Sunday, October 9, 2016

ኢትዮጵያ ፦ ከዳግም ክኅደት ያድንሽ ! የፍኖተ ራዲዮ ወቅታዊ ሀተታ!

ዛሬ በመላው  ሀገራችን ፤ እንደ መንጠር  ዕሳት እየተቀጣጠለ በመሄድ ላይ የሚገኘው  ሕዝባዊ አመጽ፤  አዝጋሚ ሳይሆን፤ ስር የሰደደና አግማሱን እያሰፋ የሚጓዝ ተንቀሳቃሽ  ሀገር-አቀፍ ኃይል  ሆኗል ፡፡ ይህንን ሕዝባዊ ዕምቢተኝነት፤ ማንም ሊያቆመው - ሊበርዘው -ሊያደበዝዘው-  ሊቀለብሰው-  ሊያስጨነግፈው  የሚችል ኃይል አይኖርም ። የውጭ ጣልቃ ገብነትም ሆነ  የጠላት   ርብርቦሽ   ሊያመክነው  አይችልም      የወያኔ አፈና-ጭፍጨፋ- የዘር -ማጥፋት ርምጃ  አይበግረውም ።   
የኢትዮጵያን  ሕዝብ  የተባበረ  የነፃነት  ትግል  ፤ ደርቡሾች  ቱርኮችና  ጣሊያኖችም  ሊቋቋሙት  ሞክረው  አልተሳካላቸውም  !    "ላይክስ  አይበድልም  "  እንዲሉ ፤ ይኽ የዛሬው ሕዝባዊ  አመፅ መነሳሳት ፤ የመላውን ኢትዮጵያ ሕዝብ  አንድነት- አብሮነት- ሀገራዊነት- ኢትዮጵያዊነት   እንደገና  ለማረጋገጥ  የተነሳ አዲስ የታሪክ  ምዕራፍ ከፋች ነው ። ጊዜውን ጠብቆ የመጣን አመፅ ማስቆም አይቻልም ።
 የታሪካዊቷን - የዘለዓለማዊቷን- የጥንታዊቷን-  ሀገር  እንደገና፤  የዓለም ኅብረተሰብ  አባል የምትሆንበትን  ዕድል የሚያረጋግጥላት ሂደትና  ክስተት ነው ።  ይኽ  ደግሞ  መፈፀሙ  አይቀርም  ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤ ለዕድሜህ ፤ ዕድሜ ይስጠው ! አንድነትህን ጠብቀህ-  ተባብረህ- ታግለህ - የጋራ ጠላትህን አስውግድ ! የነፃነትህ ባለቤት እራስህ ነህና  ዛሬም እንደ  ትላንቱ ታሪክህ፤ ራስህን አስከብር !  ለከፋፋዮቹ  ጫጫታ ዦሮህን ንሳቸው  !
"እኛ ከሌለን ፤ ሀገሪቱ ትፈርሳለች  ፤ ሕዝቡም ፤ እርስ በዕርሱ  ይፋጃል  ። እንደ  ሩዋንዳ - ቡሩንዲ የዘር መጠፋት  ይመጣል ። "  እያሉ ማስፈራራት  ውሃ  አይቋጥርም ።  የኢትዮጵያን  ሕዝብ  ማንነትና - ምንነት በጥልቀት  ካለመረዳት የመነጨ  ድንቆርና  ብቻ ሳይሆን፤  ኃላፊነት የጎደለው ከንቱ  ዝባዝንኪም ነው ። የሕዝቡን አልገዛም ባይነት እንቅስቃሴ፤ ለራሳቸው ሥልጣንና ኅልውና አስጊ መሆኑን በመረዳት  ሁኔታዎቹን  እያጦዙ፤  የጎሰኝነት መርዝ ይረጫሉ ። የመስፈራሪያ ጭንቀታቸውን  ያራግባሉ ።     ይኽ ዘዴ፤ ያፋጀ-ያረጀ- የላሸቀ - የደቀቀ- የጠነዛ- የመረተ-  የወየበ፤ ጊዜው ያለፈበት ኋላ ቀር አስተሳሰብ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤ ከዚህ ባላይ በልጦ በመገኘት፤ በአዲስ ምዕራፍ ውስጥ ይገኛል። ይኽንን ሃቅ አለመቀበል፤ በራስ ላይ መቀልድ ነው ።
እረ ለመሆኑ፤  ኤርትራን አስግንጥሎ፤ ኢትዮጵያን ወደብ አልባ ያደርገ  ወያኔ ፤ ምን  የሞራል ብቃት ኖሮት ነው፤ ስለ ኢትዮጵያ አስባለሁ የሚለው  ?
" ዕውነት፤ የዕውነቶች  ቀመር "   መሆኗን ከለመገንዘብ  በመጣ አላዋቂነት ምክንያት፤ ዕውነት  ያለቸው ከእኛ ከወያኔወች እጅ  ብቻ ነች  " ብለው ራሳቸውን ያታልላሉ።  የዘር ማጥፋት መሠረታዊው መንስዔ፤  የዴሞክራሲ  አለመኖር ነው ብለው ብዙ  የፖለቲካ ጠበብቶች  ያምናሉ።  የሀገራችንም መሠረታዊው ችግር የደሞክራሲ አስተዳደር ደብዛው መጥፋት ሆኖ ይገኛል።  የሀገራችንን ሁለንተናዊ  ችግሮች  ለመስወገድ  ፤ የመጀመሪያ  ርምጃ  የደሞክራሲ ሥር ዓትን   መስፈን መሆኑ ተደጋግሞ ተደጋግሞ የተገለጸ በመሆኑ፤ በዚያ ላይ ማተኮሩን ለጊዜው እንገተዋልን  ። ምክንያቱም፤  ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ አመፅ ያተኮረው በኅልውና ጥያቄ ላይ በመሆኑ ነው ። በአንዳንድ የኢትዮጵያ ዜጎች ላይ በተለየ ሁኔታ የዘር ማጥፋቱ ሂደት በአደገኛ  አኳኋን  እየተከሄደ በመሆኑ ፤ጥቃቱ ለሚካሄድባቸው ኢትዮጵያውን ዜጎች፤ የሞት-ሽረት ጥያቄ በመሆኑም ጭምር ነው ።
ዘር ማጥፋት   የሚለው  ቃል     ለመጀመሪያ   ጊዜ    በዓለም  ፖለቲካ  መድረክ    ሊታወቅ   የቻለው ፤ በ 1919  ዓም   (  እ .አ. ዘ . አ ) አካባቢ  የኦቶማን  ኢምፓየር   መፈረካከስ  ሲጀምር   እንደነበር   የታሪክ  ሊቃውንት  ይናገራሉ ። ጀኖ- ሳይድ (Genocide ) የተባሉትን ሁለት የእንግሊዝኛ ቃላት በመገጣጠም የተፈጠረ  መዝገበ ቃል  እንደሆነ ይነገራል  ። ጀኖ (Geno ) ዘር   ሲሆን ( ሳይድ Cide)   ደግሞ መግደል  ማለት እንደሆነ ይገልጻሉ ፡፤ ታዲያ  ጀኖ ሳይድ ( Genocide  )  የሚል ቀል ፈጥረው  ታዋቂነት እንዲያገኝ ተደርጓል።   ጥፋቱ የሚያተኩረው ፤ በተለየ፤ ብሄር ፤ ጎሣ፤ ዘርና ኃይማኖት ላይ  እንደሚሆን፤  የዓለም አቀፍ ህግ ያሳውቃል።  ይመዘግባል 
የወያኔ መሪዎች ዛሬ የሚፈጽሙት የዘር ማጥፋት  ወንጀል ፤ ጠላታችን ነው በለው  በፈረጁት በአማራው ላይ የነጣጠረ ለመሆኑ የአደባባይ  ምሥጢር ሆኗል ። " ንእዚዮም ርጉማት አጥፋ አዮ !  "   " እነኝኽን  ዕርጉሞች አጥፋቸው "  በሚል መሪ ቃል የጥፋት  ቋሚ መርዘኛ  ትእዛዛቸውን ያስተለልፋሉ ። 
ይህንን ሕዝባዊ አመፅ ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ  እንደ ዐይኑ ብሌን  ተንክክባክቦ ይዞታል ።  እንዳይኮላሽም  ይዋደቅለታል ። የተነሳበትን  ግብ እስኪመታም ድረስ የሰዋለታል፡፡ በመጨረሻም ፤ በዳግማዊ የካቲት 66 ዓም መንፈስና ዓላማ ፤ በኢትዮጵያ  ትንሣዔ  ይጠናቀቃል እንጅ፤ በዳግማዊ ክኅደት አይኮላሽም !
 ይኽ ስለተባለ ግን፤ ወያኔ በሥልጣን እስከቆየ ደርስ ፤ እጅ-እግሩን አጣጥፎ ይቀመጣል  ማለት አይደለም። እየጨነቀው እየጠበበው በሄደ መጠን፤ ሕዝብ መጨፍጨፉን ፤ንብረት ማውደሙንና፤ሀገር በይበልጥ ማጥፋቱን ባስከፊ መልኩ ይቀጥልበታል ።  አሁን እያደረገ ያለውም ይኽንኑ ነው።  እስር ቤት እያቃጠለ፤ እስረኞችን በጥይት መቁላቱ ፤ ዕውነተኛ ማንነቱን ለመላው ዓለም   በይበልጥ ግልጽ እያደረገ መጥቷል ።
 በጎንደር ክፍለ-ሀገር፤  በግዙፍነቱ   የታወቀውን   ቅዳሜ ገበያ  እየተባለ  የሚጠራውን የጎንደር  ከተማ   ገበያ አዳራሽ  ጨለማን  ተግን በማድረግ  ቢንዚን ስያርከፈክፍ አድሮ  በእሳት አጋይቶታል ።  የሱቆቹ ባለቤቶች ፤ ቃጠሎውን ለመከላከል ቢሄዱም ፤ ንብረታቸውን ለማዳን እንዳይችሉ  ከልክሏቸዋል ። ግምቱ፤ በበርካታ ሚሊዮን በር የሚገመት የሕዝቡ ንብረት የዶግ አመድ ሆኖ ቀርቷል። ቤትስቦቻቸውም  አውላላ ሜዳ  ፈስሰዋል፡፡ ይኽ ዘግናኝ ድርጊት ከአንድ  የውጭ ጠላት እንጅ፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ ከሚል  " ወገን" የሚፈፀም አልነበረም ። 
ታላቁ የትግራይ ሕዝብ ሆይ ! በስምህ ይኽ አሰቃቂ  ወንጀል ሲፈጸም ምን  ይሰማኽ ይሆን ?      
የወያኔን ወንጀል   ተቃውሞ፤  መሠረት አድርጎ የተነሳውን አመፅ ፤ አቅጣጫ ለማስቀየር  የሚደርግ የውስጥና  የውጭ ቡድኖች፤ በማሴር ላይ መሆናቸውን  ሁሉም ዜጋ ጠንቅቆ  ያውቀዋል ።  ነቅቶ  የከታተለዋል።  አድመኞቹ ማን ማን እንደሆኑ በሚገባ  አውቋቸዋል። ተረድቷቸዋል ። የሀገሪቱ ዕውነተኛ ወዳጆችን ፤ የአዞ  እምባ  ከሚየለቅሱት  ለይቶ  ተረድቷል ። ክፉ ቀን ፤ አስተዛዛቢ ዘመን ፤ ወዳጅን ከጠላት ለይቶ ለማወቅ  አስችሏል ።  በኢትዮጵያ ጥፋት የሚክብሩ፤  በወገናቸው ሀዘን የሚደነክሩ፤  በሦስት ተፈራራቂ  ሥርዓቶች  የሚያደናግሩ፤  ሀሰት መስካሪ፤  ለማጣው ሁሉ አጫፋሪ፤  የታሪክ መጋኛ    ጊዜያዊ  ጥቅመኛ ፤  ሁሉ የሚጋለጥበት  ወቅጥ ዕሩቅ  አይሆንም    ልብ ያለህ፤  ልብ ብለህ ታገል ! ልብ  የሌለህ፤ ልብ ይስጥህ እንጅ ልብ ይንሳህ አትባልም !  ዦሮ ያለህ ስማ እንጅ፤ መስማሚያ ይንሳህ አትባልም !
  ብሩኅ  አዕምሮ፤ ንፁኅ ኅሊና  ያላቸው ዜጎች፤ ለዕውነት የቆሙ ፤ ለኅሊናቸው የተገዙ፤ ለመርህ ያደሩ ፤ ስብዕናቸውን  አክብረው ያስከበሩ፤  ሰዎቿን  ፤ ኢትዮጵያ የምትፈልግበት  ጊዜ መምጣቱ አይቀርም ።  ሀገሪቱ ዛሬ ድምጿን  ከፍ አድርጋ የምትጮኸውም፤  እነኝኽን ሰዎችና  ድርጅቶችን  ፈልጋ ነው ። ድምጻቸውን አሰምተው፤  አቤት ብለው ገና አልወጡም ይሆናል  እንጅ ፤ በየቦታው አንገታቸውን  ደፍተው፤ ድምጻቸውን አድፍጠው  ማንነታቸውን  ሰውረው ፤  እንደሚጠባበቁ  ግን  ታምናለች      የእነርሱና  የኢትዮጵያ መገጣጠም  የሀገሪቱን  ፖለቲካ ምኅዳር ፤ በመሠረታዊ መልኩ እንደሚለውጠው ይታመናል ። ይኽ እንዳይሆን ነው ፤ባሁኑ ወቅት ፤ የውስጥና የውጭ የሀገሪቱ ባላንጣዎች የተቀነባበረ ስውር ሴራ በመካሄድ ላይ የሚገኙት !
የወያኔ አገዛዝ በመንገዳገድ ላይ መሆኑን በመገንዘባቸው፤  የነፍስ -አድን ጥሪ በማድረግ  እየተሯሯጡ ይገኛሉ። ሀገሪቱ ተቆርቋሪ ኃይል የሌላት መሆኗን በመረዳት፤ አሁንም እንደ ትላንቱ፤ የወደፊት ዕድሏን እኛው እንወስንላታለን ብለው ተነስተዋል፡፡ አሁንም፤ የወያኔን የበለይነት እንደገና  ባረጋገጠ  መልኩ፤ ያንድነት መንግሥት፤ የሽግግር  መንግሥት፤ የአደራ መንግሥት፤  ጊዚያዊ  መንግሥት፤ የስደት መንግሥት፤  የተውጣጣ መንግሥት፤  ወዘተ.....  የሚል  ማደንዘዣ፤ ትጥቅ አስፈች፤ አቅጣጫ ነሽና፤ ውዥንብር ፈጣሪ  ሁኔታን በመፍጠር ፤ የሕዝቡን ትግል ለማኮላሸት ይሞክራሉ ።
አሁንም እንደ ትላንቱ  የኢትዮጵያን ሕዝብ ትግል፤ አኮላሽተው፤ የራሳቸው አሻንጉሊት አገልጋይና ጥቅማችወን የሚጥብቅላቸው  ቡድን  ለመሰየም  ይጥራሉ  ። ዳግም  ምፅዓቱን  ፤ በዳግም ክኅደቱ  ለመተካት  ፤ ሟችን ሥርዓት፤ በአዲስ ሀርግ-ሬሣ ለመቀየር  ይሞክራሉ።  በኢትዮጵያ ሕዝብ አመፅ ጎርፍ-  መካከል አዲስ የሚጋልቡትን  ፈረስ ለመለወጥ ኮረቻቸውን በመደላደል ላይ ናቸው ።  የሥልጣን መላሾ  እያሳዩ የሚመለምሏቸው አዳዲስ አገልጋዮችም ተደርድረውላቸዋል።
በአሁኑ የሀገሪቱ ሁኔታ፤ ሁለት አማራጭ ለውጦች   በኢትዮጵያ ሰማይ ተንሳፍፈዋል።
1ኛ.  በይስሙላና  በውሽልሽል፤ ለውጥ ጠጋግኖ፤ የወያኔ አገዛዝ እድሜ ለመስጠት የሚድረግ  ውሽንፍር ነው። መሠረታዊ ለውጥ ሳይኖር፤  ያለው ፖለቲካ ምኅዳር ሳይነካ-ሳይናጋ-  ፀረ ሕዝብ የሆነው የወያኔ  "  ሀገ መንግሥት"  ሳይሸራረፍ ፤ ጥቂት ግለስቦችን  ለዋውጦ ማስቀጥል  ነው።   ከሆነላቸው፤ የፖለቲካው ምኅዳር  አሁንም  በወያኔ ሙሉ ቁጥጥር ስር  እንዳለ ሆኖ፤ እንዲቀጥል  ማድረግ የማጀመሪያው  ምርጫቸው  ነው።  ሕዝቡ ያነሳቸው ፤ የዴሞክራሲ ፤  የነፃነት፤ የፍትኅ-ርትዕ፤ የአድነት -የዕኩለት፤ የህግ የበላይነት ፤ የሀገራዊ  ሉዓላዊነት ጥያቄዎች  ሁሉ ተድበስብስው እንዲቀሩ  ይደረጋል ።  ሠላም ወረደ፤ አካባቢው ተርጋጋ፤ ሕዝቡ  ተደስቶ ወደ ቤቱ ገባ፤ የሚል መለከተ - ፍሰሃ ሳይሆን፤ በረከተ መርገም  ያውጃሉ ።
2ኛ.  የመላውን  ሕዝብ ፍልጎት መሠረት ያደረግ   የመሠረታዊ  ለውጥ ጥያቄ  ነው ። ስር -ነቀል የሆነ ፤ የሥርዓት ለውጥ ነው።  የወያኔን የበላይነት በሁለንተናዊ  ገፅታው  እንዳይንሰራራ አድርጎ ለማምከን የሚቻለው፤ በስር-ነቀል ለውጥ ብቻ መሆኑን  አምኖበት፤ መላው ሕዝብ ዛሬ፤ ከባድ መሥዋዕት እየከፈለ የሚታገለውም ለዚህ  ነው ። ጥጋናዊ  ለውጥ አድርጎ የወያኔን  ዕድሜ ለማስቀጠልና ወደ  ሁለተኛ የባርነት ምዕራፍ  ለመሸጋገር አይደለም ።
ሙሉ ነፃነት፤ አይከፍሉ ዋጋ እንደሚያስከፍል አምኖበት ነው ፤ ዛሬ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ  ከወያኔ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች ጋር እየተዋደቀ  ያለው።  ይኽ ከባድ መሥዋዕትን ያስከፈለ አመፅ ፤ መሠረታዊ  የሥርዓት ለውጥ እስካላገኘ ድረስ የሕዝቡ ትግል ይቀጥላል እንጅ፤ በቀላሉ አይቆምም ።
ከላይ የተጠቀሱት  እነኝህ ሁለት አማራጮች ዛሬ  በኢትዮጵያ የፖለቲካ  መልከዐ ምድር  የንዣብባሉ ።  እነኝህ ሁሉት አማራጮች፤ ሁሉት ተጻጻራሪ ባላቤቶች፤ ለ/በ ተጻራሪ ምክንያቶች ሊቆጣጠሯቸው ይሻሉ።
አንደኛው  ባለቤት፤  የጥግና ለውጥ ፈላጊ በመሆኑ፤ የህዝቡን መሠረታዊ ለውጥ የሚያደናቅፍ ነው። በመሆኑም የሕዝቡን መሠረታዊ የሆነ  የሥር ዓት ለውጥ ጥያቄ ሊመልስ አይቻለውም ። ለውጥ- አጋጅና  አደናቃፊ በመሆን የቆመ ኃይል ነው። ለውጭ ጣልቃ-ገብነት ተባባሪና አጎብዳጅ ሆኖ የሀገሪቱን ስትራተጂያዊ  ጥቅም አሳልፎ  ለመስጠት ኅሊናው የማይቆጠቁጠው ክፍል በመሆኑ፤ ለባዕዳን  አገልጋይና ጥቅም አስጠባቂ ሆኖ ይቀርባል  ። የሀገር ፍቅርም ሆነ፤  የሕዝብ  ተቆርቋሪነት ስሌለው፤ የውጭ ባዕዳንን ድጋፍና ትብብር አግኝቶ የመንግሥት ሥልጣን  ነጥቆ ፤ ሕዝቡ ከመግዛት ያለፈ ምኞት አይኖረው። በዚህ ዓይነት መንገድ  ወደ ሥልጣን  የመጣ ቡድን ፤  ዴሞክራሲ ፤ ነፃነት፤  የህግ የበላይነት ፤ የሀገር ሉዓላዊነት፤ የህግ የበላይነት ፤ የመንግሥት - ሥልጣን ክፍፍል ( ሴፓሬሽን ኦፍ ፓወር )  የነፃ ፍርድ ቤት  ኅልውና፤ የፕሬስ ነፃነት የሚባሉ ጉዳዮች በመዝገበ -ቃላቱ ውስጥ አይታወቁም ። ይኽ  ቡድን አምባ ገነን ነው ላለመባል፤ የምዕራብያኑን  የምስከር ወረቀት  ( ሰርትፊኬት ) ካገኘ ይበቀዋል ።
ሁለተኛው     ባለቤት፤ መሠረታዊ የሆነ ለውጥ ፈላጊና የወያኔ አገዛዝ በሕዝባዊ መንግሥት መተካት አለበት ብሎ ከሕዝብ ወገን የቆመ ኃይል ነው፡፡  የሥልጣን ምንጩ  ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰለሆነ መንግሥት፤ መመስረት የሚገባው፤ በዴሞክራሲ ሥር ዓትና ሂደት፤ እንጅ እንደ ሸቀጥ ዕቃ  ከውጭ ሊመጣ አይገበውም ባይ ነው። ተጠያቂነቱ፤ ኃላፊነቱና ተገዥነቱ በቀጥታ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሆነ መንግሥት ፤ ያለ ስጋትና ጭንቀት  የመረጠውን ሕዝብ ለማገልገል ግዴታ እንዳለበት ያምናል ። የዚህ ሁሉ መሠረቱ፤ የዴሞክራሲ ሥርዓት  በመላው የሀገሪቱ ግዛት ዋስትና ባለው መልኩ  መረጋገጥ ነው። ይኽ እንዲሳካ ሁሉም ኃይሎች የሚሳተፉበት የሽግግር ሂደት  እውን እንዲሆን መጣር ግድ ይላል።
ሀገራችንን ከተቃጣባት ዳግም ክኅደት እንታደጋታለን !
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኖራልች  !  


No comments:

Post a Comment