Thursday, September 15, 2016

አሞራው በሰማይ ሲያሽ ዋለ ፤ "ይዤሽ ልብረር እያለ ! " የፍኖተ ሬድዮ ወቅታዊ ሀተታ


 መብረጃና መቆሚያ፤ መድከሚያና   ማክተሚያ ፤ የሌለው ሕዝባዊ ፤  አመፅ በመላው ሀገራችን  እየተቀጣጠለ በመሄድ ላይ ይገኛል ። ይኽ አመፅ ፤ ከጭቆና አገዛዝ ፤ ከበደልና ግፍ ማህጸን  የተወለደ ነው ። ለአለፉት 25 ዓመታት፤ መላው የሀገሪቱ  ዜጎች ፤ በረዥም ዘመን ታሪካቸው ፤  አጋጥሟቸው የማያውቅ፤ ተዘርዝሮ የማያልቅ ፤ አሰቃቂና አንገፍጋፊ በደል ተፈጽሞባቸዋል።  ይኽም፤ በየጊዜው የተፈራረቁት ባዕዳን ወራሪ ጠላቶች ከፈፀሙት  በእጅጉ የበለጠ ነው ። 
ወያኔ፤ በሀገሪቱና በዜጎቿ  ላይ የፈጸመው ወንጀል፤ ድርቡሾች፤ ግብጾች፤  ቱርኮች፤  ጣሊያኖች ፤ እንግሊዞች  አልፈጸሙበትም። ይኽ የአሁኑ ሕዝባዊ አመፅ፤ መነሻውና ዐላማው፤ የፍትኅ- ርትዕና   የዴምክራሲ አስተዳደር፤ ማጣት ጥያቄ ብቻ ሳይሆኑ ፤ የሀገሪቱ ኅልውና፤ የሕዝቦቿም አብሮ የመኖር ያለመኖር ጥያቄም ጭምር ሆኗል  ። በመሆኑም አሁን ፤ የተጀመረው አመፅ  ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ፤ የሞት - ሽረት ትግል ነው።  ይኽ በመሆኑ የተነሳበት ዓላማ ግቡን ሳይመታ አይቆምም፡፡
የአሁኑን  አመፅ የተለየ የሚያደርጉት በርካታ ምክንያቶች ቢኖርም፤ ዋና ዋናዎችን መጥቀስ ፤ መሠረታዊ ዕይታን ለማየትና ተጫባጭ ግንዛቤንም  ለመረዳት    ያስችላል ።
1ኛ.  ይኽ የሚካሄደው ሕዝባዊ አመፅ ሀገር አቀፍ አመፅ ነው። ፀረ ወያኔነቱ፤ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ፤ ያካተተ-ያጠቃለለ-ያስተባበረ -ያዋኸደ  በመሆኑ፤ ኃያል ሕዝባዊ አመፅነቱ የሚያጠያይቅ አይደለም ። ግቡን ሳይመታም አይቆምም ።
2ኛ.    " ሁሉም መንገዶች፤ ወደ ሮማ ያመራሉ። "   እንደሚባለው፤  በየአካባቢው ተጀምረው የሚቀጣጠሉት  ሕዝባዊ  ትግሎች፤ የመጨረሻው ግባቸውና መደምደሚያቸው፤  ያው ዞሮ-ዞሮ፤ ሀገራዊ አንድነትና የዜጎቹን ሁሉ  ነፃነት  ለማረጋገጥ ያነጣጠሩ ናቸው።  ስትራተጃዊ  ዓላማቸው፤  የኢትዮጵያን ሀገራዊ  ልዕልና  ማስገኘት ፤ የዜጎቿንም አንድነት-አብሮነት ማረጋገጥ ብቻ ነው ። የመጨረሻ ግባቸውም ፤ የዘረኞችን ዕኩይ ሴራና ተንኮል ሰባብሮ  በመጣል ፤ ዳግም  እንዳይንሰራራ  ማድረግ ይሆናል    
ሕዝባዊው አመፅ፤ ማነኛቸውንም ዜጋ ሁሉ ያሳተፈ ስለሚሆን፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ፤ ወንድ ሴት፤ ህፃን ሽማግሌ ከተሜ- ገጠሬ፤  ገበሬ- መምህሬ ሳይል፤ ሁሉም፤ የአመጹ ተሳታፊ፤ የትግሉ ተባባሪ ፤ የመሥዋዕቱና የውጤቱ ባለቤት  መሆኑን ያረገግጥለታል። ሁሉም እንደ አቅሙ፤ የተሳተፈበት ትግል በመሆኑም፤ የድሉ  ተቋዳሽ፤  የማዕዱ ቆራሽ ፤  የነፃነቱ ለባሽ፤   የፅጋው  ተካፋይ መሆኑን ፤ ያረጋግጥለታል ።
3ኛ.   አመፁን አካሂዶና ታግሎ፤ የሚያስፈልገውንም  መሥዋዕት ከፍሎ  ድሉን ያስገኘው፤  ራሱ ባለቤቱ  የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለሚሆን፤ የወደፊት  ዕድሉንም የሚወስነው እርሱ ባለቤቱ - ሕዝቡ እንደሚሆን ስለሚረጋገጥ፤ ማንም አፈ-ጮሌና ፤ የሥልጣን ጥም ያሰከረው ቡድን የማቋመጥ ዕድል አይኖረውም ። ይኽ በመሆኑ፤ የዴሞክራሲ  ሥርዓትና የነፃነት ዋስትና  ዕድሉ የጠነከረ ይሆናል። የአምባገነን አገዛዝና የውጭ ጣልቃ ገብነትን አመጹን የሚያካሄደው ታጋይ ሕዝብ እንደማይቀበል ይገመታል።
ነፃ አውጣሁህና   ነፃ አወጣኸኝ   የሚል  ስለማይኖር ፤  ወለታ ሰጭም ሆነ ውለታ ከፋይ አይገኝም ። ይኽ ሁኔታ፤ በኩሉ፤  ነፃ ሕዝብና ነጻ የፖለቲካ  መልከዐ- ምድር ይፈጥራል ።   የነፃ  መድረክ እንቅስቃሴ እንዲኖር  ዕድል  ይከፍታል ።  የፖለቲካ  ምኅዳሩም  ለሁሉም ሰፊና ክፍት  ይሆናል   ክፍትና ሰፊ የሆነ የፖለቲካ   ምኅዳር  በበኩሉ   ሁሉንም  አሳታፊ  ይሆናል   በሀገሩ   ጉዳይ   ማነኛው   ዜጋ ፤ " የበይ -ተመልካች " ሊሆን አይችልም  ፡፡ የዴሞክራሲ ዓይነተኛ ባኅርይና ተግባር ደግሞ ፤  አሳታፊ ዴሞክራሲ መሆኑን ማረጋገጥ ነው 
ወሳኙ፤ የጠብ-መንጃ አፈሙዝ መሆኑ ቀርቶ፤  የብርዕ ልሳን ይሆናል። ፍርሃትና መሸማቀቅ  ቀርቶ፤  ድፍረትና በራስ መተማመን ይስፍናል ፡፡ ይህ  ደግሞ ለዴሞክራሲ ማኅበረስብ ፤ ድልዳልና ዋስትና ይሆናል ።
የሕዝቡን አመፅ ለማኮላሸት ያቆበቆቡ ሁሉ " ተነቅቶባችኋል !  አይሳካላችሁም ፤ "  ሊባሉ ይገባል።
"  ያም የእኔ  ፤ ያም የእኔ፤  ያም የእኔ ይሏታል ፤
   ሲያምር ይቅር እንጅ  ፤ ማን ያቀምሳቸዋል  ! "
  መባል አለባቸው ።
4ኛ.  የሕዝቡን የነጻነት አመፅ  " እኛ እንመራዋለን ፤ መርተነዋል " ብለው የሚያቋምጡ የሥልጣን ጥመኞች ፤ በሕዝቡ የነፃነት ጥያቄ ላይ ጣልቃ  ለመግባት የሚያደርጉት  ጥረት ሁሉ ዋጋ ቢስ ሊሆን የሚችለበት ዕድሉ  ሰፊ  ሊሆን ይችላል ።   ዛሬ፤ ለባዕዳን  መሳርያ በመሆን የሀገሪቱን ብሄራዊ  ጥቅም አሳልፈው ለማስጠት የተዛጋጁ እንዳሉ ቢታወቅም ፤  የእነርሱን  ስውር ደባ ለማኮላሸት  ግን አመፁን የሚያካሂደው  እራሱ ሕዝቡ ነቅቶ መጠባብቅ አለበት ። የሚያንዣብቡ አሞራዎች በየትኛውም አድማስ እየተጠባበቁ መሆናቸውን መዝንጋት አያስፈልግም ። በየቦታው አድፍጠው የተቅመጡ ተኩላዎችንም መከታተል አስፍልጊ ነው።
5ኛ. የተጀመረውን  ሕዝባዊ   የአመፅ  እንቅስቃሴ ፤  እጅግ ያሰጋቸው ፤ ሌሎች  የኢትዮጵያ ሕዝብ  ባለንጣዎች በዐይነ- ቆራኛ በቅርብ እየተከታተሉ፤ የሚከሽፍበትን ሴራ እንደሚያውጠነጥኑ መረሳት የለበትም ።  ዋና ዋናዎቹ  የሚከተሉት ናቸው ።
  ሀ )  ሻዓቢያ   ለ) ግብፅ   ሐ)  ሱዳን    መ) ወያኔና ግብረ-አበሮቹ፤ ዐለቆቹና የበላይ ጠባቂዎቹ፤በግንባር -ቀደም  ተሰልፈዋል ። ሁሉም የየራሳቸው መሠረታዊ ምክንያቶች አሏቸው ። ሁሉንም መዘርዘር ላይኖርብን ይችላል ።  ምክንያቶቻቸው  የተሰወሩ አይደሉምና  !    
ከላይ ከአንድ እስከ አምስት ተራ ቁጥር የተጠቀሱት  ጉዳዮች፤  በአውንታዊ መልካቸው እንዲገባደዱ ካስፈለግ ደግሞ፤  የሚከተሉት ተግባሮች  በአስቸኳይ ሊከናወኑ ይገባል ።
1ኛ.  በኢትዮጵያ ሀገራዊ  ነጻነትና  በሕዝቧም እኩለነት- አብሮነት ከልብ የሚያምኑ-የሚፈልጉ ወገኖች-ኃይሎች  በአስቸኳይ በአንድ ጎራ መሰለፍ የጠበቅባቸዋል ። ሕዝባዊውን አመፅ ደግፎ መቆም አለባቸው ። እንድ ጅብ ጎዞ ጎን -ለጎን  በጥርጣሬ  መግዛቸውን አቁመው የሕዝባዊው ትግል አንድ  አካል -አንድ አምሳል ሆነው ካልቆሙ፤ በዘመነዊቷ  ኢትዮጵያ ታሪክ ተተፍተው እንደሚቀሩ ማወቅ አለባቸው 
2ኛ.  በዕዳን ኃይሎች፤ አሁንም እንደ ትላንቱ ፤ እንደ ሎንዶኑ  1991 ዓመተ ምህረቱ፤  የዛሬውንም ሕዝባዊ አመፅ ለማኮላሸት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ መንገንዘብ ያስፈልጋል ። ወያኔን፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አመፅ ለማዳን ፤ ጉጉት ይኖራቸዋል ማለት ሳይሆን፤ በኢትዮጵያ ዋስጥ ያላቸው ጥቅም እንዲቀጥል  ስለሚፈልጉ፤ አዲስ ጥቅም አስጠባቂ ታማኞችን  በማዘጋጀት ላይ እንደሆኑ ነቅቶ መጠበቅ አስፈላጊ ነው ። " ወያኔ ይወገድ እንጅ ፤ የፈለገው ይምጣ  " የሚለው አባባል ።  " ደርግ ብቻ ይጥፋ እንጅ ማነኛው ቡድን  የተሻለ ይሆናል  "   ተብሎ የነበረው  ምኞት ምን አንዳመጣብን ሊዘነጋ አይገባውም 
ዐጼ ኃይለ ሥላሴ በ 1933 ዓም ከስደት እንደተመለሱ  የተቀነቀነውን ስንኝ ማስታዎሱ ለአሁን ሁኔታ ግንዛቤ ይሰጣል ብለን እናስባለን  ። ስንኙ ይህንን ይመስል ነበር ።
 " እንግሊዝ እናቱ  አማሪካ አባቱ ፤
  ደግፈው ደጋግፈው አስገቡት  ከቤቱ ። "    
በውጭ ድጋፍና ትብብር የሚመጣ ማነኛው ቡድን፤ ለኢትዮጵያ እንዳማይጠቅም መዘርዘር የለብንም ። እርሱ ፤ ባለቤቱ ፤የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በሚጋባ ያውቀዋልና !
4ኛ.  ከአፅናፍ- እስከ አፅናፍ የተቀጣጠለውን  ይኽንን ሕዝባዊ አመፅ ፤ ሁሉም ተበብሮ  ድል እንዲያገኝ ካላስቻለ፤ የዘለዓለም ፀፀትና ቁጭትን ፤ ውርደትንና  ሀፍረትን  ተከናንቦ እንደሚኖር ማውቅ አለበት ። ያ ደግሞ፤ እየኖሩ መኖር ሳይሆን ፤ እየሞቱ መኖር ነው ።  እየሞቱ ከመኖር  ይልቅ   በክብር  መሞት ዘለዓለማዊ  ህይወት ነው ።
በሀገራችን ሰማይ የሚያንዣብቡትን  ነጣቂ አሞሮች  ነቅተን እንድንጠብቅ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን !
ኢትዮጵያ ለዘለዓም ትኖራለች  !!         

         

No comments:

Post a Comment