Wednesday, November 23, 2016

ነፍስ ገዳይዋን ታውቃለች/ ነፍስ ተአምር ቀታሊሃ ! ሀገር ግን አጥፊዎቿን ታምናለች ! በማመኗም ትጎዳለች !

በፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምፅ
ሕዳር 2009  ዓም  የተላለፈ   ሐተታ

           ነፍስ  ገዳይዋን  ታውቃለች/  ነፍስ  ተአምር  ቀታሊሃ !
       
 ሀገር ግን  አጥፊዎቿን  ታምናለች ! በማመኗም ትጎዳለች !

ሀገርና  ሕዝብ፤ አንድም ሁለትም ናቸው።  አንዱን ከሌላው ለይቶ ማየት ያስቸግራል።  በብዙ ሀብሎች  የተሳሰሩ፤ የተዋኻዱ ናቸውና ! ያንዱ አለመኖር፤የሌላውን አለመኖርን ያስከትላል። ሀገር ማለት፤ መሬቱና አፈሩ፤ ጋራና ሸንተረሩ፤  ወንዙና ባህሩ፤ ብቻ የሚመስላቸው ይኖሩ ይሆናል ። ይኽ አባባል ግን ብቻውን፤ ሀገርን ለመግለጽ በቂ ሊሆን አይችልም ፡፡ ያ ቢሆንማ ኖሮ ፤  እንደ ሳሃራ፤ ካላሃሪና ጎቢ የመሳሰሉ ምድረ-በዳ (በረሃዎች )   እንደ ሀገር በተቆጠሩ ነበር !  ሕዝብ ስለማይኖርባቸው የሀገርን መስፈርት ሊያሟሉ አልቻሉም ። ሀገርን፤ ሀገር ብሎ ለመጥራት፤ በግድ ነዋሪ ህዝብ መኖር አለበት ! አምጡ-ደገሙ ቢባል ሕዝብን የሚተካ  አንዳችም ነገር አይኖርም ።
 በዘመናት፤ ኢትዮጵያን/ ሀገሪቱን እንጅ ፤ ሕዝቧን አንፈልገውም በማለት፤  ዜጎቿን አጥፍተው፤ መሬቱን ለመወረስ  የሞከሩ ብዙ  የውጭ ባዕዳን  ኃይሎች ነበሩ  ። ቬኒቶ ሙሶሊኒ  በበኩሉ ፤ ወራሪውን ጦር ወደ  ኢትዮጵያ ሲልክ፤ በሮማ አደባባይ ባደረገው ዲስኩር ( ንግግር) ፤  " ሁሉን ጨርስና ብቻህን ተመለስ " ( አማሳቶ ቱቲ ኦርቶርኖ  ሶሎ !  ) ነበር ያለው።  ዓላማውም፤ ሕዝበ-አበሻን አጥፍቶ፤ በመሬቷ ላይ የኢጣሊያንን ህዝብ ለማሰፈር ነበር።  በተሰጠው መመሪያ መሠረት፤ የፋሽስቱ ኢጣሊያ ወራሪ ጦር፤ የሀበሻን ዘር ለማጥፋት የተቻለውን ሁሉ አድርጎ ነበር። ግን፤ በቂ ጊዜ ስለ አልነበረው   የኢትዮጵያን ሕዝብ  ጨርሶ ለመምተር ዕድል ሳያገኝ ቀረ።  የኢትዮጵያ  ዐርበኞች፤  ሠማዕታቱ - ጀግኖች ፤ ምስጋና  ይድረሳቸውና፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠፍቶ ሳይጠፋ ቀርቷል!  በዐርበኞቿ መሥዋዕት፤ ሕዝቧ  ከጥፋት ተርፏል ።
አምላከ- ኢትዮጵያም ፤ ሕዝቧን ከምድረ-ገፅ  ሊያጠፋባት ስለአልፈለገ ፤  ከተቃጣባት  አደጋ ተርፋለች  ብለው ፤  ምዕመናኑ ያምናሉ ። እስላምና ክርስቲያኑ !
የኢትዮጵያ ነፍስም ፤ ገዳይዋን  አውቃለች። አሁንም  ማን እንደ ሚገድላት  በሚገባ  ታውቃለች። ደርሳበታለች ! ነፍሷ እንጅ ፤ ሀገሪቱ ግን ፤ ወዳጅ ጠላቷን  ገና በሚገባ ስለአላወቀች፤ ዛሬ፤ ሀገር በቀል የሆኑ የትግራይ ፋሽስቶች፤ መሬቷን እየዘረፉ ዜጎቿን እያጠፉ ናቸው። ለዚህ እኩይ ዓላማ የመጀመሪያው ዒላማቸው ዐማራ ስለሆነ፤ ዘር- ማንዘሩን  ለማጥፋት  በሰፊው  ተያይዘውታል  ። እንደ  ወራሪው  የኢጣሊያን  ጥቁር ሸሚዝ  ለባሽ ( ኻሚሻ ኔራ )  ነብሰ-ገዳይ ጦር፤  ወያኔም  ዛሬ፤  ዐጋዓዚ የሚባል ነፍሰ ገዳይ ታጣቂ  አዘጋጅቶ፤ ይጨፈጭፋል ።  ያስጨፈጭፋል ! እነኝህ ዘረኞች ፤ጊዜ ከተሰጣቸው፤ ብዙ ሳይቆዩ   መጀመሪያ ዐማራን አጥፍተው፤ ሌላውንም በየተራው  እያጠፉ፤  የተመኙትን ድል መጎናፀፋቸው አይቀርም ። ለወያኔ ፤ መሬት እንጅ፤ ሕዝብ ኖረ አልኖረ፤  ጉዳዩ አይደለም።   
ወትሮውኑም ቢሆን፤ ነፍስ ፤ የሚያጠፋትን  እያወቀች፤ ዐውቃ ትጠፋለች።  ግዑዟ መሬትም በበኩሏ ፤ አጥፊዎቿን እያመነች በእነርሱ እየተዝናጋች  ትከስማለች።  " በሬ ካራጁ ጋር ይኖራል ! " እንዲሉ፤ ሀገርም  በአራጆቿ  ትታረዳለች ! ያሞራ ሲሳይ ሆና ትቀራለች  ! ሕዝብ ከጠፋ ፤ ሀገር ፤ምድረ -በዳ ሆና ትጠፋለች  ማለት ነው።
" የጨነቀው ዕርጉዝ ያገባል " እንዲሉ፤ አንዳንድ ግራ የተጋቡ ክፍሎች፤  መንግሥትን መለወጥ ሲያቅታቸው፤  " ሕዝብ ይቀየርልን " ብለው ሰላማዊ ሰልፍ ይወጣሉ። የትኛውን ሕዝብ ቀይረው፤ በየትኛው ሕዝብ እንደሚተኩ  ግን  ምንም ሃሳብ  የላቸውም ። ይኽ ደግሞ፤ ለሰሚው ግራ፤ ሆኗል።
 ተወደደም ተጠላ ፤ ዛሬ ፤ ደም አፍሳሽ ፤ ዕልቂት ደጋሽ የሆነ ፤ኢትዮጵያን እያጠፋ  የሚገኝ ዘረኛ ቡድን አለ።  በሕዝብ ትኩሳት የተኮማተረ ፤  በሠረዊቱ  ክዳት፤ የተወጠረ፤  ስረ- መሠረቱ የፈረሰ ፤ ዕለተ- ሞቱ የደረሰ ፤ በሕዝብ የተተፋ፤ ስብዕናው የከረፋ ፤ የገዥ ስብስብ አለ ። ሰማይ - ምድሩ ቢደፋበትም ፤ እርሱን ግን በአፍ-ጢሙ የሚደፋው ኃይል ገና አልተሰባሰበም ።  "  ይኽንን ሀቅ፤ እየጎመዘዘ ቢሆን፤ የሚመለከተው ሁሉ  አምኖ መቀበል ይኖርበታል  !
 " እረ ለምን ይሆን ያልተሰባሰበ፤ ያልተስተባበረ ?
   ዕውቀት  ጠፍቶበት ነው  ያልተመራመረ ?
   ፍቅር  ተነፍጎቶ  ነው  የልተመካከረ  ?
   ቋንቋውን  አጥቶ ነው  ያልተነጋገረ  ?
   ዓላማ ቢስ ሆኖ  በከንቱ  የቀረ፤ ሀፍረተ-ቢስ ሆኖ አንገት የቀበረ  ?
እየተባለ  ዘወትር የሚጠየቀውን የሕዝብ ጥያቄ ፤ በድፍረት ለመመለስ የሚችል ባለመገኘቱ ፤የሁሉም ዜጋ አግራሞት ሆኗል     እንደ ምንም ብሎ  ያመረቃ  መልስ  አግኝቶ መፍተሄውን ካላመጣ፤  ማለቂያ- መዛለቂያ ወደማይገኝለት አዙሪት ገብቶ፤ እየተሽከረከረ ፤  ፍፃሜ ህይወቱን ይጠብቃል   እስከዚያው ድረስ ግን ፤  ከህያው በታች፤ ከሙታን በላይ ሆኖ ፤ ህይወት አይሉት ኖሩ፤ ሞት አይሉት፤ ፃዕረ- ሞት እያስተናገደ ለመቆየት ይገደዳል።
 የተስፋ ጭላንጭል የተዳፈነበት ኅብረተስብ፤ ምን ጊዜም ቢሆን፤ በራስ መተማመን አልሆንለት ሲለው ፤ የውጭ  ባዕዳንን ርዳታና ትብብር ለማግኘት  ይፍጨረጨራል ። ባዕዳኑ  ደግሞ፤ የእርሱ መፍጨርጨር ፤ ጉዳያቸው አይደለም።  ሠላማዊ ሠልፍም ሆነ፤ የአቤቱታና የተማፅንኦ ጋጋታ ፤ ብቻውን የትም እንዳለደረሰ  ለመረዳት እንኳ ፤ ገና አልተዘጋጀም ።  አሁንም ፤ የፈረንጆቹን  መዝጊያ ማንኳኳት ፤
 ሥራየ-ጉዳየ ብሎ ቀጥሎበታል    ፈረንጆች ግን፤ ቅድሚያ የሚሰጡት ለራሳቸው ብሄራዊ ጥቅም በመሆኑ፤  የፈለገው መጥቶ በራፋቸውን ቢያንኳኳ፤ ገርበብ አያድርጉለትም። ይኽ ሀቅ ደግሞ፤ ለአለፉት ዐርባ  ዓመታት በግልፅ  የተረጋገጠ ዕውነታ ነው ። በራስ መተማመን መተኪያ የለውም።
 ያ ስለተባለ ግን፤ ማነኛውም  የውጭው  ርዳታ ጭራሽ አያስፈልግም  የሚል ነገር ማስተናገድ የፖለቲካ  እንዝኅላልነት  ብቻ ሳይሆን፤  የዓለምን ዲፕሎማሲ ይትብሃልንም አለመረዳት ጭምር መሆኑን እንገነዘባለን።  ዛሬ በሥልጣን ላይ ያሉት ሻዓቢና ወያኔ ዓላማቸውን ያሳኩት ፤ ያለቋረጠ- ያልተቆጠበ ፤ የውጭ ርዳታን  በማግነታቸው እንደሆነ የማይካድ ሃቅ ነው ።  የውጭ ርዳታን  ሲቀበሉ ግን፤  በኢትዮጵያ ኅልውና  በዜጎቿንም አንድነት ላይ በመደራደር  መሆኑ  የሚካድ አይደለም ። ይኽ ደግሞ፤ በብዙዎቻችን  ዘንድ የሚታሰብ፤ የሚሞከር ፤ የሚፈትን ፤ የሚዋጥ  አልነበረም።  ውጤትም ፤ይኸው ዛሬ ገሃድ ሆኖ ተቀምጧል ። ነብስም ገዳይዋን አውቃለች። ሀገርንም የሚያድናትን  ትፈልጋለች።   ነፍስ የሌላት ሀገር፤ አዳኝ ከሌላት ፤ ገዳይዋን እያወቀች መኖሯ ብቻውን የትም አያድርሳትም።
መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ያቀፈች ሀገር ፤ ትልቅ ኃይል እንዳላት አውቃ ከልተጠቀመችበት፤  ካልዳነችበት፤ ለነፃነቷ ዋስትና እንዲሆን ካላደረገችው ፤ የታሪክ መተረቻ፤ የትውልድ መዘባበቻ ሆና  ከመቅረት አትተርፍም።  ሀገራችን፤ ይህንን ዕምቅ ኃይሏን  በአግባቡ ገና አልተጠቀመችበትም ። ዛሬ፤  በየቦታው የፈነዳውን ሕዝባዊ አምፅ  እንኳ፤  ባንድ ምዕራፍ እንዲተባበር ያደረገ ኃይል/ ድርጅት  ገና አልወጣም  ።ያ እስካለመጣ ድረስ፤የትግሉ  ሜዳ፤ እንደ አህያ ርሻ፤ ፈር አልባ ሆኑ ይቀራል  ። ይህ ክስተት በበኩሉ፤ ኢትዮጵያ ፤ ገዳይዋን ያወቀች ምድር ብትሆንም ቅሉ፤ አዳኟን ለማግኘት ያልቻለ  ሀገር ሆና ትቀራለች።
ባሁኑ ወቅት፤  አብዛኛው እጅ-እግሩን  አጣጥፎ  የሕዝቡን አመፅ  በአርምሞ ከመመልከት ያለፈ፤ እንቅስቃሴ ሲያደርግ አይታይም።  አመፁን፤ በቀጥታም ይሁን  በተዘዋዋሪ ለመርዳት የሚያደርገው አንዳችም እንቅስቃሴ አልተከሰተም ። የተስፋ ዳቦ እየቆመጠ  መጠባበቅን  የመረጠ ይመስላል።
ጎንደር- ጎጃም አምፅዋል!  ኦሮሞ ተንቅሳቅሷል !   የአዲስ አበባ ነዋሪ አድፍጧል  "አኮርፏል!። ወሎና  ሸዋ በልቡ ሸፍቷል !   አድብቶ ተቀምጧል ! አመች ጊዜ እየጠበቀ ነው  !  ሌላው ሌላው ወያኔን ጠልቶ  ፊቱን አዙሮበታል !  የወያኔ ሠራዊትም ፤ አድፍጦ  ቁጭ ብሏል !  መናልባት መፈንቅለ መንግሥት  ያደርግ ይሆን ? " አይተነው ጊዜ ወደ አደላበት " የሚለው ዜጋ ቁጥሩ ብዙ ነው  !  ውድ  ሕይወቱን   እየከፈለ  የሚታገለው   ወጣት እኮ ፤   እስካሁን   መሪ አላገኘም ! " እናቴን ያገባ ሁሉም አባቴ  ነው ! እኔ ምን ቸገረኝ !  "  የሚሄደው ሄዶ ፤ የመጣው ቢመጣ፤ ኩርማን እንጀራ አላጣ ? " ሽ ቢታለም ፤ ያው በገሌ " በላ የለ እንዴ ድመቷ  ?  የሚለው ዜጋ  ቁጥሩ  የሚናቅ አልሆነም ። " ኽረ ለመሆኑ፤ የትግራይ ሕዝብ፤ ለምን ዝም አለ  ? "  እነኝህና ሌሎች  ተመሳሳይ  አባባሎች፤ በአሁኑ ወቅት፤ በማኅበራዊ  መድረኮችና የውይይት ማዕከላት( ሶሻል ሜዲያ ) በመንሸራሸር ላይ ናቸው።  
እነኝህ ሁሉ አስተሳሰቦች፤  ምናልባት " ሥራ ከመፍተት ፤ልጄን ከትዳሯ ላፋትት " ለሚለው ወግ ይጠቅሙ  እንደህ እንጅ፤  የሚፈይዱት ዕርባና ግን  አይኖርም።  ሕዝብ የፈለገውን አስተያየት ሊገልጽ አይገባው  ለማለት  ባይቻልም ፤  ትኩረት  አስመጭ ፤ አቅጣጫ ሰጭ  የሚሆኑ አይደሉም ።  ወያኔ ዛሬ የሚፈልገው  ደግሞ ፤ ሕዝቡ ትኩረቱን  ወደ አንድ አቅጣጭ አዝንብሎ እንዳይተባበር ማድረግ ስለሆነ፤  የሕዝቡ አቅጣጫ  ማጣት ፤  እርሱን  ይጠቅመዋል እንጅ ፤ የሕዝቡን ትግል ግን ወደፊት ሊያራምደው አይችልም ።
ይኽን ሁሉ ክስተት ሊፈጠር  የቻለው ፤ ሀገራዊ የሆነ አመራር ተፈጥሮ ፤ የትግል አቅጣጫ  የሚሰጥ ኃይል ባለመኖሩ እንደሆነ ማንም የሚክደው አይደለም። እታገላለሁ የሚለው ፤ በአመዛኙ፤ በልሃቱን ገና ሊያገኘው አልቻለም ።  
 " ኢትዮጵያ፤ ጉደኛ ሀገር ነች ! " ከሚያስብላት አንዱ እኮ፤ የችግሯ ውስብስብነት ብቻ ሳይሆን፤ ዜጎቿም መስማማት አለመቻላቸውም ጭምር ነው።   በዚህም ይመስላል ፤  አንደኛው፤  ከሌሎቹ  ቀድሞ ፤ ሌሎቹን መንቀፍና ማሳጣት ፤ እርሱን ከወቀሳ ነፃ የሚወጣው እየመሰለው፤ የጭቃ- ጅራፉን ማሰማት የሚሽቀዳደመው ። ሌሎቹን ማስጠላት፤ የእርሱን ተወዳጅነት የሚያስገኝለት ይመስለዋል ።  
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ፤ ካሳሽና ተከሳሽ፤ ቁጥር-ስፍር የሌለው  መሆኑ ቢታወቅም ቅሉ፤ ከኅሊና -ወቀሳ ነፃ የሆነ  ዳኛ ግን ሀገሪቱ ልታገኝ አላገኘችም። አላፈራችም። የኅሊናቸው ተገዥ የሆኑ ዳኞችንና መሪዎችን  ማፍራት ያልቻለ ሀገር ሆናለች  !  የሚከበር - የሚታፈር ሽማግሌም በሀገሪቱ ጥፍቷል ።  የተከበረ ሽማግሌ ካልተገኘ ደግሞ፤ የተሳሳተውን አራሚ፤ ያጠፋውን  መካሪ፤ የተጣላውን አስታራቂ፤  ትዕቢተኛውን  አራቂ ፤  የተወናበደውን ምክር ሰጭ ፤  ባድባሩ- ባውጋሩ በሀገሩ ፤  በሰፈሩ  ጠፍቷል ።  ያ በጠፋበት ሀገር ደግሞ ፤ የተረጋጋ ህይወትና  የኅሊና ነፃነት  ተገኝቶ በምክንያታዊ ላይ የተመሰረት ውይይትና መደማማጥ አይመጠም ።  በአመዛኙ፤ እስካሁን የተደረጉት ውይይቶች ሁሉ " የጨረባ  ተስካር  " ከመሆን አላለፉም  ። በዚህ ምክንያት ነው ፤ እርስ-በእርስ፤ መተማመን- መደማመጥ- መቻቻል- መሰማማት  እየጠፋ ፤ አስታራቂ ፍለጋ  በየፈረንጆቹ ቢሮ ማንኳኳት ፤ እንደ ቆም ነገር የተያዘው።   ለዚህም እኮ ነው፤ ያገራችን ታዛቢ፦
   " እንከረተታለሁ አራዳ ለአራዳ ፤
     በፈረንጆቹ  ሀገር በማላውቀው  ጓዳ
     እጁ እንደተያዘ  ከብቱ እንደተነዳ ! "
    መክፈል እያቃተኝ  ያባት የናት   ዕዳ፤
    አስተላላፊ ሆንኩ  ለተከታይ ትውልድ፤ ለምጭው እንግዳ ።  "
ብሎ የተቀኘው ።
አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ፤ ምን ያህል በትክክል ፤ወዳጅ-ጠለቷን ፤ ማወቅ- አለማወቋን  ለመረዳት ባይቻልም፤ ነፍሷ ግን ገዳይዋን ታውቃለች !   " በሬ ካራጁ ጋር ይኖራል "  እንዲሉ፤  እርሷም ፤ ከገዳዮቿ  ጋር ለመኖር ተገድዳለች  የሚያላቅቃት ግን ገና አላገኘችም !  ማግኘቷ ደግሞ አይቀርም !
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኖራለች  !
         No comments:

Post a Comment