Wednesday, July 5, 2017

የጀግናውን ትውልድ ታሪክ ጥላሸት መቀባት የራስን ወንጀል አይደብቀውም ! የፍኖተ ራዲዮ ሐተታ

የጀግናውን ትውልድ ታሪክ ጥላሸት መቀባት

የራስን   ወንጀል   አይደብቀውም  !
ያለፈውን ታሪክ በትክክል አውቆ  መገንዘብ ፤ የወቅቱን ሁኔታ በሚገባ ለመረዳት ያስችላል። ያንን አውቆ መገኘት ደግሞ፤ የወደፊቱን ራዕይ አርቆ ለማየት ዕድል ይሰጣል  ።ከዛሬው ትውልድ በፊት መልካም ተግባር አስመዝግበው ያለፉትን ቀደምት ጀግኖች ፈለግ ለመከተል መነሻ ይሆናል ። የተፈፀሙትን ስህተቶች እያረሙ ፤ የጎደለውን  እያሟሉና   የተዛነፈውን እያስተካከሉ  መጓዝ  ሀገርን ለመገንባት  መሠረት ይሆናል ። በዘመናት የተገነባውን  መልካም ተግባር እያፈረሱ  አገር መገንባት ግን  አይቻልም። የራስን ጥፋት በሌላ ለማላከክ ሲባል ፤ ያልሆነና  ያልነበረ  ኩነትን  ማሰራጨት  የታሰበውን ውጤት አያስገኝም።  እንዲያው፤ " በሬ ወልዶ፤ ዕመጫት ሆነ " ከሚለው ተረት -ተረት አያልፍም።
የቀድምት ሠማዕታትን  ታሪክ ጥላሸት እየቀቡ፤ የራስን ከንቱ ውዳሴ  ማሞካሸት ተቀባይነት አያስገኝም። ለአላፉት ሃያ ሰባት ዐመታት የተፈፀሙትን ሀገራዊ  ወንጀሎች ለመሸፈን ሲባል ፤ ስውዕ ጀግኖችን ለመሥዋዕት ጠቦት ማቅረብ  ትርፉ  ቅሌት ብቻ ነው። ይኽንን ለማድረግ፤ የአሁኑ ነባራዊ  ሁኔታ  የሚፈቅድ አይደለም ። ዘመኑ፤ የመረጃ ፍሰትና የዜናዎች ስርጭት ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ  ከመቅፅበት የሚናኝበት በመሆኑ፤ ምንም ሃቅ ከማንም  ሊሚሰወር አይችለም ።
አምባገነኖች፤ ምን ጊዜም እውነት እንዲወጣ፤ ሀቁ እንዲገለፅ አይፈልጉም ። የሀቅ ደመኞች ፤ የዕውነት ባላንጣዎች በመሆናቸው፤ ጉዳቸውን ለመሸፈን፤ ድርጊታቸውን ለመሰወር፤ ይደክማሉ። ከሚያደርጉት ፍሬ ቢስ ሙከራ፤ የሕዝቡ ትኩረት በሀቅ ላይ እንዳያዘነብል፤ የዕይታ አቅጣጨውን ለማስቀየር ፤ ይጣጣራሉ። የወንጀላቸው መሸፈኛ  እንዲሆንላቸው፤ በግድ ሌላ የመሥውዕት ጠቦት ይፈልጋሉ።  አዳም በሚስቱ፤ ሚስቱ በዕባብ፤ ዕባቡ በዳቢሎስ፤ ወንጀላቸውን እያላከኩ የሚሸሸጉበት  ጊዜ፤ በዘመነ ኦሪት አልፏል።   ዛሬ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ንቃተ ኅሌና ከሚጠበቀው የዕድገት ዕርከን  አልፎ ፤ ላዕላይ ደረጃ ስለደረሰ፤ በዘረኞች የታሪክ ብረዛ ሊወናበድ  አይችልም።
አምባገነን  ገዥዎች ይኽንን ሃቅ በመጠኑም ቢሆን ስለሚረዱ፤ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን  ከማፈን በቀር፤  ወያኔዎች ሌላ ምርጫ አላገኙም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ  መብቱን አግኝቶ እንደልቡ የመጠየቅና  ሁሉን  የማወቅ  ዕድሉን ሲያገኝ ፤ ብሎም፤  ማን ምን እንደፈፀመ ፤ዕርግጠኛውን  መረዳቱ አይቀሬ ነው ። አንድ ድርጊት ፤ መቸና የት እንደተፈፀመ፤  በማንስ እንደተፈፀመ ፤ መታወቁ አይቀርም    " ጊዜ  መሥተዋት " ስለሆነ ፤ ማነኛውንም ጉዳይ  ፍንትው አድርጎ  የሚያሳይበት ወቅት  ይመጣል   " ዕይኝ-ዕዩኝ  " የሚለው  ሁሉ ፤ " ደብቁኝ፤ደብቁ ኝ " ማለቱ አይቀርም ።  በፍርድ ቀን ፤ " የዕናቴ ቀሚስ አደናቅፎኝ !  ወይም ደግሞ፤ "  ከበላይ አለቆቼ ታዝዠ ነው " የሚባል ነገር አያዋጣም ።  በዐለም-አቀፉ  ፍርድ  ሸንጎ ፤ የናዚ ወንጀለኞች " የበላይን ትዕዛዝ ለመፈፀመ ነው  " ያሉት  ተማጽንኦ፤  ከተወሰነባቸው ቅጣት ሊያድናቸው አልቻለም ። እርሱ ራሱ ሂትለርም ቢሆን፤ የፈፀመውን ወንጀል አስቀድሞ በመረዳቱ፤ ራሱን በቢንዚን ነበር አቃጥሎ የተገላገለው።  ከፍርድ ሸንጎ  ለመሰወር  ቢሞክርም እንኳ ፤ ከታሪክ ወቀሳና ብይን ግን  ሊያመልጥ አልቻለም።
ከሦስት ሽ ዘመን በላይ  ያስቆጠረ ታሪክ  ያስመዘገበች  ሀገር ፤ የኅልውንዋ አሃዝ  አንድ ተብሎ የሚቆጠረው/ የሚጀምረው፤ ኅወሃት ሥልጣን ከጨበጠ ወዲህ ነው ብለው ይኽንን ትውልድ ሊያስተምሩ ይደክማሉ። የወጣት አዕምሮ፤ በመሠረቱ፤ ተከታታይ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ምክንያታዊና ተመራማሪ ጭንቅላት ስለሚኖረው፤ የወያኔን " ዶሮ ጭራ በቀላሉ የምታመጣውን መልስና አምክንዮ አይቀበልም።  ከእርሱ በፊት የነበረውን  መሥዋዕታናዊ ጀግና ትውልድ ገድለ- ታሪክ፤  ትክክለኛውን ምክንያትና ድርጊት ተመራምሮ ድርሶበታል  ። ያልደረስበትንም ወደፊት  እየጠየቀ  ይደርስበታል   ነግ -ተነገ ወዲያ ዕቅጩን ሃቅ ያገኘዋል 
ትላንት ወያኔዎቹ  "ብጣሽ ጨርቅ ነች" ብለው የረገጧትን  ታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ፤ ዛሬ፤ ወጣቱ ትውልድ፤ ዕርማዋን ከፍ አድርጎ ይዞ ፤ ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ እያከበራት ነው። የወያኔን ፀረ ኢትዮጵያ ድካም መና አስቀርቶታል !   ይኽ ክስተት ጎልቶ የሚያሳየው አንድ ሃቅ ቢኖር፤ የኢትዮጵያ መሠረት በቀላሉ የማይናወጥ መሆኑን ነው። የውስጥ ሰር ሳሪዎቿንና የውጭ ወራሪዎቿን፤ እንደ አመጣጣቸው የተጋተረቻቸውም፤ ዋናው  ምክንያትና ዐብነት ይኽ ነበር።
የኛ ብርቱ ችግር፤ የውጭ ጠላቶቻችን ብርታትና የውስጥ ቀበኞች ተንኮልና ችሎታ  ሳይሆን ፤ የራሳችን-የግላችን  ድክመትና ያለመተባበር አባዜ  መሆኑን  ከመራራው ትግል ለመገንዝብ  ችለናል   ከውጭ አጥቂዎች ልንጠቃ የምንችለው፤ በአመዛኙ በውስጥ ከሃዲዎችና ቅጥረኞች የክኅደት ትብብር  መሆኑ፤ በተደጋጋሚ የተመዘገበ ሀቅ ነው። በጥርኝ  ሽምብራ፤ የሀገርን ዘላቂ ጥቅም የመለወጡ ክህደት በየዘመናቱ ተመዝግቦ ቆይቷል ። ይኽ ክስተት ደግሞ፤ ማነኛውም  ኅብረተሰብ፤ እንደ ኅብረተሰብ መቀጠሉ እስከቀጠለ ድረስ መቀጠሉ አይቀርም።
ምናልባት ከዚህ አደጋ ባስተማማኝ ደረጃ መከላከል የሚቻለው፤ የሀገሪቱ ነዋሪዎች፤ ሁሉም ተማምነው በሚያቋቁሟቸው ተቋማት ጥንካሬና ችሎታ ይሆን ይሆናል ። የተቋማቱ ሁሉ  ተቋም፤ሕዝቡ በፈቃዱ ተስማምቶ የመሠረተው የሀገሪቱ ህገ መንግሥት መሆኑ አያከራክርም። ይኽንን የሀገሪቱ ላዕላይ ተቋም መሠረት አድርገው የሚቋቋሙት  ሎሎች ተቋሞች የህገ መንግሥቱ ንዑሳን ተቋሞች ይሆናሉ። በመሆኑም፤ ብሄራዊ ድኅነትንና  የሕዝቡን ሠላም የመጠበቅ ተግባር ብቻ ሲባል የሚመሠረቱትን  ተቋማት በኃላፊነት የሚመሩት  ባለሥልጣናት፤ ተዐማኒነታቸውና ምሉዕነታቸው  እንከን የማይወጣባቸው መሆናቸው ሊረጋገጥ ይግባል። በዋናነትም፤ ኃላፊነታቸውና ተጠያቂነታቸው ለሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ብቻ   ስለሚሆን ፤ የተግባር አፈጻጸማቸውና ኃልፊነታቸው በህግ ይገደባል  ። ከዚህም በተጨሪ፤ ሥልጣንን ያለአግባብ እየተጠቀሙ  ሕዝብን እየበድሉና ሀገርንም እየጎዱ ሊቆዩ አይችሉም።
ያ ትውልድ ፤ ለህግ የበላይነትና  ተጠያቂነት ፤ለሕዝብ ለዕልና፤ ለሀገር ሉዓላዊነት የሚለውን መሠረታዊ መነሻ በማድረግ፤  የሚያኮራ መሥዋዕት ከፍሎ ያለፈ በመሆኑ፤ ሀገሩንና ህዝቡን አኩርቶ ከንዱን ተንተርሷል ።  እጁን ለማንም አልሰጠም። አንገቱን አልደፋም ። ቅስሙን  አላሰበረም ።  የዕወቀት ደረጃውና  የዕድሜ መጠኑ የፈቀደለትን  ያኽል፤ የሀገሩን ታሪክና የህዝቡን  አኗኗርና ሁኔታ ተገንዝቦ ነበረ።   ይህንን የተቀደሰ ዓላማ አንግቦ በመታገል፤ ለተተኪው ትውልድ መልካም ዐርዓያነቱን አስረክቦ አልፏል ። ከማንምና ከምንም በላይ፤ የሀገሩንና  የሕዝቡን ስትራተጂያዊ ጥቅም  ጠብቆ ማስጠበቅ፤የትግሉ ምክንያት ነበረ። ይኽም በድቡሽት ላይ የተሰራ የሳር ጎጆ ሳይሆን ፤ በፅንዑ ዐለት ላይ የተገነባ  ዕምነት ነበር። የማይናወጥ! በጊዜና በሁኔታዎች የማይሸረሸረ ! የማይበገርና የማይፍረከረክ፤ ኢትዮጵያዊ ዕምነቱ ነበር።  አሁንም ቀጥሏል !
አፍራሽ ኃይሎችና ተገንጣይ ቡድኖች፤ ከኢሕአፓ ጋር ዕሣትና ገለባ የሆኑትም ዋናው ምክንያት ይኸው ነበር። ይኽ ሁኔታ አሁንም ቀጥሏል።  ኢትዮጵያ ከመፈጥፋቷ አስቀድሞ  ፓርቲው  ይጠፋ እንደሁ እንጅ፤  ኢሕአፓ፤ ከአፍራሽ ኃይሎች ጋር  በተጻጻሪነት መቆሙን ይቀጥላል። እነርሱም ይኽንን ሃቅ በሚገባ  ያውቁታል !  የተዋወቀ ባላንጣ፤ እንደ አባት -አደሩ፤ ምላጭ ተሳስቦ እንደሚቆይ፤ የታወቀ ነው።  በዚህ ምክንያት፤ ነው ዛሬም ወያኔ የዚያን  ሠማዕታዊ ትውልድ ታሪክ፤  ጥላሸት  ለመቀባት ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኘው!
ለእኛ፤ የሀገራችን ታሪክ፤ ወያኔዎቹ እንደሚያሽሟጥጡት፤ " የደብተራዎች ድርሰት፤ በብራና የተገነዘ  የአፍ- ታሪክ "  አይደለም።  የኢትዮጵያ  ታሪክ ፤ በሕዝቦቿ ደምና አፅም  የተገነባ፤ ክቡር-ድንቅ  የሆነ ሕያውና ዘለዓለማዊ  የዜግነታችን መሠረትና የማነነታችን ስንክሳር ነው።  የመንግሥታት አገዛዝና  የሥርዓት መለዋወጥ ኽይንን ሃቅ አይለውጠውም። የዛሪዎቹ  አደገኛ ፀረ-ኢትዮጵያ ቡድኖች፤  የሀራቸውን  ዕውነተኛ ታሪክ  ወጣቱ ትውልድ እንዳይማር  ዕድሉን ዘገተውበታል ።   በሀገሪቱ የትምህርት ተቋማት በሙሉ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ሥርዓተ- የሚባል ነገር የለም።  የዚህ ትምህርት  ክፍለ ጊዜ ተሰርዟል  ። ይኽ የሚያሳየው፤ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንዳልነበረች፤ አሁን እንደሌለችና ወደፊትም ልትኖር እንደ ማይገባት የሚመኙት  ፅልመተ- ራዕይ ነፀብራቃቸው ሆኗል ። ትውልድ ገዳዮች ሆነዋል ።  አንድ ትውልድ፤  የሀገሩን ታሪክ እንዳይማር ዕድል ከሚዘጋ የበለጠስ ምን ትውልድ ገዳይ ሥርዓት ሊኖርስ/ ሊመጣስ  ይችላል?
ኢትዮጵያን  ጥንታዊትና  ታሪካዊት  ሀገር መሆኗን የሚመሰክሩ፤ መጻፍትና ልዩ ልዩ ድርሳናት፤ መተኪያ የማይግኝላቸው ዕጹብ-ድንቅ የሆኑ ዕቃዎች፤ አልባሳት፤ ሃይማኖታዊ ምልክቶችና የታሪክ ማስረጃዎች  ሁሉ፤ በመዘረፍ ላይ ይገኛሉ። በሚያስደነግጥ ፍጥነት ወደ ባዕድ ሀገራት እየኮበለሉ ለዐለም ገበያዎች በሃራጅ ይቸበቸባሉ።  አድባራት፤ ገዳማት፤ ሌሎች ሃይማኖታዊ መካናት እየተበዘበሩ ባዷቸውን  ወና ሆነው ቀርተዋል ። ሀገሪቱ ተቋርቋሪ ኃይል በማጣቷ ምክንያት ጓዳዋ ክፍት በመሆኑ፤ ለዘራፊዎችና  ወራሪዎች ተመቻችታ ተስጥታለች።  ውስጠ- ምሥጢሯ፤ ጓዳ -ማጀቷ፤ ለበዕዳን ሀገር-ጉብኝዎችና ሰላዮች  የወርቅ ማዕደን ሆናለች።
ሀገራችን ፤ በረዥም ዘመናት ታሪኳ ገጥሟት የማያውቅ ምዝበራ እየተፈፀመባት ትገኛለች ። ይኽ ሁሉ በደል መፈጸሙ አልበቃ ብሏቸው፤ ወያኔዎቹ፤ ወጣቱን ትውልድ የሀገሩን ታሪክና ባኅል፤ እንዳያውቅ  ፈርደውበታል  ። በሙያ ዘርፉ የታካኑት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ጠበብትና ተመራማሪዎች ከቦታቸው እየተነሱ የምሁር  ጥልቅ  አገልግሎት  እንዳይሰጡ ተባረዋል ። የዩኒቨርሲቲው የታሪክ ክፍል ተዘግቷል  ። ወያኔ ይኽንን ፀረ- ኢትዮጵያ ወንጀል የሚፈፅመው ያለምክንያት አይደለም።  ጥንታዊቷ ሀገር ደብዘዋ ጠፍቶ፤ ታሪኳ ተደምስሦ ፤ ማንነቷ የውሃ ሽታ ሆኖ እንዲቀር በመመኘት  ነው።
ይኽ ምኞቱ ግን ተፈፃሚነት አይኖረውም ። ይኽ ሙከራ፤ በተደጋጋሚ ታይቶ ነበር። ቱርኮች፤ ግብፆች  ዐረቦች፤ ድርቡሾት፤ ጣሊያኖች፤ ስፓኞች፤ ፖርቱጋሎች፤  እንግሊዞች፤  ሁሉም በየተራ ሞክረው ነበር። የዘረፉት ዘርፈው ሄዱ እንጅ፤ጥንታዊቷን  ኢትዮጵያ፤ እንዳልነበረች ሆና እንድቀር አላደረጓትም። ለጥንት ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት አባቶች፤ ጀግኖች ዐርበኞችና በተቅላላውም ሕዝበ-ክርስቲያኑና ሙስሊሙ ዜጋ  ክብር-ምስጋና ይድረሳቸው እንጅ፤ ሁሉም በመተባብር ኢትዮጵያን አቆይቷታል ። ዛሬስ ?  ይኽንን ጥያቄ ለመመስ ፤ ዴታው፤ በወቱ ትውልድ ላይ አነጣጥሯል  !ኃላፊነቱን በብቃት እንደሚወጣም ይጠበቅበታል።  ይኽ ዕምነትና ተስፋ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የሚከተሉት ጥሪዎች፤ በቅደም -ተከተል  ተላለፋሉ፦
1ኛ. የዛሬ ትውልድ፤ የሀገሩን ታሪክና ባኅል እየተከላከለ፤ የወያኔን አፍራሽ ፕሮፕጋንዳ ዋጋ ሳይሰጥ፤ ሃቁን እየመረመረ ፤ እየፈተሸ፤ እየጠየቀ እራሱ መረዳት አለበት።
2ኛ. ሀገሩ ከተቃጣባት ዐደጋ ለማውት በሚደረገ  የሞት-ሽረት ትግል፤  የትውልድ ኃላፊነት እንዳለበት ሊያውቅ ይገባል  ። ስለራሱ ሀገር ታሪክ፤ ከእርሱ- ከራሱ-ከባለቤቱ የበለጠ ሊያስተምረው የሚችል እንደሌለ ይወቀው።
3ኛ. ለፋፋዮችና ለዘረኞች፤ ሮውን ነፍጎ፤ አንድነቱን አንክሮ፤ ተባብሮ መታገ አለበት ።
4ኛ. የነገውን ኢትዮጵያ ታሪክ ለመስራት በትምህርትና ዕውቀት ተስናድቶ መቆየት አማራጭ የለውም ።
5ኛ.  ሀገር ማለት ጋራና ሸንተረሩ፤ ሜዳውና ሸለቆው፤ ጠረፉና ዳር ድምባሩ ብቻ ሳይሆን፤ ሕዝቡ፤ ታሪኩ ባኅሉና  ቋንቋው፤ ዕምነቱና ስተጋብሩንም ጭምር  የሚያካትት ስለሆነ ፤ ይክንን አስመልክቶ የሁለንተናዊ ግንዛቤ  ባለቤት መሆኑና በራስ የመተማመን  ዕምነት እንዲኖረው እናሳስባለን 
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኖራለች !


1 comment:

  1. በደንብ አድርጎ ኢህአፓ መንቀሳቀስ ያሻዋል ኢትዮጵያ በጣም አደገኛ ግዜውስጥ ነው ያለችው የኢትዮጵያን ፖለቲካ አቀማመጥ እና መነሻና መድረሻ እንደኢሕአፓ አበጥሮ የሚያውቅ ፓርቲ የለም ፣አሁን ሰአት ያሉት ፖለቲከኞች በሙሉ እንዳሉ ብደርግ ግዜ ወጣቱን ያሯርጡ የነበሩ በመኢሶን እንዲሁም በእጫት ስር ደርግን ሲያገለግሉ ፡ የነበሩ የሰይጣን እና የነዋይ ሃይሎች እንደ እስስት ቀለማቸውን ለውጠው የወያኔን ወያኔ ሰራሽ ፓርቲዎችን በመቀላቀል ያው የተካኑበትን የአገር ሻጭነት እና የአገር ክህዲነታቸውን ቀጥለውበት ካራክተር አሷስኔት ተግባራቸውን አሁንም ኢሕአፓ ላይ አድርገዋል ስለዚህ እንዲ አይነት ፅሁፎች በጣም አስፈላጊዎች ናቸው ስለዚህ ይልመድብህ እላለው ለፀሃፊው ወንድሜ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር።........

    ReplyDelete