Monday, November 27, 2017

ለመጪው ትውልድ አይለጉት ሐኬት---- ዴሞክራሲያ

ዴሞ ቅጽ 43 ቁ 1

መስከረም/ጥቅምት 2010 ዓ.ም
ለመጪው ትውልድ አይለጉት ሐኬት
ታሪክ ራሱን ይደግማል ተብሏል። ሲደግም ግን መቸም ቢሆን ያለፈው መቶ በመቶ ቅጂ እንደማይሆንም እንዲሁ ተነግሯል። የኅብረተሰብ ዕድገት ሕግ የሁኔታዎችን ለውጥ ግድ የሚል ነውና ታሪክ መመሳሰሉ አንድ ነው የሚያስብል አይደለም ።የአንድ ሀገር ሁኔታም ከሌላው ተወራራሽና ተመሳሳይ--ወይም አንድ ወጥ- ሊሆን እንደማይችልም የታወቀ ነው። የጅምላ ድምዳሜ ወደ ስህተት ሊያመራ የሚችል መሆኑን መገንዘብ የሚገባው ለዚህ ነው። ለዚህም ነው የየካቲትን አብዮት መደናቀፍ ካለፉ መፈንቅሎች ጋር ለማመሳሰል ሆነ በግፍና አምባገነንነት፤በአረመኔነትንና በፋሺስትነት ያላቸው መመሳሰል እንዳለ ሆኖ የወያኔን የስልጣን ንጥቂያ ከ 66ኡ የሻለቆች አብዮትን ማጅራት ምት ጋር አንድ ማድረጉ የማይቻለው።
የየካቲት አብዮት ጽኑ መሠረትና ምክንያት ይዞ የፈነዳ ቢሆንም ግቡን ስላልመታ ከሚቀርቡት አሉታዊ ትችቶች አንዱ ጊዜው አልነበረም የሚል ነበር ። ዛሬም የወያኔ አገዛዝ በሞት አፋፉ ላይ ደርሶ ባለበት ሁኔታ ለመተካት የተዘጋጀ ኃይል የለምና ውድቀቱ ወቅታዊና ጠቃሚ አይሆንም የሚሉ ብቅ ብቅ እያሉ ነው ። በቅድሚያ ማጤን ያለብን አቢይ ጉዳይ አብዮት ወይም ስር ነቀል ለውጥ ወይም የሥዓአት ቅየራ የሚመጣው በማንም ውሳኔ ሳይሆን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት ሕዝብ በሚያደርገው ትግል ወይም አመጽ ነው። ትግል ወይም የአብዮት ፍንዳታ አልተዘጋጀንምና ቆይ ተብሎ ሊታገድ የሚችል አይደለም ። በውስጥ ውስጥም ሆነ በብቅ ጥልቅ ለዓመታት ሲግም ሲያስገመግም የቆየውን የአብዮት ፍንዳታ በሚያጎመራ ጊዜ ግብታዊ የሚል የተሳሳተ ቅጽል መስጠት የተለመደ ቢሆንም የአብዮት ፍንዳታ--የሕዝብ አመጽ ወቅቱን ጠብቆ የሚመጣ ነው ። ለምሳሌ በቦልሼቪክ ፓርቲ መሪነት የተካሄደው ታላቁ የሩስያ አብዮት ከመፈንዳቱ ስድስት ወር በፊት ሌኒን ራሱ ሁናቴዎች ገና ናቸውና ብዙ መስራት አለብን ያለው ሊጠቀስ የሚችል ሲሆን አብዮትን የሚጠብቁትም ቢሆን መቸ እንደሚፈነዳ አያውቁም የሚለውን አስተሳሰብ ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ይሆናል። የየካቲት አብዮት ሲፈነዳ የህቡዕ እንቅስቃሴ በማድረግና ድርጅቱን በመገንባት ተግባር ተጠምዶ የነበረው ኢሕአፓ ገና ሁለት ዓመቱ ነበር ። በወቅቱ በተቻለው መጠን ትግሉን ሊያጠናክርና አቅጣጫ ሊያስይዝ ቢሞክርም የደርግን መፈንቅለ መንግሥት ሊያግድም ሆነ የድል ቅሚያውንም ሊያስቆምና ሊያከሽፍ አልቻለም ። ሆኖም የሕዝብ ጥያቄዎች መሠረታዊ ነበሩና፤ በወቅቱ ምላሽም ያገኙ አልነበሩምና ጸረ ደርጉን ትግል በስፋት በማካሄድና ትግሉን በመቀጠል ታሪካዊ ምዕራፎችን ጽፏል ። በቅድሚያ በመሠረቱ እስካዛሬም ምላሽ ያጣው የሕዝብ ጥያቄ ዴሞክራሲ ለሰፊው ሕዝብ አለገደብ የሚል ነበርና የደርግ ሕገ ወጥ ሥልጣን ይህንን መሠረታዊ ፍላጎት ተጻሮ የቆመ ሆነ ። ደርግ ዴሞክራሲን ማፈን ብቻ ሳይሆን ያሰበና ያሳሰበ ወንጀለኛ ነው ብሎ አፋኝ አዋጆችን አዥጎድጉዶ የግፍ አገዛዙን
ጀመረ ። በዚህም የተባበሩት ሁሉ ወደዱም ጠሉም --ዛሬ ለወያኔ ተባባሪዎች እንድምንላቸው ሁሉ--የወንጀሉ ተባባሪ ሆነው አልፈዋል ። ቀጥሎ የተከሰተውን ሁሉም የሚያውቀው ነው።
የየካቲት አብዮት ለምን ፈነዳ ? አብዮት በዘፈቀደና በአልባሌ ምክንያቶች የሚፈነዳ አይደለም ። ታምቆ ቢቆይም፤ ውስጥ ውስጡን እንደ እሳተ ገሞራ ቢያጉረመርም አብዮት የቆዩና መሠረታዊ የሕዝብ ቅራኔዎች ነጸብራቅና ፍንዳታ ነው። ፍናዳታው እውን ይሆን ዘንድ ሕዝብ አልገዛም በቃ ብሎ መነሳት አለበት። ገዢው መደብም እንደበፊቱ እንዳፈተተው ተንደላቆ የሚገዛበት ሁኔታ መዳከም ይገባዋል ። ሕዝብም በተወሰነ ደረጃ ለማመጽ ድፍረትን ኅብረትን ማግኘት ይኖርበታል ። እነዚህ ሁኔታዎች ሲሟሉና አብዩት ሲፈነዳ ለድል አስፈላጊ ሆኖ የሚገኘው የድርጅትና የኅብረቱ ጥያቄ ይሆናል። በየካቲት 66 ይህን ሁኔታ ከማሟላት አኳያ ግልጽ ድክመትና ጉድለት ነበርና ደርግ የተባለው የታጠቀ አድሃሪ ቡድን የሕዝብ ድል ሊቀማ ቻለ ። የቻይናም፤የሩስያም፤ የካቲትም ሁሉ አለጊዜያቸው የመጡ አብዮቶች ተብለዋል ። አብዮትን ማቆየትና ማስወገድም የሚቻለው በሥልጣን ያለው ሥርዓት መሠረታዊ ለውጥ ካደረገ ብቻ ነው ። አድሃሪ አገዛዞች ይህን ማድረግ ካልቻሉ አብዮት አየቀሬ ነው። አጼ ኃይለሥላሴ የለውጥን አስፈላጊነት ሊረዱ ባለመቻላቸው፤ መሠረታዊ ለውጥ ለማካሄድ ፈቃደኛ ሊሆኑ ባለመቻላቸው፤ ለመጣው አመጽ ማብረጃና ማስተንፈሻ የሚሆን ባለማቅረባቸው አብዮቱ ፈነዳባቸው ። መሬት ለአራሹ፤ ሕዝባዊ መንግስት፤ዴሞክራሲ አለገደብ ለጭቁኖች፤ ሉአላዊነት ለኢትዮጵያ፤ እኩልነት በሁሉም መስክና ፍትሐዊ አስተዳደር የሚሉትሕዝባዊ ጥያቄዎች--እንኳን ያኔም ዛሬም ቢሆን መፍትሔ ያገኙ አይደሉምና-- በዚህ የተነሳ አብዮት መፈንዳቱ ጊዜውና ወቅቱ ነበር ። ያን ትውልድ አብዮት አመጣብን ብለው የሚያወግዙትና የሚያላዝኑበት አንድም የወዳቂው ሥርዓት ተጠቃሚዎችና አዳናቂዎች ሲሆኑ በሌላም በኩል የለውጥ ተጻራሪዎች መሆናቸው ከወዲያው ታውቆ የተወገዙበት ነው ። ያን ሥርዓት እየጎዱትና ለውድቀት የዳረጉት ራሳቸው የሥርዓቱ ባለቤቶች ናቸው ። ወቅቱ የጠየቀውን ለውጥ ቢያደርጉ ኖሮ ሂደቱ ሌላ በሆነ ነበር ። የተቃዋሚዎቹ መፈክሮች ምላሽ አግኝተው አቀጣጣይነታቸውና አብዮት ቀስቃሽነታቸውም ባለተከሰተ ነበር ማለትም እንችላለን ።ለአንገብጋቢ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጠተው በነበር የየካቲት አብዮት ባልመጣባቸው ነበርም ማለት እንችላለን።
የየካቲት አብዮት ሊከሰት የቻለባቸውና በኋላ የአብዮቱ መፈክሮቹ የሆኑት ዋና ዋና ጥያቄዎች ዛሬም ምላሽ ያላገኙ ጉዳዮች ናቸው ። አብዮቱን ካቀጣጠሉት ዋና ዋና ጥያቄዎች መከካል መሬት ለአራሹ፤ ዴምክራሲ ለጭቁኑ፤ ሉዓላዊነት ለኢትዮጵያ፤ ሕዝባዊ መንግስት ወዘት የሚሉት ይገኙባቸዋል። ምላሽ ባለማግኘታቸው ትግሉ ቀጠለ ። እስከዛሬ። እነዚህ መፈክሮችና ጥያቄዎች ደግሞ የሕዝብ ብሶት አንጽባራቂ ነበሩና፤ ችላ ተብለው ከርመው ቆይተዋልና በነበረው ተጨባጭ ሁኔ ታ ሕዝብ በቃኝ ብሎ ምላሽ ሊጠይቅ ሲነሳ--አብዮት ሲፈነዳ-- ገዢው ቡድን ወራጅ አለ ተብሎ ሊጨብጠው ሊይዘው ተስኖት ሲወጠር እውን የሆነው እውነታ ተጨባጩ ሁኔታ ያመጣው እንጂ የተወሰኑ ተራማጅ ወጣቶች ከብብታችው ስበው ያወጡት ክስተት አልነበረም ። ያ ትውልድ የተበላሹ ገዢዎችና ሥርዓቶች ያመጡትን ሀገራዊ ችግር ተጋፍጦ ለችግሮቹ መፍትሔ ለመሰጠት ጥረት አደረገ እንጂ ያልነበረን ችግር ፈጥሮ ሊያሰፍን አልተንቀሳቀሰም ። ለምንስ ማለቱ ቦታው ነው ። ምን ሊጠቀም? ምን ሊፈይድ ? ለተረከበው ችግር መፍትሔ ለማግኘት ሲነሳ ስህተት ፈጸመ በሚል ሊወቀስ ቢችልም የችግሩ ፈጣሪ ግን ከቶም የሚሆን አይደለም ። የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በተመለከተ ምን መደረግ ነበረበት ለሚለው ወሳኝ ጥያቄ ምላሽ ሊሰጥ የጣረው ትውልድ ሊወቀስ ሳይሆን ሊመሰገን የሚገባው ሲሆን ለአቅዋሙ ደሙን ያፈሰሰ በመሆኑ ማንም--በተለይም ሀገርን ለመታደግ ትንሿን ጣቱንም ያላንቀሳቀሰው--ሊወቅሰው ሊያወግዘው የሚችልበት የሞራል የበላይነት የለውም ። ለማንኛውም
ሀገር ገንቢ መንገድን የቀየሰው ትውልድ ዕድል ተነፍጎት፤ ታፍኖና ተጨፍጭፎ በመገኘቱ ለሀገራችን የነበረው ብሩህ ተስፋ ከስሞ ደርግ የተባለው መርገም በሀገራችን ላይ ሰፍኖ-- ከርሞብን፤ ለወያኔ ጨለማ አሳልፎም ሰጥቶናል፤ዳርጎናል ። በዚህ ረገድ ወያኔ የደርግ ውላጅ ነው ማለቱ አከራካሪም የሚሆን አይደለም።
ይህን በተመለከተ የሐምሌ 2001 ዴሞክራሲያ (ቅጽ 34 ቁጥር 39) የሚከተለውን አስፍሮ እንደነበር መጥቀስ እንፈልጋለን፣
" የስድሳ ስድስቱ የኢትዮጵያዊ አብዮታዊ ትውልድ በብሔርም ሆነ በሃይማኖት ሳይከፋፈል ባንድ ላይ ተባብሮ የቆመው ለሀገሩና ለዜጎቿ መልካምን በማሰብ ነበር። ለዚህም አይከፍሉ መስዋዕትነት ከፍሏል ። ያ ሁሉ እንደ ቅጠል የረገፈው ምሁርና ወጣት ለሀገሩ የነበረው ራዕይ በብሩህ ተስፋ፤ በሀገር አንድነትና በሕዝብ እኩልነት ላይ የተመሠረተ ነበር ። ታዲያ ከደርግ ባለስልጣኖችና ጀሌዎች ይህንን ለኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ አንግቦ የቆመውን አዲስ ትውልድ እየጨፈጨፉ ኢትዮጵያን ለመከፋፈልና ለመቆራረስ ዓላማ አድርጎ የተነሳውን ጠባብ ብሔረተኛ ድርጅት ሰተት ብሎ አዲስ አበባ በመግባት ዓላማውን በተግባር እንዲተረጉም ዕድል ሰጡት ። ወደዱም ጠሉት በተጨባጭ ተባበሩት ። በአሁኑ ወቅት አንዳንድ የመረጃ ሰነዶች እንደሚመሰክሩት ሕሊናቸውን በመሸጥ ከወያኔ ጋር ተባብረው የውስጥ መረጃ በማቀበል አሳፋሪ ድርጊት የፈጸሙት የደርግ ባለሥልጣናት ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም። እነኚህ ደግሞ ለሀገር የቆመውን ኃይል በማጥፋት ብቻ ሳይወሰኑ ተተኪውን ትውልድም ጭምር እያወደሙ፤ኢትዮጵያን ለአውዳሚ ተምች አሳልፈው አስረክበዋል ። ይኽም ደግሞ ከጠፉም በኋላ የጥፋታቸው ጠንቅ እንዲቀጥል ሆኗል ። የኢትዮጵያን ጉዳይ የኋላ ልጅ ይጨነቅበት እንዳይሉ እንኳ የኋላ ልጅ እንዲተርፍ አላደረጉም ። መጪው ትውልድ በጠፋበት ኃላፊነት ይሰጠው ቢባል እንኳን የሚለጋለት ሀኬት ሊኖር አይችልም--አልቋልና ። ለአንድ ህገር ከሚወረሱት ውርሶች መካከል የኋላ ልጅ ይጨነቅበት የሚባለው ነገር፤ሀገር እንደ ሀገር ለመቀጠል እንዳትችል የሚደረግ ጠላትነት ነው ። በግድ ኢትዮጵያ ሀገራችን የነገን ተረካቢ ትውልድ እንድትፈጥር ዕድል ሊሰጣት ይገባል"።
ደርግ ተብዬው ይህን ዕድል አልሰጣትም--ወያኔ ለሚባል በሽታ ዳረጋት እንጂ ። በየካቲቱ ትውልድና በአብዮቱ ላይ ሊጨፍሩ የተነሱ የወያኔ አጋሮችና የደርግ የወንጀል ተካፋዮዎች አብዮቱ ያነሳው ጥያቄ ሁሉ ከመስመር ውጪ ነው ወይም በደፈናው የሆነ ርዕዮተ ዓለም ጭፍን ነጸብራቅ ነው ሊሉ እስካዛሬ አልተቻላቸውም ። ፊውዳሊዚም ይውደም፤ መሬትም ለአራሹ ይሁን መባሉ አግባብ አልነበረም ካላሉ በስተቀር ። የዘውድ አገዛዝ ተገርስሶ ሕዝብ የዴምክራሲ ባለቤት መሆኑ ሐጢያት ነው ለማለት ካልደፈሩ በቀር ። የእኩልነት ጥያቄ ሲነሳም በየዘርፉ ጭቆና መኖሩን በወቅቱ የነበረው ተጨባጭ ሁኔታ በሀቅ የሚመሰክር ሲሆን ይህንን መካድ የሕዝብን መብትና ፍላጎት መጻረር ካልሆነ በስተቀር ሌላ ትርጉም አልነበረውም ። የሀገራችንም ሉዓላዊነት ይከበር የሚለው ጥያቄ ያኔም ዛሬም እንደሌሎቹ ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ አጥቶ የሀገራችንን ችግሮች ገላጭ ሆኖ ይገኛል ። እናም የካቲት ጊዜውን የጠበቀ አብዮት ነበረ ። ያ ትውልድም ግዳጁን ተሸክሞ ከፍተኛ ዋጋን ከፍሎ ሀገሩን ሊታደግና አብዮቱንም ሊያስከብር መነሳቱና አልፎም የህይወት መስዋእትነት መክፈሉ የሚደነቅ እንጂ የያኔ ፈርጣጮችና የወንጀል ተባባሪዎች ዛሪ እንደሚጥሩት የሚወቀስ ከቶም አልነበረም፤አይደለምም ። የየካቲት አብዮት የሕዝብና የሀገርን አንድነት መሠረት አድርጎ የፈነዳና የተካሄደ ነው ። ቀን ሲደርስ አምባ ይፈርስ ነው ። በሁኔታው ሂደት የሕዝብ ኃይሎች ተጠናክረው አብዮቱን ሊጠብቁ ባልመቻላቸውና ድል በመቀመታቸው ዛሬም በተስፋ ቆራጭነት በመጠቃት ድል እንቀማለን ብሎ ሙሾ ከወዲሁ ከመደርደር ድላችንን የማንቀማበትን ቅድመ ሁኔታ ጸንቶ ማዘጋጀት እንዳለብን ታሪክም ያስተምረናል ።
ለማንኛውም የታሪክ ግዳጁን ተቀብሎ ውድ ህይወቱን ለሀገሩ የሰጠውን ትውልድ እንደ አርአያ በመቀበል ፈንታ ወደ 40 ዓመት ታሪክ ተመልሶ --ያውም የተከለሰን ታሪክ በማቀንቀን- ያውም ያንን ትግል የሚያስንቅ ምንም ዓይነት ግብግብ ሳይታይ- - ወቀሳና ውግዘት መደርደር የሚያስገምት እንጂ ሌላ ትርጉም የለውም ። ከዚህ ባሻገር ደግሞ ጊዜ የሰጠው ቅል በመሆን የኋላ መብራትን ቦግ አድርጎ እንዲህ ቢሆን ኖር ፤ ይህ ቢደረግ ኖሮ ዓይነት ግምገማ ጥሩና ትክክለኛ ግንዛቤን የሚሰጥ አይደለም ። መንግስቱም መለስም ጭራሽ ባይወለዱ ኖሮስ እንዳይከተል!
በየካቲት 1966 የአብዮቱ ፍንዳታ ይጠብቁት የነበሩትን ሳይቀር ድንገተኛ ግብታዊ ስለሆነባቸው በዚያ ወቅት ኢሕአፓ በበቂ ተደራጅቶ፤ተመክሮ አካብቶ፤ ተዘጋጅቶ የተገኘ ባለመሆኑ አብዮቱን ማጅራት መትተው ጥቂት ምርጥ መኮንኖች-- ራሳቸውን ደርግ ብለው ሰይመው በኃይል የሕዝብን ድል ሊነጥቁና በሥልጣን ሊሰየሙ ችለዋል ። ኢሕአፓ አብዮቱ ሞግዚት አያሻውምና ሁሉን የሚያሳታፍ ጊዜያው ሕዝባዊ መንግሥት ይመሥረት በሚል ሕዝብን አደራጅቶ ታሪክ የመዘገበውን ትግል አካሂዷል ። ይህን የዴሞክራሲያዊ ሽግግር አማራጭ ደርግና የምሁር አጋሮቹ እምቢኝ ብለው ባይጥሉትና በድርጅቱም ላይ አፈና ለማካሄድ ባይወስኑ ኖሮ የታሪክ ሂደት ሌላ ሊሆን እንደሚችል ማንም ሊከራከር አይችልም ። ሁሉን አቀፍ መፍትሔ መመረጡ ሥልጣን በተወሰነ ቡድን እጅ ገብታ የጭቆና ሥርዓት በአዲስ መልክ እንዳይቀጥል እንደነበረም የተገለጸ ነበር ። ይህ አማራጭ በመጣሉ ደርግ ራሱን የአብዮቱ ጠባቂና ሞግዚት ብሎ ሰይሞ ሙሉ ሥልጣንንም በእጁ ለማስገባት ወደ ደም ማፍሰስ ተሸጋገረ ።ያስከተለውን አስከፊ ሁኔታ ታሪክ መዝግቦታል ። በሽግግሩ ዕቅድ ኢሕአፓ ያኔ ተሓህት ይባል የነበረውን ወያኔ፤ ኦነግን፤ልዩ ልዩ ቡድኖችና የሕዝብ ማኅበራትን፤ወታደሮችና መኮንኖችን፤ታዋቂ ግለሰቦችን ወዘተ ባካተተ መልኩ አማራጩን ማቅረቡም የሚታወስ ነው ። ዛሬም ወቅታዊ ሁኔታው ይህን አማራጭ ግድ የሚለው ወያኔና ሕዝብ ተፋጠው ባሉበት፤ወያኔ ዘረኝነትንና የርስ በርስ ግጭትን አስፋፍቶ ባለበት፤ አሁንም ወታደሩና የጸጥታው ክፍል በወያኔ ቁጥጥር ስር ባለበትና ጦሩ ወደ ሕዝብ ጎራ ባልገባበት ሁኔታ ተቃዋሚ ኃይሎች ተባብረው ከፍተኛ ብስለትና ጥበብን በማሳየት በወሳኝነት በሚካሄደው ግብግብ በአሸናፊነት መውጣት ይጠበቅባቸዋል ።
ከ 15 ዓመት በፊት የነበረውን ሐቅ ስናቀርብ የጻፍነው ዛሬ ለዛሬም የሚሰራና መሠረት ያለው ሆኖ እናገኘዋለን ፤ "የተቃዋሚ ሃይሎች ኅብረት ቀዳማይ ተግባር ለሽግግር ወቅት የሚያስፈልጉትን ዝግጅቶች ማሟላትና ለአጭር፤ ለመካከለኛ ለሩቅ ጊዜ የሚሆኑ አጀንዳዎችን መንደፍ ይሆናል። ይህንንም ለማድረግ የኅሊናም ይሁን ነባራዊ ሁኔታዎች ዛሬ በሀገሪቷ ተሟልተው ይገኛሉ ማለት ይቻላል ። ዘረኛ የወያኔ ቡድን እየተፍረከረከ ይገኛል። "
በሚል የሀገራችንን አስከፊ ሁኔታና የወያኔን ግፍ ከዘረዘረ በኋላ መሠረታዊ ና የሚያመረቃ ለውጥ ለማምጣትም ዋስትናው የሽግግር መንግሥት ነው ሲልም ደምድሞ ነበር ።ዛሬም የተለየ መፍትሔና አካሄድ ሊኖር አይገባንም ማለት ነው። ቀድሞ የነበሩትን ችግሮች ለመፍታት የታቀዱት ሁሉ በሥራ ባለመዋላቸው ጭቆናና ቀውስ፤ችግርና ግፍ ኑሮአችንን አጅበው ቆይተዋል ። የነበረውን የእኩልነት አለመኖር ችግር በፌዴራላዊ አወቃቀርና በዴሞክራሲና እኩልነት ለመፍታት የታለመውን እቅድ ወያኔ ወደ ጎን አድርጎት በትግሬ የበላይነት በተለጣፊ ቅፍቀፋ እና በአንቀጽ 39ኝ ግንጠላና ጠባብነት ተክቶ አበለሻሸው ። ለዚህም ነው በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ጽንፍ የያዙትን በዴሞክራሲና በኢትዮጵያ አንድነትን በማይንድ አወቃቀር ዙሪያ አብረን መሰለፍ

እንችላለን የምንላችው ። መሬት ለአራሹ ዛሬም ምላሽን የሚጠብቅ ጉዳይ ሆኗል ። የሠርቶ አደሩ ሕዝብ መብት ተረግጧል፤ የሃይማኖት እኩልነትና የአማኞች መብትም ተደፍሯል፤የፖለቲካ እስረኞች ቁጥር ብዙ ብዙ ሺ ነው። ሕዝብ ተበዝብዞ ለረሃብና ለስቃይ ተዳርጓል... ወዘተ። ባጠቃላይም የየካቲት ጥያቄዎች እንኳን መፍትሔ ሊያገኙ ቀርቶ በየዘርፉ ተባብሰው፤ ሕዝባችንም አንዱ አምባገንን ሲሄድ የከፋውና የባሰው እየመጣበት ከዛሬውስ የትላንቱ ይሻላል ወደሚል አሳዛኝ ድምዳሜና ምጸት እየተዳረገ ይገኛል።
በአንክሮና አንገብጋቢነት የሚቀርበው የኅብረት ጉዳይ ባሉት ውስብስብ ችግሮች የተነሳ አሁንም አስፈላጊና ወሳኝ ሆኖ የሚገኝ ነው ። በደርግ ውድቀት ዋዜማ የኅብረትን ችግር ምላሽ ለመስጠት በመካከላቸው ከፍተኛ የሆነ ጠብና ግጭት የነበራቸው ቡድኖችና ድርጅቶች ሳይቀሩ ሁሉም ኅብረት ሊመሰርቱ ሲዋደቁ ወያኔ፤ሻዕቢያና ለነሱ ያደሩ ምሁሮች እንቅፋት ሆነው የኅብረት ምስረታውን ለማደናቀፍ መጣራቸው ታሪክ የመዘገበው ነው ። ኢዴኅቅ ዘግይቶ ሲቋቋምም ከመቅጽበት ወያኔም አሜሪካም ሊያፈርሱት መነሳታቸው የሚታወቅ ሲሆን ከይሲው ወያኔ ለሥልጣን ሲበቃ በኅበረቱ ከተሰለፉት አባል ድርጅቶች ውስጥ የተወሰኑት ወደ ወያኔ ጉያ የገቡ መሆናቸውም ሐቅ ነው። የወያኔ የሥስልጣን ባለቤት እንዳይሆን ለማስቆምም ሆነ ለማገድ አልተቻለም ። ኢሠፓ ከላይ እስከታች ተፍረክርኮ፤ዋና መሪው በሚያሳፍር ሁኔታ የሀገር ሀብት ዘርፎ ፈርጥጦ፤ ጦሩ ፈርሶ ለወያኔ ሁሉ ነገር አመቻችቶ እንደሰጠ ደግሞ የምንረሳው አይደለም ። የኢሕአፓ ጦርም በወያኔ ፤ ሻዕቢያና ሱዳን ትብብርና በራሱም ድክመትም ሊመታ ቻለ ። ጸረ ወያኔውን የከተሞች ትግልም ምሁሮችና ጠባቦች ነጥለው በማዳከማቸው ሁኔታው ለወያኔ አመች ሆኖ ዘረኝነትን ተጠቅሞና አፈናን አጠናክሮ ሥልጣኑን ለማደላደል ችሏል። ይህን ወያኔን በሥልጣን በከፍተኛ ደረጃ ያገለገለውን የዘረኝነትና ሕዝብን የመከፋፈል ፖለቲካ በማጀብ በጸረ አማራነትና ኢትዮጵያዊነትን በመካድ የተሰማሩት ኃይሎች ሁሉ- ወደዱም ጠሉም- ለወያኔ የሥልጣን ዘመን መራዘም ከፍተኛ ጠቀሜታ አበርክተዋል። ወደ 1997 ዓ.ም. አካባቢ ብቅ ያሉት ኅብረትና ቅንጅት ሁለትነታቸው ራሱ የድክመታቸው ነጸብራቅ ሆኖ ፤አስፈላጊውን አንድነት አጥተው ግን በትግላቸው ወያኔን በምርጫ ቢያሸንፉም ድላቸውን ለማስከበር ዝግጅቱም ጽናትም እንዳልነበራቸው የተከተለው ሁኔታ ገሃድ አድርጎታል ። ካቸነፍን በኋላ ድላችንን ወያኔ ቢቀማስ ለሚለው ስጋት ይሰጥ የነበረው መልስ አሜሪካ አይፈቅድለትምና ብዙ የሚያሳስብ አይደለም የሚለው ከመሰረቱ የተሣተ ድምዳሜ ነበር ማለት ይቻላል። ልጁ ቀማኛ አባቱ ዳኛ ሆኖ ፍትህን መሻት ማለት ነው። ወይኔ ብዙ ሕዝብ ፈጅቶ እንደተፈራው ከሥልጣን አልወርድም ብሎ ሲደነፋ ይህን በመቃወም የሙት ከተማ አድማ ቢጠራ ይህን ያፈረሱት ራሳቸው የተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎች መሆናቸውንም የምንረሳው አይደለም ። የወያኔ የክፍፍል ዓላማ በጎንደር ሕዝብ ታሪካዊ መፈክር ተሰርዞ፤ የሕዝብ ኅብረት በኢትዮጵዊነት ተጠናክሮ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ የሥልጣን መሠረቱ እየተንገዳገደ ያለው ወያኔ ሕዝብን ለመከፋፈል አሁንም ከመወራጨቱ ባሻገር ኢትዮጵያን የእርስ በርስ ደም መፋሰስ አውድማ አድርጎ ካልሆነለትም ትግራይን ገንጥሎ ሊፈረጥጥ (የጎንደርማ የወሎን ለም መሬቶች ጠቅልሎ ከሱዳንም ተዋሳኝ ሆኖ የለ!) ተዘጋጅቷልና የተቃዋሚና ሀገር ወዳድ ኃይሎች ኅብረት ቀነ ቀጠሮ የማይሰጥ፤ለመጪው ትውልድ የማይለጋ ሐኬት ሆኖ ይገኛል። የተቃዋሚና የአገር ወዳድ ኃይሎች ኅበረት እየተንገዳገደ ያለውን የወያኔ ዘረኛና ከፋፋይ አገዛዝ ከሥሩ ለማስወገድም ሆነ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚወስደውን የሽግግር ሂደት ሰላማዊ፤ የተረጋጋና ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል።
ከሽግግሩ ሂደትም ርዕስ ጋር ከዚህ ቀደም ያቀረብነውን አንድ አቢይ ጉዳይ አሁንም ደግመን ማቅረብ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል ፤
"በሽግግሩ ሂደት የፖለቲካ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ በእውቀታቸው፤በተመክሯቸው በሀገር ወዳድነታቸውና በዲሞክራሲ ዕምነታቸው እንከን ሊወጣባቸው የማይችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሊሳተፉ የሚችሉበት መመዘኛ/መድረክ ቢኖር መሰረተ ሰፊ የሽግግር ወቅት ይሆናል እንላለን ። ይህም ማለት የመንግሥት፤ የኤኮኖሚውንና የሲቪል ኅብረተሰቡን ሚና በሚዛን አስተካክለው የሚያዩና የሚተረጉሙ ክፍሎች ከተሳተፉበት ለዴሞክራሲያዊው ሂደት አቅጣጫ ያረጋግጣል፤ይሰምራል ማለት ነው ።በዕርግጥም በአንድ ሀገር ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ካስፈለገ የመንግሥትና የሲቪል ኅብረተሰቡን ሚና በግልጽ ተለይቶ መደንገግ ይኖርበታል ። በሀገራችን የዴሞክራሲ ሂደትና ዕድገት በአመዛኙ ሊረጋገጥ የሚችለው የሲቪል ኅብረተሰቡ ሙሉ ተሳትፎ ሲረጋገጥ ነው። የዴሞክራሲንና የነጻነትን ዋስትናና ማረጋገጫ ለማስገኘት የሲቪል ኅብረተሰቡና በነጻ የሚንቀሳቀሱ ተሳታፊ ሕዝባዊ ተቋማት እንዲኖሩ የግድ ነው ። ሚዛኑ ያላጋደለ ቁጥጥር የመንግሥትን ኃይል ለመገደብ ዋስትና አለው ። በሕዝብ ፍላጎትና ተሳትፎ ላይ የተማከለ የማኅበራዊ ኑሮና የኤኮኖሚ ዕድገት ዕውን እንዲሆን ከተፈለገ ሁሉን ሊያሳትፉ የሚችሉ የኅብረተስብ ልዩ ልዩ ድርጅቶች በመላ ሀገሪቱ መስፋፋት አለባቸው ብለን እናምናለን ። ለዚህ ሁሉ ዘር መዘራት ያለበት በሽግግሩ ውቅት ቢሆን ተገቢ ይሆናል ።" ዴሞ ነሐሴ 1995
ስለ ሽግግሩ ከኅብረቱ በእኩል ማቅረባችን ጋሪውን ከፈረሱ ማስቀደማችን ሳይሆን ለሽግግሩ ወሳኝ የሆነውን ኅብረት ስናነሳ ሽግግሩንም በዕይታችን ማስገባቱ የግድ በመሆኑ ነው ። በተጨማሪም የሕዝብን ሚና--ወሳኝነትና የውሳኔ ባለቤትነት--ተገቢውን ቦታ ለመስጠት፤ በምርጦች ሕዝቡ ወደ ጥግ እንዳይደረግ ያለንን ጽኑ ፍላጎት ጫና ለመስጠትና የነገ ኢትዮጵያ ዕጣ አቅጣጫዋ የሕዝብ ውሳኔ ውጤት መሆን አለበት ለማለት ነው። ፈረሱማ ኅብረት ነው ። ተከታዩ የሽግግር መንግስት ነው ። ከዚህም አንጻርጥሪያችን ከዴሞክራሲናኢትዮጵያአንጻርበሁሉምጉዳይበጥሞናተወያይተንመፍትሔእንፈልግነው--ለጋራሀገራችን ።
ያሉትን መለስተኛ ልዩነቶች ወደ ጎን በመተው ለሀገር ጠቃሚ የሆነ ኅብረት መመስረት ይገባል ብቻ ሳይሆን ይቻላልም ።ይህ ግን ግለኝነትን አቸንፎ ሀገርን ማፍቀርና ማስቀደምን ይጠይቃል ።ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ፤ ከሁሉም በፊት ሕዝባችን ካልን ሌሎች ጉዳዮች ፤ የሀሳብና የአቋም ልዩነቶች ክብደታቸው ይቀንሳል ። በሀገራችን ህልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ ከመጋተርና ከማስወገድ በፊት ሊቀድም የሚችል ምንም ግዳጅ የለም። አደጋውን ለማስወገድ መሳሪያ የሚሆነውን ኅብረት ከመመስረት የሚያግድ ምንም ጉዳይና ችግር ሊኖር አይችልም፤ አይገባም ማለት ነው ። ኅብረቱ እውን ከሆነ የሽግግሩ ሂደትም ቀና አቅጣጫን ይዞ መጓዙ የማያቀር ነው ። ተቃዋሚዎች ዓላማ የላቸውም፤ተከፋፍለዋል፤ወያኔ ከተወገደ ሕዝብ ያልቃል፤ለመሆኑ ማን ወያኔን ሊተካ ይችላል የሚሉት ተስፋ አስቆራጭ አነጋገሮች ሁሉ ያከትማሉ ማለት ነው ። ወያኔን አስወግዶ ሀገርን በፍትህና በዲሞክራሲ ለማስተዳደር--እንደ ወያኔ ለማጥፋት ለመበጥበጥ ሳይሆን--ችሎታውና ከዚያም በላይ ፍላጎቱ እንዳለን ሳናወላውል የተናገርነው ነው ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አቸናፊ ይሆናል !

No comments:

Post a Comment