Friday, August 19, 2016

ውዥንብሩ ለምን አስፈለገ? ( በፍኖተ ሬዲዮ እንደተነበበ . . . )
ውዥንብሩ ለምን አስፈለገ?

ሰማዩ ጥርት ሲል ፀሀይ ሲፈነጥቅ ዓይንን መጋረዱ ህልም አያሳልምም። የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ የአንድነት ጥያቄ ከሆነ ውሎ አድሯል። የሀገር ህልውና ጥያቄ ከሆነ ሰንብቷል። የነፃነት ጥያቄ የማንነት ጥያቄ፣ የመብት ጥያቄ ከሆነ ዓመታት አስቆጥሯል። ጥያቄው የፖለቲካ ጥያቄ ቢሆንም ዲሞክራሲያዊ ድልዳል አልተበጀለትም። ይህ ዲሞክራሲያዊ መድረክ እንዳይፈጠር የሚፈልጉም አልጠፉ። ማወቅ የሚገባቸውን ከማይገባቸው ጋር እያጣረሱ ግራ ተጋብተዋል። እናም ከህዝብ መሸሸግን፣ ሚሰጢር አድርጎ መያዝን ከመላ፣ ከዘዴ ይቆጥሩታል። አንዱን ኢ- ዲሞክራሲያዊ ሀይል አስወግዶ ሌላኛውን ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሀይል መተካት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት አለመሆኑን ማወቅ ተስኗቸዋል።
ወያኔ ኢህዴግ አዲስ አበባ በገባበት አንድ ዓመት እንኳ ሳይሆን ህዝብ ይህ ሊከሰት እንደሚችል አውቆ እንዲህ እያለ ይፅፍ ነበር።

"የዘመነ መሳፍንት ህመም የሆነው የቀበሌ ድሁርነት መንፈስ ገና ከውስጣችን
ተነቅሎ አልወጣም። በዚህኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ለኢምፔሪያሊስቶች
ማለትም በመሳሪያነት ሲጠቀሙበት የምናውቀውን የዛሬውን ሻዕቢያ ወያኔ
ኦነግ መልክ ሊይዝ ችሏል። በተግባርም የኢምፔሪያሊስቶች መሳሪያና ደቀ
መዝሙር መሆንን ያረጋግጣል።"

የህዝብ ፍላጎት ድርጅቶች ሁሉንም ያካተተ የሽግግር መንግስት መስርተው ህዝባዊ ለሆነ በህዝብ ለተመረጠ መንግስት ስፍራቸውን መልቀቅ እንጂ ከአምባገነን አገዛዝ ጋር ተደራድሮ ስልጣን በመጋራት መከራውን እንዲያራዝሙበት ህዝብ አይፈልግም። ታዲያ! ይህንን ለመፍጠር በሚደረገው ትግል በፅናት መቆም ሲገባ፣ በአማላጅና በሽማግሌ ድርድር ውስጥ ለመግባት ሲባዝኑ የሚስተዋሉ ድርጅቶች አልጠፉም። አንዳንድ ድርጅቶች የትግሉን ጎዳና አለመምረጣቸው ምናልባትም በውጭ ሀይላት በሚደርስባቸው ጫና ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። በተለይም በኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ወገኖቻችን ስም የተደራጁ ድርጅቶች እርስ በእርሳቸው ሳይስማሙ መግለጫዎችን በማዥጎድጎድ የህዝብ ውክልና እንዳለቸው ሁሉ፣ በኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ስም ሲምሉና ሲገዘቱ፣ ለድርድር ሲባዝኑ ይስተዋላሉ። በነዚህም ጎጠኛ ድርጅቶች አማካይነት ተባብሮ ለአንዲት አገር መታገል በቀጠሮ የተያዘ ፋይል ሆኗል።

በዚህም ምክንያት ህብረት እንዲኮሰምን ትግል እንዲጓተት ምክንያት እየሆኑ ይገኛሉ። አብዛኞቹ ከኢትዮጵያ ጋር ጠብ አላቸው። እየተጫወቱ ያሉት አፋዊ ፖለቲካ ከወያኔ "ትግራይ ትግሪኝ" ቅዠት የተለየ አይደለም።

ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ለምትመሰረት ታላቋ ኦሮሚያ አፈ ቀላጢ እንሁን ነው የሚሉት። ይህ የፖለቲካ ጨዋታቸው ሀገር ወዳዱን ዜጋ በጥርጣሬ እንዲያይ አድርጎታል። ተሸፋፍኖ ቢዶልቱ ገላልጦ የሚያይ ህዝብ እስካለ ድረስ ትርፉ መታፈን እንጂ! መደበቅም ንፁህ አየር መተንፈስም እንዳልሆነ መገንዘብ ያሻል።

በሸር በተንኮል የትም መድረስ አይቻልም። በእነዚህ ድርጅቶች አዲስ ታክቲክ ተብሎ የተያዘው፣ እኛ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ይሉት የነበረው መፈክር ቢያንስ ባደባባይ መነገሩ ቀርቶ፣ ኢትዮጵያዊ ነን ግን የራሳችን አርማ፣ የራሳችን ሀገር አለን፣ የሚል አታሞ ሲደልቁ ይስተዋላሉ። በዚህ በኩል ለውጥ ታየ እያሉ የሚያረግዱላቸው ኢትዮጵያዊ ድርጅቶችም፣ ነገሩ የለበጣ መሆኑ ጠፍቷቸው ሳይሆን፣ እከክልኝ ልከክልህ በሚል የተጃጃለ ስሌት ውስጥ በመግባታቸው ነው። ኢትዮጵያዊው እሴቶቹን ለሚያረካክስ ማንኛውም ሀይል ሊዋዛ አይችልም። ተመክሮው የሚያሳየው ያንን ነውና። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ በብሄረሰብ፣ በቋንቋ ሳይለያይ፣ በአንድነት ተጋድሎው የነፃነት ምልክቴ ብሎ የያዘውን፣ የጋራ ድል ባለቤት የሆነበትን - አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ! ማጣጣል፣ በዚህም ላይ መዝመት፣ ( ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንዳትቆይ መመኘት) የኢትዮጵያ ወዳጅ ሊያሰኝ አይችልም። ውስጥ ውስጡን ለመገንጠል እየቀሰቀሱ ላይ ላዩን ኢትዮጵያዊ ነን እያሉ መማል መገዘት የሚያሳየው የራስን ተላላነት እንጂ! የሌላውን ነፈዝ መሆን ወይም መጃጃል አይደለም። በኢትዮጵያ ላይ ድብቅ ጥላቻን አዝሎ የኢትዮጵያውያንን ድጋፍ መፈለግ ጊዜው ያለፈበት ታክቲክ መሆኑን ማወቅ ብልህነት ነው።
የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በሌላ ምልክት ለመለወጥ መሞከር ለወያኔም አላዋጣ። የኦሮሞ ህዝብ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ የራሱን መንግስት ይመሰርታል ማለት፣ የኦሮሞን ኢትዮጵያዊነት መካድ ነው። የኦሮሞ ህዝብ ለኢትዮጵያዊነቱ አልታገለም፣ አልደማም፣ አልቆሰለም፣ አልሞተም ብሎ እንደማለት ነው። የኦሮሞ ህዝብ ከሌላው ማህበረሰብ ጋር ተዋልዶ፣ ተዛምዶ በፍቅር የኖረበትን ዘመን ማውገዝ ነው። እነ ይልማ ዴሬሳን፣ አብዲሳ አጋን፣ እነ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህንን ወዘተ. የክብር ቦታ ማሳጣት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ባባህሉ የተካለሰ፣ በቋንቋው የተደባለቀ፣ በአንድ ሳይኮሎጂ የተሳሰረ፣ መሆኑን አለመቀበል ነው። ስለዚህም እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ መሰረት የሌለው ከመሆኑም ሌላ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ በጎ ሀሳብ ነው ማለት አይቻልም። ኢትዮጵያዊነት በአፍ ብቻ የሚያወሩት ባዶ ቃል አይደለም። በተግባርም የሚፈተን እንደሆነ ህዝቡ ደጋግሞ አስመስክሯል። ጠባብ ጎጠኞች ከዚህ አይነቱ አፍራሽ ተግባር ቢቆጠቡ ይጠቅማል።የህዝብ ጥያቄ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርን እንዴት እንፍጠር የሚል እንጂ! በሆነ ባልሆነው ሰበብ እየፈለጉ ልክ እንደወያኔ በቋንቋ አሳቦ መከፋፈልን ማራገብ አይደለም። ህዝብና ወያኔ የተራራቁት ኢትዮጵያንና እምነቶችን፣ ኢትዮጵያንና ማንነትን፣ ለማጥፋት
አልሞ በተነሳበት ፖሊሲው ምክንያት ነው። ወጣቱ መስዋዕት እየከፈለበት ያለው፣ ይህንን በመጥላት ነው። በወያኔ ድርጊት በመናደድ ነው። ወጣቱ አንድነቱን ለማጠንከር እንጂ በዘር ገመድ ተስቦ ቂም በቀል ለመፍጠር ወይም በቂም በቀል ተመስርቶ እርስ በእርስ ለመናቆር አለመሆኑን፣ በቅርብ ጊዜው ተቃውሞ የ አዳማ፣ የጎንደር፣ የጎጃም ወጣቶች በአንድነት አረጋግጠውታል። ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ የአንድነት ጥያቄን ለማደብዘዝ የሚደረግ ደባን በዝምታ አይመለከተውም። ሰንደቅ ዓላማን ማክበር የትግሉ አንዱ ክፍል መሆኑን፣ ወያኔን ከነዝባዝንኬው ለማስወገድ መሰረታዊ ምክንያት መሆኑን፣ መቀበል የግድ ይላል። ህዝቡና ወጣቱ በውጭም በግቢም አንድነቱን ለማስከበር ሰንደቅ ዓላማውን ከፍ አድርጎ ይዞ በሚፋለምበት ወቅት ከፋፋይ የሆነ ፕሮፓጋንዳ ማካሄድ ወይም ኢትዮጵያዊ ነኝ በሚል ጭምብል ስር ተከልሎ፣ በታኝ የሆነ ድርጊትን መፈፀም ከህዝብ ወዳጅነት አያስቆጥርም። ለወደቀና ለከሸፈ ጠባብ ብሄርተኝነት ህዝብን ለማሰለፍ መጣር፣ ህዝብን ስቃይ ውስጥ የጣለ፣ ሀገርን አደጋ ላይ ያደረሰ የጎጥ ፖለቲካን፣ ልዩ ልዩ የማታለያ ታክቲኮችን በመጠቀም፣ ለማስቀጠል መሞከር፣ እራስን ለትዝብት ይዳርጋል እንጂ የሚያተርፈው አንዳችም ነገር አይኖር። በኢትዮጵያዊነት ስም ኢትዮጵያን መጉዳት በወያኔም ተሞክሮ የከሸፈ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከዳር የጠባብ ዘረኞች ዓላማ ምን እንደሆን ተረድቶታል። የዘር ፖለቲካ ንብረቱን፣ መብቱን፣ አስቀማው እንጂ ሌላ ያተረፈለት ነገር እንደሌለ ለ 25 ዓመታት እያንገሸገሸው ቀምሶታል። የስልጣን ናፋቂዎችና ጠባቦች፣ መሰል ዘረኞችን ከስልጣን ለማስወገድ ፈቃደኛ ሆነው እንደማይሰለፉ ግልፅ ቢሆንም። ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡ ተገቢ ነው። የኢትዮጵያ ወጣት ህይወቱን መስጠት ካለበት ልክ እንደበፊቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት፣ ያልተሸራረፈ መብትና፣ ብልፅግና እንጂ ለጠባብነት ሊሆን አይችልም። የዘረኝነት ሳማ የለበለበው ሁሉንም ነው። ህዝቡ በዘር በጎሳ ተከፋፍሎ ያገኘው፣ ኦሮሞው ከኖረበት መሬት እየተፈናቀለ፣ አማራው ከኖረበት ስፍራ እየተባረረ፣ ሌሎቹም መሬታቸው እየተቀማ ለባዕድ ሀብታሞች እየተሸጠ ለባርነት ለስደት ሲዳረጉ ማየት ነው።
ህዝብ የዚህ፣ የዚያ ጎሳ ሳይባል ለጭቆና የሚዳረገው በመደቡ መሆኑ ግልፅ ነው። የጎሰኝነት ስሜት ያገለገለው ለወያኔ ስልጣን መወጣጫነት ብቻ እንደሆነ ታይቷል። ደሃውን የትግራይ ገበሬ የወርቁ ዘር ፕሮፓጋንዳ አላደመቀውም። ወያኔ በሰላም የኖረውን ህዝብ ለማለያየት ዘረኝነትን በመጠቀሙ ያተረፈው ህዝባዊ ሰላምና ብልፅግና የለም። ዘረኝነት የራሴ ለሚሉት ወገን የማድላት በሽታ ነው ቢባልም። አዶልፍ ሂትለር እንኳ ከደጋፊዎቹ ውጭ በምስራቅ ጀርመን ለነበሩት ጀርመኖች አላዘነላቸውም። ጨፍጭፏቸዋል።


ዘረኛ የሚያምነው ወገን የለውም። ድርጊቱ ከሰብአዊነት ውጭ በመሆኑ ማንኛውም ሰውኛ አስተሳሰብ ያስበረግገዋል።
ስለዚህም ነው ወያኔ ከማይደግፉት ትግሬዎች ይበልጥ በሚደግፉት ሆዳም አማሮች፣ ኦሮሞዎች፣ ጉራጌዎች፣ ወላይታዎች ወዘተ. ተከቦ ወንጀል እየፈፀመ ያለው። በዘር ተሸፋፍኖ ስልጣን ላይ ቢወጣም፣ ስልጣኑ የጠቀመው ለመደብ አጋሮቹ እንጂ ለድሃው ህዝብ አይደለም።

አንዱን ማህበረሰብ ከሌላው እያጋጨ 25 ዐመታት አሳልፏል። አማራውና ኦሮሞው እንዳይገናኝ፣ አንድ የሚያግባባው ቋንቋ እንዳይኖረው ክርስቲያኑና እስላሙ እንዲጣላ ለማድረግ ሲጣር የኖረው በጌቶቹ በባዕዳኖች ቢሆንም፣ በጣልያን በእንግሊዝ ሲዶለት የኖረውን የውስጥ ለውስጥ ተንኮል፣ ወያኔ ይፋ አውጥቶ አሳይቶናል።
አሁን ላይ ደግሞ አሜሪካንን አግኝተዋል። ኢትዮጵያ ያለ ህዝቧ በቀር ሌላ ረዳት የሌላት ሀገር ነች። ለአማራው ጉራጌው፣ አፋሩ፣ ዶርዜው፣ ለኦሮሞው እንደዚያው አማራው፣ ሀድያው፣ ከምባታው፣ ወላይታው ወዘተ. አንዱ ለአንዱ ደራሽ፣ ወገኑ ነው። ስጋው ነው። ዘመዱ ነው። የወጣቶቹ ጥሪ ይህንን ነው ያንፀባረቀው።

የዘር ሀረጋችን ኢትዮጵያዊነት ሲሆን ቋንቋችንና፣ የተለያየው ባህላችን የማህበረሰባችን ልዩ አርማ ነው። ከዚህ ውጭ ጠላቶች እንደሚያስወሩት ህዝቦች ሳንሆን አንድ የኢትዮጵያ ህዝብ ነን። በደም የገነባነው፣ ብዙ መስዋዕት ያስከፈለን ኢትዮጵያዊነት የሁላችንም ነው። ስለዚህም የተቃውሟችን ሚና በግልፅ መታወቅ ይኖርበታል። ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰንደቅ ዓላማ የማይቀረቆር ተቃውሞ ኢትዮጵያዊ ሊሰኝ አይበቃም። ይኸንን የትግል መፈክሩ ያላደረገ ትግልም ሚናው በውል ሊታወቅ አይችልም። የሚጠቅመውም ለዘረኞች፣ በተለይም ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከጠላት ጋር ለሚዶልቱት ነው። በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የሚደረገው ንቅናቄ፣ ዘረኝነት ያስከተለውን መራራ ህይወት በመጥላት የሚደረግ እንጂ! ጥላቻን ጋቢ አከናንቦ፣ ልዩነትን አራግቦ፣ ትግልን ደባብቆና፣ ሸፋፍኖ፣ ጠባብነትን ዳግመኛ በሀገር ላይ ለማንገስ የሚደረግ አይደለም። ከዚህ በፊት በባዕዳን እየተመሩ ሻዕቢያ፣ ወያኔና ኦነግ የሽግግር መንግስት መሰረትንልህ ሲሉት እስቲ ልየው በሚል ህዝብ ተጃጅሏል። ውጤቱንም አይቶታል።

አሁን በዚሁ ጦስ ህዝብ እየተሰቃየ ነው ያለው፣ ወጣቱ ለጋ ህይወቱን እየከፈለ ነው ያለው፣ ሀገር ወዳዱ ሴት ወንድ ሳይል፣ ጎሳ ሳይለይ፣ ለአርበኝነት ተጋድሎ ተሰለፎ ነው እሚገኘው፣ ይህ ሁሉ የዘረኝነት ፖሊሲ በፈጠረው ኢ-ሰብአዊና ኢ-ፍህታዊ የሆነ አስተዳደር ሳቢያ መሆኑ ሊሳት አይገባም።

ዘረኝነት እራስ ሲይዙት ቆንጆ፣ ሌላው ሲይዘው አስጠሊታ የሚሆንበት ምክንያት የለም። ዘረኝነት ያው ዘረኝነት ነው። ጠባብነት ነው። ግለኝነት ነው። አንድነትን ህብረትን አብሮ መኖርን መቃወም ማለት ነው። በዘረኝነት የሚገኝ ፍሬን ተካፋዩ ማን ሊሆን እንደሚችል ወያኔ አሳይቶናል ለባዕዳን ሲሳይ እንጂ ለሀገሬው ህዝብ አይደለም። ስለዚህም ሻዕቢያ ወያኔና ኦነግ በሽግግር መንግስታቸው የፈጠሩልንን ዘረኛ አገዛዝ አይተነዋል። ኖረነዋልም። እናም ይበቃናል። ዘረኝነት ለኢትዮጵያ የሚሰራ አይደለም። እንኳንስ እንደ መንግስት እንደ ግለሰብም ሊያዝ የሚገባ አይደለም። ዘረኞች ህዝባዊ ትግሉን ሰርቀው ለዚህ መከራ ዳርገውናል። ከአንዱ ዘረኛ ወደ ሌላ ዘረኛ መሸጋገር ግን "ከዝንጀሮ ቆንጆ..." መመራረጥ ይሆናል። ስለዚህም ወጣቱ ምርትና ግርዱን ለመለየት ብስለቱም፣ ዕውቀቱም፣ ችሎታውም፣ ዕድሜውም አለውና፣ ይህን አይነቱን የጠባቦች ውዥንብር ለማጥራት አይቸገርም። ሆኖም ግን! ውዥንብር ለምን አስፈለገ?


ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

No comments:

Post a Comment