንኳ በዐቅሟ፤ በብሄር ነፃ አውጭ ስም ፤ የቱን ያኅል ብሄራዊ ጥፋት አያደረገች እንደሆነ ለመዘርዘር አይሞከርም ። ውቅያኖስን በጭልፋ ይሆናልና!  ሁሉንም ፤ ለታሪክ መዝጋቢዎችና ለዜና መዋዕል ፀሀፊዎች   ትተነዋል ።
በዚህ አንቀጽ  የተዘረዘረው፤ ለጥቅሻ ያኅል የሀገራችን ታሪክ አካል መሆቅሰን  ማለፍን መርጠናል ።  ሌላው ቢቀር፤ለአሁኑ ትውልዱ  ግንዛቤ ይረዳል ብለን እንገምታለን።  ይኽ ሀቅ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን፤  በከፉም ሆነ በደግ  ገፅታው፤ባለፈ  ታሪክ ላይ ብቻ ትኩረት እያሰጡ  መኖር ፋይዳ ቢስ ነው ።  ባለፈ ታሪክ  ብቻ፤ መኖር፤ መቀጠል፤ መራመድ ፤ መበልፀግ፤ ማደግ፤ መከበር፤ መገስገስ አልቻልንም።  በታሪክ  እሳቤ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ፤ ያሁኑን ሁኔታ ከመጨው ጋር  እያጣስን መራመድ ያዋጣናል ። 
 ለዘመናችን ታሪክ  መመዝገብ ያለብን፤ በዚህ ዘመን የምንኖር  ዜጎችና ትውልድ ብቻ ነን ። በቀደምት፤ ጀግኖች፤ ዐርበኞች፤ ሠማዕታት፤ ደሲያን፤ መዘምራን፤  ወዘተ..  ታሪክ ሰሪነት ብቻ እተኩራን ከቀጠልን፤ አዲስ ጀግና፤ መሪ፤ ማውጣት  የሚቸግረን ይመስለናል።  በዘመናችን አዳዲስ ግኖች ለማውጣት ግን ቀደምት ጀግኖቻችንን ማክበርና ማወድስ  ተገቢ  ነው ። ቀደምቶችን ካለከበርን ደግሞ፤ አዳዲስ ጀግኖች ማውጣት ይቸግረናል ። "ኢትዮጵያ፤  አንድ መቶ ዓመት ታሪክ የሌላት ሀገር ነች " የሚሉ ገለሰቦች፤ ከሚገዟት ሀገር የሚያድግ ትውልድ፤ እንዴትስ ብሎ አዳዲስ ጀግኖች ማውጣት ይቻላል ? አዲስ ጀግና ለማውጣት፤ የቆየ ኣርዓያን ማግኘት ይጠይቃል   
 አሁን ያለው ትውልድ፤ ልተማረውን  ዕውነተኛ ታሪክ ፤ ከየት አምጥቶ፤ ሊያውቅ ይችላል ? ጀግናን፤ በአርዓያነት ሊቅስ ካልቻለ፤ እንዴት አድርጎ ነው  የራሱን   ጀግና  የሚያወጣ ? የራሱን  መሪ ፈጥሮ - አውጥቶ  ካልመረጠ  ፤ መሪ  ማን  ሊሰጠው  ይችላል?  " ሀገ  ኢትዮጵያ ፤ የደጋጎች  ምድር  ነበረች  "  የሚል የሕዝብ  ዕምነት ቢኖርም፤ ዛሬ ደጋጎቹ ስለሌሉ ፤ ኢትዮጵያዊ ሙሴን  በመሪነት የሚሰጣቸው አላገኙም።  ኢትዮጵያውያን ፤ ያላቸው ምርጫ፤  የሚሆነው አንድ ብቻ ነው ። እራሳቸው ተስማምተው፤ የራሳቸውን ኢትዮጵያዊ መሪ ማውጣት ብቻ ይሆናል ። ይኽንን ጥረት  ግን እስካሁን አልሞከሩትም።   ይኽንን  ሞክረው  ውጤት  ካስመዘገቡ ግን  የችግራቸው  መወገጃ ፤  የመፍትሄያቸው  የመጀመሪያ ምዕራፍ ፤  ይሆንላቸዋል ።
አዲሱን  ምዕራፍ ለመክፈት ፤ አንድ  የተጋረደባቸውን  ደንቃራ  መስበር አለባቸው ።  እርስ በእርስ መነታረካቸውን ማቆም አለባቸው። አንዱ በሌላው ላይ ማሳበብ  መፍሄ አላስገኘም እስካሁን ! ጎይቶም በጌታቸው፤ በለጠ በጭላ፤ ጫልቱ፤ በማሚቱ እያመካኙ አብሮ መኖር አይቻልም ። የጋራ መሪ ለማውጣት፤ አስቀድሞ የጋራ ችግርን በጋራ የማስወገድ ችሎታ እንዲኖር ግድ ነው።         
 ይኽንን በቅጡ ከተገነዘብን ፤ ጀኔቫ ሂዶ ሰልፍ መውጣት ፤ ኒውዮርክ መጥቶ አቤቱታ ማቅረብ፤ የዕልፍ አዕላፍ  ፊርማዎችን ሰብስቦ ፔቲሽን ማስፈረም ፤ ቅንጣት ያኽል መፍትሄ አያመጣም ። "የጨነቀው ነፍስ-ጡር  ያገባል። "  እንደሚባለው፤  የሚይዙት የሚጨብጡት በማጣታቸው ምክንያት፤ ሻዐቢያ ነፃ ያወጣናል  የሚሉ ክፍሎች መኖራቸውን ታዝቦ፤  የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤ "  ይህንን ሊያሰማኝ  ነው እንዴ ፤ ሲቃዠኝ ያደረው ? " ብሎ አሹፎባቸዋል ።  
" በተመሳሳይ ሁኔታና የጊዜ አጋጣሚ፤ ታሪክ ራሱን ይደግማል። "  እንደሚባለው፤ ፤ ቤኒቶ ሙሶሊኒ፤  ኢትዮጵያን ለመውረር ምክንያት ካደረጋቸው  ማጠየቂያዎች  አንዱ፤ " አቢሲኒያን   ከባርነት  ነፃ  ለማውጣት ነው ። " የሚል ዲስኩር / ፕሮፓጋንዳ  ነበር ። ከ70 ዓመታት በኋላም ዛሬ፤ " ሻዕቢያ ፤  የኢትዮጵያን  ሕዝብ ነፃ  ያወጣል "  የሚሉ ፕሮፓጋንዲስቶች  ተፈጥረዋል።  ዕድሜ ዘልዛላ ነው ፤ የማያሰማው ጉድ የለም ! እስቲ  እናያለን፤ ሻዐብያ ኢትዮጵያን ከወያኔ አዛዝ ነፃ ሲያወጣት !    
ያም ሆኖ፤ ግን በአለፈው አኩሪ ታሪካችን  ብቻ  እየተፅናናን መኖርን  መርጠናል ።  " የኋለኞቹ  ወደፊት ፤ የፊተኞቹ  ወደ  ኋላ " እንደሚባለው፤  በኋላቸው የነሩ ሀገራትና ሕዝቦች  እየቀደሟቸው ሲራመዱ ፤ እነርሱ ግን  ባሉበት መርገጣቸውን ብቻ ሳይሆን፤ ወደ ኋላ መቅረታቸውን እንኳን አልተገነዘቡትም ።  ይህ አልበቃ ብሏቸው፤ ዛሬማ ፤ ይባስ ተብሎ፤ በማንነትና ኅልውና ጥያቄ መካከል የሚኖሩ ሰዎች ሆነዋል ።  ኢትዮጵያውያን/ ያት!
 " ነኝ፤ ወደ ነበርኩ፤ እየተለወጠ ብቻ ሳይሆን፤ አለሁ፤ የሚለውም ወደ አልቦነት እየተለወጠ በመሄድ ላይ ነው።   ሀገር ሲያረጅ ጃርት ያበቅላል ።"  ሆኖ ነው መስል፤ የጃርት ሥርዓት አራማጆች፤ እንደ ጃርት እየቆረጠሟቸው ይገኛሉ።  አንገቷ የተቆረጠባትን  ሀገር ብቻ ይዘው፤  መተንፈሻ -መናፈሻ ያጡ  ዜጎች ከሆኑ ጥቂት ዓመታትን አሳልፈዋል ።   " መቃበር፤ ከለመዱት ይሞቃል። " እንደሚባለው፤ ችግርና መከራን ተለማምደው የሚኖሩ ሁነዋል።  በዚህ ምክንያት ይመስላል፤ ያለፈ ታሪካቸውን እንደ መጽናኛ  እየተጠቀሙ  ኑሯቸውን  መግፋት  መርጠው ተቀምጠዋል ። 
 የሀገሪቱ ቀደምት ነዋሪዎች፤ ባቆዩት  ገናና ታሪክና አኩሪ ሥራ ብቻ እየተኩራሩ መኖር፤ ለሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ነዋሪ የሚያመጣው ፍይዳ አለመኖርን አውቆ፤ የራስን አኩሪ ታሪክ እያስመዘገቡ፤   ለዘመኑ የሚጠቅም ሥራ ካልሰሩ ፤ ወደፊት መራመድ የሚቻል አይደለም።   የራስን ታሪክ እየሰሩና  በራስ ጥረት ላይ የተመሰረተን ውጤት እያስመዘገቡ መሄድ ከተቻለ ግን ፤ የወደፊቱን ራዕይ ለመቀየስም ዕድል ይኖራል ። ያለፈን ታሪክ ስንቅ እያደረጉ መኖርንም ሊያስቀር ይችላል ።  
ይኽ የወቅቱ ትውልድ፤  ያለፈውን መጥፎም ይሁን  መልካም  ታሪክ ፤ እንደ አግባቡ  ለትምህርት ግንዛቤ እየተጠቀመ ፤ ያለበትን  ወቅታዊ /ነባራዊ ሁኔታ እየገመገመ ፤  በራሱ ጊዜ እየተጠቀመ፤  የራሱን ታሪክ እየሰራ/ እያስመዘገበ መቀጠል አለበት።  የወደፊት ዕድሉን ለመወሰን የሚችለው፤ የራሱ ተገዥ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ የራስ  ዥ ለመሆን ደግሞ፤ በራስ መተማመንን ይጠይቃል። በራሱ የሚተማመን ዜጋ ማፍረት የምትችል ሀገር፤ የራሷን መሪዎች መፍጠር ትችላለች። የራሷን መሪ  መፍጠር ከቻለች፤ ብዙዎቹ ችግሮቿ ሊቃለሉላት ይችላሉ ። በሂደት !
 ብዙኅነትን በአግባቡ የምታስተናግድ  ሀገር ትሆናለች።  የዘውግ ፖለቲካን ማስተናገድ አትመኝም ፡፡ አይሆንላትምም።  የዘውግ ፖለቲካ አጥፊ / ከፋፋይ እንጅ አልሚ ሊሆን አይችልም ። ለአንድነት ጠንቅ ነው። ይኽ ፖለቲካ ፤ በወያኔ አገዛዝ የታየ ሀቅ ነው።  በምትኩ ግን ፤ የዴሞክራሲ ሥርዓተ- መንግሥት መገንባት አማራጭ አይኖረውም።  በዴሞክራሲያዊ  ሥርዓት ስር ፤  በሀገረ- መንግሥት (State Power) እና በፓርቲ መካከል በህግ የተገደበ ልዩነት ይኖራል።  ይህ ልዩነት ከሌለ ግን እውር ድንብሱን እንደሚሄድ መልኅቅ- አልባ ጀልባ መሆን ነው ። ይህ ከሆነ ደግሞ መንግሥቱም ሆነ ፓርቲው በባኅር ውስጥ ጠፍተው ይቀራሉ። የደርግን መንግስትና ኢሠፓን መጥፋት ያጤኗል! የሚቀጥለው ተራም፤ የወያኔ   እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው።
 በመጨረሻም፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር መኖሯ ሊያከትም የሚችልበት ዕድል ሰፊ  የማይሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም። የወያኔ መሪዎች ዛሬ የሚፈልጉትም ይኽንኑ ነው።  ይህንን ሕዝቡ እየተከታተለ እንዳይቃወማቸው፤  በፕሮፓጋንዳ  ሊያደነዝዙት  ይጥራሉ ። ወያኔን፤  የዴሞክራሲነት  ፀዳል  ለማልስ የሞከሩ ባዕዳንም በመጨረሻ የሚያፍሩበት ቀን ይመጣል ።  ትርጉም  በሌላቸው ተግታልታይ ቃላት መጠም እንኳንስ ለወያኔ፤  የፕሮፓጋንዳ   ጠቢብ ለነበረው  ለናዚ ጀርመኑ ፕሮፓጋንዲስት፤ ለጆሴፍ ጎብልም አልፈየደ። ናዚዎቹ  በመጨረሻ እራሳቸው ጠፍተው፤ አገራቸውን  ጀርመንንም እንዳልነበረች አድርገዋት ሄዱ ። 
የሀገራችንም ዕድል በዚህ አቅጣጫ እያመራ ይገኛል ። ይኽ እንዳይሆን፤ የውቅቱ  ትውልድ የራሱን ታሪክ እየሰራ፤ ሀገሩን ማዳን ይጠበቅበታል ። ሀገሩን ማዳን ከቻለ ደግሞ፤ የራሱን ኅልውና ማረጋገጥ ይችላል ። ባለፈ ታሪክ  ማፈርም ሆነ መኩራራት፤ ማዘንም ሆነ መደሰት ብቻውን መፍሄ አልሆልንም።   የራስ ታሪክ እየሰሩ ማለፍ፤ ለሀገር ኅልውና  ስትና ሊሰጥ ይችላል ።

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኖራለች  !                  

No comments:

Post a Comment