Monday, August 8, 2016

በጎንደር የታወጀው አዋጅ የወያኔ የስልጣን ግዜና የጠባብ ብሄርተኝነት ፖለቲካ ማብቂያ መሆኑን አረጋግጡዋል


በጎንደር የታወጀው አዋጅ የወያኔ የስልጣን ግዜና የጠባብ ብሄርተኝነት ፖለቲካ ማብቂያ መሆኑን አረጋግጡዋል
ቢንያም ሙሉጌታ ከኖርዌ
የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ትላንትናም ዛሬም ወደ አቸናፊነት ሊጉዋዝ የቻለው በወጣቶች ፅኑና ቆራጥ ተሳትፎ መረጋገጥ ነው በጣሊያን ወረራ ጊዜ በርካታ ወጣቶች የሕይወት ዋጋ ከፍለዋል ለነፃነትና ለሉዋላዊነት ሲሉ።
እነ ዘርዓይ ደረሰ፣ አሉላና አብርሃም ቢጠቀሱም በጥቁር አንበሳ ስብሰባ ደረጃ ሆነ በልዩ ልዩ የአርበኞች ቀጠና ወጣቱ ጠላትን በቆራጥነት ተዋግተዋል ይህን አርዓያነት በመከተልም ወጣቱ በፀረ ዘውድ አገዛዝ ትግል ትልቁን ቦታ ይዞ ሲገኝ ፋሺስት ደርግ የህዝብን ድል ሲነጥቅም ወጣቱ በተለይም በኢሕአፓ ስርና ዙሪያ ተሰልፎ ታሪክ የማይረሳውን መስዋዕትነት ለህዝብና ለሀገር ሲል ከፍሏል።
ወጣት የነብር ጣት መሆኑን ዛሬም በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች አስመስክረዋል። ካለፉት ወጣቶች ወኔንና ጀግንነትን ልበ ሙሉነትንና ድፍረትን ልንወርስ ይገባል። በሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ ተስፋፍቶ ያለው የወያኔን ስርዓት ለመጣል እንደ ቀደምቶቹ ወጣቶች በአንድነት ክንዳችንን በማንሳት እንዲሁም በፅናት ትግልን የመምራት ልምድ ባላቸው በመታገዝ ልናስወግደው ይገባል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በጉልበተኞች በጠመንጃ የተቀማውን መብቱንና ነፃነቱን ለማስመለስ የሚጠበቅበትን ሚና ልክ እንደቀደምቶቹ ወጣቶች አስፈላጊ ዋጋ ሁሉ እየከፈለ ይገኛል። ጨቋኙን ስርዓት ገርስሶ ለመጣል ኢትዮጵያ ሀገራችንን ከሚያሰጏት አደጋዎች ደርሶ ለማዳን በጉዞ ላይ ነው የወያኔ ስርዓት ኢትዮጵያውያኑን ወጣት አፍኖ ለመያዝ ቢተጋም በፅናትና በቆራጥነት እየታገለ ነው አከርካሪውንም መስበር ቀላል እንደሆነ ተገንዝቡዋል።
የቀደሙትን ወጣቶች ጀግንነት ማስታወስ ያስፈልጋል የዘውድን አገዛዝ እንዲሁም የፋሺስትን ደርግ ስርዓት እንዴት እንደታገሉት ኢህአወሊ(የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ወጣት ሊግ) በሚል በዋና መልኩ የተደራጀው ወጣት በሕይወት የከፈለው ዋጋ ቀላል እንዳልሆነ ታሪክ መዝግቧል።
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች የወያኔ የዘር ፖለቲካ አገሽግሾታል ሰብዓዊ ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችን መገፈፍ አስቆጥቶናል በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ነፃ ሚዲያ፣ ነፃ ፖሊስ፣ ነፃ መከላከያ፣ ነፃ ፍርድ ቤት፣ ነፃ የሆነ የፍትህ አካል ነፃ የሆነ ተቋም የለም ሁሉ ነገር በአምባ ገነኑ በዘረኛው ወያኔ ቁጥጥር ስር ነው ለዚህ ነው የተደራጀና በጽናት የቆመ አላማ ያነገበ ወጣት የሚያስፈልገን።
አሁን ላይ ግን በጎንደርና በቀሪው የሀገራችን ክፍል የሚገኙ ወጣቶች አላማ አንገበው ቆርጠው ተነስተዋል ወያኔን አንገቱን እያስደፉት መግቢያ መውጫ እያሳጡት ይገኛል ታሪክም እራሱን እየደገመ እያየን ነው ብዙ ጀግኖች የሞቱለትን ሰንደቃላማ ወያኔ ለ25 ዓመታት እንዳይውለበለብ አግዶ ቢቆይም ዛሬ ግን ጀግናው የጎንደር ወጣት በልቡ ታትሞ ያለውን ብዙዎች የወደቁለትን ሰንደቅ ከፍ አድርጎ በኢትዮጵያ ምድር ዳግም አውለብልቧል። ወያኔዎች የዘረኝነትን መርዝ በኢትዮጵያ ላይ ሲረጩ ቢኖሩም ኢትዮጵያዊው በዘረኝነት መርዝ አለመበከሉን በጎንደር ወጣቶች ድምፅ ተረጋግጡዋል።
የኦሮሞ ወንድሞቻችን ግድያ ይቁም፣ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ይፈቱ በማለት ነበር ኢትዮጵያዊው ጎንደሬ ድምፁን ያሰማው። ወያኔ ወደ ስልጣን ከመጣ ግዜ ጀምሮ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ወጣቱ በወያኔ ጥይት ይገደል የነበረ ቢሆንም አሁን ግን የጎንደር ህዝብ እራሱን ወያኔን የሕይወት ዋጋ ማስከፈል ጀምሩዋል። ኢትዮጵያውያን በወያኔ ላይ እያደረጉ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ ሀገራዊ እየሆነ መምጣቱ ለወያኔ ሰላም ነስቶታል።
ጎንደር ላይ ህዝቡ ባካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ለወያኔ ባስተላለፈው መልክት ከእንግዲህ ከፋፍሎ መግዛት እንደማይቻል ነው። የጎንደር ህዝብ ኢትዮጵያዊነት በተላበሰ ታሪካዊ ሰልፍ በኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ሶማሊያ እንዲሁም በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚፈፀመው ግፍ አውግዙዋል ታዲያ በዚሁ ታሪካዊ ሰልፍ የጎንደር ህዝብ ድል አይቀሬ መሆኑን አረጋግጡዋል።
ወያኔ በሀገሪቱ ላይ ያለውን ውጥረት ያበርድልኛል ብሎ ያሰበውን ሁሉ እያከናወነ ይገኛል በኢትዮጵያ ውስጥ የማህበራዊ ሚዲያዎች አገልግሎት ማቋረጡ እንዲሁም በብቸኝነት በተቆጣጠረው የቴሌቭዥን ጣቢያ የበሬ ወለደ ፕሮፕጋንዳውን ለማይሰማውና ለማያምነው ህዝብ ማስተላለፉን ተያይዞታል።
ሕወሓት ወያኔ የሀገርና የህዝብ ጠላት መሆኑን ዛሬ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተረድቶታል የወያኔ የቂም በቀል ሰለባ ያልሆነ ዜጋም በፍፁም አይገኝም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው እያፈናቀለ በነርሱ ስቃይ እርሱ ይደሰታል በኦሮሚያ ክልል የተነሳበትን ተቃውሞ ለበለጠ በቀል አነሳሰቶታል ለዚህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያውቀው ወያኔ የኦሮሞ ወጣቶችን ተኩሶ መግደል ከጀመረ 9 ወራትን አስቆጥሩዋል ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ታሪክ ይቅር የማይለውን ስህተት ሰርቱዋል በወያኔ የስልጣን ዘመን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የስቃይ አመታትን አሳልፍዋል አሁን ላይ ኢትዮጵያዊው ሁሉ የነፃነት ሽታ እየሸተተው ይገኛል። የተያያዝነው ወያኔን የመጣል ትግል ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። የወያኔ የበላይነት አክትሙዋል ከአሁን በኋላ ወያኔ አብቅቶለታል የሚለው የኢትዮጵያውያን ድምፅ ከዳር እስከዳር እየተስተጋባ ይገኛል። ከወያኔ ጋር መደራደር ለወያኔ መቅለስለስ ለወያኔ ጊዜ መስጠት ወያኔን ማመን ፈፅሞ የሚታሰብ እንዳልሆነ ሁሉም ዜጋ ያምናል የወያኔ ድርጅትም አመራሮቹም በስብሰዋል።
ባህር የሆነው ህዝብ ባለው የወያኔ ስርዓት ላይ ማዕበል ሆኖ ተነስቷል ጠራርጎ መውሰድ ብቻ ነው የቀረው።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!! 

No comments:

Post a Comment